በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 43

ይሖዋ ድርጅቱን እየመራ ነው

ይሖዋ ድርጅቱን እየመራ ነው

“‘በመንፈሴ እንጂ፣ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”—ዘካ. 4:6

መዝሙር 40 የማን ንብረት ነን?

ማስተዋወቂያ *

1. የተጠመቁ ክርስቲያኖች ምን ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው?

የተጠመቅክ የይሖዋ ምሥክር ነህ? ከሆንክ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለህና ከድርጅቱ ጋር ተባብረህ ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆንክ በይፋ አሳውቀሃል። * እርግጥ ነው፣ በይሖዋ ላይ ያለህ እምነት እያደገ መሄድ አለበት። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በድርጅቱ እንደሚጠቀም ያለህን እምነትም በቀጣይነት መገንባት ያስፈልግሃል።

2-3. በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው? የትኞቹን ሦስት ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል?

2 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው ባሕርይውን፣ ዓላማውንና መሥፈርቱን በሚያንጸባርቅ መንገድ ነው። እስቲ በድርጅቱ ላይ ተንጸባርቀው የምናያቸውን ሦስት የይሖዋ ባሕርያት እንመልከት።

3 አንደኛ፣ ‘አምላክ አያዳላም።’ (ሥራ 10:34) አምላክ በፍቅሩ ተነሳስቶ ልጁን ‘ለሁሉም ሰው’ ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (1 ጢሞ. 2:6፤ ዮሐ. 3:16) ይሖዋ ሕዝቦቹ ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን እንዲሰብኩ አድርጓል። ይህም በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል። ሁለተኛ፣ ይሖዋ የሥርዓትና የሰላም አምላክ ነው። (1 ቆሮ. 14:33, 40) ከዚህ አንጻር፣ አገልጋዮቹም ሥርዓታማና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው እንደሚያገለግሉት መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው። ሦስተኛ፣ ይሖዋ ‘ታላቅ አስተማሪ’ ነው። (ኢሳ. 30:20, 21) ድርጅቱ በጉባኤም ሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ በእሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክን ቃል በማስተማር ላይ የሚያተኩረው ለዚህ ነው። እነዚህ ሦስት የይሖዋ ባሕርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ የተንጸባረቁት እንዴት ነው? በዘመናችን እየተንጸባረቁ ያሉትስ እንዴት ነው? እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ድርጅት ጋር ተባብረን ስናገለግል መንፈስ ቅዱስ በግለሰብ ደረጃ የሚረዳን እንዴት ነው?

አምላክ አያዳላም

4. በሐዋርያት ሥራ 1:8 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል? ምን እርዳታስ ያገኛሉ?

4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን። ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ለመላው የሰው ዘር ተስፋ የሚፈነጥቅ ነበር። (ሉቃስ 4:43) ተከታዮቹም “እስከ ምድር ዳር ድረስ” በመመሥከር እሱ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥሉ አዟቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ በራሳቸው ኃይል ይህን ሥራ ማከናወን አይችሉም። ኢየሱስ ቃል የገባላቸው “ረዳት” ማለትም የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር።—ዮሐ. 14:26፤ ዘካ. 4:6

5-6. መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ተከታዮች የረዳቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 የኢየሱስ ተከታዮች በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። በዚህ መንፈስ እርዳታ ወዲያውኑ የስብከቱን ሥራቸውን ጀመሩ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን ተቀበሉ። (ሥራ 2:41፤ 4:4) ተቃውሞ ባጋጠማቸው ወቅት ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት አልተሸነፉም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን እርዳታ ጠየቁ። “[ባሪያዎችህ] ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው” በማለት ጸለዩ። ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሲሆን ‘የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራቸውን’ ቀጠሉ።—ሥራ 4:18-20, 29, 31

6 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የቅዱሳን መጻሕፍትን ቅጂዎች እንደ ልብ ማግኘት አይችሉም ነበር። ዛሬ ያሉንን ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ መሣሪያዎች አልነበሯቸውም። በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚናገሩ ሰዎች መስበክ ነበረባቸው። እነዚህ ሁሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩባቸውም እነዚያ ቀናተኛ ደቀ መዛሙርት ፈጽሞ የማይቻል የሚመስለውን ነገር ማከናወን ችለዋል፤ በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ምሥራቹን “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” ሰብከዋል።—ቆላ. 1:6, 23

7. ከ100 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ ከእነሱ የሚፈልገውን ነገር በተመለከተ ምን ተገንዝበዋል? ምን ምላሽስ ሰጡ?

7 በዘመናችን። በዘመናችንም ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያና ብርታት መስጠቱን ቀጥሏል። በዋነኝነት መመሪያ የሚሰጠው በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በቃሉ አማካኝነት ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት የሚገልጸውን ዘገባና ኢየሱስ ተከታዮቹ እሱ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥሉ የሰጠውን ትእዛዝ እናገኛለን። (ማቴ. 28:19, 20) ይህ መጽሔት በሐምሌ 1881 በወጣው እትሙ ላይ እንኳ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “የተጠራነው ወይም የተቀባነው ክብር ለማግኘት ወይም ሀብት ለማካበት ሳይሆን ያለንን ነገር ሁሉ ተጠቅመን ምሥራቹን ለመስበክ ነው።” በ1919 የታተመው ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ (እንግሊዝኛ) የተባለው ቡክሌት “ሥራው ሰፊ ቢመስልም የጌታ ሥራ በመሆኑ እሱ በሚሰጠን ኃይል እንወጣዋለን” ይላል። አዎ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እነዚህ ወንድሞችም በድፍረትና በትጋት ሥራውን አከናውነዋል። መንፈስ ቅዱስ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመስበክ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነበሩ። እኛም መንፈስ ቅዱስ እንደሚረዳን እንተማመናለን።

የይሖዋ ድርጅት ምሥራቹን ለማስፋፋት ውጤታማ መሣሪያዎችን ይጠቀማል (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

8-9. የይሖዋ ድርጅት የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት የትኞቹን ዘዴዎች ተጠቅሟል?

8 የይሖዋ ድርጅት ምሥራቹን ለማስፋፋት ውጤታማ መሣሪያዎችን ሲጠቀም ቆይቷል። ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል የታተሙ ጽሑፎች፣ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ”፣ የሸክላ ማጫወቻዎች፣ የድምፅ ማጉያ የተገጠመላቸው መኪናዎች፣ የሬዲዮ ስርጭቶች እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢንተርኔትና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች ይገኙበታል። በተጨማሪም የአምላክ ድርጅት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ በማያውቅ መጠን የትርጉም ሥራ እያከናወነ ነው። ለምን? ሁሉም ዓይነት ሰዎች ምሥራቹን በራሳቸው ቋንቋ እንዲሰሙ ለማድረግ ነው። ይሖዋ አያዳላም፤ ምሥራቹ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” እንደሚሰበክ አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 14:6, 7) ሁሉም ሰው የመንግሥቱን መልእክት የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲያገኝ ይፈልጋል።

9 ቤታቸው ልናገኛቸው የማንችላቸውን፣ ምናልባትም ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? የይሖዋ ድርጅት እነዚህን ሰዎች ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ የስብከት አማራጮችን ሲጠቀም ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2001 የበላይ አካሉ በፈረንሳይ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የጽሑፍ ጋሪዎችንና ሌሎች የጽሑፍ መደርደሪያዎችን ተጠቅመው እንዲመሠክሩ ፈቃድ ሰጠ። ይህ የስብከት ዘዴ በኋላ ላይ በሌሎች አገሮችም ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን የተገኘው ውጤት አበረታች ነበር። በ2011 በኒው ዮርክ ሲቲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ ፍሰት ባለበት አካባቢ አንድ ለየት ያለ የስብከት ዘዴ ተሞክሮ ነበር። በመጀመሪያው ዓመት 102,129 መጻሕፍትና 68,911 መጽሔቶች ተበርክተዋል። እንዲሁም 4,701 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጠይቀዋል! ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይህን ሥራ እየደገፈው እንዳለ ግልጽ ነበር። በመሆኑም የበላይ አካሉ የጽሑፍ መደርደሪያዎች በዓለም ዙሪያ እንዲሠራባቸው ፈቃድ ሰጠ።

10. አገልግሎታችንን በተሻለ መንገድ ለማከናወን ምን ማድረግ እንችላለን?

10 ምን ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጠውን ሥልጠና በሚገባ ተጠቀምበት። ከመስክ አገልግሎት ቡድንህ ጋር አዘውትረህ አገልግል። በአገልግሎት ቡድንህ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ማሻሻል በሚያስፈልጉህ መስኮች እርዳታ ያደርጉልሃል። እንዲሁም የእነሱ ግሩም ምሳሌ የብርታት ምንጭ ይሆንሃል። በጽናት ማገልገልህን ቀጥል። ጥናታችን ከተመሠረተበት ጥቅስ መረዳት እንደምንችለው፣ የአምላክን ፈቃድ የምንፈጽመው በራሳችን ኃይል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ነው። (ዘካ. 4:6) ሥራው የአምላክ ስለሆነ እሱ የሚያስፈልገንን ብርታት እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ይሖዋ የሥርዓትና የሰላም አምላክ ነው

11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ አንድ ሆኖ የሠራው እንዴት ነው?

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን። በኢየሩሳሌም የነበረው የበላይ አካል በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሥርዓትና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ አንድ ሆኖ ይሠራ ነበር። (ሥራ 2:42) ለምሳሌ ያህል፣ በ49 ዓ.ም. ገደማ ከግርዘት ጋር በተያያዘ ጥያቄ በተነሳበት ወቅት የበላይ አካሉ በመንፈስ ተመርቶ ጉዳዩን ተመልክቶት ነበር። ጉባኤው በዚህ ጉዳይ የተነሳ እንደተከፋፈለ ቢቀጥል ኖሮ የስብከቱ ሥራ ይስተጓጎል ነበር። ሐዋርያቱና ሽማግሌዎቹ አይሁዳዊ ቢሆኑም የአይሁድ ወግ ወይም ይህን አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች ተጽዕኖ እንዲያደርጉባቸው አልፈቀዱም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ቃልና የመንፈሱን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። (ሥራ 15:1, 2, 5-20, 28) ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? ይሖዋ ውሳኔያቸውን ባርኮታል፣ ሰላምና አንድነት ሰፍኗል እንዲሁም የስብከቱ ሥራ ይበልጥ መስፋፋቱን ቀጥሏል።—ሥራ 15:30, 31፤ 16:4, 5

12. በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ሥርዓትና ሰላም እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ጥቀስ።

12 በዘመናችን። የይሖዋ ድርጅት በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሥርዓትና ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል። የሚገርመው ነገር፣ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ በኅዳር 15, 1895 እትሙ ላይ “በአግባብና በሥርዓት” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። በ1 ቆሮንቶስ 14:40 ላይ የተመሠረተው ይህ ርዕስ በውስጡ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “ሐዋርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረው ጉባኤ ሥርዓትን በተመለከተ ብዙ ነገር ጽፈዋል። . . . ‘ለእኛ ትምህርት ሲባል ቀደም ብለው የተጻፉትን ነገሮች’ በጥብቅ መከተል የተሻለ አካሄድ ነው።” (ሮም 15:4) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች መካከል ሥርዓትና ሰላም ሰፍኖ ነበር። የይሖዋ ድርጅት በዛሬው ጊዜም እንዲህ ያለ ሥርዓትና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ተግቶ ይሠራል። ለምሳሌ ያህል፣ ሌላ ጉባኤ አልፎ ተርፎም ሌላ አገር ሄደህ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ብትገኝ ጥናቱ እንዴት እንደሚመራም ሆነ የትኛው ርዕስ እንደሚጠና ታውቃለህ። ምንም የእንግድነት ስሜት አይሰማህም! ይህን የመሰለ አስገራሚ አንድነት በአምላክ መንፈስ እርዳታ ካልሆነ ሌላ በምን ሊገኝ ይችላል?—ሶፎ. 3:9 ግርጌ

13. ያዕቆብ 3:17⁠ን መሠረት በማድረግ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?

13 ምን ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ ሕዝቦቹ “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት [እንዲጠብቁ]” ይፈልጋል። (ኤፌ. 4:1-3) በመሆኑም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በጉባኤው ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ጥረት አደርጋለሁ? አመራር ለሚሰጡት ወንድሞች እታዘዛለሁ? በተለይ በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ካለኝ ሌሎች እምነት የሚጥሉብኝ ዓይነት ሰው ነኝ? ሰዓት አክባሪ፣ ተባባሪና ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ ነኝ?’ (ያዕቆብ 3:17ን አንብብ።) በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ከተሰማህ መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ጸልይ። መንፈስ ቅዱስ ማንነትህንና ድርጊትህን እንዲቀርጸው በፈቀድክ መጠን ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ የሚወዱህ ከመሆኑም ሌላ የምታከናውነውን አስተዋጽኦ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።

ይሖዋ ያስተምረናል እንዲሁም ያስታጥቀናል

14. በቆላስይስ 1:9, 10 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሕዝቦቹን ያስተማረው እንዴት ነው?

14 በመጀመሪያው መቶ ዘመን። ይሖዋ ሕዝቡን ማስተማር ያስደስተዋል። (መዝ. 32:8) እሱን እንዲያውቁት፣ እንዲወዱትና የተወደዱ ልጆቹ ሆነው ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። ይሖዋ ሕዝቡን ባያስተምር ኖሮ እነዚህ ነገሮች እውን ሊሆኑ አይችሉም ነበር። (ዮሐ. 17:3) ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የክርስቲያን ጉባኤ ሕዝቡን ለማስተማር ተጠቅሞበታል። (ቆላስይስ 1:9, 10ን አንብብ።) ኢየሱስ ቃል የገባው “ረዳት” ማለትም መንፈስ ቅዱስ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። (ዮሐ. 14:16) ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን ቃል ይበልጥ ማስተዋል እንዲችሉ እንዲሁም ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን በርካታ ነገሮች እንዲያስታውሱ ረድቷቸዋል። ከጊዜ በኋላም እነዚህን ነገሮች በወንጌል ዘገባዎች ላይ አስፍረዋቸዋል። በዚህ መልኩ የተገኘው እውቀት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች እምነት ለማጠናከር እንዲሁም ለአምላክ፣ ለልጁ ብሎም አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ለማሳደግ አስችሏል።

15. ይሖዋ በኢሳይያስ 2:2, 3 ላይ የገባውን ቃል ሲፈጽም ያያችሁት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

15 በዘመናችን። ይሖዋ “በዘመኑ መጨረሻ” ላይ ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ስለ መንገዶቹ ለመማር ወደ እሱ ምሳሌያዊ ተራራ እንደሚጎርፉ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 2:2, 3ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ እያየን ነው። እውነተኛው አምልኮ ከየትኛውም የሐሰት አምልኮ በላይ ከፍ ከፍ ብሏል። በተጨማሪም ይሖዋ ለሕዝቡ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበ ነው! (ኢሳ. 25:6) ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት የተትረፈረፈ ብቻ ሳይሆን በዓይነቱ የተለያየ መንፈሳዊ ምግብ ያዘጋጅልናል፤ ይህ መንፈሳዊ ምግብ ከጽሑፎች አንስቶ እስከ ንግግሮች፣ ከአኒሜሽኖች አንስቶ እስከ ቪዲዮዎች ድረስ በተለያየ መንገድ ይቀርብልናል። (ማቴ. 24:45) ይህን ሁሉ ስናይ የኢዮብ ጓደኛ ኤሊሁ እንዳለው “እንደ [አምላክ] ያለ አስተማሪ ማን ነው?” ለማለት እንነሳሳለን።—ኢዮብ 36:22

እውነት ወደ ልብህ ጠልቆ እንዲገባ አድርግ፤ እንዲሁም የተማርካቸውን ነገሮች ሥራ ላይ አውል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት) *

16. ይሖዋ ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

16 ምን ማድረግ ትችላለህ? የአምላክ መንፈስ ከአምላክ ቃል ላይ የምታነበውንና የምታጠናውን ነገር በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ እንድታደርግ ይረዳሃል። እንደ መዝሙራዊው እንዲህ ብለህ ጸልይ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ። በእውነትህ እሄዳለሁ። ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ።” (መዝ. 86:11) በተጨማሪም ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ መመገብህን ቀጥል። እርግጥ ነው፣ ዓላማህ እውቀት መሰብሰብ ብቻ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ እውነት ወደ ልብህ ጠልቆ እንዲገባ ማድረግና የተማርካቸውን ነገሮች ተግባር ላይ ማዋል ይኖርብሃል። የይሖዋ መንፈስ እንዲህ እንድታደርግ ይረዳሃል። ከዚህም በተጨማሪ ወንድሞችህንና እህቶችህን ማበረታታት አለብህ። (ዕብ. 10:24, 25) ለምን? ምክንያቱም መንፈሳዊ ቤተሰቦችህ ናቸው። የአምላክ መንፈስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከልብ የመነጨ ሐሳብ መስጠት እንድትችልና ክፍል ሲሰጥህ አቅምህ በፈቀደ መጠን ጥሩ አድርገህ ማቅረብ እንድትችል እንዲረዳህ ጸልይ። በእነዚህ መንገዶች ውድ ለሆኑት በጎች ፍቅር እንዳለህ ለይሖዋና ለልጁ ማሳየት ትችላለህ።—ዮሐ. 21:15-17

17. የይሖዋን ድርጅት በታማኝነት እንደምትደግፍ ማሳየት የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

17 በቅርቡ በምድር ላይ የሚቀረው ብቸኛው ድርጅት በአምላክ መንፈስ የሚመራው ድርጅት ይሆናል። እንግዲያው ከይሖዋ ድርጅት ጋር አብረህ በቅንዓት አገልግል። ለምታገኛቸው ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን በመስበክ ልክ እንደ አምላክ ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ሁሉንም ሰው እንደምትወድ አሳይ። በጉባኤ ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን በማድረግ ሥርዓትና ሰላም የሚወደውን አምላክ ምሳሌ ተከተል። አምላክ ከሚያዘጋጀው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ሙሉ ተጠቃሚ በመሆን ታላቁ አስተማሪህን እንደምትሰማ አሳይ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የሰይጣን ዓለም ሲጠፋ በፍርሃት አትዋጥም። ከዚህ ይልቅ ከይሖዋ ድርጅት ጋር ተባብረው በታማኝነት ሲያገለግሉ ከነበሩት ሰዎች ጎን በልበ ሙሉነት ትቆማለህ።

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

^ አን.5 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ድርጅቱን እየመራ እንዳለ ሙሉ እምነት አለህ? በዚህ ርዕስ ላይ ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የክርስቲያን ጉባኤ የመራውና በዛሬው ጊዜም ሕዝቡን እየመራ ያለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

^ አን.1 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ሰማያዊና ምድራዊ ክፍል አለው። በዚህ ርዕስ ውስጥ “ድርጅት” የሚለው ቃል የተሠራበት ምድራዊውን ክፍል ለማመልከት ነው።

^ አን.52 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት አቅኚ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ስለሚያገለግሉ አስፋፊዎች በቪዲዮ ካየች በኋላ ምሳሌያቸውን ለመከተል ተነሳሳች። በኋላም ግቧ ላይ ደርሳ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል ጀመረች።