በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 31

“እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ” እየተጠባበቅህ ነው?

“እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ” እየተጠባበቅህ ነው?

“አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።”—ዕብ. 11:10

መዝሙር 22 በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ይምጣልን!

ማስተዋወቂያ *

1. ብዙዎች ምን ዓይነት መሥዋዕት ከፍለዋል? እንዲህ ያለ መሥዋዕት የከፈሉትስ ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች መሥዋዕት ያደረጓቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ። በርካታ ወንድሞችና እህቶች ሳያገቡ ለመኖር ወስነዋል። ባለትዳር የሆኑት ደግሞ በአሁኑ ወቅት ልጆች ላለመውለድ መርጠዋል። አንዳንድ ቤተሰቦች አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል። ሁሉም እንዲህ ያለ ውሳኔ ያደረጉት በአንድ ወሳኝ ምክንያት የተነሳ ነው፤ በይሖዋ አገልግሎት የተቻላቸውን ያህል ተሳትፎ ማድረግ ስለፈለጉ ነው። እነዚህ ሰዎች ባላቸው ረክተው የሚኖሩ ሲሆን ይሖዋ በእርግጥ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ እንደሚያሟላላቸው ይተማመናሉ። ታዲያ ውሳኔያቸው ለቁጭት ይዳርጋቸው ይሆን? በፍጹም! ይህን እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በጥንት ዘመን ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ አሟልቶላቸዋል፤ ለምሳሌ “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” የተባለውን አብርሃምን ባርኮታል።—ሮም 4:11

2. (ሀ) በዕብራውያን 11:8-10, 16 መሠረት አብርሃም ዑርን ለቆ ለመውጣት ፈቃደኛ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

2 አብርሃም በዑር ከተማ የነበረውን የተደላደለ ሕይወት ትቶ ለመውጣት ፈቃደኛ ሆኗል። ለምን? “እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ” ይጠባበቅ ስለነበር ነው። (ዕብራውያን 11:8-10, 16ን አንብብ።) ይህች “ከተማ” የትኛዋ ናት? አብርሃም ይህች ከተማ እስክትገነባ ሲጠባበቅ ምን ፈተናዎች አጋጥመውታል? እኛስ የአብርሃምንና እንደ እሱ ያለ አካሄድ የተከተሉ በዘመናችን ያሉ ሰዎችን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

‘እውነተኛ መሠረት ያላት ከተማ’ የትኛዋ ናት?

3. አብርሃም ይጠባበቃት የነበረችው ከተማ ምንን ታመለክታለች?

3 አብርሃም ይጠባበቃት የነበረችው ከተማ የአምላክን መንግሥት ታመለክታለች። ይህ መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስና በ144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተዋቀረ ነው። ጳውሎስ ይህን መንግሥት ‘የሕያው አምላክ ከተማ የሆነችው ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም’ በማለት ጠርቶታል። (ዕብ. 12:22፤ ራእይ 5:8-10፤ 14:1) ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል፤ እንዲህ ብለው ሲጸልዩ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲፈጸም መጠየቃቸው ነው።—ማቴ. 6:10

4. በዘፍጥረት 17:1, 2, 6 መሠረት አብርሃም አምላክ ስለሚገነባት ከተማ ወይም መንግሥት ምን ያህል ያውቅ ነበር?

4 አብርሃም የአምላክ መንግሥት ስለሚዋቀርበት መንገድ ዝርዝር ነገሮችን ያውቅ ነበር? አያውቅም ነበር። እነዚህ ነገሮች ለበርካታ መቶ ዘመናት “ቅዱስ ሚስጥር” ነበሩ። (ኤፌ. 1:8-10፤ ቆላ. 1:26, 27) ሆኖም አብርሃም የእሱ ዘር የሆኑ አንዳንዶች፣ ነገሥታት እንደሚሆኑ ያውቅ ነበር። ይሖዋ ይህ እንደሚሆን ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍጥረት 17:1, 2, 6ን አንብብ።) አብርሃም፣ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ በጣም ጠንካራ እምነት ነበረው፤ በመሆኑም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሚሆነውን መሲሕ ያየው ያህል ነበር። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን አይሁዳውያን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ።” (ዮሐ. 8:56) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አብርሃም፣ ዘሮቹ ይሖዋ የሚያቋቁመው መንግሥት ክፍል እንደሚሆኑ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ የገባው ይህ ቃል የሚፈጽምበትን ጊዜ ለመጠባበቅ ፈቃደኛ ነበር።

አብርሃም ይሖዋ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

5. አብርሃም፣ አምላክ ንድፍ ያወጣላትን ከተማ ይጠባበቅ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?

5 አብርሃም፣ አምላክ ንድፍ ያወጣላትን ከተማ ወይም መንግሥት ይጠባበቅ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው? አንደኛ፣ የየትኛውም ምድራዊ መንግሥት ዜጋ አልሆነም። በአንድ ቦታ ላይ ሰፍሮ ከመኖርና ለየትኛውም ሰብዓዊ ንጉሥ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ይኖር ነበር። ከዚህም ሌላ አብርሃም የራሱን መንግሥት ለማቋቋም አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ይሖዋን ይታዘዝና እሱ የገባለትን ቃል እስኪፈጽም ይጠባበቅ ነበር። አብርሃም ይህን ማድረጉ በይሖዋ ላይ አስደናቂ እምነት እንደነበረው ያሳያል። አብርሃም ያጋጠሙትን አንዳንድ ፈተናዎች እንዲሁም ከእሱ ምሳሌ የምናገኛቸውን ትምህርቶች እስቲ እንመልከት።

አብርሃም ምን ፈተናዎች አጋጥመውታል?

6. ዑር ምን ዓይነት ከተማ ነበረች?

6 አብርሃም ትቷት የወጣው ከተማ በአንጻራዊ ሁኔታ ስትታይ ከስጋት ነፃ የሆነች፣ የሠለጠነችና ምቹ ነበረች። በከተማዋ ዙሪያ ግዙፍ ግንብ የነበረ ሲሆን በሦስት አቅጣጫዎች በውኃ አካል የተከበበች ነበረች። የዑር ነዋሪዎች በሥነ ጽሑፍና በሒሳብ ጥሩ ችሎታ ነበራቸው። ዑር በነበረችበት ቦታ ላይ በርካታ የንግድ ሰነዶች መገኘታቸውም ይህች ከተማ የንግድ ማዕከል እንደነበረች የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። በከተማዋ ውስጥ ያሉት መኖሪያ ቤቶች በጡብ ተሠርተው ከተለሰኑ በኋላ ነጭ ቀለም ይቀቡ ነበር። አንዳንዶቹ ቤቶች 13 ወይም 14 ክፍሎች የነበሯቸው ሲሆን ግቢያቸው የድንጋይ ንጣፍ ይኖረው ነበር።

7. አብርሃም፣ እሱንም ሆነ ቤተሰቡን ይሖዋ እንደሚጠብቃቸው መተማመን ያስፈለገው ለምን ነበር?

7 አብርሃም፣ እሱንም ሆነ ቤተሰቡን ይሖዋ እንደሚጠብቃቸው መተማመን ያስፈልገው ነበር። ለምን? አብርሃምና ሣራ በዑር ከተማ የነበራቸውን ምቹ ቤትና ከስጋት ነፃ የሆነ ሕይወት ትተው በከነአን ሜዳዎች ላይ ድንኳን ውስጥ መኖር እንደጀመሩ እናስታውስ። አብርሃምና ቤተሰቡ አሁን የመረጡት ሕይወት፣ ግዙፍ በሆነ ግንብ በታጠረና በውኃ በተከበበ ከተማ የመኖርን ያህል ጥበቃ አያስገኝም። እንዲያውም ለጠላት ጥቃት የተጋለጡ ነበሩ።

8. በአንድ ወቅት አብርሃም ምን ችግር አጋጥሞት ነበር?

8 አብርሃም የአምላክን ፈቃድ ቢያደርግም በአንድ ወቅት ቤተሰቡን ለመመገብ ተቸግሮ ነበር። ይሖዋን ታዝዞ በሄደበት ምድር ላይ ከባድ ረሃብ ተከሰተ። ረሃቡ በጣም ስለከፋ አብርሃም ቤተሰቡን ይዞ ለጊዜው በግብፅ ለመኖር ወሰነ። ሆኖም በግብፅ እያሉ፣ የአገሪቱ ገዢ የሆነው ፈርዖን ሚስቱን ወሰደበት። ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ ፈርዖን ሣራን እንዲመልሳት እስኪያደርግ ድረስ አብርሃም ምን ያህል ተጨንቆ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።—ዘፍ. 12:10-19

9. አብርሃም በቤተሰቡ ውስጥ ምን ችግሮች አጋጥመውታል?

9 አብርሃም በቤተሰብ ሕይወቱም ችግሮች አጋጥመውት ነበር። የሚወዳት ሚስቱ ሣራ፣ ልጅ መውለድ አልቻለችም። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት፣ ይህን ስሜት የሚጎዳ ሁኔታ ተቋቁመው መኖር ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ ሣራ፣ አገልጋይዋን አጋርን ለአብርሃም ሰጠችው፤ ይህን ያደረገችው ልጆች እንድትወልድላቸው አስባ ነበር። ይሁንና አጋር፣ እስማኤልን ስትፀንስ ሣራን መናቅ ጀመረች። ሣራ ሁኔታው በጣም ስለከበዳት አጋርን እንድትኮበልል አደረገቻት።—ዘፍ. 16:1-6

10. አብርሃም ከእስማኤልም ሆነ ከይስሐቅ ጋር በተያያዘ በይሖዋ መተማመን እንዲያስፈልገው ያደረጉ ምን ሁኔታዎች አጋጥመውታል?

10 በመጨረሻም ሣራ ፀነሰችና ወንድ ልጅ ወለደች፤ አብርሃምም ልጁን ይስሐቅ ብሎ ሰየመው። አብርሃም፣ እስማኤልንም ሆነ ይስሐቅን ይወዳቸው ነበር። ይሁን እንጂ እስማኤል በይስሐቅ ላይ ባደረገበት ነገር የተነሳ አብርሃም እስማኤልንና አጋርን ከቤት ለማስወጣት ተገደደ። (ዘፍ. 21:9-14) በኋላ ላይ ደግሞ ይሖዋ፣ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብለት አብርሃምን ጠየቀው። (ዘፍ. 22:1, 2፤ ዕብ. 11:17-19) በሁለቱም ወቅቶች አብርሃም፣ ልጆቹን በተመለከተ ይሖዋ የገባውን ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር መተማመን አስፈልጎት ነበር።

11. አብርሃም ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ያስፈለገው ለምን ነበር?

11 በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ አብርሃም ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ አስፈልጎት ነበር። ቤተሰቡን ይዞ ከዑር ሲወጣ ዕድሜው ከ70 ዓመት በላይ የነበረ ይመስላል። (ዘፍ. 11:31 እስከ 12:4) ከዚያም መቶ ገደማ ለሚሆኑ ዓመታት በከነአን ምድር ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ድንኳን ውስጥ ኖሯል። አብርሃም የሞተው በ175 ዓመቱ ነው። (ዘፍ. 25:7) ሆኖም የተዘዋወረባትን ምድር ለዘሮቹ እንደሚሰጥ ይሖዋ የገባለት ቃል ሲፈጸም ለማየት አልበቃም። ይጠብቃት የነበረችው ከተማ ማለትም የአምላክ መንግሥት ስትቋቋምም አላየም። ያም ቢሆን አብርሃም “በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ” እንደሞተ ተገልጿል። (ዘፍ. 25:8) አብርሃም ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም እምነቱ ምንጊዜም ጠንካራ ነበር፤ ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠባበቅም ፈቃደኛ ነበር። አብርሃም መጽናት የቻለው ለምንድን ነው? በሕይወቱ በሙሉ ይሖዋ ጥበቃ ስላደረገለትና እንደ ወዳጁ አድርጎ ስለተንከባከበው ነው።—ዘፍ. 15:1፤ ኢሳ. 41:8፤ ያዕ. 2:22, 23

የአምላክ አገልጋዮች እንደ አብርሃምና ሣራ እምነትና ትዕግሥት እያሳዩ ያሉት እንዴት ነው? (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) *

12. ምን እየተጠባበቅን ነው? ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመረምራለን?

12 እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ እየተጠባበቅን ነው። በእርግጥ ይህች ከተማ እስክትገነባ መጠበቅ አያስፈልገንም። የአምላክ መንግሥት በ1914 የተቋቋመ ሲሆን ሰማይን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል። (ራእይ 12:7-10) ሆኖም ምድርን ሙሉ በሙሉ እስኪቆጣጠር መጠበቅ ያስፈልገናል። ይህ የሚሆንበትን ጊዜ በምንጠባበቅበት ወቅት፣ አብርሃምና ሣራ ካጋጠሟቸው ጋር የሚመሳሰሉ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ታዲያ በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች የአብርሃምን ምሳሌ መከተል ችለዋል? በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡት የሕይወት ታሪኮች እንደሚያረጋግጡት በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች እንደ አብርሃምና ሣራ ዓይነት እምነትና ትዕግሥት አሳይተዋል። እስቲ ከእነዚህ ታሪኮች ጥቂቶቹን ብቻ በመመልከት ከእነሱ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመርምር።

የአብርሃምን ምሳሌ መከተል

ቢል ዋልደን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር፤ ይህም የይሖዋን በረከት አስገኝቶለታል

13. ከወንድም ቢል ዋልደን ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

13 መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ሁን። አብርሃም አምላክን ለማስደሰት ሲል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር፤ እኛም በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን ከተማ ማለትም መንግሥቱን ከምንም በላይ ማስቀደም ከፈለግን የእሱን ምሳሌ መከተል አለብን። (ማቴ. 6:33፤ ማር. 10:28-30) ቢል ዋልደን * የተባለውን ወንድም ምሳሌ እንመልከት። በ1942 ቢል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት በጀመረበት ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕንፃ ምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን ለመቀበል የቀረው ጥቂት ጊዜ ነበር። ቢልን የሚያስተምረው ፕሮፌሰር፣ ቢል ከተመረቀ በኋላ ሥራ እንዲቀጠር ሁኔታዎችን አመቻችቶለት ነበር፤ ቢል ግን ግብዣውን አልተቀበለም። በአምላክ አገልግሎት የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ ሲል ዓለማዊ ሥራ ላለመቀበል መወሰኑን ለፕሮፌሰሩ አስረዳው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ቢል ለወታደራዊ አገልግሎት ተመለመለ። በወታደራዊ አገልግሎት እንደማይካፈል በአክብሮት ቢያስረዳም 10,000 የአሜሪካ ዶላር መቀጮ እንዲከፍልና ለአምስት ዓመታት እንዲታሰር ተፈረደበት። ሦስት ዓመት ከታሰረ በኋላ ተፈታ። ከጊዜ በኋላ በጊልያድ ትምህርት ቤት እንዲካፈል የተጋበዘ ሲሆን በአፍሪካ ሚስዮናዊ ሆኖ አገልግሏል። ቢል፣ ኢቫን ካገባ በኋላም በአፍሪካ አብረው አገልግለዋል፤ ይህም ብዙ መሥዋዕት መክፈል ጠይቆባቸዋል። በኋላ ላይ የቢልን እናት ለመንከባከብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለሱ። ቢል ያሳለፈውን ሕይወት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋን የማገልገል ልዩ መብት ማግኘቴን ሳስብ እንባ በዓይኔ ግጥም ይላል። የእሱን አገልግሎት የዕድሜ ልክ ሥራዬ አድርጌ እንድይዘው ስለረዳኝ ይሖዋን ብዙ ጊዜ አመሰግነዋለሁ።” አንተስ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ዋነኛው ሥራህ ማድረግ ትችል ይሆን?

እሌኒ እና አሪስቶተሊስ አፖስቶሊዲስ ይሖዋ ኃይል እንደሰጣቸው ተሰምቷቸዋል

14-15. ከወንድም አሪስቶተሊስ እና ከእህት እሌኒ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

14 ሕይወትህ ምንም ችግር የሌለበት እንዲሆን አትጠብቅ። መላ ሕይወታቸውን በይሖዋ አገልግሎት ለማሳለፍ የወሰኑ ክርስቲያኖችም እንኳ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ከአብርሃም ታሪክ እንማራለን። (ያዕ. 1:2፤ 1 ጴጥ. 5:9) የወንድም አሪስቶተሊስ አፖስቶሊዲስ * የሕይወት ታሪክ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። ይህ ወንድም ግሪክ ውስጥ በ1946 ተጠመቀ። በ1952 እሌኒ ከተባለች እንደ እሱ ዓይነት ግብ ካላት እህት ጋር ተጫጩ። ሆኖም እሌኒ ታመመች፤ የአንጎል ዕጢ እንዳለባት ታወቀ። ሐኪሞች ዕጢውን ቢያወጡላትም ከተጋቡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ አንጎሏ ላይ እንደገና ዕጢ ተገኘ። እሌኒ እንደገና ቀዶ ሕክምና ቢደረግላትም ግማሽ አካሏ ሽባ ሆነ፤ እንዲሁም የመናገር እክል አጋጠማት። እሌኒ እንዲህ ያለ የጤና እክል ያለባት ከመሆኑም ሌላ በወቅቱ መንግሥት የጣለው እገዳ ቢኖርም በቅንዓት ማገልገሏን ቀጥላ ነበር።

15 ወንድም አሪስቶተሊስ ለ30 ዓመታት ባለቤቱን ተንከባክቧል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በትላልቅ ስብሰባ ኮሚቴዎች ውስጥ ሠርቷል፤ እንዲሁም በትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ግንባታ ተካፍሏል። ከዚያም በ1987 እሌኒ አገልግሎት ላይ ሳለች በደረሰባት አደጋ በጣም ተጎዳች። ከዚያ በኋላ ለሦስት ዓመታት ራሷን አታውቅም ነበር፤ በኋላም በሞት አንቀላፋች። ወንድም አሪስቶተሊስ ስላሳለፈው ሕይወት ጠቅለል አድርጎ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ባለፉት ዓመታት የገጠሙኝ አስቸጋሪ፣ ፈታኝና ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ከፍተኛ ጥንካሬንና ጽናትን ጠይቀውብኛል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁልጊዜ እነዚህን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችል ኃይል ይሰጠኛል።” (መዝ. 94:18, 19) ይሖዋ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡም እሱን ለማገልገል የሚችሉትን ሁሉ የሚያደርጉ አገልጋዮቹን በጣም እንደሚወዳቸው ጥያቄ የለውም!

ኦድሪ ሃይድ በወደፊቱ ጊዜ ላይ በማተኮር፣ አዎንታዊ አመለካከት ይዛ ለመኖር ጥረት አድርጋለች

16. ወንድም ኖር ለባለቤቱ ምን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷታል?

16 በወደፊቱ ጊዜ ላይ አተኩር። አብርሃም ወደፊት ይሖዋ በሚሰጠው ሽልማት ላይ አተኩሮ ነበር፤ ይህም በወቅቱ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመቋቋም ረድቶታል። እህት ኦድሪ ሃይድ እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አድርጋለች፤ የመጀመሪያ ባሏ የሆነው ናታን ሆመር ኖር በካንሰር ሕመም ምክንያት በሞት የተለያት ሲሆን ሁለተኛው ባሏ ግሌን ሃይድ ደግሞ አልዛይመርስ የተባለ በሽታ ይዞት ነበር። * እህት ኦድሪ፣ ወንድም ኖር ከመሞቱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የነገራት ነገር በጣም እንደጠቀማት ትገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “ናታን ‘ስንሞት ተስፋችን የተረጋገጠ ይሆናል፤ ከዚያ በኋላ አንሠቃይም’ ካለኝ በኋላ እንዲህ ሲል አጥብቆ መከረኝ፦ ‘ሽልማትሽን የምትቀበይው ወደፊት ስለሆነ ያንን ጊዜ አሻግረሽ ለመመልከት ሞክሪ። . . . ሌሎችን የሚጠቅም ነገር በማከናወን ሕይወትሽ በሥራ የተጠመደ እንዲሆን ጥረት አድርጊ። እንዲህ ማድረግሽ በሕይወትሽ ደስተኛ እንድትሆኚ ይረዳሻል።’” ይህ በእርግጥም ጠቃሚ ምክር ነው፤ ለሌሎች መልካም በማድረግ መጠመዳችንና ‘በተስፋው መደሰታችን’ እንደሚጠቅመን ጥርጥር የለውም!—ሮም 12:12

17. (ሀ) በወደፊቱ ጊዜ ላይ ለማተኮር የሚያነሳሳ ምን ምክንያት አለን? (ለ) ሚክያስ 7:7⁠ን ተግባራዊ ማድረጋችን ወደፊት በረከት እንድናገኝ የሚያስችለን እንዴት ነው?

17 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ፣ በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንድናተኩር የሚያነሳሳ ምክንያት አለን። የዓለም ሁኔታዎች በግልጽ እንደሚጠቁሙት የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት መጨረሻ ላይ ነው። እውነተኛ መሠረት ያላት ከተማ ምድርን ሙሉ በሙሉ እስክትቆጣጠር የምንጠብቅበት ጊዜ በቅርቡ ያበቃል። በዚያ ወቅት ከምናገኛቸው ብዙ በረከቶች አንዱ የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት ሲነሱ ማየት ነው። ያን ጊዜ ይሖዋ፣ አብርሃምንና ቤተሰቡን ከሞት በማስነሳት ይህን ታማኝ አገልጋዩን ላሳየው እምነትና ትዕግሥት ወሮታ ይከፍለዋል። አንተስ በዚያ ጊዜ በሕይወት ኖረህ እነሱን ለመቀበል ትበቃ ይሆን? እንደ አብርሃም ለአምላክ መንግሥት ስትል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ከሆንክ፣ ችግሮች እያሉም ጠንካራ እምነት ይዘህ ከኖርክ እንዲሁም ይሖዋን በትዕግሥት ከተጠባበቅህ ለዚያ ጊዜ ትበቃለህ።—ሚክያስ 7:7ን አንብብ።

መዝሙር 74 የመንግሥቱን መዝሙር ዘምሩ!

^ አን.5 ቃል የተገባልን ነገር እስኪፈጸም መጠበቅ ትዕግሥታችንን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እምነታችንን ሊፈትነው ይችላል። ታዲያ ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ በትዕግሥት ለመጠበቅ የአብርሃም ምሳሌ የሚረዳን እንዴት ነው? በዘመናችን የኖሩ የይሖዋ አገልጋዮችስ ምን ግሩም ምሳሌ ትተውልናል?

^ አን.13 የወንድም ቢል ዋልደን ተሞክሮ በታኅሣሥ 1, 2013 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-10 ላይ ይገኛል።

^ አን.14 የወንድም አሪስቶተሊስ አፖስቶሊዲስ የሕይወት ታሪክ በየካቲት 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 24-28 ላይ ይገኛል።

^ አን.16 የእህት ኦድሪ ሃይድ የሕይወት ታሪክ በሐምሌ 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-29 ላይ ይገኛል።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ በዕድሜ የገፉ አንድ ባልና ሚስት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩባቸውም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሰጠው ተስፋ ላይ በማተኮር፣ እምነታቸው ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ።