በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 13

በአገልግሎት ላይ የምታገኟቸውን ሰዎች ስሜት የምትረዱ ሁኑ

በአገልግሎት ላይ የምታገኟቸውን ሰዎች ስሜት የምትረዱ ሁኑ

“በጣም አዘነላቸው። ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።”—ማር. 6:34

መዝሙር 70 የሚገባቸውን ሰዎች ፈልጉ

የትምህርቱ ዓላማ *

1. ኢየሱስን እንድንወደው ከሚያደርጉን ባሕርያት መካከል አንዱ ምንድን ነው? አብራራ።

ኢየሱስን እንድንወደው ከሚያደርጉን ባሕርያት መካከል አንዱ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚረዳ መሆኑ ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ‘ደስ ከሚላቸው ጋር ይደሰት’ እንዲሁም ‘ከሚያለቅሱ ጋር ያለቅስ ነበር።’ (ሮም 12:15) ለምሳሌ ያህል፣ 70ዎቹ ደቀ መዛሙርት የተሰጣቸውን የስብከት ተልእኮ በተሳካ ሁኔታ ከተወጡ በኋላ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹለት ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት [አድርጓል]።” (ሉቃስ 10:17-21) በሌላ በኩል ደግሞ የአልዓዛር ሞት በሚወዱት ሰዎች ላይ ያስከተለውን ሐዘን ሲመለከት ‘እጅግ አዝኖና ተረብሾ’ ነበር።—ዮሐ. 11:33

2. ኢየሱስ ለሌሎች ርኅራኄ ሊያሳይ የቻለው እንዴት ነው?

2 ይህ ፍጹም ሰው ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ይህን ያህል ምሕረትና ርኅራኄ ሊያሳይ የቻለው እንዴት ነው? በዋነኝነት ሰዎችን ስለሚወድ ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ‘በተለይ በሰው ልጆች እጅግ ይደሰት ነበር።’ (ምሳሌ 8:31) ለሰው ልጆች የነበረው እንዲህ ያለ ፍቅር እነሱ የሚያስቡበትን መንገድ ጠንቅቆ እንዲያውቅ አስችሎታል። ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስን አስመልክቶ ሲናገር “በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ [ነበር]” ብሏል። (ዮሐ. 2:25) ኢየሱስ ለሰዎች ከልቡ ይራራ ነበር። የመንግሥቱን መልእክት የሰበከላቸው ሰዎች ኢየሱስ እንደሚወዳቸው ስለተገነዘቡ ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። እኛም ለሰዎች ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት ባደረግን መጠን በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ እንሆናለን።—2 ጢሞ. 4:5

3-4. (ሀ) የሌሎችን ስሜት የምንረዳ ከሆነ ለአገልግሎታችን ምን አመለካከት ይኖረናል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሰዎች የመስበክ ግዴታ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር፤ እኛም ተመሳሳይ ግዴታ እንዳለብን እንገነዘባለን። (1 ቆሮ. 9:16) ሆኖም የሰዎችን ስሜት የምንረዳ ከሆነ አገልግሎታችንን የምናከናውነው ግዴታችን እንደሆነ ስለሚሰማን ብቻ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ለሰዎች የምንሰብከው ስለምናስብላቸውና እነሱን መርዳት ስለምንፈልግ ነው። “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ [እንደሚያስገኝ]” እናውቃለን። (ሥራ 20:35) ለአገልግሎታችን እንዲህ ያለ አመለካከት ለማዳበር ጥረት ባደረግን ቁጥር የምናገኘው ደስታም የዚያኑ ያህል ይጨምራል።

4 በዚህ ርዕስ ውስጥ በአገልግሎታችን ላይ የሌሎችን ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በመጀመሪያ ኢየሱስ ለሰዎች ከነበረው ስሜት ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን። ከዚያም እሱ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እንመረምራለን።—1 ጴጥ. 2:21

ኢየሱስ በአገልግሎት የሚያገኛቸውን ሰዎች ስሜት ይረዳ ነበር

ኢየሱስ የሌሎችን ስሜት የሚረዳ መሆኑ እነሱን የሚያጽናና መልእክት እንዲሰብክ አነሳስቶታል (ከአንቀጽ 5-6⁠ን ተመልከት)

5-6. (ሀ) ኢየሱስ ለእነማን ርኅራኄ አሳይቷል? (ለ) በኢሳይያስ 61:1, 2 ላይ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ኢየሱስ ለሚሰብክላቸው ሰዎች ያዘነላቸው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ የሰዎችን ስሜት እንደሚረዳ የሚያሳይ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ ወቅት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያለምንም እረፍት ምሥራቹን ሲሰብኩ ስለቆዩ በጣም ደክሟቸው ነበር። ሌላው ቀርቶ “ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም” ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ትንሽ አረፍ እንዲሉ’ ሲል “ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ” ይዟቸው ሄደ። ሆኖም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሮጠው በመሄድ ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ቀድመው ወደዚያ ስፍራ ደረሱ። ኢየሱስ እዚያ ቦታ ደርሶ ሰዎቹን ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን? “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩ . . . በጣም አዘነላቸው። * ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።”—ማር. 6:30-34

6 ኢየሱስ ለሕዝቡ ያዘነላቸው ወይም የራራላቸው ለምንድን ነው? ሕዝቡ ‘እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንደነበሩ’ አስተውሎ ነበር። ምናልባትም ኢየሱስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ድሆች እንደሆኑና ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ሲሉ አድካሚ ሥራ እንደሚሠሩ አስተውሎ ይሆናል። አንዳንዶቹ ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት አጥተው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መረዳት አይከብደውም። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ በእሱም ላይ ሳይደርሱበት አይቀሩም። ኢየሱስ ለሌሎች ያስብ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እነሱን የሚያጽናና መልእክት መናገር ይፈልግ ነበር።—ኢሳይያስ 61:1, 2ን አንብብ።

7. ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? በኢየሱስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዘመናችንም በርካታ ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” ሆነዋል። ከተለያዩ ችግሮች ጋር ይታገላሉ። እኛ ደግሞ እነዚህ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማለትም የመንግሥቱን መልእክት ይዘናል። (ራእይ 14:6) በመሆኑም ‘ለችግረኛውና ለድሃው የሚያዝነውን’ የጌታችንን ምሳሌ በመከተል ምሥራቹን እንሰብክላቸዋለን። (መዝ. 72:13) ለሰዎች ስለምንራራ እነሱን ለመርዳት ስንል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን።

የሌሎችን ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

እያንዳንዱ ሰው ምን እንደሚያስፈልገው ለማሰብ ሞክር (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

8. በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

8 የምንሰብክላቸውን ሰዎች ስሜት መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን በአገልግሎት ላይ በምናገኛቸው ሰዎች ቦታ ማስቀመጥ እንዲሁም ሌሎች እኛን እንዲይዙን በምንፈልገው መንገድ እነሱን መያዝ ይኖርብናል። * (ማቴ. 7:12) እንዲህ ማድረግ የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት። አንደኛ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ምን እንደሚያስፈልገው ለማሰብ ሞክር። የምሥራቹ ሰባኪ በመሆን የምናከናውነው ሥራ አንድ ሐኪም ከሚያከናውነው ሥራ ጋር ይመሳሰላል። አንድ ጥሩ ሐኪም እያንዳንዱ ታካሚ ምን እንደሚያስፈልገው ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። ጥያቄዎችን የሚጠይቅ ከመሆኑም ሌላ ታካሚው ስለሚሰማው ሕመም ወይም ስለሚታዩበት ምልክቶች ሲናገር በጥሞና ያዳምጣል። ወደ አእምሮው የመጣውን አንድ መድኃኒት ዝም ብሎ ከማዘዝ ይልቅ ታካሚው የሚታዩበትን ምልክቶች ለመገምገም ሲል የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ ሊወስን ይችላል፤ ከዚያም ትክክለኛውን መድኃኒት ያዛል። እኛም በተመሳሳይ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ መግቢያ አንጠቀምም። ከዚህ ይልቅ የእያንዳንዱን ግለሰብ ሁኔታና አመለካከት ግምት ውስጥ እናስገባለን።

9. የትኛውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ማስወገድ አለብን? ምን ብናደርግ የተሻለ ይሆናል?

9 በአገልግሎት ላይ አንድ ሰው ስታገኙ ግለሰቡ ያለበትን ሁኔታ፣ የሚያምንበትን ነገር ወይም እንዲህ ዓይነት እምነት የያዘበትን ምክንያት እንደምታውቁ ሊሰማችሁ አይገባም። (ምሳሌ 18:13) ከዚህ ይልቅ ጥያቄዎችን በዘዴ በመጠቀም ግለሰቡ የውስጡን አውጥቶ እንዲናገር አድርጉ። (ምሳሌ 20:5) የአካባቢያችሁ ባሕል የሚፈቅድ ከሆነ ስለ ሥራው፣ ስለ ቤተሰቡ፣ ስለ አስተዳደጉና ስለሚያምንባቸው ነገሮች ጠይቁት። ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ስናደርግ በተዘዋዋሪ መንገድ ምሥራቹ የሚያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነ እንዲነግሩን እያደረግን ነው። ይህን ካወቅን ልክ እንደ ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ምን እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብና በዚያ ላይ ተመሥርተን እርዳታ መስጠት እንችላለን።—ከ1 ቆሮንቶስ 9:19-23 ጋር አወዳድር።

የምትሰብክለት ሰው ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚመራ ለማሰብ ሞክር (ከአንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት)

10-11. ከ2 ቆሮንቶስ 4:7, 8 ጋር በሚስማማ መልኩ፣ የሌሎችን ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት የምንችልበት ሁለተኛው መንገድ ምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

10 ሁለተኛ፣ ሕይወታቸው ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በተወሰነ መጠን መረዳት አይከብደንም። ምክንያቱም ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን እኛም ችግር ይደርስብናል። (1 ቆሮ. 10:13) በዚህ ሥርዓት ውስጥ መኖር በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን። እነዚህን ችግሮች መቋቋም የቻልነው በይሖዋ እርዳታ ብቻ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:7, 8ን አንብብ።) ይሁንና ከይሖዋ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የሌላቸው ሰዎች በዚህ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም ምን ያህል ሊከብዳቸው እንደሚችል አስብ። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ለእነዚህ ሰዎች እናዝንላቸዋለን፤ ይህም “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ [የሚያበስረውን] ምሥራች” እንድናውጅላቸው ያነሳሳናል።—ኢሳ. 52:7

11 ሰርጌ የተባለን ወንድም ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሰርጌ እውነትን ከመስማቱ በፊት ዓይናፋርና ዝምተኛ ነበር። ከሰዎች ጋር መነጋገር በጣም ይከብደዋል። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ሰርጌ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁ ስሄድ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለሌሎች የማካፈል ግዴታ እንዳለባቸው ተማርኩ። ይህን ፈጽሞ ላደርገው እንደማልችል ይሰማኝ ነበር።” ሆኖም ሰርጌ እውነትን ያልሰሙ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ ማለትም ይሖዋን ሳያውቁ የሚመሩት ሕይወት ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “እየተማርኳቸው የነበሩት አዳዲስ ነገሮች ከፍተኛ ደስታና ውስጣዊ ሰላም አስገኝተውልኛል። ሌሎችም እነዚህን እውነቶች መማር እንደሚያስፈልጋቸው አውቅ ነበር።” ሰርጌ የሰዎቹን ስሜት ይበልጥ በተረዳ መጠን ለመስበክ ያለው ድፍረትም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ሄደ። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም የሚያስገርመው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች ሰዎች መናገሬ በራስ የመተማመን ስሜቴን ከፍ አደረገልኝ። እንዲሁም የማምንባቸው አዳዲስ እውነቶች በልቤ ውስጥ ሥር እንዲሰዱ አደረጋቸው።” *

አንዳንዶች መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል (ከአንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)

12-13. በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ስናስተምር ትዕግሥተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

12 ሦስተኛ፣ ሰዎችን ስታስተምር ትዕግሥተኛ ሁን። በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች እኛ ጠንቅቀን የምናውቃቸውን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጨርሶ ላያውቁ እንደሚችሉ አስታውስ። በተጨማሪም በርካታ ሰዎች፣ የሚያምኑባቸውን ነገሮች እጅግ ከፍ አድርገው ይመለከቷቸዋል። እምነታቸው ከቤተሰባቸው፣ ከባሕላቸውና ከማኅበረሰቡ ጋር እንደሚያስተሳስራቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ያሉ ሰዎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

13 እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ለማሰብ ሞክር፦ አንድን ያረጀና እየፈራረሰ ያለ ድልድይ መቀየር ቢያስፈልግ ምን ይደረጋል? በአብዛኛው አሮጌው ድልድይ አገልግሎት እየሰጠ እያለ አዲሱ ድልድይ መገንባት ይጀምራል። አዲሱ ድልድይ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ አሮጌው ድልድይ እንዲፈርስ ይደረጋል። እኛም በተመሳሳይ ሰዎች “አሮጌውን” እምነታቸውን እንዲተዉ ከመጠየቃችን በፊት አሁን እየተማሯቸው ላሉት “አዲስ” እውነቶች ማለትም ከዚህ በፊት ለማያውቋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አድናቆት እንዲያዳብሩ መርዳት ሊያስፈልገን ይችላል። ቀደም ሲል የነበራቸውን አመለካከት ሊተዉ የሚችሉት እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። ሰዎች እንዲህ ያሉ ለውጦችን እንዲያደርጉ መርዳት ጊዜ ሊወስድ ይችላል።—ሮም 12:2

14-15. ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋችንን በተመለከተ ለሰዎች ማስረዳት የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

14 በአገልግሎት ስንካፈል ትዕግሥተኞች ከሆን ሰዎች ከዚህ በፊት ሰምተዋቸው የማያውቋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ወዲያውኑ እንዲረዱ ወይም እንዲቀበሉ አንጠብቅባቸውም። የሌሎችን ስሜት የምንረዳ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ቀስ በቀስ እንዲያስተውሉ እንረዳቸዋለን። ለምሳሌ ያህል፣ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋችንን በተመለከተ ለሰዎች ማስረዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በርካታ ሰዎች ስለዚህ ትምህርት ፈጽሞ አያውቁም፤ ቢያውቁም እውቀታቸው ውስን ነው። ሞት የሁሉም ነገር መጨረሻ እንደሆነ ያምኑ ይሆናል። አሊያም ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ሊያስቡ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎችን ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

15 አንድ ወንድም በዚህ ረገድ ውጤታማ ሆኖ ያገኘውን አቀራረብ ተናግሯል። ለሚያነጋግራቸው ሰዎች በመጀመሪያ ዘፍጥረት 1:28⁠ን ያነብላቸዋል። ከዚያም አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠራቸው የትና በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ አስቦ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል። አብዛኞቹ ሰዎች “ምድር ላይ አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ ነው” በማለት ይመልሳሉ። ከዚያም ወንድም ኢሳይያስ 55:11⁠ን ያነብላቸውና “አምላክ ዓላማውን ይለውጣል?” ብሎ ይጠይቃቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎቹ “አይ፣ አይለውጥም” ብለው ይመልሱለታል። በመጨረሻም ወንድም መዝሙር 37:10, 11⁠ን ካነበበላቸው በኋላ የሰው ልጆች ወደፊት ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚጠብቃቸው ይጠይቃቸዋል። ይህ ወንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በዚህ መንገድ ተጠቅሞ አምላክ አሁንም ጥሩ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ እንደሚፈልግ በማብራራት በርካታ ሰዎችን መርዳት ችሏል።

አበረታች ደብዳቤ እንደመጻፍ ያሉ ደግነታችንን ለማሳየት የምናደርጋቸው ቀለል ያሉ ነገሮች ሌሎችን በእጅጉ ሊጠቅሙ ይችላሉ (ከአንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት)

16-17. በምሳሌ 3:27 ላይ በተገለጸው መሠረት አሳቢነት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ምሳሌ ስጥ።

16 አራተኛ፣ አሳቢነት ልታሳይ የምትችልበትን ተግባራዊ መንገድ አስብ። ለምሳሌ የቤቱ ባለቤት በማይመቸው ጊዜ ላይ ሄደህ ይሆን? ከሆነ ይቅርታ ከጠየቅክ በኋላ አመቺ በሆነ ጊዜ ተመልሰህ እንደምትመጣ ልትገልጽለት ትችላለህ። የቤቱ ባለቤት ቀለል ያለ ሥራ ለመሥራት እገዛ ቢያስፈልገውስ? ወይም ከቤት መውጣት የማይችል ቢሆንና ወደ ገበያ የሚልከው ሰው ቢፈልግስ? እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ግለሰቡን መርዳት የምትችልባቸው ጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው።—ምሳሌ 3:27ን አንብብ።

17 አንዲት እህት ቀላል በሚመስል ጉዳይ ደግነት በማሳየቷ ጥሩ ውጤት አግኝታለች። ልጃቸውን በሞት ላጡ አንድ ባልና ሚስት በርኅራኄ ተነሳስታ ደብዳቤ ጻፈችላቸው። በደብዳቤው ላይ አንዳንድ የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ጽፋ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ደብዳቤውን ሲያነብቡ ምን ተሰማቸው? እናትየው እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ትናንት በጣም ከፍቶኝ ነበር። የጻፍሽልን ደብዳቤ ከምታስቢው በላይ ጠቅሞናል። ምስጋናዬን ምን ብዬ ልገልጽልሽ እንደምችል አላውቅም። በትናንትናው ዕለት ደብዳቤውን ከ20 ጊዜ በላይ ሳላነበው አልቀርም። ደግነትና አሳቢነት የተንጸባረቀበት እንዲሁም የሚያጽናና መሆኑ በጣም አስገርሞኛል። ከልብ እናመሰግንሻለን።” ራሳችንን መከራ እየደረሰባቸው ባሉ ሰዎች ቦታ በማስቀመጥ እነሱን ለመርዳት ተግባራዊ እርምጃ የምንወስድ ከሆነ ጥሩ ውጤት እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ስለሚጠበቅባችሁ ነገር ሚዛናዊ አመለካከት ይኑራችሁ

18. በ1 ቆሮንቶስ 3:6, 7 መሠረት ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ምን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

18 እርግጥ ነው፣ በአገልግሎት ላይ የምንጫወተውን ሚና በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ሰዎች ስለ አምላክ እንዲማሩ በመርዳት ረገድ የተወሰነ አስተዋጽኦ የምናበረክት ቢሆንም ዋናውን ሚና የምንጫወተው ግን እኛ አይደለንም። (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7ን አንብብ።) ሰዎችን ወደ ራሱ የሚስበው ይሖዋ ነው። (ዮሐ. 6:44) ደግሞም እያንዳንዱ ግለሰብ ምሥራቹን የመቀበሉ ወይም ያለመቀበሉ ጉዳይ የተመካው በራሱ የልብ ሁኔታ ላይ ነው። (ማቴ. 13:4-8) ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩ ሰዎች ሁሉ የበለጠ የማስተማር ችሎታ ቢኖረውም በርካታ ሰዎች መልእክቱን እንዳልተቀበሉ ማስታወስ ይኖርብናል። እንግዲያው በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ለመልእክታችን በጎ ምላሽ ባይሰጡ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም።

19. በአገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ስሜት መረዳታችን ምን ጥቅም ያስገኛል?

19 በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ስሜት መረዳታችን ብዙ ጥቅም ያስገኛል። የስብከቱ ሥራችን ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል። ከመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ ማጣጣም እንችላለን። እንዲሁም “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ” ምሥራቹን መቀበል ቀላል እንዲሆንላቸው እናደርጋለን። (ሥራ 13:48) እንግዲያው “[አጋጣሚውን] እስካገኘን ድረስ ለሁሉም . . . መልካም እናድርግ።” (ገላ. 6:10) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በሰማይ ያለውን አባታችንን ስለምናስከብር ደስተኞች እንሆናለን።—ማቴ. 5:16

መዝሙር 64 በመከሩ ሥራ በደስታ መካፈል

^ አን.5 የሌሎችን ስሜት የምንረዳ ከሆነ በአገልግሎታችን ይበልጥ ደስተኛና ውጤታማ እንሆናለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ የምናገኘውን ትምህርት እንመለከታለን። እንዲሁም በስብከቱ ሥራችን የምናገኛቸውን ሰዎች ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እንመረምራለን።

^ አን.5 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ማዘን የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ መከራ እየደረሰበት ላለ ወይም በደል ለተፈጸመበት ሰው መራራትን ያመለክታል። እንዲህ ያለው ስሜት አንድን ሰው ሌሎችን ለመርዳት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል።

^ አን.8 በግንቦት 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በአገልግሎታችሁ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ አድርጉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።