በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 35

ሌሎች በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ቦታ አክብሩ

ሌሎች በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ቦታ አክብሩ

“ዓይን እጅን ‘አንተ አታስፈልገኝም’ ሊለው አይችልም፤ ወይም ደግሞ ራስ እግርን ‘አንተ አታስፈልገኝም’ ሊለው አይችልም።”—1 ቆሮ. 12:21

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ለእያንዳንዱ ታማኝ አገልጋዩ ምን አድርጓል?

ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ስለሚወዳቸው እያንዳንዳቸው በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው አድርጓል። የምናበረክተው ድርሻ የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም ጠቃሚ ቦታ አለን፤ እንዲሁም አንዳችን ለሌላው እናስፈልጋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አስፈላጊ ትምህርት እንድንገነዘብ የሚረዳ ሐሳብ አስፍሮልናል። እንዴት?

2. ኤፌሶን 4:16 እንደሚያሳየው አንዳችን ሌላውን ከፍ አድርገን መመልከትና ተባብረን መሥራት ያለብን ለምንድን ነው?

2 በዚህ ርዕስ የጭብጥ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ ጎላ አድርጎ እንደገለጸው ማንኛችንም ብንሆን አንድን የይሖዋ አገልጋይ “አንተ አታስፈልገኝም” ልንለው አንችልም። (1 ቆሮ. 12:21) በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አንዳችን ሌላውን ከፍ አድርገን መመልከትና ተባብረን መሥራት ይኖርብናል። (ኤፌሶን 4:16ን አንብብ።) እርስ በርስ ተባብረን የምንሠራ ከሆነ ጉባኤው ይጠናከራል እንዲሁም በፍቅር ይታነጻል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 በጉባኤው ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች አክብሮት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ አቅጣጫዎች የትኞቹ ናቸው? በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የጉባኤ ሽማግሌዎች አብረዋቸው ለሚያገለግሉት ሽማግሌዎች አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንማራለን። ቀጥሎም፣ ሁላችንም ያላገቡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከታቸው ማሳየት የምንችልበትን መንገድ እናያለን። በመጨረሻም፣ የእኛን ቋንቋ አቀላጥፈው መናገር የማይችሉ ክርስቲያኖችን እንደምናደንቃቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

አብረዋችሁ ለሚያገለግሉት ሽማግሌዎች አክብሮት አሳዩ

4. ሽማግሌዎች ጳውሎስ በሮም 12:10 ላይ የሰጠውን የትኛውን ምክር መከተል ይኖርባቸዋል?

4 ሁሉም የጉባኤ ሽማግሌዎች የተሾሙት በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ነው። ያም ቢሆን እያንዳንዳቸው ያላቸው ስጦታና ችሎታ የተለያየ ነው። (1 ቆሮ. 12:17, 18) አንዳንዶቹ ሽማግሌዎች በቅርቡ የተሾሙና በአንጻራዊ ሁኔታ ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል የተነሳ ማከናወን የሚችሉት ነገር ውስን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሽማግሌ፣ አብሮት ለሚያገለግል ለየትኛውም ሽማግሌ “አንተ አታስፈልገኝም” የሚል አመለካከት ሊኖረው አይገባም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሽማግሌ ጳውሎስ በሮም 12:10 ላይ የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርበታል።—ጥቅሱን አንብብ።

ሽማግሌዎች አብረዋቸው የሚያገለግሉ ሽማግሌዎችን በትኩረት በማዳመጥ እንደሚያከብሯቸው ያሳያሉ (ከአንቀጽ 5-6⁠ን ተመልከት)

5. ሽማግሌዎች፣ አብረዋቸው የሚያገለግሉትን ሽማግሌዎች እንደሚያከብሩ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

5 ሽማግሌዎች፣ አብረዋቸው የሚያገለግሉትን ሽማግሌዎች ሐሳብ በትኩረት በማዳመጥ እንደሚያከብሯቸው ያሳያሉ። በተለይ ደግሞ ከበድ ባሉ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በሚሰበሰቡበት ወቅት ይህን ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። ለምን? የጥቅምት 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ምን እንደሚል እንመልከት፦ “ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞ፣ በሽማግሌዎች አካል ውስጥ የሚገኝን ማንኛውንም ሽማግሌ ለአንድ ሁኔታ መፍትሔ የሚሆን ወይም አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እንዲመጣለት ሊያደርግ እንደሚችል ሽማግሌዎች ይገነዘባሉ። (ሥራ 15:6-15) መንፈስ ቅዱስ የሚያግዘው በሽማግሌዎች አካል ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ሽማግሌዎች እንጂ አንድን ሽማግሌ ብቻ አይደለም።”

6. ሽማግሌዎች በአንድነት መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋቸው ለጉባኤው ምን ጥቅም ያስገኛል?

6 አብረውት የሚያገለግሉትን ሽማግሌዎች የሚያከብር አንድ ሽማግሌ፣ በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ሁልጊዜ መጀመሪያ ለመናገር አይሞክርም። በውይይቱ ላይ እሱ ብቻ ተናጋሪ ከመሆን ይቆጠባል፤ እንዲሁም የእሱ አመለካከት ምንጊዜም ቢሆን ትክክል እንደሆነ አያስብም። ከዚህ ይልቅ ሐሳቡን የሚገልጸው በትሕትና እና ልኩን እንደሚያውቅ በሚያሳይ መንገድ ነው። ሌሎች ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ሐሳብ በትኩረት ያዳምጣል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማካፈል እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሰጠውን መመሪያ ለመከተል ይጥራል። (ማቴ. 24:45-47) ሽማግሌዎች ስብሰባቸውን የሚያደርጉት ፍቅርና አክብሮት በሰፈነበት መንገድ ከሆነ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በመካከላቸው ይኖራል፤ ይህ መንፈስ ደግሞ ጉባኤውን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳቸዋል።—ያዕ. 3:17, 18

ላላገቡ ክርስቲያኖች አክብሮት አሳዩ

7. ኢየሱስ ለነጠላነት ምን አመለካከት ነበረው?

7 በዛሬው ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ባለትዳሮችና ቤተሰቦች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ያላገቡ በርካታ ወንድሞችና እህቶችም ይገኛሉ። ታዲያ ላላገቡ ክርስቲያኖች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረውን አመለካከት እንመልከት። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አላገባም ነበር። ሳያገባ በመኖር ሙሉ ጊዜውንና ትኩረቱን ለአገልግሎቱ ሰጥቷል። ኢየሱስ ማግባትም ሆነ ነጠላነት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት እንደሆነ አስተምሮ አያውቅም። ሆኖም አንዳንድ ክርስቲያኖች ላለማግባት ሊመርጡ እንደሚችሉ ተናግሯል። (ማቴ. 19:11, 12፤ ለ⁠ማቴዎስ 19:12 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።) ኢየሱስ ላላገቡ የአምላክ አገልጋዮች አክብሮት ነበረው። ያላገቡ ሰዎችን ዝቅ አድርጎ አልተመለከታቸውም፤ የሚጎድላቸው ነገር እንዳለም አልተሰማውም።

8. በ1 ቆሮንቶስ 7:7-9 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ምን እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል?

8 እንደ ኢየሱስ ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስም አገልግሎቱን ያከናወነው ነጠላ ሆኖ ነው። ጳውሎስ ክርስቲያኖች ቢያገቡ ስህተት እንደሆነ አስተምሮ አያውቅም። ይህ የግል ውሳኔ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ያም ቢሆን ጳውሎስ፣ ይሖዋን በነጠላነት ማገልገል ይችሉ እንደሆነ እንዲያስቡበት ክርስቲያኖችን አበረታቷል። (1 ቆሮንቶስ 7:7-9ን አንብብ።) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ያላገቡ ክርስቲያኖችን ዝቅ አድርጎ አልተመለከታቸውም። እንዲያውም ነጠላ የነበረውን ወጣቱን ጢሞቴዎስን ከባድ ኃላፊነት እንዲሸከም መርጦታል። * (ፊልጵ. 2:19-22) የአንድን ወንድም ብቃት፣ በማግባቱ ወይም ባለማግባቱ መመዘን ስህተት እንደሆነ ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል።—1 ቆሮ. 7:32-35, 38

9. ስለ ትዳርና ስለ ነጠላነት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

9 ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ፣ ማግባት ወይም በነጠላነት መቆየት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ መሥፈርት እንደሆነ አላስተማሩም። ታዲያ ስለ ትዳርና ስለ ነጠላነት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? የጥቅምት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ እንደሚከተለው በማለት ነጥቡን ግሩም አድርጎ አስቀምጦታል፦ “ጋብቻም ሆነ ነጠላነት ከአምላክ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው ሊባል ይችላል። . . . ይሖዋ ነጠላነትን ለኃፍረት ወይም ለሐዘን እንደሚዳርግ ነገር አድርጎ አይመለከተውም።” ይህን በመገንዘብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ነጠላ ወንድሞችንና እህቶችን ልናከብራቸው ይገባል።

ላላገቡ ክርስቲያኖች ስሜት ያለን አክብሮት ምን ከማድረግ እንድንቆጠብ ሊያነሳሳን ይገባል? (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. ያላገቡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደምናከብራቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ያላገቡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ስሜት እንደምናከብር እንዲሁም ሳያገቡ በመኖራቸው ዝቅ አድርገን እንደማንመለከታቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ክርስቲያኖች ያላገቡት፣ በነጠላነት ለመኖር ስለመረጡ መሆኑን ልናስታውስ ይገባል። ሌሎች ደግሞ ማግባት ቢፈልጉም የሚሆናቸው ሰው አላገኙም። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ክርስቲያኖችም አሉ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች እነዚህን ክርስቲያኖች ያላገቡት ለምን እንደሆነ መጠየቃቸው ተገቢ ነው? ወይም ደግሞ የትዳር ጓደኛ በመፈለግ ሊረዷቸው እንደሚችሉ ቢገልጹ ተገቢ ይሆናል? እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ነጠላ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት እገዛ እንዲደረግላቸው ይጠይቁ ይሆናል። ሆኖም ሳንጠየቅ እንዲህ ያለ ሐሳብ ማቅረባችን ባላገቡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ ምን ስሜት ሊፈጥር ይችላል? (1 ተሰ. 4:11፤ 1 ጢሞ. 5:13) ታማኝ የሆኑ አንዳንድ ነጠላ ወንድሞችና እህቶች ምን እንዳሉ እስቲ እንመልከት።

11-12. ካልተጠነቀቅን ያላገቡ ክርስቲያኖችን ቅር ልናሰኛቸው የምንችለው እንዴት ነው?

11 በአገልግሎት ምድቡ በጣም ውጤታማ የሆነ አንድ ያላገባ የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ በነጠላነት ማገልገል ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ይሰማዋል። ይሁንና ወንድሞችና እህቶች በአሳቢነት ተነሳስተው ቢሆንም እንኳ “የማታገባው ለምንድን ነው?” ብለው ሲጠይቁት ደስ እንደማይለው ገልጿል። በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግል አንድ ያላገባ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ወንድሞችና እህቶች፣ ነጠላዎች ሊታዘንላቸው ይገባል የሚል አመለካከት እንዳላቸው አስተውላለሁ። እንዲህ ያለው አመለካከት፣ ነጠላነትን ስጦታ ሳይሆን ሸክም ሊያስመስለው ይችላል።”

12 በቤቴል የምታገለግል አንዲት ያላገባች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ አስፋፊዎች፣ ያላገቡ ሰዎች በሙሉ የትዳር ጓደኛ እየፈለጉ እንደሆነ ወይም በማኅበራዊ ዝግጅቶች ላይ በሚገኙበት ጊዜ ሁሉ የትዳር ጓደኛ የሚሆናቸው ሰው እንደሚፈልጉ ያስባሉ። በአንድ ወቅት ለሥራ ወደ ሌላ አካባቢ ሄጄ ነበር፤ በቦታው የደረስኩት ስብሰባ በሚደረግበት ምሽት ነበር። በእንግድነት የተቀበለችኝ እህት፣ በጉባኤዋ ውስጥ በእኔ የዕድሜ ክልል ያሉ ሁለት ያላገቡ ወንድሞች እንዳሉ ነገረችኝ። በእርግጥ ልታገናኘኝ እየሞከረች እንዳልሆነ ገለጸችልኝ። ወደ ስብሰባ አዳራሹ እንደገባን ግን ሁለቱ ወንድሞች ወዳሉበት እየጎተተች ወሰደችኝ። ሁኔታው ለእኔም ሆነ ለሁለቱ ወንድሞች በጣም የሚያሳፍር ነበር።”

13. አንዲት ያላገባች እህት በእነማን ምሳሌ ተበረታታለች?

13 በቤቴል የምታገለግል ሌላ ነጠላ እህትም እንዲህ ብላለች፦ “በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ያላገቡ አቅኚዎችን አውቃለሁ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ብስለት ያላቸው፣ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩሩና የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ከመሆናቸውም ሌላ በአገልግሎታቸው ደስተኛ ናቸው፤ እንዲሁም ለጉባኤያቸው ብዙ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ነጠላነታቸውን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት አላቸው፤ ነጠላ ሆነው በመቆየታቸው ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ አይሰማቸውም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የትዳር ጓደኛና ቤተሰብ ስለሌላቸው የጎደላቸው ነገር እንዳለ አያስቡም።” እያንዳንዱ ሰው እንደሚከበርና እንደሚወደድ እንዲሰማው በሚያደርግ ጉባኤ ውስጥ መታቀፍ አስደሳች የሆነው ለዚህ ነው። እንዲህ ባለው ጉባኤ ውስጥ ማንኛውም ሰው እንደሚታዘንለትም ሆነ እንደሚቀናበት፣ ችላ እንደተባለም ሆነ የሁሉም ሰው ትኩረት በእሱ ላይ እንዳረፈ አይሰማውም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰው በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንዳለው ይሰማዋል።

14. ያላገቡ ክርስቲያኖችን እንደምናከብራቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ያላገቡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ ነጠላ በመሆናቸው እንደምናዝንላቸው ሳይሆን ያሏቸውን ግሩም ባሕርያት ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ስናሳያቸው ደስ ይላቸዋል። የጎደላቸው ነገር እንዳለ ከማሰብ ይልቅ ታማኝነታቸውን ልናደንቅ ይገባል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ያላገቡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን “አንተ አታስፈልገኝም” እንደምንላቸው አይሰማቸውም። (1 ቆሮ. 12:21) ከዚህ ይልቅ እንደምናከብራቸውና በጉባኤው ውስጥ ያላቸውን ቦታ ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ይሰማቸዋል።

የእናንተን ቋንቋ በደንብ መናገር ለማይችሉ ክርስቲያኖች አክብሮት አሳዩ

15. አንዳንዶች አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ ምን ማስተካከያዎች አድርገዋል?

15 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ አስፋፊዎች አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ ሌላ ቋንቋ እየተማሩ ነው። ይህም የተለያዩ ማስተካከያዎችን ማድረግ ጠይቆባቸዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች፣ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት በሌላ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ሲሉ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚካሄድ ጉባኤያቸውን ትተው መሄድ አስፈልጓቸዋል። (ሥራ 16:9) እነዚህ ክርስቲያኖች ይህን ውሳኔ ያደረጉት በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ መካፈል ስለፈለጉ ነው። አዲሱን ቋንቋ በደንብ ለመልመድ ዓመታት ሊወስድባቸው ቢችልም ጉባኤውን በብዙ መንገድ ይጠቅማሉ። ያሏቸው ግሩም ባሕርያትና ያካበቱት ተሞክሮ ጉባኤውን ያጠናክረዋል። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉትን እነዚህን ወንድሞችና እህቶች እናደንቃቸዋለን!

16. ሽማግሌዎች አንድ ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ወይም አገልጋይ ሆኖ ለማገልገል ብቃቱን ማሟላቱን ሲገመግሙ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለባቸው ነገር ምንድን ነው?

16 አንድ ወንድም ጉባኤው የሚመራበትን ቋንቋ አቀላጥፎ መናገር ስላልቻለ ብቻ የሽማግሌዎች አካል፣ ይህ ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ወይም አገልጋይ እንዲሆን የድጋፍ ሐሳብ ከማቅረብ ወደኋላ ማለት የለበትም። ሽማግሌዎች አንድን ወንድም ሲገመግሙ ከግምት የሚያስገቡት፣ ከሽማግሌዎችና ከአገልጋዮች የሚጠበቁ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ማሟላቱን እንጂ ጉባኤው የሚካሄድበትን ቋንቋ በደንብ መቻል አለመቻሉን አይደለም።—1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9

17. ወደ ሌላ አገር የሄዱ አንዳንድ ቤተሰቦች ውሳኔ የሚጠይቅ ምን ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?

17 አንዳንድ ክርስቲያን ቤተሰቦች አደገኛ ሁኔታን ለመሸሽ ወይም ሥራ ለማግኘት ሲሉ ወደ ሌላ አገር ሄደዋል። ወደ ሌላ አገር ከሄዱ በኋላ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት የሚማሩት በአገሪቱ ዋነኛ ቋንቋ ሊሆን ይችላል። ወላጆችም ቢሆኑ ሥራ ለማግኘት ሲሉ የአገሪቱን ቋንቋ መማር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በሄዱበት አገር በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚመራ ጉባኤ ወይም ቡድን ቢኖርስ? ቤተሰቡ ወደ የትኛው ጉባኤ ቢሄድ ይሻላል? በአገሪቱ ዋነኛ ቋንቋ ወደሚመራው ጉባኤ ወይስ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወደሚካሄደው ጉባኤ?

18. ገላትያ 6:5 እንደሚለው የቤተሰቡ ራስ የሚያደርገውን ውሳኔ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ቤተሰቡ ወደ የትኛው ጉባኤ እንደሚሄድ መወሰን ያለበት የቤተሰቡ ራስ ነው። የቤተሰቡ ራስ ይህን ውሳኔ ሲያደርግ ለቤተሰቡ የሚበጀውን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። (ገላትያ 6:5ን አንብብ።) ሌሎቻችን የቤተሰቡ ራስ ያደረገውን ውሳኔ ልናከብር ይገባል። ውሳኔው ምንም ይሁን ምን፣ ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ ሞቅ አድርገን በመቀበል ውሳኔያቸውን እንደምናከብር እናሳያቸው።—ሮም 15:7

19. የቤተሰብ ራሶች በጸሎት ሊያስቡበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

19 ሌሎች ቤተሰቦች ደግሞ በወላጆቹ የአፍ መፍቻ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ያገለግሉ ይሆናል፤ ልጆቹ ግን የወላጆቻቸውን ቋንቋ አቀላጥፈው መናገር አይችሉ ይሆናል። ጉባኤያቸው የሚገኘው፣ የሚኖሩበት አገር ብሔራዊ ቋንቋ በሚነገርበት ክልል ውስጥ ከሆነ ልጆቹ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትምህርቱን መረዳትና መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ሊከብዳቸው ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ልጆቹ ትምህርት ቤት ሲሄዱ የሚጠቀሙት የአገሩን ቋንቋ እንጂ የወላጆቻቸውን ቋንቋ አይደለም። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር የቤተሰብ ራሶች፣ ልጆቻቸው ወደ ይሖዋ እና ወደ ሕዝቦቹ እንዲቀርቡ ለመርዳት ምን ቢያደርጉ የተሻለ እንደሆነ በጸሎት ሊያስቡበት ይገባል። አንደኛው አማራጭ ልጆቻቸው የእነሱን ቋንቋ በደንብ እንዲችሉ መርዳት ነው፤ ካልሆነ ደግሞ የቤተሰቡ ራስ፣ ልጆቹ በደንብ በሚችሉት ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ስለ መዛወር ሊያስብ ይችላል። የቤተሰቡ ራስ ያደረገው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን፣ በሚሄዱበት ጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች እሱንና ቤተሰቡን እንደሚያከብሯቸውና ከፍ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ሊያሳዩአቸው ይገባል።

አዲስ ቋንቋ የሚማሩ ክርስቲያኖችን ከፍ አድርገን እንደምንመለከታቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት)

20. አዲስ ቋንቋ እየተማሩ ያሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደምናከብራቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

20 እስካሁን በተመለከትናቸው ምክንያቶች የተነሳ በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ አዲስ ቋንቋ ለመማር እየታገሉ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ይኖራሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ሐሳባቸውን መግለጽ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ያም ቢሆን ከቋንቋ ችሎታቸው ባሻገር ለመመልከት ጥረት ካደረግን ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅርና እሱን ለማገልገል ያላቸውን ፍላጎት ማስተዋል እንችላለን። እነዚህን ግሩም ባሕርያት ካስተዋልን ደግሞ ለእነሱ ያለን ፍቅርና አክብሮት ይጨምራል። የእኛን ቋንቋ በደንብ ስለማይችሉ ብቻ “አንተ አታስፈልገኝም” አንላቸውም።

በይሖዋ ዘንድ ውድ ነን

21-22. ምን ግሩም መብት አግኝተናል?

21 ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንዲኖረን በማድረግ ግሩም መብት ሰጥቶናል። ወንዶችም ሆንን ሴቶች፣ ያገባንም ሆንን ያላገባን፣ ወጣትም ሆንን አረጋዊ እንዲሁም አንድን ቋንቋ አቀላጥፈን መናገር ቻልንም አልቻልን ሁላችንም በይሖዋ ዘንድ ውድ ነን፤ አንዳችን በሌላው ዘንድም ዋጋ አለን።—ሮም 12:4, 5፤ ቆላ. 3:10, 11

22 እንግዲያው ጳውሎስ የሰው አካልን በመጠቀም ከሰጠው ምሳሌ ያገኘናቸውን በርካታ ግሩም ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረጋችንን እንቀጥል። እንዲህ ስናደርግ በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ እኛም ሆንን ሌሎች ያላቸውን ቦታ ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችልባቸውን ተጨማሪ መንገዶች እናገኛለን።

መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ

^ አን.5 የይሖዋ ሕዝቦች የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ሲሆን በጉባኤው ውስጥ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦም የተለያየ ነው። ይህ ርዕስ፣ በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ሰው ማክበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.8 ጢሞቴዎስ ሳያገባ እንደኖረ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።