በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 28

በእገዳ ሥር ሆናችሁም ይሖዋን ማምለካችሁን ቀጥሉ

በእገዳ ሥር ሆናችሁም ይሖዋን ማምለካችሁን ቀጥሉ

“ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።”—ሥራ 4:19, 20

መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!

የትምህርቱ ዓላማ *

1-2. (ሀ) ይሖዋን እንዳናመልክ እገዳ ቢጣልብን የማያስገርመን ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

በ2018 መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችን ሙሉ በሙሉ በታገደባቸው አሊያም በሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከ223,000 የሚበልጡ የምሥራቹ አስፋፊዎች ነበሩ። ይህ መሆኑ አያስገርመንም። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው እውነተኛ ክርስቲያኖች ስደት እንደሚደርስባቸው ይጠብቃሉ። (2 ጢሞ. 3:12) የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ ባለሥልጣናት ለአፍቃሪው አምላካችን ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ላይ ሳናስበው በድንገት እገዳ ሊጥሉ ይችላሉ።

2 የምትኖሩበት አገር መንግሥት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ ገደብ ቢጥል እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ይፈጠሩባችሁ ይሆናል፦ ‘ስደት የአምላክን ሞገስ እንዳጣን የሚያሳይ ነው? በሥራችን ላይ እገዳ መጣሉ ይሖዋን ከማምለክ ያግደናል? አምላክን በነፃነት ማምለክ ወደምችልበት አገር ብሄድ ይሻል ይሆን?’ በዚህ ርዕስ ላይ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን። በተጨማሪም ሥራችን ቢታገድ ይሖዋን ማምለካችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮችን እናያለን።

ስደት የይሖዋን ሞገስ እንዳጣን የሚያሳይ ነው?

3. በ2 ቆሮንቶስ 11:23-27 ላይ እንደተገለጸው ታማኙ ሐዋርያ ጳውሎስ ምን ዓይነት ስደት አጋጥሞታል? ከእሱ ምሳሌስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

3 መንግሥት በአምልኳችን ላይ እገዳ ቢጥል ‘የአምላክን በረከት አጥተናል’ የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንደርስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ስደት ይሖዋ እንዳዘነብን የሚያሳይ ነገር እንዳልሆነ እናስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ የአምላክን ሞገስ ያገኘ ሰው እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉ 14 ደብዳቤዎችን የመጻፍ መብት ያገኘ ከመሆኑም ሌላ ለአሕዛብ የተላከ ሐዋርያ ነበር። ያም ቢሆን ከባድ ስደት ደርሶበት ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27ን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ ካጋጠመው ነገር እንደምንማረው ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ ስደት እንዲደርስባቸው ይፈቅዳል።

4. ዓለም የሚጠላን ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ተቃውሞ እንደሚገጥመን ልንጠብቅ የሚገባው ለምን እንደሆነ ገልጿል። የምንጠላው የዓለም ክፍል ስላልሆንን እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 15:18, 19) ስደት የይሖዋን በረከት እንዳጣን የሚጠቁም አይደለም። እንዲያውም ትክክለኛውን ነገር እያደረግን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው!

በሥራችን ላይ እገዳ መጣሉ ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ያስቆመዋል?

5. የሰው ልጆች ለይሖዋ የሚቀርበውን አምልኮ ሊያስቆሙት ይችላሉ? አብራራ።

5 የሰው ልጆች፣ ሁሉን ቻይ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ሊያስቆሙት አይችሉም። ብዙዎች ይህን ለማድረግ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ምን እንደተከሰተ እንመልከት። በዚያ ወቅት የብዙ አገሮች መንግሥታት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከባድ ስደት ያደርሱ ነበር። የጀርመን የናዚ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የአውስትራሊያ፣ የካናዳና የሌሎች አገሮች መንግሥታትም የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ አግደው ነበር። ይሁንና ውጤቱ ምን ሆነ? በ1939 ጦርነቱ ሲጀምር በዓለም ዙሪያ 72,475 አስፋፊዎች ነበሩ። ይሁንና የይሖዋ በረከት ስላልተለያቸው በ1945 ጦርነቱ ሲያበቃ 156,299 አስፋፊዎች እንደነበሩ ሪፖርቶች አሳይተዋል። የአስፋፊዎቹ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ነበር!

6. ተቃውሞ በፍርሃት እንድንሽመደመድ ከማድረግ ይልቅ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

6 ተቃውሞ በፍርሃት እንድንሽመደመድ ከማድረግ ይልቅ ይሖዋን ይበልጥ እንድናገለግል ሊያነሳሳን ይችላል። ሥራችን በመንግሥት በታገደበት አገር የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስትን ምሳሌ እንመልከት፤ እነዚህ ባልና ሚስት ትንሽ ልጅ አላቸው። ባልና ሚስቱ በፍርሃት ተሸንፈው ወደኋላ ከማለት ይልቅ የዘወትር አቅኚዎች ሆኑ። እንዲያውም ሚስትየው አቅኚ ለመሆን ስትል ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝላትን ሥራዋን ተወች። እገዳው ብዙዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ለማወቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው እንዳደረገ ባልየው ተናግሯል። በዚህም ምክንያት ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ቀላል ሆኖለታል። እገዳው ሌላም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። በዚህ አገር የሚገኝ አንድ ሽማግሌ እንደተናገረው ይሖዋን ማገልገል ያቆሙ ብዙዎች እንደገና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀምረዋል።

7. (ሀ) ዘሌዋውያን 26:36, 37 ምን ትምህርት ይዞልናል? (ለ) በእገዳ ሥር ብትሆን ምን ታደርጋለህ?

7 ጠላቶቻችን በአምልኳችን ላይ እገዳ ሲጥሉ፣ ዓላማቸው ፈርተን ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንተው ማድረግ ነው። እገዳ ከመጣል በተጨማሪ ስለ እኛ የሐሰት ወሬ ያናፍሱ፣ በፖሊሶች ቤታችን እንዲፈተሽ ያደርጉ፣ ፍርድ ቤት ያቀርቡን ሌላው ቀርቶ አንዳንዶቻችንን ያስሩን ይሆናል። ፍላጎታቸው ከመካከላችን ጥቂት ሰዎችን በማሰር እኛን ማስፈራራት ነው። በፍርሃት እንድንርድ እንዲያደርጉን ከፈቀድን እኛው ራሳችን በአምልኳችን ላይ እገዳ እንጥላለን። በዘሌዋውያን 26:36, 37 ላይ እንደተገለጹት ሰዎች መሆን አንፈልግም። (ጥቅሱን አንብብ።) ፍርሃት፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን እንድንቀንስ ወይም እንድናቆም እንዲያደርገን መፍቀድ የለብንም። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የምንታመን ሲሆን ፈጽሞ አንደናገጥም። (ኢሳ. 28:16) ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠን እንጸልያለን። ይሖዋ ከእኛ ጋር እስከሆነ ድረስ በጣም ኃያል የሚባለው ሰብዓዊ መንግሥትም ቢሆን አምላካችንን በታማኝነት ከማምለክ ሊያግደን እንደማይችል እናውቃለን።—ዕብ. 13:6

ወደ ሌላ አገር ብሄድ ይሻል ይሆን?

8-9. (ሀ) እያንዳንዱ ግለሰብ ወይም የቤተሰብ ራስ ምን የግል ውሳኔ ማድረግ አለበት? (ለ) አንድ ሰው ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርግ ምን ሊረዳው ይችላል?

8 የምትኖርበት አገር መንግሥት በአምልኳችን ላይ እገዳ ቢጥል ‘ይሖዋን በነፃነት ማምለክ ወደሚቻልበት አገር ብሄድ ይሻል ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይህ የግል ውሳኔ ነው፤ ማንም ሰው ይህንን ሊወስንልህ አይችልም። አንዳንዶች፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ስደት ሲደርስባቸው ያደረጉትን ነገር ያስታውሱ ይሆናል። የክርስትና ጠላቶች እስጢፋኖስን ወግረው ከገደሉት በኋላ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት ደቀ መዛሙርት በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች የተበተኑ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶች እስከ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ሄደዋል። (ማቴ. 10:23፤ ሥራ 8:1፤ 11:19) ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በሌላ ጊዜ ስደት ባጋጠማቸው ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ላይ ተቃውሞ የተነሳበትን አካባቢ ለቆ ላለመሄድ ወስኗል። ጳውሎስ በዚያ መቆየቱ ለአደጋ የሚያጋልጠው ቢሆንም ምሥራቹን ለመስበክ እና ከባድ ስደት በተነሳባቸው ከተሞች ውስጥ የሚኖሩትን ወንድሞች ለማበረታታት ሲል ይህን አድርጓል።—ሥራ 14:19-23

9 ከእነዚህ ዘገባዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? ወደ ሌላ ቦታ መሄድን በተመለከተ እያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ የግሉን ውሳኔ ማድረግ አለበት። ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ቤተሰቡ ስላለበት ሁኔታ እንዲሁም ወደ ሌላ አካባቢ መሄዳቸው ስለሚኖሩት ጥቅሞችና ጉዳቶች በጸሎትና በጥሞና ማሰብ አለበት። በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።” (ገላ. 6:5) ሌሎች ምንም ዓይነት ውሳኔ ቢያደርጉ ልንተቻቸው አይገባም።

በእገዳ ሥር ሆነን ይሖዋን ማምለክ የምንችለው እንዴት ነው?

10. ቅርንጫፍ ቢሮውና ሽማግሌዎች ምን ዓይነት መመሪያ ይሰጣሉ?

10 በእገዳ ሥር ብትሆን ይሖዋን ማምለክህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው? መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት፣ ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ እንዲሁም ምሥራቹን መስበክ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ቅርንጫፍ ቢሮው ለጉባኤህ ሽማግሌዎች መመሪያዎችና ጠቃሚ ሐሳቦች ይሰጣል። ቅርንጫፍ ቢሮው ከሽማግሌዎች ጋር መገናኘት ካልቻለ ደግሞ ሽማግሌዎቹ አንተም ሆንክ የጉባኤው አባላት በሙሉ ይሖዋን ማምለካችሁን እንድትቀጥሉ ይረዷችኋል። በመጽሐፍ ቅዱስ እና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር የሚስማማ መመሪያ ይሰጧችኋል።—ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 5:29፤ ዕብ. 10:24, 25

11. መንፈሳዊ ምግብ እንደምታገኝ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው? ያለህን መንፈሳዊ ምግብ ለመጠበቅስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

11 ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 65:13, 14፤ ሉቃስ 12:42-44) በመሆኑም የይሖዋ ድርጅት የሚያስፈልግህን መንፈሳዊ ማበረታቻ እንድታገኝ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። አንተስ ምን ማድረግ ትችላለህ? በእገዳ ሥር ከሆንክ መጽሐፍ ቅዱስህን እንዲሁም ሌሎች ጽሑፎችህን የምትደብቅበት ቦታ አዘጋጅ። የታተሙትንም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የተዘጋጁትን እነዚህን ውድ መንፈሳዊ ጽሑፎች በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉበት ቦታ ላይ ፈጽሞ አትተዋቸው። ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ይዘን ለመቀጠል እያንዳንዳችን አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ አለብን።

ይሖዋ ስለሚረዳን በድፍረት ለአምልኮ መሰብሰብ እንችላለን (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) *

12. ሽማግሌዎች የተቃዋሚዎችን ትኩረት በማይስብ መልኩ ስብሰባዎችን ማደራጀት የሚችሉት እንዴት ነው?

12 በየሳምንቱ የምናደርጋቸውን ስብሰባዎች በተመለከተስ? ሽማግሌዎች የተቃዋሚዎችን ትኩረት በማይስብ መልኩ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ዝግጅት ያደርጋሉ። በትናንሽ ቡድኖች እንድንሰበሰብ መመሪያ ይሰጡ እንዲሁም የስብሰባዎቹ ሰዓትና ቦታ በየጊዜው እንዲቀያየር ያደርጉ ይሆናል። ወደ ስብሰባ ስትገባም ሆነ ስትወጣ ብዙ ድምፅ ባለማሰማት በስብሰባ ላይ የሚገኙትን ሁሉ ደህንነት ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላለህ። አለባበስህም ቢሆን ትኩረት የማይስብ እንዲሆን ጥንቃቄ ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል።

መንግሥት እገዳ ቢጥልም መስበካችንን አናቆምም (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት) *

13. በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ከነበሩት ወንድሞቻችን ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታው ከቦታ ቦታ ሊለያይ ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ስለምንወድና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች መናገር ስለሚያስደስተን ለመስበክ የሚያስችሉ መንገዶችን እንፈልጋለን። (ሉቃስ 8:1፤ ሥራ 4:29) ኤምሊ ብሩደርለ ቤረን የተባሉ የታሪክ ምሁር በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የይሖዋ ምሥክሮች ስላከናወኑት የስብከት ሥራ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እምነታቸው ለሌሎች እንዳይናገሩ መንግሥት ሲከለክላቸው ለጎረቤቶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው ይሰብኩ ነበር። ይህን በማድረጋቸው ምክንያት የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች ሲላኩ ደግሞ አብረዋቸው የታሰሩ ሰዎችን አማኝ ማድረግ ጀመሩ።” በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የነበሩት ወንድሞቻችን በእገዳ ሥር ቢሆኑም መስበካቸው አላቆሙም። አንተም በምትኖርበት ቦታ በስብከቱ ሥራ ላይ እገዳ ቢጣል እንዲህ ዓይነት ቆራጥነት ይኑርህ!

ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮች

ዝም ለማለት ጊዜ እንዳለው ማወቅ አለብን (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት) *

14. መዝሙር 39:1 ምን ዓይነት ጥንቃቄ እንድናደርግ ይረዳናል?

14 ለሌሎች በምትሰጡት መረጃ ረገድ ጥንቃቄ አድርጉ። በእገዳ ሥር ስንሆን “ዝም ለማለት ጊዜ” እንዳለው መገንዘብ ይኖርብናል። (መክ. 3:7) የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ስም፣ ስብሰባ የምናደርግባቸውን ቦታዎች፣ አገልግሎታችንን የምናከናውንበትንና መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝበትን መንገድ እንዲሁም እንደነዚህ ያሉ በሚስጥር ሊያዙ የሚገባቸው መረጃዎችን በጥንቃቄ መያዝ አለብን። እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ለመንግሥት ባለሥልጣናት መናገር የለብንም፤ በአገር ውስጥም ሆነ በሌላ አገር ላሉ ወዳጆቻችን ወይም ዘመዶቻችንም ቢሆን አንናገርም። በዚህ ረገድ ካልተጠነቀቅን ወንድሞቻችንን አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን።—መዝሙር 39:1ን አንብብ።

15. ሰይጣን ምን ሊያደርገን ይጥራል? በእሱ ወጥመድ ላለመውደቅስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 በትናንሽ ጉዳዮች የተነሳ መከፋፈል እንዳይፈጠር ተጠንቀቁ። ሰይጣን እርስ በርሱ የተለያየ ቤት ጸንቶ ሊቆም እንደማይችል ያውቃል። (ማር. 3:24, 25) በመሆኑም በመካከላችን መከፋፈል ለመፍጠር የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል። በዚህ መንገድ፣ ከእሱ ጋር ከመዋጋት ይልቅ እርስ በርስ እንድንዋጋ ሊያደርገን ይፈልጋል።

16. እህት ጌርትሩድ ፖትጺንገር ምን ግሩም ምሳሌ ትታለች?

16 የጎለመሱ ክርስቲያኖችም እንኳ በዚህ ወጥመድ እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። ጌርትሩድ ፖትጺንገር እና ኤልፍሪደ ለር የተባሉትን ሁለት የተቀቡ እህቶች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ እህቶች በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ከሌሎች እህቶች ጋር ታስረው ነበር። ኤልፍሪደ በካምፑ ውስጥ ላሉ ሌሎች እህቶች የሚያበረታቱ ንግግሮች ስትሰጥ ጌርትሩድ መቅናት ጀመረች። በኋላ ላይ ግን ነገሩ ስላሳፈራት ይሖዋ እንዲረዳት ጸለየች። “ሌሎች ከእኛ የበለጠ ችሎታ ወይም ኃላፊነት ሲኖራቸው ይህን መቀበልን መማር አለብን” በማለት ጽፋለች። ቅናቷን ማሸነፍ የቻለችው እንዴት ነው? ጌርትሩድ በኤልፍሪደ መልካም ባሕርያትና በጥሩ ጠባይዋ ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመረች። ይህን ማድረጓ ከኤልፍሪደ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻሻል ረድቷታል። ሁለቱም እህቶች ከማጎሪያ ካምፕ ተርፈው የወጡ ሲሆን ምድራዊ ሕይወታቸውን እስካጠናቀቁበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። እኛም ከወንድሞቻችን ጋር ያሉን ልዩነቶች ችግር እንዳይፈጥሩብን የተቻለንን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ልዩነቶቻችን ለመከፋፈል ምክንያት አይሆኑም።—ቆላ. 3:13, 14

17. በራስ የመመራት መንፈስን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?

17 በራስ የመመራት መንፈስን አስወግዱ። እምነት የሚጣልባቸው ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚሰጡንን መመሪያ የምንከተል ከሆነ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መከላከል እንችላለን። (1 ጴጥ. 5:5) ለምሳሌ ያህል፣ ሥራችን በታገደበት አንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች፣ አስፋፊዎች በአገልግሎት ላይ ጽሑፎች እንዳያበረክቱ መመሪያ ሰጥተው ነበር። በዚያ አካባቢ የሚኖር አንድ አቅኚ ወንድም ግን ይህን መመሪያ በመጣስ ጽሑፎችን አበረከተ። ታዲያ ይህ ምን አስከተለ? እሱና ሌሎች አስፋፊዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ያከናወኑትን አገልግሎት ጨርሰው ሲሄዱ ፖሊሶች ለምርመራ ያዟቸው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ከመንግሥት የተላኩ ሰዎች ይከታተሏቸው የነበረ ሲሆን ወንድሞች ካነጋገሯቸው ሰዎች ጽሑፎቹን መውሰድ ችለው ነበር። ከዚህ ተሞክሮ ምን እንማራለን? የተሰጠውን መመሪያ ባንስማማበትም እንኳ መታዘዝ አለብን። ይሖዋ በመካከላችን ሆነው አመራር እንዲሰጡ ከሾማቸው ወንድሞች ጋር ስንተባበር ምንጊዜም የእሱን በረከት እናገኛለን።—ዕብ. 13:7, 17

18. አላስፈላጊ ደንቦችን ከማውጣት መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?

18 አላስፈላጊ ደንቦችን አታውጡ። ሽማግሌዎች አላስፈላጊ ደንቦችን የሚያወጡ ከሆነ በሌሎች ላይ ሸክም ይጭናሉ። ወንድም ዩራይ ካሚንስኪ በቀድሞዋ ቼኮስሎቫኪያ ወንድሞች በእገዳ ሥር በነበሩበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችና በርካታ ሽማግሌዎች ከታሰሩ በኋላ በጉባኤዎችና በወረዳዎች ውስጥ ሥራውን ይመሩ የነበሩ አንዳንድ ወንድሞች፣ አድርግ/አታድርግ የሚል ዝርዝር የያዙ ደንቦችን ለአስፋፊዎቹ ማውጣት ጀመሩ።” ይሖዋ ለሌሎች የግል ውሳኔ የማድረግ ሥልጣን አልሰጠንም። አላስፈላጊ ደንቦችን የሚያወጣ ሰው ወንድሙን ከአደጋ እየጠበቀ ሳይሆን በወንድሙ እምነት ላይ እያዘዘ ነው።—2 ቆሮ. 1:24

ይሖዋን ማምለካችሁን ፈጽሞ አታቋርጡ

19. ሰይጣን ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ፣ 2 ዜና መዋዕል 32:7, 8 እንደሚያሳየው ልበ ሙሉ እንድንሆን የሚያደርግ ምን ምክንያት አለን?

19 ቀንደኛው ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ በይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ላይ ስደት ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት አያቆምም። (1 ጴጥ. 5:8፤ ራእይ 2:10) ሰይጣንና ወኪሎቹ ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ላይ እገዳ ለመጣል መሞከራቸውን ይቀጥላሉ። ያም ቢሆን በፍርሃት የምንርድበት ምንም ምክንያት የለም! (ዘዳ. 7:21) ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው፤ ሥራችን ቢታገድም እንኳ እኛን መደገፉን ይቀጥላል።2 ዜና መዋዕል 32:7, 8ን አንብብ።

20. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ወንድሞቻችን በዘመኑ ለነበሩት ባለሥልጣናት እንዲህ ብለዋቸው ነበር፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ። እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።” እኛም እንዲህ ዓይነት ቁርጥ አቋም ይኑረን።—ሥራ 4:19, 20

መዝሙር 73 ድፍረት ስጠን

^ አን.5 መንግሥት ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ላይ እገዳ ቢጥል ምን ማድረግ ይኖርብናል? እንዲህ ባለው ወቅት ይሖዋን ማምለካችንን መቀጠል እንድንችል ምን ማድረግ እንዳለብንና ምን ማድረግ እንደሌለብን የሚገልጹ ጠቃሚ ሐሳቦችን በዚህ ርዕስ ላይ እናገኛለን።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁሉም ፎቶግራፎች፣ በሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉባቸው አገሮች የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ የሚያሳዩ ናቸው። በዚህ ፎቶግራፍ ላይ ጥቂት ወንድሞች በአንድ ወንድም የዕቃ ማስቀመጫ ክፍል ውስጥ ስብሰባ ሲያደርጉ ይታያል።

^ አን.61 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት (በስተ ግራ) ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችላት አጋጣሚ ለማግኘት ከአንዲት ሴት ጋር ስትጨዋወት።

^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ ፖሊሶች ምርመራ የሚያደርጉበት አንድ ወንድም ስለ ጉባኤው መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።