በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 40

“በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ”

“በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ”

“ጢሞቴዎስ ሆይ፣ . . . በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ።”—1 ጢሞ. 6:20

መዝሙር 29 እንደ ስማችን መኖር

ማስተዋወቂያ *

1-2. በ1 ጢሞቴዎስ 6:20 መሠረት ጢሞቴዎስ ምን ተሰጥቶታል?

ውድ የሆኑ ንብረቶቻችንን ለሌሎች በአደራ የምንሰጥበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ገንዘባችንን ባንክ እናስቀምጥ ይሆናል። ይህን የምናደርገው ገንዘባችን አስተማማኝ ቦታ እንደሚቀመጥ እንዲሁም እንደማይጠፋ ወይም እንደማይሰረቅ ተማምነን ነው። ከዚህ አንጻር፣ ውድ ተደርጎ የሚታይን ነገር ለሌላ ሰው በአደራ መስጠት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አይከብደንም።

2 አንደኛ ጢሞቴዎስ 6:20ን አንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን ውድ የሆነ ነገር እንደተቀበለ አስታውሶታል፤ ይህ ውድ ነገር አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ የሚገልጸው ትክክለኛ እውቀት ነው። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ ‘ቃሉን የመስበክ’ እንዲሁም ‘የወንጌላዊነትን ሥራ የማከናወን’ መብት በአደራ ተሰጥቶት ነበር። (2 ጢሞ. 4:2, 5) ጢሞቴዎስ በአደራ የተሰጠውን ነገር እንዲጠብቅ ጳውሎስ ማሳሰቢያ ሰጥቶታል። እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም ውድ ነገሮች በአደራ ተሰጥተውናል። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? ይሖዋ የሰጠንን ውድ ነገሮች ልንጠብቃቸው የሚገባውስ ለምንድን ነው?

ውድ እውነቶች በአደራ ተሰጥተውናል

3-4. የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ውድ ናቸው የምንልባቸው አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

3 ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ውድ እውነቶች ትክክለኛ እውቀት እንድናገኝ በማድረግ ደግነት አሳይቶናል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ውድ ናቸው፤ ምክንያቱም ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት እንደሆነና በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ያስተምሩናል። እነዚህን እውነቶች ስንቀበልና በሕይወታችን ውስጥ መመሪያ አድርገን ስንጠቀምባቸው፣ ባሪያ ከሚያደርጉ የሐሰት ትምህርቶችና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ነፃ እንወጣለን።—1 ቆሮ. 6:9-11

4 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶች ውድ የሆኑበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ይሖዋ እነዚህን እውነቶች የሚገልጠው “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ላላቸው ትሑት ሰዎች ብቻ መሆኑ ነው። (ሥራ 13:48) እነዚህ ሰዎች ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እውነትን የሚያስተምረው በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል መሆኑን ይቀበላሉ። (ማቴ. 11:25፤ 24:45) እነዚህን እውነቶች በራሳችን ልናውቃቸው አንችልም፤ ደግሞም የእነዚህን እውነቶች ያህል ውድ የሆነ ሌላ ምንም ነገር የለም።—ምሳሌ 3:13, 15

5. ይሖዋ በአደራ የሰጠን ሌላው ነገር ምንድን ነው?

5 ይሖዋ፣ ስለ እሱና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች የማስተማር መብትንም በአደራ ሰጥቶናል። (ማቴ. 24:14) የምንሰብከው መልእክት በጣም ውድ ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች የይሖዋ ቤተሰብ አባላት እንዲሆኑና የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲኖራቸው ያደርጋል። (1 ጢሞ. 4:16) እያንዳንዳችን በአገልግሎቱ የምናደርገው ተሳትፎ ትንሽም ይሁን ትልቅ በዚህ ዘመን ከሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ሥራ እየደገፍን ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—1 ቆሮ. 3:9

የተሰጠህን ነገር አጥብቀህ ያዝ!

አንዳንዶች ከእውነት በራቁበት ወቅት ጢሞቴዎስ በእውነት ውስጥ ጸንቶ መቆም አስፈልጎት ነበር (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. አንዳንዶች የተሰጣቸውን ነገር ባለመጠበቃቸው ምን አጋጥሟቸዋል?

6 በጢሞቴዎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የመሥራት መብታቸውን ሳያደንቁ ቀርተዋል። ዴማስ ይህን ሥርዓት ስለወደደ ከጳውሎስ ጋር የማገልገል መብቱን ትቶ ሄዷል። (2 ጢሞ. 4:10) ፊጌሎስና ሄርሞጌኔስ፣ በጳውሎስ ላይ የደረሰው ዓይነት ስደት እንዳይገጥማቸው ስለፈሩ ማገልገላቸውን ያቆሙ ይመስላል። (2 ጢሞ. 1:15) ሄሜኔዎስ፣ እስክንድርና ፊሊጦስ ደግሞ በክህደት ትምህርት ስለተማረኩ እውነትን ትተዋል። (1 ጢሞ. 1:19, 20፤ 2 ጢሞ. 2:16-18) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ሁሉም በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ጠንካራ ነበሩ፤ በኋላ ላይ ግን ውድ ለሆኑ ነገሮች የነበራቸውን አድናቆት አጥተዋል።

7. ሰይጣን እኛን ከእውነት ለማስወጣት የትኞቹን ዘዴዎች ይጠቀማል?

7 ሰይጣን፣ ይሖዋ በአደራ የሰጠንን ውድ ነገሮች እንድንተው ለማድረግ የሚሞክረው እንዴት ነው? ይህን የሚያደርግባቸውን አንዳንድ ዘዴዎች እስቲ እንመልከት። ሰይጣን የያዝነውን እውነት ቀስ በቀስ እንድንለቅ ሊያደርጉን የሚችሉ የሥነ ምግባር እሴቶችን፣ አመለካከቶችንና ባሕርያትን በመዝናኛው ዓለም እና በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ያስፋፋል። በእኩዮች ተጽዕኖ ወይም በስደት ተሸብረን መስበካችንን እንድናቆም ለማድረግ ይሞክራል። በተጨማሪም “በውሸት ‘እውቀት’ ተብለው [በሚጠሩ]” የከሃዲዎች ትምህርቶች ተማርከን ከእውነት እንድንወጣ ለማድረግ ይጥራል።—1 ጢሞ. 6:20, 21

8. ዳንኤል የተባለ ወንድም ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?

8 ጠንቃቃ ካልሆንን የያዝነውን እውነት ቀስ በቀስ ልንለቀው እንችላለን። የቪዲዮ ጌሞች መጫወት ይወድ የነበረውን የዳንኤልን * ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “የቪዲዮ ጌሞች መጫወት የጀመርኩት ዕድሜዬ አሥር ዓመት ገደማ እያለ ነው። መጀመሪያ ላይ የምጫወታቸው ጌሞች ጎጂ አልነበሩም። ከጊዜ በኋላ ግን ዓመፅና አጋንንታዊ ድርጊት የሚንጸባረቅባቸው ጌሞች መጫወት ጀመርኩ።” ውሎ አድሮ ዳንኤል በየቀኑ ለ15 ሰዓታት ያህል የቪዲዮ ጌሞች ይጫወት ጀመር። እንዲህ ብሏል፦ “የምጫወታቸው የጌም ዓይነቶችም ሆኑ በጨዋታው የማሳልፈው ጊዜ ከይሖዋ እያራቁኝ እንደሆነ ውስጤ ይነግረኝ ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለእኔ እንደማይሠሩ ራሴን አሳምኜ ነበር።” መዝናኛ የሚያሳድረው ስውር ተጽዕኖ አጥብቀን የያዝነውን እውነት ቀስ በቀስ እንድንለቅ ሊያደርገን ይችላል። ይህ ደግሞ ይሖዋ የሰጠንን ውድ ነገሮች ሊያሳጣን ይችላል።

እውነትን አጥብቀን መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?

9. በ1 ጢሞቴዎስ 1:18, 19 ላይ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ከማን ጋር አመሳስሎታል?

9 አንደኛ ጢሞቴዎስ 1:18, 19ን አንብብ። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ከወታደር ጋር ያመሳሰለው ሲሆን ‘መልካሙን ውጊያ መዋጋቱን እንዲቀጥል’ አሳስቦታል። ይህ ውጊያ ቃል በቃል የሚደረግ ሳይሆን መንፈሳዊ ውጊያ ነው። ክርስቲያኖች በውጊያ ላይ ካሉ ወታደሮች ጋር የሚመሳሰሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው? የክርስቶስ ወታደሮች እንደመሆናችን መጠን የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ያስፈልገናል? ጳውሎስ ከሰጠው ምሳሌ የምናገኛቸውን አምስት ትምህርቶች እስቲ እንመልከት። እነዚህ ትምህርቶች እውነትን አጥብቀን እንድንይዝ ይረዱናል።

10. ለአምላክ ማደር ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማዳበር የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው?

10 ለአምላክ ማደርን አዳብሩ። ጎበዝ ወታደር ታማኝ ነው። የሚወደውን ሰው ወይም ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር ለመጠበቅ ሲል ይፋለማል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለአምላክ ማደርን እንዲያዳብር አበረታቶታል፤ ይህ ባሕርይ አምላክን መውደድን እና ለእሱ ታማኝ መሆንን የሚያመለክት ነው። (1 ጢሞ. 4:7) ለአምላክ ያለን ፍቅርና ታማኝነት እየጨመረ ሲሄድ እውነትን አጥብቀን ለመያዝ ያለን ፍላጎት ያድጋል።—1 ጢሞ. 4:8-10፤ 6:6

ቀኑን ሙሉ ስንደክም ውለን ስብሰባ ላይ ለመገኘት ራሳችንን ማስገደድ ያስፈልገን ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችን ግን ይክሰናል! (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ራሳችንን መገሠጽ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

11 ራስን የመገሠጽ ችሎታ አዳብሩ። አንድ ወታደር ምንጊዜም ለውጊያ ብቁ እንዲሆን ራሱን መገሠጽ ያስፈልገዋል። ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ብቃቱን ጠብቆ መመላለስ ችሏል፤ ለዚህ የረዳው ከክፉ ምኞቶች እንዲሸሽ፣ አምላካዊ ባሕርያትን እንዲከታተል እንዲሁም ከእምነት አጋሮቹ ጋር እንዲሆን ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ነው። (2 ጢሞ. 2:22) ይህን ለማድረግ ደግሞ ራሱን መገሠጽ ጠይቆበት ነበር። እኛም ከሥጋ ምኞቶቻችን ጋር በምናደርገው ውጊያ ድል ለመቀዳጀት ራሳችንን መገሠጽ ያስፈልገናል። (ሮም 7:21-25) አሮጌውን ስብዕና አውልቀን ለመጣልና አዲሱን ስብዕና ለመልበስ የምናደርገው ያልተቋረጠ ጥረትም ራስን መገሠጽ ይጠይቃል። (ኤፌ. 4:22, 24) በተጨማሪም ቀኑን ሙሉ ስንደክም ውለን ምሽት ላይ ስብሰባ ለመገኘት ራሳችንን ማስገደድ ይኖርብናል።—ዕብ. 10:24, 25

12. መጽሐፍ ቅዱስን የምንጠቀምበትን መንገድ ለማሻሻል የሚረዱን ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

12 አንድ ወታደር መሣሪያዎቹን እንዴት እንደሚጠቀም መለማመድ ይኖርበታል። በመሣሪያ አጠቃቀሙ ረገድ የተካነ መሆን የሚችለው አዘውትሮ ልምምድ ካደረገ ነው። እኛም የአምላክን ቃል በምንጠቀምበት መንገድ የተካንን መሆን አለብን። (2 ጢሞ. 2:15) ለዚህ የሚረዱንን አንዳንድ ክህሎቶች በስብሰባዎቻችን ላይ እንማራለን። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለሰዎች አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን አዘውትረን ማጥናት ይኖርብናል። የአምላክን ቃል ተጠቅመን እምነታችንን ማጠናከር ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ባለፈ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ብሎም በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር ማድረግ ይጠይቃል፤ ይህም በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የምናነበውን ነገር በትክክል መረዳት እንዲሁም ማብራራት እንድንችል ይረዳናል። (1 ጢሞ. 4:13-15) እንዲህ ካደረግን በአምላክ ቃል ተጠቅመን ሌሎችን ማስተማር እንችላለን። ሰዎችን ስናስተምርም ቢሆን ጥቅስ አውጥተን ከማንበብ ያለፈ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። የሚያዳምጡን ሰዎች ጥቅሱን እንዲረዱትና ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ መርዳት እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን በግላችን የማጥናት ልማድ ካለን የአምላክን ቃል ለሰዎች የማስተማር ችሎታችን እየተሻሻለ ይሄዳል።—2 ጢሞ. 3:16, 17

13. በዕብራውያን 5:14 መሠረት አስተዋዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

13 አስተዋይ ሁኑ። አንድ ወታደር ሊያጋጥመው የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ማሰብና ከአደጋው ለማምለጥ እርምጃ መውሰድ አለበት። እኛም ጉዳት ሊያደርሱብን የሚችሉ ሁኔታዎችን ለይተን የማወቅ ችሎታ ማዳበር እንዲሁም ከአደጋው ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ምሳሌ 22:3፤ ዕብራውያን 5:14ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ የምንዝናናበትን ነገር በጥበብ መምረጥ ያስፈልገናል። የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ብዙውን ጊዜ መጥፎ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅበት ነገር ያቀርባሉ። እንዲህ ያለው ምግባር አምላክን የሚያሳዝን ከመሆኑም ሌላ ውሎ አድሮ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። ስለዚህ ለአምላክ ያለን ፍቅር ቀስ በቀስ እንዲቀዘቅዝ ከሚያደርግ መዝናኛ መራቃችን የተገባ ነው።—ኤፌ. 5:5, 6

14. የማስተዋል ችሎታ ዳንኤልን የጠቀመው እንዴት ነው?

14 ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል ዓመፅና አጋንንታዊ ድርጊቶች የሚንጸባረቁባቸውን የቪዲዮ ጌሞች መጫወት ጉዳት እንደሚያስከትል ማስተዋል ጀመረ። ይህን ችግር ለማሸነፍ የሚረዱ ሐሳቦችን ለማግኘት ዎችታወር ላይብረሪ (እንግሊዝኛ) ላይ ምርምር አደረገ። ታዲያ ይህ ምን ጥቅም አስገኘለት? መጥፎ የሆኑ የቪዲዮ ጌሞች መጫወት አቆመ። ኢንተርኔት ላይ ጌም ከሚጫወትባቸው ድረ ገጾች አባልነቱን ሰረዘ፤ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ። ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “የቪዲዮ ጌሞች ከመጫወት ይልቅ ከቤት ወጣ ብዬ አንዳንድ ነገሮችን ማከናወን ወይም በጉባኤ ውስጥ ካሉ ጓደኞቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ።” ዳንኤል በአሁኑ ጊዜ አቅኚና የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው።

15. የሐሰት ወሬዎች አደገኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

15 እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም ከሃዲዎች የሚያሰራጩት የሐሰት መረጃ አደገኛ መሆኑን ማስተዋል አለብን። (1 ጢሞ. 4:1, 7፤ 2 ጢሞ. 2:16) ለምሳሌ ያህል፣ ከሃዲዎች ስለ ወንድሞቻችን የሐሰት ወሬዎችን ያናፍሱ ወይም በይሖዋ ድርጅት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብን የሚያደርግ መረጃ ያሰራጩ ይሆናል። እንዲህ ያለው የተሳሳተ መረጃ እምነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። እንደዚህ ባለው ፕሮፓጋንዳ እንዳንታለል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ወሬዎች የሚሰራጩት “አእምሯቸው በተበላሸና እውነትን መረዳት ባቆሙ ሰዎች” ነው። ዓላማቸውም ‘ጭቅጭቅና ክርክር’ ማስነሳት ነው። (1 ጢሞ. 6:4, 5) የወንድሞቻችንን ስም ለማጥፋት የሚያሰራጩትን ውሸት እንድናምንና እነሱን በጥርጣሬ ዓይን ማየት እንድንጀምር ማድረግ ይፈልጋሉ።

16. ትኩረታችንን የሚከፋፍሉትን የትኞቹን ነገሮች ማስወገድ አለብን?

16 ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን አስወግዱ። ጢሞቴዎስ “የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር” እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም በአገልግሎቱ ላይ ትኩረት ማድረግ ነበረበት፤ ዓለማዊ ወይም ቁሳዊ ነገሮች ትኩረቱን እንዲከፋፍሉበት መፍቀድ አልነበረበትም። (2 ጢሞ. 2:3, 4) እኛም ብንሆን ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮች የማግኘት ምኞት ትኩረታችንን እንዲከፋፍለው መፍቀድ አይኖርብንም። “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ለይሖዋ ያለንን ፍቅር፣ ለአምላክ ቃል ያለንን አድናቆት እንዲሁም ይህን እውነት ለሌሎች የማስተማር ፍላጎታችንን ሊያንቀው ይችላል። (ማቴ. 13:22) እንግዲያው አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ እንዲሁም ጊዜያችንን እና ኃይላችንን ‘ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥት ለመፈለግ’ መጠቀም ይኖርብናል።—ማቴ. 6:22-25, 33

17-18. መንፈሳዊ ጉዳት ከሚያስከትልብን ነገር ለማምለጥ ምን ማድረግ እንችላለን?

17 ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጁ። አንድ ወታደር ራሱን ለመከላከል ምን እርምጃ እንደሚወስድ አስቀድሞ ማሰብ ይኖርበታል። እኛም ይሖዋ በአደራ የሰጠንን ነገሮች መጠበቅ እንድንችል፣ አደጋ ስናይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ይህን ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን እንደምናደርግ አስቀድመን ማሰብ አለብን።

18 ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ሁኔታ እንመልከት፤ ብዙውን ጊዜ አንድ ዝግጅት ላይ የተገኙ ሰዎች፣ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በአቅራቢያቸው ያለውን መውጫ በር እንዲያስተውሉ ይጠየቃሉ። ለምን? አደጋ ቢፈጠር ወዲያውኑ ቦታውን ለቅቀው መውጣት እንዲችሉ ነው። በተመሳሳይ እኛም ኢንተርኔት ስንጠቀምና ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስንመለከት፣ የጭካኔ ድርጊትና ብልግና የሚታይበት ምስል ወይም ከሃዲዎች የሚያቀርቡት መረጃ በድንገት ብቅ ቢል የትኛውን “መውጫ በር” እንደምንጠቀም አስቀድመን መዘጋጀት አለብን። ሊያጋጥመን ለሚችለው ነገር አስቀድመን ከተዘጋጀን መንፈሳዊ ጉዳት ከሚያስከትልብን ነገር ቶሎ ማምለጥ እንዲሁም በይሖዋ ዓይን ንጹሕ ሆነን መኖር እንችላለን።—መዝ. 101:3፤ 1 ጢሞ. 4:12

19. ይሖዋ የሰጠንን ውድ ነገሮች መጠበቃችን ምን በረከት ያስገኝልናል?

19 ይሖዋ የሰጠንን ውድ ነገሮች ይኸውም ውድ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና እነዚህን እውነቶች ለሌሎች የማስተማር መብታችንን ልንጠብቃቸው ይገባል። ይህን ስናደርግ ንጹሕ ሕሊና፣ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲሁም ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት የሚያስገኘው ደስታ ይኖረናል። ይሖዋ በሚያደርግልን እርዳታ፣ እሱ በአደራ የሰጠንን ነገሮች መጠበቅ እንችላለን።—1 ጢሞ. 6:12, 19

መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?

^ አን.5 እውነትን የማወቅና ይህን እውነት ለሌሎች የማስተማር ታላቅ መብት አግኝተናል። ይህን መብታችንን አጥብቀን ለመያዝና መቼም ከእጃችን እንዳይወጣ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦችን በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

^ አን.8 ስሙ ተቀይሯል።