በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 10

እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?

እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?

“ሁለቱም ወርደው ውኃው ውስጥ ገቡ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው።”—ሥራ 8:38

መዝሙር 52 ራስን ለአምላክ መወሰን

የትምህርቱ ዓላማ *

1. አዳምና ሔዋን ምን ነገር አጥተዋል? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?

መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው ማን ይመስልሃል? አዳምና ሔዋን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ፍሬ በበሉ ጊዜ በዚህ ረገድ ያላቸውን አቋም በግልጽ አሳይተዋል፦ ሁለቱም በይሖዋም ሆነ እሱ ባወጣቸው መሥፈርቶች ላይ እምነት አልነበራቸውም። መልካምና ክፉ ከሆነው ነገር ጋር በተያያዘ የራሳቸውን መሥፈርት ለማውጣት መርጠዋል። (ዘፍ. 3:22) ሆኖም ይህ ምን ኪሳራ እንዳስከተለባቸው ተመልከት። ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት አጥተዋል። በተጨማሪም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን ያጡ ከመሆኑም ሌላ ኃጢአትንና ሞትን ለልጆቻቸው አስተላልፈዋል። (ሮም 5:12) በእርግጥም አዳምና ሔዋን ያደረጉት ምርጫ ብዙ መከራ አስከትሏል።

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በኢየሱስ ካመነ በኋላ ወዲያውኑ መጠመቅ ፈልጓል (ከአንቀጽ 2-3⁠ን ተመልከት)

2-3. (ሀ) ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ ፊልጶስ ሲሰብክለት ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) ጥምቀት ምን በረከቶች ያስገኝልናል? የትኞቹን ጥያቄዎችስ እንመረምራለን?

2 አዳምና ሔዋን ያደረጉትን ነገር ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ ፊልጶስ በሰበከለት ጊዜ ከሰጠው ምላሽ ጋር ለማወዳደር ሞክር። ጃንደረባው፣ ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉለት ነገር ከፍተኛ አድናቆት ስለነበረው ወዲያውኑ ለመጠመቅ ተነሳስቷል። (ሥራ 8:34-38) ራሳችንን ለአምላክ ስንወስንና ልክ እንደዚያ ጃንደረባ ስንጠመቅ አቋማችን በግልጽ እንዲታይ እናደርጋለን። ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። በተጨማሪም ይህን እርምጃ መውሰዳችን በይሖዋ እንደምንታመን እንዲሁም መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው እሱ እንደሆነ እንደተገነዘብን ያሳያል።

3 እስቲ ይሖዋን ማገልገላችን ምን በረከቶችን እንደሚያስገኝልን አስብ! አንደኛ፣ የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር በሙሉ መልሰን የማግኘት ተስፋ ይኖረናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት መሠረት በማድረግ ይሖዋ በደላችንን ይቅር የሚለን ከመሆኑም በላይ ንጹሕ ሕሊና ይሰጠናል። (ማቴ. 20:28፤ ሥራ 10:43) በተጨማሪም ይሖዋ ሞገሱን ከሚያሳያቸው አገልጋዮቹ መካከል እንደ አንዱ ስለምንቆጠር ወደፊት አስደናቂ ሕይወት ይጠብቀናል። (ዮሐ. 10:14-16፤ ሮም 8:20, 21) ጥምቀት እንዲህ ያሉ በረከቶችን እንደሚያስገኝ የታወቀ ቢሆንም ስለ ይሖዋ የተማሩ አንዳንድ ሰዎች የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ምሳሌ ከመከተል ወደኋላ ይላሉ። እነዚህን ሰዎች እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው ነገር ምንድን ነው? እንቅፋት የሚሆኑባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የሚችሉትስ እንዴት ነው?

አንዳንዶችን ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ የሚያደርጓቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች

አንዳንዶችን ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ የሚያደርጓቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች

ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት (ከአንቀጽ 4-5⁠ን ተመልከት) *

4-5. አቬሪና ሐና ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል?

4 ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት። የአቬሪ ወላጆች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። አባቱ የተዋጣለት የጉባኤ ሽማግሌና አፍቃሪ አባት በመሆን ረገድ ግሩም ስም አትርፏል። ያም ሆኖ አቬሪ ለመጠመቅ ያመነታ ነበር። ለምን? “እንደ አባቴ ዓይነት ሰው መሆን እንደማልችል ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግሯል። በተጨማሪም አቬሪ ወደፊት ሊሰጡት የሚችሉትን ኃላፊነቶች ለመሸከም ብቁ እንዳልሆነ ይሰማው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በሕዝብ ፊት እንድጸልይ፣ ንግግር እንድሰጥ ወይም አንድን ቡድን በመስክ አገልግሎት እንድመራ ብጠየቅስ ብዬ እፈራ ነበር።”

5 የ18 ዓመት ወጣት የሆነችው ሐና፣ ብቁ አይደለሁም ከሚል ሥር የሰደደ ስሜት ጋር ትታገል ነበር። ወላጆቿ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው። ያም ቢሆን የይሖዋን መሥፈርቶች መጠበቅ እንደማትችል ይሰማት ነበር። ለምን? ሐና ለራሷ ያላት ግምት በጣም ዝቅተኛ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በሐዘን ከመደቆሷ የተነሳ ሆን ብላ ራሷን ትጎዳ ነበር፤ ይህ ደግሞ ሁኔታውን ከማባባስ ውጭ ምንም ፋይዳ አልነበረውም። ሐና እንዲህ ብላለች፦ “ስለዚህ ጉዳይ ለማንም ሌላው ቀርቶ ለወላጆቼ እንኳ ተናግሬ አላውቅም። በራሴ ላይ በማደርገው ነገር ምክንያት ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይፈልገኝ ይሰማኝ ነበር።”

የጓደኞች ተጽዕኖ (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት) *

6. ቫኔሳን እንዳትጠመቅ የከለከላት ነገር ምን ነበር?

6 የጓደኞች ተጽዕኖ። የ22 ዓመቷ ቫኔሳ እንዲህ ብላለች፦ “አሥር ዓመት ገደማ ለሚሆን ጊዜ የማውቃት በጣም ጥሩ ጓደኛ ነበረችኝ።” ሆኖም ቫኔሳ የመጠመቅ ግቧ ላይ እንድትደርስ ጓደኛዋ ምንም ድጋፍ አታደርግላትም ነበር። ይህም ቫኔሳን በጣም ጎድቷት ነበር፤ እንዲህ ብላለች፦ “ከሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ይከብደኛል፤ ስለዚህ ከእሷ ጋር ያለኝን ጓደኝነት ካቆምኩ መቼም ቢሆን ሌላ የቅርብ ጓደኛ አላገኝም የሚል ስጋት ነበረኝ።”

ስህተት ልሠራ እችላለሁ የሚል ፍርሃት (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) *

7. ማኬላ የተባለች ወጣት ምን ፍራቻ አድሮባት ነበር? ለምንስ?

7 ከባድ ስህተት እሠራለሁ የሚል ፍርሃት። ማኬላ ወንድሟ ሲወገድ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረች። ወንድሟ የፈጸመው ድርጊት በወላጆቿ ላይ ምን ያህል ሐዘን እንዳስከተለ ከልጅነቷ አንስቶ ተመልክታለች። ማኬላ እንዲህ ብላለች፦ “ከተጠመቅኩ በኋላ ስህተት ብሠራ እንደምወገድና ይህም በወላጆቼ ላይ የባሰ ሐዘን እንደሚያስከትል ይሰማኝ ነበር።”

ተቃውሞ ሊደርስብኝ ይችላል የሚል ፍራቻ (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት) *

8. ሚልዝ የተባለ ወጣት ምን ፍርሃት አድሮበት ነበር?

8 ተቃውሞ ሊደርስብኝ ይችላል የሚል ፍራቻ። ሚልዝ የተባለውን ወጣት ሁኔታ እንመልከት። አባቱና የእንጀራ እናቱ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ ወላጅ እናቱ ግን አይደለችም። ሚልዝ እንዲህ ብሏል፦ “ለ18 ዓመት ያህል የኖርኩት ከእናቴ ጋር ነው። አባቴ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን ምን ያህል እንደተቃወመችው ስላየሁ መጠመቅ እንደምፈልግ ለእሷ መንገር አስፈርቶኝ ነበር። በእኔም ላይ ስደት ታደርስብኛለች ብዬ ፈርቼ ነበር።”

እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምትችለው እንዴት ነው?

9. ይሖዋ ምን ያህል ታጋሽና አፍቃሪ እንደሆነ መማርህ ምን ውጤት ይኖረዋል?

9 አዳምና ሔዋን ይሖዋን ለማገልገል ያልመረጡት ለእሱ ጥልቅ ፍቅር ስላላዳበሩ ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ ረዘም ያለ ዕድሜ ኖረው ልጆች እንዲወልዱና እነዚህን ልጆች ራሳቸው ባወጡት መሥፈርት መሠረት እንዲያሳድጉ ፈቅዶላቸዋል። አዳምና ሔዋን ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት ያደረጉት ውሳኔ ምን ያህል ሞኝነት የተንጸባረቀበት እንደሆነ ብዙም ሳይቆይ ታይቷል። የመጀመሪያ ልጃቸው ምንም ጥፋት የሌለበትን ወንድሙን ገድሏል፤ እንዲሁም በጊዜ ሂደት የሰው ዘር ሕይወት በዓመፅና በራስ ወዳድነት የተሞላ ሆኗል። (ዘፍ. 4:8፤ 6:11-13) ይሁንና ይሖዋ ከአዳምና ከሔዋን ልጆች መካከል እሱን ለማገልገል የመረጡትን ሁሉ የሚያድንበት መንገድ አዘጋጅቷል። (ዮሐ. 6:38-40, 57, 58) ይሖዋ ምን ያህል ታጋሽና አፍቃሪ እንደሆነ እየተማርክ ስትሄድ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ ማደጉ አይቀርም። አዳምና ሔዋን ከተከተሉት ጎዳና በመራቅ ራስህን ለይሖዋ መወሰን እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።

እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምትችለው እንዴት ነው?

(ከአንቀጽ 9-10⁠ን ተመልከት) *

10. በመዝሙር 19:7 ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋን ለማገልገል የሚረዳህ እንዴት ነው?

10 ስለ ይሖዋ መማርህን ቀጥል። ስለ ይሖዋ ያለህ እውቀት እየጨመረ ሲሄድ እሱን በተሳካ ሁኔታ ማገልገል እንደምትችል ይበልጥ እርግጠኛ ትሆናለህ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አቬሪ እንዲህ ብሏል፦ በመዝሙር 19:7 ላይ የሚገኘውን ማረጋገጫ ማንበቤና በዚያ ላይ ማሰላሰሌ ብቁ አይደለሁም የሚለውን ስሜት እንዳሸንፍ ረድቶኛል።” (ጥቅሱን አንብብ።) አቬሪ፣ ይሖዋ ይህን ቃል የፈጸመው እንዴት እንደሆነ ሲመለከት ለእሱ ያለው ፍቅር አድጓል። ፍቅር፣ ብቁ አይደለሁም የሚለውን ስሜት እንድናሸንፍ ብቻ ሳይሆን በይሖዋና እሱ በሚፈልገው ነገር ላይ እንድናተኩር ጭምር ይረዳናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሐና እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤና የግል ጥናት ማድረጌ በራሴ ላይ ጉዳት ሳደርስ ይሖዋም እንደሚጎዳ እንድገነዘብ አድርጎኛል።” (1 ጴጥ. 5:7) ሐና ‘የአምላክን ቃል የምታደርጉ ሁኑ’ የሚለውን ምክር በሥራ ላይ አዋለች። (ያዕ. 1:22) ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን መታዘዝ ምን ያህል እንደጠቀመኝ ስመለከት ለእሱ ያለኝ ፍቅር ጨመረ። አሁን፣ ይሖዋ የእሱን እርዳታ በምፈልግበት ጊዜ ሁሉ እንደሚመራኝ እርግጠኛ ነኝ።” ሐና ራሷን እንድትጎዳ የሚገፋፋትን ስሜት ማሸነፍ ቻለች። ከዚያም ራሷን ለይሖዋ ወስና ተጠመቀች።

(አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) *

11. ቫኔሳ ጥሩ ወዳጆችን ለማፍራት ምን አድርጋለች? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?

11 ጓደኞችህን በጥበብ ምረጥ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ቫኔሳ፣ ጓደኛዋ ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንድትል እያደረገቻት እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተገነዘበች። በመሆኑም ከልጅቷ ጋር ያላትን ጓደኝነት አቋረጠች። ሆኖም በዚህ ብቻ አላበቃችም። በጉባኤ ውስጥ አዳዲስ ጓደኞች ለማፍራት ከፍተኛ ጥረት አደረገች። ቫኔሳ ኖኅና ቤተሰቡ የተዉት ምሳሌ በጣም እንደጠቀማት ተናግራለች። “ዙሪያቸውን የተከበቡት ይሖዋን በማይወዱ ሰዎች ቢሆንም እርስ በርስ ጥሩ ወዳጅነት መሥርተው ነበር” ብላለች። ቫኔሳ ከተጠመቀች በኋላ አቅኚ ሆነች። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “[አቅኚነት] በራሴ ጉባኤ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉባኤዎችም ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ጥሩ ጓደኝነት እንድመሠርት ረድቶኛል።” አንተም ይሖዋ በሰጠን ሥራ ላይ የቻልከውን ያህል ተሳትፎ በማድረግ ጥሩ ወዳጆችን ማፍራት ትችላለህ።—ማቴ. 24:14

(ከአንቀጽ 12-15⁠ን ተመልከት) *

12. አዳምና ሔዋን የትኛውን ዓይነት ፍርሃት አላዳበሩም? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?

12 ተገቢ የሆነ ፍርሃት አዳብር። ፍርሃት፣ ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን እንዳናሳዝን መፍራታችን ተገቢ ነው። (መዝ. 111:10) አዳምና ሔዋን እንዲህ ያለውን ፍርሃት አዳብረው ቢሆን ኖሮ በይሖዋ ላይ አያምፁም ነበር። ካመፁ በኋላ ዓይኖቻቸው ተከፈቱ፤ በሌላ አባባል ኃጢአተኛ መሆናቸውን ሙሉ በሙሉ ተገነዘቡ። ለልጆቻቸው ኃጢአትንና ሞትን ከማውረስ ውጭ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። ያሉበትን ሁኔታ ማየት ወይም መረዳት ስለቻሉ ራቁታቸውን መሆናቸው አሳፈራቸው፤ በመሆኑም ሰውነታቸውን የሚሸፍኑበት ነገር ሠሩ።—ዘፍ. 3:7, 21

13-14. (ሀ) በ1 ጴጥሮስ 3:21 መሠረት ሞትን ከልክ በላይ ልንፈራ የማይገባን ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?

13 ለይሖዋ ተገቢ የሆነ ፍርሃት ልናዳብር እንደሚገባ የታወቀ ነው፤ ለሞት ግን ከልክ ያለፈ ፍርሃት ሊኖረን አይገባም። ይሖዋ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት መንገድ አዘጋጅቶልናል። ኃጢአት ብንሠራም ከልብ ንስሐ የምንገባ ከሆነ ይሖዋ ይቅርታ ያደርግልናል። በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ካለን በደላችንን ይቅር ይለናል። እምነት እንዳለን የምናሳይበት ዋነኛው መንገድ ደግሞ ራሳችንን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ነው።—1 ጴጥሮስ 3:21ን አንብብ።

14 ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉ። በየዕለቱ የምናገኛቸውን መልካም ነገሮች የሚሰጠን እሱ ከመሆኑም ሌላ ስለ ራሱና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን አስተምሮናል። (ዮሐ. 8:31, 32) መመሪያና ድጋፍ የምናገኝበትን የክርስቲያን ጉባኤ አዘጋጅቶልናል። በዛሬው ጊዜ ሸክማችንን የሚሸከምልን ሲሆን ወደፊት ደግሞ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቶናል። (መዝ. 68:19፤ ራእይ 21:3, 4) ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ሲል እስካሁን ድረስ ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ስናሰላስል እሱን ለመውደድ እንገፋፋለን። እሱን ስንወደው ደግሞ ለእሱ ተገቢ የሆነ ፍርሃት እናዳብራለን። በጥልቅ የምንወደውን አካል እንዳናሳዝን እንፈራለን።

15. ማኬላ ስህተት ልሠራ እችላለሁ የሚለውን ፍርሃት ያሸነፈችው እንዴት ነው?

15 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ማኬላ ይሖዋ ምን ያህል ይቅር ባይ እንደሆነ መገንዘቧ ስህተት ልሠራ እችላለሁ የሚለውን ፍርሃት እንድታሸንፍ ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን እንደሆንንና ስህተት እንደምንሠራ ተገነዘብኩ። ሆኖም ይሖዋ እንደሚወደንና በቤዛው አማካኝነት ይቅር እንደሚለንም ተረድቻለሁ።” ለይሖዋ ያላት ፍቅር ራሷን ለእሱ እንድትወስንና እንድትጠመቅ አነሳስቷታል።

(አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት) *

16. ሚልዝ የእናቱን ተቃውሞ እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው?

16 የእናቱን ተቃውሞ በመፍራት ከመጠመቅ ወደኋላ ብሎ የነበረው ሚልዝ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲረዳው ጠየቀ። ሚልዝ እንዲህ ብሏል፦ “እሱም ያደገው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ነው። እናቴን ለማሳመን ምን ልላት እንደምችል አንዳንድ ሐሳቦችን አካፈለኝ። ለመጠመቅ የወሰንኩት በራሴ ተነሳስቼ እንጂ አባቴ ገፋፍቶኝ እንዳልሆነ ልነግራት እንደምችል ጠቆመኝ።” የሚልዝ እናት በውሳኔው አልተደሰተችም። በመሆኑም ሚልዝ ከጊዜ በኋላ ከእናቱ ቤት ለመውጣት የተገደደ ቢሆንም በውሳኔው ጸንቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ስላደረገልኝ መልካም ነገሮች ማወቄ ልቤን ነክቶታል። በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ በጥልቀት ማሰላሰሌ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደኝ እንድገነዘብ አድርጎኛል። ይህም ራሴን ለይሖዋ እንድወስንና እንድጠመቅ አነሳስቶኛል።”

በውሳኔህ ጽና

አምላክ ላደረገልን ነገር አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. ሁላችንም ምን አጋጣሚ ተከፍቶልናል?

17 ሔዋን በኤደን ገነት ውስጥ ካለው ዛፍ ፍሬ በበላች ጊዜ በአባቷ ላይ ዓምፃለች። አዳምም ከእሷ ጋር ሲተባበር፣ ይሖዋ ላደረገለት ነገሮች ሁሉ ምንም ዓይነት አድናቆት እንደሌለው አሳይቷል። ሁላችንም አዳምና ሔዋን ያደረጉትን ውሳኔ ምን ያህል እንደምንቃወም የምናሳይበት አጋጣሚ ተከፍቶልናል። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ለእኛ መሥፈርት የማውጣት ሥልጣን ያለው ይሖዋ ነው፤ ራሳችንን ወስነን ስንጠመቅ ይህን አምነን እንደተቀበልን ለይሖዋ እናሳያለን። አባታችንን እንደምንወደውና እንደምንተማመንበት እናረጋግጣለን።

18. ይሖዋን በማገልገል ረገድ እንዲሳካልህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

18 ከተጠመቅን በኋላ በየዕለቱ በራሳችን ሳይሆን በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት አለብን፤ ይህ ደግሞ ተፈታታኝ እንደሆነ አይካድም። ሆኖም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ እያደረጉ ነው። አንተም የአምላክን ቃል በጥልቀት የምታጠና፣ ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር አዘውትረህ የምትሰበሰብ እንዲሁም አፍቃሪ ስለሆነው አባትህ የተማርከውን ነገር ለሌሎች በቅንዓት የምትሰብክ ከሆነ ልክ እንደ እነሱ በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ትችላለህ። (ዕብ. 10:24, 25) ውሳኔዎችን ስታደርግ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን ምክር ስማ። (ኢሳ. 30:21) እንዲህ ካደረግክ የምታከናውነው ነገር ሁሉ ይሳካልሃል።—ምሳሌ 16:3, 20

19. የትኛውን ሐቅ እየተገነዘብክ መሄድ ይኖርብሃል? ለምንስ?

19 የይሖዋን አመራር መከተልህ ምን ያህል እንደሚጠቅምህ እየተገነዘብክ ስትሄድ ለይሖዋም ሆነ እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች ያለህ ፍቅር ያድጋል። ይህም ሰይጣን በሚያቀርበው ማንኛውም ዓይነት ማታለያ እንዳትሸነፍና ይሖዋን ማገልገልህን እንዳታቆም ይረዳሃል። እስቲ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ሕይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ወደኋላ መለስ ብለህ ስታስብ በሕይወትህ ውስጥ ካደረግካቸው ውሳኔዎች ሁሉ የላቀው ለመጠመቅ ያደረግከው ውሳኔ እንደሆነ መረዳትህ አይቀርም!

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

^ አን.5 በሕይወትህ ውስጥ ከምታደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለመጠመቅ የምታደርገው ውሳኔ ነው። ይህ ውሳኔ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን። በተጨማሪም ለመጠመቅ እያሰቡ ያሉ ሰዎች ይህን ውሳኔ ከማድረግ ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት፦ አንድ ወጣት በጉባኤ ላይ ሐሳብ መስጠት ያስፈራዋል።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ ጓደኞች፦ መጥፎ ጓደኝነት የመሠረተች አንዲት ወጣት እህት፣ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ስታይ አፈረች።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ ስህተት እሠራለሁ የሚል ፍርሃት፦ አንዲት ወጣት፣ ወንድሟ ከጉባኤ ተወግዶ ከቤት ሲወጣ ስታይ ‘እኔም ስህተት ሠርቼ ልወገድ እችላለሁ’ የሚል ፍርሃት አደረባት።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ ተቃውሞ፦ አንድ ልጅ የማታምን እናቱ እያየችው መጸለይ ፈራ።

^ አን.65 የሥዕሉ መግለጫ፦ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት፦ አንድ ወጣት የግል ጥናቱ ይበልጥ ጥልቀት ያለው እንዲሆን አደረገ።

^ አን.67 የሥዕሉ መግለጫ፦ ጓደኞች፦ አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር በመሆኗ መኩራት እንዳለባት ተገነዘበች።

^ አን.69 የሥዕሉ መግለጫ፦ ስህተት እሠራለሁ የሚል ፍርሃት፦ አንዲት ወጣት እውነትን የራሷ አድርጋ ተጠመቀች።

^ አን.71 የሥዕሉ መግለጫ፦ ተቃውሞ፦ አንድ ልጅ፣ የይሖዋ ምሥክር ላልሆነች እናቱ ስለሚያምንበት ነገር በድፍረት አስረዳት።