በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

“የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች በገላትያ 5:22, 23 ላይ የተጠቀሱት ባሕርያት ብቻ ናቸው?

ይህ ጥቅስ፣ ዘጠኝ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ይዘረዝራል፤ ጥቅሱ “የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው” ይላል። ይሁንና በአምላክ መንፈስ እርዳታ የምናፈራቸው መልካም ባሕርያት እነዚህ ብቻ እንደሆኑ ማሰብ አይኖርብንም።

ሐዋርያው ጳውሎስ ቀደም ባሉት ቁጥሮች ላይ ምን ብሎ እንደጻፈ እንመልከት፦ “የሥጋ ሥራዎች . . . የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ዓይን ያወጣ ምግባር፣ ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው።” (ገላ. 5:19-21) ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ጳውሎስ “የሥጋ ሥራዎች” ተብለው የሚጠሩትን ነገሮች በሙሉ አልዘረዘረም፤ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በቆላስይስ 3:5 ላይ የተጠቀሱት ይገኙበታል። በተመሳሳይም ዘጠኙን መልካም ባሕርያት ከዘረዘረ በኋላ “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚከለክል ሕግ የለም” ብሏል። ስለዚህ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ልናፈራቸው የምንችላቸውን መልካም ባሕርያት በሙሉ መዘርዘሩ አልነበረም።

ይህን በግልጽ ለመረዳት፣ በገላትያ ላይ የሚገኘውን ዝርዝር ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር እናወዳድር፤ ጥቅሱ “የብርሃን ፍሬ ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት፣ ጽድቅና እውነት የያዘ ነው” ይላል። (ኤፌ. 5:8, 9) “ጥሩነት” እንዲሁም ጽድቅና እውነት “የብርሃን ፍሬ” ተብለው ተጠቅሰዋል፤ ሆኖም ጥሩነት “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታም ነው።

በተመሳሳይም ጳውሎስ፣ ስድስት መልካም ባሕርያትን ይኸውም “ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትንና ገርነትን” እንዲያፈራ ጢሞቴዎስን መክሮታል። (1 ጢሞ. 6:11) ከእነዚህ መካከል “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታ እንደሆኑ የተጠቀሱት ሦስቱ ብቻ (እምነት፣ ፍቅር እና ገርነት) ናቸው። ይሁንና ጢሞቴዎስ ሌሎቹንም ባሕርያት ማለትም ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርንና ጽናትን ለመከታተል የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገዋል።—ከቆላስይስ 3:12 እና ከ2 ጴጥሮስ 1:5-7 አወዳድር።

በመሆኑም በገላትያ 5:22, 23 ላይ የተዘረዘሩት፣ ክርስቲያኖች ሊያፈሯቸው የሚገቡት ሁሉም ባሕርያት አይደሉም። “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታ እንደሆኑ የተጠቀሱትን ዘጠኝ ባሕርያት በአምላክ መንፈስ እርዳታ ማዳበር እንችላለን። ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ እየጎለመስን ለመሄድ እንዲሁም “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና [ለመልበስ]” ሌሎች ባሕርያትንም ማፍራት ይኖርብናል።—ኤፌ. 4:24