በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 47

መስተካከላችሁን ለመቀጠል ፈቃደኛ ናችሁ?

መስተካከላችሁን ለመቀጠል ፈቃደኛ ናችሁ?

‘በተረፈ ወንድሞች፣ መደሰታችሁንና መስተካከላችሁን ቀጥሉ።’—2 ቆሮ. 13:11

መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”

ማስተዋወቂያ *

1. ማቴዎስ 7:13, 14 እንደሚገልጸው በጉዞ ላይ ነን ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?

ሁላችንም በጉዞ ላይ ነን። የጉዟችን መዳረሻ ወይም ግባችን አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ በሚያስተዳድረው አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር ነው። ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ ለመጓዝ በየዕለቱ ጥረት እናደርጋለን። ሆኖም ኢየሱስ እንዳለው ይህ መንገድ ቀጭን ነው፤ አንዳንድ ጊዜም በዚህ መንገድ ላይ መጓዝ አስቸጋሪ ነው። (ማቴዎስ 7:13, 14ን አንብብ።) ፍጹማን ስላልሆንን በቀላሉ ከዚህ ጎዳና ስተን ልንወጣ እንችላለን።—ገላ. 6:1

2. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን? (“ ትሕትና አካሄዳችንን ለማስተካከል ይረዳናል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

2 ወደ ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ መጓዛችንን መቀጠል ከፈለግን አስተሳሰባችንን፣ ዝንባሌያችንን እና ምግባራችንን ለማስተካከል ፈቃደኞች መሆን አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ‘መስተካከላችሁን ቀጥሉ’ በማለት አበረታቷቸዋል። (2 ቆሮ. 13:11) ይህ ምክር ለእኛም ይሠራል። በዚህ ርዕስ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ አካሄዳችንን ለማስተካከል የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወዳጆቻችን ከሕይወት ጎዳና እንዳንወጣ እንዴት እንደሚረዱን እንመለከታለን። በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት የሚሰጠውን መመሪያ መከተል ተፈታታኝ ሊሆንብን የሚችለው መቼ እንደሆነ እናያለን። አካሄዳችንን ማስተካከል በሚኖርብን ወቅት ትሕትና በይሖዋ አገልግሎት ደስታችንን ሳናጣ ይህን እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን።

የአምላክ ቃል እንዲያርማችሁ ፍቀዱ

3. የአምላክ ቃል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

3 የራሳችንን አስተሳሰብና ስሜት ለመመርመር ጥረት ስናደርግ አንድ ተፈታታኝ ሁኔታ ይገጥመናል። ልባችን ከዳተኛ ስለሆነ ወዴት እየመራን እንዳለ በትክክል ማወቅ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። (ኤር. 17:9) “የውሸት ምክንያት” እያቀረብን ሳይታወቀን ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። (ያዕ. 1:22) እንግዲያው ራሳችንን ለመመርመር የአምላክን ቃል መጠቀም ያስፈልገናል። የአምላክ ቃል ውስጣዊ ማንነታችንን ይኸውም የልባችንን “ሐሳብና ዓላማ” ግልጽልጽ አድርጎ ያሳየናል። (ዕብ. 4:12, 13) እንደ ራጅ መሣሪያ ሁሉ የአምላክ ቃልም በውስጣችን ያለውን ለማየት ያስችለናል። ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከአምላክ ወኪሎች የምናገኘውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ትሑቶች መሆን ያስፈልገናል።

4. ንጉሥ ሳኦል ከጊዜ በኋላ ኩራት እንደተጠናወተው የሚያሳየው ምንድን ነው?

4 ትሑት አለመሆን ምን እንደሚያስከትል ከንጉሥ ሳኦል መማር እንችላለን። ሳኦል ከመጠን በላይ ኩሩ በመሆኑ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው ለራሱ እንኳ አልታየውም ነበር። (መዝ. 36:1, 2፤ ዕን. 2:4) ይህን በግልጽ የሚያሳይ አንድ ሁኔታ እንመልከት፦ ሳኦል አማሌቃውያንን ድል ከነሳ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለበት ይሖዋ ግልጽ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። ሳኦል ግን ይሖዋን ሳይታዘዝ ቀረ። ነቢዩ ሳሙኤል ስለ ጉዳዩ ሲያነጋግረው ደግሞ ሳኦል ስህተቱን አምኖ አልተቀበለም። ከዚህ ይልቅ ስህተቱን በማቃለልና ጥፋቱን በሌሎች ላይ በማላከክ ድርጊቱን ለማስተባበል ሞከረ። (1 ሳሙ. 15:13-24) ሳኦል ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ዝንባሌ አሳይቷል። (1 ሳሙ. 13:10-14) ልቡ እንዲታበይ መፍቀዱ የሚያሳዝን ነው። አስተሳሰቡን አላስተካከለም፤ በመሆኑም ይሖዋ ተግሣጽ የሰጠው ከመሆኑም ሌላ የእሱን ንግሥና አልተቀበለውም።

5. ሳኦል ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?

5 እንደ ሳኦል ዓይነት ስህተት ላለመሥራት ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘በአምላክ ቃል ላይ የሚገኝን ምክር ሳነብ ምክሩን ተግባራዊ ላለማድረግ ሰበብ አስባብ እፈጥራለሁ? ድርጊቴ ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ራሴን ለማሳመን እሞክራለሁ? ጥፋቴን በሌሎች ላይ አላክካለሁ?’ ከእነዚህ ጥያቄዎች ለአንዱም እንኳ የምንሰጠው መልስ ‘አዎ’ ከሆነ አስተሳሰባችንን እና ዝንባሌያችንን ማስተካከል ይኖርብናል። እንዲህ ካላደረግን ልባችን እየታበየ ይሄዳል፤ ትዕቢተኛ ከሆንን ደግሞ ይሖዋ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ አይቀበለንም።—ያዕ. 4:6

6. በንጉሥ ሳኦልና በንጉሥ ዳዊት መካከል ያለውን ልዩነት ግለጽ።

6 እስቲ ንጉሥ ሳኦልን፣ በእሱ ምትክ ከነገሠው ከንጉሥ ዳዊት ጋር እናነጻጽረው፤ ዳዊት ‘የይሖዋን ሕግ’ የሚወድ ሰው ነበር። (መዝ. 1:1-3) ይሖዋ ትሑታንን እንደሚያድን፣ ትዕቢተኞችን ግን እንደሚቃወም ዳዊት ያውቅ ነበር። (2 ሳሙ. 22:28) ስለዚህ ዳዊት የአምላክ ሕግ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክልለት ፈቅዷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ። በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ ያርመኛል።”—መዝ. 16:7

የአምላክ ቃል

የአምላክ ቃል መንገዳችንን ስተን ስንወጣ ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል። ትሑት ከሆንን የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንን እንዲያስተካክልልን እንፈቅዳለን (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

7. ትሑት ከሆንን ምን እናደርጋለን?

7 ትሑት ከሆንን በውስጣችን ያሉ የተሳሳቱ ሐሳቦች ወደ መጥፎ ድርጊት ከማምራታቸው በፊት የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንን እንዲያስተካክለው እንፈቅዳለን። የአምላክ ቃል “መንገዱ ይህ ነው። በእሱ ሂድ” በማለት የሚመራን ድምፅ ይሆንልናል። መንገዳችንን ስተን ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ስንወጣ ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል። (ኢሳ. 30:21) ይሖዋን መስማታችን በብዙ መንገዶች ይጠቅመናል። (ኢሳ. 48:17) ለምሳሌ፣ አንድ ሰው መጥቶ እርማት ሲሰጠን ከሚሰማን የኀፍረት ስሜት ያድነናል። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚወደው ልጁ እንደቆጠረን ስለምንገነዘብ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን።—ዕብ. 12:7

8. በያዕቆብ 1:22-25 ላይ እንደተገለጸው የአምላክን ቃል እንደ መስተዋት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

8 የአምላክ ቃል እንደ መስተዋት ሊሆንልን ይችላል። (ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ።) አብዛኞቻችን ጠዋት ከቤት ከመውጣታችን በፊት መስተዋት እናያለን። ይህን የምናደርገው ከሰዎች ጋር ከመገናኘታችን በፊት፣ የሚያስፈልገንን ማስተካከያ ለማድረግ ነው። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ስናነብ ከአስተሳሰባችን እና ከዝንባሌያችን ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ልናደርግባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን እንመለከታለን። ብዙዎች ጠዋት ከቤት ከመውጣታቸው በፊት የዕለቱን ጥቅስ ማንበብ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በሚያነቡት ነገር ላይ ተመሥርተው አስተሳሰባቸውን ያርማሉ። ከዚያም በቀኑ ውስጥ፣ ከአምላክ ቃል ያገኙትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉባቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ። በተጨማሪም በየቀኑ የአምላክን ቃል የምናነብበትና ባነበብነው ላይ የምናሰላስልበት ፕሮግራም ሊኖረን ይገባል። ይህ ቀላል ነገር ቢመስልም ወደ ሕይወት ከሚወስደው ቀጭን መንገድ ሳንወጣ ለመጓዝ ከሚረዱን በጣም አስፈላጊ ነገሮች አንዱ ነው።

የጎለመሱ ወዳጆቻችሁን አዳምጡ

የጎለመሱ ወዳጆች

አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በደግነት ማስጠንቀቂያ ይሰጠን ይሆናል። ወዳጃችን ድፍረት ቢጠይቅበትም ይህን በማድረጉ አመስጋኝ እንሆናለን? (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

9. አንድ ወዳጅህ እርማት የሚሰጥህ ለምን ሊሆን ይችላል?

9 ከይሖዋ የሚያርቅህን ጎዳና መከተል የጀመርክበት ጊዜ ነበር? (መዝ. 73:2, 3) አንድ የጎለመሰ ወዳጅህ፣ ድፍረት ቢጠይቅበትም ምክር ሰጥቶህ ይሆናል። ታዲያ ምክሩን ሰምተህ ተግባራዊ አደረግኸው? ከሆነ ትክክለኛውን ነገር አድርገሃል። ጓደኛህ ማስጠንቀቂያ ስለሰጠህ አመስጋኝ እንደምትሆንም ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 1:5

10. አንድ ወዳጅህ እርማት ቢሰጥህ ምላሽህ ምን ሊሆን ይገባል?

10 የአምላክ ቃል “የወዳጅ ማቁሰል ከታማኝነት የሚመነጭ ነው” ይለናል። (ምሳሌ 27:6) ይህ ሐሳብ ምን ትርጉም አለው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ መኪና የሚበዛበት አንድ መንገድ ለመሻገር ቆመሃል እንበል። ስልክህን እየነካካህ ትኩረትህ ስለተከፋፈለ ግራ ቀኙን ሳታይ መሻገር ጀመርክ። ልክ በዚያ ቅጽበት አንድ ወዳጅህ እጅህን ጎትቶ ወደ ዳር አወጣህ። ጥብቅ አድርጎ ስለያዘህ እጅህ በለዘ፤ ሆኖም የወሰደው አፋጣኝ እርምጃ በመኪና ከመገጨት አድኖሃል። እጅህን የያዘበት ቦታ ላይ ለተወሰኑ ቀናት ቢያምህም ወዳጅህ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ በመውሰዱ ቅር ትሰኛለህ? ቅር እንደማይልህ ጥያቄ የለውም። እንዲያውም ላደረገልህ ነገር አመስጋኝ ትሆናለህ። በተመሳሳይም አነጋገርህ ወይም ድርጊትህ ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር እንደማይስማማ አንድ ወዳጅህ ቢነግርህ መጀመሪያ ላይ ቅር ትሰኝ ይሆናል። ሆኖም ወዳጅህ በሰጠህ ምክር አትበሳጭ። እንዲህ ማድረግ ሞኝነት ነው። (መክ. 7:9) ከዚህ ይልቅ ጓደኛህ ድፍረት ቢጠይቅበትም አንተን በማነጋገሩ አመስጋኝ ሁን።

11. አንድ ሰው ወዳጁ የሚሰጠውን ጥሩ ምክር እንዳይቀበል እንቅፋት የሚሆንበት ምን ሊሆን ይችላል?

11 አንድ ሰው ከሚወደው ወዳጁ የሚሰጠውን ጥሩ ምክር እንዳይቀበል እንቅፋት የሚሆንበት አንዱ ነገር ምንድን ነው? ኩራት ነው። ኩሩ ሰዎች መስማት የሚፈልጉት ‘ጆሯቸውን የሚኮረኩርላቸውን’ ነገር ነው። “እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ።” (2 ጢሞ. 4:3, 4) ለራሳቸው አመለካከት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ፤ ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑም ያስባሉ። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው” ሲል ጽፏል። (ገላ. 6:3) ንጉሥ ሰለሞንም ነጥቡን ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ እንዳያደርግ ማስተዋል ከጎደለው በዕድሜ የገፋ ሞኝ ንጉሥ ይልቅ ድሃ የሆነ ጥበበኛ ልጅ ይሻላል።”—መክ. 4:13

12. በገላትያ 2:11-14 ላይ የሚገኘው ዘገባ እንደሚያሳየው ሐዋርያው ጴጥሮስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 እስቲ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት፤ በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በሰዎች ፊት ለጴጥሮስ እርማት ሰጥቶት ነበር። (ገላትያ 2:11-14ን አንብብ።) ጴጥሮስ ትኩረት ያደረገው እርማቱ በተሰጠበት መንገድ ወይም በሰው ፊት በመሰጠቱ ላይ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ በተናገረው ነገር ቅር ሊሰኝ ይችል ነበር። ሆኖም ጴጥሮስ ጥበበኛ ነበር። ምክሩን ተቀብሏል፤ በጳውሎስ ላይም ቂም አልያዘም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ስለ ጳውሎስ ሲናገር “የተወደደው ወንድማችን” በማለት ጠርቶታል።—2 ጴጥ. 3:15

13. ምክር ስንሰጥ የትኞቹን ነጥቦች ልናስታውስ ይገባል?

13 ለአንድ ወዳጅህ ምክር መስጠት እንዳለብህ ከተሰማህ የትኞቹን ነጥቦች ልታስታውስ ይገባል? ወዳጅህን ከማነጋገርህ በፊት ‘“ከልክ በላይ ጻድቅ” እየሆንኩ ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (መክ. 7:16) ከልክ በላይ ጻድቅ የሆነ ሰው በይሖዋ መሥፈርቶች ሳይሆን የራሱን መሥፈርቶች በማውጣት በሌሎች ላይ ይፈርዳል፤ ይህን በሚያደርግበት ወቅትም ምሕረት ላያሳይ ይችላል። ራስህን ከመረመርክ በኋላም ጓደኛህን ማነጋገር እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል፤ ከሆነ ማስተካከል ያለበትን ችግር ለይተህ ጥቀስ፤ እንዲሁም የአመለካከት ጥያቄዎችን በመጠቀም ስህተቱ እንዲገባው እርዳው። ወዳጅህ ተጠያቂ የሆነው በይሖዋ እንጂ በአንተ ፊት እንዳልሆነ አስታውስ፤ በመሆኑም የምትናገረው ነገር በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ይሁን። (ሮም 14:10) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተጠቀም፤ እንዲሁም ምክር ስትሰጥ እንደ ኢየሱስ ርኅራኄ አሳይ። (ምሳሌ 3:5፤ ማቴ. 12:20) እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ እኛን የሚይዘን ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ነው።—ያዕ. 2:13

የአምላክ ድርጅት የሚሰጣችሁን መመሪያ ተከተሉ

የአምላክ ድርጅት

የአምላክ ድርጅት፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱን ጽሑፎች፣ ቪዲዮዎችና ስብሰባዎች ያዘጋጃል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የበላይ አካሉ ሥራው ከሚደራጅበት መንገድ ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ያደርጋል (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

14. የአምላክ ድርጅት ምን ዝግጅት አድርጎልናል?

14 ይሖዋ ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንድንጓዝ እኛን ለመምራት በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል ይጠቀማል። ይህ ድርጅት ደግሞ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱንን ቪዲዮዎች፣ ጽሑፎችና ስብሰባዎች ያዘጋጃል። የይሖዋ ድርጅት የሚያዘጋጀው ትምህርት ሙሉ በሙሉ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ነው። የበላይ አካሉ የስብከቱን ሥራ ማከናወን ስለሚቻልበት የተሻለ መንገድ ውሳኔ ሲያደርግ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ይጠይቃል። ያም ቢሆን የበላይ አካሉ ሥራው ከተደራጀበት መንገድ ጋር በተያያዘ ያደረጋቸውን ውሳኔዎች በየጊዜው ይገመግማል። ለምን? ምክንያቱም “የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው”፤ በመሆኑም የአምላክ ድርጅት ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።—1 ቆሮ. 7:31

15. አንዳንድ አስፋፊዎች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል?

15 ከመሠረተ ትምህርት ወይም ከሥነ ምግባር ደንቦች ጋር በተያያዘ ድርጅቱ የሚሰጠውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ መከተል እንደማይከብደን የታወቀ ነው። ሆኖም የአምላክ ድርጅት ሌሎች የሕይወታችንን ዘርፎች የሚነካ ለውጥ በሚያደርግበት ጊዜ ምን ምላሽ እንሰጣለን? ለምሳሌ ያህል፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአምልኮ ቦታዎችን መገንባትና መንከባከብ የሚጠይቀው ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በመሆኑም የበላይ አካሉ፣ የስብሰባ አዳራሾች በሙሉ አቅማቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል ውሳኔ አድርጓል። በዚህ ለውጥ የተነሳ አንዳንድ ጉባኤዎች ተዋህደዋል፤ የተወሰኑ የስብሰባ አዳራሾችም ተሸጠዋል። በዚህ መንገድ የተገኘው ገንዘብ፣ አዳራሾች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት ውሏል። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ጉባኤዎች ተዋህደው እንዲሁም አዳራሾች ተሸጠው ከሆነ ከአዲሱ ሁኔታ ጋር መላመድ ሊከብድህ ይችላል። በዚህ ለውጥ የተነሳ አንዳንድ አስፋፊዎች በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ከበፊቱ ራቅ ወዳለ ቦታ መጓዝ አስፈልጓቸዋል። አንድን አዳራሽ በመገንባቱ ወይም በመንከባከቡ ሥራ ብዙ የደከሙ ክርስቲያኖች ደግሞ አዳራሹ ሲሸጥ ያዝኑ ይሆናል። ጊዜያቸውና ጉልበታቸው እንደባከነ ሊሰማቸው ይችላል። ያም ቢሆን ከዚህ አዲስ ዝግጅት ጋር ተባብረዋል፤ በመሆኑም ሊመሰገኑ ይገባል።

16. በቆላስይስ 3:23, 24 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ደስታችንን ጠብቀን ለመቀጠል የሚረዳን እንዴት ነው?

16 የምንሠራው ለይሖዋ እንደሆነና እሱ ድርጅቱን እየመራ እንዳለ ካስታወስን ደስታችንን አናጣም። (ቆላስይስ 3:23, 24ን አንብብ።) ንጉሥ ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ በሰጠበት ወቅት የተናገረው ነገር ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። እንዲህ ብሏል፦ “በፈቃደኝነት ተነሳስተን እንዲህ ያለ መባ ማቅረብ እንችል ዘንድ እኔም ሆንኩ ሕዝቤ ማን ነን? ሁሉም ነገር የተገኘው ከአንተ ነውና፤ የሰጠንህም ከገዛ እጅህ የተቀበልነውን ነው።” (1 ዜና 29:14) እኛም የገንዘብ መዋጮ ስናደርግ ከይሖዋ እጅ የተቀበልነውን ነገር መልሰን እየሰጠነው ነው። ያም ቢሆን ይሖዋ የእሱን ሥራ ለመደገፍ የምንሰጠውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ንብረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—2 ቆሮ. 9:7

ከቀጭኑ መንገድ አትውጡ

17. አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ቢያስፈልግህ ተስፋ መቁረጥ የሌለብህ ለምንድን ነው?

17 ሁላችንም ወደ ሕይወት ከሚመራው ቀጭን መንገድ ሳንወጣ መጓዝ ከፈለግን የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል አለብን። (1 ጴጥ. 2:21) ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንዳለብህ ቢሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። እንዲያውም ይህ፣ ለይሖዋ መመሪያዎች ምላሽ የሚሰጥ ልብ እንዳለህ የሚያሳይ ስለሆነ ጥሩ ምልክት ነው። ይሖዋ የኢየሱስን ምሳሌ ፍጹም በሆነ መንገድ እንድንከተል እንደማይጠብቅብን አስታውስ፤ ምክንያቱም ፍጹማን እንዳልሆንን ያውቃል።

18. ግባችን ላይ መድረስ ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

18 እንግዲያው ሁላችንም ወደፊት በምናገኘው ሽልማት ላይ ትኩረት እናድርግ፤ እንዲሁም በአስተሳሰባችን፣ በዝንባሌያችን እና በምግባራችን ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች እንሁን። (ምሳሌ 4:25፤ ሉቃስ 9:62) ምንጊዜም ትሑት እንሁን፤ እንዲሁም ‘መደሰታችንንና መስተካከላችንን’ እንቀጥል። (2 ቆሮ. 13:11) እንዲህ ካደረግን ‘የፍቅርና የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል።’ በተጨማሪም በሕይወት ጎዳና ላይ የጀመርነውን ጉዞ አጠናቅቀን ያሰብነው ቦታ ላይ መድረስ ብቻ ሳይሆን በጉዟችን ደስተኛ መሆን እንችላለን።

መዝሙር 34 በንጹሕ አቋም መመላለስ

^ አን.5 አንዳንዶቻችን በአስተሳሰባችን፣ በዝንባሌያችን እና በምግባራችን ላይ ለውጥ ማድረግ ይከብደን ይሆናል። ይህ ርዕስ ሁላችንም ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ ያብራራል። በተጨማሪም ማስተካከያ ማድረግ በሚያስፈልገን ጊዜ ደስታችንን እንዳናጣ ምን እንደሚረዳን ይገልጻል።

^ አን.76 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት ወንድም የተሳሳተ ውሳኔ በማድረጉ የገጠመውን ነገር በዕድሜ ለሚበልጠው ወንድም (በስተ ቀኝ) ሲያጫውተው፤ በዕድሜ የሚበልጠው ወንድም፣ ምክር መስጠት ያስፈልገው እንደሆነ ለማወቅ በጥሞና እያዳመጠው ነው።