በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 45

ሰዎች የክርስቶስን ትእዛዛት እንዲጠብቁ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

ሰዎች የክርስቶስን ትእዛዛት እንዲጠብቁ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

“ሂዱና . . . ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19, 20

መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ

ማስተዋወቂያ *

1. በማቴዎስ 28:18-20 ላይ ኢየሱስ ምን ትእዛዝ ሰጥቷል?

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ፣ በገሊላ ተሰብስበው ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ተገለጠ። ሊነግራቸው ያሰበው አስፈላጊ ነገር ነበር። ምን ይሆን? የተናገረው ሐሳብ በማቴዎስ 28:18-20 ላይ ይገኛል።—ጥቅሱን አንብብ።

2. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 በዛሬው ጊዜ ያለ እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ ማድረግ የሰጠውን መመሪያ መታዘዝ ይጠበቅበታል። እንግዲያው ኢየሱስ ከሰጠን ኃላፊነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሦስት ጥያቄዎችን እስቲ እንመርምር። አንደኛ፣ ለአዳዲስ ደቀ መዛሙርት አምላክ ምን እንደሚጠብቅባቸው ከማስተማር በተጨማሪ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሁለተኛ፣ በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ? ሦስተኛ፣ የቀዘቀዙ የእምነት ባልንጀሮቻችን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንደገና መካፈል እንዲጀምሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

ትእዛዛቱን እንዲጠብቁ አስተምሯቸው

3. ኢየሱስ በሰጠው ትእዛዝ ላይ የትኛውን ነጥብ አካትቷል?

3 ኢየሱስ የሰጠው መመሪያ ግልጽ ነው። እሱ ያዘዘውን ነገር ለሰዎች ማስተማር አለብን። ሆኖም ኢየሱስ በሰጠው ትእዛዝ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ አስፈላጊ ነጥብ አለ። ኢየሱስ ‘ያዘዝኳችሁንም ሁሉ አስተምሯቸው’ አላለም። ከዚህ ይልቅ “ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]” ብሏል። ይህን መመሪያ ለመታዘዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ማስተማር ብቻ ሳይሆን መምራትም ይኖርብናል። (ሥራ 8:31) እንዲህ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

4. አንድ ተማሪ የክርስቶስን መመሪያ እንዲጠብቅ ማስተማር የምንችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

4 ታዲያ አንድ ሰው የኢየሱስን ትእዛዝ እንዲጠብቅ ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የተጠቀሰው ምሳሌ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠቁመናል። መኪና ማሽከርከር የሚያሠለጥን አንድ ሰው፣ ተማሪው የትራፊክ ሕጎችን እንዲጠብቅ የሚያስተምረው እንዴት ነው? መጀመሪያ ላይ፣ አስተማሪው ስለ ትራፊክ ሕጎች ክፍል ውስጥ ያስተምረው ይሆናል። ሆኖም ተማሪው እነዚህን ሕግጋት እንዴት እንደሚታዘዝ ለማስተማር ሌላም ማድረግ የሚጠበቅበት ነገር አለ። ተማሪው መኪና ለማሽከርከር ሲወጣ አብሮት ይሆናል። ከዚያም የተማረውን ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥር መመሪያ ይሰጠዋል። ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

5. (ሀ) በዮሐንስ 14:15 እና በ1 ዮሐንስ 2:3 መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ምን እንዲያደርጉ ልናስተምራቸው ይገባል? (ለ) ጥናቶቻችንን ልንመራቸው የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና አምላክ ምን እንደሚጠብቅብን እናስተምራቸዋለን። ይሁን እንጂ ሌላም ማድረግ የሚኖርብን ነገር አለ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን የተማሩትን ነገር በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስተማር ይኖርብናል። (ዮሐንስ 14:15ን እና 1 ዮሐንስ 2:3ን አንብብ።) ጥናቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በሚዝናኑበት ወቅት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ምሳሌ ሆነን እናሳያቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋችን ከጉዳት የጠበቀን ወይም ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የረዳን እንዴት እንደሆነ የራሳችንን ተሞክሮ እንንገራቸው። ጥናቶቻችን ባሉበት ስንጸልይ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንዲመራቸው እንለምን።—ዮሐ. 16:13

6. ጥናቶቻችን የክርስቶስን ትእዛዛት እንዲጠብቁ ማስተማር ምን ይጨምራል?

6 ጥናቶቻችን የኢየሱስን ትእዛዛት እንዲጠብቁ ማስተማር ምን ይጨምራል? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የመካፈል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ልንረዳቸው ይገባል። አንዳንዶች በስብከቱ ሥራ ስለ መካፈል ሲያስቡ ራሱ ያስፈራቸው ይሆናል። በመሆኑም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር በትዕግሥት መርዳታችንን መቀጠል ያስፈልገናል። የተማሩት ነገር ልባቸውን ሲነካው በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ይነሳሳሉ። ታዲያ ጥናቶቻችን ምሥራቹን ለሌሎች የመናገር ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመርዳት የትኛውን ዘዴ መጠቀም እንችላለን?

7. ጥናታችን ምሥራቹን ለሌሎች የመናገር ፍላጎት እንዲያድርበት ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው?

7 ጥናታችንን * እንዲህ እያልን ልንጠይቀው እንችላለን፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግህ ሕይወትህን ያሻሻለው እንዴት ነው? ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መስማታቸው እንደሚጠቅማቸው ይሰማሃል? እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?” (ምሳሌ 3:27፤ ማቴ. 9:37, 38) በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የሚገኙትን ትራክቶች ለጥናትህ አሳየው፤ ከዚያም ቤተሰቦቹን፣ ጓደኞቹን ወይም የሥራ ባልደረቦቹን ሊማርኳቸው የሚችሉ ትራክቶችን እንዲመርጥ ጋብዘው። ለጥናትህ የተወሰኑ ትራክቶች ስጠው። ትራክቱን በደግነት እንዴት ማበርከት እንደሚችል አለማምደው። በእርግጥ ጥናታችን ያልተጠመቀ አስፋፊ በሚሆንበት ጊዜ አብረነው አገልግሎት በመውጣት ልንመራው ይገባል።—መክ. 4:9, 10፤ ሉቃስ 6:40

ጉባኤው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እድገት እንዲያደርጉ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?

8. ጥናቶቻችን ለአምላክና ለባልንጀራቸው ጥልቅ ፍቅር ማዳበራቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (“ ጥናቶቻችን ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

8 ኢየሱስ፣ ያዘዘውን “ሁሉ እንዲጠብቁ” ሰዎችን እንድናስተምር መመሪያ እንደሰጠን እናስታውስ። ኢየሱስ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል፣ ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት እንደሚገኙበት የታወቀ ነው፤ እነሱም አምላክንና ባልንጀራን መውደድ ናቸው። እነዚህ ትእዛዛት ደግሞ ከስብከቱና ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ጋር በጥብቅ የተያያዙ ናቸው። (ማቴ. 22:37-39) የሚያያዙት እንዴት ነው? በስብከቱ ሥራ ለመካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለአምላክና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ነው። እርግጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በስብከቱ ሥራ መካፈል ያስፈራቸው ይሆናል። እንዲህ ላሉት ጥናቶች፣ በይሖዋ እርዳታ ቀስ በቀስ የሰው ፍርሃትን ማሸነፍ እንደሚችሉ ልናረጋግጥላቸው እንችላለን። (መዝ. 18:1-3፤ ምሳሌ 29:25) በዚህ ርዕስ ላይ የሚገኘው ሣጥን፣ ጥናታችን ለአምላክ ያለው ፍቅር እንዲያድግ ልንወስዳቸው የምንችላቸውን እርምጃዎች ያብራራል። አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ለአምላክና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር እንዲያድግ በመርዳት ረገድ ጉባኤውስ ምን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል?

9. መኪና መንዳት ስለሚማረው ሰው ባነሳነው ምሳሌ ላይ ተማሪው ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት የሚችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

9 መኪና ማሽከርከር ስለሚማረው ሰው ያነሳነውን ምሳሌ እስቲ መለስ ብለን እንመልከት። ይህ ተማሪ ከአስተማሪው ጋር ሆኖ በሚያሽከረክርበት ወቅት ትምህርት መቅሰም የሚችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? አስተማሪው የሚነግረውን በማዳመጥ እንዲሁም ሌሎች ጠንቃቃ ሹፌሮች የሚነዱበትን መንገድ በመመልከት ነው። ለምሳሌ አስተማሪው፣ ለሌላ መኪና በደግነት ቅድሚያ የሚሰጥን ሹፌር ያሳየው ይሆናል። አሊያም ደግሞ ከፊት የሚመጡ አሽከርካሪዎች እንዳይቸገሩ ሲል የፊት መብራቱን የሚቀንስን ሹፌር ይጠቁመው ይሆናል። ተማሪው እንዲህ ያሉ ምሳሌዎችን በማየት፣ በሚነዳበት ወቅት የሚጠቅመው ትምህርት ያገኛል።

10. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ የሚረዳው ምንድን ነው?

10 በተመሳሳይም በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዝ የጀመረ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርት የሚቀስመው ከአስተማሪው ብቻ ሳይሆን ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች ከሚተዉት ግሩም ምሳሌም ነው። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ምንድን ነው? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘታቸው ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በስብሰባዎቻችን ላይ የሚያገኙት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት እውቀታቸው እንዲያድግ፣ እምነታቸው እንዲጠነክር እንዲሁም ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል። (ሥራ 15:30-32) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በሚገኝበት ወቅት፣ አስተማሪው እንደ እሱ ዓይነት ሁኔታ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር ሊያስተዋውቀው ይችላል። ተማሪው በጉባኤ ውስጥ ሌሎች ክርስቲያናዊ ፍቅር ሲያሳዩ የመመልከት አጋጣሚ ያገኛል። እስቲ የሚከተሉትን ሁኔታዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት።

11. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ምሳሌዎችን የማየት አጋጣሚ ያገኛል? ይህስ ምን እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል?

11 ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በጉባኤ ውስጥ እንደ እሷ ዓይነት ሁኔታ ያላትን እህት ትመለከታለች። ተማሪዋ፣ እህታችን ትናንሽ ልጆቿን ይዛ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ለመምጣት የምታደርገውን ጥረት ስትመለከት ልቧ ይነካል። ሲጋራ ማጨሱን ለማቆም የሚታገል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ፣ እንዲህ ያለውን ሱስ ማሸነፍ ከቻለ አስፋፊ ጋር ይተዋወቃል። አስፋፊው ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ መሄዱ ትእዛዛቱን ለመጠበቅ እንዴት እንደረዳው ለተማሪው ይነግረዋል። (2 ቆሮ. 7:1፤ ፊልጵ. 4:13) አስፋፊው የራሱን ተሞክሮ ከነገረው በኋላ “አንተም ሊሳካልህ ይችላል” ሲለው ተማሪው ይበልጥ ይበረታታል። አንዲት ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ደግሞ ይሖዋን በደስታ የምታገለግል ወጣት በስብሰባዎች ላይ ትመለከታለች። ተማሪዋ፣ እህታችን ምን ያህል ደስተኛ እንደሆነች ስትመለከት ሁልጊዜ ደስተኛ የሆነችበትን ሚስጥር ለማወቅ ትነሳሳለች።

12. በጉባኤ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመርዳት ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

12 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ስብሰባ ሲመጡ የተለያየ ሁኔታ ካላቸው ታማኝ አስፋፊዎች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ ያገኛሉ፤ የእነሱን ምሳሌ መመልከታቸው፣ አምላክንና ባልንጀራችንን እንድንወድ ክርስቶስ የሰጠውን ትእዛዝ መጠበቅ ምን እንደሚጠይቅ ለመማር ያስችላቸዋል። (ዮሐ. 13:35፤ 1 ጢሞ. 4:12) በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው እንደ እሱ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ካሉባቸው አስፋፊዎች ትምህርት መቅሰም ይችላል። ተማሪው እነዚህን ምሳሌዎች ማየቱ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልጉትን ማስተካከያዎች ማድረግ ከአቅሙ በላይ እንዳልሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። (ዘዳ. 30:11) በእርግጥም በጉባኤ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በተለያዩ መንገዶች አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል። (ማቴ. 5:16) ወደ ስብሰባዎች የሚመጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማበረታታት አንተ በበኩልህ ምን እያደረግክ ነው?

የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን በሥራው እንደገና እንዲካፈሉ እርዷቸው

13-14. ኢየሱስ ተስፋ የቆረጡ ሐዋርያቱን የያዛቸው እንዴት ነው?

13 የቀዘቀዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ በሰጠው ሥራ እንደገና መካፈል እንዲጀምሩ መርዳት እንፈልጋለን። ኢየሱስ ተስፋ የቆረጡ ሐዋርያቱን የያዘበት መንገድ እኛም ምን ማድረግ እንደምንችል ያስተምረናል።

14 ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት ‘ሁሉም ሐዋርያቱ ጥለውት ሸሽተዋል።’ (ማር. 14:50፤ ዮሐ. 16:32) ታዲያ ኢየሱስ ሐዋርያቱ እምነታቸው ተዳክሞ በነበረበት ወቅት የያዛቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ለአንዳንድ ተከታዮቹ ‘አትፍሩ! ሂዱና ለወንድሞቼ፣ እንደተነሳሁ ንገሯቸው’ ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:10ሀ) ኢየሱስ በሐዋርያቱ ተስፋ አልቆረጠም። ጥለውት ቢሄዱም እንኳ “ወንድሞቼ” በማለት ጠርቷቸዋል። እንደ ይሖዋ ሁሉ ኢየሱስም መሐሪና ይቅር ባይ መሆኑን አሳይቷል።—2 ነገ. 13:23

15. በአገልግሎት መካፈል ስላቆሙ የእምነት ባልንጀሮቻችን ምን ይሰማናል?

15 እኛም በአገልግሎት መካፈላቸውን ላቆሙ ክርስቲያኖች ከልብ እናስባለን። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለሆኑ እንወዳቸዋለን። እነዚህ የእምነት ባልንጀሮቻችን ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው በትጋት ያከናወኑትን አገልግሎት እናስታውሳለን፤ አንዳንዶቹ ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን አገልግለዋል። (ዕብ. 6:10) እንደገና ልናያቸው በጣም እንጓጓለን! (ሉቃስ 15:4-7) ታዲያ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል አሳቢነታችንን ልናሳያቸው የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

16. ለቀዘቀዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቡላቸው። ኢየሱስ ተስፋ የቆረጡ ሐዋርያቱን ያበረታታበት አንዱ መንገድ እሱ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ መጋበዝ ነበር። (ማቴ. 28:10ለ፤ 1 ቆሮ. 15:6) ዛሬም በተመሳሳይ፣ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ልናበረታታቸው እንችላለን። በእርግጥ ስብሰባ መምጣት እንዲጀምሩ በተደጋጋሚ መጋበዝ ሊያስፈልገን ይችላል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ግብዣውን በመቀበላቸው በጣም ተደስቶ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም።—ማቴ. 28:16፤ ከሉቃስ 15:6 ጋር አወዳድር።

17. አንድ የቀዘቀዘ ክርስቲያን ስብሰባ ሲመጣ እንዴት ልንቀበለው ይገባል?

17 በደስታ ተቀበሏቸው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተገናኘበት ወቅት እነሱን በማየቱ እንደተደሰተ እንዲሰማቸው አድርጓል፤ እነሱ እስኪመጡ ከመጠበቅ ይልቅ እሱ ራሱ ሄዶ አነጋግሯቸዋል። (ማቴ. 28:18) እኛስ አንድ የቀዘቀዘ አስፋፊ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሲመጣ ምን ልናደርግ ይገባል? ቅድሚያውን ወስደን በደስታ ልንቀበለው ይገባል። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ምን ማለት እንዳለብን ግራ ይገባን ይሆናል። የሚያሸማቅቀው ነገር አንናገር፤ ከዚህ ይልቅ ስላየነው በጣም እንደተደሰትን እንግለጽለት።

18. የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን ልናበረታታቸው የምንችለው እንዴት ነው?

18 አበረታቷቸው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ በመላው ዓለም እንዲሰብኩ የተሰጣቸው ተልእኮ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እኔ . . . ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:20) ታዲያ ይህን ማለቱ ደቀ መዛሙርቱን አበረታቷቸዋል? በሚገባ! ብዙም ሳይቆይ ደቀ መዛሙርቱ ‘ምሥራቹን በማስተማሩና በማወጁ’ ሥራ ተጠመዱ። (ሥራ 5:42) የቀዘቀዙ አስፋፊዎችም ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። እንደገና በስብከቱ ሥራ መካፈል ያስፈራቸው ይሆናል። እንግዲያው ለአገልግሎት በሚወጡበት ወቅት ብቻቸውን እንደማይሆኑ ልናረጋግጥላቸው እንችላለን። አገልግሎት ለመውጣት ዝግጁ ሲሆኑ ደግሞ አብረናቸው ልናገለግል እንችላለን። እንደገና ምሥራቹን መስበክ በሚጀምሩበት ወቅት እኛ ለምናደርግላቸው ድጋፍ አመስጋኝ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን እንደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አድርገን እንደምንመለከታቸው ስናሳያቸው በመንፈሳዊ ሊነቃቁ ይችላሉ፤ ይህም መላውን ጉባኤ ያስደስታል።

በአደራ የተሰጠንን ሥራ ማጠናቀቅ እንፈልጋለን

19. ልባዊ ምኞታችን ምንድን ነው? ለምንስ?

19 ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ የምናከናውነው እስከ መቼ ነው? የዚህ ሥርዓት መደመደሚያ እስኪያበቃ ድረስ ነው። (ማቴ. 28:20፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ ላይ “የሥርዓቱ መደምደሚያ” የሚለውን ተመልከት።) ታዲያ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ኢየሱስ የሰጠንን ተልእኮ መወጣት እንችል ይሆን? ቁርጥ ውሳኔያችን ይህ ነው! “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን ለመፈለግ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ንብረታችንን በደስታ እንሰጣለን። (ሥራ 13:48) እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” ብሏል። (ዮሐ. 4:34፤ 17:4) የእኛም ልባዊ ምኞት ይህ ነው። በአደራ የተሰጠንን ሥራ ማጠናቀቅ እንፈልጋለን። (ዮሐ. 20:21) በተጨማሪም የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን ጨምሮ ሌሎችም በዚህ ሥራ አብረውን እንዲጸኑ እንፈልጋለን።—ማቴ. 24:13

20. ፊልጵስዩስ 4:13 እንደሚገልጸው ኢየሱስ የሰጠንን ተልእኮ መፈጸም እንደምንችል እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

20 ኢየሱስ የሰጠንን ታላቅ ተልእኮ መፈጸም ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ይህንን ሥራ የምንሠራው ብቻችንን አይደለም። ኢየሱስ አብሮን እንደሚሆን ቃል ገብቷል። ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ተልእኮ “ከአምላክ ጋር አብረን [የምንሠራው]” ሥራ ነው፤ በተጨማሪም ይህ “ከክርስቶስ ጋር በመተባበር” የምናከናውነው ሥራ ነው። (1 ቆሮ. 3:9፤ 2 ቆሮ. 2:17) በመሆኑም ሊሳካልን ይችላል። ይህን ተልእኮ መፈጸም እና ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው፤ ደግሞም ታላቅ ደስታ ያስገኛል!—ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብብ።

መዝሙር 79 ጸንተው እንዲቆሙ አስተምሯቸው

^ አን.5 ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ተከታዮቹን አዟቸዋል፤ በተጨማሪም ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲያስተምሯቸው ነግሯቸዋል። ይህ ርዕስ የኢየሱስን መመሪያ እንዴት መታዘዝ እንደምንችል ያብራራል። ትምህርቱ በከፊል የተወሰደው በሐምሌ 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14-19 ላይ ከሚገኝ ርዕስ ነው።

^ አን.7 ስለ ጥናቱ ስንናገር በተባዕታይ ፆታ የተጠቀምነው ለአጻጻፍ እንዲያመች ነው።

^ አን.67 የሥዕሉ መግለጫ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራች ያለች አንዲት እህት፣ ለአምላክ ያላት ፍቅር እንዲያድግ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንዳለባት ለጥናቷ ስታብራራ። በኋላ ላይ ተማሪዋ፣ አስተማሪዋ የነገረቻትን ሦስት ነገሮች ተግባራዊ ስታደርግ ይታያል።