በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያናዊ ሕይወት

ለአምላክና ለባልንጀራችን ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

ለአምላክና ለባልንጀራችን ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም አምላክንና ባልንጀራችንን እንድንወድ የሚያዝዙት በሕጉ ውስጥ የሚገኙት ሁለት ታላላቅ ትእዛዛት ይሖዋ ከእኛ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ጠቅለል አድርገው ይገልጻሉ። (ማቴ 22:37-39) ይህ ዓይነቱ ፍቅር እንዲሁ በራሱ ሊመጣ ስለማይችል ይህን ፍቅር ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። እንዴት? አንዱ ወሳኝ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ነው። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የአምላክ ባሕርያት የተንጸባረቁባቸውን የተለያዩ መንገዶች እያወቅን በሄድን መጠን “ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን” እየተረዳን እንሄዳለን። (መዝ 27:4) በውጤቱም ለእሱ ያለን ፍቅር የሚያድግ ከመሆኑም ሌላ አስተሳሰባችን ከእሱ አስተሳሰብ ጋር ይበልጥ እየተመሳሰለ ይሄዳል። ይህም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ፍቅር እንድናሳይ የተሰጠንን ትእዛዝ ጨምሮ ሁሉንም የአምላክ ትእዛዛት እንድንጠብቅ ያነሳሳናል። (ዮሐ 13:34, 35፤ 1ዮሐ 5:3) የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች ማድረግህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ይረዳሃል፦

  • ዘገባውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል እንዲሁም የስሜት ሕዋሳትህን ለመጠቀም ሞክር። ራስህን በቦታው እንዳለህ አድርገህ አስብ። በአካባቢው የነበረውን ሁኔታ ለማየት፣ ድምፆቹን ለመስማት፣ መዓዛውን ለማሽተት እንዲሁም የባለታሪኮቹን ስሜት ለመረዳት ሞክር።

  • የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቀም። የሚከተሉትን ዘዴዎች መጠቀም ይቻላል፦ ጮክ ብሎ ማንበብ ወይም በድምፅ የተቀዳውን ንባብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥቶ መከታተል። መጽሐፍ ቅዱስን መደዳውን ከማንበብ ይልቅ በአንድ ባለታሪክ ወይም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ ማንበብ። ለምሳሌ ያህል፣ አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ መረጃ ሀ7 ወይም ለ12 ተጠቅሞ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ ዘገባዎችን ማንበብ ይቻላል። የዕለቱን ጥቅስ ስናነብ ጥቅሱ የተወሰደበትን ሙሉውን ምዕራፍ ማንበብ። የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት በተጻፉበት የጊዜ ቅደም ተከተል ማንበብ።

  • የምታነበውን ለመረዳት ሞክር። ላይ ላዩን በማንበብ ብዙ ምዕራፎችን ከመሸፈን ይልቅ አንድ ምዕራፍ ብቻ አንብቦ በዚያ ላይ ማሰላሰልና ሐሳቡን ለመረዳት ጥረት ማድረግ የተሻለ ነው። መቼቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክር። ከዘገባው ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማገናዘብ ጥረት አድርግ። ካርታዎችንና የኅዳግ ማጣቀሻዎችን ተጠቀም። ግልጽ ካልሆኑልህ ነገሮች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ምርምር አድርግ። የሚቻል ከሆነ ለማንበብ የወሰደብህን ጊዜ ያህል በማሰላሰልም ለማሳለፍ ሞክር።