በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሰይጣን ወጥመድ አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘት

ከሰይጣን ወጥመድ አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘት

የጥንቶቹ እስራኤላውያን አምላክ ቃል ወደገባላቸው ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሊሻገሩ እየተዘጋጁ በነበሩበት ወቅት አንዳንድ እንግዶች ወደ ሰፈራቸው መጡ። እንግዶቹ፣ ወዳዘጋጁት ድግስ እስራኤላውያን ወንዶችን ለመጋበዝ የመጡ ባዕድ ሴቶች ነበሩ። ይህ ግብዣ በሌላ ጊዜ የማይገኝ ግሩም አጋጣሚ ይመስል ነበር። አዳዲስ ወዳጆችን ማፍራት፣ መጨፈርና ጥሩ ምግብ መመገብ ለእስራኤላውያኑ በጣም አጓጊ ሊሆን ይችላል። የጋባዦቹ ባሕልና ሥነ ምግባር አምላክ ለእስራኤል ከሰጠው መመሪያ ጋር የማይጣጣም ቢሆንም አንዳንዶቹ እስራኤላውያን ወንዶች ‘ምንም አንሆንም፤ እንጠነቀቃለን’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል።

ታዲያ ምን ሆነ? በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ “ሕዝቡ ከሞዓብ ሴቶች ጋር የፆታ ብልግና መፈጸም ጀመረ” በማለት ይነግረናል። እንደ እውነቱ ከሆነ የሴቶቹ ዓላማ እስራኤላውያን ወንዶች የሐሰት አማልክትን እንዲያመልኩ ማድረግ ነበር። ደግሞም ተሳክቶላቸዋል! ይሖዋ “በእስራኤል ላይ እጅግ [መቆጣቱ]” አያስገርምም።—ዘኁ. 25:1-3

እነዚያ እስራኤላውያን በሁለት መንገዶች የአምላክን ሕግ ጥሰዋል፦ ለጣዖታት ሰግደዋል፤ እንዲሁም የፆታ ብልግና ፈጽመዋል። አምላክን ባለመታዘዛቸው የተነሳ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞቱ። (ዘፀ. 20:4, 5, 14፤ ዘዳ. 13:6-9) ሁኔታውን ይበልጥ አሳዛኝ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ወቅቱ ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት እነዚያ እስራኤላውያን በዚያ ወቅት የአምላክን ሕግ ባይጥሱ ኖሮ፣ ብዙም ሳይቆይ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት በቻሉ ነበር።—ዘኁ. 25:5, 9

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ሲጽፍ “እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ በእነሱ ላይ ደረሱ፤ የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 10:7-11) በዚያን ጊዜ ከነበሩት እስራኤላውያን መካከል አንዳንዶቹ ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸውና ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ሳይበቁ በመቅረታቸው ሰይጣን በጣም እንደተደሰተ ጥርጥር የለውም። በእርግጥም ይህን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለታችን የጥበብ አካሄድ ነው! ምክንያቱም ሰይጣን ወደ አምላክ አዲስ ዓለም እንዳንገባ ከማድረግ የበለጠ የሚያስደስተው ነገር እንደሌለ እናውቃለን።

አደገኛ ወጥመድ

ሰይጣን በደንብ የተካነባቸውንና በብዙ ሰዎች ላይ ውጤታማ ሆነው ያገኛቸውን ዘዴዎች በመጠቀም ክርስቲያኖችን ለማጥመድ ያደባል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሰይጣን እስራኤላውያንን ለማጥመድ የተጠቀመው በፆታ ብልግና ነው። በእኛም ዘመን የፆታ ብልግና አደገኛ ወጥመድ ሆኖ ቀጥሏል። ሰይጣን በዚህ ወጥመድ እንድንወድቅ ለማድረግ በብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ይጠቀማል።

በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው፣ ሌሎች ሳያውቁ የብልግና ምስሎችን ማየት ይችላል። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት፣ የብልግና ምስሎች ማየት የፈለገ ሰው ተገቢ ያልሆኑ ፊልሞችን ለማየት ወደ ሲኒማ ቤቶች ወይም እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች ወደሚሸጡባቸው ሱቆች መሄድ ይኖርበት ነበር። እንደዚህ ባሉት ቦታዎች ወይም በአቅራቢያቸውም እንኳ መታየት አሳፋሪ ነገር ስለነበረ ብዙዎች ወደዚያ መሄድ ይፈሩ ነበር። አሁን ግን ኢንተርኔት ማግኘት የሚችል ማንኛውም ሰው፣ በሥራ ቦታው አሊያም በቆመ መኪና ውስጥ ሆኖም እንኳ የብልግና ምስሎችን መመልከት ይችላል። ደግሞም በብዙ አገሮች አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ከቤታቸው እንኳ መውጣት ሳያስፈልጋቸው የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ማግኘት ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ሞባይል ስልኮችና ታብሌቶች የብልግና ምስሎችን መመልከት ቀላል እንዲሆን አድርገዋል። ሰዎች በመንገድ ላይ በእግራቸው ሲሄዱ ወይም በአውቶብሶችና በባቡሮች ውስጥ ሆነው፣ በእጃቸው በያዙት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ የብልግና ምስሎችን መመልከት ይችላሉ።

የብልግና ምስሎችን መመልከትና ድርጊቱን ሌሎች እንዳያውቁ ማድረግ ቀላል መሆኑ፣ ከቀድሞው የበለጠ በጣም ብዙ ሰዎች በዚህ ወጥመድ እንዲወድቁ አድርጓል። እንዲህ ያሉ ምስሎችን የሚመለከቱ በርካታ ሰዎች ትዳራቸው ተናግቷል፤ ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት አጥተዋል፤ እንዲሁም ሕሊናቸው ቆሽሿል። ከዚህ የከፋው ደግሞ ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና መበላሸቱ ነው። የብልግና ምስሎችን የሚመለከት ሰው ራሱን እንደሚጎዳ ጥያቄ የለውም። እንዲህ ያለው ድርጊት ብዙውን ጊዜ ከባድ ጉዳት ያስከትላል። ጉዳቱን ለማስተካከል ረጅም ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም ሌላ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ሊሄድ ይችላል።

ይሁንና ይሖዋ ከዚህ ሰይጣናዊ ወጥመድ ጥበቃ እንደሚያደርግልን ቃል ገብቷል። የይሖዋን ጥበቃ ማግኘት ከፈለግን ደግሞ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ሳያደርጉ የቀሩትን ነገር ማድረግ፣ ይኸውም እሱን ‘በጥብቅ መታዘዝ’ አለብን። (ዘፀ. 19:5) አምላክ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን አጥብቆ እንደሚጠላ አምነን መቀበል ያስፈልገናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

አንተም እንደ ይሖዋ የብልግና ምስሎችን ተጸየፍ

አምላክ ለእስራኤል ብሔር የሰጣቸው ሕጎች፣ በጥንቱ ዓለም ከነበሩ ሌሎች ብሔራት ሕጎች በጣም የተለዩ እንደነበሩ እናስታውስ። እነዚህ ሕጎች ልክ እንደ አጥር በመሆን፣ እስራኤላውያንን በዙሪያቸው የሚኖሩት ሕዝቦች ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንዲሁም እነዚህ ሕዝቦች ከነበሯቸው ወራዳ ልማዶች ጠብቀዋቸዋል። (ዘዳ. 4:6-8) ሕጎቹ አንድን ወሳኝ እውነት ይኸውም ይሖዋ የፆታ ብልግናን እንደሚጠላ በግልጽ አሳይተዋል።

ይሖዋ፣ በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት ስለሚፈጽሙት አስጸያፊ ድርጊት ለእስራኤላውያን ሲናገር እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እኔ በማስገባችሁ በከነአን ምድር ያሉ ሰዎች [እንደሚያደርጉት] አታድርጉ። . . . ምድሪቱ ረክሳለች፤ እኔም ለሠራችው ስህተት ቅጣት አመጣባታለሁ።” ቅዱስ የሆነው የእስራኤል አምላክ፣ የከነአናውያን አኗኗር እጅግ የረከሰ ከመሆኑ የተነሳ ይኖሩባት የነበረችው ምድርም እንደረከሰችና እንደተበከለች ተሰምቶት ነበር።—ዘሌ. 18:3, 25

ይሖዋ ከነአናውያንን ቢቀጣቸውም እንኳ የፆታ ብልግና መፈጸማቸውን የቀጠሉ ሌሎች ሕዝቦች ነበሩ። ከ1,500 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በሚኖሩባቸው ቦታዎች ያሉት ሕዝቦች “የሥነ ምግባር ስሜታቸው [የደነዘዘ]” እንደሆኑ ገልጿል። እንዲያውም “በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ዓይን ላወጣ ምግባር አሳልፈው ሰጥተዋል” በማለት ተናግሯል። (ኤፌ. 4:17-19) በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ዓይን ያወጣ ብልግና የሚፈጽሙ ሲሆን በዚህም ኀፍረት አይሰማቸውም። የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎችን የብልግና ድርጊት ከመመልከት ለመቆጠብ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው።

የብልግና ምስልና ጽሑፍ፣ አምላክን የሚያቃልል ነገር ነው። አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በራሱ መልክና አምሳል ነው፤ ጨዋነት የጎደለው ምግባር የትኛው እንደሆነ ማስተዋል እንድንችል አድርጎ ፈጥሮናል። ጠቢብ የሆነው አምላክ የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ምክንያታዊ ገደቦችን አስቀምጧል። የፆታ ግንኙነትን የፈጠረበት ዓላማ ባለትዳሮች አግባብነት ባለው መልኩ እንዲደሰቱበት ነው። (ዘፍ. 1:26-28፤ ምሳሌ 5:18, 19) ሆኖም የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን የሚያዘጋጁትም ሆኑ እንደ ጥሩ መዝናኛ አድርገው የሚያቀርቡት ሰዎች ምን እያደረጉ ነው? ለአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከፍተኛ ንቀት እያሳዩ ነው። በእርግጥም እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ይሖዋን እያቃለሉ ነው። አምላክ ደግሞ የእሱን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በመጣስ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን በሚያዘጋጁ ወይም በሚያስፋፉ ሰዎች ላይ ይፈርዳል።—ሮም 1:24-27

ይሁንና ሆን ብለው የብልግና ምስሎችን የሚመለከቱ ወይም የብልግና ጽሑፎችን የሚያነቡ ሰዎችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? አንዳንዶች እንዲህ ያሉት ነገሮች ጉዳት የሌላቸው መዝናኛዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች፣ የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚንቁ ግለሰቦችን እየደገፉ ነው። የብልግና ምስሎችን መመልከት የጀመሩት ይህን አስበው ላይሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን አጥብቀው መጥላት እንዳለባቸው ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ” በማለት በጥብቅ ያሳስባል።—መዝ. 97:10

እርግጥ ነው፣ የብልግና ምስሎች ከማየት መቆጠብ የሚፈልጉ ሰዎችም ጭምር ይህን ማድረግ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ርኩስ የሆኑ ፆታዊ ፍላጎቶችን ለመቋቋም መታገል ሊኖርብን ይችላል። ከዚህም በላይ ፍጹም ያልሆነው ልባችን የአምላክን ሕግ ገሸሽ ለማድረግ ሰበብ ይፈላልግ ይሆናል። (ኤር. 17:9) ይሁንና ክርስቲያን የሆኑ ብዙ ሰዎች በዚህ ትግል ማሸነፍ ችለዋል። አንተም ተመሳሳይ ትግል ካለብህ በትግሉ ያሸነፉ ሰዎች መኖራቸውን ማወቅህ ሊያበረታታህ ይችላል። ሰይጣን በሚጠቀምበት፣ የብልግና ምስሎችን የመመልከት ወጥመድ እንዳትያዝ የአምላክ ቃል የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

በብልግና ምኞቶች ላይ አታውጠንጥን

ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ብዙ እስራኤላውያን ለጥፋት የተዳረጉት መጥፎ ምኞት በውስጣቸው እንዲያድግ ስለፈቀዱ ነው። በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥም ይችላል። የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ አደጋውን እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች።” (ያዕ. 1:14, 15) አንድ ሰው ተገቢ ያልሆነ የፆታ ምኞት በልቡ ውስጥ እንዲያድግ ከፈቀደ ውሎ አድሮ ግለሰቡ ኃጢአት መሥራቱ አይቀርም። በመሆኑም የብልግና ሐሳቦችን ከውስጣችን ማውጣት እንጂ በእነሱ ላይ ማውጠንጠን የለብንም።

ርኩስ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እየመጡ ካስቸገሩህ አፋጣኝ እርምጃ ውሰድ። ኢየሱስ “እጅህ ወይም እግርህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው። . . . እንዲሁም ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው” ብሏል። (ማቴ. 18:8, 9) ኢየሱስ የተናገረው፣ ቃል በቃል እጅን ወይም እግርን ስለ መቁረጥና ዓይንን አውጥቶ ስለ መጣል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚያሰናክለንን ነገር በአፋጣኝና በቆራጥነት ማስወገድ እንደሚያስፈልግ በምሳሌ መግለጹ ነበር። ታዲያ ከብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ጋር በተያያዘ ይህን ምክር ሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

የብልግና ምስሎች ድንገት ካጋጠሙህ ‘ምንም አልሆንም’ ብለህ አታስብ። ወዲያውኑ ፊትህን አዙር። በፍጥነት ቴሌቪዥኑን አጥፋው። ኮምፒውተርህን ወይም ሞባይል ስልክህንም ቢሆን በአፋጣኝ ዝጋው። ትኩረትህን ቀይረህ፣ ንጹሕ ስለሆነ ነገር አስብ። እንዲህ ማድረግህ መጥፎ ምኞቶች እንዲቆጣጠሩህ ከመፍቀድ ይልቅ ሐሳብህን ለመቆጣጠር ይረዳሃል።

ቀደም ሲል ያየሃቸው የብልግና ምስሎች ትዝ እያሉህ ብትቸገርስ?

የብልግና ምስሎችን መመልከትህን ለማቆም ቢሳካልህም ቀደም ሲል ያየሃቸው ነገሮች አንዳንድ ጊዜ ትዝ የሚሉህ ቢሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? የብልግና ምስሎችና ሐሳቦች ከአንድ ሰው አእምሮ ሳይጠፉ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ። ደግሞም በድንገት ብቅ እያሉ ያስቸግሩህ ይሆናል። በዚህም የተነሳ፣ እንደ ማስተርቤሽን ያለ ርኩስ ነገር ለመፈጸም ትፈተን ይሆናል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቶቹ ሐሳቦች በድንገት ሊመጡብህ እንደሚችሉ በመገንዘብ በእነሱ ላለመሸነፍ ራስህን አዘጋጅ።

አስተሳሰብህንም ሆነ ድርጊትህን ለአምላክ ፈቃድ ለማስገዛት ያለህን ቁርጠኝነት አጠናክር። ‘ሰውነቱን እየጎሰመ እንደ ባሪያ እንዲገዛለት ያደረገውን’ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርግ። (1 ቆሮ. 9:27) ርኩስ ምኞቶች ባሪያ እንዲያደርጉህ አትፍቀድላቸው። ከዚህ ይልቅ ‘ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምረህ ማረጋገጥ ትችል ዘንድ አእምሮህን በማደስ ተለወጥ።’ (ሮም 12:2) እጅግ የላቀ እርካታ የሚያስገኘው፣ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ አስተሳሰብና ተግባር እንጂ ለኃጢአት ምኞቶች መገዛት እንዳልሆነ መዘንጋት የለብህም።

እጅግ የላቀ እርካታ የሚያስገኘው፣ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ አስተሳሰብና ተግባር እንጂ ለኃጢአት ምኞቶች መገዛት አይደለም

በዚህ ረገድ ሊረዱህ የሚችሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃልህ ለማጥናት ሞክር። ከዚያም መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ ሲመጡ ስለ እነዚህ ጥቅሶች ለማሰብ ራስህን አስገድድ። እንደ መዝሙር 119:37፤ ኢሳይያስ 52:11፤ ማቴዎስ 5:28፤ ኤፌሶን 5:3፤ ቆላስይስ 3:5 እና 1 ተሰሎንቄ 4:4-8 ያሉት ጥቅሶች፣ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንድታዳብርና እሱ ከአንተ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ እንድትገነዘብ ይረዱሃል።

የብልግና ምስሎችን የመመልከት ወይም እንደነዚህ ስላሉ ነገሮች የማሰብ ምኞትህን መቋቋም ከአቅምህ በላይ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ ምን ማድረግ ትችላለህ? አርዓያችን የሆነውን የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ ተከተል። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ሰይጣን በተደጋጋሚ ፈትኖት ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? ሰይጣንን መቃወሙን አላቋረጠም። ኢየሱስ የተለያዩ ጥቅሶችን በመጠቀም፣ ሰይጣን ያቀረበለትን ፈተና ተቋቁሟል። “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” ያለው ሲሆን ሰይጣንም ትቶት ሄዷል። ኢየሱስ ለሰይጣን ፈተና ፈጽሞ እጅ እንዳልሰጠ ሁሉ አንተም ብትሆን ፈጽሞ እጅ መስጠት የለብህም። (ማቴ. 4:1-11) ሰይጣንና የእሱ ዓለም አእምሮህን በብልግና ሐሳቦች ለመሙላት መጣራቸውን ይቀጥላሉ፤ አንተ ግን በትግልህ ግፋበት እንጂ ፈጽሞ እጅ አትስጥ። የብልግና ምስሎችን በመመልከት ወጥመድ ላለመውደቅ የምታደርገውን ትግል በድል መወጣት ትችላለህ። በይሖዋ እርዳታ ጠላትህን ማሸነፍ ትችላለህ።

ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ ታዘዘውም

ይሖዋ እንዲረዳህ ወደ እሱ አዘውትረህ ጸልይ። ጳውሎስ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” ብሏል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ከኃጢአት ጋር በምታደርገው ውጊያ ማሸነፍ እንድትችል አምላክ የአእምሮ ሰላም ይሰጥሃል። ወደ ይሖዋ የምትቀርብ ከሆነ ‘እሱም ወደ አንተ ይቀርባል።’—ያዕ. 4:8

ከየትኛውም የሰይጣን ጥቃት የሚከላከል ከሁሉ የተሻለ ጥበቃ የምናገኘው ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ጋር ጠንካራ ዝምድና በመመሥረት ነው። ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ [ሰይጣን] እየመጣ” መሆኑን ከገለጸ በኋላ “እሱም በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም” ብሏል። (ዮሐ. 14:30) ኢየሱስ የዚህን ያህል እርግጠኛ መሆን የቻለው ለምንድን ነው? “እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም” በማለት በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 8:29) አንተም ይሖዋን ደስ የሚያሰኘውን የምታደርግ ከሆነ እሱ ፈጽሞ አይተውህም። ስለዚህ የብልግና ምስሎችን በመመልከት ወጥመድ ላለመውደቅ ተጠንቀቅ፤ እንዲህ ካደረግህ የሰይጣን ወጥመድ ሰለባ አትሆንም።