በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 11

ለመጠመቅ ዝግጁ ነህ?

ለመጠመቅ ዝግጁ ነህ?

“ጥምቀት . . . እያዳናችሁ ነው።”—1 ጴጥ. 3:21

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

ማስተዋወቂያ *

1. አንድ ሰው ቤት መገንባት ከመጀመሩ በፊት ምን ማድረግ ይኖርበታል?

አንድ ሰው ቤት ለመገንባት እያሰበ ነው እንበል። መገንባት የሚፈልገው ምን ዓይነት ቤት እንደሆነ ያውቃል። ታዲያ ወዲያውኑ የግንባታ ቁሳቁስ በመግዛት ግንባታውን መጀመር ይኖርበታል? በፍጹም። ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ማድረግ ያለበት አንድ አስፈላጊ ነገር አለ፤ ለግንባታው ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ማስላት አለበት። ለምን? ምክንያቱም እጁ ላይ ያለው ገንዘብ ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ የሚበቃ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። አስቀድሞ ወጪውን በሚገባ ካሰላ ቤቱን ገንብቶ የመጨረሱ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል።

2. በሉቃስ 14:27-30 ላይ በተገለጸው መሠረት ከመጠመቅህ በፊት ስለ ምን ነገር በጥሞና ማሰብ ይኖርብሃል?

2 ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና አድናቆት ለመጠመቅ እንድታስብ አነሳስቶሃል? ከሆነ፣ ሁኔታህ ቤት ለመገንባት ካሰበው ሰው ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በሉቃስ 14:27-30 ላይ የተናገረውን ሐሳብ አስታውስ። (ጥቅሱን አንብብ።) በወቅቱ ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ምን እንደሚጠይቅ እየተናገረ ነበር። የእሱ ተከታዮች መሆን ከፈለግን “ወጪውን” ለማውጣት ማለትም ፈተናዎቹን ለመጋፈጥና መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል። (ሉቃስ 9:23-26፤ 12:51-53) ስለዚህ ከመጠመቅህ በፊት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ነገሮችን እንደሚጠይቅ በጥሞና ማሰብ ያስፈልግሃል። እንዲህ ማድረግህ ከተጠመቅክ በኋላም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን ለመቀጠል ብቁ እንድትሆን ይረዳሃል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ተጠምቆ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን በእርግጥ መሥዋዕት ሊከፈልለት የሚገባ ነገር ነው? እንዴታ! ጥምቀት አሁንም ሆነ ወደፊት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን በረከቶች ያስገኛል። ጥምቀትን በተመለከተ አንዳንድ ወሳኝ ጥያቄዎችን እስቲ እንመልከት። ይህም “ለመጠመቅ ዝግጁ ነኝ?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳሃል።

ራስን መወሰንን እና መጠመቅን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብሃል?

4. (ሀ) ራስን መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) በማቴዎስ 16:24 ላይ በተገለጸው መሠረት ‘ራስን መካድ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

4 ራስን መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው? ከመጠመቅህ በፊት ራስህን መወሰን ይኖርብሃል። ራስህን ወሰንክ የሚባለው ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ሕይወትህን በሙሉ እሱን እንደምታገለግለው ቃል ስትገባ ነው። ራስህን ለአምላክ ስትወስን ‘ራስህን ትክዳለህ።’ (ማቴዎስ 16:24ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ የይሖዋ ንብረት ትሆናለህ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ መብት ነው። (ሮም 14:8) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ራስህን በማስደሰት ላይ ሳይሆን እሱን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት እንደምትመራ ለይሖዋ ቃል ትገባለህ። ራስህን ስትወስን ለአምላክ ስእለት ትሳላለህ። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ስእለት እንድንሳል አያስገድደንም። አንዴ ከተሳልን በኋላ ግን ቃላችንን እንድናከብር ይጠብቅብናል።—መዝ. 116:12, 14

5. ራስን በመወሰን እና በጥምቀት መካከል ምን ዝምድና አለ?

5 ራስን በመወሰን እና በጥምቀት መካከል ምን ዝምድና አለ? ራስን መወሰን በአንተና በይሖዋ መካከል ብቻ ያለ ጉዳይ ነው፤ ይህን ውሳኔ ማድረግህን ሌላ ሰው ሊያውቅ አይችልም። ጥምቀት ደግሞ በሕዝብ ፊት የሚፈጸም ክንውን ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚካሄደው በወረዳ ወይም በክልል ስብሰባ ላይ ነው። በምትጠመቅበት ጊዜ ሌሎች ሰዎችም ራስህን ለይሖዋ መወሰንህን ማየት ይችላሉ። * ስለዚህ መጠመቅህ ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ እንደምትወደው እንዲሁም እሱን ለዘላለም ለማገልገል እንደወሰንክ ሰዎች እንዲያዩ ያደርጋል።—ማር. 12:30

6-7. በ1 ጴጥሮስ 3:18-22 ላይ በተገለጸው መሠረት ጥምቀት አስፈላጊ የሆነባቸው ሁለት ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

6 መጠመቅ የግድ አስፈላጊ ነው? አንደኛ ጴጥሮስ 3:18-22 ምን እንደሚል ልብ በል። (ጥቅሱን አንብብ።) የኖኅ መርከብ ኖኅ እምነት እንዳለው የሚያረጋግጥ በዓይን የሚታይ ማስረጃ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም ራስህን ለይሖዋ መወሰንህን የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ይሁንና መጠመቅ በእርግጥ አስፈላጊ ነው? በሚገባ። ጴጥሮስ ምክንያቱን ገልጿል። አንደኛ፣ ጥምቀት ‘ያድናል።’ በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን ይኸውም ኢየሱስ እንደሞተልን፣ ተነስቶ ወደ ሰማይ እንደሄደና ‘በአምላክ ቀኝ እንደሚገኝ’ እንደምናምን በተግባር ካሳየን ጥምቀት ሊያድነን ይችላል።

7 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጥምቀት “ጥሩ ሕሊና” ያስገኛል። ራሳችንን ለአምላክ ወስነን ስንጠመቅ ከእሱ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና ይኖረናል። ከልባችን ንስሐ በመግባታችንና በቤዛው ላይ እምነት በማሳደራችን አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር ይልልናል። በዚህ መንገድ በእሱ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ እንችላለን።

8. ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ምን ሊሆን ይገባል?

8 ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ምን ሊሆን ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናትህ ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ብዙ ትምህርት ቀስመሃል። ስለ ይሖዋ በተማርከው ነገር ልብህ ስለተነካ ለእሱ ጥልቅ ፍቅር አዳብረሃል። ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ ያለህ ፍቅር መሆን ይኖርበታል።

9. በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ በተገለጸው መሠረት በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

9 ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ሌላው ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች መማርህና አምነህ መቀበልህ ነው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ተልእኮ በሰጠበት ወቅት ምን እንዳለ ልብ በል። (ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።) ኢየሱስ ሰዎች መጠመቅ ያለባቸው “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንደሆነ ተናግሯል። ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? በሙሉ ልብህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ፣ ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስና ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት ማመን አለብህ ማለት ነው። እነዚህ እውነቶች ልብህን የመንካት ከፍተኛ ኃይል አላቸው። (ዕብ. 4:12) ከእነዚህ እውነቶች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

10-11. አብን በተመለከተ የተማርካቸውና አምነህ የተቀበልካቸው እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

10 አብን በተመለከተ የሚከተሉትን እውነቶች የተማርክበትን ጊዜ መለስ ብለህ አስብ፦ የአብ ‘ስም ይሖዋ ነው’፤ እሱ “በመላው ምድር ላይ ልዑል” ነው፤ ከዚህም ሌላ ‘እውነተኛው አምላክ’ እሱ ብቻ ነው። (መዝ. 83:18፤ ኢሳ. 37:16) እሱ ፈጣሪያችን ነው፤ እንዲሁም “ማዳን የይሖዋ ነው።” (መዝ. 3:8፤ 36:9) ይሖዋ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንድንወጣ የሚያስችለንን ዝግጅት ያደረገልን ከመሆኑም ሌላ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 17:3) ራስህን መወሰንህና መጠመቅህ የይሖዋ ምሥክር እንደሆንክ ያሳያል። (ኢሳ. 43:10-12) ስትጠመቅ በአምላክ ስም በመጠራታቸው የሚኮሩና ስሙን ለሌሎች የሚያሳውቁ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችን ያቀፈውን ቤተሰብ ትቀላቀላለህ።—መዝ. 86:12

11 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብ ምን እንደሚያስተምር መረዳት በእርግጥም ታላቅ መብት ነው! እነዚህን ውድ እውነቶች አምነህ ስትቀበል ራስህን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ ትነሳሳለህ።

12-13. ወልድን በተመለከተ የተማርካቸውና አምነህ የተቀበልካቸው እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

12 ወልድን በተመለከተ የሚከተሉትን እውነቶች ስትማር ምን ተሰምቶህ ነበር? በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ሁለተኛውን ቦታ የያዘው ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ቤዛችን ነው። በፈቃደኝነት ሕይወቱን ለእኛ ሲል አሳልፎ ሰጥቷል። በቤዛው ላይ እምነት እንዳለን በተግባር የምናሳይ ከሆነ የኃጢአት ይቅርታ፣ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት መብት እንዲሁም የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ ሊቀ ካህናታችን ነው። ከቤዛው ጥቅም እንድናገኝና ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት ሊረዳን ይፈልጋል። (ዕብ. 4:15፤ 7:24, 25) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ስሙን የሚያስቀድሰው፣ ክፋትን የሚያጠፋው እንዲሁም ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ ዘላለማዊ በረከቶችን የሚያመጣው በእሱ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 6:9, 10፤ ራእይ 11:15) ኢየሱስ አርዓያችን ነው። (1 ጴጥ. 2:21) በሕይወቱ ውስጥ የአምላክን ፈቃድ በማስቀደም ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—ዮሐ. 4:34

13 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የሚያስተምረውን እውነት አምነህ ስትቀበል ለአምላክ ውድ ልጅ ፍቅር ይኖርሃል። ይህ ፍቅር የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ እንድታስቀድም ያነሳሳሃል። በውጤቱም ራስህን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ ትገፋፋለህ።

14-15. መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ የተማርካቸውና አምነህ የተቀበልካቸው እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

14 መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ የሚከተሉትን እውነቶች ስትማር ምን ተሰምቶህ ነበር? መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል ሳይሆን በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል ነው። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው፤ መንፈስ ቅዱስ በቃሉ ውስጥ የምናነበውን ሐሳብ እንድንረዳና በሥራ ላይ እንድናውል ይረዳናል። (ዮሐ. 14:26፤ 2 ጴጥ. 1:21) ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ” ኃይል ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 4:7) መንፈስ ቅዱስ ምሥራቹን እንድንሰብክ፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን እንድንወጣ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን እንድናሸንፍ እንዲሁም መከራን በጽናት እንድንቋቋም ብርታት ይሰጠናል። በተጨማሪም “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታ የሆኑትን ግሩም ባሕርያት እንድናንጸባርቅ ይረዳናል። (ገላ. 5:22) አምላክ ለሚታመኑበትና ከልባቸው ለሚለምኑት ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በነፃ ይሰጣል።—ሉቃስ 11:13

15 የይሖዋ ሕዝቦች እሱን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ መንፈስ ቅዱስ እንደሚረዳቸው ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ስለ መንፈስ ቅዱስ የተማርካቸውን እውነቶች አምነህ ስትቀበል ራስህን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ ትነሳሳለህ።

16. እስካሁን ድረስ የትኞቹን ነገሮች ተመልክተናል?

16 ራስህን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ የምታደርገው ውሳኔ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እርምጃ ነው። እስካሁን እንደተመለከትነው ይህን ውሳኔ ለማድረግ፣ “ወጪውን” ለማውጣት ማለትም ፈተናዎቹን ለመጋፈጥና መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን ይኖርብሃል። ሆኖም የምታገኘው በረከት ከምትከፍለው መሥዋዕት በእጅጉ የላቀ ነው። ጥምቀት ሊያድንህ ይችላል፤ እንዲሁም በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና እንዲኖርህ ይረዳሃል። ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ አምላክ ያለህ ፍቅር መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ስለ አብ፣ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ የተማርካቸውን እውነቶች በሙሉ ልብህ አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። ታዲያ እስካሁን ከተወያየንባቸው ነጥቦች አንጻር “ለመጠመቅ ዝግጁ ነኝ?” ለሚለው ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ?

ከመጠመቅህ በፊት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

17. አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት የሚወስዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?

17 ለመጠመቅ ዝግጁ እንደሆንክ የሚሰማህ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት እስካሁን ድረስ ብዙ እርምጃዎችን ወስደህ መሆን አለበት። * መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት በመማርህ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ብዙ ነገሮችን አውቀሃል። እምነትም አዳብረሃል። (ዕብ. 11:6) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ይሖዋ የሰጠን ተስፋዎች ላይ ሙሉ እምነት አለህ፤ እንዲሁም በኢየሱስ መሥዋዕት ማመንህ ከኃጢአትና ከሞት እንደሚያድንህ ትተማመናለህ። ከኃጢአትህ ንስሐ ገብተሃል፤ ይኸውም በፈጸምከው በደል በመጸጸት ይሖዋ ይቅር እንዲልህ ለምነኸዋል። በተጨማሪም ተመልሰሃል፤ በሌላ አባባል መጥፎ አኗኗርህን በመተው አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር ጀምረሃል። (ሥራ 3:19) ስለ እምነትህ ለሌሎች ለመናገር ትጓጓለህ። ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን ስላሟላህ ከጉባኤው ጋር ማገልገል ጀምረሃል። (ማቴ. 24:14) እነዚህን ወሳኝ እርምጃዎች በመውሰድህ ይሖዋ በጣም ይኮራብሃል። ልቡን በእጅጉ ደስ አሰኝተኸዋል።—ምሳሌ 27:11

18. ከመጠመቅህ በፊት ልታደርጋቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

18 ከመጠመቅህ በፊት ልታደርጋቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ራስህን ለአምላክ መወሰን ይኖርብሃል። ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ሕይወትህን በሙሉ የእሱን ፈቃድ እንደምትፈጽም ቃል መግባት አለብህ። (1 ጴጥ. 4:2) ከዚያም መጠመቅ እንደምትፈልግ ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ንገረው። እሱም ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩህ ዝግጅት ያደርጋል። ከእነዚህ ሽማግሌዎች ጋር መነጋገር ሊያስፈራህ አይገባም። እነዚህ ወንድሞች በደንብ እንደሚያውቁህና እንደሚወዱህ አትጠራጠር። ሽማግሌዎቹ የተማርካቸውን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አብረውህ ይከልሳሉ። ይህን የሚያደርጉት እነዚህን ትምህርቶች በደንብ መረዳትህን ብሎም ራስን መወሰንና መጠመቅ ያለውን ትርጉም መገንዘብህን ለማረጋገጥ ነው። ለመጠመቅ ዝግጁ እንደሆንክ ከተሰማቸው በቀጣዩ የወረዳ ወይም የክልል ስብሰባ ላይ መጠመቅ እንደምትችል ይነግሩሃል።

ከተጠመቅክ በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

19-20. ከተጠመቅክ በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እንዲህ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው?

19 ከተጠመቅክ በኋላስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? * ራስን መወሰን ስእለት እንደሆነና ይሖዋ ስእለትህን እንድትፈጽም እንደሚጠብቅብህ አስታውስ። ስለዚህ ከተጠመቅክ በኋላ፣ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል መጠበቅ አለብህ። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

20 ከጉባኤው ጋር ተቀራርበህ ኑር። ከተጠመቅክበት ጊዜ አንስቶ ‘የወንድማማች ማኅበሩ’ ክፍል እንደሆንክ አስታውስ። (1 ጴጥ. 2:17) በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ ቤተሰቦችህ ናቸው። በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ በመገኘት ከእነሱ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማጠናከር ትችላለህ። በየዕለቱ የአምላክን ቃል አንብብ እንዲሁም ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል። (መዝ. 1:1, 2) የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካነበብክ በኋላ ስላነበብከው ነገር ጊዜ ወስደህ በጥልቀት አስብ። ይህም ያነበብከው ሐሳብ ልብህን እንዲነካው ያስችላል። በተጨማሪም ‘ሳታሰልስ ጸልይ።’ (ማቴ. 26:41) ልባዊ ጸሎት ማቅረብህ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ይረዳሃል። ‘ከሁሉ አስቀድመህ የአምላክን መንግሥት ፈልግ።’ (ማቴ. 6:33) ይህን ማድረግ የምትችለው በሕይወትህ ውስጥ ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ነው። አዘውትረህ በአገልግሎት መካፈልህ እምነትህ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳሃል፤ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎችም የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መርዳት ትችል ይሆናል።—1 ጢሞ. 4:16

21. መጠመቅህ ምን ያስገኝልሃል?

21 በሕይወትህ ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ውሳኔ ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ለመጠመቅ የምታደርገው ውሳኔ ነው። እርግጥ ይህ ውሳኔ መሥዋዕት እንደሚያስከፍል የታወቀ ነው። ይሁንና ይህን ማድረጉ የሚያስቆጭ ነው? በጭራሽ! በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥምህ ማንኛውም ፈተና “ጊዜያዊና ቀላል” ነው። (2 ቆሮ. 4:17) በአንጻሩ ግን መጠመቅህ በአሁኑ ጊዜ አርኪ የሆነ ሕይወት፣ ወደፊት ደግሞ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” እንድታገኝ መንገድ ይከፍትልሃል። (1 ጢሞ. 6:19) እንግዲያው እባክህ “ለመጠመቅ ዝግጁ ነኝ?” የሚለውን ጥያቄ በጸሎት ታግዘህ በጥሞና አስብበት።

መዝሙር 50 ራሴን ለአምላክ ለመወሰን ያቀረብኩት ጸሎት

^ አን.5 ለመጠመቅ እያሰብክ ነው? ከሆነ ይህ ርዕስ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለአንተ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከጥምቀት ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ እንወያያለን። የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመጠመቅ ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ለማወቅ ይረዳሃል።

^ አን.19 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? እና ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ የተባሉትን መጻሕፍት አጥንተህ ካልጨረስክ ሁለቱንም መጻሕፍት እስክትጨርስ ድረስ ከአስጠኚህ ጋር ማጥናት ይኖርብሃል።