በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 1

አትረበሹ፣ በይሖዋ ታመኑ

አትረበሹ፣ በይሖዋ ታመኑ

የ2021 የዓመት ጥቅስ፦ “ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።”—ኢሳ. 30:15

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

ማስተዋወቂያ *

1. አንዳንዶቻችን እንደ ንጉሥ ዳዊት ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን?

ሁላችንም ምንም የሚረብሸን ነገር ሳይኖር በሰላም ብንኖር ደስ ይለናል። መጨነቅ የሚወድ ሰው የለም። ሆኖም በጭንቀት የምንዋጥባቸው ጊዜያት አሉ። እንዲያውም አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ንጉሥ ዳዊት የጠየቀው ዓይነት ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን “ልቤ በየዕለቱ በሐዘን እየተደቆሰ፣ በጭንቀት ተውጬ የምኖረው እስከ መቼ ነው?” ብሎት ነበር።—መዝ. 13:2

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 ምንም እንኳ ሙሉ በሙሉ ከጭንቀት ነፃ መሆን ባንችልም ጭንቀታችንን ለመቆጣጠር ማድረግ የምንችላቸው ነገሮች አሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ እንድንጨነቅ የሚያደርጉንን አንዳንድ ነገሮች በቅድሚያ እንመለከታለን። ከዚያም የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተረጋጋ መንፈስ ለመወጣት የሚረዱንን ስድስት ነገሮች እናያለን።

እንድንጨነቅ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

3. ምን የሚያስጨንቁ ነገሮች ያጋጥሙናል? እነዚህ ነገሮች እንዳያጋጥሙን ማድረግ እንችላለን?

3 እንድንጨነቅ የሚያደርጉን አንዳንዶቹ ነገሮች ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የምግብ፣ የልብስና የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳይወደድ ማድረግ አንችልም፤ ወይም ደግሞ አብረውን የሚሠሩ ወይም አብረውን የሚማሩ ሰዎች ሐቀኝነታችንን እንድናጎድል ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር እንድንፈጽም ይፈትኑን ይሆናል፤ የእነሱን ድርጊት መቆጣጠርም አንችልም። በተጨማሪም በአካባቢያችን ወንጀል እንዳይፈጸም ማድረግ አንችልም። እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚያጋጥሙን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች የማይከተሉ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ነው። የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን፣ “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት” አንዳንድ ሰዎችን ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንዲሉ እንደሚያደርጋቸው ያውቃል። (ማቴ. 13:22፤ 1 ዮሐ. 5:19) ከዚህ አንጻር ዓለማችን በሚያስጨንቁ ነገሮች የተሞላ መሆኑ አያስገርመንም።

4. ውጥረት ምን ሊያስከትልብን ይችላል?

4 አንዳንድ ጊዜ፣ የሚሰማን ከፍተኛ ውጥረት አስተሳሰባችንን ሊቆጣጠረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘የማገኘው ገቢ ቤተሰቤን ለማስተዳደር ባይበቃኝስ?’ ‘ብታመምና መሥራት ቢያቅተኝ ወይም ከሥራ ብቀነስስ?’ እያልን እንጨነቅ ይሆናል። ‘በፈተና ተሸንፌ የአምላክን ሕግ ብጥስስ?’ ብለንም እንሰጋ ይሆናል። በተጨማሪም በቅርቡ ሰይጣን በእሱ ቁጥጥር ያሉ ሰዎችን ተጠቅሞ በአምላክ ሕዝብ ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፤ ‘ይህ በሚሆንበት ወቅት ታማኝ እሆናለሁ?’ የሚለው ጉዳይም ሊያስጨንቀን ይችላል። ከዚህ አንጻር ‘እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች በተወሰነ መጠንም ቢሆን መጨነቅ ስህተት ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል።

5. ኢየሱስ “አትጨነቁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

5 ኢየሱስ ተከታዮቹን “አትጨነቁ” እንዳላቸው እናውቃለን። (ማቴ. 6:25) ታዲያ ይህ ሲባል ጨርሶ ጭንቀት የሚባል ነገር እንዳይሰማን ይጠብቅብናል ማለት ነው? እንዲህ ማለት አይደለም። ደግሞም አንዳንድ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በጭንቀት የተዋጡባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ሆኖም በዚህ ምክንያት ይሖዋ አላዘነባቸውም። * (1 ነገ. 19:4፤ መዝ. 6:3) በመሠረቱ ኢየሱስ “አትጨነቁ” ያለው እኛን ለማረጋጋት ነው። በኑሮ ጭንቀት ከመዋጣችን የተነሳ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት እንዲነካብን አይፈልግም። ታዲያ ጭንቀታችንን መቆጣጠር የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?—“ ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

እንዳንረበሽ የሚረዱን ስድስት ነገሮች

አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት *

6. በፊልጵስዩስ 4:6, 7 መሠረት ስንጨነቅ ምን ሊያረጋጋን ይችላል?

6 (1) አዘውትራችሁ ጸልዩ። የሚያስጨንቅ ነገር ያጋጠማቸው ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ በመጸለይ እፎይታ ሊያገኙ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 5:7) ይሖዋም ‘ከሰው የመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ በመስጠት ጸሎታቸውን ይመልስላቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።) ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል ባለው ቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የተጨነቀውን ልባችንን ያረጋጋልናል።—ገላ. 5:22

7. ወደ አምላክ ስንጸልይ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

7 ወደ ይሖዋ ስትጸልዩ የሚሰማችሁን ሁሉ ንገሩት። ችግራችሁን ለይታችሁ ጥቀሱ፤ ችግሩ የፈጠረባችሁን ስሜትም ግለጹለት። ችግሩ መፍትሔ እንዳለው ከተሰማችሁ መፍትሔውን ለማግኘት ጥበብ እንዲሰጣችሁ እንዲሁም መፍትሔውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ብርታት እንዲሰጣችሁ ለምኑት። ችግሩን መፍታት ከአቅማችሁ በላይ ከሆነ፣ ስለ ጉዳዩ ከልክ በላይ እንዳትጨነቁ እንዲረዳችሁ ይሖዋን ጠይቁት። በጸሎታችሁ ላይ የምትፈልጉትን ነገር ለይታችሁ የምትጠቅሱ ከሆነ ይሖዋ የሚሰጣችሁን መልስ ማየት ቀላል ይሆንላችኋል። ጸልያችሁ ቶሎ መልስ ሳታገኙ ብትቀሩ ተስፋ አትቁረጡ። ይሖዋ በጸሎታችሁ ላይ የምትፈልጉትን ነገር ለይታችሁ እንድትጠቅሱ ብቻ ሳይሆን ስለ ጉዳዩ ደጋግማችሁ እንድትጸልዩም ይፈልጋል።—ሉቃስ 11:8-10

8. በጸሎታችን ላይ ምን ማካተት ይኖርብናል?

8 ለይሖዋ በጸሎት የሚያስጨንቃችሁን ነገር ስትገልጹ እሱን ማመስገንም አትርሱ። አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለንበት ወቅትም እንኳ ይሖዋ ያደረገልንን ነገር መቁጠራችን ይጠቅመናል። አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመጨነቃችሁ የተነሳ ስሜታችሁን አውጥታችሁ መግለጽ ያቅታችሁ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ‘ይሖዋ፣ እባክህ እርዳኝ!’ ብላችሁ ብቻ እንኳ ብትጸልዩ መልስ እንደሚሰጣችሁ አትርሱ።—2 ዜና 18:31፤ ሮም 8:26

አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት *

9. እውነተኛ ደህንነት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

9 (2) በራሳችሁ ሳይሆን በይሖዋ ጥበብ ታመኑ። በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. የይሁዳ ነዋሪዎች አሦራውያን ጥቃት ይሰነዝሩብናል ብለው ሰግተው ነበር። በአሦራውያን ቀንበር ሥር ላለመውደቅ ሲሉ አረማዊ የሆነችውን የግብፅን እርዳታ ጠየቁ። (ኢሳ. 30:1, 2) ሆኖም ይሖዋ፣ ይህ አካሄዳቸው ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው አስጠንቅቋቸው ነበር። (ኢሳ. 30:7, 12, 13) ይሖዋ እውነተኛ ደህንነት ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ በኢሳይያስ በኩል ጠቆማቸው። “ሳትረበሹ፣ [በይሖዋ] ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ” አላቸው።—ኢሳ. 30:15ለ

10. በይሖዋ እንደምንታመን ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

10 በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። የተሻለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ እንድትቀበሉ ግብዣ ቀረበላችሁ እንበል፤ ሆኖም ይህ ሥራ ጊዜያችሁን የሚወስድባችሁ ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችሁን ያስተጓጉልባችኋል። ወይም ደግሞ በሥራ ቦታ አንድ የሥራ ባልደረባችሁ የፍቅር ስሜት እንደሚያሳያችሁ አስተዋላችሁ፤ ሆኖም ይህ ሰው የተጠመቀ የአምላክ አገልጋይ አይደለም። አሊያም የምትወዱት አንድ የቤተሰባችሁ አባል “ከእኔ ወይ ከአምላክህ አንዱን ምረጥ” አላችሁ። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ውሳኔ ማድረግ በጣም ከባድ ነው፤ ሆኖም ይሖዋ በእያንዳንዱ ሁኔታ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳችሁ መመሪያ ይሰጣችኋል። (ማቴ. 6:33፤ 10:37፤ 1 ቆሮ. 7:39) አሁን ጥያቄው፣ ‘በይሖዋ በመተማመን እሱ የሚሰጣችሁን መመሪያ ትታዘዛላችሁ?’ የሚለው ነው።

አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት *

11. ተቃውሞ ሲያጋጥመን እንዳንረበሽ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ማጥናት እንችላለን?

11 (3) ጥሩ ምሳሌ ከሆኑና መጥፎ ምሳሌ ከሆኑ ሰዎች ተማሩ። መጽሐፍ ቅዱስ አለመረበሽና በይሖዋ መታመን ያለውን አስፈላጊነት የሚያጎሉ ብዙ ታሪኮች ይዟል። እነዚህን ታሪኮች ስታጠኑ የአምላክ አገልጋዮች ከባድ ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው እንዳይረበሹ የረዳቸው ምን እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐዋርያቱን እንዳይሰብኩ አዟቸው ነበር፤ ሐዋርያቱ ግን በፍርሃት አልራዱም። ከዚህ ይልቅ በድፍረት “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት መልስ ሰጥተዋል። (ሥራ 5:29) ከተገረፉ በኋላም እንኳ ሐዋርያቱ አልተሸበሩም። ለምን? ይሖዋ ከጎናቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። በእነሱ እንደተደሰተ እርግጠኞች ነበሩ። በመሆኑም ምሥራቹን መስበካቸውን ቀጠሉ። (ሥራ 5:40-42) በተመሳሳይም ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ፣ ሊገደል በተወሰደበት ወቅት በጣም ከመረጋጋቱ የተነሳ ፊቱ “እንደ መልአክ ፊት ሆኖ” ታይቷቸው ነበር። (ሥራ 6:12-15) እንዲህ እንዲረጋጋ የረዳው ምንድን ነው? በይሖዋ ፊት ሞገስ እንዳገኘ እርግጠኛ መሆኑ ነው።

12. በ1 ጴጥሮስ 3:14 እና 4:14 መሠረት ስደት ቢደርስብንም እንኳ ደስተኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

12 ሐዋርያት ይሖዋ ከእነሱ ጋር እንደሆነ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ አግኝተዋል። ተአምራት እንዲፈጽሙ ኃይል ሰጥቷቸው ነበር። (ሥራ 5:12-16፤ 6:8) በእርግጥ፣ እኛ ተአምራት የመፈጸም ችሎታ የለንም። ያም ቢሆን ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ማረጋገጫ ሰጥቶናል፤ ለጽድቅ ስንል መከራ በሚደርስብን ወቅት በእኛ ደስ እንደሚሰኝና መንፈሱን እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል። (1 ጴጥሮስ 3:14፤ 4:14ን አንብብ።) እንግዲያው ‘ወደፊት ከባድ ስደት ቢደርስብኝ ታማኝነቴን አጎድል ይሆን?’ እያልን መጨነቅ አያስፈልገንም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እኛን ለመደገፍና ለማዳን ባለው ችሎታ ላይ ያለንን እምነት ከአሁኑ ማጠናከራችን የተሻለ ነው። ልክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ደቀ መዛሙርት እንዳደረጉት ኢየሱስ በገባው ቃል ላይ እምነት እንጣል፤ ኢየሱስ “ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። በተጨማሪም “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” የሚል ዋስትና ተሰጥቶናል። (ሉቃስ 21:12-19) እንዲሁም ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ ቢሞቱም እንኳ ስለ እነሱ እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ያስታውሳል። በመሆኑም ከሞት ሊያስነሳቸው ይችላል።

13. መጥፎ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ታሪክ መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳይረበሹ በይሖዋ ተማምነው መኖር ሲገባቸው እንዲህ ሳያደርጉ የቀሩ ሰዎች ምሳሌም ተጠቅሷል፤ የእነዚህን ሰዎች ታሪክ በመመርመርም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። የእነሱን ታሪክ ማጥናታችን የሠሩትን ስህተት እንዳንደግም ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው አሳ በአንድ ወቅት ታላቅ ሠራዊት ሊወረው መጥቶ ነበር፤ አሳ ግን በይሖዋ በመታመኑ ድል ማድረግ ችሏል። (2 ዜና 14:9-12) በኋላ ላይ የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ባኦስ ከዚያ በጣም ያነሰ ሠራዊት ይዞ ሊወረው መጣ፤ በዚህ ጊዜ ግን አሳ እንደ ቀድሞው የይሖዋን እርዳታ ከመለመን ይልቅ ብርና ወርቅ ልኮ የሶርያን ሠራዊት እርዳታ ጠየቀ። (2 ዜና 16:1-3) በሕይወቱ መገባደጃ ላይ በጠና በታመመበት ወቅትም አሳ የይሖዋን እርዳታ አልጠየቀም።—2 ዜና 16:12

14. አሳ ከሠራው ስህተት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

14 አሳ መጀመሪያ ላይ ችግር ሲያጋጥመው በይሖዋ ታምኖ ነበር። በኋላ ላይ ግን የይሖዋን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ ችግሩን በራሱ መንገድ ለመፍታት ሞከረ። መጀመሪያ ላይ ሲታይ፣ አሳ የእስራኤልን ሠራዊት ለመመከት የሶርያውያንን እርዳታ መጠየቁ የጥበብ አካሄድ ይመስል ይሆናል። ያገኘው ስኬት ግን ዘላቂ አልነበረም። ይሖዋ አንድ ነቢይ ልኮ “በአምላክህ በይሖዋ ከመታመን ይልቅ በሶርያ ንጉሥ ስለታመንክ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጧል” አለው። (2 ዜና 16:7) እንግዲያው ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሰጠውን መመሪያ ሳንፈልግ ችግሮቻችንን በራሳችን መፍታት እንችላለን ብለን እንዳናስብ እንጠንቀቅ። አፋጣኝ ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ቢያጋጥመን እንኳ ተረጋግተን የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል፤ እሱም እንዲሳካልን ይረዳናል።

አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት *

15. መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብብ ምን ማድረግ እንችላለን?

15 (4) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላችሁ ያዙ። መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብብ፣ ሳይረበሹ በይሖዋ ታምኖ መኖር ያለውን አስፈላጊነት የሚያጎላ ጥቅስ ካገኘህ ጥቅሱን በቃልህ ለመያዝ ጥረት አድርግ። የጥቅሱን ሐሳብ ጮክ ብሎ ማንበብ ወይም ጥቅሱን ከጻፍከው በኋላ አልፎ አልፎ መለስ ብሎ ማየት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ኢያሱ ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ከፈለገ የሕጉን መጽሐፍ አዘውትሮ በለሆሳስ ማንበብ እንዳለበት ተነግሮት ነበር። እንዲህ ማድረጉ በፍርሃት ከመሸነፍ ይልቅ የተሰጠውን ኃላፊነት በድፍረት እንዲወጣ ረድቶታል። (ኢያሱ 1:8, 9) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ጥቅሶች እንድትጨነቁ ወይም እንድትፈሩ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ አእምሯችሁና ልባችሁ እንዲረጋጋ ይረዷችኋል።—መዝ. 27:1-3፤ ምሳሌ 3:25, 26

አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት *

16. ይሖዋ እንድንረጋጋና በእሱ እንድንታመን ለመርዳት በጉባኤው የሚጠቀመው እንዴት ነው?

16 (5) ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ጊዜ አሳልፉ። ይሖዋ እንድንረጋጋና በእሱ እንድንታመን ለመርዳት በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ይጠቀማል። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ከመድረክ የሚተላለፈው ትምህርት፣ አድማጮች የሚሰጧቸው ሐሳቦች እንዲሁም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የምናደርጋቸው የሚያንጹ ጭውውቶች በጣም ይጠቅሙናል። (ዕብ. 10:24, 25) በጉባኤ ውስጥ ላሉ የምንቀርባቸው ወዳጆቻችን ስሜታችንን አውጥተን መናገራችንም በእጅጉ ሊያበረታታን ይችላል። ወዳጆቻችን የሚነግሩን “መልካም ቃል” ጭንቀታችን ቀለል እንዲልልን ሊያደርግ ይችላል።—ምሳሌ 12:25

አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት *

17. ዕብራውያን 6:19 እንደሚገልጸው የመንግሥቱ ተስፋ ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙን እንዳንናወጥ የሚረዳን እንዴት ነው?

17 (6) ተስፋችሁ እውን ሆኖ እንዲታያችሁ አድርጉ። የመንግሥቱ ተስፋ “ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ” ነው፤ ከባድ ችግሮች ወይም የሚያስጨንቁ ሐሳቦች ሲያጋጥሙን እንዳንናወጥ ይረዳናል። (ዕብራውያን 6:19ን አንብብ።) ወደፊት ይሖዋ የገባው ቃል በሚፈጸምበት ወቅት ስለሚኖረን ሕይወት አሰላስሉ፤ በዚያን ጊዜ ምንም ዓይነት መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯችን አይመጣም። (ኢሳ. 65:17) የሚያስጨንቁ ነገሮች በሌሉበት ሰላማዊ ዓለም ውስጥ ስትኖሩ ይታያችሁ። (ሚክ. 4:4) ተስፋችሁ እውን ሆኖ እንዲታያችሁ ማድረግ የምትችሉበት ሌላው መንገድ ደግሞ ስለ ተስፋችሁ ለሌሎች መናገር ነው። በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ አድርጉ። እንዲህ በማድረግ “ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ እስከ መጨረሻው መያዝ” ትችላላችሁ።—ዕብ. 6:11

18. ወደፊት ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚገጥሙን እንጠብቃለን? እነዚህን ሁኔታዎች መወጣት የምንችለውስ እንዴት ነው?

18 ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲሄድ ጭንቀት የሚፈጥሩ ተጨማሪ ችግሮች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ እንጠብቃለን። የ2021 የዓመት ጥቅስ፣ እነዚህ ችግሮች ሲያጋጥሙን እንዳንረበሽ እንዲሁም በራሳችን ብርታት ሳይሆን በይሖዋ እንድንታመን ይረዳናል። እንግዲያው በ2021 ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለን በተግባር እናሳይ፦ “ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።”ኢሳ. 30:15

መዝሙር 8 ይሖዋ መጠጊያችን ነው

^ አን.5 የ2021 የዓመት ጥቅሳችን፣ አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙንን አስጨናቂ ሁኔታዎች ለመቋቋም በይሖዋ መታመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። ይህ ርዕስ፣ በዓመት ጥቅሳችን ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸውን መንገዶች ያብራራል።

^ አን.5 አንዳንድ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ከልክ ባለፈ ጭንቀት ወይም ፍርሃት ይሠቃያሉ። እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከባድ የጤና እክል ነው፤ ኢየሱስ የተናገረው ስለ እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት አይደለም።

^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ (1) አንዲት እህት ስለሚያስጨንቋት ነገሮች በቀኑ ውስጥ በተለያየ ጊዜ አጥብቃ ስትጸልይ።

^ አን.65 የሥዕሉ መግለጫ፦ (2) ሥራ ቦታ በምሳ እረፍቷ ወቅት ጥበብ ለማግኘት የአምላክን ቃል ስታነብብ።

^ አን.67 የሥዕሉ መግለጫ፦ (3) ጥሩ ምሳሌና መጥፎ ምሳሌ ስለሆኑ ሰዎች በሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ስታሰላስል።

^ አን.69 የሥዕሉ መግለጫ፦ (4) በቃሏ ልትይዘው የምትፈልገውን የሚያበረታታ ጥቅስ ጽፋ ፍሪጇ ላይ ስትለጥፍ።

^ አን.71 የሥዕሉ መግለጫ፦ (5) በአገልግሎት ላይ ከሌሎች ጋር ጥሩ ጊዜ ስታሳልፍ።

^ አን.73 የሥዕሉ መግለጫ፦ (6) ስለ ወደፊቱ ጊዜ በማሰብ ተስፋዋ እውን ሆኖ እንዲታያት ለማድረግ ስትጥር።