በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኃላፊነትህን በቅንዓት ተወጣ!

ኃላፊነትህን በቅንዓት ተወጣ!

አንድ የቅርብ ጓደኛህ የሚያበረታታ ደብዳቤ ቢልክልህ ምን ይሰማሃል? የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነው ጢሞቴዎስ ከሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለ ደብዳቤ ደርሶት ነበር፤ ይህ ደብዳቤ በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲሆን 2 ጢሞቴዎስ በመባል ይታወቃል። ጢሞቴዎስ፣ የሚወደው ጓደኛው የላከለትን ደብዳቤ ጸጥ ያለ ቦታ ላይ ሆኖ ለማንበብ ጓጉቶ መሆን አለበት። ምናልባትም ጢሞቴዎስ ‘ጳውሎስ እንዴት ሰንብቶ ይሆን? ከተሰጠኝ ኃላፊነት ጋር በተያያዘ የጻፈልኝ ምክር ይኖር ይሆን? ይህ ደብዳቤ በክርስቲያናዊ አገልግሎቴ ስኬታማ ለመሆንና ሌሎችን ለመርዳትስ ያግዘኛል?’ በማለት አስቦ ሊሆን ይችላል። ቀጥለን እንደምንመለከተው ጢሞቴዎስ በዚህ ግሩም ደብዳቤ ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስና ሌሎች ጠቃሚ ሐሳቦችን አግኝቷል። እኛም በዚህ ደብዳቤ ውስጥ የምናገኛቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች እስቲ እንመልከት።

“ሁሉንም ነገር በጽናት ተቋቁሜ እኖራለሁ”

ጢሞቴዎስ ልክ ደብዳቤውን ማንበብ ሲጀምር ጳውሎስ ለእሱ ያለውን ፍቅር በግልጽ ተመልክቷል። ጳውሎስ “ተወዳጁ ልጄ” በማለት ጠርቶታል። (2 ጢሞ. 1:2) ጢሞቴዎስ በ65 ዓ.ም. ገደማ ይህ ደብዳቤ ሲደርሰው በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ወጣት ሳይሆን አይቀርም። ያም ቢሆን ተሞክሮ ያካበተ የጉባኤ ሽማግሌ ነበር። ከአሥር ዓመት በላይ ከጳውሎስ ጋር ሲሠራ ስለቆየ ብዙ ነገር ተምሯል።

ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ የደረሰበትን ፈተና በታማኝነት እየተቋቋመ መሆኑን ሲያውቅ በጣም ተበረታትቶ መሆን አለበት። ጳውሎስ ሮም ውስጥ እስር ላይ የነበረ ሲሆን ሞት ተፈርዶበታል። (2 ጢሞ. 1:15, 16፤ 4:6-8) ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ድፍረት በግልጽ መመልከት ችሎ ነበር፤ ምክንያቱም ጳውሎስ “ሁሉንም ነገር በጽናት ተቋቁሜ እኖራለሁ” ብሏል። (2 ጢሞ. 2:8-13) እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም የጳውሎስን አስደናቂ የጽናት ምሳሌ በመመልከት መበረታታት እንችላለን።

‘የተቀበልከውን ስጦታ እንደ እሳት አቀጣጥል’

ጢሞቴዎስ በአምላክ አገልግሎት የተሰጠውን ኃላፊነት እጅግ ከፍ አድርጎ እንዲመለከተው ጳውሎስ አበረታቶታል። “የተቀበልከውን የአምላክ ስጦታ እንደ እሳት እንድታቀጣጥል አሳስብሃለሁ” ብሎታል። (2 ጢሞ. 1:6 ግርጌ) እዚህ ላይ “ስጦታ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ካሪስማ የሚል ነው። ይህ ቃል፣ ተቀባዩ ይገባኛል ሊለው የማይችል ነፃ ስጦታን ያመለክታል፤ ስጦታው ለተቀባዩ የድካሙ ወይም የልፋቱ ዋጋ አይደለም። ጢሞቴዎስ ይህን ስጦታ የተቀበለው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለልዩ የአገልግሎት መብት በተመረጠበት ወቅት ነው።—1 ጢሞ. 4:14

ጢሞቴዎስ ይህን ስጦታ ሊጠቀምበት የሚገባው እንዴት ነው? ጢሞቴዎስ “እንደ እሳት እንድታቀጣጥል” የሚለውን አገላለጽ ሲያነብ፣ ሰዎች ቤት ለማሞቅ የሚጠቀሙበት እሳት ወደ አእምሮው መጥቶ ሊሆን ይችላል። እሳቱ እየደከመ ሲሄድ ፍሙ ብቻ ይቀራል፤ እሳቱ እንደገና እንዲቀጣጠልና ሙቀት እንዲሰጥ ፍሙ መቆስቆስ አለበት። አንድ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ግስ (አናዞፒሬኦ) “መቆስቆስ፣ አራግቦ ማቀጣጠል” የሚል ትርጉም አለው። በምሳሌያዊ ሁኔታ ሲሠራበት ደግሞ “እንደ አዲስ ለሥራ ማነሳሳት” የሚል መልእክት ያስተላልፋል። በአጭር አነጋገር፣ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘ኃላፊነትህን በቅንዓት ተወጣ!’ በማለት እየመከረው ነው። እኛም በተመሳሳይ አገልግሎታችንን በቅንዓት ማከናወን ያስፈልገናል።

“ይህን መልካም አደራ . . . ጠብቅ”

ጢሞቴዎስ፣ የሚወደው ወዳጁ የላከለትን ደብዳቤ ማንበቡን ሲቀጥል በአገልግሎቱ ስኬታማ ለመሆን ሊረዳው የሚችል ሌላ ሐሳብ አገኘ። ጳውሎስ “ይህን መልካም አደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጠብቅ” በማለት ጽፎለታል። (2 ጢሞ. 1:14) ይህ አደራ ምንድን ነው? ለጢሞቴዎስ በአደራ የተሰጠው ነገር ምንድን ነው? በቁጥር 13 ላይ ጳውሎስ ስለ ‘ትክክለኛው ትምህርት’ ማለትም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለሚገኘው እውነት ተናግሯል። (2 ጢሞ. 1:13) ጢሞቴዎስ ክርስቲያን አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን በጉባኤው ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች እውነትን ማስተማር ነበረበት። (2 ጢሞ. 4:1-5) በተጨማሪም ጢሞቴዎስ የአምላክን መንጋ እንዲጠብቅ ሽማግሌ ሆኖ ተሹሞ ነበር። (1 ጴጥ. 5:2) ጢሞቴዎስ የተሰጠውን አደራ ማለትም የሚያስተምረውን እውነት መጠበቅ የሚችለው በይሖዋ ቅዱስ መንፈስና በቃሉ በመታመን ነው።—2 ጢሞ. 3:14-17

እኛም ለሌሎች ሰዎች የምናስተምረው እውነት በአደራ ተሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20) ለዚህ ውድ አደራ ያለንን አድናቆት ይዘን መቀጠል የምንችለው በጸሎት በመጽናት እና የአምላክን ቃል የማጥናት ልማድ በማዳበር ነው። (ሮም 12:11, 12፤ 1 ጢሞ. 4:13, 15, 16) የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው የማገልገል ወይም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ተጨማሪ መብት ያገኙ ክርስቲያኖችም አሉ። እንዲህ ያለ አደራ ከተሰጠን ትሑት መሆንና ምንጊዜም የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን መገንዘብ ይኖርብናል። ስለዚህ የተሰጠንን አደራ መጠበቅ የምንችለው፣ አደራውን ከፍ አድርገን በመመልከትና አደራውን ለመወጣት የይሖዋን እርዳታ በመሻት ነው።

“ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ”

ለጢሞቴዎስ የተሰጠው ኃላፊነት፣ ይህን ሥራ ሌሎችም ማከናወን እንዲችሉ እነሱን ማሠልጠንን ይጨምር ነበር። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “ከእኔ የሰማኸውን . . . ነገር፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ” የሚል ምክር የሰጠው ለዚህ ነበር። (2 ጢሞ. 2:2) አዎ፣ ጢሞቴዎስ ከክርስቲያን ወንድሞቹ መማርና የተማረውን ለሌሎች ማስተማር ነበረበት። በዛሬው ጊዜ በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ የበላይ ተመልካቾችም ይህን ለማድረግ መጣራቸው አስፈላጊ ነው። ጥሩ የበላይ ተመልካች ስለ አንድ ሥራ ያለውን እውቀት ከሌሎች አይደብቅም። ከዚህ ይልቅ ሌሎችም ሥራውን ማከናወን እንዲችሉ ያስተምራቸዋል። የሚያስተምራቸው ሰዎች በእውቀት ወይም በችሎታ በልጠውት እንዳይገኙ አይሰጋም። ስለዚህ አንድ የበላይ ተመልካች ስለ አንድ ሥራ መሠረታዊ ነገሮችን ብቻ በማስተማር አይወሰንም። ከዚህ ይልቅ የሚያሠለጥናቸው ሰዎች የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲጠቀሙና በመንፈሳዊ እንዲጎለምሱ ይረዳቸዋል። እንዲህ ካደረገ እሱ ያስተማራቸው ‘ታማኝ የሆኑ ሰዎች’ ጉባኤውን ይበልጥ መጥቀም ይችላሉ።

ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ የላከለትን አበረታች ደብዳቤ እንደ ውድ ሀብት አድርጎ እንደተመለከተው ምንም ጥያቄ የለውም። ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ የሰጠውን ጠቃሚ ምክር በተደጋጋሚ እንዳነበበውና ኃላፊነቱን ሲወጣ ምክሩን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል እንዳሰላሰለበት መገመት እንችላለን።

እኛም የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንፈልጋለን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ስጦታችንን እንደ እሳት ለማቀጣጠል፣ የተሰጠንን አደራ ለመጠበቅ እንዲሁም እውቀታችንን እና ተሞክሯችንን ለሌሎች ለማካፈል ጥረት በማድረግ ነው። እንዲህ ካደረግን ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም” በማለት የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ማዋል እንችላለን።—2 ጢሞ. 4:5