በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 9

ፍቅርና ፍትሕ—በጥንቷ እስራኤል ውስጥ

ፍቅርና ፍትሕ—በጥንቷ እስራኤል ውስጥ

“ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል። ምድር በይሖዋ ታማኝ ፍቅር ተሞልታለች።”—መዝ. 33:5

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

የትምህርቱ ዓላማ *

1-2. (ሀ) ሁላችንም ምን ፍላጎት አለን? (ለ) ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

ሁላችንም በሌሎች የመወደድ ፍላጎት አለን። በተጨማሪም ሁላችንም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንድንያዝ እንፈልጋለን። በተደጋጋሚ ፍቅርና ፍትሕ የምንነፈግ ከሆነ ዋጋ ቢስ እንደሆንን ሊሰማንና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን።

2 ይሖዋ ፍቅርና ፍትሕ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን ያውቃል። (መዝ. 33:5) አምላካችን በጥልቅ እንደሚወደንና ፍትሕ እንድናገኝ እንደሚፈልግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ በሙሴ በኩል ለእስራኤል ብሔር የሰጠውን ሕግ መመርመራችን ይህን እውነታ በሚገባ ለመረዳት ያስችለናል። ፍቅር እንደተነፈግክ የሚሰማህ ወይም በተፈጸመብህ ኢፍትሐዊ ድርጊት ምክንያት መንፈስህ የተደቆሰ ክርስቲያን ከሆንክ የሙሴ ሕግ * ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን አሳቢነት የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

3. (ሀ) በሮም 13:8-10 ላይ እንደተገለጸው የሙሴን ሕግ ስንመረምር ምን እንገነዘባለን? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

3 የሙሴን ሕግ ስንመረምር አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን እንገነዘባለን። (ሮም 13:8-10ን አንብብ።) በዚህ ርዕስ ውስጥ ለእስራኤል ብሔር የተሰጡትን አንዳንድ ሕጎች በመመርመር ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እንሞክራለን፦ ሕጉ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ሕጉ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል የምንለው ከምን አንጻር ነው? ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሕጉን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸው እንዴት ነው? እንዲሁም ሕጉ በተለይ ለእነማን ጥበቃ ያደርግ ነበር? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን መጽናኛና ተስፋ ይሰጠናል፤ እንዲሁም አፍቃሪ ወደሆነው አባታችን ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል።—ሥራ 17:27፤ ሮም 15:4

በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሕግ

4. (ሀ) የሙሴ ሕግ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በማቴዎስ 22:36-40 መሠረት ኢየሱስ የትኞቹን ትእዛዛት ጎላ አድርጎ ገልጿል?

4 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ስለሆነ የሙሴ ሕግ የተመሠረተው በፍቅር ላይ ነው ማለት እንችላለን። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ጠቅላላውን የሙሴን ሕግ ያወጣው ‘አምላክህን ውደድ’ እና ‘ባልንጀራህን ውደድ’ በሚሉት ሁለት መሠረታዊ ትእዛዛት ላይ ተመሥርቶ ነው። (ዘሌ. 19:18፤ ዘዳ. 6:5፤ ማቴዎስ 22:36-40ን አንብብ።) በመሆኑም በሕጉ ውስጥ የተካተቱት ከ600 የሚበልጡ ትእዛዛት በሙሉ የይሖዋን ፍቅር የተለያዩ ገጽታዎች የሚያንጸባርቁ እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

5-6. ይሖዋ ባለትዳሮች ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል? የትኛውንስ ነገር ይመለከታል? ምሳሌ ስጥ።

5 ለትዳር ጓደኛህ ታማኝ ሁን፤ እንዲሁም ልጆችህን ተንከባከብ። ይሖዋ ባለትዳሮች ዕድሜ ልካቸውን የሚዘልቅ ጠንካራ ፍቅር እንዲያዳብሩ ይፈልጋል። (ዘፍ. 2:24፤ ማቴ. 19:3-6) ምንዝር አንድ ሰው ሊፈጽም ከሚችላቸው እጅግ አስከፊ የሆኑና ፍቅር የጎደላቸው ድርጊቶች መካከል አንዱ ነው። በእርግጥም ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል ሰባተኛው “አታመንዝር” የሚል መሆኑ ተገቢ ነው። (ዘዳ. 5:18) ምንዝር “በአምላክ ላይ” የሚፈጸም ኃጢአትና በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም የጭካኔ ድርጊት ነው። (ዘፍ. 39:7-9) ምንዝር የተፈጸመበት ግለሰብ በሚወደው ሰው በመከዳቱ ምክንያት ከባድ የስሜት ቁስል የሚደርስበት ሲሆን ይህ ቁስል ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ላይሽር ይችላል።

6 ይሖዋ ባለትዳሮች አንዳቸው ሌላውን የሚይዙበትን መንገድ በትኩረት ይመለከታል። በተለይ ደግሞ ሚስቶች በደል እንዳይደርስባቸው ይፈልግ ነበር። ለሕጉ አክብሮት ያለው ባል ሚስቱን የሚወድ ከመሆኑም ሌላ በማይረባ ምክንያት አይፈታትም። (ዘዳ. 24:1-4፤ ማቴ. 19:3, 8) ሆኖም በመካከላቸው ከባድ ችግር ቢፈጠርና ሊፈታት ቢወስን የፍቺ ምሥክር ወረቀት ሊሰጣት ይገባ ነበር። ይህ የምሥክር ወረቀት ሚስትየዋ የፆታ ብልግና ፈጽማለች ተብላ በሐሰት እንዳትከሰስ ጥበቃ ያደርግላታል። በተጨማሪም ባልየው ለሚስቱ የፍቺ የምሥክር ወረቀቱን ከመስጠቱ በፊት የከተማይቱን ሽማግሌዎች ማማከር ሳይኖርበት አይቀርም፤ እነዚህ ሽማግሌዎች ደግሞ ባልና ሚስቱ ትዳራቸውን እንዲታደጉ ለመርዳት ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ። እርግጥ እስራኤላውያን፣ ሚስታቸውን በራስ ወዳድነት ተነሳስተው በሚፈቱበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ጣልቃ ይገባ ነበር ማለት አይደለም። ሆኖም በደል የደረሰባት ሚስት የምታፈሰውን እንባና ያለችበትን ሥቃይ ይመለከት ነበር።—ሚል. 2:13-16

ይሖዋ፣ ልጆች የደህንነት ስሜት ተሰምቷቸው እንዲያድጉ እንዲሁም ወላጆች ልጆቻቸውን ተንከባክበው እንዲያሳድጉና እንዲያስተምሩ ይፈልጋል (ከአንቀጽ 7-8⁠ን ተመልከት) *

7-8. (ሀ) ይሖዋ ለወላጆች ምን ትእዛዝ ሰጥቷል? (ሽፋኑን ተመልከት።) (ለ) ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 በተጨማሪም ሕጉ ይሖዋ ለልጆች ደህንነት ከልብ እንደሚያስብ ያሳያል። ይሖዋ ወላጆች የልጆቻቸውን ቁሳዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎት ጭምር እንዲያሟሉ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። ወላጆች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ልጆቻቸው የይሖዋን ሕግ እንዲያውቁና ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ እንዲሁም ይሖዋን እንዲወዱ ማስተማር ነበረባቸው። (ዘዳ. 6:6-9፤ 7:13) ይሖዋ እስራኤላውያንን የቀጣበት አንዱ ምክንያት በልጆቻቸው ላይ አሰቃቂ ነገር ማድረጋቸው ነው። (ኤር. 7:31, 33) ወላጆች ልጆቻቸውን ሊመለከቷቸው የሚገባው ችላ ሊሉት ወይም የፈለጉትን ነገር ሊያደርጉበት እንደሚችሉት ንብረት አድርገው ሳይሆን በጥንቃቄ ሊይዙት እንደሚገባ ከይሖዋ የተገኘ ውርሻ አድርገው ነው።—መዝ. 127:3

8 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ ባለትዳሮች አንዳቸው ሌላውን የሚይዙበትን መንገድ በትኩረት ይመለከታል። ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲወዱ የሚፈልግ ከመሆኑም ሌላ ልጆቻቸውን ለሚይዙበት መንገድ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።

9-11. ይሖዋ መጎምጀትን የሚከለክለውን ሕግ የሰጠው ለምንድን ነው?

9 አትጎምጅ። ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የመጨረሻው መጎምጀትን ወይም የሌላ ሰው የሆነን ነገር መመኘትን ይከለክላል። (ዘዳ. 5:21፤ ሮም 7:7) ይሖዋ ይህን ሕግ የሰጠው አንድ አስፈላጊ ትምህርት ለማስተላለፍ ይኸውም ሕዝቡ ልባቸውን ማለትም አስተሳሰባቸውን፣ ስሜታቸውንና የማመዛዘን ችሎታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ለማስገንዘብ ነው። ይሖዋ ክፉ ድርጊት የሚመነጨው ከክፉ ሐሳብና ምኞት እንደሆነ ያውቃል። (ምሳሌ 4:23) አንድ እስራኤላዊ በልቡ ውስጥ መጥፎ ምኞት እንዲያቆጠቁጥ ከፈቀደ ሌሎችን ፍቅር በጎደለው መንገድ መያዙ አይቀርም። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት በዚህ ወጥመድ ውስጥ ወድቋል። በጥቅሉ ሲታይ ዳዊት ጥሩ ሰው ነበር። በአንድ ወቅት ግን የሌላ ሰው ሚስት አይቶ ተመኘ። ይህ ምኞት ደግሞ ኃጢአት ወደመፈጸም መራው። (ያዕ. 1:14, 15) ዳዊት ምንዝር ፈጽሟል፣ የሴትየዋን ባል ለማታለል ሞክሯል፣ ከዚያም ሰውየውን አስገድሎታል።—2 ሳሙ. 11:2-4፤ 12:7-11

10 ይሖዋ ልብን ማንበብ ስለሚችል፣ አንድ እስራኤላዊ “አትጎምጅ” የሚለው ሕግ ሲተላለፍ ያውቃል። (1 ዜና 28:9) መጎምጀትን የሚከለክለው ሕግ ሕዝቡ መጥፎ ምግባር ወደማሳየት የሚመራ አስተሳሰብን ማስወገድ እንዳለበት ያስገነዝባል። ይሖዋ እንዴት ያለ ጥበበኛና አፍቃሪ አባት ነው!

11 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ ከውጫዊ ገጽታችን ባሻገር ያለውን ነገር የማየት ችሎታ አለው። ልባችንን ማለትም ውስጣዊ ማንነታችንን ይመለከታል። (1 ሳሙ. 16:7) ከእሱ ሊደበቅ የሚችል ምንም ዓይነት ሐሳብ፣ ስሜት ወይም ድርጊት የለም። ይሖዋ በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር ያያል፤ እንዲሁም ያን መልካም ነገር ማሳደግ እንድንችል ይረዳናል። ሆኖም በልባችን ውስጥ ያለ መጥፎ አስተሳሰብ አድጎ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ከመፈጸማችን በፊት ይህን አስተሳሰብ ለይተን እንድናውቀውና እንድንቆጣጠረው ይፈልጋል።—2 ዜና 16:9፤ ማቴ. 5:27-30

ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሕግ

12. የሙሴ ሕግ የትኛውን እውነታ ጎላ አድርጎ ያሳያል?

12 በተጨማሪም የሙሴ ሕግ ይሖዋ ፍትሕን እንደሚወድ ጎላ አድርጎ ያሳያል። (መዝ. 37:28፤ ኢሳ. 61:8) ይሖዋ ሰዎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መያዝ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። እስራኤላውያን እሱ ያወጣቸውን ሕጎች ሲታዘዙ ይሖዋ ይባርካቸው ነበር። የፍትሕና የጽድቅ መሥፈርቶቹን ችላ ሲሉ ደግሞ በራሳቸው ላይ ችግር ያመጡ ነበር። እስቲ ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ሕጎችን እንመልከት።

13-14. ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትእዛዛት ምን ማድረግን ይጠይቁ ነበር? እስራኤላውያን እነዚህን ሕጎች ሲታዘዙ ምን ጥቅም ያገኙ ነበር?

13 ይሖዋን ብቻ አምልክ። ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትእዛዛት፣ እስራኤላውያን ይሖዋን ብቻ እንዲያመልኩና ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁ የሚያሳስቡ ናቸው። (ዘፀ. 20:3-6) ይሖዋ እነዚህን ትእዛዛት የሰጠው ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ለሕዝቡ ጥቅም ሲል ነው። ሕዝቡ ለይሖዋ ታማኝ ሲሆኑ ብዙ በረከት ያገኙ ነበር። ሌሎች ብሔራት የሚያመልኳቸውን አማልክት ሲያመልኩ ግን መከራ ይደርስባቸው ነበር።

14 ከነአናውያንን እንደ ምሳሌ አድርገን መውሰድ እንችላለን። ከነአናውያን ሕያውና እውነተኛ ከሆነው አምላክ ይልቅ በድን የሆኑ ጣዖታትን ያመልኩ ነበር። በዚህም ምክንያት ራሳቸውን አዋርደዋል። (መዝ. 115:4-8) አምልኳቸው አስጸያፊ የሆነ የፆታ ብልግና መፈጸምንና ልጆችን አሰቃቂ በሆነ መንገድ መሥዋዕት ማድረግን የሚያካትት ነው። በተመሳሳይም እስራኤላውያን ይሖዋን በመተው ጣዖታትን ሲያመልኩ ራሳቸውን የሚያዋርዱ ከመሆኑም ሌላ ቤተሰባቸውን ይጎዳሉ። (2 ዜና 28:1-4) ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች የይሖዋን የፍትሕ መሥፈርቶች ችላ ይላሉ። ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ይጠቀማሉ፤ እንዲሁም ደካማና ምስኪን የሆኑትን ይጨቁናሉ። (ሕዝ. 34:1-4) ይሖዋ ረዳት በሌላቸው ሴቶችና ልጆች ላይ ግፍ የሚፈጽሙ ሰዎችን እንደሚቀጣ እስራኤላውያንን አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘዳ. 10:17, 18፤ 27:19) በተቃራኒው ደግሞ ሕዝቦቹ ለእሱ ታማኝ ሲሆኑና እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ፍትሐዊ ሲሆኑ ይባርካቸው ነበር።—1 ነገ. 10:4-9

ይሖዋ የሚወደን ከመሆኑም ሌላ ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጸምብን ያውቃል (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ስለ ይሖዋ ምን ትምህርት እናገኛለን?

15 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ እሱን እንደሚያመልኩ የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች መሥፈርቶቹን ችላ በማለት በሕዝቡ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ተጠያቂ አይደለም። ሆኖም ይሖዋ እንደሚወደንና የሚፈጸምብንን ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አንዲት እናት የልጇ ሥቃይ ከሚሰማት በላይ ይሖዋ ሥቃያችን ይሰማዋል። (ኢሳ. 49:15) ወዲያውኑ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ ባይወስድ እንኳ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን በሌሎች ላይ ለፈጸሙት በደል ተገቢ ነው ባለው ጊዜ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።

ሕጉ ተግባራዊ መሆን ያለበት እንዴት ነበር?

16-18. የሙሴ ሕግ የአንድን እስራኤላዊ ሕይወት እስከ ምን ድረስ ይነካል? እኛስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 የሙሴ ሕግ የአንድን እስራኤላዊ ሕይወት በብዙ አቅጣጫዎች ስለሚነካ የተሾሙት ሽማግሌዎች በይሖዋ ሕዝብ ላይ የጽድቅ ፍርድ መፍረዳቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። እነዚህ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን ጭምር የመመልከት ኃላፊነት ነበረባቸው። እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት።

17 አንድ እስራኤላዊ ነፍስ ቢያጠፋ በቀጥታ የሞት ፍርድ አይፈረድበትም ነበር። የከተማው ሽማግሌዎች ግለሰቡ በሞት ሊቀጣ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ከመወሰናቸው በፊት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ይመረምራሉ። (ዘዳ. 19:2-7, 11-13) በተጨማሪም ሽማግሌዎቹ በዕለት ተዕለት ሕይወት በሚያጋጥሙ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፍርድ ይሰጡ ነበር፤ እነዚህ ጉዳዮች ከንብረት ጋር ከተያያዙ ውዝግቦች አንስቶ በባልና ሚስት መካከል እስከሚፈጠሩ አለመግባባቶች ድረስ ያሉ ክሶችን የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዘፀ. 21:35፤ ዘዳ. 22:13-19) ሽማግሌዎቹ ፍትሐዊ ሲሆኑና ሕዝቡ ሕጉን ሲታዘዝ ሁሉም የሚጠቀም ከመሆኑም በላይ ብሔሩ ለይሖዋ ክብር ያመጣ ነበር።—ዘሌ. 20:7, 8፤ ኢሳ. 48:17, 18

18 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ እያንዳንዱን የሕይወታችንን ክፍል ይመለከታል። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ፍትሐዊና አፍቃሪ እንድንሆን ይፈልጋል። ከዚህም በላይ ከሌሎች እይታ ውጭ ሆነን ቤታችን ውስጥ የምንናገረውንም ሆነ የምናደርገውን ነገር ጭምር ትኩረት ሰጥቶ ያያል።—ዕብ. 4:13

19-21. (ሀ) ሽማግሌዎችና ዳኞች የአምላክን ሕዝቦች እንዴት እንዲይዙ ይጠበቅባቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል የትኞቹን ሕጎች አውጥቶ ነበር? እኛስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

19 ይሖዋ ሕዝቦቹን በአካባቢያቸው የሚኖሩት ሰዎች ከሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ መጠበቅ ይፈልጋል። ስለዚህ ሽማግሌዎችና ዳኞች ሕጉን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያስፈጽሙ ይጠብቅባቸው ነበር። ሆኖም ሕዝቡን እንዲዳኙ የተሾሙት ሰዎች በጭካኔ ሊፈርዱ ወይም ከልክ በላይ ጥብቅ ሊሆኑ አይገባም ነበር። ከዚህ ይልቅ ፍትሕን መውደድ ነበረባቸው።—ዘዳ. 1:13-17፤ 16:18-20

20 ይሖዋ ለሕዝቦቹ ስለሚራራ ኢፍትሐዊ የሆነ ነገር እንዳይፈጸምባቸው የሚከላከሉ ሕጎችን አውጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሕጉ አንድ ሰው በሐሰት የሚወነጀልበት አጋጣሚ ጠባብ እንዲሆን ያደርግ ነበር። አንድ ሰው ክስ ከተሰነዘረበት ከሳሹን የማወቅ መብት ነበረው። (ዘዳ. 19:16-19፤ 25:1) በተጨማሪም ግለሰቡ ጥፋተኛ ነው የሚል ፍርድ ከመተላለፉ በፊት ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች ቀርበው መመሥከር ነበረባቸው። (ዘዳ. 17:6፤ 19:15) አንድ ሰው ብቻ የመሠከረበትን ወንጀለኛ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እንዲህ ያለው ሰውም ቢሆን ከቅጣት እንደሚያመልጥ ሊሰማው አይገባም። ያደረገውን ነገር ይሖዋ አይቶታል። በቤተሰብ ውስጥ ደግሞ አምላክ ለአባቶች ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፤ ሆኖም ሥልጣናቸው ገደብ ነበረው። የከተማዋ ሽማግሌዎች በአንዳንድ የቤተሰብ ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ ገብተው የመጨረሻውን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር።—ዘዳ. 21:18-21

21 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ ፍትሐዊ በመሆን ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል፤ እሱ ፍትሕ የጎደለው አንዳች ነገር አያደርግም። (መዝ. 9:7) የእሱን መሥፈርቶች በታማኝነት ለሚጠብቁ ሰዎች ወሮታቸውን ይከፍላቸዋል፤ ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙትን ግን ይቀጣቸዋል። (2 ሳሙ. 22:21-23፤ ሕዝ. 9:9, 10) አንዳንዶች የክፋት ድርጊት ፈጽመው ከቅጣት ያመለጡ ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ ተገቢ ነው ባለው ጊዜ እነዚህ ሰዎች የእጃቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል። (ምሳሌ 28:13) ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች ካልሆኑ “በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር” እንደሆነ መገንዘባቸው አይቀርም።—ዕብ. 10:30, 31

ሕጉ በተለይ ለእነማን ጥበቃ ያደርግ ነበር?

ሽማግሌዎች አለመግባባቶችን ሲፈቱ ይሖዋ ለፍትሕ ያለውን አመለካከትና ለሰዎች ያለውን ፍቅር እንዲያንጸባርቁ ይጠበቅባቸው ነበር (አንቀጽ 22⁠ን ተመልከት) *

22-24. (ሀ) ሕጉ በተለይ ለእነማን ጥበቃ ያደርግ ነበር? ይህስ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? (ለ) በዘፀአት 22:22-24 ላይ ምን ማሳሰቢያ ይገኛል?

22 ሕጉ በተለይ ራሳቸውን መከላከል ለማይችሉ ሰዎች ለምሳሌ ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች፣ ለመበለቶችና ለባዕድ አገር ሰዎች ጥበቃ ያደርግ ነበር። በእስራኤል የነበሩ ዳኞች “የባዕድ አገሩን ሰው ወይም አባት የሌለውን ልጅ ፍርድ አታዛባ፤ የመበለቲቱን ልብስ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ” የሚል መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳ. 24:17) ይሖዋ በማኅበረሰቡ ውስጥ ላሉ ይበልጥ ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ከዚህም በላይ በእነሱ ላይ በደል የሚፈጽሙ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋቸው ነበር።—ዘፀአት 22:22-24ን አንብብ።

23 በተጨማሪም ሕጉ በዘመዳሞች መካከል ማንኛውም ዓይነት የፆታ ግንኙነት እንዳይፈጸም ስለሚያዝዝ የቤተሰብ አባል በሆነ ሰው የሚፈጸምን የፆታ ጥቃት ይከላከል ነበር። (ዘሌ. 18:6-30) በእስራኤል ዙሪያ የነበሩት ብሔራት እንዲህ ያለውን ድርጊት በቸልታ ያልፉ አልፎ ተርፎም ያበረታቱ ነበር፤ የአምላክ ሕዝቦች ግን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት በማዳበር ይህን ድርጊት ሊጸየፉት ይገባ ነበር።

24 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች በሥራቸው ላሉት ሁሉ ፍቅራዊ አሳቢነት እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል። ፆታዊ ጥቃቶችን የሚጠላ ከመሆኑም ሌላ ሁሉም ሰው በተለይም ይበልጥ ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች ፍትሕና ጥበቃ እንዲያገኙ ይፈልጋል።

“ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው”

25-26. (ሀ) ፍቅርና ፍትሕ ልክ እንደ እስትንፋስና ሕይወት ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ተከታታይ ርዕስ ቀጣይ ክፍል ላይ ምን እንመረምራለን?

25 ፍቅርና ፍትሕ ልክ እንደ እስትንፋስና ሕይወት ናቸው፤ በምድር ላይ አንዳቸው ያለ ሌላው ሊኖሩ አይችሉም። ይሖዋ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደሚይዘን እርግጠኞች ስንሆን ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። ለአምላክና ለጽድቅ መሥፈርቶቹ ፍቅር ካለን ደግሞ ሌሎችን ለመውደድና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመያዝ እንነሳሳለን።

26 የሕጉ ቃል ኪዳን በይሖዋና በእስራኤላውያን መካከል ለነበረው ዝምድና ልክ እንደ እስትንፋስ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ሕጉን ከፈጸመ በኋላ የሙሴ ሕግ ይበልጥ በተሻለ ነገር ተተክቷል። (ሮም 10:4) ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” እንደሆነ ተናግሯል። (ዕብ. 10:1) የዚህ ተከታታይ ርዕስ ቀጣይ ክፍል ከእነዚህ መልካም ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም ፍቅርና ፍትሕ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ሚና እንዳላቸው ያብራራል።

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ

^ አን.5 ይህ ርዕስ ይሖዋ እንደሚያስብልን እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርጉንን ምክንያቶች ከሚያብራሩ አራት ተከታታይ ርዕሶች መካከል የመጀመሪያው ነው። የቀሩት ሦስት ርዕሶች በግንቦት 2019 መጠበቂያ ግንብ ላይ ይወጣሉ። ርዕሳቸው “ፍቅርና ፍትሕ—በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ፣” “ፍቅርና ፍትሕ—ክፋት በሞላበት ዓለም ውስጥ” እና “ጥቃት የደረሰባቸውን ማጽናናት” የሚል ነው።

^ አን.2 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ይሖዋ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ከ600 የሚበልጡ ሕጎች “ሕጉ፣” “የሙሴ ሕግ” ወይም “ትእዛዛቱ” ተብለው ይጠራሉ። በተጨማሪም ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ብዙ ጊዜ “ሕጉ” ተብለው ተጠርተዋል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ቃል መላውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ለማመልከት ተሠርቶበታል።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እስራኤላዊ እናት ምግብ በምታዘጋጅበት ወቅት ከሴት ልጆቿ ጋር አስደሳች ውይይት ስታደርግ። ከበስተጀርባ አባትየው በጎችን መንከባከብ ስለሚቻልበት መንገድ ወንድ ልጁን ሲያሠለጥነው።

^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ በከተማዋ በር ላይ ያሉት ሽማግሌዎች በአንድ ነጋዴ በደል ለተፈጸመባት መበለትና ለልጇ ፍቅራዊ እርዳታ ሲያደርጉ።