በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 27

ከአሁኑ ለስደት ተዘጋጁ

ከአሁኑ ለስደት ተዘጋጁ

“የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።”—2 ጢሞ. 3:12

መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን

የትምህርቱ ዓላማ *

1. ለስደት መዘጋጀት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

ጌታችን ኢየሱስ፣ የእሱ ደቀ መዛሙርት መሆን የሚፈልጉ ሁሉ እንደሚጠሉ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ተናግሯል። (ዮሐ. 17:14) እውነተኛውን አምልኮ የሚቃወሙ ሰዎች፣ ታማኝ በሆኑ ክርስቲያኖች ላይ ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ስደት እያደረሱባቸው ነው። (2 ጢሞ. 3:12) የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረበ ሲሄድ ደግሞ ከጠላቶቻችን የሚደርስብን ተቃውሞ እየባሰ እንደሚሄድ እንጠብቃለን።—ማቴ. 24:9

2-3. (ሀ) ፍርሃትን በተመለከተ ልናውቀው የሚገባው ነገር ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 ስደት ሲደርስብን ለመጽናት ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? በስደት ጊዜ ሊደርሱብን በሚችሉ መጥፎ ነገሮች ላይ ማውጠንጠን አያስፈልገንም። እንዲህ ካደረግን በፍርሃትና በጭንቀት ልንዋጥ እንችላለን። በአእምሯችን የፈጠርናቸው አስጨናቂ ሁኔታዎች ገና ፈተናው ሳይመጣ በፍርሃት ተሸንፈን እጅ እንድንሰጥ ሊያደርጉን ይችላሉ። (ምሳሌ 12:25፤ 17:22) ፍርሃት ‘ጠላታችን ዲያብሎስ’ እኛን ለማሸነፍ የሚጠቀምበት ኃይለኛ መሣሪያ ነው። (1 ጴጥ. 5:8, 9) ታዲያ ራሳችንን ለማጠናከር ከአሁኑ ምን ማድረግ እንችላለን?

3 በዚህ ርዕስ ላይ፣ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንዴት ማጠናከር እንደምንችል እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት እንመረምራለን። በተጨማሪም ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን ምን ማድረግ እንደምንችል እናያለን። በመጨረሻም፣ ተቃዋሚዎች ሲጠሉን ሁኔታውን መቋቋም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና ማጠናከር የምትችሉት እንዴት ነው?

4. ዕብራውያን 13:5, 6 እንደሚለው ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን አለብን? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ እንደሚወዳችሁና ፈጽሞ እንደማይተዋችሁ እርግጠኞች ሁኑ። (ዕብራውያን 13:5, 6ን አንብብ።) ከበርካታ ዓመታት በፊት በመጠበቂያ ግንብ ላይ “በፈተና ወቅት በአምላክ ይበልጥ የሚታመነው፣ አምላክን በሚገባ የሚያውቀው ሰው ነው” የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር። ይህ በእርግጥም እውነት ነው! ስደት ሲደርስብን መጽናት ከፈለግን ይሖዋን መውደድና በእሱ ሙሉ በሙሉ መታመን ይኖርብናል፤ እንዲሁም እኛን እንደሚወደን ፈጽሞ ልንጠራጠር አይገባም።—ማቴ. 22:36-38፤ ያዕ. 5:11

5. ይሖዋ እንደሚወዳችሁ እንዲሰማችሁ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

5 ወደ ይሖዋ ይበልጥ የመቅረብ ግብ ይዛችሁ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብቡ። (ያዕ. 4:8) መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ፣ የይሖዋን ፍቅር በሚያንጸባርቁት ባሕርያቱ ላይ ትኩረት አድርጉ። ይሖዋ የተናገራቸው ወይም ያደረጋቸው ነገሮች ፍቅሩን የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ አስተውሉ። (ዘፀ. 34:6) ፍቅር አግኝተው የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች፣ አምላክ እንደሚወዳቸው መቀበል ይከብዳቸው ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የይሖዋን ምሕረትና ደግነት ያየኸው በየትኞቹ መንገዶች እንደሆነ በየዕለቱ በዝርዝር ጻፍ። (መዝ. 78:38, 39፤ ሮም 8:32) ስለ ራሳችሁ ሕይወት ስታስቡ እንዲሁም ከአምላክ ቃል ባነበባችሁት ነገር ላይ ስታሰላስሉ ይሖዋ ያደረገላችሁን ብዙ ነገሮች መዘርዘር ትችላላችሁ። ይሖዋ ላደረገላችሁ ነገሮች ያላችሁ አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ ከእሱ ጋር ያላችሁ ዝምድናም ይበልጥ ይጠናከራል።—መዝ. 116:1, 2

6. መዝሙር 94:17-19 እንደሚገልጸው ከልብ የመነጨ ጸሎት ምን ጥቅም አለው?

6 ዘወትር ጸልዩበአባቱ እቅፍ ውስጥ ያለን አንድ ትንሽ ልጅ በአእምሯችሁ ለመሳል ሞክሩ። ልጁ በአባቱ ስለሚተማመን በቀኑ ውስጥ ስላጋጠሙት ጥሩም ሆኑ መጥፎ ነገሮች ለአባቱ በነፃነት ይነግረዋል። እናንተም በየዕለቱ ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት የምታቀርቡ ከሆነ ከእሱ ጋር እንዲህ ዓይነት ዝምድና ሊኖራችሁ ይችላል። (መዝሙር 94:17-19ን አንብብ።) ወደ ይሖዋ ስትጸልዩ ‘በእሱ ፊት ልባችሁን እንደ ውኃ አፍስሱ’፤ እንዲሁም ለአፍቃሪው አባታችሁ የሚያስፈራችሁንና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ ንገሩት። (ሰቆ. 2:19) እንዲህ ማድረግ ምን ያስገኛል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም” ይኖራችኋል። (ፊልጵ. 4:6, 7) በዚህ መንገድ መጸለይን ልማድ ካደረጋችሁ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እየቀረባችሁ ትሄዳላችሁ።—ሮም 8:38, 39

ድፍረት የሚገኘው በይሖዋና በመንግሥቱ ላይ ጠንካራ እምነት በማዳበር ነው

ስታንሊ ጆንስ ስለ አምላክ መንግሥት ያለው እውቀት በአቋሙ እንዲጸና ረድቶታል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚያመጣቸው ቃል የገባቸው ነገሮች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን ያለባችሁ ለምንድን ነው?

7 የአምላክ መንግሥት እንደሚያመጣቸው ቃል የተገባልን በረከቶች እንደሚፈጸሙ ተማመኑ። (ዘኁ. 23:19) አምላክ በሰጣቸው በእነዚህ ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ከሌላችሁ ሰይጣንና ወኪሎቹ በቀላሉ ሊያሸብሯችሁ ይችላሉ። (ምሳሌ 24:10፤ ዕብ. 2:15) በአምላክ መንግሥት ላይ ያላችሁን እምነት ከአሁኑ ማጠናከር የምትችሉት እንዴት ነው? አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚያመጣቸው ቃል ስለገባቸው ነገሮች እንዲሁም እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ መተማመን የምትችሉት ለምን እንደሆነ ጊዜ ወስዳችሁ ምርምር አድርጉ። ይህን ማድረጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? በእምነቱ ምክንያት ለሰባት ዓመት ታስሮ የነበረውን ስታንሊ ጆንስን እንደ ምሳሌ እንመልከት። * ይህ ወንድም በታማኝነት እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ስለ አምላክ መንግሥት ያለኝ እውቀት እምነቴን ያጠናከረው ከመሆኑም ሌላ መንግሥቱ እውን መሆኑን እርግጠኛ መሆኔና ይህን ለቅጽበትም እንኳ አለመጠራጠሬ በአቋሜ እንድጸና ረድቶኛል።” እናንተም አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ካላችሁ ወደ ይሖዋ ይበልጥ የምትቀርቡ ከመሆኑም ሌላ በፍርሃት አትሸነፉም።—ምሳሌ 3:25, 26

8. በስብሰባዎች ላይ ስለ መገኘት ያለን አመለካከት ምን ይጠቁማል? አብራራ።

8 ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኙ። ስብሰባዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዱናል። በአሁኑ ጊዜ በስብሰባዎች ላይ ስለ መገኘት ያለን አመለካከት፣ ወደፊት ስደት ቢመጣ ምን ያህል እንደምንጸና ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። (ዕብ. 10:24, 25) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አሁን በትንሽ በትልቁ ስብሰባ የምንቀር ከሆነ ወደፊት ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ለመሰብሰብ ስንል ራሳችንን ለአደጋ ማጋለጥ የሚጠይቅ ሁኔታ ቢገጥመን ምን እናደርጋለን? በሌላ በኩል ግን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን ተቃዋሚዎች እንዳንሰበሰብ ለማድረግ በሚሞክሩበት ጊዜ አቋማችንን አናላላም። ለስብሰባዎቻችን ፍቅር ማዳበር ያለብን አሁን ነው። ስብሰባዎቻችንን የምንወዳቸው ከሆነ ተቃውሞም ሆነ መንግሥታት የሚጥሉት እገዳ ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን እንዳንታዘዝ እንቅፋት አይሆኑብንም።—ሥራ 5:29

በአሁኑ ጊዜ ጥቅሶችንና የመንግሥቱን መዝሙሮች በቃላችሁ ማጥናታችሁ በስደት ወቅት ይጠቅማችኋል (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት) *

9. ጥቅሶችን በቃል ማጥናት ለስደት ጊዜ ለመዘጋጀት የሚረዳን እንዴት ነው?

9 የምትወዷቸውን ጥቅሶች በቃላችሁ ለመያዝ ጥረት አድርጉ። (ማቴ. 13:52) በእርግጥ በቃላችሁ ያጠናችሁትን ሁሉ ታስታውሳላችሁ ማለት አይደለም፤ ያም ቢሆን ይሖዋ ኃያል በሆነው ቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ እነዚህን ጥቅሶች እንድታስታውሱ ይረዳችኋል። (ዮሐ. 14:26) በምሥራቅ ጀርመን ከሰው ተለይቶ ለብቻው ታስሮ የነበረ አንድ ወንድም ምን እንዳለ ልብ እንበል፦ “በዚያን ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃሌ አውቅ ስለነበር በጣም ደስ አለኝ! ያለምንም ሥራ ብቻዬን በታሰርኩበት በዚያን ወቅት በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማሰላሰል ጊዜዬን አሳልፍ ነበር።” እነዚህ ጥቅሶች ወንድማችን ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ጠብቆ መቀጠል እንዲችልና በታማኝነት እንዲጸና ረድተውታል።

(አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት) *

10. መዝሙሮችን በቃላችን ማጥናታችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ይሖዋን የሚያወድሱ መዝሙሮችን በቃላችሁ አጥኑ እንዲሁም ዘምሩ። ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ታስረው በነበሩበት ወቅት፣ ከዚያ ቀደም በቃላቸው ያጠኗቸውን መንፈሳዊ መዝሙሮች ዘምረው ነበር። (ሥራ 16:25) በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የነበሩ ወንድሞቻችንስ ወደ ሳይቤሪያ በተጋዙበት ወቅት ራሳቸውን ማጠናከር የቻሉት እንዴት ነበር? እህት ማሪያ ፌዱን “በመዝሙር መጽሐፋችን ውስጥ ያሉትን የምናውቃቸውን መዝሙሮች በሙሉ እንዘምር ነበር” በማለት ታስታውሳለች። ይህች እህት፣ እነዚያን መዝሙሮች ሲዘምሩ ሁሉም እንደተበረታቱና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደቀረቡ እንደተሰማቸው ተናግራለች። እናንተም የምትወዷቸውን መንፈሳዊ መዝሙሮች ስትዘምሩ እንደምትበረታቱ ጥያቄ የለውም። እንግዲያው ከአሁኑ እነዚህን መዝሙሮች በቃላችሁ አጥኗቸው!—“ ድፍረት ስጠኝ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

 

ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

11-12. (ሀ) በ1 ሳሙኤል 17:37, 45-47 ላይ እንደተገለጸው ዳዊትን ደፋር እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? (ለ) ከዳዊት ምሳሌ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

11 ስደትን በጽናት ለመቋቋም ድፍረት ያስፈልጋችኋል። ይህን ባሕርይ ይበልጥ ማዳበር እንደሚያስፈልጋችሁ ከተሰማችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? እውነተኛ ድፍረት፣ ግዙፍ ወይም ጠንካራ በመሆናችን አሊያም በችሎታችን ላይ የተመካ እንዳልሆነ እናስታውስ። ወጣቱ ዳዊት፣ ጎልያድን በተጋፈጠበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት ከዚያ ግዙፍ ሰው በአቋምም ሆነ በጥንካሬ የሚያንስ ከመሆኑም ሌላ በቂ የጦር ትጥቅ አልነበረውም። ሌላው ቀርቶ ሰይፍ እንኳ አልያዘም። ያም ቢሆን በጣም ደፋር ነበር። ዳዊት እብሪተኛ ከሆነው ከዚያ ግዙፍ ሰው ጋር ለመዋጋት በድፍረት እየሮጠ ወደ እሱ ሄዷል።

12 ዳዊት ይህን ያህል ደፋር እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሆነ ጠንካራ እምነት ነበረው። (1 ሳሙኤል 17:37, 45-47ን አንብብ።) ዳዊት፣ ጎልያድ ከእሱ አንጻር ሲታይ ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ትኩረት ያደረገው ጎልያድ ከይሖዋ አንጻር ሲታይ በጣም ኢምንት በመሆኑ ላይ ነው። ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነ ከተማመንንና ተቃዋሚዎቻችን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ አንጻር ሲታዩ ከቁጥር የማይገቡ እንደሆኑ ካስታወስን የበለጠ ድፍረት ይኖረናል። (2 ዜና 20:15፤ መዝ. 16:8) ታዲያ ስደት ከመምጣቱ በፊት ከአሁኑ ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

13. የበለጠ ድፍረት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? አብራራ።

13 የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች በመስበክ ከአሁኑ ድፍረት ማዳበር እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የስብከቱ ሥራ በይሖዋ እንድንታመንና የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ ስለሚረዳን ነው። (ምሳሌ 29:25) ስፖርት ስንሠራ ጡንቻችን እንደሚዳብር ሁሉ ከቤት ወደ ቤት፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድና በንግድ ቦታዎች ስናገለግል ድፍረታችን እየጨመረ ይሄዳል። ለመስበክ የሚያስፈልገንን ድፍረት ከአሁኑ ካዳበርን ወደፊት ሥራችን ቢታገድም እንኳ መስበካችንን ለመቀጠል ዝግጁ እንሆናለን።—1 ተሰ. 2:1, 2

ናንሲ ዩወን ምሥራቹን መስበኳን እንድታቆም ቢነገራትም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነችም (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14-15. ከናንሲ ዩወን እና ከቫለንቲና ጋርኖፍስከየ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 አስደናቂ ድፍረት ያሳዩ ሁለት እህቶችን ምሳሌ በመመልከት ብዙ መማር እንችላለን። ናንሲ ዩወን ቁመቷ ከ1.5 ሜትር አይበልጥም፤ ሆኖም በቀላሉ የምትበረግግ ሴት አልነበረችም። * የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበኳን እንድታቆም ቢነገራትም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህም የተነሳ በኮሚኒስት ቻይና ውስጥ ለ20 ዓመታት ታስራለች። ምርመራ ያደረጉባት ባለሥልጣናት “በአገራችን ውስጥ እንደዚህች ዓይነት ግትር ሴት አይተን አናውቅም!” በማለት ተናግረዋል።

ቫለንቲና ጋርኖፍስከየ ይሖዋ ከእሷ ጋር እንደሆነ እርግጠኛ ነበረች (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15 በተመሳሳይም ቫለንቲና ጋርኖፍስከየ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ በሦስት የተለያዩ ጊዜያት በአጠቃላይ ለ21 ዓመታት ታስራለች። * የታሰረችው ለምን ነበር? መስበኳን ለማቆም ፈቃደኛ ባለመሆኗ ባለሥልጣናቱ “እጅግ አደገኛ ወንጀለኛ” ብለው ሰይመዋታል። እነዚህን ሁለት ታማኝ ሴቶች ይህን ያህል ደፋር እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ ከእነሱ ጋር እንደሆነ እርግጠኛ መሆናቸው ነው።

16. እውነተኛ ድፍረት ለማሳየት ቁልፉ ምንድን ነው?

16 እስካሁን እንደተመለከትነው ይበልጥ ደፋር መሆን ከፈለግን በራሳችን ጥንካሬና ችሎታ ላይ ትኩረት ማድረግ የለብንም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነና ተቃዋሚዎቻችንን የሚዋጋልን እሱ እንደሆነ መተማመን ይኖርብናል። (ዘዳ. 1:29, 30፤ ዘካ. 4:6) እውነተኛ ድፍረት ለማሳየት ቁልፉ ይህ ነው።

ሰዎች ሲጠሏችሁ ሁኔታውን መቋቋም የምትችሉት እንዴት ነው?

17-18. በዮሐንስ 15:18-21 ላይ ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል? ይህ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ አብራራ።

17 ሰዎች ሲያከብሩን ደስ የሚለን ቢሆንም ሌሎች ስላልወደዱን ብቻ ስለ ራሳችን መጥፎ ስሜት ሊሰማን አይገባም። ኢየሱስ “ሰዎች፣ በሰው ልጅ ምክንያት በሚጠሏችሁ፣ በሚያገሏችሁ፣ በሚነቅፏችሁና ክፉ እንደሆናችሁ አድርገው ያለስማችሁ ስም በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ” ብሏል። (ሉቃስ 6:22) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?

18 ክርስቲያኖች፣ በሌሎች መጠላታቸው በራሱ እንደሚያስደስታቸው መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እውነታውን እየነገረን ነበር። የዓለም ክፍል አይደለንም። የኢየሱስን ትምህርቶች በሕይወታችን ተግባራዊ የምናደርግ ሲሆን እሱ የሰበከውን መልእክትም እንሰብካለን። በዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላናል። (ዮሐንስ 15:18-21ን አንብብ።) የእኛ ዓላማ ይሖዋን ማስደሰት ነው። የሰማዩ አባታችንን ስለወደድን ሰዎች ከጠሉን በዚህ ቅር አይለንም።

19. የሐዋርያትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

19 ከይሖዋ አንጻር ኢምንት የሆኑት የሰው ልጆች የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር የይሖዋ ምሥክር በመሆናችሁ እንድታፍሩ ሊያደርጋችሁ አይገባም። (ሚክ. 4:5) በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ከተገደለ ብዙም ሳይቆይ ያደረጉትን ነገር መመልከታችን የሰው ፍርሃትን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁመናል። ሐዋርያቱ፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ምን ያህል እንደሚጠሏቸው ያውቁ ነበር። (ሥራ 5:17, 18, 27, 28) ይሁን እንጂ በየቀኑ ወደ ቤተ መቅደሱ መሄዳቸውንና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ በይፋ ማወጃቸውን አላቆሙም። (ሥራ 5:42) በፍርሃት አልተሽመደመዱም። እኛም በሥራ ቦታም ሆነ በትምህርት ቤት እንዲሁም በምንኖርበት አካባቢ፣ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን አዘውትረን በይፋ መናገራችን የሰው ፍርሃትን ለማሸነፍ ይረዳናል።—ሥራ 4:29፤ ሮም 1:16

20. ሐዋርያት ሰዎች ቢጠሏቸውም እንኳ ደስተኞች እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው?

20 ሐዋርያት ደስተኞች እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው? ለምን እንደሚጠሉ ያውቁ ነበር፤ ደግሞም የይሖዋን ፈቃድ በማድረጋቸው መንገላታትን እንደ ክብር ቆጥረውት ነበር። (ሉቃስ 6:23፤ ሥራ 5:41) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለጽድቅ ስትሉ መከራ ብትቀበሉ ደስተኞች ናችሁ” በማለት ከጊዜ በኋላ ጽፏል። (1 ጴጥ. 2:19-21፤ 3:14) የምንጠላው ትክክል የሆነውን ነገር በማድረጋችን እንደሆነ ከተገነዘብን ሰዎች ስለጠሉን በፍርሃት አንሸነፍም።

ዝግጅት ማድረጋችሁ ይጠቅማችኋል

21-22. (ሀ) ለስደት ለመዘጋጀት ምን ለማድረግ ወስነሃል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

21 በስደት ወይም መንግሥታት በሥራችን ላይ በሚጥሉት እገዳ የተነሳ ይሖዋን በነፃነት ማምለክ የማንችልበት ጊዜ የሚመጣው መቼ እንደሆነ አናውቅም። ይሁንና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በማጠናከር፣ ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን ጥረት በማድረግ እንዲሁም የሰዎችን ጥላቻ እንዴት መቋቋም እንደምንችል በመማር ከአሁኑ መዘጋጀት እንደምንችል እናውቃለን። በአሁኑ ጊዜ የምናደርገው ዝግጅት ወደፊት ጸንተን ለመቆም ይረዳናል።

22 ሆኖም አሁን በአምልኳችን ላይ እገዳ ቢጣልስ? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በእገዳ ሥርም እንኳ ይሖዋን ማገልገላችንን ለመቀጠል የሚረዱንን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመረምራለን።

መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”

^ አን.5 ማናችንም ብንሆን ሰዎች እንዲጠሉን አንፈልግም። ሆኖም ይዋል ይደር እንጂ ሁላችንም ስደት እንደሚደርስብን የታወቀ ነው። ይህ ርዕስ ስደትን በድፍረት መወጣት እንድንችል ያዘጋጀናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 የታኅሣሥ 15, 1965 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 756-767⁠ን ተመልከት።

^ አን.14 የሐምሌ 15, 1979 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 4-7⁠ን ተመልከት። በተጨማሪም JW ብሮድካስቲንግ ላይ የወጣውን የይሖዋ ስም እንዲታወቅ ማድረግ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት። ቪዲዮው ቃለ መጠይቅ እና ተሞክሮ በሚለው ሥር ይገኛል።

^ አን.68 የሥዕሉ መግለጫ፦ ወላጆች በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ ካርዶችን በመጠቀም ልጆቻቸው ጥቅሶችን በቃላቸው እንዲይዙ ሲረዱ።

^ አን.71 የሥዕሉ መግለጫ፦ የአንድ ቤተሰብ አባላት ወደ ስብሰባ በመኪና በሚጓዙበት ወቅት የመንግሥቱን መዝሙሮች ሲለማመዱ።