በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 40

“በመጨረሻዎቹ ቀናት” መጨረሻ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ

“በመጨረሻዎቹ ቀናት” መጨረሻ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ

“ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ፤ . . . ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።”—1 ቆሮ. 15:58

መዝሙር 58 ሰላም ወዳዶችን መፈለግ

ማስተዋወቂያ *

1. የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” እንደሆነ እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው?

የተወለድከው ከ1914 ወዲህ ነው? ከሆነ ሕይወትህን ሙሉ የኖርከው በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) ሁላችንም፣ ኢየሱስ ይህን ዘመን አስመልክቶ በትንቢት የተናገራቸው ክንውኖች እየተፈጸሙ እንዳለ እየሰማን ነው። ከእነዚህ ክንውኖች መካከል ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ የምድር ነውጥ፣ ቸነፈር፣ ክፋት እየበዛ መሄዱ እና በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የሚደርስ ስደት ይገኙበታል። (ማቴ. 24:3, 7-9, 12፤ ሉቃስ 21:10-12) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች ስለሚኖራቸው ባሕርይ የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም ተመልክተናል። (“ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሰዎች ባሕርይ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በመሆኑም እኛ የይሖዋ አገልጋዮች፣ የምንኖረው “በዘመኑ መጨረሻ” እንደሆነ እርግጠኞች ነን።—ሚክ. 4:1

2. የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ያስፈልገናል?

2 ከ1914 ወዲህ በርካታ ዓመታት ስላለፉ አሁን የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” መጨረሻ ላይ መሆን አለበት። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም ከመቅረቡ አንጻር የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን አስፈላጊ ነው፦ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ማብቂያ ላይ የትኞቹ ክንውኖች ይፈጸማሉ? እነዚህን ክንውኖች እየተጠባበቅን ባለንበት በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

“በመጨረሻዎቹ ቀናት” ማብቂያ ላይ ምን ይከናወናል?

3. በ1 ተሰሎንቄ 5:1-3 ላይ በሚገኘው ትንቢት መሠረት ብሔራት ምን ብለው ያውጃሉ?

3 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:1-3ን አንብብ። ጳውሎስ ስለ “ይሖዋ ቀን” ተናግሯል። “የይሖዋ ቀን” የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው፣ ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ (በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ታመለክታለች) ላይ በሚሰነዘረው ጥቃት ጀምሮ በአርማጌዶን የሚደመደመውን ጊዜ ነው። (ራእይ 16:14, 16፤ 17:5) ይህ “ቀን” ከመጀመሩ ትንሽ ቀደም ብሎ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ብለው ያውጃሉ። (አንዳንድ ትርጉሞች “ሰላምና መረጋጋት ሆነ” ብለው ያስቀምጡታል።) አንዳንድ ጊዜ የዓለም መሪዎች በአገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ስለ ማሻሻል ሲናገሩ እንደነዚህ ያሉ አገላለጾችን ይጠቀማሉ። * ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚለው አዋጅ ከዚህ የተለየ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይህ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት ብዙ ሰዎች፣ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ የዓለም መሪዎች እንደተሳካላቸው ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በዚያ ወቅት ‘ታላቁ መከራ’ ስለሚጀምር “ያልታሰበ ጥፋት” ይመጣል።—ማቴ. 24:21

“ሰላምና ደህንነት ሆነ!” በሚለው የመንግሥታት አዋጅ አትታለሉ (ከአንቀጽ 3-6⁠ን ተመልከት) *

4. (ሀ) “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ከሚለው አዋጅ ጋር በተያያዘ የማናውቀው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ከዚህ አዋጅ ጋር በተያያዘ የምናውቀው ነገርስ ምንድን ነው?

4 “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ከሚለው አዋጅ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የምናውቃቸው ነገሮች አሉ። ሆኖም የማናውቃቸው ነገሮችም አሉ። ይህ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች ወይም አዋጁ የሚታወጅበትን መንገድ አናውቅም። አዋጁ የሚተላለፈው በአንድ ማስታወቂያ አማካኝነት ነው? ወይስ በተከታታይ በሚነገሩ መግለጫዎች? ይህን በተመለከተም የምናውቀው ነገር የለም። በዚያ ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ የዓለም መሪዎች በእርግጥ ዓለም አቀፍ ሰላም እንዳስገኙ በማሰብ መታለል እንደሌለብን ግን በሚገባ እናውቃለን። እንዲያውም በንቃት እንድንከታተል የተነገረን ይህንን አዋጅ መሆኑን እናስታውስ። ይህ አዋጅ መነገሩ “የይሖዋ ቀን” ሊጀምር መሆኑን የሚጠቁም ምልክት ነው!

5. አንደኛ ተሰሎንቄ 5:4-6 ‘ለይሖዋ ቀን’ እንድንዘጋጅ የሚረዳን እንዴት ነው?

5 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:4-6ን አንብብ። የጳውሎስ ማሳሰቢያ ‘ለይሖዋ ቀን’ ዝግጁ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለብን ይጠቁመናል። ‘እንደ ሌሎቹ ማንቀላፋት’ የለብንም። እንዲያውም ‘ነቅተን መኖር’ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ በመግባት የገለልተኝነት አቋማችንን እንዳናላላ ንቁ መሆን ይኖርብናል። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ የምንሳተፍ ከሆነ “የዓለም ክፍል” እንሆናለን። (ዮሐ. 15:19) በዓለም ላይ ሰላም ሊያሰፍን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እናውቃለን።

6. ሰዎች ምን እንዲያደርጉ መርዳት እንፈልጋለን? ለምንስ?

6 እኛ ራሳችን ነቅተን ከመኖር በተጨማሪ ሌሎች እንዲነቁና መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ እንደሚፈጸሙ ስለተናገራቸው ክንውኖች እንዲያውቁ መርዳትም እንፈልጋለን። ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ፣ ሰዎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ የተከፈተላቸው አጋጣሚ እንደሚዘጋ እናስታውስ። የስብከቱ ሥራችን በጣም አጣዳፊ የሆነው ለዚህ ነው! *

በስብከቱ ሥራ ተጠመዱ

በዛሬው ጊዜ በስብከቱ ሥራ ስንካፈል፣ በዓለም ላይ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ሊያሰፍን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን እንናገራለን (ከአንቀጽ 7-9⁠ን ተመልከት)

7. ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

7 “የይሖዋ ቀን” ከመጀመሩ በፊት በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ ይሖዋ በስብከቱ ሥራ እንድንጠመድ ይጠብቅብናል። “የጌታ ሥራ [የበዛልን]” ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 15:58) ኢየሱስ ስለምናከናውነው ሥራ አስቀድሞ ተናግሯል። በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚኖሩት ወሳኝ ክንውኖች በተናገረበት ወቅት “አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት” ብሎ ነበር። (ማር. 13:4, 8, 10፤ ማቴ. 24:14) እስቲ አስበው፣ አገልግሎት በወጣህ ቁጥር ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አስተዋጽኦ እያደረግክ ነው!

8. የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

8 በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ስለተገኘው ስኬት ምን ማለት ይቻላል? ይህ ሥራ ከዓመት ወደ ዓመት የበለጠ ውጤት እያስገኘ ነው። በመጨረሻዎቹ ቀናት በዓለም ዙሪያ ካሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ጋር በተያያዘ የተገኘውን ጭማሪ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በ1914 በ43 አገራት የሚያገለግሉ 5,155 አስፋፊዎች ነበሩ። በዛሬው ጊዜ ግን በ240 አገራት ውስጥ 8.5 ሚሊዮን አስፋፊዎች አሉ! ያም ቢሆን ሥራችን ገና አልተጠናቀቀም። ለሰው ልጆች ችግሮች በሙሉ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን ማወጃችንን መቀጠል አለብን።—መዝ. 145:11-13

9. የመንግሥቱን መልእክት መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

9 የመንግሥቱ የስብከት ሥራችን ይሖዋ በቃ እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል። ለመሆኑ ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ ክፍት ሆኖ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? (ዮሐ. 17:3) ይህን ማወቅ አንችልም። ሆኖም ታላቁ መከራ እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ፣ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን ሰምተው የአምላክ አገልጋይ የመሆን አጋጣሚ እንደሚኖራቸው እናውቃለን። (ሥራ 13:48) ታዲያ እነዚህን ሰዎች ጊዜው ከማለቁ በፊት ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

10. ይሖዋ ለሰዎች እውነትን ለማስተማር የሚረዳን ምን ዝግጅት አድርጎልናል?

10 ይሖዋ ለሰዎች እውነትን ለማስተማር የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ በድርጅቱ በኩል እያቀረበልን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሳምንቱ መሃል ስብሰባ አማካኝነት በየሳምንቱ ሥልጠና እናገኛለን። ለሰዎች ስንመሠክርና ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ምን ማለት እንዳለብን በዚህ ስብሰባ ላይ እንማራለን። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንሠለጥናለን። የይሖዋ ድርጅት፣ የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን በተባለው ክፍል ውስጥ የሚገኙትን ጽሑፎችና ቪዲዮዎችም አዘጋጅቶልናል። እነዚህ መሣሪያዎች የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ይጠቅሙናል፦

  • ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመር፣

  • መልእክታችንን ትኩረት በሚስብ መንገድ ለማቅረብ፣

  • ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር እንዲጓጉ ለማድረግ፣

  • የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለጥናቶቻችን ለማስተማር እንዲሁም

  • ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ድረ ገጻችንን እንዲጎበኙና ወደ ስብሰባ አዳራሻችን እንዲመጡ ለመጋበዝ።

እርግጥ ነው፣ እነዚህ መሣሪያዎች በእጃችን መኖራቸው ብቻ በቂ አይደለም። ልንጠቀምባቸው ይገባል። * ለምሳሌ፣ ፍላጎት ካሳየ አንድ ሰው ጋር ጥሩ ውይይት ካደረግን በኋላ ትራክት ወይም መጽሔት ሰጥተነው ከሄድን ግለሰቡ በቀጣዩ ጊዜ እስክንገናኝ ድረስ ጽሑፉን እያነበበው ሊቆይ ይችላል። እያንዳንዳችን በየወሩ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ የመጠመድ ኃላፊነት አለብን።

11. “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በኢንተርኔት” የሚለው ዓምድ የተዘጋጀው ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ እየረዳ ያለበት ሌላው መንገድ ደግሞ jw.org® ላይ የሚወጣው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በኢንተርኔት የሚለው ዓምድ ነው። * ይህ ዓምድ የተዘጋጀው ለምንድን ነው? በየወሩ፣ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለማግኘት ሲሉ ኢንተርኔት ይቃኛሉ። በድረ ገጻችን ላይ የሚገኙት ትምህርቶች፣ እነዚህ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዲያውቁ ሊረዷቸው ይችላሉ። ምሥራቹን ከምትሰብኩላቸው ሰዎች አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የሚቀርብላቸውን ግብዣ ለመቀበል ያመነቱ ይሆናል። ከሆነ በድረ ገጻችን ላይ የሚገኘውን ይህን ዓምድ አሳዩዋቸው ወይም ሊንኩን ላኩላቸው።

12. “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በኢንተርኔት” የሚለው ዓምድ የትኞቹን ትምህርቶች ይዟል?

12 “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በኢንተርኔት” በተባለው ዓምድ ላይ ከተካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል “መጽሐፍ ቅዱስ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት፣” “የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዋና ባለታሪኮች” እና “መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ተስፋ” የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህ ርዕሶች የሚከተሉትን ትምህርቶች ይዘዋል፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ

  • የይሖዋን፣ የኢየሱስንና የመላእክትን ማንነት

  • አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረበትን ዓላማ

  • መከራና ክፋት የኖረው ለምን እንደሆነ

በተጨማሪም ይህ ዓምድ ይሖዋ . . .

  • መከራንና ሞትን የሚያስወግደው

  • ሙታንን የሚያስነሳው እንዲሁም

  • የሰው ልጆችን ችግሮች መፍታት ያልቻሉትን ሰብዓዊ መንግሥታት አጥፍቶ የራሱን መንግሥት የሚያቋቁመው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

13. በኢንተርኔት የሚሰጠው ትምህርት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት አሁን የምንጠቀምበትን ዝግጅት ያስቀረዋል? አብራራ።

13 “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በኢንተርኔት” የሚለው ዓምድ፣ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት አሁን የምንጠቀምበትን ዝግጅት አያስቀረውም። ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የማድረግ መብት ሰጥቶናል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ኢንተርኔት ላይ የሚወጡትን ትምህርቶች ከተመለከቱ በኋላ እነዚህን ትምህርቶች እንደሚወዷቸውና የበለጠ ለማወቅ እንደሚነሳሱ ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ጋር እንዲያጠኑ የሚቀርብላቸውን ግብዣ ለመቀበል ያነሳሳቸው ይሆናል። በእያንዳንዱ ትምህርት መጨረሻ ላይ፣ አንባቢው መጽሐፍ ቅዱስን በግለሰብ ደረጃ የሚያስጠናው ሰው መጠየቅ የሚችልበት ዝግጅት እንዳለ ተገልጿል። በዓለም ዙሪያ በየቀኑ በአማካይ ከ230 የሚበልጡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በድረ ገጻችን አማካኝነት ጥያቄ ያቀርባሉ! በእርግጥም ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት እስካሁን ስንጠቀምበት የቆየነው ዝግጅት አሁንም አስፈላጊ ነው!

ደቀ መዛሙርት ለማድረግ መጣራችሁን ቀጥሉ

14. ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ምን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል? ለምንስ?

14 ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች፣ ኢየሱስ ‘ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ ለማስተማርና ደቀ መዛሙርት’ እንዲሆኑ ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ያህል መጣር ይኖርብናል። ሰዎች ከይሖዋና ከእሱ መንግሥት ጎን መቆማቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ መርዳት አለብን። ይህም የተማሩትን ነገር በተግባር ለማዋል እንዲሁም ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው ለመጠመቅ እንዲነሳሱ መርዳትን ይጠይቃል። ከይሖዋ ቀን መትረፍ የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው።—1 ጴጥ. 3:21

15. ምን ለማድረግ ጊዜ የለንም? ለምንስ?

15 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም ቀርቧል። ከዚህ አንጻር የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመሆን ዓላማ የሌላቸውን ሰዎች ለማስጠናት የሚሆን ጊዜ የለንም። (1 ቆሮ. 9:26) ሥራችን አጣዳፊ ነው! ጊዜው ከማለቁ በፊት የመንግሥቱን መልእክት መስማት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች አሉ።

ከሐሰት ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ ራቁ

16. ራእይ 18:2, 4, 5, 8 እንደሚገልጸው ሁላችንም ምን ማድረግ ይኖርብናል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

16 ራእይ 18:2, 4, 5, 8ን አንብብ። ይህ ጥቅስ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀውን ሌላ ነገር ይጠቁመናል። ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖራቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ እውነትን መማር ከመጀመሩ በፊት የሐሰት ሃይማኖት አባል ሊሆን ይችላል። በዚያ ሃይማኖት የአምልኮ ፕሮግራሞች ላይ ይገኝ ወይም በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ይሳተፍ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ለድርጅቱ ገንዘብ ያዋጣ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል እንዲፈቀድለት ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ይኖርበታል። ቀድሞ ወደነበረበት የሃይማኖት ድርጅት የመልቀቂያ ደብዳቤ መላክ ወይም ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ አለበት፤ ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ንክኪ ያለው የማንኛውም ድርጅት አባል ከሆነም ይህን ማቋረጥ አለበት። *

17. ክርስቲያኖች ከሰብዓዊ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል? ለምንስ?

17 አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሰብዓዊ ሥራው ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር የሚያነካካው እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት። (2 ቆሮ. 6:14-17) ለምሳሌ ያህል፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀጥሮ አይሠራም። በሌላ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ ክርስቲያን ደግሞ ለሐሰት አምልኮ በሚውል ሕንፃ ውስጥ መጠነ ሰፊ ሥራ ለማከናወን ፈቃደኛ አይሆንም። የራሱን ሥራ የሚሠራ ከሆነም፣ የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ለሆነ ለየትኛውም ድርጅት ሥራ ለመሥራት አይጫረትም ወይም እንደዚህ ካለው ድርጅት ጋር የሥራ ውል አይፈጽምም። እንዲህ ያለ ጥብቅ አቋም የምንይዘው ለምንድን ነው? አምላክ ርኩስ እንደሆኑ አድርጎ በሚመለከታቸው ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ሥራም ሆነ ኃጢአት ተባባሪ መሆን ስለማንፈልግ ነው።—ኢሳ. 52:11 *

18. አንድ ወንድም ከሰብዓዊ ሥራው ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደሚያከብር ያሳየው እንዴት ነው?

18 ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ የራሱን ሥራ የሚሠራ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እሱ በሚኖርበት ከተማ ውስጥ ለሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ከአናጺነት ጋር የተያያዘ አነስተኛ ሥራ እንዲያከናውን ጥያቄ ቀረበለት። ይህን ጥያቄ ያቀረበው የሕንፃ ተቋራጭ፣ ይህ ወንድም ከቤተ ክርስቲያን ጋር የተያያዘ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። በዚያ ወቅት ግን የሕንፃ ተቋራጩ ሥራውን የሚሠራለት ሌላ ሰው ለማግኘት ተቸግሮ ነበር። ያም ቢሆን ወንድማችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በማክበር፣ ሥራውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ገለጸ። በቀጣዩ ሳምንት፣ ሌላ አናጺ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ መስቀል ሲሰቅል የሚያሳይ ፎቶግራፍ በአካባቢው በሚታተም ጋዜጣ ላይ ወጣ። ወንድማችን አቋሙን አላልቶ ቢሆን ኖሮ ጋዜጣው ላይ የሚወጣው የእሱ ፎቶግራፍ ይሆን ነበር። ይህ ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቹ ስለ እሱ ባላቸው አመለካከት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስበው! ይሖዋስ ምን ይሰማው ነበር?

ምን ትምህርት አግኝተናል?

19-20. (ሀ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን ትምህርት አግኝተናል? (ለ) ስለ የትኞቹ ነገሮች ማወቅ ያስፈልገናል?

19 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ከዚህ በኋላ በዓለም ላይ የሚፈጸመው ታላቅ ክንውን ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚለውን አዋጅ ማወጃቸው ነው። እኛ ግን ይሖዋ አስቀድሞ ስላስተማረን ብሔራት እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ሊያስገኙ እንደማይችሉ አውቀናል። ከዚህ አዋጅና አዋጁን ተከትሎ ከሚመጣው ድንገተኛ ጥፋት በፊት ምን እንድናደርግ ይጠበቅብናል? ይሖዋ የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድንጠመድ ይጠብቅብናል። ከዚህም ሌላ ከማንኛውም የሐሰት ሃይማኖት መራቅ ይኖርብናል። ይህም ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች አባል ከመሆንና ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር የሚያገናኝ ሥራ ከመሥራት መቆጠብን ይጨምራል።

20 “በመጨረሻዎቹ ቀናት” መጨረሻ ላይ “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚለውን አዋጅ ተከትለው የሚፈጸሙ ሌሎች ክንውኖች ይኖራሉ። ይሖዋ እንድናደርግ የሚጠብቅብን ሌሎች ነገሮችም አሉ። የሚፈጸሙት ክንውኖችና ይሖዋ የሚጠብቅብን ነገሮች የትኞቹ ናቸው? በቅርቡ ለሚፈጸሙት ነገሮች ለመዘጋጀት ምን ማድረግ እንችላለን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

መዝሙር 71 የይሖዋ ሠራዊት ነን!

^ አን.5 በቅርቡ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ብለው እንደሚያውጁ እንጠብቃለን። ይህ አዋጅ፣ ታላቁ መከራ ሊጀምር መሆኑን የሚጠቁም ምልክት ነው። ታዲያ ይህ አዋጅ እስኪነገር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል? በዚህ ርዕስ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እናገኛለን።

^ አን.3 ለምሳሌ ያህል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመበት ዓላማ ‘በዓለም ዙሪያ ሰላምና ደህንነት ማስፈን’ እንደሆነ በድረ ገጹ ላይ ተገልጿል።

^ አን.6 በዚህ እትም ላይ የወጣውን “አምላክ የፍርድ እርምጃ ሲወስድ ሁልጊዜ በቂ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.10 በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የተካተቱትን ነገሮች እንዴት መጠቀም እንደምንችል ሰፋ ያለ ሐሳብ ለማግኘት በጥቅምት 2018 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “እውነትን አስተምሩ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.11 ይህ ዓምድ በአሁኑ ወቅት የሚገኘው በእንግሊዝኛ እና በፖርቱጋልኛ ነው፤ ወደፊት በሌሎች ቋንቋዎችም ይኖራል።

^ አን.16 በተጨማሪም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ያላቸው የወጣቶች የመዝናኛ ክለቦችና ሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎች አባል መሆን የለብንም። ወወክማ (የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር) እና ወሴክማ (የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማኅበር) የተባሉትን ማኅበራት ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በአካባቢያችን ያሉት የወወክማ እና የወሴክማ ማኅበራት፣ እንቅስቃሴያቸው ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ይገልጹ ይሆናል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ድርጅቶቹ ሃይማኖታዊ አመለካከቶችንና ግቦችን የሚያራምዱ ናቸው።

^ አን.17 ከሃይማኖታዊ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በተመለከተ ሰፋ ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

^ አን.83 የሥዕሉ መግለጫ፦ በአንድ ካፌ ውስጥ የሚስተናገዱ ሰዎች “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ተብሎ እንደታወጀ የሚገልጸውን ሰበር ዜና ቴሌቪዥን ላይ በትኩረት ሲከታተሉ። ከአገልግሎት በኋላ አረፍ ለማለት ወደ ካፌው የገቡ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ግን በዚህ ዜና አልተታለሉም።