በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 50

“ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው?”

“ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው?”

“ሞት ሆይ፣ ድል አድራጊነትህ የት አለ? ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?”—1 ቆሮ. 15:55

መዝሙር 141 ሕይወት ተአምር ነው

ማስተዋወቂያ *

1-2. ሰማያዊው ትንሣኤ የሁሉንም ክርስቲያኖች ትኩረት ሊስብ የሚገባው ለምንድን ነው?

በአሁኑ ወቅት የሚኖሩ አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ተስፋቸው በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ነው። በመንፈስ የተቀቡ ጥቂት ክርስቲያኖች ግን ተስፋቸው ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ መሄድ ነው። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የወደፊቱ ሕይወታቸው ምን እንደሚመስል ለማወቅ እንደሚጓጉ የታወቀ ነው። ሆኖም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ስለዚህ ትንሣኤ ለማወቅ የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ከዚህ በመቀጠል እንደምንመለከተው ሰማያዊው ትንሣኤ፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ሰዎችም በረከት ያስገኛል። ስለዚህ ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ፣ ሰማያዊው ትንሣኤ ትኩረታችንን ሊስበው ይገባል።

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ እንዲጽፉ አምላክ በመንፈሱ መርቷቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኛ አሁን የአምላክ ልጆች ነን፤ ሆኖም ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እሱ በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን።” (1 ዮሐ. 3:2) ስለዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አካል ይዘው ከሞት ሲነሱ በሰማይ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው አያውቁም። ሆኖም ሽልማታቸውን ሲያገኙ ይሖዋን ቃል በቃል ያዩታል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ አይገልጽልንም፤ ያም ቢሆን ሐዋርያው ጳውሎስ የተወሰነ መረጃ ሰጥቶናል። ክርስቶስ “ማንኛውንም መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን” በሚያጠፋበት ጊዜ ቅቡዓኑ ከእሱ ጋር ይሆናሉ። ከሚጠፉት ነገሮች መካከል “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት” ይገኝበታል። በመጨረሻም ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ ራሳቸውን እንዲሁም ሁሉንም ነገር ለይሖዋ ያስገዛሉ። (1 ቆሮ. 15:24-28) እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! *

3. በ1 ቆሮንቶስ 15:30-32 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ በትንሣኤ ላይ ያለው እምነት ምን እንዲያደርግ ረድቶታል?

3 ጳውሎስ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለው እምነት የተለያዩ መከራዎችን በጽናት ለመወጣት ረድቶታል። (1 ቆሮንቶስ 15:30-32ን አንብብ።) ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “እኔ በየቀኑ ሞትን እጋፈጣለሁ” ብሏቸዋል። ጳውሎስ “በኤፌሶን ከአውሬዎች ጋር [ታገልኩ]” በማለትም ጽፏል። ይህን ሲል ምናልባት በኤፌሶን በሚገኝ ስታዲየም ውስጥ ቃል በቃል ከእንስሳት ጋር እንደታገለ መግለጹ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 1:8፤ 4:10፤ 11:23) ወይም ደግሞ እንደ “አውሬ” ጨካኝ የሆኑ አይሁዳውያን ወይም ሌሎች ሰዎች ያደረሱበትን ተቃውሞ እየገለጸ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 19:26-34፤ 1 ቆሮ. 16:9) ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ጳውሎስ ከባድ መከራዎችን ተጋፍጧል፤ ይሁን እንጂ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል።—2 ቆሮ. 4:16-18

በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉበት አገር የሚኖር አንድ ቤተሰብ አባላት፣ አምላክ ወደፊት የተሻለ ነገር እንደሚሰጣቸው በመተማመን በአምልኳቸው ጸንተዋል (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. የትንሣኤ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች ብርታት የሰጣቸው እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

4 የምንኖረው አደገኛ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። አንዳንድ ወንድሞቻችን የወንጀል ሰለባ ሆነዋል። በጦርነት በሚታመስ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሕይወታቸው ሁልጊዜ አደጋ ላይ ነው። ሌሎች ደግሞ የሚኖሩት በስብከቱ ሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉባቸው አልፎ ተርፎም ሥራችን ጨርሶ በታገደባቸው አገሮች ውስጥ ነው። በዚህም የተነሳ ይሖዋን የሚያገለግሉት ሕይወታቸውን ወይም ነፃነታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነው። ያም ቢሆን እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ በጽናት ይሖዋን ማምለካቸውን ቀጥለዋል፤ በዚህም ግሩም ምሳሌ ሆነውልናል። በዚህ ሥርዓት ሕይወታቸውን ቢያጡም እንኳ ይሖዋ ወደፊት የላቀ ነገር እንደሚሰጣቸው ስለሚያውቁ አይፈሩም።

5. በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት የሚያዳክመው የትኛው አደገኛ አመለካከት ነው?

5 ጳውሎስ በዘመኑ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች የነበራቸውን “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል አደገኛ አመለካከት አስመልክቶ ወንድሞቹን አስጠንቅቋቸዋል። ይህ አመለካከት ከጳውሎስ ዘመን በፊትም ነበር። ምናልባትም ጳውሎስ እስራኤላውያን የነበራቸውን ዝንባሌ የሚገልጸውን ኢሳይያስ 22:13⁠ን እየጠቀሰ ሊሆን ይችላል። እስራኤላውያን ወደ አምላክ ከመቅረብ ይልቅ ተድላን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመሩ ነበር። በሌላ አባባል እነዚህ እስራኤላውያን “ሺህ ዓመት አይኖር” ያሉ ያህል ነው፤ እንዲህ ያለው አመለካከት ዛሬም በስፋት ይታያል። ሆኖም ይህ አመለካከት በእስራኤላውያን ላይ ያስከተለውን መዘዝ ከታሪካቸው መመልከት ይቻላል።—2 ዜና 36:15-20

6. የትንሣኤ ተስፋ በጓደኛ ምርጫችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

6 ይሖዋ ሙታንን እንደሚያስነሳ ማወቃችን በጓደኛ ምርጫችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። በቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ ወንድሞች ትንሣኤን ከሚክዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ላለመመሥረት መጠንቀቅ ነበረባቸው። ከዚህ ግሩም ትምህርት እናገኛለን፤ ለዛሬ ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን ጓደኛ አድርገን መምረጣችን ጎጂ ነው። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፉ በአመለካከቱና በሥነ ምግባሩ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል፤ ይባስ ብሎም አምላክ የሚጠላውን ዓይነት ሕይወት እንዲከተል ማለትም በኃጢአት ጎዳና እንዲመላለስ ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም ጳውሎስ “ጽድቅ የሆነውን በማድረግ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአት መሥራትን ልማድ አታድርጉ” የሚል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—1 ቆሮ. 15:33, 34

ከሞት የሚነሱት ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው?

7. በ1 ቆሮንቶስ 15:35-38 ላይ እንደምንመለከተው አንዳንዶች ትንሣኤን በተመለከተ ምን ጥያቄ አንስተው ሊሆን ይችላል?

7 አንደኛ ቆሮንቶስ 15:35-38ን አንብብ። በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጥርጣሬ መዝራት የሚፈልግ ሰው “ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው? ከሞት የሚነሱትስ ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው?” የሚል ጥያቄ ያነሳ ይሆናል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት የተለያየ አመለካከት ስላላቸው ጳውሎስ የሰጠውን መልስ መመርመራችን አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ጳውሎስ ዘርንና ተክልን እንደ ምሳሌ በመጠቀም አምላክ ከሞት ለሚነሱት ሰዎች ተስማሚ አካል እንደሚሰጣቸው አስረድቷል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8. ሰማያዊ ትንሣኤን ለመረዳት የሚያግዘን የትኛው ምሳሌ ነው?

8 ሰው ሲሞት፣ አካሉ ይበሰብሳል። ይሁን እንጂ ጽንፈ ዓለምን ከምንም የፈጠረው አምላክ፣ ሰውየውን ከሞት አስነስቶ ተስማሚ አካል ሊሰጠው ይችላል። (ዘፍ. 1:1፤ 2:7) አምላክ ያንኑ አካል መልሶ ማስነሳት እንደማያስፈልገው ለማስረዳት ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ተጠቅሟል። አንድን “ዘር” ወደ አእምሯችን እናምጣ። መሬት ላይ የተዘራ ዘር ሲበቅል አዲስ ተክል ይሆናል። አዲሱ ተክል፣ ከተዘራው ዘር ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው። ጳውሎስ ይህን ንጽጽር የተጠቀመው፣ ፈጣሪ “የፈለገውን አካል” መስጠት እንደሚችል ለማስረዳት ነው።

9. አንደኛ ቆሮንቶስ 15:39-41 የተለያዩ አካሎችን በተመለከተ ምን ይላል?

9 አንደኛ ቆሮንቶስ 15:39-41ን አንብብ። ጳውሎስ፣ አምላክ የተለያየ ዓይነት አካል እንደፈጠረ ገልጿል። የተለያዩ ዓይነት ሥጋዊ አካሎች አሉ፤ ለምሳሌ የከብት ሥጋ፣ የወፎች ሥጋ እንዲሁም የዓሣ ሥጋ አለ። ጳውሎስ፣ ሰማይ ላይ የምንመለከታቸው ፀሐይና ጨረቃም የተለያዩ እንደሆኑ ገልጿል። በተጨማሪም “የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል” ብሏል። በዓይናችን ልንለያቸው ባንችልም እንኳ የሳይንስ ሊቃውንት የተለያዩ ዓይነት ከዋክብት እንዳሉ ይገልጻሉ፤ አንዳንዶቹ ትላልቅ፣ አንዳንዶቹ ትናንሽ፣ አንዳንዶቹ ቀይ፣ አንዳንዶቹ ነጭ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ ፀሐያችን ቢጫ ናቸው። በተጨማሪም ጳውሎስ “ሰማያዊ አካላት አሉ፤ ምድራዊ አካላትም አሉ” በማለት ጽፏል። ምን ማለቱ ነበር? በምድር ላይ ያለነው ሥጋዊ አካል አለን፤ በሰማይ ያሉት ደግሞ ልክ እንደ መላእክት መንፈሳዊ አካል አላቸው።

10. ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ምን ዓይነት አካል ይኖራቸዋል?

10 ጳውሎስ በመቀጠል ምን እንዳለ ልብ እንበል፦ “የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው። የሚዘራው የሚበሰብስ ነው፤ የሚነሳው የማይበሰብስ ነው።” አንድ ሰው ሲሞት አካሉ እንደሚበሰብስና ወደ አፈር እንደሚመለስ እናውቃለን። (ዘፍ. 3:19) ታዲያ አንድ አካል “የማይበሰብስ” ሆኖ የሚነሳው እንዴት ነው? ጳውሎስ እየተናገረ ያለው፣ ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ መኖራቸውን ስለቀጠሉ ሰዎች አይደለም፤ እንዲህ ዓይነት ትንሣኤ ካገኙ ሰዎች መካከል ኤልያስ፣ ኤልሳዕና ኢየሱስ ከሞት ያስነሷቸው ሰዎች ይገኙበታል። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ሰማያዊ አካል ወይም “መንፈሳዊ አካል” ይዘው ስለሚነሱ ሰዎች መናገሩ ነበር።—1 ቆሮ. 15:42-44

11-12. ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ምን ዓይነት አካል ይዞ ነው? ቅቡዓኑስ ተመሳሳይ ነገር የሚያጋጥማቸው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሥጋዊ አካል ነበረው፤ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ግን “ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ” ሆኖ ወደ ሰማይ ተመለሰ። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞት የሚነሱት መንፈሳዊ አካል ይዘው ነው። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ከአፈር የተሠራውን ሰው መልክ እንደመሰልን ሁሉ የሰማያዊውንም መልክ እንመስላለን።”—1 ቆሮ. 15:45-49

12 ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ የሰጠውን ማብራሪያ እየደመደመ ነበር። ኢየሱስ ሥጋዊ አካል ይዞ እንዳልተነሳ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ጳውሎስ “ሥጋና ደም የአምላክን መንግሥት አይወርስም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:50) ሐዋርያትም ሆኑ ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሥጋና ደም ይኸውም የሚበሰብስ አካል ይዘው አይደለም። ለመሆኑ ከሞት የሚነሱት መቼ ነው? ጳውሎስ ይህ ትንሣኤ ወደፊት የሚከናወን ነገር እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል፤ ቅቡዓኑ እንደሞቱ ወዲያውኑ ከሞት አልተነሱም። ጳውሎስ አንደኛ ቆሮንቶስን በጻፈበት ወቅት አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ‘በሞት አንቀላፍተው’ ነበር፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ ሐዋርያው ያዕቆብ ነው። (ሥራ 12:1, 2) ሌሎቹ ሐዋርያትና የተቀቡ ክርስቲያኖችም ከጊዜ በኋላ ‘በሞት አንቀላፍተዋል።’—1 ቆሮ. 15:6

በሞት ላይ የተገኘ ድል

13. በኢየሱስ መገኘት ወቅት ምን ይከናወናል?

13 ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ልዩ ስለሆነ ወቅት ይኸውም ስለ ክርስቶስ መገኘት ተናግረው ነበር። የክርስቶስን መገኘት ለይተው ከሚያሳውቁ ክስተቶች መካከል ጦርነት፣ የምድር ነውጥ፣ ቸነፈር እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ክንውኖች ይገኙበታል። ከ1914 አንስቶ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እየተፈጸመ ነው። ይህ ምልክት ሌላ ወሳኝ ገጽታም አለው። ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት እንደተቋቋመ የሚገልጸው “ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 24:3, 7-14) ጳውሎስ “በሞት አንቀላፍተው ያሉት” ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ትንሣኤ የሚያገኙት ‘ጌታ በሚገኝበት ጊዜ’ እንደሆነ ገልጿል።—1 ተሰ. 4:14-16፤ 1 ቆሮ. 15:23

14. በክርስቶስ መገኘት ወቅት የሚሞቱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ያጋጥማቸዋል?

14 በዛሬው ጊዜ ምድራዊ ሕይወታቸውን የሚያጠናቅቁ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወዲያውኑ ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:51, 52 ላይ የተናገረው ሐሳብ ይህን ያረጋግጥልናል፤ እንዲህ ብሏል፦ “በሞት የምናንቀላፋው ሁላችንም አይደለንም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን።” ጳውሎስ የተናገረው ይህ ሐሳብ በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። እነዚህ የክርስቶስ ወንድሞች ከሞት ከተነሱ በኋላ ‘ሁልጊዜ ከጌታ ጋር ስለሚሆኑ’ የተሟላ ደስታ ይኖራቸዋል።—1 ተሰ. 4:17

“በቅጽበተ ዓይን” የሚለወጡት ቅቡዓን ከኢየሱስ ጋር በመሆን ብሔራትን ያደቅቃሉ (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. “በቅጽበተ ዓይን” የሚለወጡት ሰዎች ምን ሥራ ይጠብቃቸዋል?

15 “በቅጽበተ ዓይን” የሚለወጡት ሰዎች ሰማይ ሄደው ምን እንደሚያከናውኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ኢየሱስ እንዲህ ይላቸዋል፦ “ድል ለሚነሳና በሥራዬ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በብሔራት ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤ ይህም ከአባቴ የተቀበልኩት ዓይነት ሥልጣን ነው። ድል የነሳውም ሕዝቦችን እንደ ሸክላ ዕቃ እንዲደቅቁ በብረት በትር ይገዛቸዋል።” (ራእይ 2:26, 27) በሰማይ ያሉት ቅቡዓን፣ መሪያቸውን ተከትለው ብሔራትን እንደ እረኛ በብረት በትር ይገዛሉ።—ራእይ 19:11-15

16. ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በሞት ላይ ድል የሚጎናጸፉት እንዴት ነው?

16 ቅቡዓኑ በሞት ላይ ድል እንደሚጎናጸፉ ግልጽ ነው። (1 ቆሮ. 15:54-57) ትንሣኤ ማግኘታቸው፣ በመጪው የአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ከኢየሱስ ጋር ሆነው በክፋት ላይ ድል እንዲቀዳጁ ያስችላቸዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ደግሞ “ታላቁን መከራ አልፈው” ወደ አዲሱ ዓለም ይገባሉ። (ራእይ 7:14) እነዚህ ሰዎች ሞት በሌላ መንገድ ድል ሲነሳ ይኸውም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀደም ሲል የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙ ይመለከታሉ። ይህን አስደናቂ ድል ስንመለከት ምን ያህል እንደምንደሰት እስቲ አስበው! (ሥራ 24:15) ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ታማኝ የሚሆኑ ሁሉ ከአዳም በወረሱት ሞት ላይም ጭምር ድል ይቀዳጃሉ። ለዘላለም መኖር ይችላሉ።

17. አንደኛ ቆሮንቶስ 15:58 እንደሚናገረው በአሁኑ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 በዛሬው ጊዜ በሕይወት ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ጳውሎስ የትንሣኤ ተስፋን አስመልክቶ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጻፈላቸው የሚያበረታታ መልእክት አመስጋኞች መሆን አለባቸው። ጳውሎስ ‘በጌታ ሥራ’ እንድንጠመድ የሰጠንን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለን። (1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።) በዚህ ሥራ በታማኝነትና በትጋት ከተካፈልን፣ ወደፊት አስደሳች የሆነ ሕይወት ይጠብቀናል። ይህ ሕይወት ልናስብ ከምንችለው ከማንኛውም ነገር የላቀ ይሆናል። ይህን ሕይወት ስናገኝ፣ ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት ያከናወንነው ሥራ ከንቱ አለመሆኑን እርግጠኛ እንሆናለን።

መዝሙር 140 መጨረሻ የሌለው ሕይወት

^ አን.5 የ​አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ሁለተኛ ክፍል ስለ ትንሣኤ በተለይም ስለ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንሣኤ በዝርዝር ያወሳል። ሆኖም ጳውሎስ የጻፈው ሐሳብ የሌሎች በጎችንም ትኩረት ይስባል። ይህ ርዕስ የትንሣኤ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችንን ሊነካው የሚገባው እንዴት እንደሆነ ያብራራል፤ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት እንድንጠባበቅ ይረዳናል።

^ አን.2 በዚህ እትም ውስጥ የሚገኘው “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:29 ላይ የተናገረውን ሐሳብ ያብራራል።