በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 20

በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው?

በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው?

“ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ የሚረዳውም አይኖርም።”—ዳን. 11:45

መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው

ማስተዋወቂያ *

1-2. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻዎቹ ቀናት ማብቂያ ላይ እንደሆነ የሚጠቁሙ ማስረጃዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በግልጽ እየታዩ ነው። በቅርቡ ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የአምላክን መንግሥት የሚቃወሙ መንግሥታትን በሙሉ ያጠፋሉ። እስከዚያ ድረስ ግን የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ እርስ በርስ መዋጋታቸውንና የአምላክን ሕዝብ ማጥቃታቸውን ይቀጥላሉ።

2 በዚህ ርዕስ ላይ፣ ከዳንኤል 11:40 እስከ 12:1 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ትንቢት እንመረምራለን። በአሁኑ ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ ማን እንደሆነ እናያለን፤ በተጨማሪም ከፊታችን የሚጠብቁንን ፈተናዎች በልበ ሙሉነት መጋፈጥ እንችላለን የምንልባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን።

አዲስ የሰሜን ንጉሥ ብቅ አለ

3-4. በዛሬው ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥ ማን ነው? አብራራ።

3 ሶቪየት ኅብረት በ1991 ከፈራረሰ በኋላ ሰፊ በሆነው ግዛቱ የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች “መጠነኛ እርዳታ” ማለትም ለተወሰነ ጊዜ ነፃነት አግኝተው ነበር። (ዳን. 11:34) በመሆኑም በነፃነት መስበክ ችለው ነበር፤ በሶቪየት ኅብረት ሥር በነበሩት አገሮች ውስጥ የአስፋፊዎች ቁጥር ብዙም ሳይቆይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሆነ። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሩሲያ እና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ ሆነው ብቅ አሉ። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አንድ መንግሥት የሰሜኑ ንጉሥ ወይም የደቡቡ ንጉሥ እንዲባል የሚከተሉትን ሦስት መሥፈርቶች ማሟላት አለበት፦ (1) ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል፤ (2) ድርጊቱ፣ ይሖዋንና ሕዝቦቹን እንደሚጠላ ሊያሳይ ይገባል፤ (3) ከተቀናቃኙ ንጉሥ ጋር መፎካከር አለበት።

4 በዛሬው ጊዜ፣ ሩሲያና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ ናቸው የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት። (1) ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፤ በስብከቱ ሥራ ላይ እገዳ ጥለዋል፤ እንዲሁም በግዛታቸው ሥር በሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ላይ ስደት እያደረሱ ነው። (2) እንዲህ ማድረጋቸው ይሖዋን እና ሕዝቡን እንደሚጠሉ ያሳያል። (3) የደቡቡ ንጉሥ ከሆነው ከአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ጋር እየተፎካከሩ ነው። ሩሲያና አጋሮቿ፣ የሰሜኑ ንጉሥ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ምን ነገር እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት።

የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ እርስ በርስ መጋፋታቸውን ይቀጥላሉ

5. ዳንኤል 11:40-43 የሚገልጸው ስለ የትኛው ጊዜ ነው? በዚህ ጊዜስ ምን ይፈጸማል?

5 ዳንኤል 11:40-43ን አንብብ። ይህ የትንቢቱ ክፍል፣ በፍጻሜው ዘመን የሚከናወነውን ነገር ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል። ዘገባው በሰሜኑ ንጉሥና በደቡቡ ንጉሥ መካከል ስለሚኖረው ሽኩቻ ይናገራል። ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው፣ በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር “ይጋፋል” ወይም “ይጣላል።”—ዳን. 11:40 ግርጌ

6. ሁለቱ ነገሥታት መጋፋታቸውን እንደቀጠሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

6 የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ፣ በዓለም ላይ ኃያል መንግሥት ለመሆን የሚያደርጉትን ሽኩቻ አያቆሙም። ለምሳሌ ያህል፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሶቪየት ኅብረት እና አጋሮቹ በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍል ላይ ተጽዕኖ ባሳደሩበት ወቅት ምን እንደተፈጠረ እንመልከት። የሰሜኑ ንጉሥ ያደረገው ነገር፣ የደቡቡ ንጉሥ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የተባለ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ኅብረት እንዲመሠርት ምክንያት ሆኗል። የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ፣ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የጦር መሣሪያ በማከማቸት እርስ በርስ መፎካከራቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም በአፍሪካ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ በተቀሰቀሱ ዓመፆች ውስጥ ተቃራኒ ቡድኖችን በመደገፍ በእጅ አዙር ተዋግተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ሩሲያ እና አጋሮቿ በዓለም ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እየጨመረ መጥቷል። ከዚህም ሌላ በደቡቡ ንጉሥ ላይ የሳይበር ጥቃት (በኮምፒውተር አማካኝነት የሚሰነዘር ጥቃት) ሰንዝረዋል። ሁለቱ ነገሥታት፣ ኢኮኖሚያቸውንና የፖለቲካ ሥርዓታቸውን የሚጎዳ የኮምፒውተር ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው በመግለጽ አንዳቸው ሌላውን ሲወነጅሉ ቆይተዋል። በተጨማሪም ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክን ሕዝቦች ማጥቃቱን ቀጥሏል።—ዳን. 11:41

የሰሜኑ ንጉሥ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ይገባል

7. ‘ውብ የሆነችው ምድር’ የቷ ነች?

7 ዳንኤል 11:41 የሰሜኑ ንጉሥ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር እንደሚገባ’ ይናገራል። ይህች ምድር የቷ ነች? በጥንት ዘመን የእስራኤል ምድር “ከሌሎች አገሮች ሁሉ ይበልጥ ውብ” ተደርጋ ትቆጠር ነበር። (ሕዝ. 20:6) ሆኖም ይህችን ምድር ልዩ ያደረጋት የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል የነበረች መሆኗ ነው። በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ወዲህ ግን ይህች “ምድር” ቃል በቃል አንድን ቦታ ልታመለክት አትችልም፤ ምክንያቱም የይሖዋ ሕዝቦች የሚገኙት በመላው ዓለም ነው። በዛሬው ጊዜ፣ ‘ውብ የሆነችው ምድር’ የሚለው አገላለጽ የይሖዋን ሕዝቦች መንፈሳዊ ግዛት የሚያመለክት ነው፤ ይህ መንፈሳዊ ግዛት፣ የይሖዋ ሕዝቦች በስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ላይ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ያጠቃልላል።

8. የሰሜኑ ንጉሥ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ የገባው እንዴት ነው?

8 በመጨረሻዎቹ ቀናት፣ የሰሜኑ ንጉሥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል። በናዚዎች ይመራ የነበረው የጀርመን መንግሥት የሰሜን ንጉሥ በነበረበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል፤ ይህ የሰሜን ንጉሥ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአምላክን ሕዝቦች በማሳደድና በመግደል ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰሜን ንጉሥ የሆነው ሶቪየት ኅብረትም ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል፤ ይህን ያደረገው የአምላክን ሕዝቦች በማሳደድ እና በግዞት እንዲሄዱ በማድረግ ነው።

9. ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ ሩሲያ እና አጋሮቿ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ የገቡት እንዴት ነው?

9 ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ሩሲያ እና አጋሮቿ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብተዋል። ይህን ያደረጉት እንዴት ነው? በ2017 ይህ የሰሜን ንጉሥ፣ በይሖዋ ሕዝቦች ሥራ ላይ እገዳ የጣለ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን አስሯል። ከዚህም ሌላ አዲስ ዓለም ትርጉምን ጨምሮ ጽሑፎቻችንን አግዷል። በተጨማሪም በሩሲያ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሯችንን እንዲሁም የጉባኤ ስብሰባና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን ወርሷል። ይህ ከሆነ በኋላ በ2018 የበላይ አካሉ፣ ሩሲያና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ መሆናቸውን ግልጽ አደረገ። የይሖዋ ሕዝቦች፣ ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም በሰብዓዊ መንግሥታት ላይ ለማመፅ ወይም እነሱን ለመገልበጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለመካፈል ፈቃደኛ አይሆኑም። ከዚህ ይልቅ ‘በሥልጣን ላይ ላሉት ሁሉ’ እንድንጸልይ የሚያበረታታውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ፤ በተለይም እነዚህ መንግሥታት የአምልኮ ነፃነታችንን ሊነኩ የሚችሉ ውሳኔዎች በሚያደርጉበት ወቅት እንዲህ ማድረግ አለብን።—1 ጢሞ. 2:1, 2

የሰሜኑ ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ ያሸንፈዋል?

10. የሰሜኑ ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ ያሸንፈዋል? አብራራ።

10 በዳንኤል 11:40-45 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዋነኝነት የሚያተኩረው የሰሜኑ ንጉሥ በሚያደርገው ነገር ላይ ነው። ታዲያ ይህ፣ የሰሜኑ ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ እንደሚያሸንፈው የሚጠቁም ነው? አይደለም። የደቡቡ ንጉሥ፣ ይሖዋና ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት በሚያጠፉበት ወቅት “በሕይወት” ይኖራል። (ራእይ 19:20) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በዳንኤልና በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ትንቢቶች ምን እንደሚጠቁሙ እስቲ እንመልከት።

በድንጋይ የተመሰለው የአምላክ መንግሥት፣ በግዙፉ ምስል የተወከሉትን ሰብዓዊ መንግሥታት በአርማጌዶን ጦርነት ያጠፋል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ዳንኤል 2:43-45 ምን ይጠቁማል? (ሽፋኑን ተመልከት።)

11 ዳንኤል 2:43-45ን አንብብ። ነቢዩ ዳንኤል፣ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላቸውና በተከታታይ ስለሚነሱ ሰብዓዊ መንግሥታት ገልጿል። እነዚህ መንግሥታት፣ በግዙፉ ምስል የተለያዩ ክፍሎች ተመስለዋል። ከእነዚህ ሰብዓዊ መንግሥታት የመጨረሻው፣ የብረትና የሸክላ ቅልቅል በሆነው የምስሉ እግር ተመስሏል። የምስሉ እግር፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ያመለክታል። የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን ለማጥፋት እርምጃ በሚወስድበት ወቅት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በሥልጣን ላይ እንደሚሆን ትንቢቱ ይጠቁማል።

12. የአውሬው ሰባተኛ ራስ ማንን ያመለክታል? ይህስ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

12 ሐዋርያው ዮሐንስም በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩና በተከታታይ ስለሚነሱ የዓለም ኃያል መንግሥታት ገልጿል። ዮሐንስ፣ እነዚህን መንግሥታት ሰባት ራስ ባለው አውሬ መስሏቸዋል። የዚህ አውሬ ሰባተኛ ራስ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ያመለክታል። ይህ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም አውሬው ሌላ ራስ እንደሚያወጣ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ክርስቶስና ሰማያዊ ሠራዊቱ ይህን ሰባተኛ ራስ ጨምሮ አውሬውን ለማጥፋት እርምጃ በሚወስዱበት ወቅት ሰባተኛው ራስ በሥልጣን ላይ ይሆናል። *ራእይ 13:1, 2፤ 17:13, 14

የሰሜኑ ንጉሥ በቅርቡ ምን ያደርጋል?

13-14. ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ማን ነው? የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት የሚያነሳሳውስ ምን ሊሆን ይችላል?

13 የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ ከመጥፋታቸው በፊት ምን እንደሚፈጠር የሕዝቅኤል ትንቢት አንዳንድ መረጃ ይሰጠናል። በሕዝቅኤል 38:10-23፣ በዳንኤል 2:43-45፤ 11:44 እስከ 12:1 እንዲሁም በራእይ 16:13-16, 21 ላይ የሚገኙት ትንቢቶች የሚናገሩት ስለ ተመሳሳይ ጊዜ እና ክንውኖች ይመስላል፤ ይህ እውነት ከሆነ፣ የሚከተሉት ነገሮች ይፈጸማሉ ብለን መጠበቅ እንችላለን።

14 ታላቁ መከራ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‘የዓለም ነገሥታት’ ጥምረት ይፈጥራሉ። (ራእይ 16:13, 14፤ 19:19) ይህን ጥምረት፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ብለው ይጠሩታል። (ሕዝ. 38:2) ጥምረት የፈጠሩት ብሔራት፣ የአምላክን ሕዝቦች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ይህን ጥቃት እንዲሰነዝሩ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ በዚህ ጊዜ ስለሚፈጸመው ነገር ሲናገር እጅግ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ በአምላክ ጠላቶች ላይ እንደሚወርድ ገልጿል። ይህ ምሳሌያዊ በረዶ፣ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያውጁትን ከባድ የፍርድ መልእክት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። የማጎጉ ጎግ የአምላክን ሕዝቦች ከምድር ገጽ ለማጥፋት የሚነሳው ይህ መልእክት ስለሚያስቆጣው ሊሆን ይችላል።—ራእይ 16:21

15-16. (ሀ) ዳንኤል 11:44, 45 የሚገልጸው ስለ የትኞቹ ክንውኖች ሊሆን ይችላል? (ለ) የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ ሌሎቹ የማጎጉ ጎግ አባላት ምን ይጠብቃቸዋል?

15 የአምላክ ሕዝቦች የሚያውጁት ይህ ከባድ መልእክትና የአምላክ ጠላቶች የሚሰነዝሩት የመጨረሻ ጥቃት በዳንኤል 11:44, 45 ላይ በትንቢት የተገለጹት ክንውኖች ሊሆኑ ይችላሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) ዳንኤል በዚህ ትንቢት ላይ እንደገለጸው “ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣ ወሬ [የሰሜኑን ንጉሥ] ይረብሸዋል፤” በመሆኑም “በታላቅ ቁጣ ይወጣል።” የሰሜኑ ንጉሥ የሚወጣው “ብዙዎችን ለመደምሰስ” ነው። በጥቅሱ ላይ “ብዙዎች” የተባሉት የይሖዋ ሕዝቦች ሳይሆኑ አይቀሩም። * ዳንኤል በዚህ ትንቢት ላይ እየተናገረ ያለው፣ የአምላክን ሕዝቦች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ስለሚሰነዘረው ጥቃት ይመስላል።

16 የሰሜኑ ንጉሥ ከሌሎቹ የዓለም መንግሥታት ጋር በመሆን የሚሰነዝረው ይህ ጥቃት ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ቁጣ ይቀሰቅሰዋል፤ ከዚያም የአርማጌዶን ጦርነት ይጀምራል። (ራእይ 16:14, 16) በዚያን ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ ሌሎቹ የማጎጉ ጎግ አባላት ወደ ፍጻሜያቸው ይመጣሉ፤ የሰሜኑን ንጉሥ “የሚረዳውም አይኖርም።”—ዳን. 11:45

ኢየሱስ ክርስቶስ እና ሰማያዊ ሠራዊቱ በአርማጌዶን ጦርነት የሰይጣንን ክፉ ዓለም ያጠፋሉ፤ እንዲሁም የአምላክን ሕዝቦች ይታደጋሉ (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. በዳንኤል 12:1 ላይ የተጠቀሰው “ታላቁ አለቃ ሚካኤል” ማን ነው? ምንስ ያደርጋል?

17 ዳንኤል በጻፈው ዘገባ ላይ የሚገኘው ቀጣዩ ሐሳብ፣ የሰሜኑ ንጉሥና አጋሮቹ ወደ ፍጻሜያቸው የሚመጡበትንና መዳን የምናገኝበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል። (ዳንኤል 12:1ን አንብብ።) በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው? ሚካኤል፣ የንጉሣችን የክርስቶስ ኢየሱስ ሌላ ስም ነው። ሚካኤል ለአምላክ ሕዝቦች ‘መቆም’ የጀመረው መንግሥቱ በ1914 በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ነው። በቅርቡ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ደግሞ “ይነሳል” ማለትም ወሳኝ እርምጃ ይወስዳል። ይህ ጦርነት፣ ዳንኤል ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ “የጭንቀት ጊዜ” በማለት የጠራው ወቅት የመጨረሻ ክንውን ይሆናል። ይህ ጦርነትና ከዚያ በፊት ያለው ጊዜ፣ ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ ላይ ባሰፈረው ትንቢት ላይ ‘ታላቁ መከራ’ ተብሎ ተጠርቷል።—ራእይ 6:2፤ 7:14

ስምህ ‘በመጽሐፍ ላይ ይጻፍ’ ይሆን?

18. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

18 የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም ዳንኤልም ሆነ ዮሐንስ፣ ይሖዋንና ኢየሱስን የሚያገለግሉ ሁሉ በታሪክ ውስጥ ሆኖ ከማያውቀው ከዚህ የጭንቀት ጊዜ እንደሚተርፉ ገልጸዋል። ዳንኤል፣ ስማቸው ‘በመጽሐፍ ላይ የተጻፈ’ ሁሉ ከጥፋቱ እንደሚተርፉ ተናግሯል። (ዳን. 12:1) ታዲያ ስማችን በዚህ መጽሐፍ ላይ እንዲጻፍ ምን ማድረግ አለብን? የአምላክ በግ በሆነው በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን በግልጽ ማሳየት ይኖርብናል። (ዮሐ. 1:29) ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በጥምቀት ማሳየት አለብን። (1 ጴጥ. 3:21) በተጨማሪም ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን በማድረግ የአምላክን መንግሥት እንደምንደግፍ ማሳየት ይኖርብናል።

19. አሁኑኑ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

19 በይሖዋና ታማኝ አገልጋዮቹን ባቀፈው ድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያለብን አሁን ነው። የአምላክን መንግሥት መደገፍ ያለብንም አሁን ነው። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ መንግሥት የሰሜኑን ንጉሥና የደቡቡን ንጉሥ በሚያጠፋበት ወቅት ለመዳን ያስችለናል።

መዝሙር 149 የድል መዝሙር

^ አን.5 በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው? ወደ ፍጻሜው የሚመጣውስ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን እምነታችንን ያጠናክርልናል፤ እንዲሁም በቅርቡ ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች እንድንዘጋጅ ይረዳናል።

^ አን.12 ዳንኤል 2:36-45⁠ን እና ራእይ 13:1, 2⁠ን በተመለከተ ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት የሰኔ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 7-19⁠ን ተመልከት።

^ አን.15 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-30⁠ን ተመልከት።