በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ ሊቀ ካህናት የሆነው መቼ ነው? አዲሱ ቃል ኪዳን የጸደቀበትና የተመረቀበት ጊዜ የተለያየ ነው?

አንዳንድ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢየሱስ ሊቀ ካህናት የሆነው በ29 ዓ.ም. በተጠመቀበት ወቅት ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ሲጠመቅ በመሠዊያ በተመሰለው የአምላክ “ፈቃድ” ላይ መሥዋዕት ለመሆን ራሱን አቅርቧል። (ገላ. 1:4፤ ዕብ. 10:5-10) ይህ ምሳሌያዊ መሠዊያ ሥራ የጀመረው ኢየሱስ ከተጠመቀበት ጊዜ አንስቶ ስለሆነ በቤዛው አማካኝነት ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ለማቅረብ የሚያስችለውን ዝግጅት የሚያመለክተው ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስም ሥራ የጀመረው በዚህ ወቅት መሆን አለበት። መሠዊያው የዚህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ወሳኝ ክፍል ነው።—ማቴ. 3:16, 17፤ ዕብ. 5:4-6

ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሲቋቋም በዚያ የሚያገለግል ሊቀ ካህናት ያስፈልግ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ኢየሱስን ሊቀ ካህናት አድርጎ “በመንፈስ ቅዱስ ቀባው፤ ደግሞም ኃይል ሰጠው።” (ሥራ 10:37, 38፤ ማር. 1:9-11) ይሁንና ኢየሱስ ከመሞቱና ትንሣኤ ከማግኘቱ በፊት ሊቀ ካህናት ሆኖ እንደተሾመ እንዴት ማወቅ እንችላለን? በሙሴ ሕግ ሥር ሊቀ ካህናት ሆነው ያገለግሉ የነበሩትን የአሮንንና የዘሮቹን ምሳሌ ስንመረምር ወደዚህ መደምደሚያ የሚያመራ አሳማኝ ምክንያት እናገኛለን።

በሙሴ ሕግ መሠረት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ቅድስተ ቅዱሳንም ሆነ ከጊዜ በኋላ ወደተሠራው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር። ቅድስተ ቅዱሳኑ ከቅድስቱ የሚለየው በመጋረጃ ነበር። ሊቀ ካህናቱ መጋረጃውን አቋርጦ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚገባው በስርየት ቀን ላይ ብቻ ነበር። (ዕብ. 9:1-3, 6, 7) አሮንና ዘሮቹ ሊቀ ካህናት ሆነው የተቀቡት ቃል በቃል በማደሪያ ድንኳኑ “መጋረጃ” ከማለፋቸው በፊት እንደሆነ ሁሉ ኢየሱስም የታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሾመው ከመሞቱና “በመጋረጃው ማለትም በሥጋው በኩል” አልፎ ወደ ሰማይ ከመግባቱ በፊት ነው። (ዕብ. 10:20) ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ‘ሊቀ ካህናት ሆኖ እንደመጣና’ ከዚያም “በሰው እጅ ወዳልተሠራው . . . ይበልጥ ታላቅና ፍጹም ወደሆነው ድንኳን” እና “ወደ ሰማይ” እንደገባ የተናገረው ለዚህ ነው።—ዕብ. 9:11, 24

አዲሱ ቃል ኪዳን የጸደቀበትና የተመረቀበት ጊዜ የተለያየ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሄዶ ለእኛ ሲል ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ባቀረበበት ጊዜ አዲሱ ቃል ኪዳን እንዲጸድቅ ወይም ሕጋዊ እንዲሆን የሚያደርገውን ሂደት አስጀመረ። አዲሱ ቃል ኪዳን እንዲመረቅ ወይም በሥራ ላይ እንዲውል ያስቻለውም ይኸው ሂደት ነው። ይህ ሂደት የትኞቹን እርምጃዎች ያካትታል?

በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ በይሖዋ ፊት ቀረበ፤ ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የመሥዋዕቱን ዋጋ ለይሖዋ አቀረበ፤ በመጨረሻም ይሖዋ የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም ዋጋ ተቀበለ። አዲሱ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ የዋለው እነዚህ ሦስት ነገሮች ከተከናወኑ በኋላ ነው።

ይሖዋ የኢየሱስን መሥዋዕት ዋጋ የተቀበለበትን ትክክለኛ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። በመሆኑም አዲሱ ቃል ኪዳን የጸደቀበትንና በሥራ ላይ የዋለበትን ትክክለኛ ጊዜ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ያም ቢሆን ኢየሱስ ወደ ሰማይ ያረገው የጴንጤቆስጤ በዓል ከመከበሩ ከአሥር ቀን በፊት እንደሆነ እናውቃለን። (ሥራ 1:3) በእነዚህ ቀናት ውስጥ ባለ የሆነ ወቅት ላይ ኢየሱስ የመሥዋዕቱን ዋጋ ለይሖዋ አቀረበ፤ ይሖዋም ተቀበለው። (ዕብ. 9:12) በጴንጤቆስጤ ዕለት የተከናወነው ነገር አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራ መጀመሩን የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነበር። (ሥራ 2:1-4, 32, 33) በወቅቱ አዲሱ ቃል ኪዳን ተቋቁሞና ሥራ ጀምሮ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም።

ለክለሳ ያህል፣ አዲሱ ቃል ኪዳን የጸደቀውና የተመረቀው ይሖዋ የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም ዋጋ ከተቀበለ እንዲሁም ቅቡዓኑ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ እንዲካተቱ ካደረገ በኋላ ነው። ከዚያም ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ መካከለኛ የሆነለት ቃል ኪዳን ሥራ ጀመረ።—ዕብ. 7:25፤ 8:1-3, 6፤ 9:13-15