በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 28

እውነትን ማግኘታችሁን አረጋግጡ

እውነትን ማግኘታችሁን አረጋግጡ

“በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር።”—2 ጢሞ. 3:14

መዝሙር 56 እውነትን የራስህ አድርግ

ማስተዋወቂያ *

1. “እውነት” ስንል ምን ማለታችን ነው?

“እውነትን የሰማኸው እንዴት ነው?” “ያደግከው እውነት ቤት ውስጥ ነው?” “እውነት ውስጥ ስንት ዓመት ቆይተሃል?” እነዚህን ጥያቄዎች ተጠይቀህ ወይም ጠይቀህ ታውቅ ይሆናል። ይሁንና “እውነት” ስንል ምን ማለታችን ነው? በአብዛኛው ቃሉን የምንጠቀምበት እምነታችንን፣ አምልኳችንን እና ሕይወታችንን የምንመራበትን መንገድ ለመግለጽ ነው። “እውነት ውስጥ” ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ያውቃሉ፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይከተላሉ። በዚህም የተነሳ ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ነፃ የሚወጡ ከመሆኑም ሌላ ፍጹም ያልሆነ ሰው ሊኖረው የሚችለውን ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ማጣጣም ይችላሉ።—ዮሐ. 8:32

2. በዮሐንስ 13:34, 35 መሠረት አንድን ሰው መጀመሪያ ላይ ወደ እውነት የሚስበው ምን ሊሆን ይችላል?

2 መጀመሪያ ላይ ወደ እውነት የሳበህ ምንድን ነው? ምናልባት የይሖዋ ሕዝቦች የሚያሳዩት መልካም ምግባር ሊሆን ይችላል። (1 ጴጥ. 2:12) ወይም ደግሞ ፍቅራቸው ሊሆን ይችላል። ብዙዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባችን ላይ ሲገኙ ይህን አስተውለዋል፤ እንዲያውም ከመድረክ ላይ ከተላለፈው ትምህርት ይበልጥ የሚያስታውሱት ይህን ፍቅር ነው። ደግሞም ይህ መሆኑ አያስገርምም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ።) ይሁንና ጠንካራ እምነት ማዳበር ከፈለግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም።

3. በአምላክ ላይ ያለን እምነት የተመሠረተው የአምላክ ሕዝቦች በሚያሳዩት ክርስቲያናዊ ፍቅር ላይ ብቻ ከሆነ ምን ሊያጋጥመን ይችላል?

3 እምነታችን የአምላክ ሕዝቦች በሚያሳዩት ክርስቲያናዊ ፍቅር ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ለምን? ለምሳሌ አንድ የእምነት ባልንጀራችን፣ ምናልባትም አንድ ሽማግሌ ወይም አቅኚ ከባድ ኃጢአት ቢሠራስ? አሊያም አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በሆነ መንገድ ቢጎዱህስ? ወይም ደግሞ አንድ ሰው ከሃዲ ሆኖ እምነታችን እውነት እንዳልሆነ ቢናገርስ? እንዲህ ዓይነት ነገር ቢያጋጥምህ ተሰናክለህ ይሖዋን ማገልገልህን ታቆማለህ? ነጥቡ ይህ ነው፦ በአምላክ ላይ ያለህ እምነት የተመሠረተው ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች በሚያደርጉት ነገር ላይ ብቻ ከሆነ እምነትህ ጠንካራ አይሆንም። እምነትህን ለመገንባት እንደ ስሜት ያለ ደካማ ጥሬ ዕቃ ብቻ ሳይሆን እንደ እውቀትና አሳማኝ ማስረጃ ያሉ ጠንካራ ጥሬ ዕቃዎችንም መጠቀም ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ እውነቱን እንደሚያስተምረን ለራስህ ማረጋገጥ አለብህ።—ሮም 12:2

4. በማቴዎስ 13:3-6, 20, 21 መሠረት አንዳንዶች ፈተና ሲደርስባቸው ምን ያጋጥማቸዋል?

4 ኢየሱስ አንዳንዶች እውነትን “በደስታ” ቢቀበሉም ፈተና ሲደርስባቸው እምነታቸው እንደሚጠፋ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:3-6, 20, 21ን አንብብ።) ምናልባት ኢየሱስን መከተል ተፈታታኝ ሁኔታዎችና መከራ እንደሚያስከትል አልተገነዘቡ ይሆናል። (ማቴ. 16:24) ወይም ደግሞ ክርስትና በበረከት ብቻ የተሞላና ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ይሁንና በዚህ ዓለም ውስጥ ችግር ማጋጠሙ አይቀርም። ያለንበት ሁኔታ ሊቀየርና ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደስታችን ሊቀንስ ይችላል።—መዝ. 6:6፤ መክ. 9:11

5. አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ መሆናቸው በግልጽ የሚታየው እንዴት ነው?

5 አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ መሆናቸው በግልጽ ይታያል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የእምነት ባልንጀሮቻቸው ቢጎዷቸው ወይም ክርስቲያናዊ ያልሆነ ምግባር ቢያሳዩም እንኳ እምነታቸው አይናወጥም። (መዝ. 119:165) ፈተና ባጋጠማቸው ቁጥር እምነታቸው ከመዳከም ይልቅ እየተጠናከረ ይሄዳል። (ያዕ. 1:2-4) ታዲያ እንዲህ ያለውን ጠንካራ እምነት መገንባት የምንችለው እንዴት ነው?

“ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት” አግኙ

6. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እምነታቸውን የገነቡት በምን ላይ ነበር?

6 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እምነታቸውን የገነቡት ባላቸው የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ይኸውም ‘በምሥራቹ እውነት’ ላይ ነበር። (ገላ. 2:5) ይህ እውነት ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትና ስለ ትንሣኤው የሚገልጸውን ትምህርት ጨምሮ ሁሉንም የክርስትና ትምህርቶች ያጠቃልላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ትምህርቶች እውነት መሆናቸውን እርግጠኛ ነበር። ይህን እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም “ክርስቶስ መከራ መቀበሉና ከሞት መነሳቱ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ” ያሳምን ነበር። (ሥራ 17:2, 3) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች የተቀበሉ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የአምላክን ቃል ለመረዳት ይጥሩ ነበር። እነዚህ ትምህርቶች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ለራሳቸው አረጋግጠዋል። (ሥራ 17:11, 12፤ ዕብ. 5:14) እምነታቸው የተመሠረተው በስሜት ላይ ብቻ አልነበረም፤ እንዲሁም ይሖዋን የሚያገለግሉት ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር መሆን ስለሚያስደስታቸው ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እምነታቸው የተገነባው ስለ አምላክ ባገኙት “ትክክለኛ እውቀት” ላይ ነበር።—ቆላ. 1:9, 10

7. በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ያለን እምነት ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

7 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አይለዋወጥም። (መዝ. 119:160) ለምሳሌ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ቢያስቀይመን ወይም ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም እውነት አይቀየርም። ችግር ቢደርስብንም እውነት አይቀየርም። ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በሚገባ መተዋወቅ እንዲሁም እውነት መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን ያስፈልገናል። መልሕቅ በማዕበል ወቅት አንድን መርከብ እንዳይናወጥ እንደሚያደርገው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ላይ ያለን ጠንካራ እምነትም በፈተና ወቅት ያጸናናል። ታዲያ እውነትን እንዳገኛችሁ ይበልጥ መተማመን የምትችሉት እንዴት ነው?

‘አምናችሁ ተቀበሉ’

8. ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:14, 15 እንደሚያሳየው ጢሞቴዎስ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ የሆነው እንዴት ነው?

8 ጢሞቴዎስ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ ነበር። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ የረዳው ምንድን ነው? (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15ን አንብብ።) እናቱና አያቱ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ አስተምረውት ነበር። ሆኖም እሱ ራሱ ጊዜ ወስዶ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዳጠና ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍት እውነትን እንደያዙ ‘አምኖ ተቀብሏል።’ ከጊዜ በኋላ ጢሞቴዎስ እንዲሁም እናቱና አያቱ ክርስትናን ተቀበሉ። ጢሞቴዎስ የኢየሱስ ተከታዮች በሚያሳዩት ፍቅር ተደንቆ መሆን አለበት፤ እንዲሁም ከመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ጊዜ ማሳለፍና እነሱን መርዳት ይፈልግ ነበር። (ፊልጵ. 2:19, 20) ሆኖም እምነቱ የተገነባው ለሰዎች ባለው ስሜት ላይ ሳይሆን ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ በሚረዱት ትምህርቶች ላይ ነበር። አንተም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ የሚያስተምረውን ነገር በማገናዘብ አሳማኝ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይኖርብሃል።

9. የትኞቹን ሦስት መሠረታዊ እውነቶች ለራስህ ማረጋገጥ ይኖርብሃል?

9 በመጀመሪያ ቢያንስ ሦስት መሠረታዊ እውነቶችን ለራስህ ማረጋገጥ ይኖርብሃል። አንደኛ፣ ይሖዋ አምላክ የሁሉም ነገር ፈጣሪ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል። (ዘፀ. 3:14, 15፤ ዕብ. 3:4፤ ራእይ 4:11) ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ መሪነት ለሰዎች ያስጻፈው መጽሐፍ መሆኑን ለራስህ ማረጋገጥ አለብህ። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ሦስተኛ፣ ይሖዋ በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው እሱን የሚያመልኩ የተደራጁ ሕዝቦች እንዳሉትና እነሱም የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ እርግጠኛ መሆን አለብህ። (ኢሳ. 43:10-12፤ ዮሐ. 14:6፤ ሥራ 15:14) እነዚህን መሠረታዊ እውነቶች ለራስህ ለማረጋገጥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ማወቅ አይጠበቅብህም። ዓላማህ ‘የማሰብ ችሎታህን’ ተጠቅመህ፣ እውነትን ማግኘትህን ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል።—ሮም 12:1

ሌሎችን ለማሳመን ተዘጋጁ

10. እውነትን ከማወቅ ባለፈ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

10 ስለ አምላክ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ አምላክ ሕዝቦች የሚገልጹትን ሦስት መሠረታዊ እውነቶች ለራስህ ካረጋገጥክ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመህ እነዚህን እውነቶች ለሌሎች ለማስረዳት ዝግጁ መሆን ይኖርብሃል። ለምን? ምክንያቱም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የተማርናቸውን እውነቶች ለሚሰሙን ሁሉ የማስተማር ኃላፊነት አለብን። * (1 ጢሞ. 4:16) ደግሞም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሌሎችን ለማሳመን በሞከርን መጠን በእነዚህ ትምህርቶች ላይ ያለን እምነት እየተጠናከረ ይሄዳል።

11. ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን በማስተማር ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን ሲያስተምር “በኢየሱስ እንዲያምኑ ለማድረግ ከሙሴ ሕግና ከነቢያት እየጠቀሰ” ያስረዳቸው ነበር። (ሥራ 28:23) ታዲያ እውነትን ለሌሎች ስናስተምር የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? መረጃ ከማስተላለፍ ያለፈ ነገር ማድረግ አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በጥቅሶቹ ላይ በማመዛዘን ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት ይኖርብናል። እኛን ስለሚያደንቁን ብቻ እውነትን እንዲቀበሉ አንፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ እውነትን የሚቀበሉት አፍቃሪ ስለሆነው አምላካችን የተማሩት ነገር እውነት መሆኑን ለራሳቸው ስላረጋገጡ መሆን አለበት።

ወላጆች፣ ለልጆቻችሁ “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” በማስተማር እምነት እንዲያዳብሩ እርዷቸው (ከአንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት) *

12-13. ወላጆች ልጆቻቸው እውነት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ እውነት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ እንደምትፈልጉ ጥያቄ የለውም። ልጆቻችሁ በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ጓደኞች ካገኙ መንፈሳዊ እድገት እንደሚያደርጉ ይሰማችሁ ይሆናል። ይሁንና ልጆቻችሁ እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ እንዲሆኑ ከተፈለገ ጥሩ ጓደኞች ማፍራታቸው ብቻ በቂ አይደለም። በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ነገር እውነት መሆኑን ማመን አለባቸው።

13 ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ አምላክ እውነቱን ማስተማር የሚችሉት እነሱ ራሳቸው ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመሆን ረገድ ምሳሌ ከሆኑ ነው። በተማሩት ነገር ላይ ጊዜ ወስደው ማሰላሰል አለባቸው። እንዲህ ካደረጉ ልጆቻቸውም የእነሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ማስተማር ይችላሉ። ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸውን እንደሚያሠለጥኑት ሁሉ ለልጆቻቸውም የምርምር መሣሪያዎችን አጠቃቀም ሊያሠለጥኗቸው ይገባል። በዚህ መልኩ ልጆቻቸው ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸውና ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ በሚጠቀምበት መስመር ማለትም ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲተማመኑ መርዳት ይችላሉ። (ማቴ. 24:45-47) ወላጆች፣ ለልጆቻችሁ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ብቻ በማስተማር ልትረኩ አይገባም። ዕድሜያቸውና ችሎታቸው በሚፈቅደው መጠን “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” በማስተማር ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ እርዷቸው።—1 ቆሮ. 2:10

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን አጥኑ

14. የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ማጥናት ያለብን ለምንድን ነው? (“ እነዚህን ትንቢቶች ማብራራት ትችላለህ?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

14 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ለማዳበር የሚረዳን ወሳኝ የአምላክ ቃል ክፍል ነው። እምነትህን ያጠናከሩልህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው? ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” የሚናገሩትን ትንቢቶች ትጠቅስ ይሆናል። (2 ጢሞ. 3:1-5፤ ማቴ. 24:3, 7) ይሁንና እምነትህን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ሌሎች ትንቢቶችስ አሉ? ለምሳሌ ያህል፣ በዳንኤል ምዕራፍ 2 እና በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ ያሉት ትንቢቶች እስካሁን ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዲሁም በአሁኑ ጊዜም እየተፈጸሙ ያሉት እንዴት እንደሆነ ማብራራት ትችላለህ? * እምነትህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጸንቶ ከተመሠረተ ፈጽሞ አይናወጥም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባድ ስደት የደረሰባቸውን የጀርመን ወንድሞቻችንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሙሉ በሙሉ ባይረዱም እንኳ በአምላክ ቃል ላይ ጠንካራ እምነት ነበራቸው።

ትንቢቶችን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን በፈተና ወቅት በድፍረት እንድንጸና ይረዳናል (ከአንቀጽ 15-17⁠ን ተመልከት) *

15-17. በናዚ አገዛዝ ወቅት ስደት የደረሰባቸው ወንድሞቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው ያጠናከራቸው እንዴት ነው?

15 በናዚ አገዛዝ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተልከው ነበር። ሂትለር እና የኤስ ኤስ አዛዥ የሆነው ሃይንሪክ ሂምለር የይሖዋ ምሥክሮችን ይጠሉ ነበር። አንዲት እህት እንደገለጸችው ሂምለር በአንድ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ለነበሩ እህቶች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የእናንተ ይሖዋ በሰማይ ላይ ይገዛ ይሆናል፤ በምድር ላይ የምንገዛው ግን እኛ ነን! ከእኛና ከእናንተ ማን ጸንቶ እንደሚቆይ እናሳያችኋለን!” ታዲያ የይሖዋ ሕዝቦች ታማኝነታቸውን እንዲጠብቁ የረዳቸው ምንድን ነው?

16 እነዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክ መንግሥት በ1914 መግዛት እንደጀመረ ያውቁ ነበር። ከባድ ስደት የደረሰባቸው መሆኑ አላስገረማቸውም። ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት የአምላክ ዓላማ እንዳይፈጸም ማገድ እንደማይችል እርግጠኞች ነበሩ። ሂትለር እውነተኛውን አምልኮ ማጥፋትም ሆነ ከአምላክ መንግሥት ጋር የሚተካከል መንግሥት ማቋቋም አልቻለም። ወንድሞቻችን ይዋል ይደር እንጂ የሂትለር አገዛዝ ማክተሙ እንደማይቀር እርግጠኞች ነበሩ።

17 የእነዚህ ወንድሞችና እህቶች እምነት በከንቱ አልቀረም። ብዙም ሳይቆይ የናዚ አገዛዝ ወደቀ፤ ‘በምድር ላይ የምንገዛው እኛ ነን’ ሲል የነበረው ሃይንሪክ ሂምለርም ሕይወቱን ለማትረፍ ሸሸ። በዚህ ወቅት ከወንድም ሉፕከ ጋር ተገናኘ፤ ሂምለር ወንድም ሉፕከ ታስሮ እያለ ያውቀው ነበር። ሂምለር በሽንፈት ስሜት ወንድም ሉፕከን “እሺ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ፣ ቀጥሎስ ምን ሊሆን ነው?” በማለት ጠየቀው። ወንድም ሉፕከም የይሖዋ ምሥክሮች የናዚ አገዛዝ መውደቁ እንደማይቀርና እነሱም ነፃነት እንደሚያገኙ ያውቁ እንደነበር ነገረው። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ መጥፎ ነገር ያወራ የነበረው ሂምለር በዚህ ወቅት የሚለው አጣ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሂምለር ሕይወቱን አጠፋ። ነጥቡ ምንድን ነው? ትንቢቶችን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን በአምላክ ላይ የማይናወጥ እምነት እንድንገነባና በፈተና ወቅት በድፍረት እንድንጸና ይረዳናል።—2 ጴጥ. 1:19-21

18. ዮሐንስ 6:67, 68 እንደሚያሳየው ጳውሎስ የገለጸውን ዓይነት “ትክክለኛ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ” ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

18 እያንዳንዳችን የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል። ይሁንና “ትክክለኛ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ” ማግኘትም ያስፈልገናል። (ፊልጵ. 1:9) ካልሆነ የከሃዲዎችን ትምህርት ጨምሮ “በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎች የማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ” ልንታለል እንችላለን። (ኤፌ. 4:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በርካታ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል ባቆሙበት ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” እንዳለው እንደሚተማመን ገልጿል። (ዮሐንስ 6:67, 68ን አንብብ።) በወቅቱ ጴጥሮስ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ሙሉ በሙሉ ባይረዳም ስለ ክርስቶስ እውነቱን ማወቁ በታማኝነት እንዲጸና ረድቶታል። እናንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ያላችሁን የመተማመን ስሜት ማጠናከር ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ ማንኛውንም ፈተና የሚቋቋም እምነት ይኖራችኋል፤ እንዲሁም ሌሎችም ጠንካራ እምነት እንዲገነቡ መርዳት ትችላላችሁ።—2 ዮሐ. 1, 2

መዝሙር 72 የመንግሥቱን እውነት ማሳወቅ

^ አን.5 ይህ ርዕስ በአምላክ ቃል ውስጥ ላለው እውነት አድናቆት እንድናዳብር ይረዳናል። በተጨማሪም የምናምንበት ነገር እውነት ስለመሆኑ ይበልጥ መተማመን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.10 መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች ለማስረዳት እንዲረዳህ መጠበቂያ ግንብ ላይ ከ2010 እስከ 2015 የወጡትን “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት። ከተካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል “ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው?” “የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው?” እና “አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ያቃጥላል?” የሚሉት ይገኙበታል።

^ አን.14 እነዚህን ትንቢቶች በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት የሰኔ 15, 2012 እና የግንቦት 2020 የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን ተመልከት።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ወላጆች ስለ ታላቁ መከራ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ከልጆቻቸው ጋር ሲያጠኑ።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ ይህ ቤተሰብ በታላቁ መከራ ወቅት በተከናወነው ነገር አልተደናገጠም።