በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 29

“ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

“ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

“ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።”—ማቴ. 28:19

መዝሙር 60 ስብከታችን ሰው ያድናል

የትምህርቱ ዓላማ *

1-2. (ሀ) ኢየሱስ በማቴዎስ 28:18-20 ላይ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የክርስቲያን ጉባኤ ዋነኛ ተልእኮ ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ሐዋርያቱ በአንድ ተራራ ላይ ተሰብስበዋል፤ በወቅቱ ልባቸው በጉጉት ተሞልቶ መሆን አለበት። ኢየሱስ በዚህ ተራራ ላይ ከእሱ ጋር እንዲገናኙ ከሞት ከተነሳ በኋላ ነግሯቸው ነበር። (ማቴ. 28:16) “በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች” የታየውም በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮ. 15:6) ኢየሱስ በዚህ ቦታ እንዲሰበሰቡ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ለምንድን ነው? “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን አስደሳች ተልእኮ ሊሰጣቸው ስለፈለገ ነው።ማቴዎስ 28:18-20ን አንብብ።

2 ኢየሱስ ይህን ተልእኮ ሲሰጥ የሰሙት ደቀ መዛሙርት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ሆነዋል። የዚያ ጉባኤ ዋነኛ ተልእኮ ደግሞ ተጨማሪ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማፍራት ነበር። * በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ እውነተኛ የክርስቲያን ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን የእነዚህ ጉባኤዎች ዋነኛ ተልእኮም አልተለወጠም። በዚህ ርዕስ ላይ የሚከተሉትን አራት ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ ደቀ መዛሙርት ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ ሥራ ምን ማድረግ ይጠይቃል? ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሁሉም ክርስቲያኖች ድርሻ አላቸው? ይህ ሥራ ትዕግሥት የሚጠይቀው ለምንድን ነው?

ደቀ መዛሙርት ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3. በዮሐንስ 14:6 እና 17:3 መሠረት ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ደቀ መዛሙርት ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰዎች የአምላክ ወዳጆች መሆን የሚችሉት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከሆኑ ብቻ ነው። በተጨማሪም የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት የሚመሩ ከመሆኑም ሌላ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። (ዮሐንስ 14:6⁠ን እና 17:3ን አንብብ።) በእርግጥም ኢየሱስ በአደራ የሰጠን ኃላፊነት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ይህን ሥራ የምናከናውነው ብቻችንን አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱና አብረውት ስለሚያገለግሉ አንዳንድ ወዳጆቹ ሲናገር “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:9) ይሖዋና ክርስቶስ ፍጹም ላልሆኑ ሰዎች የሰጡት ይህ መብት ምንኛ ውድ ነው!

4. ኢቫን እና ማቲልዴ ካጋጠማቸው ሁኔታ ምን እንማራለን?

4 ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል። በኮሎምቢያ የሚኖሩት ኢቫን እና ማቲልዴ የተባሉ ባልና ሚስት ያጋጠማቸውን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት ዳቪየር ለተባለ አንድ ወጣት መሠከሩ፤ ዳቪየር “ሕይወቴን ማስተካከል ብፈልግም ይህን ማድረግ አልቻልኩም” አላቸው። ዳቪየር ቦክሰኛ ሲሆን ዕፅ ይወስድና ከልክ በላይ ይጠጣ ነበር፤ በወቅቱ የሚኖረው ኤሪካ ከተባለች የሴት ጓደኛው ጋር ነበር። ኢቫን እንዲህ ብሏል፦ “ዳቪየርን ቤቱ እየሄድን ማስጠናት ጀመርን፤ የሚኖረው ርቆ በሚገኝ መንደር ውስጥ ስለነበር በጭቃ መንገድ ላይ ለረጅም ሰዓታት በብስክሌት መጓዝ ነበረብን። ኤሪካ የዳቪየር ባሕርይ እና አመለካከት እየተለወጠ መሆኑን ስትመለከት አብራው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች።” ውሎ አድሮ ዳቪየር ዕፅ መውሰዱን፣ መጠጣቱንና በቦክስ ስፖርት መካፈሉን አቆመ። ከኤሪካ ጋርም ተጋቡ። ማቲልዴ እንዲህ ብላለች፦ “በ2016 ዳቪየርና ኤሪካ ሲጠመቁ፣ ዳቪየር ‘ሕይወቴን ማስተካከል ብፈልግም ይህን ማድረግ አልቻልኩም’ ይለን የነበረው ትዝ አለን። እንባችንን መቆጣጠር አቃተን።” ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ስንረዳ ወደር የሌለው ደስታ እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም።

ደቀ መዛሙርት ማድረግ ምን ይጠይቃል?

5. ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ልንወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ምንድን ነው?

5 ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ልንወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ‘መፈለግ’ ነው። (ማቴ. 10:11) ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ የምንመሠክር ከሆነ እውነተኛ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን እናሳያለን። ክርስቶስ እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ የምናከብር ከሆነም እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን እናሳያለን።

6. በአገልግሎታችን ስኬታማ ለመሆን ምን ይረዳናል?

6 አንዳንድ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች የመማር ጉጉት አላቸው፤ በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ብዙዎቹ ሰዎች ግን መጀመሪያ ላይ ያን ያህል ፍላጎት ያላቸው አይመስሉ ይሆናል። ስለዚህ ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ ጥረት ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። በአገልግሎታችን ስኬታማ ለመሆን በሚገባ መዘጋጀት ያስፈልገናል። የምታገኛቸውን ሰዎች ሊማርኩ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ምረጥ። ከዚያም ምን መግቢያ እንደምትጠቀም ተዘጋጅ።

7. ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመር ምን ማለት ትችላለህ? ሰዎቹን ማዳመጥህና ለእነሱ አክብሮት ማሳየትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ለምሳሌ ያህል፣ የቤቱን ባለቤት እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ፦ “ስለ አንድ ጉዳይ ያለህን አመለካከት ልጠይቅህ ፈልጌ ነበር። በዛሬው ጊዜ ብዙ ችግሮች ያጋጥሙናል። እነዚህን ችግሮች ሊያስወግድ የሚችል መንግሥት ሊኖር የሚችል ይመስልሃል?” ከዚያም ዳንኤል 2:44⁠ን ጠቅሰህ ልታብራራለት ትችላለህ። አሊያም ደግሞ የምታነጋግረውን ሰው “ጨዋ ልጆችን ለማሳደግ ሚስጥሩ ምን ይመስልሃል?” ልትለው ትችላለህ። ከዚያም ዘዳግም 6:6, 7⁠ን ጠቅሰህ አብራራለት። ለመወያየት የመረጥከው ርዕስ ምንም ይሁን ምን፣ መልእክቱን ስለምትነግራቸው ሰዎች አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማወቃቸው እንዴት እንደሚጠቅማቸው ለማሰብ ሞክር። ከሰዎቹ ጋር ስትወያይ እነሱን ማዳመጥህና አመለካከታቸውን ማክበርህ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረግህ የእነሱን አመለካከት ይበልጥ ለመረዳት ያስችልሃል፤ እነሱም አንተን ለማዳመጥ ይበልጥ ይነሳሳሉ።

8. ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ያላሰለሰ ጥረት የሚጠይቀው ለምንድን ነው?

8 አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ እስኪሆን ድረስ በተደጋጋሚ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ወደ ሰዎች ቤት ተመልሰን ስንሄድ ላናገኛቸው እንችላለን። በተጨማሪም የቤቱ ባለቤት ከአንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ የሚሆነው በተደጋጋሚ ተገናኝታችሁ ከለመደህ በኋላ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ተክል እንዲያድግ አዘውትሮ ውኃ መጠጣት ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም፣ ፍላጎት ያሳየ አንድ ሰው ለይሖዋና ለክርስቶስ ያለው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ስለ አምላክ ቃል አዘውትረን ልናወያየው ይገባል።

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሁሉም ክርስቲያኖች ድርሻ አላቸው?

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መልእክቱን መስማት የሚገባቸውን ሰዎች በመፈለጉ ሥራ ይካፈላሉ (ከአንቀጽ 9-10⁠ን ተመልከት) *

9-10. ሁሉም ክርስቲያኖች ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ በማግኘቱ ሥራ ድርሻ አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?

9 ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ በማግኘቱ ሥራ ሁሉም ክርስቲያኖች ድርሻ አላቸው። ይህን ሥራ፣ የጠፋን ልጅ ፈልጎ ከማግኘት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። እንዴት? አንድን እውነተኛ ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጠፍቶ የነበረ አንድ የሦስት ዓመት ልጅን ለማግኘት 500 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተሰማርተው ነበር። ልጁ ከጠፋ ከ20 ሰዓታት ገደማ በኋላ፣ ለፍለጋ ከተሰማሩት ሰዎች አንዱ ልጁን በበቆሎ እርሻ ውስጥ አገኘው። ይህ ሰው ልጁን በማግኘቱ የተለየ ምስጋና እንደሚገባው አልተሰማውም። “ልጁ የተገኘው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ባደረጉት ጥረት ነው” በማለት ተናግሯል።

10 ብዙ ሰዎች ልክ እንደዚህ ልጅ ናቸው። ተስፋ የሚያደርጉት ነገር ስለሌላቸው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ኤፌ. 2:12) እንደነዚህ ያሉትን መልእክቱን መስማት የሚገባቸው ሰዎች ለማግኘት ከስምንት ሚሊዮን የምንበልጥ ክርስቲያኖች ተሰማርተናል። አንተ በግልህ መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ፍላጎት ያለው ሰው ፈልገህ አጥተህ ይሆናል። ይሁንና በዚያው ክልል ውስጥ የሚሰብኩ ሌሎች አስፋፊዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት መማር የሚፈልግ ሰው ሊያገኙ ይችላሉ። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚሆን ሰው ሲያገኙ በፍለጋው ሥራ የተካፈሉ ሁሉ ይደሰታሉ።

11. መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናው ሰው ባይኖርም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

11 በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናው ሰው ባይኖርም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አዲሶች ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሲመጡ ሞቅ ያለ አቀባበል ልታደርግላቸውና ልትቀርባቸው ትችላለህ። በዚህ መንገድ፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ፍቅር እንደምናሳይ እንዲያስተውሉ ልትረዳቸው ትችላለህ። (ዮሐ. 13:34, 35) በስብሰባዎች ላይ የምትሰጠው መልስ አጭር ቢሆንም እንኳ ከእኛ ጋር መሰብሰብ የጀመሩ አዲስ ሰዎች የሚያምኑበትን ነገር ከልብ በመነጨና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዴት መግለጽ እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል። በተጨማሪም ከአዲስ አስፋፊ ጋር አብረህ አገልግሎት በመውጣት፣ ጥቅሶችን ተጠቅሞ ከሰዎች ጋር መወያየት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ልታሳየው ትችላለህ። በዚህ መንገድ፣ ክርስቶስን እንዲመስል ታስተምረዋለህ።—ሉቃስ 10:25-28

12. ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ለየት ያለ ችሎታ ያስፈልገናል? አብራራ።

12 ማናችንም ብንሆን፣ ሰዎችን አስተምረን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ለየት ያለ ችሎታ እንደሚያስፈልገን ሊሰማን አይገባም። ለምን? በቦሊቪያ የምትኖረውን ፋውስቲናን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ፋውስቲና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተገናኘችበት ወቅት ማንበብ አትችልም ነበር። በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ ማንበብ ችላለች። ፋውስቲና የተጠመቀች ሲሆን ሌሎችን ማስተማር ያስደስታታል። አብዛኛውን ጊዜ በየሳምንቱ አምስት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናለች። ፋውስቲና የአብዛኞቹን ጥናቶቿን ያህል ማንበብ ባትችልም ስድስት ሰዎች ለጥምቀት እንዲበቁ መርዳት ችላለች።—ሉቃስ 10:21

13. ጊዜያችን የተጣበበ ቢሆንም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈላችን ምን በረከቶች ያስገኛል?

13 በርካታ ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ኃላፊነቶች ስላሉባቸው ጊዜያቸው የተጣበበ ነው። ያም ቢሆን ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የሚሆን ጊዜ አያጡም፤ ይህን በማድረጋቸውም ከፍተኛ ደስታ አግኝተዋል። ሜላኒን እንደ ምሳሌ እንመልከት። በአላስካ የምትኖረው ሜላኒ የስምንት ዓመት ሴት ልጇን የምታሳድገው ብቻዋን ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ሙሉ ቀን ትሠራ እንዲሁም የካንሰር ሕመም ያለበትን አባቷን ትንከባከብ ነበር። ሜላኒ፣ በምትኖርበት ርቆ የሚገኝ ከተማ ውስጥ ብቸኛዋ የይሖዋ ምሥክር ናት። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናው ሰው ማግኘት በጣም ትፈልግ ስለነበር ብርዱን ተቋቁማ አገልግሎት ለመውጣት የሚያስፈልጋትን ብርታት እንዲሰጣት ወደ ይሖዋ ትጸልይ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከሣራ ጋር ተገናኘች፤ ሣራ አምላክ የግል ስም እንዳለው ስታውቅ እጅግ ተደሰተች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሣራ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። ሜላኒ እንዲህ ብላለች፦ “ዓርብ ምሽት ላይ በጣም እዝላለሁ፤ ሆኖም እኔም ሆንኩ ልጄ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት መሄዳችን ጠቅሞናል። ሣራ ለምታነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ምርምር ማድረግ ያስደስተን ነበር፤ ሣራ የይሖዋ ወዳጅ ስትሆን ደግሞ በጣም ተደሰትን።” ሣራ የደረሰባትን ተቃውሞ በድፍረት የተቋቋመች ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗን ለቃ በመውጣት ተጠመቀች።

ደቀ መዛሙርት ማድረግ ትዕግሥት የሚጠይቀው ለምንድን ነው?

14. (ሀ) ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ዓሣ ከማጥመድ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 4:1, 2 ላይ የተናገረው ሐሳብ ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

14 አገልግሎትህ ውጤታማ እንዳልሆነ ቢሰማህም እንኳ ደቀ መዛሙርት የሚሆኑ ሰዎች ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ተስፋ አትቁረጥ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ዓሣ ከማጥመድ ጋር እንዳመሳሰለው አስታውስ። ዓሣ አጥማጆች፣ ዓሣ ለመያዝ ረጅም ሰዓት መሥራት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ በጣም አምሽተው አሊያም በሌሊት ተነስተው መሥራት ይኖርባቸው ይሆናል፤ አንዳንድ ጊዜም በጀልባቸው ረጅም ርቀት መጓዝ አለባቸው። (ሉቃስ 5:5) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚካፈሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ ረጅም ሰዓት የሚያሳልፉ ሲሆን በተለያየ ጊዜና ቦታ በትዕግሥት መረባቸውን ይጥላሉ። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ማግኘት ስለሚፈልጉ ነው። ብዙውን ጊዜ በዚህ ረገድ ተጨማሪ ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች፣ ለመልእክቱ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በማግኘት ይካሳሉ። አንተስ ሰዎችን በምታገኝበት ሰዓት ወይም ቦታ ለመስበክ ይበልጥ ጥረት ማድረግ ትችል ይሆን?2 ጢሞቴዎስ 4:1, 2ን አንብብ።

ጥናቶቻችሁ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በትዕግሥት እርዷቸው (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ትዕግሥት የሚጠይቀው ለምንድን ነው?

15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ትዕግሥት የሚጠይቀው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ተማሪው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረተ ትምህርቶች እንዲያውቅና እንዲወድ ከመርዳት ያለፈ ነገር ማድረግ ያለብን መሆኑ ነው። የምናስጠናው ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን ይሖዋን እንዲያውቅና እንዲወደው ልንረዳው ይገባል። በተጨማሪም ተማሪውን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ ከማስተማር ባለፈ፣ የኢየሱስን ትምህርት በሕይወቱ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል እንዲያውቅ መርዳት ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተግባር ለማዋል ጥረት ሲያደርግ በትዕግሥት ልንረዳው ይገባል። አንዳንዶች በአመለካከታቸውና በልማዶቻቸው ላይ ለውጥ ለማድረግ ጥቂት ወራት ይበቋቸዋል። ሌሎች ግን ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል።

16. ከራውል ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

16 በፔሩ የነበረ አንድ ሚስዮናዊ ታጋሽ የመሆንን ጥቅም የሚያሳይ ሁኔታ አጋጥሞታል። እንዲህ ብሏል፦ “ራውል ከሚባል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ጋር ሁለት መጻሕፍትን አጥንተን ጨርሰን ነበር። ሆኖም በሕይወቱ ውስጥ ከባድ ችግሮች ነበሩበት። ትዳሩ ውጥረት የነገሠበት ከመሆኑም ሌላ ተሳዳቢ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ልጆቹ አያከብሩትም ነበር። ያም ቢሆን ወደ ስብሰባዎች አዘውትሮ ይመጣ ስለነበር እሱንም ሆነ ቤተሰቡን እየሄድኩ መርዳቴን ቀጠልኩ። ከራውል ጋር ከተገናኘን ከሦስት ዓመት በኋላ ለመጠመቅ ብቁ ሆነ።”

17. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

17 ኢየሱስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ብሎናል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ ይህን ተልእኮ ለመፈጸም ከእኛ በጣም የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ማነጋገር ያስፈልገናል፤ ከእነዚህ መካከል ሃይማኖት የሌላቸው ወይም በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ይገኙበታል። የሚቀጥለው ርዕስ እንደነዚህ ላሉት ሰዎች ምሥራቹን እንዴት መስበክ እንደምንችል ያብራራል።

መዝሙር 68 የመንግሥቱን ዘር መዝራት

^ አን.5 የክርስቲያን ጉባኤ ዋነኛ ተልእኮ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። ይህ ርዕስ ይህን ተልእኳችንን ለመወጣት የሚረዱን ጠቃሚ ሐሳቦች ይዟል።

^ አን.2 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ያስተማረውን ከመማር የበለጠ ነገር ያደርጋሉ። የተማሩትን ነገር በተግባር ያውላሉ። የኢየሱስን ፈለግ ወይም ምሳሌ በጥብቅ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ።—1 ጴጥ. 2:21

^ አን.52 የሥዕሉ መግለጫ፦ ለእረፍት ወደ ሌላ ቦታ የሚሄድ አንድ ሰው በአየር ማረፊያ ውስጥ ከይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፍ ሲወስድ። በኋላ ላይ እየተንሸራሸረ ሳለ የአደባባይ ምሥክርነት እየሰጡ ያሉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ተመለከተ። ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ አስፋፊዎች ቤቱን አንኳኩ።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ ይኸው ግለሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ተጠመቀ።