በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 34

አዲስ የአገልግሎት ምድብን መልመድ

አዲስ የአገልግሎት ምድብን መልመድ

“አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።”—ዕብ. 6:10

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

የትምህርቱ ዓላማ *

1-3. አንዳንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በአገልግሎት ምድባቸው ላይ መቀጠል እንዳይችሉ ያደረጓቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

“በሚስዮናዊነት ምድባችን ላይ 21 አስደሳች ዓመታት ካሳለፍን በኋላ የሁለታችንም ወላጆች እንክብካቤ አስፈለጋቸው” በማለት ሮበርትና ሜሪ ጆ ያስታውሳሉ። አክለውም “ወላጆቻችንን መንከባከብ በመቻላችን ደስተኛ ነን። ያም ቢሆን በጣም የምንወደውን ቦታ ትተን መሄዳችን በእጅጉ አሳዝኖን ነበር” ብለዋል።

2 ዊልያም እና ቴሪ እንዲህ ብለዋል፦ “የጤንነታችን ሁኔታ ምድባችን ላይ ለመቆየት እንደማያስችለን ስናውቅ አለቀስን። ከዚህ በኋላ ይሖዋን በሌላ አገር ማገልገል አንችልም።”

3 አሌክሴይ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ተቃዋሚዎቻችን ቅርንጫፍ ቢሮውን መዝጋት እንደፈለጉ ቀድሞውንም እናውቅ ነበር። ቢሮው ሲዘጋና ቤቴልን ለቀን ለመውጣት ስንገደድ ግን እንደ አዲስ አዘንን።”

4. በዚህ ርዕስ ላይ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

4 ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች በተጨማሪ አዲስ የአገልግሎት ምድብ የተሰጣቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የቤቴል ቤተሰብ አባላትና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ማሰብ እንችላለን። * እነዚህ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች የሚወዱትን የአገልግሎት ምድብ መተው ከብዷቸው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ለውጡን ለመልመድ ምን ሊረዳቸው ይችላል? እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ፣ ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን ለውጦች ጋር ለመላመድ ይረዳናል።

ለውጥን መልመድ የሚቻለው እንዴት ነው?

የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ምድባቸውን ትተው መሄድ ተፈታታኝ የሚሆንባቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት) *

5. የአገልግሎት ምድባችን መለወጡ ምን ሊያስከትል ይችላል?

5 የምናገለግለው መስክ ላይም ሆነ ቤቴል ውስጥ፣ በምድባችን ላይ ላሉት ሰዎች ሌላው ቀርቶ ለምናገለግልበት ቦታ ጭምር ፍቅር ቢኖረን አያስገርምም። ስለዚህ በሆነ ምክንያት ምድባችንን መተው ቢያስፈልገን በእጅጉ ማዘናችን አይቀርም። በምድባችን ላይ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ይናፍቁናል፤ በተለይ ደግሞ ምድባችንን ትተን የሄድነው በስደት ምክንያት ከሆነ የእነሱ ሁኔታ ያሳስበናል። (ማቴ. 10:23፤ 2 ቆሮ. 11:28, 29) ከዚህም ሌላ በማናውቀው አካባቢ እንድናገለግል ስንመደብ ወይም ወደ ትውልድ አገራችን ተመልሰን ስንሄድ እንኳ የባሕል ለውጥ ሊያጋጥመን ይችላል። ሮበርት እና ሜሪ ጆ እንዲህ ብለዋል፦ “የራሳችንን ባሕልም ሆነ በገዛ ቋንቋችን መስበክ ረስተን ነበር። በገዛ አገራችን የባዕድ አገር ሰዎች የሆንን ያህል ተሰምቶን ነበር።” የአገልግሎት ምድባቸው የተለወጠ አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ ያልተጠበቁ ወጪዎች ያጋጥሟቸው ይሆናል። እነዚህ ክርስቲያኖች ግራ ይጋቡ፣ ስጋት ያድርባቸውና ተስፋ ይቆርጡ ይሆናል። ታዲያ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረባችንና በእሱ መታመናችን አስፈላጊ ነው (ከአንቀጽ 6-7⁠ን ተመልከት) *

6. ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?

6 ወደ ይሖዋ ይበልጥ ቅረቡ። (ያዕ. 4:8) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? “ጸሎት ሰሚ” በሆነው አምላክ በመታመን ነው። (መዝ. 65:2) መዝሙር 62:8 “ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ” ይላል። ይሖዋ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” ይችላል። (ኤፌ. 3:20) ይሖዋ በጸሎታችን ላይ ለይተን የጠየቅነውን ነገር በመስጠት ብቻ አይወሰንም። ለችግሮቻችን መፍትሔ ለመስጠት ሲል በፍጹም ያላሰብነውንና ጨርሶ ያልጠበቅነውን ነገር ሊያደርግልን ይችላል።

7. (ሀ) ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንድንችል ምን ይረዳናል? (ለ) ዕብራውያን 6:10-12 እንደሚያሳየው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን መቀጠላችን ምን ውጤት ይኖረዋል?

7 ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንድትችሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ አንብቡ እንዲሁም አሰላስሉባቸው። ሚስዮናዊ የነበረ አንድ ወንድም “በቀድሞ ምድባችሁ ታደርጉ እንደነበረው የቤተሰብ አምልኮና የስብሰባ ዝግጅት የምታደርጉበት ቋሚ ፕሮግራም ይኑራችሁ” ብሏል። በተጨማሪም በአዲሱ ጉባኤያችሁ ውስጥ በስብከቱ ሥራ የምትችሉትን ያህል መካፈላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ ቀደም ሲል ያደርጉ የነበረውን ያህል ባይሆንም እንኳ እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን የሚቀጥሉ ክርስቲያኖችን አይረሳም።ዕብራውያን 6:10-12ን አንብብ።

8. በ1 ዮሐንስ 2:15-17 ላይ የሚገኘው ሐሳብ አኗኗራችሁን ቀላል ለማድረግ የሚረዳችሁ እንዴት ነው?

8 አኗኗራችሁን ቀላል አድርጉት። የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረው ጭንቀት መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችሁን ‘እንዲያንቀው’ ወይም እንዲገድበው አትፍቀዱ። (ማቴ. 13:22) ይህ ዓለምም ሆነ አሳቢ የሆኑ ወዳጅ ዘመዶቻችሁ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ቁሳዊ ንብረት በማካበት ላይ እንድታተኩሩ ለሚያሳድሩት ተጽዕኖ እጅ አትስጡ። (1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።) በመንፈሳዊ፣ በስሜታዊና በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የሚያስፈልገንን ማንኛውንም እርዳታ “በሚያስፈልገን ጊዜ” ለማሟላት ቃል በገባው በይሖዋ ታመኑ።—ዕብራውያን 4:16፤ 13:5, 6

9. ምሳሌ 22:3, 7 እንደሚያሳየው አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው? ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግስ ምን ሊረዳን ይችላል?

9 አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አትግቡ። (ምሳሌ 22:3, 7ን አንብብ።) ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ያልተጠበቀ ወጪ ሊያስከትል ይችላል፤ በመሆኑም ሳታስቡት ዕዳ ውስጥ ልትገቡ ትችላላችሁ። ዕዳ ውስጥ እንዳትዘፈቁ፣ የማያስፈልጋችሁን ነገር በዱቤ ከመግዛት ተቆጠቡ። የቤተሰባችንን አባል እንደ ማስታመም ያለ ውጥረት የሚፈጥር ሁኔታ ውስጥ ስንሆን፣ ምን ያህል መበደር እንደሚያስፈልገን መወሰን ከባድ ሊሆንብን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ‘ጸሎትና ምልጃ’ ማቅረባችሁ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ እንደሚረዳችሁ አስታውሱ። ይሖዋም ጸሎታችሁን በመስማት “ልባችሁንና አእምሯችሁን” ለመጠበቅ የሚያስችል ሰላም ይሰጣችኋል፤ ይህም ጉዳዩን በተረጋጋ መንፈስ እንድታስቡበት ይረዳችኋል።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ 1 ጴጥ. 5:7

10. አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ምንጊዜም ጥሩ ወዳጆች ይኑሯችሁ። ስሜታችሁንና ያጋጠሟችሁን ነገሮች ለምትቀርቧቸው ወዳጆቻችሁ በተለይ እንደ እናንተ ዓይነት ሁኔታ ላሳለፉ ጓደኞቻችሁ ማካፈላችሁ ይጠቅማችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ ስሜታችሁ እንዲረጋጋ ይረዳችኋል። (መክ. 4:9, 10) በቀድሞው ምድባችሁ ካፈራችኋቸው ጓደኞቻችሁ ጋር ያላችሁ ወዳጅነት እንደማይቋረጥ የታወቀ ነው። በአዲሱ ምድባችሁ ላይ ደግሞ ሌሎች ወዳጆች ያስፈልጓችኋል። ጓደኛ ማግኘት ከፈለጋችሁ እናንተ ራሳችሁ ለሌሎች ጥሩ ጓደኛ መሆን እንዳለባችሁ አስታውሱ። አዳዲስ ጓደኞች ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፋችሁት አስደሳች ሕይወት በመናገር ሌሎች ደስታችሁን እንዲያዩ አድርጉ። አንዳንድ የጉባኤው አባላት ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያላችሁን ፍቅር መረዳት ቢከብዳቸው እንኳ ሌሎች የእናንተ ምሳሌ ሊማርካቸውና ወዳጆቻችሁ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ስላከናወናችኋቸው ነገሮች ብዙ በማውራት ወደ ራሳችሁ ትኩረት እንዳትስቡ ተጠንቀቁ፤ እንዲሁም የተፈጠረባችሁን አሉታዊ ስሜት ከመናገር ተቆጠቡ።

11. ትዳራችሁ አስደሳች ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

11 በአገልግሎት ምድባችሁ ላይ መቀጠል ያልቻላችሁት፣ የትዳር ጓደኛህ የጤና እክል ስለገጠማት ከሆነ ባለቤትህን አትውቀሳት። የጤና እክል ያጋጠመህ አንተ ከሆንክ ደግሞ ለትዳር ጓደኛህ እንቅፋት እንደሆንክባት በማሰብ ራስህን አትውቀስ። “አንድ ሥጋ” እንደሆናችሁና ምንም ዓይነት ነገር ቢያጋጥማችሁ አንዳችሁ ሌላውን ለመንከባከብ በይሖዋ ፊት ቃል እንደገባችሁ አትዘንጉ። (ማቴ. 19:5, 6) አገልግሎታችሁን ያቆማችሁት ባልታቀደ እርግዝና ምክንያት ከሆነ ደግሞ ልጃችሁን ከአገልግሎት ምድባችሁ ይበልጥ ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቱት አረጋግጡለት። ከይሖዋ እንዳገኛችሁት “ስጦታ” አድርጋችሁ እንደምታዩት ለልጃችሁ ንገሩት። (መዝ. 127:3-5) በሌላ በኩል ደግሞ በአገልግሎት ምድባችሁ ላይ ያገኛችኋቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች አካፍሉት። ይህን ማድረጋችሁ ልጃችሁም ልክ እንደ እናንተ ሕይወቱን ይሖዋን ለማገልገል እንዲጠቀምበት ሊያነሳሳው ይችላል።

ሌሎች ምን እርዳታ ማበርከት ይችላሉ?

12. (ሀ) በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖች በአገልግሎት ምድባቸው ላይ እንዲቀጥሉ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አዲሱን ምድብ መልመድ ቀላል እንዲሆንላቸው ምን ማድረግ እንችላለን?

12 ደስ የሚለው ነገር፣ በርካታ ጉባኤዎችና ወንድሞች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖች በአገልግሎት ምድባቸው ላይ እንዲቀጥሉ ለመርዳት የቻሉትን ያህል ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቹ በአገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ በማበረታታት፣ በገንዘብ ወይም በሌሎች ቁሳዊ ነገሮች እነሱን በመደገፍ፣ የሚያገለግሉት ራቅ ባለ ቦታ ከሆነ ደግሞ የቤተሰባቸውን አባላት በመንከባከብ ነው። (ገላ. 6:2) በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይካፈሉ የነበሩ ወንድሞች በጉባኤያችሁ እንዲያገለግሉ ከተመደቡ፣ ምድባቸው የተለወጠው የሆነ ጥፋት ስለሠሩ ወይም ተግሣጽ ስለተሰጣቸው እንደሆነ አድርጋችሁ አታስቡ። * ከዚህ ይልቅ ለውጡን መልመድ ቀላል እንዲሆንላቸው እርዷቸው። ሞቅ አድርጋችሁ ተቀበሏቸው፤ እንዲሁም በጤንነታቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት ማድረግ የሚችሉት ነገር ውስን ቢሆንም እንኳ ያከናወኑትን አገልግሎት እንደምታደንቁ ግለጹላቸው። ከእነሱ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ጥረት አድርጉ። ካካበቱት እውቀት፣ ካገኙት ሥልጠና እንዲሁም ከተሞክሯቸው ትምህርት ለማግኘት ሞክሩ።

13. አዲስ ምድብ የተሰጣቸውን ክርስቲያኖች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

13 በአዲስ ምድብ እንዲያገለግሉ የተመደቡ ክርስቲያኖች መኖሪያ ቤት፣ መጓጓዣ፣ ሥራ እና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት መጀመሪያ ላይ የእናንተ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ከዚህም ሌላ ግብር ከመክፈል ወይም ከሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዘ ወቅታዊ መረጃ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ከምንም በላይ የሚፈልጉት ግን ያሉበትን ሁኔታ እንድትረዱላቸው ነው። እነሱ ራሳቸው ወይም የቤተሰባቸው አባል የጤና እክል አጋጥሟቸው ሊሆን ይችላል። የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው በሐዘን ተደቁሰው ሊሆን ይችላል። * በተጨማሪም ለሌሎች ባይናገሩትም እንኳ በቀድሞ የአገልግሎት ምድባቸው ያፈሯቸው ወዳጆቻቸው ናፍቆት ያስቸግራቸው ይሆናል። እንዲህ ያሉትን ግራ የሚያጋቡ ስሜቶች መቋቋም ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

14. አንዲት እህት አዲሱን ምድቧን እንድትለምደው የጉባኤዋ አስፋፊዎች የረዷት እንዴት ነው?

14 እናንተ የምታደርጉላቸው ድጋፍና ጥሩ ምሳሌነታችሁ አዲሱን ምድባቸውን ለመልመድ ይረዳቸዋል። በሌላ አገር ለበርካታ ዓመታት ያገለገለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በቀድሞ የአገልግሎት ምድቤ ላይ በየቀኑ ብዙ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠና ነበር። በአዲሱ ምድቤ ላይ ግን በአገልግሎት ላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብ ወይም ቪዲዮ ማሳየት እንኳ ብርቅ ነበር። በጉባኤዬ ያሉት አስፋፊዎች ተመላልሶ መጠየቅ ወይም ጥናት ሲኖራቸው ይጋብዙኛል። እነዚህ ቀናተኛና ደፋር ወንድሞችና እህቶች፣ እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ሲመሩ ማየቴ አዎንታዊ አመለካከት እንዳዳብር ረድቶኛል። በአዲሱ ምድቤ በአገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር የሚቻልበትን መንገድ ተማርኩ። ይህ ሁሉ እንደገና ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል።”

አቅማችሁ የሚፈቅደውን ማድረጋችሁን ቀጥሉ!

በትውልድ አገራችሁ አገልግሎታችሁን ማስፋት የምትችሉባቸውን መንገዶች ፈልጉ (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. በአዲሱ ምድባችሁ ላይ ውጤታማ መሆን የምትችሉት እንዴት ነው?

15 በአዲሱ ምድባችሁ ላይ ውጤታማ መሆን ትችላላችሁ። የአገልግሎት ምድባችሁ የተለወጠው በቀድሞ ምድባችሁ ላይ በደንብ ስላልሠራችሁ ወይም ያን ያህል ጠቃሚ ስላልሆናችሁ እንደሆነ አታስቡ። ይሖዋ በሕይወታችሁ ውስጥ እያደረገላችሁ ያለውን ነገር አስተውሉ፤ እንዲሁም መስበካችሁን ቀጥሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ታማኝ ክርስቲያኖች ምሳሌ ተከተሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች “በሄዱበት ቦታ ሁሉ የአምላክን ቃል ምሥራች [ሰብከዋል]።” (ሥራ 8:1, 4) እናንተም መስበካችሁን ከቀጠላችሁ ጥሩ ውጤት ልታገኙ ትችላላችሁ። አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ከአንድ አገር እንዲወጡ የተደረጉ የተወሰኑ አቅኚዎች ወደ ጎረቤት አገር ሄዱ፤ በዚያም የእነሱን ቋንቋ የሚናገሩ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች አገኙ። በዚህም የተነሳ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ ፈጣን እድገት የሚያደርጉ ቡድኖች መቋቋም ችለዋል።

16. በአዲሱ ምድባችሁ ላይ ደስታ ለማግኘት ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

16 “የይሖዋ ደስታ ብርታታችሁ” ነው። (ነህ. 8:10 ግርጌ) የአገልግሎት ምድባችንን በጣም ብንወደውም እንኳ ከምንም በላይ የሚያስደስተን ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና እንጂ ምድባችን መሆን የለበትም። ስለዚህ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና ጠብቃችሁ ኑሩ፤ እንዲሁም ጥበብ፣ መመሪያና እርዳታ ለማግኘት በእሱ መታመናችሁን ቀጥሉ። የቀድሞ የአገልግሎት ምድባችሁን እንድትወዱት ያደረጋችሁ እዚያ ያሉትን ሰዎች ለመርዳት ከልባችሁ ጥረት ማድረጋችሁ እንደሆነ አስታውሱ። በአዲሱ የአገልግሎት ምድባችሁም ከልባችሁ ለመሥራት ጥረት አድርጉ፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ አዲሱን ምድባችሁንም እንድትወዱት እንደሚረዳችሁ ማየት ትችላላችሁ።—መክ. 7:10

17. በአሁኑ ጊዜ ከተሰጠን ምድብ ጋር በተያያዘ ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

17 ይሖዋን የምናገለግለው ለዘላለም እንደሆነ፣ አሁን ያለን ምድብ ግን ጊዜያዊ እንደሆነ እናስታውስ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሁላችንም አሁን ካለን የተለየ የአገልግሎት ምድብ ሊሰጠን ይችላል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው አሌክሴይ፣ አሁን ያጋጠመው ሁኔታ ለዚያ ጊዜ እያዘጋጀው እንደሆነ ይሰማዋል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋና አዲሱ ዓለም እውን እንደሆኑ ቀድሞውንም ቢሆን አውቅ ነበር። ይሖዋ ፊት ለፊቴ ያለ ያህል እውን የሆነልኝና አዲሱ ዓለም በጣም ቅርብ እንደሆነ የተሰማኝ ግን አሁን ነው።” (ሥራ 2:25) አዲሱ ምድባችን የትም ይሁን የት ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን እንኑር። ይሖዋ በፍጹም አይተወንም፤ እንዲያውም የተመደብነው የትም ይሁን የት፣ በእሱ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል።—ኢሳ. 41:13

መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ

^ አን.5 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ይህን አገልግሎታቸውን ለማቆም የሚገደዱበት ጊዜ አለ፤ አሊያም ደግሞ አዲስ ምድብ ይሰጣቸው ይሆናል። ይህ ርዕስ እነዚህ ክርስቲያኖች ስለሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ምን ሊረዳቸው እንደሚችል ያብራራል። በተጨማሪም ሌሎች እንዴት ሊያበረታቷቸውና ሊደግፏቸው እንደሚችሉ እናያለን፤ ከዚህም ሌላ ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን ለውጦች ጋር ለመላመድ የሚረዱንን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመለከታለን።

^ አን.4 በተመሳሳይም በኃላፊነት ቦታ ላይ ያገለግሉ የነበሩ በርካታ ወንድሞች የተወሰነ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ኃላፊነታቸውን በዕድሜ ከእነሱ ለሚያንሱ ወንድሞች አስረክበዋል። በመስከረም 2018 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አረጋውያን ክርስቲያኖች—ይሖዋ ታማኝነታችሁን ከፍ አድርጎ ይመለከታል” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በጥቅምት 2018 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ሁኔታዎች ቢለዋወጡም ውስጣዊ ሰላማችሁን ጠብቃችሁ ኑሩ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.12 የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቹ በነበሩበት ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች በተቻለ ፍጥነት፣ እነዚህ ክርስቲያኖች ወደተመደቡበት ጉባኤ የማስተዋወቂያ ደብዳቤ መጻፍ አለባቸው፤ ይህን ማድረጋቸው እነዚህ ክርስቲያኖች ወደ አዲሱ ጉባኤ እንደሄዱ አቅኚ፣ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል።

^ አን.13 በ2018 ንቁ! ቁጥር 3 ላይ “ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ” በሚል ዋና ርዕስ ሥር የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሚስዮናውያን ሆነው ከሚያገለግሉበት አገር መውጣት ግድ የሆነባቸው አንድ ባልና ሚስት ጉባኤያቸውን በእንባ ሲሰናበቱ።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ እነዚህ ባልና ሚስት ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም እንዲረዳቸው ይሖዋን አጥብቀው ሲለምኑ።

^ አን.61 የሥዕሉ መግለጫ፦ ባልና ሚስቱ በይሖዋ እርዳታ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መመለስ ቻሉ። ሚስዮናውያን ሳሉ የተማሩትን ቋንቋ በመጠቀም በአዲሱ ጉባኤያቸው ክልል ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች ምሥራቹን ሲሰብኩ።