በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ “አሜን” ለሚለው ቃል ትልቅ ቦታ ይሰጣል

ይሖዋ “አሜን” ለሚለው ቃል ትልቅ ቦታ ይሰጣል

ይሖዋ አምልኳችንን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። አገልጋዮቹን ‘በትኩረት ያዳምጣል’፤ ከዚህም በተጨማሪ እሱን ለማወደስ የምናደርገው ማንኛውም ነገር የቱንም ያህል ትንሽ ቢሆን በእሱ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው። (ሚል. 3:16) ለምሳሌ ያህል፣ ስፍር ቁጥር ለሌለው ጊዜ የተናገርነውን አንድ ቃል እንመልከት። ይህ ቃል “አሜን” የሚለው ቃል ነው። ለመሆኑ ይሖዋ ለዚህ አጭር አገላለጽ እንኳ፣ ትልቅ ቦታ ይሰጣል? እንዴታ! እንዲህ ያልንበትን ምክንያት ለማወቅ ቃሉ ምን ትርጉም እንዳለውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምን መንገድ እንደተሠራበት እንመልከት።

“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል”

“አሜን” የሚለው ቃል “ይሁን” ወይም “በእርግጥ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል “ታማኝ፣ እምነት የሚጣልበት” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ሥርወ ቃል የመጣ ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ ሕግ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል። አንድ ሰው መሐላ ከፈጸመ በኋላ “አሜን” ማለቱ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን እንዲሁም መሐላው የሚያስከትልበትን መዘዝ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን ያረጋግጣል። (ዘኁ. 5:22) ግለሰቡ ይህን ቃል የሚናገረው በሕዝብ ፊት ከሆነ ደግሞ ቃሉን የሚጠብቅበት ተጨማሪ ምክንያት ይኖረዋል።—ነህ. 5:13

በዘዳግም ምዕራፍ 27 ላይ “አሜን” የሚለው ቃል ትኩረት በሚስብ መንገድ ተሠርቶበታል። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ በኤባል ተራራና በገሪዛን ተራራ መካከል ተሰብስበው ሕጉ ሲነበብ እንዲሰሙ ታዘው ነበር። እስራኤላውያን በዚያ እንዲሰበሰቡ የታዘዙት፣ ለመስማት ብቻ ሳይሆን ሕጉን መቀበላቸውን ለመናገር ጭምር ነው። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ አለመታዘዝ የሚያስከትለው መዘዝ ሲነበብ “አሜን!” ብለው በመመለስ ነው። (ዘዳ. 27:15-26) በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች አንድ ላይ ጮክ ብለው ሲመልሱ የሚፈጠረውን አስገምጋሚ ድምፅ ለማሰብ ሞክር! (ኢያሱ 8:30-35) እነዚህ እስራኤላውያን በዚያን ዕለት የተናገሩትን ነገር ፈጽሞ እንደማይረሱት የተረጋገጠ ነው። ደግሞም የገቡትን ቃል ጠብቀዋል፤ ምክንያቱም ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያን ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከኢያሱ በኋላ በሕይወት በኖሩትና ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሲል ያደረገውን ነገር በሙሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ሁሉ ዘመን ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጠሉ።”—ኢያሱ 24:31

ኢየሱስም ቢሆን የተናገረውን ነገር እውነትነት ለማረጋገጥ “አሜን” የሚለውን ቃል ተጠቅሟል፤ ሆኖም ይህን ቃል የተጠቀመው ለየት ባለ መንገድ ነው። “አሜን” (በአማርኛ “እውነት” ተብሎ ተተርጉሟል) የሚለውን ቃል አንድ ሰው ለተናገረው ሐሳብ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን እሱ ራሱ አንድን ሐሳብ ከመናገሩ በፊት ሐሳቡ እውነት እንደሆነ ለማረጋገጥ ተጠቅሞበታል። አንዳንድ ጊዜ ቃሉን በመደጋገም “አሜን አሜን” ይል ነበር። (ማቴ. 5:18፤ ዮሐ. 1:51) በዚህ መንገድ፣ የተናገረው ነገር ፍጹም እውነት እንደሆነ ለአድማጮቹ አረጋግጧል። ኢየሱስ እንዲህ ባለ የእርግጠኝነት ስሜት ሊናገር የቻለው አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች ሁሉ እውን እንዲሆኑ የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው እሱ ስለሆነ ነው።—2 ቆሮ. 1:20፤ ራእይ 3:14

“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ አሉ፤ ይሖዋንም አወደሱ”

እስራኤላውያን ለይሖዋ ውዳሴ ወይም ጸሎት ሲያቀርቡም “አሜን” ይሉ ነበር። (ነህ. 8:6፤ መዝ. 41:13) ጸሎቱን የሚያዳምጡት ሰዎች መጨረሻ ላይ “አሜን” በማለት በጸሎቱ መስማማታቸውን ያሳያሉ። በቦታው የተገኙት ሁሉ በዚህ መንገድ ተሳትፎ ማድረጋቸው መንፈሳዊውን ዝግጅት ይበልጥ አስደሳች ያደርገዋል። ንጉሥ ዳዊት የይሖዋን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ ሲመጣ የተፈጠረውም ነገር ይኸው ነው። ታቦቱን ይዞ ከገባ በኋላ በተከበረው በዓል ላይ ዳዊት የመዝሙር ይዘት ያለው ልብ የሚነካ ጸሎት አቀረበ፤ ይህ ጸሎት በ1 ዜና መዋዕል 16:8-36 ላይ ይገኛል። በበዓሉ ላይ የተገኙት ሁሉ በጸሎቱ ልባቸው በጥልቅ ስለተነካ “‘አሜን!’ አሉ፤ ይሖዋንም አወደሱ።” አዎ፣ እነዚህ ሰዎች በአንድነት የሰጡት ምላሽ ሥነ ሥርዓቱ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን አድርጓል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም ይሖዋን ሲያወድሱ “አሜን” የሚለውን ቃል ይጠቀሙ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በተደጋጋሚ ይህን ቃል በደብዳቤያቸው ውስጥ አካተውታል። (ሮም 1:25፤ 16:27፤ 1 ጴጥ. 4:11) የራእይ መጽሐፍ በሰማይ ያሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንኳ “አሜን! ያህን አወድሱ!” በማለት ይሖዋን እንዳከበሩ ይገልጻል። (ራእይ 19:1, 4) በጥንት ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በስብሰባዎቻቸው ላይ ጸሎት ከቀረበ በኋላ “አሜን” የማለት ልማድ ነበራቸው። (1 ቆሮ. 14:16) ሆኖም ይህን ቃል እንዲሁ በዘልማድ ሊደጋግሙት አይገባም ነበር።

“አሜን” ማለታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በጥንት ዘመን የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች “አሜን” የሚለውን ቃል የተጠቀሙበት እንዴት እንደሆነ ማወቃችን በጸሎታችን መደምደሚያ ላይ ይህን ቃል መጠቀማችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝበናል። በግል በምናቀርበው ጸሎት መጨረሻ ላይ “አሜን” ማለታችን የተናገርነውን ነገር ከልብ እንደምናምንበት ይጠቁማል። በሕዝብ ፊት ለቀረበ ጸሎት በልባችንም ሆነ ጮክ ብለን “አሜን” ማለታችን ደግሞ በጸሎቱ ላይ የተገለጹትን ሐሳቦች እንደምንደግፍ ያሳያል። ይህን ቃል መጠቀማችን አስፈላጊ የሆነባቸውን ሌሎች ምክንያቶችም መጥቀስ እንችላለን።

ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር በተያያዘ ንቁ እንደሆንን ያሳያል። በጸሎት አማካኝነት ለይሖዋ አምልኮ የምናቀርበው ከጸሎት በኋላ በምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን በጸሎት ወቅት በምናሳየው ምግባር ጭምር ነው። “አሜን” በማለት የምንናገረው ቃል ከልባችን የመነጨ እንዲሆን ያለን ፍላጎት፣ ጸሎት በሚቀርብበት ጊዜ ትክክለኛ ምግባር እንድናሳይና ጸሎቱን ትኩረት ሰጥተን እንድናዳምጥ ያነሳሳናል።

ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ አንድ እንድንሆን ያደርጋል። በጉባኤ ውስጥ ጸሎት ሲቀርብ ሁላችንም ተመሳሳይ መልእክት እንሰማለን። (ሥራ 1:14፤ 12:5) ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አንድ ላይ ሆነን ለጸሎቱ ምላሽ ስንሰጥ በመካከላችን ያለው አንድነት ይበልጥ ይጠናከራል። ይሖዋ በልባችንም ሆነ ጮክ ብለን የተናገርነውን “አሜን” የሚለውን ቃል ሲሰማ፣ በጋራ ላቀረብነው ልመና መልስ ለመስጠት ሊነሳሳ ይችላል።

እያንዳንዳችን የምንናገረው “አሜን” የሚለው ቃል ለይሖዋ ለሚቀርበው ውዳሴ አስተዋጽኦ ያደርጋል

ይሖዋን የምናወድስበት አጋጣሚ ይሰጠናል። ይሖዋ ከእሱ አምልኮ ጋር በተያያዘ የምናደርገውን ትንሹን ነገር እንኳ ትኩረት ሰጥቶ ያያል። (ሉቃስ 21:2, 3) ከድርጊታችን በስተጀርባ ያለውን ምክንያትና በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ይመለከታል። አንዳንድ ጊዜ፣ ባለንበት ሁኔታ ምክንያት ስብሰባዎችን በስልክ ለማዳመጥ እንገደድ ይሆናል፤ ይሖዋ በዚህ ጊዜም እንኳ “አሜን” በማለት የምንሰጠውን መልስ በትኩረት እንደሚያዳምጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። “አሜን” ማለታችን በስብሰባው ላይ ከተገኙት ጋር በኅብረት ይሖዋን እንድናወድስ ያስችለናል።

“አሜን” የሚለው ቃል ያን ያህል ዋጋ ያለው አይመስል ይሆናል፤ እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እንደተገለጸው፣ የአምላክ አገልጋዮች “በዚህ አንድ ቃል አማካኝነት በልባቸው ውስጥ ያለውን የመተማመን ስሜት፣ ጠንካራ ድጋፍና ጽኑ ተስፋ መግለጽ ይችላሉ።” እንግዲያው ከአንደበታችን የሚወጣው እያንዳንዱ “አሜን” የሚለው ቃል ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ምኞታችን ነው።—መዝ. 19:14