በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ሰው መሆን ብቻ የወደፊት ሕይወትን አስተማማኝ ያደርጋል?

ጥሩ ሰው መሆን ብቻ የወደፊት ሕይወትን አስተማማኝ ያደርጋል?

ብዙ ሰዎች ጥሩና መልካም ሥነ ምግባር ያለው ሰው መሆን የወደፊት ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚረዳ ያምናሉ፤ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የዘለቀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሩቅ ምሥራቅ የሚኖሩ ሰዎች ፈላስፋና መምህር የሆነው ኮንፊሽየስ (551-479 ዓ.ዓ.) ለተናገረው “ሌሎች እንዲያደርጉባችሁ የማትፈልጉትን ነገር እናንተም አታድርጉባቸው” ለሚለው ሐሳብ ከፍተኛ አክብሮት አላቸው። *

ብዙዎች የሚከተሉት የሕይወት ጎዳና

በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ጥሩ ሥነ ምግባር ማሳየት የወደፊት ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ ይረዳል ብለው ያምናሉ። ሰው አክባሪና ጨዋ ለመሆን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚና በሚገባ ለመወጣትና ጥሩ ሕሊና ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ። ሊን የተባለች በቬትናም የምትኖር ሴት “ሐቀኛና ቅን ከሆንኩ የኋላ ኋላ እባረካለሁ ብዬ አምን ነበር” ብላለች።

አንዳንዶች መልካም ለማድረግ የሚነሳሱት በሃይማኖታቸው ምክንያት ነው። በታይዋን የሚኖር ሹ-ዩን የተባለ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ለዘላለም እንዲደሰት ወይም እንዲሠቃይ የሚያደርገው በሕይወት ሳለ የሠራው ሥራ እንደሆነ ተምሬያለሁ።”

ውጤቱ ምን ያሳያል?

ለሌሎች መልካም ማድረጋችን ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝልን አይካድም። ሆኖም ለሌሎች መልካም ለማድረግ ከልባቸው የሚጥሩ በርካታ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የጠበቁትን ውጤት እንደማያገኙ ተመልክተዋል። በሆንግ ኮንግ የምትኖር ሺዮ ፒንግ የተባለች ሴት “‘መልካም የሚያደርጉ ሰዎች በምላሹ ሁሌም ይባረካሉ’ የሚለው አባባል እውነት እንዳልሆነ በራሴ ሕይወት አይቻለሁ” ብላለች። አክላም እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ቤተሰቤን ለመንከባከብና ጥሩ ለማድረግ የቻልኩትን ሁሉ እጥር ነበር። ሆኖም ትዳሬ ፈረሰ፤ ባለቤቴ እኔንና ልጄን ትቶን ሄደ።”

ብዙዎች፣ ሃይማኖተኛ የሚባሉ ሰዎችም እንኳ መጥፎ ነገር እንደሚያደርጉ አስተውለዋል። ኤትስኮ የተባለች በጃፓን የምትኖር ሴት “አንድ የሃይማኖት ድርጅት ውስጥ ገብቼ የወጣቶችን እንቅስቃሴ እስከማደራጀት ደርሼ ነበር” ብላለች። አክላም “በዚያ ውስጥ ያለውን የሥነ ምግባር ዝቅጠትና የሥልጣን ሽኩቻ እንዲሁም ገንዘብ ለማጭበርበር የሚያደርጉትን ጥረት ሳይ በጣም ደነገጥኩ” በማለት ተናግራለች።

“ቤተሰቤን ለመንከባከብና ጥሩ ለማድረግ የቻልኩትን ሁሉ እጥር ነበር። ሆኖም ትዳሬ ፈረሰ፤ ባለቤቴ እኔንና ልጄን ትቶን ሄደ።”—ሺዮ ፒንግ፣ ሆንግ ኮንግ

አንዳንድ ሃይማኖተኛ ሰዎች መልካም ነገር ቢያደርጉም በምላሹ ምንም ጥሩ ነገር ባለማግኘታቸው ተስፋ ቆርጠዋል። በቬትናም የምትኖር ቫን የተባለች ሴት እንዲህ ተሰምቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “በየዕለቱ ፍራፍሬ፣ አበባና ምግብ ገዝቼ ለሞቱ ዘመዶቼ መሥዋዕት አቀርብ ነበር። እንዲህ ማድረጌ በረከት ያስገኝልኛል ብዬ አምን ነበር። ለበርካታ ዓመታት መልካም ሳደርግና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ስፈጽም የቆየሁ ቢሆንም ባለቤቴ በከባድ በሽታ ተያዘ። ከዚያም ሴት ልጄ ውጭ አገር ትምህርቷን እየተከታተለች ሳለ በለጋ ዕድሜዋ ሞተች።”

ጥሩ ሰው መሆን ብቻ ሕይወታችንን አስተማማኝ የማያደርግልን ከሆነ ሕይወታችንን አስተማማኝ ሊያደርግልን የሚችለው ምንድን ነው? መልሱን ለማወቅ አስተማማኝ መመሪያ ያስፈልገናል፤ መመሪያው ደግሞ ጥያቄዎቻችንን ሊመልስልንና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጠን የሚችል መሆን አለበት። እንዲህ ያለ መመሪያ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

^ አን.2 ኮንፊሽየስ ያስተማረው ትምህርት በሰዎች ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7፣ ከአንቀጽ 31-35 ተመልከት፤ መጽሐፉ www.pr418.com ላይ ይገኛል።