በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 3

የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ አምላክንና ክርስቶስን ያወድሳሉ

የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ አምላክንና ክርስቶስን ያወድሳሉ

“መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው።”—ራእይ 7:10

መዝሙር 14 አዲሱን የምድር ንጉሥ አወድሱ

ማስተዋወቂያ *

1. በ1935 በተካሄደ ስብሰባ ላይ የቀረበ አንድ ንግግር በአንድ ወጣት ላይ ምን ለውጥ አስከትሏል?

ወጣቱ በ1926 ሲጠመቅ 18 ዓመቱ ነበር። ወላጆቹ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት መጠሪያ ነው) ነበሩ። ይህ ወጣት ሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች ነበሩት፤ ወላጆቻቸው፣ ይሖዋ አምላክን እንዲያገለግሉና ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመስሉ በመርዳት ጥሩ አድርገው አሳድገዋቸዋል። በዚያን ጊዜ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደሚያደርጉት ይህ ወጣትም በየዓመቱ የጌታ ራት ሲከበር ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ይካፈል ነበር። በኋላ ላይ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሚል ርዕስ ያለውን ታሪካዊ ንግግር ሲሰማ ግን ስለ ወደፊት ሕይወቱ ያለው አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ይህ ንግግር የቀረበው በ1935 በዋሽንግተን ዲሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሲሆን ንግግሩን ያቀረበው ወንድም ራዘርፎርድ ነው። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ ስብሰባ ላይ ምን ግንዛቤ አገኙ?

2. ወንድም ራዘርፎርድ በንግግሩ ላይ ምን አስደናቂ እውነት አብራርቷል?

2 ወንድም ራዘርፎርድ በራእይ 7:9 ላይ የተገለጹትን ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ማንነት በንግግሩ ላይ አብራራ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ እጅግ ብዙ ሕዝብ በቂ ታማኝነት ባለማሳየታቸው በሰማይ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ክርስቲያኖችን እንደሚያመለክት ይታሰብ ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ እጅግ ብዙ ሕዝብ ለሰማያዊ ሕይወት የተመረጡ ሰዎችን እንደማያመለክት ጥቅሶችን ተጠቅሞ አብራራ፤ ከዚህ ይልቅ “ታላቁን መከራ” በሕይወት አልፈው በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ የክርስቶስ ሌሎች በጎችን * እንደሚያመለክት ገለጸ። (ራእይ 7:14) ኢየሱስ “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል” ሲል ቃል ገብቷል። (ዮሐ. 10:16) እነዚህ በግ መሰል ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። (ማቴ. 25:31-33, 46) ይህ መንፈሳዊ የብርሃን ብልጭታ ቀደም ሲል ያነሳነውን የ18 ዓመት ወንድም ጨምሮ የብዙ የይሖዋ አገልጋዮችን አመለካከት እንዴት እንደቀየረ እስቲ እንመልከት።—መዝ. 97:11፤ ምሳሌ 4:18

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አመለካከት የቀየረ አዲስ ግንዛቤ

3-4. በ1935 በተካሄደው የክልል ስብሰባ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ስለ ተስፋቸው ምን ተገነዘቡ? እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱትስ ለምንድን ነው?

3 በስብሰባው ላይ ወንድም ራዘርፎርድ “በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላችሁ ሁሉ፣ እባካችሁ አንድ ጊዜ ብድግ በሉ” ሲል አንድ አስደሳች ነገር ተፈጸመ። አንድ የዓይን ምሥክር እንደገለጸው በዚህ ጊዜ 20,000 ገደማ ከሚሆኑት ተሰብሳቢዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ብድግ አሉ። ከዚያም ወንድም ራዘርፎርድ “እነሆ! እጅግ ብዙ ሕዝብ!” አለ። ይህን ተከትሎም ተሰብሳቢዎቹ በደስታ ጩኸታቸውን አቀለጡት። የቆሙት ሰዎች፣ ለሰማያዊ ሕይወት እንዳልተመረጡ ተገነዘቡ። ምክንያቱም በአምላክ መንፈስ እንዳልተቀቡ ተረድተው ነበር። በቀጣዩ ቀን 840 ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን ከእነዚህ አብዛኞቹ የሌሎች በጎች ክፍል ነበሩ።

4 ከዚህ ንግግር በኋላ፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ወጣትና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ክርስቲያኖች በጌታ ራት ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈላቸውን አቆሙ። አንድ ወንድም እንደሚከተለው በማለት በትሕትና የተናገረው ሐሳብ የብዙዎችን ስሜት ይገልጻል፤ እንዲህ ብሏል፦ “በ1935 ከተከበረው የመታሰቢያ በዓል ወዲህ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈሌን አቆምኩ። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለሰማያዊ ተስፋ እንዳልመረጠኝ ተገንዝቤ ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ተስፋዬ፣ በምድር ላይ ለዘላለም መኖርና ምድርን ወደ ገነትነት በመለወጡ ሥራ መካፈል እንደሆነ ገባኝ።” (ሮም 8:16, 17፤ 2 ቆሮ. 1:21, 22) ከዚያን ጊዜ ወዲህ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ከቅቡዓን ቀሪዎች * ጋር ተባብረው እየሠሩ ነው።

5. ይሖዋ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈላቸውን ያቆሙ ክርስቲያኖችን እንዴት ይመለከታቸዋል?

5 ከ1935 በኋላ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈላቸውን ያቆሙ ክርስቲያኖችን ይሖዋ እንዴት ይመለከታቸዋል? በዛሬው ጊዜስ በቅን ልቦና ተነሳስቶ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈል አንድ የይሖዋ ምሥክር በኋላ ላይ በመንፈስ እንዳልተቀባ ቢገነዘብስ? (1 ቆሮ. 11:28) አንዳንዶች ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ሲካፈሉ የነበሩት ተስፋቸውን በተመለከተ የተሳሳተ ግንዛቤ ስለነበራቸው ነው። ሆኖም በሐቀኝነት ስህተታቸውን አምነው ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈላቸውን ካቆሙና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ከቀጠሉ ይሖዋ የሌሎች በጎች ክፍል አድርጎ እንደሚቆጥራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ክርስቲያኖች ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈላቸውን ቢያቆሙም ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉላቸው ነገር ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ለማሳየት በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ።

አስደናቂ ተስፋ

6. ኢየሱስ ለመላእክቱ ምን ትእዛዝ ሰጥቷል?

6 ከፊታችን ታላቁ መከራ ይጠብቀናል፤ ከዚህ አንጻር ራእይ ምዕራፍ 7 ስለ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና የሌሎች በጎች ክፍል ስለሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ ምን እንደሚል መከለሳችን ያበረታታናል። በዚህ ራእይ ላይ ኢየሱስ፣ መላእክቱ አራቱን የጥፋት ነፋሳት አጥብቀው እንዲይዙ ትእዛዝ ሰጥቷል። ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች እስኪታተሙ ማለትም ከይሖዋ የመጨረሻ ማረጋገጫ እስኪሰጣቸው ድረስ መላእክቱ የጥፋት ነፋሳቱን በምድር ላይ እንዳይለቁ ተነግሯቸዋል። (ራእይ 7:1-4) የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በሰማይ ከእሱ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሲሆኑ፣ ላሳዩት ታማኝነት ወሮታ ያገኛሉ። (ራእይ 20:6) በሰማይ ያሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት በሙሉ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ።

እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘዋል፤ ግርማ በተላበሰው የአምላክ ዙፋንና በበጉ ፊት ቆመዋል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. በራእይ 7:9, 10 ላይ እንደተገለጸው ዮሐንስ እነማንን በራእይ ተመልክቷል? ምንስ እያደረጉ ነበር? (ሽፋኑን ተመልከት።)

7 ዮሐንስ፣ ነገሥታትና ካህናት ስለሚሆኑት 144,000 ሰዎች ከተናገረ በኋላ አንድ አስደናቂ ነገር ይኸውም አርማጌዶንን በሕይወት የሚያልፉትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተመለከተ። ይህ ቡድን፣ ዮሐንስ መጀመሪያ ካየው ቡድን በቁጥር በጣም ይበልጣል፤ ቁጥሩም የተገደበ አይደለም። (ራእይ 7:9, 10ን አንብብ።) የዚህ ቡድን አባላት “ነጭ ልብስ” ለብሰዋል፤ ይህም ‘ከሰይጣን ዓለም እድፍ ራሳቸውን እንደጠበቁ’ እንዲሁም ለአምላክና ለክርስቶስ ታማኝ ሆነው እንደኖሩ የሚጠቁም ነው። (ያዕ. 1:27) በታላቅ ድምፅ እየጮሁ፣ መዳን ያገኙት ይሖዋና የአምላክ በግ የሆነው ኢየሱስ ባደረጉላቸው ነገር የተነሳ እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም የዘንባባ ዝንጣፊዎች ይዘዋል፤ ይህም ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ንጉሥ እንደሆነ በደስታ መቀበላቸውን ያሳያል።—ከዮሐንስ 12:12, 13 ጋር አወዳድር።

8. ራእይ 7:11, 12 በሰማይ ስላሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ምን ይነግረናል?

8 ራእይ 7:11, 12ን አንብብ። በሰማይ ያሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት እጅግ ብዙ ሕዝብን ሲያዩ ምን ተሰማቸው? ዮሐንስ በራእይ እንደተመለከተው፣ በደስታ ተሞልተው አምላክን አወድሰዋል። በሰማይ ያሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት፣ ይህ ራእይ በሚፈጸምበት ወቅት ማለትም እጅግ ብዙ ሕዝብ ታላቁን መከራ በሕይወት ሲሻገሩ ሲያዩ በደስታ ይሞላሉ።

9. በራእይ 7:13-15 ላይ እንደተገለጸው የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረጉ ነው?

9 ራእይ 7:13-15ን አንብብ። ዮሐንስ፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ ልብሳቸውን “በበጉ ደም አጥበው ነጭ” እንዳደረጉት ገልጿል። ይህም ንጹሕ ሕሊናና በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዳላቸው ይጠቁማል። (ኢሳ. 1:18) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑና የተጠመቁ ክርስቲያኖች ናቸው፤ በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ጋር ዝምድና መሥርተዋል። (ዮሐ. 3:36፤ 1 ጴጥ. 3:21) በአምላክ ዙፋን ፊት ለመቆምና በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ላይ ሆነው ‘ቀንና ሌሊት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት’ ለማቅረብ ብቁ የሆኑት በዚህ የተነሳ ነው። በአሁኑ ጊዜ በሚከናወነው የመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ትልቁን ድርሻ እየተወጡ ያሉትም እነሱ ናቸው፤ እንዲህ በማድረግም ከራሳቸው ጥቅም ይበልጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ እንደሚሰጡ እያሳዩ ነው።—ማቴ. 6:33፤ 24:14፤ 28:19, 20

የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ ታላቁን መከራ አልፈው ሲመጡ፤ ሁሉም ደስተኞች ናቸው (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. እጅግ ብዙ ሕዝብ ምን ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል? የትኛው ተስፋ ሲፈጸምስ ይመለከታሉ?

10 እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ ታላቁን መከራ ካለፉ በኋላም ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል፤ ምክንያቱም ጥቅሱ “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል” ይላል። የሌሎች በጎች አባላት ለረጅም ጊዜ ሲጓጉለት የነበረው የሚከተለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:3, 4

11-12. (ሀ) በራእይ 7:16, 17 ላይ እንደተገለጸው እጅግ ብዙ ሕዝብ ምን በረከት ይጠብቃቸዋል? (ለ) የሌሎች በጎች አባላት በመታሰቢያው በዓል ወቅት ምን ያደርጋሉ? ለምንስ?

11 ራእይ 7:16, 17ን አንብብ። ከባድ የኢኮኖሚ ጫና ወይም አለመረጋጋትና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በረሃብ እየተጠቁ ነው። ሌሎች ደግሞ በእምነታቸው ምክንያት ታስረዋል። ያም ቢሆን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ ይህ ክፉ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ምንጊዜም የተትረፈረፈ ቁሳዊና መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያገኙ ስለሚያውቁ ደስተኞች ናቸው። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ የሰይጣን ሥርዓት በሚጠፋበት ወቅት ይሖዋ በብሔራት ላይ የሚያፈሰው እንደ ‘ሐሩር’ የሚያቃጥል ቁጣ አይነካቸውም። ታላቁ መከራ ካበቃ በኋላ ኢየሱስ ከጥፋቱ የተረፉትን እነዚህን ሰዎች “ወደ [ዘላለም] ሕይወት ውኃ” ይመራቸዋል። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ምን ዓይነት አስደሳች ተስፋ እንዳላቸው እስቲ አስበው። በምድር ላይ ከኖሩት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ሞትን የማይቀምሱት እነሱ ናቸው።—ዮሐ. 11:26

12 በእርግጥም የሌሎች በጎች አባላት ለይሖዋና ለኢየሱስ አመስጋኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሳ አስደናቂ ተስፋ አላቸው! በሰማይ እንዲኖሩ አልተመረጡም፤ ይህ ማለት ግን በይሖዋ ዘንድ ያላቸው ቦታ ወይም ዋጋ ያነሰ ነው ማለት አይደለም። የሁለቱም ቡድኖች አባላት አምላክንና ክርስቶስን ማወደስ ይችላሉ። እንዲህ የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ በጌታ ራት በዓል ላይ መገኘት ነው።

በመታሰቢያው በዓል ላይ በሙሉ ልባችሁ ውዳሴ አቅርቡ

በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚዞረው ቂጣና የወይን ጠጅ፣ ኢየሱስ ሕይወት እንድናገኝ ሲል የከፈለውን መሥዋዕት ያስታውሰናል (ከአንቀጽ 13-15⁠ን ተመልከት)

13-14. ሁላችንም በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ መገኘት ያለብን ለምንድን ነው?

13 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ሰዎች ብዛት፣ ከ1,000 ሰዎች 1 ቢሆን ነው። በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ውስጥ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈል ሰው የለም። በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚገኙት መካከል አብዛኞቹ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ናቸው። ታዲያ በጌታ ራት በዓል ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው? ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት፣ ሰዎች በወዳጃቸው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሚገኙበት ምክንያት ጋር ይመሳሰላል። ሰዎች በወዳጆቻቸው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚገኙት ጋብቻቸውን ለሚፈጽሙት ጥንዶች ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ እንዲሁም ከጎናቸው እንደሆኑ ለማሳየት ነው። በተመሳሳይም የሌሎች በጎች አባላት በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት ለክርስቶስና ለቅቡዓኑ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ እንዲሁም ከጎናቸው እንደሆኑ ለማሳየት ነው። የሌሎች በጎች አባላት በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ለተከፈለላቸው መሥዋዕት ያላቸውን አድናቆት ለማሳየት ነው፤ ምክንያቱም ይህ መሥዋዕት በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚችሉበትን አጋጣሚ እንደከፈተላቸው ያውቃሉ።

14 ከዚህም በተጨማሪ የሌሎች በጎች አባላት፣ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ ለማክበር ሲሉ በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ። ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የጌታ ራት በዓልን ባቋቋመበት ወቅት “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏቸው ነበር። (1 ቆሮ. 11:23-26) በመሆኑም ቅቡዓን ቀሪዎች በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ይህ በዓል መከበሩን ይቀጥላል፤ የሌሎች በጎች አባላትም በበዓሉ ላይ ይገኛሉ። እንዲያውም ሌሎች ሰዎችም አብረዋቸው በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ይጋብዛሉ።

15. በመታሰቢያው በዓል ላይ አምላክንና ክርስቶስን ማወደስ የምንችለው እንዴት ነው?

15 በመታሰቢያው በዓል ላይ ስንገኝ፣ አምላክንና ክርስቶስን በመዝሙርና በጸሎት የምናወድስበት አጋጣሚ እናገኛለን። በዚህ ዓመት በበዓሉ ላይ የሚቀርበው ንግግር “አምላክ እና ክርስቶስ ላደረጉላችሁ ነገር አድናቆት እንዳላችሁ አሳዩ!” የሚል ነው። ይህ ንግግር፣ ለይሖዋና ለክርስቶስ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ቂጣውና የወይን ጠጁ በሚዞሩበት ወቅት የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚወክሉት እነዚህ ነገሮች ስላላቸው ትርጉም ለማሰብ የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። ይሖዋ፣ እኛ ሕይወት እንድናገኝ ሲል ልጁ እንዲሞትልን በማድረግ ስለከፈለው መሥዋዕት እናስባለን። (ማቴ. 20:28) የሰማዩን አባታችንንና ልጁን የሚወድ ሰው ሁሉ በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛል።

ስለ ተስፋችሁ ይሖዋን አመስግኑት

16. ቅቡዓኑንና ሌሎች በጎችን የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?

16 በአምላክ ዘንድ ካላቸው ቦታ አንጻር በቅቡዓኑና በሌሎች በጎች መካከል ምንም ልዩነት የለም። ሁለቱም ቡድኖች በይሖዋ ዘንድ እኩል ዋጋ አላቸው። ደግሞም ይሖዋ፣ ቅቡዓኑንም ሆነ ሌሎች በጎችን ለመዋጀት የከፈለው የውድ ልጁን ሕይወት ነው። በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ተስፋቸው ነው። ሁለቱም ቡድኖች ለአምላክና ለክርስቶስ ታማኝ ሆነው መኖር ይጠበቅባቸዋል። (መዝ. 31:23) በተጨማሪም የአምላክ መንፈስ በሁላችንም ላይ በእኩል ደረጃ እንደሚሠራ አንዘንጋ። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠው እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስፈልገውን ነገር ግምት ውስጥ በማስገባት እንጂ ተስፋውን መሠረት በማድረግ አይደለም።

17. ቅቡዓን ቀሪዎች የትኛውን ጊዜ በጉጉት ይጠብቃሉ?

17 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ተስፋን ይዘው አይወለዱም። ይህን ተስፋ በውስጣቸው የሚያኖረው አምላክ ነው። ስለ ተስፋቸው ያስባሉ፣ ይጸልያሉ እንዲሁም ይህን ሽልማታቸውን በሰማይ የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ሰማይ ሲሄዱ ምን ዓይነት መንፈሳዊ አካል እንደሚኖራቸው የሚያውቁት ነገር የለም። (ፊልጵ. 3:20, 21፤ 1 ዮሐ. 3:2) ያም ቢሆን እዚያ ሄደው ይሖዋን፣ ኢየሱስን፣ መላእክትንና የቀሩትን ቅቡዓን የሚያገኙበትን ጊዜ ይናፍቃሉ። በሰማያዊው መንግሥት የተዘጋጀላቸውን ቦታ ለመቀበል ይጓጓሉ።

18. ሌሎች በጎች የትኛውን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ?

18 ሌሎች በጎች በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩበትን ጊዜ ይናፍቃሉ፤ ይህ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። (መክ. 3:11) መላዋን ምድር ገነት ለማድረግ በሚከናወነው ሥራ የሚካፈሉበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቃሉ። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ቤት የሚሠሩበትን፣ መሬት የሚያለሙበትንና ፍጹም ጤናማ የሆኑ ልጆች የሚያሳድጉበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። (ኢሳ. 65:21-23) በምድር ላይ እየተዘዋወሩ ተራራውን፣ ደኑንና ባሕሩን ለመጎብኘት እንዲሁም ስፍር ቁጥር ስለሌላቸው የይሖዋ ፍጥረታት ለማጥናት ይጓጓሉ። ስለ ተስፋቸው ሲያስቡ ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስታቸው ግን ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ማወቃቸው ነው።

19. የመታሰቢያው በዓል ለሁላችንም ምን አጋጣሚ ይሰጠናል? በዓሉ በዚህ ዓመት የሚከበረውስ መቼ ነው?

19 ይሖዋ ራሳቸውን ለወሰኑ አገልጋዮቹ በሙሉ አስደናቂ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (ኤር. 29:11) አምላክና ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ላደረጉልን ነገር አመስጋኝ ነን፤ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ፣ ሁላችንም አምላክንና ክርስቶስን በማወደስ አመስጋኝነታችንን የምንገልጽበት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። የመታሰቢያው በዓል፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስብሰባ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። በዓሉ የሚከበረው ቅዳሜ፣ መጋቢት 27, 2021 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። በዚህ ዓመት ብዙዎች በዓሉን የሚያከብሩት አንጻራዊ ነፃነት ባለባቸው አካባቢዎች ነው። ሌሎች ደግሞ በዓሉን የሚያከብሩት ተቃውሞ ባለባቸው አካባቢዎች ነው። አንዳንዶች በዓሉን የሚያከብሩት እስር ቤት ሆነው ነው። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ይህን በዓል ይሖዋ፣ ኢየሱስና በሰማይ ያሉት የአምላክ ቤተሰብ አባላት እንደሚከታተሉት እናስታውስ፤ እንግዲያው ሁሉም ጉባኤዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች በዓሉን አስደሳች በሆነ ሁኔታ እንዲያከብሩ ምኞታችን ነው!

መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

^ አን.5 መጋቢት 27, 2021 ለይሖዋ ምሥክሮች ልዩ ቀን ነው። በዚያን ዕለት ምሽት ላይ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ እናከብራለን። በበዓሉ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ብሎ የጠራው ቡድን ክፍል ናቸው። በ1935 የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ቡድን በተመለከተ ምን አስደናቂ እውነት ተገንዝበዋል? ሌሎች በጎች ከታላቁ መከራ በኋላ ምን አስደሳች ሕይወት ይጠብቃቸዋል? በተጨማሪም በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው አምላክንና ክርስቶስን ማወደስ የሚችሉት እንዴት ነው?

^ አን.2 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ሌሎች በጎች የተባለው ቡድን፣ በመጨረሻው ዘመን የተሰበሰቡ ክርስቲያኖችንም ያካትታል። እነዚህ ሰዎች ክርስቶስን የሚከተሉ ከመሆኑም ሌላ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። እጅግ ብዙ ሕዝብ ክርስቶስ በታላቁ መከራ ወቅት በሰው ዘር ላይ ሲፈርድ በሕይወት የሚኖሩ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ ክርስቲያኖች ናቸው፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ታላቁን መከራ በሕይወት ያልፋሉ።

^ አን.4 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “ቀሪዎች” የሚለው ቃል አሁንም በምድር ላይ ያሉትንና በጌታ ራት ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉትን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ያመለክታል።