በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 24

“ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ”

“ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ”

“ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ። ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ በሙሉ ልቤ አወድስሃለሁ።”—መዝ. 86:11, 12

መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን

ማስተዋወቂያ *

1. አምላካዊ ፍርሃት ምንድን ነው? ይሖዋን የሚወዱ ሁሉ እንዲህ ዓይነት ፍርሃት ማዳበራቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

ክርስቲያኖች አምላክን ይወዱታል እንዲሁም ይፈሩታል። አንዳንዶች ይህ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሐሳብ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም ፍርሃት ስንል እንድንሸበር ስለሚያደርግ ስሜት እያወራን አይደለም። በዚህ ርዕስ ላይ የምንመለከተው ለየት ስላለ የፍርሃት ዓይነት ነው። እንዲህ ዓይነት ፍርሃት ያላቸው ሰዎች፣ ለአምላክ ጥልቅና ከልብ የመነጨ አክብሮት አላቸው። ከሰማዩ አባታቸው ጋር የመሠረቱት ወዳጅነት እንዲበላሽባቸው ስለማይፈልጉ እሱን የሚያሳዝን ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቃሉ።—መዝ. 111:10፤ ምሳሌ 8:13

2. ንጉሥ ዳዊት በመዝሙር 86:11 ላይ የተናገረውን ሐሳብ መሠረት በማድረግ የትኞቹን ሁለት ነገሮች እንመረምራለን?

2 መዝሙር 86:11ን አንብብ። በዚህ ጥቅስ ላይ ስታሰላስል ታማኙ ንጉሥ ዳዊት አምላካዊ ፍርሃት የማሳየትን አስፈላጊነት ተገንዝቦ እንደነበር ታስተውላለህ። ዳዊት በመንፈስ መሪነት የጻፈውን ሐሳብ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ፣ ለአምላክ ስም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲኖረን የሚያነሳሱ አንዳንድ ምክንያቶችን እናያለን። ሁለተኛ ደግሞ ለአምላክ ስም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዳለን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዴት ማሳየት እንደምንችል እንመረምራለን።

ለይሖዋ ስም አክብሮታዊ ፍርሃት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

3. ሙሴ ለአምላክ ስም ምንጊዜም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲኖረው የረዳው የትኛው ክስተት ሊሆን ይችላል?

3 ሙሴ በዓለት ዋሻ ውስጥ ሆኖ፣ የይሖዋን ክብር የማየት አጋጣሚ አግኝቶ ነበር፤ ሙሴ በዚህ ወቅት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ስለዚህ ክንውን ሲናገር “ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የትኛውም የሰው ልጅ ከገጠመው አስደናቂ ነገር ሁሉ በላይ እጅግ የሚያስደምም ክስተት ሳይሆን አይቀርም” ይላል። ሙሴ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል” ተብሎ ሲታወጅ ሰምቷል፤ ይህን ሐሳብ የተናገረው አንድ መልአክ ሊሆን ይችላል። (ዘፀ. 33:17-23፤ 34:5-7) ሙሴ፣ ይሖዋ የሚለውን ስም ሲጠቀም ይህ ክስተት ወደ አእምሮው ሳይመጣ አይቀርም። ከዚህ አንጻር ሙሴ፣ የአምላክ ሕዝብ የሆኑትን እስራኤላውያንን ‘ክብራማና አስፈሪ የሆነውን የይሖዋን ስም እንዲፈሩ’ ከጊዜ በኋላ ማስጠንቀቁ የሚያስገርም አይደለም።—ዘዳ. 28:58

4. ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን የሚያደርገው በየትኞቹ ባሕርያቱ ላይ ማሰላሰላችን ነው?

4 ይሖዋ ስለሚለው ስም ስናስብ ስለ ስሙ ባለቤት ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። እንደ ኃይል፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር ስላሉት ባሕርያቱ ልናስብ ይገባል። በእነዚህና በሌሎች ባሕርያቱ ላይ ማሰላሰላችን ለእሱ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን ያደርጋል።—መዝ. 77:11-15

5-6. (ሀ) የአምላክ ስም ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) በዘፀአት 3:13, 14 እንዲሁም በኢሳይያስ 64:8 መሠረት ይሖዋ ፈቃዱ እንዲሆን የሚያደርገው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 የአምላክ ስም ትርጉም ምንድን ነው? የይሖዋ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል በርካታ ምሁራን ይገልጻሉ። ይህ የስሙ ትርጉም፣ የይሖዋ ፈቃድ እንዳይፈጸም ሊያግድ የሚችል ምንም ነገር እንደሌለና ይሖዋ፣ የሚፈልገው ነገር ሁሉ እንዲሆን ማድረግ እንደሚችል ያስታውሰናል። ይሖዋ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በመሆን፣ የሚፈልገው እንዲሆን ያደርጋል። (ዘፀአት 3:13, 14ን አንብብ።) አምላካችን እንዲህ ያለ ማንነት ያለው መሆኑ ለእሱ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን የሚያደርግ ሲሆን ጽሑፎቻችንም በዚህ ላይ እንድናሰላስል ብዙ ጊዜ ያበረታቱናል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ እሱን ለማገልገልና ዓላማውን ለመፈጸም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዲሆኑ ማድረግ ይችላል። (ኢሳይያስ 64:8ን አንብብ።) ይሖዋ በእነዚህ መንገዶች ፈቃዱ እንዲፈጸም ያደርጋል። ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም።—ኢሳ. 46:10, 11

7. ለሰማዩ አባታችን ያለን አድናቆት እንዲጨምር ምን ማድረግ እንችላለን?

7 የሰማዩ አባታችን ባደረጋቸውና እኛም እንድናደርግ ባስቻለን ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ለእሱ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አስደናቂ በሆኑት የፍጥረት ሥራዎች ላይ ስናሰላስል ይሖዋ ባከናወናቸው ይኸውም ወደ ሕልውና እንዲመጡ ባደረጋቸው ነገሮች መደመማችን አይቀርም። (መዝ. 8:3, 4) ከዚህም ሌላ ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስፈልገንን እንድንሆን ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ለእሱ ጥልቅ አክብሮት እንዲያድርብን ያደርጋል። በእርግጥም ይሖዋ የሚለው ስም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን የሚያደርግ ነው! የአምላክ ስም ትርጉም፣ የአባታችንን አጠቃላይ ማንነት እንዲሁም እስከ ዛሬ ያደረጋቸውንና ወደፊት የሚያደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ያካትታል።—መዝ. 89:7, 8

“የይሖዋን ስም አውጃለሁ”

የሙሴ ትምህርት መንፈስን የሚያድስ ነበር። ትምህርቱ ያተኮረው በይሖዋ አምላክ ስምና በማንነቱ ላይ ነበር (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት) *

8. ዘዳግም 32:2, 3 ይሖዋ ለስሙ ስላለው አመለካከት ምን ያስተምረናል?

8 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ ይሖዋ ለሙሴ አንድ መዝሙር አስተምሮት ነበር። (ዘዳ. 31:19) ሙሴ ደግሞ መዝሙሩን ለሕዝቡ እንዲያስተምር ታዟል። (ዘዳግም 32:2, 3ን አንብብ።) በቁጥር 2 እና 3 ላይ ስናሰላስል ይሖዋ ስሙ እንዲሰወር እንደማይፈልግ በግልጽ እንረዳለን፤ በሌላ አባባል ‘ስሙ በጣም ቅዱስ ስለሆነ መጠራት የለበትም’ የሚለውን አመለካከት አይደግፍም። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ በሙሉ ስሙን እንዲያውቁት ይፈልጋል! እስራኤላውያን ስለ ይሖዋ እንዲሁም ስለ ክብራማ ስሙ የመማር አጋጣሚ በማግኘታቸው ምንኛ ታድለዋል! ካፊያ ተክልን እንደሚያረሰርሰው ሁሉ ሙሴ ያስተማራቸው ነገርም እስራኤላውያንን እምነታቸው እንዲጠናከርና መንፈሳቸው እንዲታደስ አድርጓቸው መሆን አለበት። እኛስ ትምህርታችን እንዲህ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9. የአምላክ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9 ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ወይም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ስንካፈል መጽሐፍ ቅዱሳችንን ተጠቅመን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ለሰዎች ልናሳያቸው እንችላለን። ይሖዋን የሚያስከብሩ ግሩም ጽሑፎች ልንሰጣቸው እንዲሁም ቪዲዮዎች ወይም ድረ ገጻችን ላይ የሚገኙ ነገሮችን ልናሳያቸው እንችላለን። በተጨማሪም በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት አሊያም በጉዞ ላይ ስንሆን፣ ስለምንወደው አምላካችንና ስለ ማንነቱ የመናገር አጋጣሚ እናገኝ ይሆናል። ይሖዋ ለሰው ዘሮችና ለምድር ስላለው ፍቅር የተንጸባረቀበት ዓላማ ለምናገኛቸው ሰዎች ስንነግራቸው ከዚህ በፊት ስለ ይሖዋ ፈጽሞ ሰምተው የማያውቁትን ነገር እንዲያውቁ እየረዳናቸው ሊሆን ይችላል። አፍቃሪ ስለሆነው አባታችን እውነቱን ለሌሎች ስንናገር ስሙ እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው። ሰዎች ስለ ይሖዋ የተማሯቸውን ውሸቶች በዚህ መንገድ እናጋልጣለን። በእርግጥም ለሰዎች የምናስተምረው ትምህርት ከምንም በላይ መንፈስን የሚያድስ ነው።—ኢሳ. 65:13, 14

10. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ ስለ አምላክ የጽድቅ መሥፈርቶችና ደንቦች ከማስተማር ያለፈ ነገር ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

10 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና የይሖዋን ስም እንዲያውቁና እንዲጠቀሙበት መርዳት እንፈልጋለን። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ስም የሚያካትታቸውን ነገሮች እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው እንፈልጋለን። ሆኖም መመሪያዎችን፣ መለኮታዊ መሥፈርቶችንና የሥነ ምግባር ደንቦችን በማስተማር ብቻ ይህን ማሳካት እንችላለን? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ስለ አምላክ ሕግጋት ጥሩ ግንዛቤ ሊኖረው ሌላው ቀርቶ ለእነዚህ ሕግጋት አድናቆት ሊያዳብር ይችላል። ይሁንና ተማሪው ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ እሱን ይታዘዛል? ሔዋን የአምላክን ሕግ ታውቅ እንደነበር እናስታውስ፤ ሆኖም እሷም ሆነች አዳም ሕጉን ለሰጣቸው አምላክ እውነተኛ ፍቅር አልነበራቸውም። (ዘፍ. 3:1-6) ይህ ሁኔታ እኛም ስለ አምላክ የጽድቅ መሥፈርቶችና ደንቦች ከማስተማር ያለፈ ነገር ማድረግ እንደሚጠበቅብን ይጠቁማል።

11. ጥናቶቻችንን ስለ አምላክ ሕግጋትና መሥፈርቶች ስናስተምር ሕግጋቱን የሰጠውን አካል እንዲወዱት መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

11 የይሖዋ መሥፈርቶችና ደንቦች ተወዳጅና ጠቃሚ ናቸው። (መዝ. 119:97, 111, 112) ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ለአምላክ ትእዛዛት እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲያዳብሩ ይሖዋ ሕጎቹን የሰጠን በፍቅር ተነሳስቶ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ጥናቶቻችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቃቸው እንችላለን፦ “አምላክ አገልጋዮቹን እንዲህ እንዲያደርጉ ያዘዛቸው ወይም እንዲህ እንዳያደርጉ የከለከላቸው ለምን ይመስልሃል? ይህስ ስለ አምላክ ባሕርይ ምን ያስተምረናል?” ጥናቶቻችንን ስለ ይሖዋ እንዲያስቡ እንዲሁም ለክብራማ ስሙ እውነተኛ ፍቅር እንዲያድርባቸው ከረዳናቸው ልባቸውን መንካት እንችል ይሆናል። በዚህ መንገድ የአምላክን ሕግጋት ብቻ ሳይሆን ሕጉን የሰጠውን አካልም እንዲወዱት መርዳት እንችላለን። (መዝ. 119:68) እምነታቸው እየተጠናከረ እንዲሄድና እንደ እሳት ያሉ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም እንዲችሉ እንረዳቸዋለን።—1 ቆሮ. 3:12-15

‘በይሖዋ ስም እንሄዳለን’

በአንድ ወቅት ዳዊት ልቡ እንዲከፈል ፈቅዶ ነበር (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. በአንድ ወቅት ዳዊት ልቡ የተከፈለው እንዴት ነበር? ይህስ ምን አስከተለ?

12 በመዝሙር 86:11 ላይ “ልቤን አንድ አድርግልኝ” የሚል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሐሳብ አለ። ይህን ሐሳብ በመንፈስ መሪነት የጻፈው ንጉሥ ዳዊት ነው። ዳዊት ልባችን በቀላሉ ሊከፈል እንደሚችል በገዛ ሕይወቱ ተመልክቷል። በአንድ ወቅት በቤቱ ሰገነት ላይ እያለ የሌላ ሰው ሚስት ሰውነቷን ስትታጠብ አየ። ታዲያ በዚያ ወቅት የዳዊት ልብ አንድ ነበር ወይስ ተከፍሎ ነበር? ዳዊት “የባልንጀራህን ሚስት . . . አትመኝ” የሚለውን የይሖዋ ሕግ ያውቅ ነበር። (ዘፀ. 20:17) ያም ሆኖ ሴቲቱን መመልከቱን የቀጠለ ይመስላል። በአንድ በኩል ይሖዋን ማስደሰት ቢፈልግም በሌላ በኩል ደግሞ ቤርሳቤህን ስለተመኘ ልቡ ተከፈለ። ዳዊት ሕይወቱን በሙሉ ይሖዋን የሚወድና የሚፈራ ሰው ቢሆንም ለራስ ወዳድነት ምኞቱ ተሸነፈ። በመሆኑም በጣም መጥፎ ድርጊት ፈጸመ። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ አመጣ። ከዚህም ሌላ ቤተሰቡን ጨምሮ ሌሎች ንጹሐን ሰዎች እንዲጎዱ አደረገ።—2 ሳሙ. 11:1-5, 14-17፤ 12:7-12

13. ዳዊት እንደገና ልቡን አንድ ማድረግ እንደቻለ እንዴት እናውቃለን?

13 ይሖዋ ለዳዊት ተግሣጽ የሰጠው ሲሆን እሱም ከይሖዋ ጋር ያለውን ግንኙነት ማደስ ቻለ። (2 ሳሙ. 12:13፤ መዝ. 51:2-4, 17) ዳዊት ልቡ እንዲከፈል መፍቀዱ ያስከተለውን መከራና ሥቃይ አልረሳም። በመዝሙር 86:11 ላይ የሚገኘው እሱ የተናገረው ሐሳብ “ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ታዲያ ይሖዋ፣ ልቡ ሙሉ ወይም ያልተከፋፈለ እንዲሆን ዳዊትን ረድቶት ነበር? አዎ፣ ከጊዜ በኋላ የአምላክ ቃል ስለ ዳዊት ሲናገር ‘ልቡ በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ እንደነበር’ ይገልጻል።—1 ነገ. 11:4፤ 15:3

14. ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል? ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

14 የዳዊት ምሳሌ የሚያበረታታ ብቻ ሳይሆን ማስጠንቀቂያ የሚሰጥም ነው። ዳዊት ከባድ ኃጢአት መፈጸሙ በዛሬው ጊዜ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች ማስጠንቀቂያ ነው። ይሖዋን ማገልገል የጀመርነው በቅርቡም ይሁን ከረጅም ዓመታት በፊት ‘ሰይጣን ልቤን ለመከፋፈል የሚያደርገውን ጥረት እየተቃወምኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል።

ሰይጣን ልብህ እንዲከፈል ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ልብህን እንዲከፍለው አትፍቀድለት! (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ምስል ሲገጥመን አምላካዊ ፍርሃት ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

15 ለምሳሌ ያህል፣ የፆታ ስሜት ሊቀሰቅስ የሚችል ምስል በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት ቢገጥምህ ምን ታደርጋለህ? ምስሉ ወይም ፊልሙ ፖርኖግራፊ ሊባል እንደማይችል ሰበብ ማቅረብ ቀላል ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሰይጣን ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ልብህን ለመክፈል እየጣረ ይሆን? (2 ቆሮ. 2:11) ምስሉ አንድ ሰው እንጨት ሲጠርብ ከሚጠቀምበት ሽብልቅ ወይም ትንሽ ሹል ብረት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሰውየው መጀመሪያ ላይ የብረቱን ሹል ጫፍ እንጨቱ ውስጥ ያስገባዋል። ሰውየው ብረቱን ይበልጥ ወደ ውስጥ እያስገባው ሲሄድ እንጨቱ ይሰነጠቃል። በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት ላይ የሚቀርብ አጠያያቂ ምስል እንደ ሽብልቁ ሹል ጫፍ ይሆን? አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ ትንሽ እንደሆነ ወይም ጉዳት እንደሌለው የሚሰማው ነገር እንኳ ብዙም ሳይቆይ ልቡ እንዲከፈል ሊያደርግ ይችላል፤ ይህም ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ የሚያደርግ ኃጢአት ወደ መፈጸም ሊመራው ይችላል። እንግዲያው ተገቢ ያልሆነ ማንኛውም ነገር ወደ ልብህ እንዲገባ አትፍቀድ! ልብህ ምንጊዜም የይሖዋን ስም እንዲፈራ አንድ አድርገው!

16. መጥፎ ነገር ለመፈጸም ስንፈተን ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቃችን አስፈላጊ ነው?

16 ሰይጣን የፆታ ስሜት ከሚቀሰቅሱ ምስሎች በተጨማሪ ሌሎች ነገሮችንም በመጠቀም መጥፎ ነገር እንድንፈጽም ይፈትነናል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ፈተና ሲያጋጥመን ምን እናደርጋለን? በዚህ ጊዜ ሰበብ መደርደር ይቀናን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ይህን ባደርግ ከጉባኤ አልወገድም፤ ያን ያህል ከባድ ኃጢአት ባይሆን ነው’ ብለን እናስብ ይሆናል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በጣም የተሳሳተ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ሰይጣን በዚህ ፈተና ተጠቅሞ ልቤን ለመክፈል እየሞከረ ነው? በመጥፎ ምኞቶች መሸነፌ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያመጣ ይሆን? እንዲህ ማድረጌ ወደ አምላኬ ይበልጥ ያቀርበኛል ወይስ ከእሱ ያርቀኛል?’ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ አሰላስል። ራስህን ሳታታልል በሐቀኝነት መልስ መስጠት እንድትችል ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጥህ ጸልይ። (ያዕ. 1:5) እንዲህ ማድረግህ ትልቅ ጥበቃ ይሆንልሃል። በተጨማሪም ከሰይጣን የሚቀርብልህን ፈተና እንደ ኢየሱስ አጥብቀህ እንድትቃወም ይረዳሃል፤ ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ” ብሎት ነበር።—ማቴ. 4:10

17. የተከፋፈለ ልብ ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

17 የተከፋፈለ ልብ ምንም አይጠቅምም። እርስ በርስ የማይስማሙ አባላት ያሉትን አንድ የስፖርት ቡድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንዳንዶቹ የቡድኑ አባላት የሚያሳስባቸው በግላቸው የሚያገኙት ክብር ብቻ ነው፤ ሌሎቹ ደንቦቹን ጠብቀው መጫወት አይፈልጉም፤ የተወሰኑት ደግሞ ለአሠልጣኛቸው አክብሮት የላቸውም። እንዲህ ያለው ቡድን በውድድር የማሸነፍ አጋጣሚው በጣም ጠባብ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን አንድነት ያለው ቡድን፣ የማሸነፍ አጋጣሚው ሰፊ ነው። አንተም ልብህ እንደዚህ ስኬታማ የስፖርት ቡድን እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ፤ ይህ የሚሆነው ሐሳብህን፣ ምኞትህንና ስሜትህን አንድ በማድረግ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ካስማማኸው ነው። ሰይጣን ልብህን መክፈል እንደሚያስደስተው አትርሳ። ሐሳብህ፣ ምኞትህና ስሜትህ አንድ እንዳይሆኑ እንዲሁም ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር እንዲጋጩ ማድረግ ይፈልጋል። አንተ ግን ይሖዋን ለማገልገል ልብህ ሙሉ መሆን እንዳለበት ታውቃለህ። (ማቴ. 22:36-38) እንግዲያው ሰይጣን ልብህን እንዲከፋፍለው ፈጽሞ አትፍቀድለት!

18. በሚክያስ 4:5 ላይ በሚገኘው ሐሳብ መሠረት ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

18 አንተም እንደ ዳዊት “ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ” ብለህ ይሖዋን ለምነው። ከዚህ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ የመኖር ግብ ይኑርህ። ትንሽም ይሁን ትልቅ በየዕለቱ በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ለይሖዋ ቅዱስ ስም ያለህን ጥልቅ አክብሮት ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንዲህ ስታደርግ እንደ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጠን የይሖዋን ስም ማስከበር ትችላለህ። (ምሳሌ 27:11) ሁላችንም “በአምላካችን በይሖዋ ስም ለዘላለም እንሄዳለን” ብሎ የተናገረውን የነቢዩ ሚክያስ ሐሳብ እንደምንጋራ ማሳየት እንችላለን።—ሚክ. 4:5

መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ

^ አን.5 በመዝሙር 86:11, 12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የንጉሥ ዳዊት ጸሎት በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። የይሖዋን ስም መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? ለዚህ ታላቅ ስም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲኖረን የሚያነሳሳን ምንድን ነው? አምላክን መፍራት መጥፎ ነገር ለማድረግ በምንፈተንበት ጊዜ ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

^ አን.53 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሙሴ ይሖዋን የሚያስከብር መዝሙር ለሕዝቡ አስተምሯል።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሔዋን መጥፎ ምኞቶችን አልተቃወመችም። እኛ ግን መጥፎ ምኞቶች እንዲቀሰቀሱብን ከሚያደርጉና በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ የሚያመጣ ነገር እንድናደርግ ከሚገፋፉ ምስሎች ወይም መልእክቶች እንርቃለን።