በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 29

“ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ”

“ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ”

“ስለ ክርስቶስ ስል በድክመት፣ በስድብ፣ በእጦት፣ በስደትና በችግር ደስ እሰኛለሁ።”—2 ቆሮ. 12:10

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

ማስተዋወቂያ *

1. ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ምን ጉዳይ በሐቀኝነት ተናግሯል?

ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ ጊዜ ድካም እንደሚሰማው በሐቀኝነት ተናግሯል። ሰውነቱ “እየመነመነ” እንደሄደ፣ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ትግል እንደሚጠይቅበት እንዲሁም ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ጸሎቱን እሱ በፈለገው መንገድ እንዳልመለሰት ሳይሸሽግ ገልጿል። (2 ቆሮ. 4:16፤ 12:7-9፤ ሮም 7:21-23) በተጨማሪም ጳውሎስ ተቃዋሚዎቹ እንደ ደካማ እንደሚቆጥሩት ተናግሯል። * ሆኖም የሌሎች አሉታዊ አመለካከትም ሆነ የራሱ ድክመት የከንቱነት ስሜት እንዲያሳድርበት አልፈቀደም።—2 ቆሮ. 10:10-12, 17, 18

2. በ2 ቆሮንቶስ 12:9, 10 መሠረት ጳውሎስ የትኛውን ወሳኝ ትምህርት አግኝቷል?

2 ጳውሎስ አንድ ወሳኝ ትምህርት አግኝቷል፤ አንድ ሰው ደካማ እንደሆነ በሚሰማው ጊዜም እንኳ ብርቱ ሊሆን እንደሚችል ተምሯል። (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10ን አንብብ።) ይሖዋ ጳውሎስን “ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” ብሎታል፤ ይህም ሲባል የይሖዋ ኃይል ጳውሎስ የጎደለውን ብርታት ያሟላለታል ማለት ነው። እስቲ በመጀመሪያ፣ ተቃዋሚዎች ሲሰድቡን ስሜታችን ሊጎዳ የማይገባው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

‘ስትሰደቡ ደስ ተሰኙ’

3. ስንሰደብ ደስ መሰኘት ያለብን ለምንድን ነው?

3 ማናችንም ብንሆን መሰደብ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም ጠላቶቻችን ሲሰድቡን ስሜታችን እንዲጎዳ የምንፈቅድ ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። (ምሳሌ 24:10) ታዲያ ተቃዋሚዎች ለሚሰነዝሩት ስድብ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እንደ ጳውሎስ ‘ስንሰደብ ደስ መሰኘት’ እንችላለን። (2 ቆሮ. 12:10) ለምን? ምክንያቱም ስድብና ተቃውሞ እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። (1 ጴጥ. 4:14) ኢየሱስ ተከታዮቹ ስደት እንደሚደርስባቸው ተናግሯል። (ዮሐ. 15:18-20) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው ሁኔታ ደርሶባቸዋል። በወቅቱ በግሪካውያን ባሕል ተጽዕኖ ሥር የነበሩ ሰዎች ክርስቲያኖችን ሞኝና ደካማ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። አይሁዳውያን ደግሞ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ ያሉ ክርስቲያኖችን “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” አድርገው ይቆጥሯቸው ነበር። (ሥራ 4:13) ክርስቲያኖች ደካማ መስለው ይታዩ ነበር፤ ምክንያቱም ፖለቲካዊ ሥልጣንም ሆነ ወታደራዊ ኃይል አልነበራቸውም፤ በማኅበረሰቡ ዘንድም ተቀባይነት አልነበራቸውም።

4. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተቃዋሚዎቻቸው አሉታዊ አመለካከት ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው ፈቅደዋል? አብራራ።

4 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተቃዋሚዎቻቸው አሉታዊ አመለካከት ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው ፈቅደዋል? በፍጹም። ለምሳሌ ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሱስን በመከተላቸውና ስለ እሱ ሌሎችን በማስተማራቸው ምክንያት ስደት ሲደርስባቸው እንደ ክብር ቆጥረውታል። (ሥራ 4:18-21፤ 5:27-29, 40-42) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚያፍሩበት ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። በወቅቱ የነበረው ማኅበረሰብ ለክርስቲያኖች አክብሮት ባይኖረውም እነዚህ ክርስቲያኖች ከተቃዋሚዎቻቸው ይበልጥ የሰው ልጆችን የሚጠቅም ነገር አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ በመንፈስ መሪነት የጻፏቸው መጻሕፍት አሁንም ድረስ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የእርዳታና የተስፋ ምንጭ ናቸው። እንዲሁም እነሱ ይሰብኩት የነበረው መንግሥት በአሁኑ ወቅት ተቋቁሟል፤ በቅርቡ ደግሞ የሰውን ዘር በሙሉ ይገዛል። (ማቴ. 24:14) በአንጻሩ ግን ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረው ኃያል መንግሥት ተንኮታኩቶ ከወደቀ ዘመናት ተቆጥረዋል። በተጨማሪም እነዚያ ታማኝ ክርስቲያኖች በአሁኑ ወቅት በሰማይ ነገሥታት ሆነው እየገዙ ነው። ተቃዋሚዎቻቸው ግን በሕይወት የሉም፤ ወደፊት ከሞት ቢነሱ እንኳ ይጠሏቸው የነበሩት ክርስቲያኖች ይሰብኩት በነበረው መንግሥት ለመገዛት ይገደዳሉ።—ራእይ 5:10

5. ዮሐንስ 15:19 በሚናገረው መሠረት የይሖዋ ሕዝቦች የሚናቁት ለምንድን ነው?

5 በዛሬው ጊዜ ያለን የይሖዋ ሕዝቦችም እንደ ሞኝና እንደ ደካማ ተቆጥረን የምንናቅበትና የምንሰደብበት ጊዜ አለ። ለምን? በዙሪያችን ካሉት ሰዎች የተለየ አመለካከት ስላለን ነው። ትሑት፣ የዋህና ታዛዥ ለመሆን እንጥራለን። በአንጻሩ ግን ይህ ዓለም ኩሩ፣ ግትርና ዓመፀኛ ለሆኑ ሰዎች ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል። በተጨማሪም ፖለቲካ ውስጥ አንገባም፤ የየትኛውንም አገር ወታደራዊ ኃይልም አንቀላቀልም። በዚህ ሥርዓት ለመቀረጽ ፈቃደኛ ስላልሆንን ሌሎች ዝቅ አድርገው ይመለከቱናል።—ዮሐንስ 15:19ን አንብብ፤ ሮም 12:2

6. ይሖዋ ሕዝቦቹን በመጠቀም ምን እያከናወነ ነው?

6 ዓለም እንደ ደካማ አድርጎ ቢመለከተንም ይሖዋ በእኛ አማካኝነት አስደናቂ ነገሮችን እያከናወነ ነው። ይሖዋ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሰፊ የስብከት ሥራ እንዲከናወን አድርጓል። አገልጋዮቹ በትርጉምና በስርጭት ረገድ ተወዳዳሪ የሌላቸውን መጽሔቶች እያዘጋጁ ነው፤ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ እየረዱ ነው። ለእነዚህ አስደናቂ ነገሮች ምስጋና የሚገባው ይሖዋ ነው። ይሖዋ እንደ ደካማ የሚቆጠሩ ሰዎችን በመጠቀም አስደናቂ የሆኑ ሥራዎችን አከናውኗል። ስለ እያንዳንዳችንስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ኃያል እንድንሆን ሊረዳን ይችላል? ከሆነስ የእሱን እርዳታ ለማግኘት ከእኛ ምን ይጠበቃል? እስቲ ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ የምናገኛቸውን ሦስት ትምህርቶች እንመልከት።

በራሳችሁ ብርታት አትመኩ

7. ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘው አንዱ ትምህርት ምንድን ነው?

7 ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘው አንዱ ትምህርት ይሖዋን ስናገለግል በራሳችን ብርታት ወይም ችሎታ መመካት እንደሌለብን ነው። ከሰብዓዊ እይታ አንጻር ጳውሎስ ለመኩራትና በራሱ ለመመካት የሚያነሳሳው ምክንያት ነበረው። ያደገው የአንድ የሮም ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በጠርሴስ ነበር። ጠርሴስ የበለጸገች ከተማና ታዋቂ የትምህርት ማዕከል ነበረች። ጳውሎስ የተማረ ሰው ነበር፤ እንዲያውም ያስተማረው በዘመኑ ከነበሩት እጅግ የተከበሩ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች አንዱ የሆነው ገማልያል ነው። (ሥራ 5:34፤ 22:3) በአንድ ወቅት ጳውሎስ በአይሁዳውያን መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰው ነበር። “ከወገኖቼ መካከል በእኔ ዕድሜ ካሉት ከብዙዎቹ የበለጠ በአይሁዳውያን ሃይማኖት የላቀ እድገት እያደረግኩ ነበር” በማለት ተናግሯል። (ገላ. 1:13, 14፤ ሥራ 26:4) ሆኖም ጳውሎስ በራሱ አልተመካም።

ጳውሎስ ዓለም የሚያቀርባቸውን አጓጊ የሚመስሉ ነገሮች ክርስቶስን ከመከተል መብቱ ጋር ሲያነጻጽራቸው “እንደ ቆሻሻ” ቆጥሯቸዋል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት) *

8. ፊልጵስዩስ 3:8 እና የግርጌ ማስታወሻው ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ ስለተዋቸው ነገሮች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? ‘በድክመት ደስ የተሰኘውስ’ ለምንድን ነው?

8 ጳውሎስ ከዓለም እይታ አንጻር ኃያል እንዲመስል የሚያደርጉትን ነገሮች ያለምንም ቅሬታ ትቷል። እንዲያውም እነዚህን ነገሮች “እንደ ቆሻሻ” ቆጥሯቸዋል። (ፊልጵስዩስ 3:8ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) ጳውሎስ የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ብዙ መሥዋዕት ከፍሏል። የገዛ ወገኖቹ የሆኑት አይሁዳውያን ጠልተውት ነበር። (ሥራ 23:12-14) የአገሩ ዜጎች የሆኑት ሮማውያን ደብድበው እስር ቤት ወርውረውታል። (ሥራ 16:19-24, 37) በተጨማሪም ጳውሎስ ድክመት እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። (ሮም 7:21-25) ሆኖም ተቃዋሚዎቹም ሆኑ የራሱ ድክመት እንዲያሽመደምደው ከመፍቀድ ይልቅ ‘በድክመት ደስ ተሰኝቷል።’ ለምን? ምክንያቱም የአምላክ ኃይል በሕይወቱ ውስጥ ሲሠራ ማየት የቻለው በደከመበት ወቅት ነው።—2 ቆሮ. 4:7፤ 12:10

9. ያሉብንን እንደ ድክመት ሊቆጠሩ የሚችሉ ነገሮች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

9 ይሖዋ ኃይል እንዲሰጠን ከፈለግን በእሱ ዘንድ ያለን ዋጋ የሚለካው በአካላዊ ጥንካሬያችን፣ በትምህርት ደረጃችን፣ በዘራችን ወይም በቁሳዊ ሀብታችን ላይ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ የሚጠቀምብን እነዚህን ነገሮች መሠረት አድርጎ አይደለም። እንዲያውም ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል ብዙዎቹ ‘በሰብዓዊ አመለካከት ጥበበኞች፣ ኃያላን እንዲሁም ከትልቅ ቤተሰብ የተወለዱ’ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ “የዓለምን ደካማ ነገር” ለመጠቀም መርጧል። (1 ቆሮ. 1:26, 27) እንግዲያው እንደ ድክመት ሊቆጠሩ የሚችሉ ነገሮች ይሖዋን ከማገልገል እንቅፋት እንዲሆኑባችሁ አትፍቀዱ። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ኃይል በውስጣችሁ ሲሠራ ለማየት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው። ለምሳሌ እምነታችሁን እንድትጠራጠሩ ለማድረግ ከሚሞክሩ ሰዎች ጋር መነጋገር የሚያስፈራችሁ ከሆነ ለእምነታችሁ በድፍረት ጥብቅና ለመቆም እንዲረዳችሁ ይሖዋን በጸሎት ጠይቁት። (ኤፌ. 6:19, 20) ከከባድ አእምሯዊ ወይም አካላዊ እክል ጋር እየታገላችሁ ከሆነ በእሱ አገልግሎት የቻላችሁትን ያህል ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስፈልጋችሁን ብርታት እንዲሰጣችሁ ይሖዋን ለምኑት። የይሖዋን እርዳታ ባያችሁ ቁጥር እምነታችሁ ያድጋል፤ እናንተም ይበልጥ ጠንካራ ትሆናላችሁ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ተማሩ

10. በዕብራውያን 11:32-34 ላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን ታሪክ ማጥናት ያለብን ለምንድን ነው?

10 ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ያጠና ነበር። ከቅዱሳን መጻሕፍት ብዙ እውቀት አካብቷል፤ ሆኖም በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጹ ባለታሪኮች ከተዉት ምሳሌም ትምህርት አግኝቶ ነበር። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በተለያዩ ዘመናት የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የተዉትን ምሳሌ ልብ እንዲሉ አበረታቷቸው ነበር። (ዕብራውያን 11:32-34ን አንብብ።) ከእነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አንዱን ይኸውም ንጉሥ ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዳዊት ከጠላቶቹ ብቻ ሳይሆን ወዳጆቹ ከነበሩ ሰዎችም ተቃውሞ አጋጥሞታል። የዳዊትን ምሳሌ ስንመረምር ጳውሎስ በዳዊት ሕይወት ላይ በማሰላሰል ብርታት አግኝቶ ሊሆን እንደሚችል እንመለከታለን፤ እንዲሁም የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።

ዳዊት ከጎልያድ ጋር ሲፋለም፣ ድክመት የሚመስለውን ነገር የአምላክን ኃይል ለማየት ወደሚያስችል አጋጣሚ ቀይሮታል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ዳዊት ደካማ ይመስል የነበረው ከምን አንጻር ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

11 ኃያል ተዋጊ የሆነው ጎልያድ ዳዊትን እንደ ደካማ አድርጎ ተመልክቶት ነበር። ጎልያድ ዳዊትን ሲያየው “ናቀው።” ደግሞም ጎልያድ ግዙፍ እንዲሁም በሚገባ የታጠቀና ጥሩ ሥልጠና ያገኘ ጦረኛ ነበር። ዳዊት ግን የጦርነት ልምድ የሌለውና የጦር ትጥቅ ያልለበሰ ትንሽ ልጅ ነው። ይሁንና ዳዊት ድክመት የሚመስለውን ነገር ወደ ጥንካሬ ቀይሮታል። በይሖዋ ኃይል በመታመን ጠላቱን ድል አድርጓል።—1 ሳሙ. 17:41-45, 50

12. ዳዊት ምን ሌላ ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር?

12 ዳዊት ደካማና አቅመ ቢስ እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ የሚችል ሌላም ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ዳዊት ይሖዋ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ የሾመውን ሳኦልን በታማኝነት ያገለግል ነበር። ንጉሥ ሳኦል መጀመሪያ ላይ ለዳዊት አክብሮት ነበረው። ከጊዜ በኋላ ግን ሳኦል ኩራት ስለተጠናወተው በዳዊት ቀና። በመሆኑም ሳኦል በዳዊት ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ፤ እንዲያውም ሊገድለው ሞክሮ ነበር።—1 ሳሙ. 18:6-9, 29፤ 19:9-11

13. ዳዊት ንጉሥ ሳኦል ሲበድለው ምን ምላሽ ሰጥቷል?

13 ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን ቢበድለውም ዳዊት ይሖዋ ለቀባው ንጉሥ አክብሮት ማሳየቱን ቀጥሏል። (1 ሳሙ. 24:6) ዳዊት፣ ሳኦል ላደረሰበት መጥፎ ነገር ይሖዋን ተጠያቂ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ዳዊት ይሖዋ ያንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠው ተማምኗል።—መዝ. 18:1 አናት ላይ ያለው መግለጫ

14. ሐዋርያው ጳውሎስ ከዳዊት ጋር የሚመሳሰል ምን ሁኔታ አጋጥሞት ነበር?

14 ሐዋርያው ጳውሎስም ከዳዊት ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። የጳውሎስ ጠላቶች ከእሱ ይልቅ እጅግ ኃያላን ነበሩ። በዘመኑ የነበሩ በርካታ ስመ ጥር መሪዎች ይጠሉት ነበር። በተደጋጋሚ አስደብድበውታል እንዲሁም እስር ቤት ወርውረውታል። እንደ ዳዊት ሁሉ ጳውሎስም ወዳጆቹ ሊሆኑ በሚገባቸው ሰዎች በደል ደርሶበታል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ተቃውመውታል። (2 ቆሮ. 12:11፤ ፊልጵ. 3:18) ሆኖም ጳውሎስ ተቃዋሚዎቹን በሙሉ ድል አድርጓል። እንዴት? ተቃውሞ ቢደርስበትም መስበኩን አላቆመም። ወንድሞቹና እህቶቹ ቢያሳዝኑትም እንኳ ለእነሱ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ከሁሉ በላይ ደግሞ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆኗል። (2 ጢሞ. 4:8) ይህን ሁሉ ማድረግ የቻለው በራሱ ብርታት ሳይሆን በይሖዋ በመታመኑ ነው።

ክርስቲያናዊ እምነታችሁን የማይቀበሉ ሰዎችን ለማስረዳት ጥረት ስታደርጉ አክብሮትና ደግነት አሳዩ (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት) *

15. ግባችን ምንድን ነው? ይህን ግብ ማሳካት የምንችለውስ እንዴት ነው?

15 አብረዋችሁ የሚማሩ ልጆች፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁ ወይም የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ዘመዶቻችሁ ስድብና ስደት ያደርሱባችኋል? በጉባኤ ውስጥ ያለ ሰው በድሏችሁ ያውቃል? ከሆነ ዳዊትና ጳውሎስ የተዉትን ምሳሌ አስታውሱ። ‘ምንጊዜም ክፉውን በመልካም ማሸነፍ’ ትችላላችሁ። (ሮም 12:21) ዓላማችሁ እንደ ዳዊት በሰው ግንባር ውስጥ ድንጋይ መቀርቀር እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ግባችሁ በሌሎች ልብና አእምሮ ውስጥ የአምላክን ቃል ማስረጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅማችሁ የሰዎችን ጥያቄ በመመለስ፣ በደል የሚያደርሱባችሁን ሰዎች በአክብሮትና በደግነት በመያዝ እንዲሁም ጠላቶቻችሁን ጨምሮ ለሁሉም ሰው መልካም በማድረግ ይህን ግብ ማሳካት ትችላላችሁ።—ማቴ. 5:44፤ 1 ጴጥ. 3:15-17

የሌሎችን እርዳታ ተቀበሉ

16-17. ጳውሎስ ፈጽሞ ያልረሳው የትኛውን ትምህርት ነው?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የኢየሱስን ተከታዮች የሚያሳድድ እብሪተኛ ወጣት ነበር። (ሥራ 7:58፤ 1 ጢሞ. 1:13) ሆኖም ኢየሱስ ራሱ በወቅቱ ሳኦል ተብሎ ይጠራ የነበረው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን ማሳደዱን እንዲያቆም አደረገ። ኢየሱስ ከሰማይ ጳውሎስን ያነጋገረው ከመሆኑም ሌላ ዓይኑን አሳወረው። ጳውሎስ የማየት ችሎታውን መልሶ ለማግኘት ከፈለገ ያሳድዳቸው የነበሩትን ሰዎች እርዳታ መጠየቅ ነበረበት። ጳውሎስ፣ ሐናንያ የተባለ ደቀ መዝሙር ያደረገለትን እርዳታ በትሕትና የተቀበለ ሲሆን ሐናንያም የማየት ችሎታውን መለሰለት።—ሥራ 9:3-9, 17, 18

17 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በጉባኤው ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ያለው ክርስቲያን ሆኗል፤ ያም ቢሆን ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ኢየሱስ የሰጠውን ትምህርት ፈጽሞ አልረሳም። ጳውሎስ ምንጊዜም ትሑት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ወንድሞቹና እህቶቹ ያደረጉለትን እርዳታ በፈቃደኝነት ተቀብሏል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች “የብርታት ምንጭ” እንደሆኑለት በሐቀኝነት ተናግሯል።—ቆላ. 4:10, 11

18. የሌሎችን እርዳታ መቀበል የሚከብደን ለምን ሊሆን ይችላል?

18 ከጳውሎስ ምን ትምህርት እናገኛለን? እውነትን በሰማንበት ወቅት በመንፈሳዊ ሕፃናት እንደሆንንና የምንማራቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ስለምንገነዘብ የሌሎችን እርዳታ ለመቀበል እንጓጓ ነበር። (1 ቆሮ. 3:1, 2) አሁንስ? በይሖዋ አገልግሎት በርካታ ዓመታት ካሳለፍንና ብዙ ተሞክሮ ካካበትን እንደ ቀድሞው የሌሎችን እርዳታ መቀበል ላይቀለን ይችላል፤ በተለይ እርዳታ የሚሰጠን ሰው የእኛን ያህል እውነት ውስጥ ካልቆየ እርዳታውን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ አብዛኛውን ጊዜ እኛን ለማበረታታት በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ይጠቀማል። (ሮም 1:11, 12) ይሖዋ የሚሰጠውን ኃይል ማግኘት ከፈለግን ይህን እውነታ አምነን መቀበል ይኖርብናል።

19. ጳውሎስ ስኬታማ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?

19 ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ አንዳንድ አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን ችሏል። ለምን? ምክንያቱም ጳውሎስ አንድ ሰው ስኬት ማግኘቱ የተመካው በአካላዊ ጥንካሬው፣ በትምህርት ደረጃው፣ በሀብቱ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ቦታ ላይ ሳይሆን በትሕትናውና በይሖዋ በመመካቱ ላይ እንደሆነ ተገንዝቧል። ሁላችንም (1) በይሖዋ በመመካት፣ (2) ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በመማር እንዲሁም (3) የእምነት ባልንጀሮቻችንን እርዳታ በመቀበል ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ እንከተል። እንዲህ ካደረግን በጣም ደካማ እንደሆንን ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ ብርቱ ያደርገናል!

መዝሙር 71 የይሖዋ ሠራዊት ነን!

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመረምራለን። ትሑት ከሆንን ይሖዋ የሚደርስብንን ፌዝ ለመቋቋም እና ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ የሚያስፈልገንን ኃይል እንደሚሰጠን እንመለከታለን።

^ አን.1 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ደካማ እንደሆንን እንዲሰማን የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ከእነዚህ መካከል አለፍጽምና፣ ድህነት፣ ሕመም ወይም በቀለም ትምህርት አለመግፋት ይገኙበታል። በተጨማሪም ጠላቶቻችን በቃላት ወይም በድርጊት ጥቃት በመሰንዘር ደካማ እንደሆንን እንዲሰማን ለማድረግ ይሞክራሉ።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ ጳውሎስ ፈሪሳዊ በነበረበት ወቅት ይጠቀምባቸው የነበሩትን ነገሮች ትቶ ስለ ክርስቶስ ለመስበክ ሲሄድ። ከእነዚህ መካከል ክታብና ዓለማዊ መጻሕፍትና ሊገኙበት ይችላሉ።

^ አን.61 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የሥራ ባልደረቦቹ በልደት ፕሮግራም ላይ እንዲካፈል ጫና ሲያደርጉበት።