በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 1

“ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

“ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

የ2020 የዓመት ጥቅስ፦ ‘ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።’—ማቴ. 28:19

መዝሙር 79 ጸንተው እንዲቆሙ አስተምሯቸው

ማስተዋወቂያ *

1-2. አንድ መልአክ በኢየሱስ መቃብር አጠገብ ያገኛቸውን ሴቶች ምን አላቸው? ኢየሱስ ራሱስ ምን የሚል መመሪያ ሰጣቸው?

ዕለቱ ኒሳን 16, 33 ዓ.ም. ነው። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው የተወሰኑ ሴቶች ጎህ ሲቀድ ተነስተው፣ ከ36 ሰዓታት በፊት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አስከሬን ወዳረፈበት የመቃብር ቦታ አመሩ። አስከሬኑን ጥሩ መዓዛ ባላቸው ቅመሞችና ዘይቶች ለመቀባት ተዘጋጅተው የሄዱት እነዚህ ሐዘን የደቆሳቸው ሴቶች መቃብሩ ጋ ሲደርሱ የሚያስገርም ነገር ገጠማቸው፤ መቃብሩ ባዶ ነበር! አንድ መልአክ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ ለሴቶቹ ከነገራቸው በኋላ “ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል። እዚያም ታዩታላችሁ” አላቸው።—ማቴ. 28:1-7፤ ሉቃስ 23:56፤ 24:10

2 ሴቶቹ ከመቃብሩ ቦታ ወጥተው ሲሄዱ ኢየሱስ ራሱ ያገኛቸው ሲሆን “ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል” የሚል መመሪያ ሰጣቸው። (ማቴ. 28:10) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያደረገው የመጀመሪያ ነገር ደቀ መዛሙርቱን ወደዚህ ስብሰባ መጥራት ነው፤ ይህን ያደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ በጣም አስፈላጊ መመሪያዎችን ሊሰጣቸው አስቦ መሆን አለበት።

ትእዛዙ የተሰጠው ለማን ነው?

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ከሐዋርያቱና ከሌሎች ደቀ መዛሙርቱ ጋር በገሊላ ሲገናኝ “ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል (ከአንቀጽ 3-4⁠ን ተመልከት)

3-4. በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ተልእኮ የተሰጠው ለሐዋርያት ብቻ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

3 ማቴዎስ 28:16-20ን አንብብ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለሚያከናውኑት በጣም አስፈላጊ ሥራ በስብሰባው ላይ ነገራቸው፤ ይህ ሥራ በዛሬው ጊዜም እየተከናወነ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”

4 ኢየሱስ ሁሉም ተከታዮቹ እንዲሰብኩ ይፈልጋል። ትእዛዙን የሰጠው ለ11 ታማኝ ሐዋርያቱ ብቻ አይደለም። ይህን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ትእዛዝ በገሊላ በሚገኘው ተራራ ላይ በሰጠበት ወቅት በቦታው የነበሩት ሐዋርያት ብቻ ናቸው? መልአኩ ለሴቶቹ “እዚያም [በገሊላ] ታዩታላችሁ” እንዳላቸው እናስታውስ። ስለዚህ በስብሰባው ላይ ታማኝ ሴቶችም ተገኝተው መሆን አለበት። ይሁንና ሌሎች ሰዎችም ሳይገኙ አይቀሩም። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች” እንደተገለጠ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:6) ይህ የሆነው የት ነው?

5. በ1 ቆሮንቶስ 15:6 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን እንገነዘባለን?

5 ጳውሎስ የተናገረው በማቴዎስ ምዕራፍ 28 ላይ ስለተጠቀሰውና በገሊላ ስለተካሄደው ስብሰባ ነው ብለን ለመደምደም የሚያበቁ ምክንያቶች አሉን። እነዚህ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? አንደኛ፣ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አብዛኞቹ የገሊላ ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም ብዛት ያላቸውን ሰዎች በኢየሩሳሌም በሚገኝ የግለሰብ ቤት ከመሰብሰብ ይልቅ በገሊላ ባለ ተራራ ላይ መሰብሰብ ይበልጥ ምክንያታዊ ይሆናል። ሁለተኛ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ከዚያ ስብሰባ በፊት በኢየሩሳሌም በሚገኝ የግለሰብ ቤት ውስጥ 11 ሐዋርያቱን አግኝቷቸው ነበር። ኢየሱስ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለሐዋርያቱ ብቻ ለመስጠት ቢያስብ ኖሮ ይህን እዚያው ኢየሩሳሌም እያሉ ሊነግራቸው ይችል ነበር፤ ሐዋርያቱን ጨምሮ ሴቶቹንና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱን በገሊላ ወደሚገኝ ተራራ መጥራት አያስፈልገውም ነበር።—ሉቃስ 24:33, 36

6. ማቴዎስ 28:20 ደቀ መዛሙርት ስለ ማድረግ የተሰጠው ትእዛዝ በዛሬው ጊዜም እንደሚሠራ የሚያሳየው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ይህ ሥራ ምን ያህል በስፋት እየተከናወነ ነው?

6 ሌላ ወሳኝ የሆነ ነጥብ ደግሞ እንመልከት። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት ስለ ማድረግ የሰጠው ትእዛዝ የሚመለከተው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን ብቻ አይደለም። ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ለተከታዮቹ መመሪያውን ከሰጣቸው በኋላ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:20) ኢየሱስ እንዳለውም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በዛሬው ጊዜ በስፋት እየተከናወነ ነው። እስቲ አስበው! በየዓመቱ ወደ 300,000 የሚጠጉ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮችና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ!

7. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን? ለምንስ?

7 መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ብዙ ሰዎች እድገት አድርገው ይጠመቃሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ከእኛ ጋር የሚያጠኑ አንዳንድ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያመነቱ ይመስላል። እነዚህ ሰዎች፣ ጥናቱ ቢያስደስታቸውም እድገት አድርገው ለመጠመቅ አይጥሩም። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናው ሰው ካለ ጥናትህ የተማረውን ነገር ተግባራዊ እንዲያደርግና የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን እንዲችል መርዳት እንደምትፈልግ ጥያቄ የለውም። ይህ ርዕስ የጥናታችንን ልብ መንካት እንዲሁም መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። ስለዚህ ጉዳይ መወያየት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘ጥናታችንን እንቀጥል ወይስ እናቁም?’ የሚለውን ጉዳይ መወሰን የሚያስፈልገን ጊዜ ሊኖር ይችላል።

ልባቸውን ለመንካት ጥረት አድርጉ

8. ሰዎች ይሖዋን እንዲወዱት መርዳት ተፈታታኝ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋ የሚፈልገው ሰዎች ለእሱ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው እንዲያገለግሉት ነው። ስለዚህ ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በጥልቅ እንደሚያስብላቸውና በጣም እንደሚወዳቸው እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። ይሖዋን “አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ” እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት መርዳት እንፈልጋለን። (መዝ. 68:5) ጥናቶቻችን አምላክ እንደሚወዳቸው ሲገነዘቡ ልባቸው መነካቱና ለእሱ ያላቸው ፍቅር ማደጉ አይቀርም። እርግጥ ነው፣ ከወላጅ አባታቸው ፍቅር አግኝተው ያላደጉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባት መመልከት ሊከብዳቸው ይችላል። (2 ጢሞ. 3:1, 3) እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ የይሖዋን ማራኪ ባሕርያት ጎላ አድርገህ ለመግለጽ ሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህ፣ አፍቃሪው አምላካችን የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ እንደሚፈልግ እንዲሁም እዚህ ግብ ላይ እንዲደርሱ ሊረዳቸው ዝግጁ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዳቸው። ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን?

9-10. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ የትኞቹን መጻሕፍት ልንጠቀም ይገባል? ይህን ማድረጋችንስ ምን ጥቅም አለው?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?” እንዲሁም “ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ” የተባሉትን መጻሕፍት ተጠቀም። እነዚህ ጽሑፎች የተዘጋጁት የጥናቶቻችንን ልብ መንካት እንድንችል ለመርዳት ነው። ለምሳሌ፣ ምን ያስተምረናል? የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 1 የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ይዟል፦ አምላክ ስለ እኛ ያስባል ወይስ ጨካኝ ነው? ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው አምላክ ምን ይሰማዋል? የይሖዋ ወዳጅ መሆን ትችላለህ? በአምላክ ፍቅር ኑሩ የተባለው መጽሐፍ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንዲሁም ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚረዳው እንዴት እንደሆነ ጥናቱ እንዲገነዘብ ይረዳዋል። በእነዚህ መጻሕፍት ተጠቅመህ ሌሎች ሰዎችን ያስጠናህ ቢሆንም እንኳ ተማሪው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ግምት ውስጥ አስገብተህ ለእያንዳንዱ ጥናት በሚገባ ተዘጋጅ።

10 ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ፣ ምን ያስተምረናል? እንዲሁም በአምላክ ፍቅር ኑሩ በተባሉት መጻሕፍት ውስጥ ያልተካተተ አንድ ርዕሰ ጉዳይ አንስቶ መወያየት ቢፈልግስ? ርዕሰ ጉዳዩ የሚገኝበትን ጽሑፍ በግሉ እንዲያነበው ልታበረታታው ትችላለህ፤ አንተ ግን ቀደም ሲል በተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎች ተጠቅመህ ጥናቱን መምራትህን ቀጥል።

ጥናቱን በጸሎት ጀምር (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ጥናታችንን በጸሎት መክፈትና መደምደም ያለብን ከመቼ ጀምሮ ነው? ይህን ጉዳይ አንስተን ከጥናታችን ጋር መወያየት የምንችለውስ እንዴት ነው?

11 ጥናቱን በጸሎት ጀምር። በጥቅሉ ሲታይ፣ ሰዎችን በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ከጀመርን ብዙም ሳንቆይ ይኸውም ከመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አንስቶ ጥናቱን በጸሎት መክፈታችን እና መደምደማችን ጥሩ ነው። የአምላክን ቃል መረዳት የምንችለው በአምላክ መንፈስ እርዳታ ብቻ መሆኑን ጥናታችን እንዲገነዘብ መርዳት ይኖርብናል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጥናታቸው ስለ ጸሎት አስፈላጊነት ለማንሳት በያዕቆብ 1:5 ላይ የሚገኘውን “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን” የሚለውን ጥቅስ ያነቡለታል። ከዚያም ጥናታቸውን “አምላክ ጥበብ እንዲሰጠን መለመን የምንችለው እንዴት ነው?” ብለው ይጠይቁታል። አብዛኛውን ጊዜ ተማሪው ወደ አምላክ መጸለይ እንዳለብን ይስማማል።

12. መዝሙር 139:2-4⁠ን ተጠቅመህ ጥናትህ የጸሎቱን ይዘት እንዲያሻሽል መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?

12 ጥናትህን እንዴት መጸለይ እንዳለበት አስተምረው። ከልብ በመነጨ ስሜት የሚያቀርበውን ጸሎት ይሖዋ መስማት እንደሚፈልግ ለጥናትህ አረጋግጥለት። በግላችን ለይሖዋ በምናቀርበው ጸሎት ላይ የልባችንን አውጥተን ልንነግረው ሌላው ቀርቶ ለማንም ሰው የማንነግረውን ነገር እንኳ ልናካፍለው እንደምንችል ለጥናትህ ግለጽለት። ደግሞም ይሖዋ ውስጣዊ ሐሳባችንን ሳንነግረው ያውቃል። (መዝሙር 139:2-4ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ ጥናታችን የተሳሳተ አስተሳሰቡን ለማስተካከል እና መጥፎ ልማዶቹን ለማስወገድ አምላክ እንዲረዳው እንዲጸልይ ልናበረታታው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ጥናታችን ለተወሰነ ጊዜ ሲያጠና ከቆየ በኋላም አረማዊ አመጣጥ ያለውን አንድ በዓል ይወድ ይሆናል። በዓሉን ማክበር ስህተት እንደሆነ ቢያውቅም ከበዓሉ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነገሮች ሊያስደስቱት ይችላሉ። ስሜቱን አውጥቶ ለይሖዋ እንዲነግረው እንዲሁም አምላክ የሚወዳቸውን ነገሮች ብቻ መውደድ ይችል ዘንድ ይሖዋን እንዲለምነው ማበረታታት እንችላለን።—መዝ. 97:10

ጥናትህን በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ጋብዘው (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. (ሀ) ጥናቶቻችንን በተቻለ መጠን ወዲያውኑ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲጀምሩ ማበረታታት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ጥናታችን ወደ ስብሰባ ሲመጣ እንግድነት እንዳይሰማው ምን ማድረግ እንችላለን?

13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን በተቻለ መጠን ወዲያውኑ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲጀምር አበረታታው። ጥናትህ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሰማውና የሚያየው ነገር ልቡን ሊነካውና እድገት እንዲያደርግ ሊረዳው ይችላል። በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የሚለውን ቪዲዮ ካሳየኸው በኋላ አብሮህ ወደ ስብሰባ እንዲሄድ ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርብለት። የምትችል ከሆነ የትራንስፖርት ዝግጅት አድርግለት። የተለያዩ አስፋፊዎች በጥናቱ ላይ እንዲገኙ መጋበዝህም ጥሩ ነው። እንዲህ ማድረግህ ጥናትህ ከጉባኤው አባላት ጋር እንዲተዋወቅ ያስችለዋል፤ ይህም ስብሰባ ላይ በሚገኝበት ወቅት እንግድነት እንዳይሰማው ሊያደርግ ይችላል።

መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ጥናታችሁን እርዱት

14. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ የሚያነሳሳው ምንድን ነው?

14 ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ መርዳት ነው። (ኤፌ. 4:13) አንድ ሰው ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ሲስማማ በዋነኝነት የሚያሳስበው ከጥናቱ የሚያገኘው ጥቅም ሊሆን ይችላል። ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ ሲሄድ ግን የጉባኤውን አባላት ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን መርዳት ስለሚችልበት መንገድ ማሰብ መጀመሩ አይቀርም። (ማቴ. 22:37-39) የመንግሥቱን ሥራ በገንዘብ የመደገፍ መብት እንዳለው ለጥናትህ ማሳወቁ ተገቢ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ ላይ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትበል።

ጥናትህ ችግሮች በሚያጋጥሙት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚችል አሠልጥነው (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ችግሮች በሚያጋጥሙት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚችል ልናሠለጥነው የምንችለው እንዴት ነው?

15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን ችግሮች በሚያጋጥሙት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚችል አሠልጥነው። አንድ ምሳሌ እንውሰድ፤ ያልተጠመቀ አስፋፊ የሆነ ጥናትህ በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ቅር እንዳሰኘው ነገረህ እንበል። ከአንደኛው ወገን ከመቆም ይልቅ ጥናትህ ሊወስድ ስለሚችለው እርምጃ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን አማራጮች ለምን አታሳየውም? ጥናትህ ቅር ያሰኘውን ወንድም በይቅርታ ማለፍ ይችል ይሆናል፤ ይህን ማድረግ ከከበደው ደግሞ ‘ወንድሙን የማትረፍ’ ግብ ይዞ በደግነትና በፍቅር ሊያነጋግረው ይችላል። (ከማቴዎስ 18:15 ጋር አወዳድር።) ጥናትህ ወንድምን ምን ብሎ እንደሚያነጋግረው እንዲዘጋጅ እርዳው። ሁኔታውን ለመፍታት የሚያስችሉ ጠቃሚ ሐሳቦችን JW Library®የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች እና jw.org® ላይ ማግኘት የሚችለው እንዴት እንደሆነ አሳየው። ከመጠመቁ በፊት ጥሩ ሥልጠና ማግኘቱ ከተጠመቀ በኋላ ከጉባኤው አባላት ጋር ይበልጥ ተስማምቶ ለመኖር ይረዳዋል።

16. ሌሎች አስፋፊዎች በጥናትህ ላይ እንዲገኙ መጋበዝህ ምን ጥቅሞች አሉት?

16 ሌሎች የጉባኤውን አባላት እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቹን በጥናቱ ላይ እንዲገኙ ጋብዝ። እንዲህ ማድረግህ ምን ጥቅም አለው? ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ አንዳንድ የጉባኤው አስፋፊዎች ከአንተ የተሻለ እርዳታ መስጠት የሚችሉባቸው አቅጣጫዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ጥናትህ ሲጋራ ለማቆም በተደጋጋሚ ሞክሮ አልተሳካለት ይሆናል። ይህን ልማድ ከብዙ ሙከራ በኋላ ማሸነፍ የቻለን አንድ አስፋፊ በጥናቱ ላይ እንዲገኝ ጋብዝ። ይህ አስፋፊ ለተማሪው የሚያስፈልገውን ጠቃሚ ምክር ሊሰጠው ይችል ይሆናል። ተሞክሮ ያካበተ ወንድም ባለበት ጥናቱን መምራት ከከበደህ በዚያን ዕለት ይህ ወንድም ጥናቱን እንዲመራ ልትጋብዘው ትችላለህ። ዋናው ነገር ጥናትህ ከሌሎች ተሞክሮ እንዲጠቀም ማድረግህ ነው። ግባችን ጥናቶቻችን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ መርዳት እንደሆነ አትዘንጋ።

ግለሰቡን ማስጠናቴን ባቆም ይሻል ይሆን?

17-18. አንድን ሰው ማስጠናትህን ለማቆም ከመወሰንህ በፊት ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብህ ነገር ምንድን ነው?

17 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ደረጃ በደረጃ እድገት እያደረገ ካልሆነ ‘ጥናቱን ባቆም ይሻል ይሆን?’ በሚለው ጥያቄ ላይ ቆም ብለህ ማሰብ ሊያስፈልግህ ይችላል። ሁኔታውን በምትገመግምበት ጊዜ ጥናትህ ያለውን ችሎታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። አንዳንድ ሰዎች እድገት ለማድረግ ከሌሎች የበለጠ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ካለበት ሁኔታ አንጻር የሚጠበቀውን ያህል እድገት እያደረገ ነው? የተማራቸውን ነገሮች “መጠበቅ” ማለትም ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል?’ (ማቴ. 28:20) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያደርገው እድገት ፈጣን ባይሆንም እንኳ ቀስ በቀስ በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ ማድረግ አለበት።

18 ይሁንና ለተወሰነ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና የቆየ አንድ ሰው ለጥናቱ እምብዛም ወይም ምንም አድናቆት የማያሳይ ቢሆንስ? እስቲ ይህን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ፣ ምን ያስተምረናል? የተባለውን መጽሐፍ ጨርሶ ምናልባትም በአምላክ ፍቅር ኑሩ የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት ጀምሮ ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን አንድም ቀን በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ አያውቅም፤ ሌላው ቀርቶ በመታሰቢያው በዓል ላይ እንኳ አልተገኘም! ደግሞም በረባ ባልረባ ምክንያት ጥናቱን ይሰርዛል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ከጥናትህ ጋር በግልጽ መነጋገራችሁ አስፈላጊ ነው። *

19. ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ አድናቆት እንደሌለው ላሳየ ሰው ምን ልትለው ትችላለህ? በዚህ ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብህ ነገር ምንድን ነው?

19 ጥናትህን ‘የይሖዋ ምሥክር እንዳትሆን እንቅፋት የሚሆንብህ ዋናው ነገር ምንድን ነው?’ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ጥናትህ ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ያስደስተኛል፤ መቼም የይሖዋ ምሥክር የምሆን ግን አይመስለኝም!’ ብሎ ይመልስ ይሆናል። ረዘም ላለ ጊዜ ሲያጠና ከቆየ በኋላም እንዲህ ያለ አመለካከት ካለው ጥናቱን መቀጠሉ ምን ትርጉም አለው? በሌላ በኩል ግን ጥናትህ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንዲል ያደረገውን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ይነግርህ ይሆናል። ለምሳሌ፣ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ መስበክ ፈጽሞ እንደማይችል ይሰማው ይሆናል። እንቅፋት የሆነበት ነገር ምን እንደሆነ ማወቅህ እሱን በተሻለ መንገድ ለመርዳት ያስችልሃል።

እድገት የማያደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጠናት ጊዜህን አታባክን (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት)

20. በሐዋርያት ሥራ 13:48 ላይ የሚገኘው ሐሳብ አንድን ሰው ማስጠናታችንን ማቆም ይኖርብን እንደሆነ ለመወሰን የሚረዳን እንዴት ነው?

20 የሚያሳዝነው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በሕዝቅኤል ዘመን እንደነበሩት እስራኤላውያን ናቸው። ይሖዋ እነዚህን እስራኤላውያን በተመለከተ ሕዝቅኤልን እንዲህ ብሎታል፦ “እነሆ፣ አንተ ለእነሱ ባማረ ድምፅ እንደሚዘፈንና በባለ አውታር መሣሪያ አሳምረው እንደሚጫወቱት የፍቅር ዘፈን ሆነህላቸዋል። ቃልህን ይሰማሉ፤ ሆኖም አንዳቸውም አያደርጉትም።” (ሕዝ. 33:32) ጥናታችንን ከአሁን በኋላ እንደማናስጠናው መንገር ሊከብደን ይችላል። ይሁንና “የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን” አንዘንጋ። (1 ቆሮ. 7:29) እድገት የማያደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጠናት ጊዜያችንን ከማባከን ይልቅ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” እንዳላቸው በግልጽ የሚያሳዩ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል።የሐዋርያት ሥራ 13:48ን አንብብ።

በክልልህ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎች እርዳታ ለማግኘት እየጸለዩ ሊሆን ይችላል (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት)

21. የ2020 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህ ጥቅስ ተገቢ የሆነውስ ለምንድን ነው?

21 የ2020 የዓመት ጥቅስ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ችሎታችንን በማሻሻል ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይረዳናል። የዓመት ጥቅሱ ኢየሱስ በገሊላ በሚገኝ ተራራ ላይ በጠራው ወሳኝ ስብሰባ ላይ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ የያዘ ነው፦ ‘ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።’ማቴ. 28:19

ደቀ መዛሙርት የማድረግ እንዲሁም ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ የመርዳት ችሎታችንን ለማሻሻል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ (አንቀጽ 21⁠ን ተመልከት)

መዝሙር 70 የሚገባቸውን ሰዎች ፈልጉ

^ አን.5 የ2020 የዓመት ጥቅሳችን ‘ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ ያበረታታናል። ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ይህን መመሪያ መታዘዝ ይጠበቅባቸዋል። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ልብ በመንካት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ርዕስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች ያብራራል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድን ሰው ማስጠናታችንን ማቆም ይኖርብን እንደሆነ ለመወሰን ምን እንደሚረዳን እንመለከታለን።

^ አን.18 JW ብሮድካስቲንግ ላይ የሚገኘውን እድገት የማያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ማስጠናታችንን ማቆም የተባለውን ቪዲዮ ተመልከት።