በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 9

ይሖዋ የሚያረጋጋን እንዴት ነው?

ይሖዋ የሚያረጋጋን እንዴት ነው?

“በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”—መዝ. 94:19

መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት

ማስተዋወቂያ *

1. ለጭንቀት መንስኤ የሚሆነው ምን ሊሆን ይችላል? ጭንቀት ምን ብለን እንድናስብ ሊያደርገን ይችላል?

በጭንቀት * የተዋጥክበት ጊዜ አለ? ለጭንቀትህ መንስኤ የሆነው፣ ሌሎች በተናገሩት ወይም ባደረጉት ነገር ስሜትህ መጎዳቱ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ የተጨነቅከው አንተ ራስህ በተናገርከው ወይም ባደረግከው ነገር የተነሳ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ አንድ ስህተት ሠርተህ ከሆነ ይሖዋ መቼም ይቅር እንደማይልህ በማሰብ ትጨነቅ ይሆናል። ይህም እንዳይበቃ ደግሞ በጭንቀት መዋጥህ እምነት እንደጎደለህና መጥፎ ሰው እንደሆንክ የሚጠቁም እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ይህ እውነት ነው?

2. በጭንቀት መዋጣችን እምነታችን እንዳነሰ የሚጠቁም ነገር አለመሆኑን የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?

2 እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። የነቢዩ ሳሙኤል እናት የሆነችው ሐና ታላቅ እምነት ያላት ሴት ነበረች። ይሁንና አንዲት የቤተሰቧ አባል ያደረሰችባት በደል በጭንቀት እንድትዋጥ አድርጓት ነበር። (1 ሳሙ. 1:7) ሐዋርያው ጳውሎስ ጠንካራ እምነት ቢኖረውም ‘በጉባኤዎች ሐሳብ’ የተነሳ በጣም ተጨንቆ ነበር። (2 ቆሮ. 11:28) ንጉሥ ዳዊት ጠንካራ እምነት ያለው ሰው በመሆኑ ይሖዋ በጣም ይወደው ነበር። (ሥራ 13:22) ያም ቢሆን ዳዊት በፈጸማቸው ስህተቶች የተነሳ በከባድ ጭንቀት ተደቁሶ ነበር። (መዝ. 38:4) ይሖዋ ሦስቱንም አገልጋዮቹን አጽናንቷቸዋል እንዲሁም አረጋግቷቸዋል። ከእነሱ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።

ከታማኟ ሐና የምናገኘው ትምህርት

3. ሌሎች የተናገሩት ነገር ጭንቀት ሊፈጥርብን የሚችለው እንዴት ነው?

3 ሌሎች፣ ስሜት የሚጎዳ ነገር ሲናገሩን አሊያም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉብን ጉዳዩ ይረብሸን ይሆናል። በተለይ ደግሞ ይህን ያደረገው የቅርብ ወዳጃችን ወይም የቤተሰባችን አባል ከሆነ ሁኔታው በጣም ይጎዳናል። ከግለሰቡ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዳበቃለት በማሰብ እንጨነቅ ይሆናል። ግለሰቡ ሳያስብበት የተናገረው ነገር በሰይፍ የተወጋን ያህል ስሜታችንን ሊያቆስለው ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ይባስ ብሎም አንዳንድ ጊዜ፣ አንድ ሰው ሆን ብሎ እኛን የሚጎዳ ነገር ይናገር ይሆናል። አንዲት ወጣት እህት እንዲህ ያለ ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የቅርብ ጓደኛዬ እንደሆነች የማስባት አንዲት ልጅ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢንተርኔት ስለ እኔ መጥፎ ወሬ ማሰራጨት ጀመረች። ስሜቴ የተጎዳ ከመሆኑም ሌላ ጉዳዩ በጣም ረበሸኝ። ‘እያመንኳት እንዴት እንዲህ ታደርግብኛለች?’ የሚለው ነገር ጨርሶ ሊገባኝ አልቻለም።” የቅርብ ወዳጅህ ወይም የቤተሰብህ አባል በድሎህ ከሆነ ከሐና ብዙ መማር ትችላለህ።

4. ሐና ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመዋት ነበር?

4 ሐና አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመዋት ነበር። ለበርካታ ዓመታት መሃን ሆና ቆይታለች። (1 ሳሙ. 1:2) በእስራኤላውያን ባሕል ደግሞ መሃን የሆነች ሴት እንደተረገመች ተደርጋ ትቆጠር ነበር። ይህም ሐናን እንድትሸማቀቅ አድርጓት ነበር። (ዘፍ. 30:1, 2) በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የሐና ባል፣ ፍናና የምትባል ሌላ ሚስት የነበረችው ሲሆን እሷም ልጆች ወልዳለት ነበር። የሐና ጣውንት የሆነችው ፍናና በሐና ስለምትቀና “እሷን ለማበሳጨት ዘወትር ትሳለቅባት ነበር።” (1 ሳሙ. 1:6) መጀመሪያ ላይ ሐና እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም ከብዷት ነበር። በጣም ከመረበሿ የተነሳ “እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት” ድረስ ታዝን ነበር። ሐና “በጣም ተማርራ ነበር።” (1 ሳሙ. 1:7, 10) ታዲያ ሐና መጽናኛ ያገኘችው እንዴት ነው?

5. ጸሎት ሐናን የረዳት እንዴት ነው?

5 ሐና የልቧን አውጥታ ለይሖዋ በጸሎት ነገረችው። ከጸለየች በኋላም ስላለችበት ሁኔታ ለሊቀ ካህናቱ ለኤሊ አስረዳችው። ኤሊም “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ነገር ይስጥሽ” አላት። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሐና “ተነስታ ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።” (1 ሳሙ. 1:17, 18) ሐና መጸለይዋ ሰላሟ እንዲመለስላት ረድቷታል።

በጥንት ዘመን እንደኖረችው ሐና እኛም ውስጣዊ ሰላማችንን መልሰን ማግኘትና ሰላማችንን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 6-10⁠ን ተመልከት)

6. ጸሎትን በተመለከተ ከሐና እንዲሁም በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 በጸሎት የምንጸና ከሆነ ሰላማችንን መልሰን ማግኘት እንችላለን። ሐና በሰማይ ያለውን አባቷን ለረጅም ሰዓት አነጋግራዋለች። (1 ሳሙ. 1:12) እኛም ጭንቀታችንን፣ ስጋታችንን እና ድክመታችንን ግልጽልጽ አድርገን ለይሖዋ በመንገር ረዘም ያለ ጸሎት ማቅረብ እንችላለን። ስንጸልይ ባማረና በደንብ በተቀናበረ መንገድ ሐሳባችንን መግለጽ እንዳለብን ሊሰማን አይገባም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ እንባ እየተናነቀን ምሬት የተሞላበት ነገር እንናገር ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ እኛን መስማት መቼም ቢሆን አይታክተውም። ስለ ችግሮቻችን ከመጸለይ በተጨማሪ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘውን ምክር ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) ጳውሎስ የምስጋና ጸሎት ማቅረብ እንዳለብን በግልጽ ተናግሯል። ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ስለሰጠን ሕይወት፣ ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ፣ ስለ ታማኝ ፍቅሩ እንዲሁም ስለሰጠን አስደናቂ ተስፋ ልናመሰግነው እንችላለን። ከሐና ሌላስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7. ሐና እና ባለቤቷ አዘውትረው ምን ያደርጉ ነበር?

7 ሐና ችግሮች ቢኖሩባትም ከባሏ ጋር ሆና በሴሎ ወደሚገኘው ይሖዋ የሚመለክበት ቦታ አዘውትራ ትሄድ ነበር። (1 ሳሙ. 1:1-5) ሊቀ ካህናቱ ኤሊ፣ ይሖዋ ጸሎቷን እንዲመልስላት ምኞቱን በመግለጽ ሐናን ያጽናናት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ በመጣችበት ወቅት ነበር።—1 ሳሙ. 1:9, 17

8. ስብሰባዎች የሚጠቅሙን እንዴት ነው? አብራራ።

8 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችንን ከቀጠልን ሰላማችንን መልሰን ማግኘት እንችላለን። በስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርበው የመክፈቻ ጸሎት አብዛኛውን ጊዜ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት የሚቀርብ ልመናን ያካተተ ነው። ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ሰላም ነው። (ገላ. 5:22) በጭንቀት በተዋጥንበት ጊዜም እንኳ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ይሖዋ እንዲሁም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እኛን የሚያበረታቱበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ያደርጋል፤ የምናገኘው ማበረታቻ ውስጣዊ ሰላማችንን መልሰን እንድናገኝ ይረዳናል። (ዕብ. 10:24, 25) ጸሎትና ስብሰባዎች፣ ይሖዋ እኛን ለማረጋጋት የሚጠቀምባቸው ቁልፍ መንገዶች ናቸው። ከሐና የምናገኘውን ሌላ ትምህርት ደግሞ እንመልከት።

9. ከሐና ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያልተለወጠው ነገር ምን ነበር? የተለወጠው ነገርስ?

9 ሐናን ጭንቀት የፈጠረባት ነገር ወዲያውኑ አልተስተካከለም። ሐና ይሖዋን ለማምለክ ወደ ማደሪያው ድንኳን ካደረገችው ጉዞ ስትመለስ ከፍናና ጋር በአንድ ቤት መኖሯ አልቀረም። የፍናና አመለካከትም ቢሆን እንደተለወጠ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። በመሆኑም ሐና ጣውንቷ የምትሰነዝራቸውን ልብ የሚያቆስሉ ቃላት ተቋቁማ መኖር ሳያስፈልጋት አይቀርም። ሆኖም ሐና ውስጣዊ ሰላሟን መልሳ ማግኘትና ሰላሟን ጠብቃ መኖር ችላለች። ሐና ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ከተወችው በኋላ መጨነቋን እንዳቆመች እናስታውስ። ይሖዋ እንዲያጽናናትና እንዲያረጋጋት ፈቅዳለች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ይሖዋ፣ ልጆች እንድትወልድ በማድረግ ሐናን ባርኳታል።—1 ሳሙ. 1:19, 20፤ 2:21

10. ከሐና ምሳሌ ምን እንማራለን?

10 ጭንቀት የፈጠረብን ነገር ባይስተካከልም እንኳ ሰላማችንን መልሰን ማግኘት እንችላለን። አጥብቀን መጸለያችንን እና በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችንን ብንቀጥልም አንዳንድ ችግሮች ላይቀረፉ ይችላሉ። ከሐና ምሳሌ መማር እንደምንችለው ግን ይሖዋ የተጨነቀውን ልባችንን እንዳያረጋጋልን ምንም ዓይነት ነገር ሊያግደው አይችልም። ይሖዋ ፈጽሞ አይረሳንም፤ ይዋል ይደር እንጂ ለታማኝነታችን ወሮታውን ይከፍለናል።—ዕብ. 11:6

ከሐዋርያው ጳውሎስ የምናገኘው ትምህርት

11. ጳውሎስ እንዲጨነቅ የሚያደርጉ ምን ነገሮች አጋጥመውታል?

11 ጳውሎስ እንዲጨነቅ ሊያደርጉት የሚችሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ፣ ወንድሞቹንና እህቶቹን ይወድ ስለነበር እነሱ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እረፍት ነስተውት ነበር። (2 ቆሮ. 2:4፤ 11:28) ሐዋርያ እንዲሆን የተሰጠውን ተልእኮ ሲፈጽም ደግሞ በተቃዋሚዎቹ እጅ የተደበደበበትና እስር ቤት የተጣለበት ጊዜ አለ። ‘በትንሽ ነገር ለመኖር’ መገደድን ጨምሮ እንዲጨነቅ የሚያደርጉ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመውታል። (ፊልጵ. 4:12) ቢያንስ ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞት ስለነበር በመርከብ ሲሄድ ምን ያህል ሊጨነቅ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። (2 ቆሮ. 11:23-27) ታዲያ ጳውሎስ ጭንቀትን መቋቋም የቻለው እንዴት ነው?

12. ጳውሎስ ጭንቀቱ ቀለል እንዲልለት የረዳው ምንድን ነው?

12 ጳውሎስ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ቢጨነቅም ችግሮቻቸውን በሙሉ ብቻውን ለማስተካከል አልሞከረም። ጳውሎስ አቅሙን የሚያውቅ ሰው ነበር። ጉባኤውን ከመንከባከብ ጋር በተያያዘ ሌሎች እንዲያግዙት ዝግጅት አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ እንደ ጢሞቴዎስና ቲቶ ላሉ እምነት የሚጣልባቸው ወንዶች ኃላፊነት ሰጥቷል። እነዚህ ወንድሞች ያከናወኑት ሥራ ጳውሎስ ጭንቀቱ ቀለል እንዲልለት አድርጎ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።—ፊልጵ. 2:19, 20፤ ቲቶ 1:1, 4, 5

ከሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ እንደምንማረው በጭንቀት እንዳንዋጥ ምን ማድረግ እንችላለን? (ከአንቀጽ 13-15⁠ን ተመልከት)

13. ሽማግሌዎች የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

13 የሌሎችን እገዛ ጠይቅ። እንደ ጳውሎስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ አፍቃሪ ሽማግሌዎችም የጉባኤያቸው አባላት ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ይጨነቃሉ። ሆኖም አንድ ሽማግሌ መርዳት የሚችለው ሁሉንም ሰው አይደለም። አቅሙን የሚያውቅ ሽማግሌ፣ ብቃት ላላቸው ሌሎች ወንዶች ሸክሙን የሚያጋራ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን መንጋ በመንከባከቡ ሥራ እንዲያግዙት ወጣት ወንዶችን ያሠለጥናል።—2 ጢሞ. 2:2

14. ጳውሎስ ምን ዓይነት ስጋት አላደረበትም? ከእሱ ምሳሌስ ምን እንማራለን?

14 ማጽናኛ እንደሚያስፈልግህ አምነህ ተቀበል። ጳውሎስ ትሑት ስለነበር የወዳጆቹ ማበረታቻ እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር፤ ያደረጉለትን እርዳታም ተቀብሏል። ሌሎች እንዳጽናኑት መናገሩ እንደ ደካማ ሰው ሊያስቆጥረው እንደሚችል በማሰብ ስጋት አላደረበትም። ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ስለምታሳየው ፍቅር በመስማቴ እጅግ ተደስቻለሁ እንዲሁም ተጽናንቻለሁ” ብሏል። (ፊልሞና 7) ጳውሎስ በተጨነቀባቸው ጊዜያት በእጅጉ ያበረታቱትን ሌሎች የሥራ ባልደረቦቹንም ጠቅሷል። (ቆላ. 4:7-11) ማበረታቻ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን ስንቀበል ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስፈልገንን ነገር በደስታ ያደርጉልናል።

15. ጳውሎስ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመው ጭንቀቱን ለማቅለል ምን አድርጓል?

15 ከአምላክ ቃል እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ። ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያጽናኑት ያውቅ ነበር። (ሮም 15:4) እነዚህ መጻሕፍት ማንኛውንም ችግር ለመወጣት የሚያስችል ጥበብም ይሰጡታል። (2 ጢሞ. 3:15, 16) ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በሮም በታሰረበት ወቅት የሚሞትበት ጊዜ እንደተቃረበ ተሰምቶት ነበር። ታዲያ እንዲህ ባለ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ወቅት ምን አደረገ? ጢሞቴዎስን “የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን” ይዞ በቶሎ ወደ እሱ እንዲመጣ ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:6, 7, 9, 13) ለምን? የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የተወሰኑ ክፍሎች እንደያዙ የሚገመቱትን እነዚያን ጥቅልሎች ለግል ጥናቱ ሊጠቀምባቸው ስላሰበ ይሆናል። እኛም እንደ ጳውሎስ የአምላክን ቃል አዘውትረን የምናጠና ከሆነ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ይሖዋ በቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅሞ ሊያረጋጋን ይችላል።

ከንጉሥ ዳዊት የምናገኘው ትምህርት

ንጉሥ ዳዊት ካጋጠመው ነገር እንደምንማረው ከባድ ኃጢአት ከሠራን ምን ሊረዳን ይችላል? (ከአንቀጽ 16-19⁠ን ተመልከት)

16. ዳዊት የፈጸመው ድርጊት ምን ዓይነት ጉዳት አስከትሎበታል?

16 ዳዊት በሠራው ከባድ ስህተት የተነሳ በሕሊና ወቀሳ ይሠቃይ ነበር። ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር የፈጸመና ባሏ እንዲገደል ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ኃጢአቱን ለመደበቅ ሞክሮ ነበር። (2 ሳሙ. 12:9) ዳዊት መጀመሪያ ላይ የሕሊናውን ወቀሳ ችላ ብሎ ለማለፍ ሞክሮ ነበር። ይህ ግን በመንፈሳዊ እንዲጎዳ ያደረገው ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ጭንቀትና ሕመም አስከትሎበታል። (መዝ. 32:3, 4) ታዲያ የራሱ ጥፋት ያስከተለበትን ጭንቀት እንዲቋቋም ዳዊትን የረዳው ምንድን ነው? እኛስ ከባድ ኃጢአት ብንሠራ ምን ሊረዳን ይችላል?

17. በመዝሙር 51:1-4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ዳዊት ከልቡ ንስሐ እንደገባ የሚያሳየው እንዴት ነው?

17 ምሕረት ለማግኘት ጸልይ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዳዊት ወደ ይሖዋ ጸለየ። ከልቡ ንስሐ በመግባት ኃጢአቱን ለይሖዋ ተናዘዘ። (መዝሙር 51:1-4ን አንብብ።) ይህን ማድረጉ ታላቅ እፎይታ አስገኝቶለታል! (መዝ. 32:1, 2, 4, 5) አንተም ከባድ ኃጢአት ሠርተህ ከሆነ ስህተትህን ለመሸፋፈን አትሞክር። ከዚህ ይልቅ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ኃጢአትህን በግልጽ ተናዘዝ። እንዲህ ማድረግህ በሕሊና ወቀሳ የተነሳ የሚሰማህ ጭንቀት በተወሰነ መጠን ቀለል እንዲልልህ ይረዳሃል። ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማደስ ከፈለግህ ግን ወደ እሱ ከመጸለይ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅብሃል።

18. ዳዊት ተግሣጽ ሲሰጠው ምን ምላሽ ሰጥቷል?

18 ተግሣጽን ተቀበል። ዳዊትን ስለፈጸመው ኃጢአት እንዲያነጋግረው ይሖዋ ነቢዩ ናታንን በላከው ወቅት ዳዊት ሰበብ ለማቅረብ ወይም ጥፋቱን ለማቃለል አልሞከረም። ዳዊት የቤርሳቤህን ባል፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን እንደበደለ ወዲያውኑ አምኖ ተቀብሏል። የይሖዋን ተግሣጽ የተቀበለ ሲሆን ይሖዋም ምሕረት አድርጎለታል። (2 ሳሙ. 12:10-14) እኛም ከባድ ኃጢአት ፈጽመን ከሆነ ይሖዋ እረኛ ሆነው እንዲጠብቁን የሾማቸውን ሰዎች ማነጋገር ያስፈልገናል። (ያዕ. 5:14, 15) በተጨማሪም ለስህተታችን ሰበብ አስባብ እንዳናቀርብ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የሚሰጠንን ማንኛውንም ተግሣጽ ወዲያውኑ ተቀብለን ተግባራዊ ካደረግን ሰላማችን እና ደስታችን ቶሎ ይመለስልናል።

19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምንድን ነው?

19 ስህተትህን ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ንጉሥ ዳዊት የሠራውን ኃጢአት ላለመድገም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። (መዝ. 51:7, 10, 12) ዳዊት የይሖዋን ምሕረት ካገኘ በኋላ መጥፎ ሐሳቦችን ለማስወገድ ቆርጦ ነበር። ይህን ማድረጉም ውስጣዊ ሰላሙ እንዲመለስለት ረድቶታል።

20. የይሖዋን ምሕረት እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

20 ይሖዋ ይቅር እንዲለን በመጸለይ፣ ተግሣጽን በመቀበልና ስህተታችንን ላለመድገም ጥረት በማድረግ የይሖዋን ምሕረት እንደምናደንቅ ማሳየት እንችላለን። እነዚህን እርምጃዎች ከወሰድን ውስጣዊ ሰላማችን ይመለስልናል። ከባድ ኃጢአት የሠራ ጄምስ የተባለ አንድ ወንድም ይህ እውነት መሆኑን ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል፦ “ኃጢአቴን ለሽማግሌዎች ስናዘዝ ከላዬ ላይ ትልቅ ሸክም የወረደልኝ ያህል ተሰማኝ። እንደገና የአእምሮ ሰላም አገኘሁ።” ‘ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ እንደሆነና መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውን እንደሚያድን’ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው።—መዝ. 34:18

21. ይሖዋ እንዲያረጋጋን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

21 እነዚህ የመጨረሻ ቀናት ወደ ማብቂያቸው እየተቃረቡ ሲሄዱ፣ ለጭንቀት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮች መጨመራቸው አይቀርም። የሚያስጨንቁ ሐሳቦች ሲመጡብህ ወዲያውኑ የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት አጥና። ሐና፣ ጳውሎስና ዳዊት ከተዉት ምሳሌ ትምህርት ውሰድ። የጭንቀትህን መንስኤ ለማወቅ እንዲረዳህ የሰማዩ አባትህን ጠይቀው። (መዝ. 139:23) በተለይ ከቁጥጥርህ ውጭ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ሸክምህን በእሱ ላይ ጣለው። እንዲህ ካደረግህ እንደሚከተለው በማለት እንደዘመረው መዝሙራዊ ይሰማሃል፦ “በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”—መዝ. 94:19

መዝሙር 4 “ይሖዋ እረኛዬ ነው”

^ አን.5 ሁላችንም፣ በሚያጋጥሙን ችግሮች የተነሳ የምንጨነቅበት ጊዜ አለ። ይህ ርዕስ በጥንት ዘመን የነበሩና የሚያስጨንቅ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሦስት የይሖዋ አገልጋዮችን ምሳሌ ያብራራል። በተጨማሪም ይሖዋ እያንዳንዳቸውን ያጽናናቸውና ያረጋጋቸው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።

^ አን.1 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ጭንቀት፣ የመረበሽ ወይም የስጋት ስሜት ነው። የገንዘብ ችግር፣ የጤና እክል አሊያም ከቤተሰብ ወይም ከግል ሕይወታችን ጋር የተያያዙ ችግሮች በጭንቀት እንድንዋጥ ሊያደርጉን ይችላሉ። በተጨማሪም ቀደም ሲል የሠራናቸው ስህተቶች አሊያም ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚለው ሐሳብ ጭንቀት ሊፈጥሩብን ይችላሉ።