በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 6

አባታችን ይሖዋ በጣም ይወደናል

አባታችን ይሖዋ በጣም ይወደናል

“በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ።’”—ማቴ. 6:9

መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’

ማስተዋወቂያ *

1. አንድ ሰው የፋርስን ንጉሥ ማነጋገር ቢፈልግ ምን ማድረግ ይጠበቅበት ነበር?

የዛሬ 2,500 ዓመት ገደማ በፋርስ ግዛት ውስጥ እየኖርክ ነው እንበል። ስለ አንድ ጉዳይ ንጉሡን ማነጋገር ስለፈለግህ የንጉሡ መቀመጫ ወደሆነችው ወደ ሹሻን ከተማ ተጓዝክ። በእርግጥ የንጉሡን ፈቃድ ሳታገኝ እሱ ፊት መቅረብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። እንዲህ ለማድረግ መድፈር ሕይወትህን ሊያሳጣህ ይችላል!—አስ. 4:11

2. ይሖዋ ወደ እሱ ስለ መቅረብ ምን እንዲሰማን ይፈልጋል?

2 ይሖዋ እንደዚያ የፋርስ ንጉሥ ባለመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይሖዋ ከየትኛውም ሰብዓዊ ገዢ እጅግ የላቀ ቢሆንም በማንኛውም ጊዜ እኛን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነው። በነፃነት እንድንቀርበው ይፈልጋል። ይሖዋ ታላቅ ፈጣሪ፣ ሁሉን ቻይ እና ሉዓላዊ ጌታ እንደሚሉት ባሉ የላቀ ሥልጣኑን የሚያሳዩ የማዕረግ ስሞች ይጠራል፤ ያም ቢሆን ወደ እሱ ስንጸልይ “አባታችን” በሚለው ቀረቤታን የሚያሳይ ቃል እንድንጠቀም ጋብዞናል። (ማቴ. 6:9) ይሖዋ በዚህ ደረጃ እንድንቀርበው የሚፈልግ መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

3. ይሖዋን “አባታችን” ብለን መጥራት የምንችለው ለምንድን ነው? በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

3 ይሖዋ የሕይወታችን ምንጭ ከመሆኑ አንጻር እሱን “አባታችን” ብለን መጥራታችን የተገባ ነው። (መዝ. 36:9) ይሖዋ፣ አባታችን ስለሆነ እሱን መታዘዝ ይኖርብናል። እሱ ያዘዘንን ስናደርግ አስደናቂ በረከቶችን እናገኛለን። (ዕብ. 12:9) ከእነዚህ በረከቶች አንዱ በሰማይ ወይም በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው። በዛሬው ጊዜም የምናገኛቸው ጥቅሞች አሉ። ይህ ርዕስ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እንደ አፍቃሪ አባት የሚንከባከበን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ወደፊት ፈጽሞ እንደማይተወን እርግጠኛ የምንሆንበትን ምክንያት ያብራራል። እስቲ በመጀመሪያ ግን ሰማያዊው አባታችን በጥልቅ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን መተማመን የምንችልባቸውን ምክንያቶች እንመልከት።

ይሖዋ አፍቃሪና አሳቢ አባት ነው

አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን የሚያቀርባቸውን ያህል ይሖዋም እሱን እንድንቀርበው ይፈልጋል (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. አንዳንዶች ይሖዋን እንደ አባታቸው አድርገው ማየት የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?

4 አምላክን እንደ አባትህ አድርገህ ማየት ይከብድሃል? አንዳንዶች፣ ከይሖዋ አንጻር እነሱ በጣም ኢምንት እና እዚህ ግቡ የማይባሉ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው መቀበል ይቸግራቸዋል። ይሁንና አፍቃሪው አባታችን እንዲህ እንዲሰማን አይፈልግም። ሕይወት የሰጠን ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንድንመሠርት ይፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ ለነበሩ አድማጮቹ ይህን እውነታ ከተናገረ በኋላ ይሖዋ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” ብሏቸዋል። (ሥራ 17:24-29) አንድ ልጅ የሚወደውንና የሚያስብለትን አባቱን በነፃነት እንደሚያናግረው ሁሉ አምላክም ሁላችንም ወደ እሱ ቀርበን በነፃነት እንድናነጋግረው ይፈልጋል።

5. ከአንዲት እህት ተሞክሮ ምን እንማራለን?

5 ሌሎች ደግሞ ሰብዓዊ አባታቸው ፍቅርና አሳቢነት አሳይቷቸው ስለማያውቅ ይሖዋን እንደ አባታቸው አድርገው መመልከት ይከብዳቸዋል። አንዲት እህት ምን እንዳለች እንመልከት፦ “አባቴ በጣም የሚጎዳ ነገር ይናገረኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስጀምር ይሖዋን እንደ ሰማያዊ አባቴ ተመልክቼ ወደ እሱ መቅረብ ከብዶኝ ነበር። ይሖዋን በደንብ ሳውቀው ግን አመለካከቴ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ።” አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ከሆነ ይሖዋ ከሁሉ የተሻለ አባት መሆኑን በጊዜ ሂደት እንደምትገነዘብ እርግጠኛ ሁን።

6. በማቴዎስ 11:27 መሠረት ይሖዋ እሱን እንደ አፍቃሪ አባት እንድንመለከተው እኛን ለመርዳት የተጠቀመበት አንዱ መንገድ የትኛው ነው?

6 ይሖዋ፣ እሱን እንደ አፍቃሪ አባታችን እንድንመለከተው እኛን ለመርዳት የተጠቀመበት አንዱ መንገድ ኢየሱስ የተናገራቸውና ያደረጋቸው ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገቡልን ማድረግ ነው። (ማቴዎስ 11:27ን አንብብ።) ኢየሱስ የአባቱን ማንነት ፍጹም በሆነ መንገድ ስላንጸባረቀ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ብሎ መናገር ችሏል። (ዮሐ. 14:9) ኢየሱስ ይሖዋን እንደ አባት አድርጎ ብዙ ጊዜ ገልጾታል። በአራቱ የወንጌል ዘገባዎች ላይ ብቻ ኢየሱስ “አባት” የሚለውን መጠሪያ 165 ጊዜ ገደማ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ይህን ያህል ደጋግሞ የተናገረው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ሰዎች ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባት አድርገው እንዲመለከቱት ለመርዳት ነው።—ዮሐ. 17:25, 26

7. ይሖዋ ልጁን ከያዘበት መንገድ ስለ እሱ ምን እንማራለን?

7 ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን ከያዘበት መንገድ ስለ እሱ ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ምንጊዜም የኢየሱስን ጸሎት ይሰማ ነበር። ጸሎቱን ከመስማትም ባለፈ ምላሽ ይሰጠው ነበር። (ዮሐ. 11:41, 42) ኢየሱስ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመው አባቱ እንደሚወደውና እንደሚደግፈው ተጠራጥሮ አያውቅም።—ሉቃስ 22:42, 43

8. ይሖዋ፣ ኢየሱስ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያሟላለት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

8 ኢየሱስ ሕይወት የሰጠውና ለሕይወት የሚያስፈልገውን ነገር የሚያሟላለት አባቱ እንደሆነ ሲገልጽ “ከእሱ የተነሳ በሕይወት [እኖራለሁ]” ብሏል። (ዮሐ. 6:57) ኢየሱስ በአባቱ ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር፤ ይሖዋም ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለልጁ አሟልቶለታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ የኢየሱስን መንፈሳዊ ፍላጎት አሟልቶለታል።—ማቴ. 4:4

9. ይሖዋ ለኢየሱስ አፍቃሪና አሳቢ አባት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

9 አፍቃሪ አባት የሆነው ይሖዋ፣ ኢየሱስ ምንጊዜም የአባቱ ድጋፍ እንደማይለየው እንዲተማመን አድርጓል። (ማቴ. 26:53፤ ዮሐ. 8:16) ይሖዋ፣ ኢየሱስ ጨርሶ ጉዳት እንዳይደርስበት ባይጠብቀውም ፈተናዎችን በጽናት እንዲወጣ ረድቶታል። ኢየሱስም፣ የሚደርስበት ማንኛውም ዓይነት ጉዳት ጊዜያዊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ዕብ. 12:2) ይሖዋ የኢየሱስን ጸሎት በመስማት፣ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በማቅረብ፣ ሥልጠና በመስጠትና በመደገፍ ለእሱ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐ. 5:20፤ 8:28) ሰማያዊው አባታችን ለእኛም በተመሳሳይ መንገድ ፍቅሩን የሚያሳየን እንዴት እንደሆነ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

አፍቃሪው አባታችን የሚንከባከበን እንዴት ነው?

አፍቃሪ የሆነ ሰብዓዊ አባት ልጆቹን (1) ያዳምጣል፣ (2) የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያቀርባል፣ (3) ያሠለጥናቸዋል እንዲሁም (4) ጥበቃ ያደርግላቸዋል። አፍቃሪው የሰማዩ አባታችንም በእነዚሁ መንገዶች ይንከባከበናል (ከአንቀጽ 10-15⁠ን ተመልከት) *

10. በመዝሙር 66:19, 20 መሠረት ይሖዋ እንደሚወደን የሚያሳየን እንዴት ነው?

10 ይሖዋ ጸሎታችንን ይሰማል። (መዝሙር 66:19, 20ን አንብብ።) በጸሎታችን ላይ ምንም ዓይነት ገደብ አያደርግም፤ እንዲያውም አዘውትረን እንድንጸልይ ያበረታታናል። (1 ተሰ. 5:17) በየትኛውም ቦታም ሆነ ጊዜ፣ በአክብሮት ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን። ይሖዋ የእኛን ጸሎት ለመስማት የሚሆን ጊዜ አያጣም፤ ምንጊዜም ቢሆን ጸሎታችንን በትኩረት ያዳምጣል። ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ስንመለከት ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንነሳሳለን። መዝሙራዊው “ይሖዋ ድምፄን . . . ስለሚሰማ እወደዋለሁ” ብሏል።—መዝ. 116:1

11. ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ የሚሰጠን እንዴት ነው?

11 አባታችን የምናቀርበውን ጸሎት ከመስማት ባለፈ ለጸሎታችን ምላሽ ይሰጠናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ [አምላክ] ይሰማናል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:14, 15) እርግጥ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን በጠበቅነው መንገድ ላይሆን ይችላል። ይሖዋ ለእኛ የሚበጀውን ያውቃል፤ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ የጠየቅነውን ነገር ላይሰጠን አሊያም ደግሞ መልስ ሳይሰጠን የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ ሊያደርግ ይችላል።—2 ቆሮ. 12:7-9

12-13. ሰማያዊው አባታችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች የሚያቀርብልን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

12 ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላልናል። ከሁሉም አባቶች የሚጠብቀውን ነገር እሱም ያደርጋል። (1 ጢሞ. 5:8) የልጆቹን ቁሳዊ ፍላጎት ያሟላል። ስለ ምግብ፣ ልብስ ወይም መጠለያ እንድንጨነቅ አይፈልግም። (ማቴ. 6:32, 33፤ 7:11) ይሖዋ አፍቃሪ አባት በመሆኑ ወደፊት የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንኳ ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ዝግጅት አድርጓል።

13 ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ስለ ራሱ፣ ስለ ዓላማው፣ ስለ ሕይወት ትርጉም እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ እውነቱን ነግሮናል። እውነትን መማር ስንጀምር በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶናል፤ ይኸውም በወላጆቻችን አሊያም በመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪያችን በመጠቀም ስለ እሱ እንድናውቅ ረድቶናል። አፍቃሪ በሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲሁም በጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች አማካኝነት በደግነት እኛን መርዳቱን ቀጥሏል። በተጨማሪም ይሖዋ ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት ጋር ሆነን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከእሱ እንድንማር ዝግጅት አድርጓል። ይሖዋ በእነዚህና በሌሎች መንገዶች ሁላችንንም እንደ አባት እንደሚንከባከበን አሳይቷል።—መዝ. 32:8

14. ይሖዋ የሚያሠለጥነን ለምንድን ነው? ይህን የሚያደርገውስ እንዴት ነው?

14 ይሖዋ ያሠለጥነናል። እኛ እንደ ኢየሱስ ፍጹማን አይደለንም። ስለዚህ አፍቃሪው አባታችን እኛን ለማሠልጠን ሲል አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተግሣጽ ይሰጠናል። ቃሉ “ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻል” ይላል። (ዕብ. 12:6, 7) ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ተግሣጽ ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናነበው ነገር ወይም በስብሰባዎች ላይ የምናዳምጠው ትምህርት ማስተካከያ እንደሚያስፈልገን ሊጠቁመን ይችላል። አሊያም ደግሞ ሽማግሌዎች የሚያስፈልገንን እርዳታ ሊሰጡን ይችላሉ። ይሖዋ ተግሣጽ የሚሰጥበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ ምንጊዜም ይህን የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው።—ኤር. 30:11

15. ይሖዋ ጥበቃ የሚያደርግልን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

15 ይሖዋ መከራ ሲያጋጥመን እንድንጸና ይረዳናል። አፍቃሪ የሆነ ሰብዓዊ አባት ልጆቹ ችግር ሲገጥማቸው እንደሚደግፋቸው ሁሉ ሰማያዊው አባታችንም መከራ ሲያጋጥመን ይረዳናል። መንፈሳዊ ጉዳት እንዳይደርስብን በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይጠብቀናል። (ሉቃስ 11:13) ተስፋ በምንቆርጥበት ወይም በምንጨነቅበት ጊዜም ይሖዋ ከአሉታዊ ስሜቶች ጥበቃ ያደርግልናል። ለምሳሌ፣ አስደናቂ የሆነ ተስፋ ሰጥቶናል። ይህ ተስፋ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። እስቲ አስበው፦ አፍቃሪው አባታችን ሊያስተካክለው የማይችለው ምንም ዓይነት ጉዳት ሊደርስብን አይችልም። የሚያጋጥመን ማንኛውም ችግር ጊዜያዊ ነው፤ ይሖዋ የሚያመጣው በረከት ግን ዘላለማዊ ነው።—2 ቆሮ. 4:16-18

አባታችን ፈጽሞ አይተወንም

16. አዳም በአፍቃሪ አባቱ ላይ ማመፁ ምን ውጤት አስከተለ?

16 ይሖዋ በምድራዊ ቤተሰቡ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ችግር በተፈጠረበት ወቅት የወሰደው እርምጃ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያረጋግጥ ነው። አዳም በሰማያዊ አባቱ ላይ ባመፀበት ወቅት፣ ደስተኛ በሆነው የይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የነበረውን ቦታ ያጣ ሲሆን ዘሮቹም ይህን መብት እንዲያጡ አድርጓል። (ሮም 5:12፤ 7:14) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወሰደ።

17. አዳም ካመፀ በኋላ ይሖዋ ወዲያውኑ ምን አደረገ?

17 ይሖዋ አዳምን ቢቀጣውም በአብራኩ ውስጥ ያሉ ዘሮቹ ያለተስፋ እንዲቀሩ አላደረገም። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች እንደገና የቤተሰቡ አባል እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ወዲያውኑ ቃል ገባ። (ዘፍ. 3:15፤ ሮም 8:20, 21) ይሖዋ፣ የሚወደው ልጁ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲሆን በማድረግ ይህ ዓላማው እንዲፈጸም ዝግጅት አድርጓል። ይሖዋ ልጁን ለእኛ ሲል በመስጠት ምን ያህል እንደሚወደን አረጋግጧል።—ዮሐ. 3:16

ከአምላክ ብንርቅም እንኳ ንስሐ እስከገባን ድረስ አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ እኛን ለመቀበል ፈቃደኛና ዝግጁ ነው (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. ይሖዋ ከእሱ ብንርቅም እንኳ ተመልሰን ልጆቹ እንድንሆን እንደሚፈልግ እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

18 ፍጹማን ባንሆንም ይሖዋ የቤተሰቡ አባላት እንድንሆን ይፈልጋል፤ መቼም ቢሆን እንደ ሸክም አይቆጥረንም። አንዳንድ ጊዜ እናሳዝነው ወይም ከእሱ እንርቅ ይሆናል፤ ያም ቢሆን ይሖዋ ተስፋ አይቆርጥብንም። ኢየሱስ የይሖዋን አባታዊ ፍቅር በምሳሌ ለማስረዳት ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ታሪክ ተናግሯል። (ሉቃስ 15:11-32) በዚያ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አባት ልጁ እንደሚመለስ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርግ ነበር። በኋላ ላይ ልጁ ወደ ቤት ሲመለስ አባትየው በደስታ ተቀብሎታል። እኛም ከይሖዋ ርቀን ሊሆን ይችላል፤ ንስሐ ከገባን ግን አፍቃሪው አባታችን እኛን ለመቀበል ፈቃደኛና ዝግጁ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

19. ይሖዋ አዳም ያስከተለውን ጉዳት የሚያስተካክለው እንዴት ነው?

19 አባታችን ይሖዋ፣ አዳም ያስከተለውን ጉዳት በሙሉ ያስተካክለዋል። አዳም ካመፀ በኋላ ይሖዋ ከሰው ዘሮች መካከል 144,000 ሰዎችን እንደ ልጆቹ አድርጎ ለመውሰድ ወሰነ፤ እነዚህ ሰዎች ከልጁ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። ኢየሱስና እነዚህ ተባባሪ ገዢዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ታዛዥ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይረዳሉ። ወደ ፍጽምና የደረሱት የሰው ልጆች የመጨረሻውን ፈተና ካለፉ በኋላ አምላክ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ከዚያ በኋላ አባታችን፣ ምድር ፍጹማን በሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ስትሞላ በማየት ይደሰታል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ጊዜ ይሆናል!

20. ይሖዋ በጣም እንደሚወደን ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

20 ይሖዋ በጣም እንደሚወደን በግልጽ አሳይቷል። እንደ እሱ ያለ አባት የለም። ይሖዋ ጸሎታችንን ይሰማል፤ እንዲሁም ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል። ሥልጠና ይሰጠናል እንዲሁም ይደግፈናል። ከዚህም ሌላ ለወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ በረከቶች አዘጋጅቶልናል። አባታችን እንደሚወደንና እንደሚያስብልን ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! የሚቀጥለው ርዕስ ደግሞ ልጆቹ እንደመሆናችን መጠን ለእሱ ፍቅር ምላሽ መስጠት የምንችልባቸውን መንገዶች ያብራራል።

መዝሙር 108 የአምላክ ታማኝ ፍቅር

^ አን.5 ስለ ይሖዋ ስናስብ ብዙውን ጊዜ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ፈጣሪያችንና ሉዓላዊ ገዢያችን መሆኑ ነው። ሆኖም እሱን፣ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን አባታችን አድርገን እንድንመለከተው የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉን። በዚህ ርዕስ ላይ እነዚህን ምክንያቶች እንመረምራለን። በተጨማሪም ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወን እርግጠኛ የምንሆነው ለምን እንደሆነ እንማራለን።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ አራቱም ፎቶግራፎች አባትና ልጅ ያላቸውን ግንኙነት የሚያሳዩ ናቸው፦ አንድ አባት ልጁን በትኩረት ሲያዳምጠው፣ አንድ አባት ልጁን ሲመግብ፣ አንድ አባት ልጁን ሲያሠለጥን እንዲሁም አንድ አባት ልጁን ሲያጽናና። ከአራቱ ፎቶግራፎች በስተ ጀርባ የይሖዋን እጅ የሚያሳይ ምስል መኖሩ ይሖዋ በእነዚህ መንገዶች እንደ አባት እንደሚንከባከበን የሚያሳይ ነው።