በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በጥንት ዘመን የነበረ አንድ መንገደኛ የሚሳፈርበት መርከብ የሚያገኘው እንዴት ነበር?

በጥቅሉ ሲታይ ጳውሎስ በኖረበት ዘመን ለመንገደኞች ብቻ ተብለው የተዘጋጁ መርከቦች አልነበሩም። አብዛኛውን ጊዜ መንገደኞች፣ ወደሚፈልጉበት አቅጣጫ የሚሄድና ሰዎችን ለማሳፈር ፈቃደኛ የሆነ የንግድ (የጭነት) መርከብ የሚያገኙት ሰዎችን በማጠያየቅ ነበር። (ሥራ 21:2, 3) በዚህ መልኩ የተገኘው መርከብ መንገደኛውን ወደፈለገው ቦታ ባያደርሰውም እንኳ መርከቡ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲቆም መንገደኛው ወርዶ ሌላ መርከብ መፈለግ ይችል ነበር።—ሥራ 27:1-6

በአብዛኛው የባሕር ጉዞ የሚደረገው በዓመት ውስጥ በተወሰኑ ወቅቶች ላይ ብቻ የነበረ ከመሆኑም ሌላ መርከበኞቹ ከሚነሱበትና ከሚደርሱበት ጊዜ ጋር በተያያዘ ጥብቅ የሆነ ፕሮግራም አይከተሉም። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ የአየሩ ጠባይ ተስማሚ ላይሆን ስለሚችል ነው። በተጨማሪም አጉል እምነት ያላቸው መርከበኞች፣ መጥፎ ገድ ናቸው ብለው በሚቆጥሯቸው አንዳንድ ነገሮች የተነሳ ጉዟቸውን ያዘገዩ ነበር፤ ለምሳሌ በመርከቡ ምሰሶ ላይ ከታሰሩት ገመዶች መካከል በአንዱ ላይ ቁራ ካረፈ ወይም በባሕሩ ዳርቻ የመርከብ ስብርባሪ ካዩ ጉዞ አይጀምሩም። መርከበኞቹ ተስማሚ ነፋስ የሚኖርበትን ጊዜ ጠብቀው ለጉዞ ይነሳሉ። አንድ መንገደኛ፣ የሚሳፈርበት መርከብ ካገኘ በኋላ ጓዙን ይዞ ወደ ወደቡ አቅራቢያ በመሄድ መርከቡ ለጉዞ የሚነሳበት ጊዜ እስኪታወጅ ይጠብቃል።

የታሪክ ምሁር የሆኑት ላየነል ካሰን እንዲህ ብለዋል፦ “ሮም፣ መንገደኞች መርከብ ለመፈለግ ሲሉ በየወደቡ እንዳይንከራተቱ የሚረዳ አመቺ አገልግሎት አቅርባ ነበር። ወደቧ የሚገኘው በታይበር ወንዝ አካባቢ ነበር። በዚህ ወንዝ አቅራቢያ ባለችው በኦስቲያ ከተማ፣ ዙሪያውን በርካታ ቢሮዎች የሚገኙበት አንድ ትልቅ አደባባይ ነበር። ከእነዚህ ቢሮዎች መካከል ብዙዎቹ ከተለያዩ የባሕር ወደቦች የሚነሱ መርከበኞችን የሚወክሉ ነበሩ፦ የናርቦን [የአሁኗ ፈረንሳይ]፣ የካርቴጅ [የአሁኗ ቱኒዝያ] . . . እንዲሁም የሌሎች ከተሞች መርከበኞች የየራሳቸው ቢሮ ነበራቸው። በመሆኑም የሚሳፈርበት መርከብ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በጉዞው መስመር ላይ ያሉትን ከተሞች ወደሚወክሉ ቢሮዎች ሄዶ በመጠየቅ ብቻ የሚያስፈልገውን መረጃ ማግኘት ይችላል።”

የባሕር ጉዞ ለመንገደኞች ጊዜ ይቆጥብላቸው የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ነበሩት። ለምሳሌ ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞዎቹ ላይ በተደጋጋሚ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞታል።—2 ቆሮ. 11:25