በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:29 ላይ የተናገረው ሐሳብ፣ በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለሞቱ ሰዎች ብለው ይጠመቁ እንደነበር ያሳያል?

አያሳይም። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የታሪክ መዛግብት እንዲህ ያለ ልማድ እንደነበረ አይገልጹም።

ይህ ጥቅስ በብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ የተቀመጠበት መንገድ፣ አንዳንዶች ‘በጳውሎስ ዘመን ለሙታን ብለው የተጠመቁ ሰዎች ነበሩ’ ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲህ ይላል፦ “ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው?”—አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ሆኖም ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የሰጡትን ሐሳብ እንመልከት። ዶክተር ግሬገሪ ሎክዉድ ‘እስከሚታወቀው ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በታሪክ መዛግብት ላይ ለሞቱ ሰዎች ሲባል ስለተደረገ ጥምቀት የሚገልጽ ምንም መረጃ የለም’ ብለዋል። በተመሳሳይም ፕሮፌሰር ጎርደን ዶናልድ ፊ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ታሪክም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ስላለው ጥምቀት አይናገሩም። አዲስ ኪዳን ስለዚህ ጉዳይ ምንም አይገልጽም፤ በቀጣዮቹ ክፍለ ዘመናት ውስጥ፣ በሌሎቹ ቤተ ክርስቲያናትም ሆነ በየትኛውም ጥንታዊ የክርስትና ማኅበረሰብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ልማድ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።”

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ኢየሱስ ተከታዮቹን “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) አንድ ሰው ተጠምቆ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ስለ ይሖዋ እና ስለ ልጁ መማር፣ በእነሱ ማመን እንዲሁም እነሱን መታዘዝ ይኖርበታል። ሞቶ የተቀበረ ሰው ይህን ማድረግ አይችልም፤ በሕይወት ያለ ክርስቲያንም በእሱ ፋንታ ይህን ሊያደርግለት አይችልም።—መክ. 9:5, 10፤ ዮሐ. 4:1፤ 1 ቆሮ. 1:14-16

ታዲያ ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር?

በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የሙታን ትንሣኤ እንደሌለ ይናገሩ ነበር። (1 ቆሮ. 15:12) ጳውሎስ ይህ አመለካከት ትክክል አለመሆኑን አብራርቷል። እንዴት? “በየቀኑ ሞትን እጋፈጣለሁ” ብሏል። ጳውሎስ አደገኛ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ቢኖርበትም ከሞተ በኋላ ልክ እንደ ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ እንደሚነሳ እርግጠኛ ነበር።—1 ቆሮ. 15:30-32, 42-44

በመንፈስ መቀባት፣ በየቀኑ መከራን መጋፈጥንና ሰማያዊ ትንሣኤ ከማግኘት በፊት መሞትን እንደሚጠይቅ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መገንዘብ ነበረባቸው። ‘ክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ መጠመቅ፣ እሱ ሞት ውስጥ መጠመቅን’ ይጨምራል። (ሮም 6:3) ይህም ሲባል ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደ ኢየሱስ መከራን መጋፈጥ እንዲሁም ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ለመሄድ መሞት ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።

ኢየሱስ በውኃ ከተጠመቀ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሁለት ሐዋርያቱ ‘እኔ የምጠመቀውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁ’ ብሏቸው ነበር። (ማር. 10:38, 39) ኢየሱስ ይህን ሲል በውኃ እንደሚጠመቅ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መመላለሱ ወደ ሞት እንደሚመራው መግለጹ ነበር። ጳውሎስ ስለ ቅቡዓኑ ሲናገር ‘አሁን ከክርስቶስ ጋር አብረው መከራ ከተቀበሉ፣ በኋላ ደግሞ አብረውት ክብር እንደሚጎናጸፉ’ ገልጿል። (ሮም 8:16, 17፤ 2 ቆሮ. 4:17) ስለዚህ እነሱም ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ለመሄድ መሞት አለባቸው።

በመሆኑም ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚከተለው ተብሎ በትክክል ሊቀመጥ ይችላል፦ “አለዚያማ ለመሞት ብለው በመጠመቅ ምን የሚያተርፉት ነገር ይኖራል? ሙታን ፈጽሞ የማይነሱ ከሆነ እነሱም ለመሞት ብለው የሚጠመቁበት ምን ምክንያት አለ?”