በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 17

“ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ”

“ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ”

“ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።”—ዮሐ. 15:15

መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ

ማስተዋወቂያ *

1. ከአንድ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት ነው?

ብዙውን ጊዜ ከአንድ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችለን የመጀመሪያው እርምጃ ከግለሰቡ ጋር አብረን ጊዜ ማሳለፍ ነው። እርስ በርስ ስንጨዋወት ይኸውም ስሜታችንን እና ያጋጠሙንን ነገሮች አንዳችን ለሌላው ስናካፍል ወዳጅነታችን እየጠበቀ ይሄዳል። ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከመመሥረት ጋር በተያያዘ ግን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

2. የመጀመሪያው ተፈታታኝ ሁኔታ ምንድን ነው?

2 የመጀመሪያው ተፈታታኝ ሁኔታ፣ ኢየሱስን አግኝተነው የማናውቅ መሆኑ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ያም ቢሆን ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “እሱን አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ። አሁን ባታዩትም እንኳ በእሱ ላይ እምነት እያሳያችሁ . . . ነው።” (1 ጴጥ. 1:8) ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው ከኢየሱስ ጋር ተገናኝተን ባናውቅም ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን።

3. ሁለተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ ምንድን ነው?

3 ሁለተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ፣ ኢየሱስን በቀጥታ ማነጋገር አለመቻላችን ነው። በምንጸልይበት ወቅት በቀጥታ የምናነጋግረው ይሖዋን ነው። በእርግጥ የምንጸልየው በኢየሱስ ስም ነው፤ ሆኖም እሱን በቀጥታ አናነጋግረውም። ኢየሱስም ቢሆን ወደ እሱ እንድንጸልይ አይፈልግም። ለምን? ምክንያቱም ጸሎት የአምልኮ ክፍል ነው፤ ሊመለክ የሚገባው ደግሞ ይሖዋ ብቻ ነው። (ማቴ. 4:10) ያም ቢሆን ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው መንገዶች አሉ።

4. ሦስተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ ምንድን ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

4 ሦስተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ ደግሞ ኢየሱስ የሚኖረው በሰማይ መሆኑ ነው፤ በመሆኑም ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የምንችልበት አጋጣሚ የለም። ይሁንና በአካል ከኢየሱስ ጋር መሆን ባንችልም ስለ እሱ ብዙ ነገር ማወቅ እንችላለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚረዱንን አራት ነገሮች እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመርምር።

የኢየሱስ ወዳጆች መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

5. የኢየሱስ ወዳጆች መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (በተጨማሪም “ ከኢየሱስ ጋር ወዳጅ መሆን ከይሖዋ ጋር ወዳጅ ለመሆን ያስችላል” እና “ ኢየሱስ ስላለው ሚና ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ” የሚሉትን ሣጥኖች ተመልከት።)

5 ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ሊኖረን የሚችለው የኢየሱስ ወዳጆች ከሆንን ብቻ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ ሁለት ምክንያቶችን ብቻ እንመልከት። አንደኛ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝ . . . አብ ራሱ ይወዳችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 16:27) በተጨማሪም ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 14:6) ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ሳይመሠርቱ የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን መሞከር በር ሳይጠቀሙ ወደ አንድ ሕንፃ ለመግባት ከመሞከር ተለይቶ አይታይም። ኢየሱስ ተመሳሳይ ምሳሌ በመጠቀም “በጎቹ የሚገቡበት በር እኔ ነኝ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። (ዮሐ. 10:7) ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መልኩ አንጸባርቋል። ለደቀ መዛሙርቱ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም ስለ ይሖዋ ማወቅ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ የኢየሱስን ሕይወት ማጥናት ነው። ስለ ኢየሱስ እየተማርን ስንሄድ ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እየተጠናከረ ሲሄድ ደግሞ ለአባቱ ያለን ፍቅር ይጨምራል።

6. ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት መመሥረት አስፈላጊ የሆነበት ሌላው ምክንያት ምንድን ነው? አብራራ።

6 ጸሎታችን መልስ የሚያገኘው የኢየሱስ ወዳጆች ከሆንን ብቻ ነው። በመሆኑም በጸሎታችን ላይ ለደንቡ ያህል “በኢየሱስ ስም” ከማለት ያለፈ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት ኢየሱስን የሚጠቀመው እንዴት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:13) ጸሎታችንን የሚሰማውና ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን ይሖዋ ቢሆንም የእሱን ፈቃድ እንዲያስፈጽም ለኢየሱስ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ማቴ. 28:18) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ከመስጠቱ በፊት ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጋችንን ይመለከታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴ. 6:14, 15) ይሖዋና ኢየሱስ እኛን በደግነት እንደሚይዙን ሁሉ እኛም ሌሎችን በደግነት መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

7. ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እነማን ናቸው?

7 ከቤዛው ጥቅም ማግኘት የሚችሉት ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ‘ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ እንደሚሰጥ’ ተናግሯል። (ዮሐ. 15:13) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ታማኝ ሰዎች ወደፊት ስለ እሱ መማርና ለእሱ ፍቅር ማዳበር ይኖርባቸዋል። እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴና ረዓብ ያሉ ሰዎች ወደፊት ከሞት ይነሳሉ፤ ሆኖም እነዚህ ጻድቅ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉት ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት ከመሠረቱ ብቻ ነው።—ዮሐ. 17:3፤ ሥራ 24:15፤ ዕብ. 11:8-12, 24-26, 31

8-9. በዮሐንስ 15:4, 5 ላይ እንደተገለጸው ከኢየሱስ ጋር ያለን ወዳጅነት ምን እንድናከናውን ያስችለናል? በዚህ ጥቅስ መሠረት፣ ከኢየሱስ ጋር ያለንን አንድነት መጠበቅ ያለብንስ ለምንድን ነው?

8 በዛሬው ጊዜ፣ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ከኢየሱስ ጋር የመሥራት መብት አግኝተናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አስተማሪ ነበር። ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላም የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ መምራቱን ቀጥሏል። በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ስለ እሱና ስለ አባቱ እንዲያውቁ የምናደርገውን ጥረት ያያል፤ እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ደግሞም ይህን ሥራ ማከናወን የምንችለው ይሖዋና ኢየሱስ ከረዱን ብቻ ነው።ዮሐንስ 15:4, 5ን አንብብ።

9 ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን ኢየሱስን መውደድና ይህን ፍቅራችንን ጠብቀን መኖር እንዳለብን የአምላክ ቃል በግልጽ ይናገራል። እንግዲያው የኢየሱስ ወዳጆች ለመሆን የሚረዱንን አራት ነገሮች እንመልከት።

ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው?

የኢየሱስ ወዳጅ ለመሆን የሚረዱ እርምጃዎች፦ (1) ኢየሱስን በደንብ ማወቅ፣ (2) እሱን በአስተሳሰቡና በድርጊቱ መምሰል፣ (3) የክርስቶስን ወንድሞች መደገፍ፣ (4) ጉባኤው የሚያደርገውን ዝግጅት መደገፍ (ከአንቀጽ 10-14⁠ን ተመልከት) *

10. ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚረዳን የመጀመሪያው እርምጃ ምንድን ነው?

10 (1) ኢየሱስን በደንብ እወቁት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ መጻሕፍት ማንበባችን ለዚህ ይረዳናል። ስለ ኢየሱስ ሕይወት በሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ስናሰላስል ኢየሱስ ሰዎችን እንዴት በደግነት እንደያዛቸው እንገነዘባለን፤ ይህም ለእሱ ያለን ፍቅርና አክብሮት እንዲጨምር ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ጌታቸው ቢሆንም እንኳ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ባሪያ አልያዛቸውም። ከዚህ ይልቅ የውስጡን ሐሳብና ስሜቱን አካፍሏቸዋል። (ዮሐ. 15:15) ኢየሱስ ሐዘናቸውን ተጋርቷል፤ እንዲሁም አብሯቸው አልቅሷል። (ዮሐ. 11:32-36) ተቃዋሚዎቹ እንኳ ኢየሱስ መልእክቱን ለሚቀበሉ ሰዎች ወዳጅ እንደሆነ አምነው ተቀብለዋል። (ማቴ. 11:19) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ የምንከተል ከሆነ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ይሻሻላል፤ እንዲሁም ደስታችን የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ ለክርስቶስ ያለን አድናቆት እያደገ ይሄዳል።

11. የኢየሱስ ወዳጅ ለመሆን የሚረዳን ሁለተኛው እርምጃ ምንድን ነው? ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

11 (2) ኢየሱስን በአስተሳሰቡና በድርጊቱ ምሰሉት። ኢየሱስን ባወቅነውና የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ለመያዝ ጥረት ባደረግን መጠን ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እየተጠናከረ ይሄዳል። (1 ቆሮ. 2:16) ታዲያ ኢየሱስን በየትኞቹ መንገዶች መምሰል እንችላለን? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስን ይበልጥ የሚያሳስበው ሌሎችን መርዳት እንጂ ራሱን ማስደሰት አልነበረም። (ማቴ. 20:28፤ ሮም 15:1-3) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ስለነበረው የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግና ይቅር ባይ ሰው ነበር። ሰዎች ስለ እሱ በሚናገሩት ነገር ቶሎ አይበሳጭም ነበር። (ዮሐ. 1:46, 47) በተጨማሪም ቀደም ሲል ስህተት የሠሩ ሰዎች ለውጥ ሊያደርጉ እንደማይችሉ አያስብም ነበር። (1 ጢሞ. 1:12-14) ኢየሱስ ለሌሎች የነበረውን አመለካከት ማንጸባረቃችን አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:35) እንግዲያው ‘ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በሰላም ለመኖር ስል የምችለውን ሁሉ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተልኩ ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

12. የኢየሱስ ወዳጅ ለመሆን የሚረዳን ሦስተኛው እርምጃ ምንድን ነው? ይህን እርምጃ መውሰዳችንን ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?

12 (3) የክርስቶስን ወንድሞች ደግፉ። ኢየሱስ፣ ለቅቡዓን ወንድሞቹ የምናደርገውን ነገር ለእሱ እንዳደረግነው አድርጎ ይቆጥረዋል። (ማቴ. 25:34-40) ቅቡዓኑን መደገፍ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ፣ ኢየሱስ ለተከታዮቹ በሰጠው የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 10:42) የክርስቶስ ወንድሞች በዛሬው ጊዜ እየተከናወነ ያለውን ታላቅ ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ ዳር ማድረስ የሚችሉት “ሌሎች በጎች” በሚያደርጉላቸው እርዳታ ብቻ ነው። (ዮሐ. 10:16) አንተም የሌሎች በጎች አባል ከሆንክ፣ በዚህ ሥራ በተካፈልክ ቁጥር ለቅቡዓኑ ብቻ ሳይሆን ለኢየሱስም ያለህን ፍቅር እያሳየህ ነው።

13. በሉቃስ 16:9 ላይ የተጠቀሰውን የኢየሱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

13 የይሖዋና የኢየሱስ ወዳጆች መሆናችንን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ እነሱ የሚመሩትን ሥራ በገንዘብ መደገፍ ነው። (ሉቃስ 16:9ን አንብብ።) ለምሳሌ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ እንችላለን፤ የሚዋጣው ገንዘብ ራቅ ባሉ ስፍራዎች የሚከናወነውን የስብከት ሥራ ለመደገፍ፣ ለእውነተኛው አምልኮ የሚውሉ ሕንፃዎችን ለመገንባትና ለመንከባከብ እንዲሁም አደጋ ለደረሰባቸው ክርስቲያኖች ቁሳዊ እርዳታ ለመስጠት ይውላል። በተጨማሪም ለጉባኤያችን ወጪዎች የገንዘብ መዋጮ ማድረግና ችግር እንደገጠማቸው የምናውቃቸውን ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ መርዳት እንችላለን። (ምሳሌ 19:17) በእነዚህ መንገዶች የክርስቶስን ወንድሞች መደገፍ እንችላለን።

14. በኤፌሶን 4:15, 16 መሠረት የኢየሱስ ወዳጅ ለመሆን የሚረዳን አራተኛው እርምጃ ምንድን ነው?

14 (4) የክርስቲያን ጉባኤ የሚያደርገውን ዝግጅት ደግፉ። እኛን እንዲንከባከቡን ከተሾሙ ወንዶች ጋር የምንተባበር ከሆነ የጉባኤው ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል። (ኤፌሶን 4:15, 16ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስብሰባ አዳራሾቻችን ያላቸውን አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው። ለዚህም ሲባል አንዳንድ ጉባኤዎች እንዲዋሃዱ ተደርጓል፤ እንዲሁም በአገልግሎት ክልሎች ላይ ማስተካከያ ተደርጓል። ይህ ዝግጅት በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ለመቆጠብ አስችሏል። ይሁንና ዝግጅቱ፣ በአንዳንድ አስፋፊዎች ላይ ለውጥ አስከትሏል። እነዚህ ታማኝ አስፋፊዎች በአንድ ጉባኤ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም በዚያ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተው ይሆናል። በዚህ ዝግጅት ምክንያት ግን በሌላ ጉባኤ እንዲያገለግሉ ተጠይቀዋል። ኢየሱስ፣ እነዚህ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ዝግጅቱን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!

ለዘላለም የኢየሱስ ወዳጆች መሆን

15. ከኢየሱስ ጋር ያለን ወዳጅነት ወደፊት የሚጠናከረው እንዴት ነው?

15 በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር ለዘላለም አብረው የመሆን ተስፋ አላቸው፤ የአምላክ መንግሥት ወራሾች በመሆን አብረውት ይገዛሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ቃል በቃል ከክርስቶስ ጋር የመሆን ይኸውም እሱን ፊት ለፊት የማየት፣ ከእሱ ጋር የመነጋገርና አብረው ጊዜ የማሳለፍ መብት ያገኛሉ። (ዮሐ. 14:2, 3) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ፍቅርና እንክብካቤ ያገኛሉ። ኢየሱስን ፊት ለፊት የማየት አጋጣሚ ባያገኙም ይሖዋና ኢየሱስ የሰጧቸውን አስደሳች ሕይወት ስለሚያጣጥሙ ከኢየሱስ ጋር ያላቸው ዝምድና ይበልጥ ይጠናከራል።—ኢሳ. 9:6, 7

16. ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን ምን በረከቶች ያስገኝልናል?

16 ኢየሱስ የእሱ ወዳጆች እንድንሆን ያቀረበልንን ግብዣ መቀበላችን ብዙ በረከቶች ያስገኝልናል። ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ የእሱን ፍቅርና ድጋፍ እናገኛለን። ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተዘርግቶልናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ከኢየሱስ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት የኢየሱስ አባት ከሆነው ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ያስችለናል፤ ይህ ደግሞ እጅግ የላቀ ሀብት ነው። በእርግጥም የኢየሱስ ወዳጅ ተብለን መጠራታችን ትልቅ መብት ነው!

መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”

^ አን.5 ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር በመጨዋወትና በመሥራት የተወሰኑ ዓመታት አሳልፈዋል፤ ይህም ጥሩ ወዳጆች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ኢየሱስ፣ እኛም ወዳጆቹ እንድንሆን ይፈልጋል፤ ሆኖም የእሱ ወዳጆች ለመሆን ጥረት ስናደርግ ሐዋርያቱ ያላጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ይህ ርዕስ አንዳንዶቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያብራራል፤ በተጨማሪም ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረትና ይህን ወዳጅነት ጠብቀን ማቆየት የምንችልባቸውን እርምጃዎች ይገልጻል።

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ (1) በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችን፣ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ማጥናት እንችላለን። (2) በጉባኤ ውስጥ፣ ከወንድሞቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ጥረት እናደርጋለን። (3) በአገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ የክርስቶስን ወንድሞች እንደግፋለን። (4) ጉባኤዎች እንዲዋሃዱ ዝግጅት ሲደረግ ከሽማግሌዎች ውሳኔ ጋር እንተባበራለን።