በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 52

የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

“ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።”—መዝ. 55:22

መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ

ማስተዋወቂያ *

1. የተስፋ መቁረጥ ስሜት ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል?

በየዕለቱ ችግሮች የሚያጋጥሙን ሲሆን ችግሮቻችንን ለመቋቋም የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ሆኖም ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ችግሮቻችንን መቋቋም ይበልጥ ከባድ ይሆንብናል። ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ በራስ የመተማመን ስሜታችንን፣ ድፍረታችንን እንዲሁም ደስታችንን እንደሚቀማ ሌባ ነው ሊባል ይችላል። ምሳሌ 24:10 “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል” ይላል። አዎ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት የሚያስፈልገንን ኃይል ሊያሟጥጥብን ይችላል።

2. ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርጉን የሚችሉ አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ አንዳንዶቹ ውስጣዊ፣ ሌሎቹ ደግሞ ውጫዊ ናቸው። ተስፋ ከሚያስቆርጡን ሁኔታዎች መካከል አለፍጽምናችን፣ ያሉብን ድክመቶች እንዲሁም የጤና እክል ይገኙበታል። በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የምንፈልገውን መብት ባለማግኘታችን ምክንያት ወይም የአገልግሎት ክልላችን ፍሬያማ እንዳልሆነ ስለተሰማን ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለማሸነፍ ማድረግ የምንችላቸውን አንዳንድ ነገሮች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

ከአለፍጽምናችን እና ከድክመቶቻችን ጋር ስንታገል

3. ስለ ስህተቶቻችን ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል?

3 አለፍጽምናችንን ወይም ድክመቶቻችንን በተመለከተ ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት ሊያድርብን ይችላል። ባሉብን ድክመቶችን የተነሳ ይሖዋ ፈጽሞ ወደ አዲሱ ዓለም እንደማያስገባን ይሰማን ይሆናል። እንዲህ ያለው አመለካከት ጎጂ ነው። ታዲያ ስለ ስህተቶቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሁሉም ሰዎች “ኃጢአት” እንደሠሩ ይናገራል። (ሮም 3:23) ሆኖም ይሖዋ ስህተታችን ላይ አያተኩርም፤ እንዲሁም ፍጹም እንድንሆን አይጠብቅብንም። ከዚህ ይልቅ እኛን ለመርዳት የሚፈልግ አፍቃሪ አባት ነው። ይሖዋ ታጋሽም ነው። ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ እንዲሁም ራሳችንን ከልክ በላይ ላለመኮነን መታገል እንደሚያስፈልገን ያውቃል፤ ሊረዳንም ይፈልጋል።—ሮም 7:18, 19

ይሖዋ ቀደም ሲል ያደረግነውንም ሆነ አሁን እያደረግነው ያለውን መልካም ነገር ያውቃል (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት) *

4-5. በ1 ዮሐንስ 3:19, 20 መሠረት ሁለት እህቶች ለተስፋ መቁረጥ እጅ እንዳይሰጡ የረዳቸው ምንድን ነው?

4 ዲቦራን እና ማሪያን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። * ዲቦራ ልጅ እያለች ቤተሰቦቿ የበታችነት ስሜት እንዲሰማት አድርገዋታል። አመስግነዋት አያውቁም ነበር። በመሆኑም ስለ ራሷ መጥፎ አመለካከት አዳበረች። ትንሽ ስህተት በምትሠራበት ጊዜ እንኳ ጨርሶ እንደማትረባ ይሰማት ነበር። ማሪያም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟታል። ቤተሰቦቿ ያዋርዷት ነበር። በመሆኑም ከዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር ትታገል ነበር። ወደ እውነት ከመጣች በኋላም እንኳ የአምላክን ስም ለመሸከም ብቁ እንዳልሆነች ይሰማት ነበር።

5 ሆኖም እነዚህ ሁለት እህቶች ይሖዋን ማገልገላቸውን አላቆሙም። ለዚህ የረዳቸው ምንድን ነው? አንደኛ፣ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ‘ሸክማቸውን በይሖዋ ላይ መጣላቸው’ ነው። (መዝ. 55:22) በተጨማሪም አፍቃሪው አባታችን ስለ አገልጋዮቹ ያለውን አመለካከት መረዳታቸው ጠቅሟቸዋል። ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች ስለ ራሳችን መጥፎ ስሜት እንዲያድርብን እንደሚያደርጉ ያውቃል። እንዲሁም ይሖዋ በልባችን ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ያያል፤ በሌላ አባባል እኛ ስለ ራሳችን የማናውቃቸውን መልካም ባሕርያትም ጭምር ይመለከታል።1 ዮሐንስ 3:19, 20ን አንብብ።

6. አንድ ሰው መጥፎ ልማዱ ቢያገረሽበት ምን ሊሰማው ይችላል?

6 ሥር የሰደደ መጥፎ ልማድን ለማሸነፍ እየሞከረ ያለ አንድ ክርስቲያን ልማዱ ያገረሽበት ይሆናል፤ በዚህም የተነሳ በራሱ ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ኃጢአት በምንፈጽምበት ጊዜ በተወሰነ መጠን የበደለኝነት ስሜት እንደሚሰማን የታወቀ ነው። (2 ቆሮ. 7:10) ሆኖም ወደ ሌላኛው ጽንፍ በመሄድ ‘እኔ የማልረባ ሰው ነኝ፤ ይሖዋ ፈጽሞ ይቅር ሊለኝ አይችልም’ ብለን ራሳችንን ልንኮንን አይገባም። እንዲህ ያለው አሉታዊ አመለካከት፣ ከእውነታው የራቀ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ሊያደርገን ይችላል። ምሳሌ 24:10 ምን እንደሚል ልንዘነጋ አይገባም፤ ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ጉልበታችን እጅግ ይዳከማል። ከዚህ ይልቅ ወደ ይሖዋ በመጸለይና ምሕረት እንዲያደርግልን በመለመን ችግሩን ‘መፍታታችን’ የተሻለ ነው። (ኢሳ. 1:18) ይሖዋ ከልብ ንስሐ መግባታችንን ሲመለከት ይቅር ይለናል። በተጨማሪም ሽማግሌዎችን ልናነጋግር ይገባል። ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ እንድናገግም በትዕግሥት ይረዱናል።—ያዕ. 5:14, 15

7. ትክክል የሆነውን ማድረግ አታጋይ በሚሆንብን ጊዜ ተስፋ ልንቆርጥ የማይገባው ለምንድን ነው?

7 ዣን ሉክ የተባለ በፈረንሳይ የሚኖር የጉባኤ ሽማግሌ ከድክመታቸው ጋር ለሚታገሉ ክርስቲያኖች እንዲህ ይላቸዋል፦ “በይሖዋ ዓይን ጻድቅ የሚባለው፣ ጨርሶ ኃጢአት የማይፈጽም ሰው ሳይሆን ስህተት ከሠራ በኋላ የሚጸጸትና ምንጊዜም ንስሐ የሚገባ ሰው ነው።” (ሮም 7:21-25) ስለዚህ አንተም ካለብህ ድክመት ጋር እየታገልክ ከሆነ ራስህን አትኮንን። ማናችንም ብንሆን በራሳችን ሥራ በይሖዋ ዘንድ ጻድቅ ሆነን ልንቆጠር እንደማንችል ማስታወስ ይኖርብናል። ሁላችንም በቤዛው በኩል የተገለጸው የአምላክ ጸጋ ያስፈልገናል።—ኤፌ. 1:7፤ 1 ዮሐ. 4:10

8. የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማን ማንን እርዳታ መጠየቅ እንችላለን?

8 ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን! ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ማውራት ስንፈልግ ጆሮ ሰጥተው ሊያዳምጡን እንዲሁም የሚያጽናና እና የሚያበረታታ ሐሳብ ሊያካፍሉን ይችላሉ። (ምሳሌ 12:25፤ 1 ተሰ. 5:14) ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር ስትታገል የኖረች ጆይ የተባለች በናይጄሪያ የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞቼ ባይኖሩልኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? ወንድሞቼና እህቶቼ የሚሰጡኝ ማበረታቻ ይሖዋ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እንዲያውም ከራሴ አልፌ፣ ተስፋ የቆረጡ ሌሎች ሰዎችን ማጽናናት የምችለው እንዴት እንደሆነ ከእነሱ ተምሬያለሁ።” እርግጥ ነው፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መቼ ማበረታቻ እንደሚያስፈልገን ላያውቁ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል። ስለዚህ እርዳታ ሲያስፈልገን ወደ አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ቀርበን የውስጣችንን አውጥተን መናገር ሊያስፈልገን ይችላል።

ከጤና እክል ጋር ስንታገል

9. መዝሙር 41:3 እና 94:19 የሚያበረታቱን እንዴት ነው?

9 የይሖዋን እርዳታ ጠይቁ። ጤንነታችን ጥሩ በማይሆንበት ጊዜ በተለይ ደግሞ ከማይድን በሽታ ጋር በምንታገልበት ወቅት አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ በተአምር አይፈውሰንም፤ ሆኖም ያጽናናናል እንዲሁም ለመጽናት የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል። (መዝሙር 41:3⁠ን እና 94:19ን አንብብ።) ለምሳሌ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን ወይም ገበያ በመውጣት ረገድ እርዳታ ካስፈለገን የእምነት አጋሮቻችን እንዲያግዙን ሊያነሳሳቸው ይችላል። ወንድሞቻችን አብረውን እንዲጸልዩም ሊያነሳሳቸው ይችላል። አሊያም ደግሞ በቃሉ ውስጥ የሚገኙ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን እንድናስታውስ ሊረዳን ይችላል፤ ለምሳሌ፣ ሕመምና ሥቃይ በሌለበት አዲስ ዓለም ስለሚኖረን ፍጹም ሕይወት እንድናስብ ሊያደርገን ይችላል።—ሮም 15:4

10. ኢሳንግ አደጋ ከደረሰበት በኋላ መንፈሱ ተደቁሶ እንዳይቀር የረዳው ምንድን ነው?

10 በናይጄሪያ የሚኖረው ኢሳንግ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ሰውነቱ ሽባ ሆነ። ሐኪሙ ከዚያ በኋላ ጨርሶ በእግሩ መሄድ እንደማይችል ነገረው። ኢሳንግ “ልቤ ተሰብሮ፣ መንፈሴም ተደቁሶ ነበር” በማለት ተናግሯል። ይሁን እንጂ መንፈሱ እንደተደቆሰ አልቀረም። ኢሳንግን የረዳው ምንድን ነው? “እኔና ባለቤቴ ወደ ይሖዋ መጸለያችንን እንዲሁም ቃሉን ማጥናታችንን ፈጽሞ አላቆምንም ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም “አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋችንን ጨምሮ ባሉን በረከቶች ላይ ለማተኮር ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር” በማለት ገልጿል።

የአቅም ገደብ ያለባቸው ክርስቲያኖችም እንኳ ውጤታማና አስደሳች አገልግሎት ማከናወን ይችላሉ (ከአንቀጽ 11-13⁠ን ተመልከት)

11. ሲንዲ የጤና እክል ባጋጠማት ወቅት ደስተኛ ሆና መቀጠል የቻለችው እንዴት ነው?

11 በሜክሲኮ የምትኖረው ሲንዲ ለሕይወቷ የሚያሰጋ በሽታ እንዳለባት ተነገራት። ሲንዲ ሁኔታውን ለመቋቋም ምን አደረገች? ሕክምናዋን በምትከታተልበት ወቅት በየቀኑ ምሥክርነት ለመስጠት ግብ አውጥታ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ይህን ማድረጌ በቀዶ ሕክምናው፣ በሕመሜ ወይም በሚሰማኝ ሥቃይ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሌሎችን በመርዳት ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል። እንዲህ ለማድረግ እሞክራለሁ፦ ከሐኪሞቹ ወይም ከነርሶቹ ጋር ስነጋገር ስለ ቤተሰባቸው እጠይቃቸዋለሁ። ከዚያም እንዲህ ያለ ከባድ ሙያ የመረጡት ለምን እንደሆነ እጠይቃቸዋለሁ። እንዲህ ካደረግኩ በኋላ፣ ልባቸውን የሚነካውን ነጥብ መምረጥ ቀላል ይሆንልኛል። አንዳንዶቹ፣ ታካሚዎች ‘እንዴት ነህ?’ ብለው ጠይቀዋቸው እንደማያውቁ ነግረውኛል። ብዙዎቹ ለአሳቢነቴ ያመሰግኑኛል። እንዲያውም አንዳንዶቹ አድራሻቸውን ሰጥተውኛል። በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከባድ በሆነው በዚህ ወቅት ይሖዋ ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ ደስታ እንዳገኝ ረድቶኛል፤ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩ ሳስበው እኔ ራሴ በጣም እገረማለሁ!”—ምሳሌ 15:15

12-13. የታመሙ ወይም የአቅም ገደብ ያለባቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች በአገልግሎት መካፈል የቻሉት እንዴት ነው? ምን ውጤትስ አግኝተዋል?

12 የታመሙ ወይም አቅመ ደካማ የሆኑ ክርስቲያኖች በአገልግሎት ማከናወን የሚችሉት ነገር በጣም ውስን በመሆኑ የተነሳ ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ያም ቢሆን ብዙዎቹ ግሩም ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ትኖር የነበረችው ሎረል እንደ ሳንባ ሆኖ በሚያገለግል ማሽን ውስጥ ለ37 ዓመታት ኖራለች። በካንሰር ትሠቃይ ነበር፤ ከባድ ቀዶ ሕክምናዎችን አድርጋለች እንዲሁም አስከፊ የቆዳ በሽታ ነበረባት። ሆኖም እነዚህ ከባድ መከራዎች እንኳ መስበኳን እንድታቆም አላደረጓትም። ወደ ቤቷ ለሚመጡ ነርሶች እና ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ትመሠክር ነበር። ታዲያ ምን ውጤት አገኘች? ቢያንስ 17 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ረድታለች! *

13 በፈረንሳይ የሚኖር የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ሪቻርድ፣ ከቤታቸው መውጣት ለማይችሉ ወይም በመጦሪያ ተቋም ውስጥ ላሉ አስፋፊዎች ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። እንዲህ ብሏል፦ “አነስ ያለች የጽሑፍ ማሳያ እንዲጠቀሙ አበረታታቸዋለሁ። የጽሑፍ ማሳያው የሰዎችን ትኩረት ስለሚስብ ውይይት ለመጀመር አመቺ ነው። ይሄ ደግሞ እንደ ቀድሞው ከቤት ወደ ቤት ሄደው ማገልገል ለማይችሉ ውድ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በጣም አበረታች ነው።” ከቤት መውጣት የማይችሉ ወንድሞችና እህቶች በስልክ ወይም በደብዳቤ አማካኝነት መመሥከርም ይችላሉ።

የምንፈልገውን መብት አለማግኘት

14. ዳዊት ግሩም አርዓያ የተወልን እንዴት ነው?

14 በዕድሜያችን፣ በጤንነታችን ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በጉባኤ ወይም በወረዳ ውስጥ አንድን ኃላፊነት ወይም መብት ማግኘት አንችል ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመን ከንጉሥ ዳዊት ግሩም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ዳዊት የአምላክን ቤተ መቅደስ ለመገንባት በጣም ጓጉቶ ነበር። ሆኖም ቤተ መቅደሱን ለመገንባት እንዳልተመረጠ በተነገረው ጊዜ ይሖዋ ለዚህ ኃላፊነት ለመረጠው ሰው ሙሉ ድጋፉን ሰጥቷል። እንዲያውም ዳዊት ለሥራው ከፍተኛ መዋጮ አድርጓል። ዳዊት እንዴት ያለ ግሩም አርዓያ ትቶልናል!—2 ሳሙ. 7:12, 13፤ 1 ዜና 29:1, 3-5

15. ሂዩግ ያደረበትን የተስፋ መቁረጥ ስሜት መቋቋም የቻለው እንዴት ነው?

15 ሂዩግ የተባለ በፈረንሳይ የሚኖር አንድ ወንድም በነበረበት የጤና እክል የተነሳ በሽምግልና ማገልገሉን አቆመ፤ ያደረበት ሕመም ቀላል የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንኳ እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበት ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “መጀመሪያ አካባቢ በጣም ተስፋ ቆርጬ ነበር፤ እንዲሁም የዋጋ ቢስነት ስሜት አድሮብኝ ነበር። ውሎ አድሮ ግን ያለብኝን የአቅም ገደብ አምኜ መቀበል ያለውን ጥቅም ተገነዘብኩ። በመሆኑም ሁኔታዬ በሚፈቅድልኝ መጠን ይሖዋን በማገልገል ደስታ ማግኘት ችያለሁ። እጅ ላለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ። ቢደክማቸውም እንኳ መዋጋታቸውን እንደቀጠሉት እንደ ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች መታገሌን እቀጥላለሁ!”—መሳ. 8:4

16. መላእክት ከተዉት ምሳሌ ምን እንማራለን?

16 ታማኝ መላእክት ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ንጉሥ አክዓብ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት፣ ይሖዋ ይህን ክፉ ንጉሥ ማሞኘት ስለሚቻልበት መንገድ ሐሳብ እንዲሰጡ መላእክቱን ጋብዟቸው ነበር። አንዳንዶቹ መላእክት ሐሳብ አመነጩ። ይሖዋን የአንዱን መልአክ ሐሳብ በመቀበል እንደሚሳካለት ነገረው። (1 ነገ. 22:19-22) ታዲያ ሌሎቹ ታማኝ መላእክት በዚህ ተስፋ ቆርጠው ‘መጀመሪያውኑ ቢቀርብኝ ኖሮስ?’ ብለው አስበው ይሆን? እንደዚያ ብለው እንዳሰቡ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ አናገኝም። መላእክት በጣም ትሑት ስለሆኑ የሚያሳስባቸው ለይሖዋ ክብር መሰጠቱ ነው።—መሳ. 13:16-18፤ ራእይ 19:10

17. አንዳንድ የአገልግሎት መብቶችን ባለማግኘታችን ብናዝን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መብት የይሖዋን ስም መሸከምና መንግሥቱን ማሳወቅ እንደሆነ አትርሱ። ቲኦክራሲያዊ መብት ዛሬ አግኝተነው ነገ ልናጣው የምንችለው ነገር ነው። ይሁንና በይሖዋ ፊት ውድ የሚያደርገን ያለን መብት አይደለም። በይሖዋም ሆነ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ዘንድ ተወዳጅ የሚያደርገን፣ ትሑት መሆናችን እና ልካችንን ማወቃችን ነው። ስለዚህ ምንጊዜም ትሑት ለመሆን እንዲረዳችሁ ይሖዋን በጸሎት ለምኑት። በትሕትና እና ልክን በማወቅ ረገድ ግሩም አርዓያ በሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ አሰላስሉ። አቅማችሁ በሚፈቅደው በማንኛውም መንገድ ወንድሞቻችሁን በደስታ አገልግሉ።—መዝ. 138:6፤ 1 ጴጥ. 5:5

ክልላችን ፍሬያማ እንዳልሆነ ሲሰማን

18-19. የምታገለግልበት ክልል ፍሬያማ እንዳልሆነ በሚሰማህ ጊዜም ጭምር ከአገልግሎት ደስታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

18 የምታገለግልበት ክልል ፍሬያማ እንዳልሆነ ስለተሰማህ ወይም ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት ባለመቻልህ ምክንያት ተስፋ የቆረጥክበት ጊዜ አለ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ደስታችንን ጠብቀን ለመቀጠል አልፎ ተርፎም ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል? “ አገልግሎትህን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ . . .” በሚለው ሣጥን ውስጥ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን ማግኘት ይቻላል። ለአገልግሎት ተገቢውን አመለካከት መያዝም ጠቃሚ ነው። ይህ ምን ማለት ነው?

19 የስብከታችን ዋነኛ ዓላማ የአምላክን ስም እና መንግሥቱን ማሳወቅ እንደሆነ አንዘንጋ። ኢየሱስ የሕይወትን መንገድ የሚያገኙት በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ሰዎች እንደሆኑ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 7:13, 14) አገልግሎት ስንወጣ ከይሖዋ፣ ከኢየሱስ እንዲሁም ከመላእክት ጋር አብሮ የመሥራት መብት እናገኛለን። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ቆሮ. 3:9፤ ራእይ 14:6, 7) ይሖዋ የዘላለም ሕይወት የሚገባቸውን ሰዎች ወደ ራሱ ይስባል። (ዮሐ. 6:44) ስለዚህ አንድ ሰው ስናነጋግረው ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ ባይሰጥም እንኳ በሌላ ጊዜ ስንሄድ ጆሮ ሊሰጠን ይችላል።

20. ኤርምያስ 20:8, 9 የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ማሸነፍ ስለምንችልበት መንገድ ምን ያስተምረናል?

20 ከነቢዩ ኤርምያስ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። የአገልግሎት ምድቡ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ሕዝቡ “ቀኑን ሙሉ” ይሰድቡትና ያፌዙበት ነበር። (ኤርምያስ 20:8, 9ን አንብብ።) እንዲያውም በአንድ ወቅት በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ሥራውን ለማቆም አስቦ ነበር። ሆኖም እንዲህ አላደረገም። ለምን? “የይሖዋ ቃል” በልቡ ውስጥ እንዳለ የሚነድ እሳት ስለሆነበት ቃሉን አፍኖ መያዝ አልቻለም! እኛም አእምሯችንን እና ልባችንን በአምላክ ቃል ከሞላነው የኤርምያስ ዓይነት ስሜት ይኖረናል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ እንድናጠና እና እንድናሰላስልበት የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት ነው። እንዲህ ካደረግን ደስታችን እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም አገልግሎታችን ይበልጥ ፍሬያማ ይሆንልናል።—ኤር. 15:16

21. ከተስፋ መቁረጥ ጋር የምናደርገውን ትግል ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

21 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዲቦራ “ተስፋ መቁረጥ ሰይጣን የሚጠቀምበት ኃይለኛ መሣሪያ ነው” በማለት ተናግራለች። ሆኖም አምላካችን ይሖዋ፣ ሰይጣን ከሚጠቀምበት ከማንኛውም መሣሪያ የሚበልጥ ኃይል አለው። ስለዚህ ተስፋ ያስቆረጠህ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ እንዲረዳህ ምልጃ አቅርብ። ይሖዋ፣ ካለብህ አለፍጽምና እና ከድክመቶችህ ጋር በምታደርገው ትግል እንድታሸንፍ ይረዳሃል። የጤና እክል ሲያጋጥምህ ይረዳሃል። የአገልግሎት መብቶችን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል። እንዲሁም ለአገልግሎትህ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል። በተጨማሪም የሚያሳስብህን ነገር በሰማይ ለሚኖረው አባትህ በጸሎት ግለጽለት። ከተስፋ መቁረጥ ጋር የምታደርገውን ትግል በይሖዋ እርዳታ ማሸነፍ ትችላለህ!

መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ

^ አን.5 ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር እንታገላለን። እንዲህ ዓይነት ስሜት ሲፈጠርብን የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንደምንችል በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። በይሖዋ እርዳታ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ማሸነፍ እንደምንችል እንመለከታለን።

^ አን.4 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.12 የሎረል ኒዝቤትን የሕይወት ታሪክ በጥር 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ ማንበብ ይቻላል።

^ አን.69 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ለተወሰነ ጊዜ ተስፋ ቆርጣ ነበር። ሆኖም ቀደም ሲል ታከናውን ስለነበረው አገልግሎት ታስባለች፤ እንዲሁም ወደ ይሖዋ ትጸልያለች። ይሖዋ ቀደም ሲል ያደረገችውንም ሆነ አሁን እያደረገች ያለችውን ነገር እንደሚያስታውስ እርግጠኛ ነች።