የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ የጠየቀንን ሁሉ እሺ ማለትን ተምረናል
አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ከጣለ በኋላ ወንዙ ሞልቶ አፈሩንና ትላልቅ ድንጋዮችን እየጠራረገ ይሄድ ነበር። ወንዙን መሻገር ነበረብን፤ ሆኖም ሞልቶ የሚፈሰው ወንዝ ድልድዩን ይዞት ሄዷል። እኔ፣ ባለቤቴ ሃርቪ እና የአሚስ ቋንቋ አስተርጓሚያችን በጣም ከመፍራታችን የተነሳ የምናደርገው ጠፋን። ሆኖም ወንዙን ማቋረጥ ጀመርን፤ ወንድሞች ከወንዙ ማዶ ሆነው በጭንቀት ይመለከቱን ነበር። በመጀመሪያ መኪናችንን እየነዳን ተለቅ ያለ የጭነት መኪና ላይ ወጣን። መኪናችን በገመድ ወይም በሰንሰለት ሳትታሰር፣ የጭነት መኪናው ሞልቶ የሚፈሰውን ወንዝ ቀስ እያለ ማቋረጥ ጀመረ። ወንዙን አቋርጠን የምንጨርስበት ጊዜ ራቀብን፤ ብቻ ይሖዋን በጸሎት እየተማጸንን እንደምንም ብለን ተሻገርን። ይህ የሆነው በ1971 ነው። በወቅቱ በታይዋን ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ ነበርን፤ ይህ ቦታ የሚገኘው ከትውልድ አገራችን በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ነው። እስቲ ታሪካችንን ልንገራችሁ።
ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር
ሃርቪ በቤተሰቡ ውስጥ ካሉት አራት ወንዶች ልጆች የመጀመሪያው ነው። ቤተሰቡ እውነትን የሰማው በምዕራባዊ አውስትራሊያ በምትገኘው በሚድላንድ ጃንክሽን ሳለ ነው፤ እውነትን የሰሙት በ1930ዎቹ ዓመታት ከባድ የኢኮኖሚ ድቀት በተከሰተበት ወቅት ነው። ሃርቪ ለይሖዋ ያለው ፍቅር በ14 ዓመቱ እንዲጠመቅ አነሳሳው። ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች ሲሰጡት እሺ ብሎ መቀበል እንዳለበት የሚማርበት አጋጣሚ ያገኘው ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ነበር። በአንድ ወቅት በስብሰባ ላይ መጠበቂያ ግንብ እንዲያነብ ሲጠየቅ እንቢ ብሎ ነበር፤ እንዲህ ያለው ብቃት የለኝም ብሎ ስላሰበ ነው። ሃርቪን ያነጋገረው ወንድም ግን “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለ አንድ ሰው አንድ ነገር እንድታደርግ የሚጠይቅህ ብቁ እንደሆንክ ስለሚያምን ነው” በማለት አስረዳው።—2 ቆሮ. 3:5
እኔ፣ እናቴና ታላቅ እህቴ ደግሞ እውነትን የሰማነው እንግሊዝ ውስጥ ነው። አባቴ እውነትን የተቀበለው ቆይቶ ነው፤ መጀመሪያ ላይ ግን ይቃወመን ነበር። እሱ ባይስማማም ገና በዘጠኝ ዓመቴ ተጠመቅኩ። በመጀመሪያ አቅኚ ከዚያም ሚስዮናዊ ለመሆን ግብ አወጣሁ። አባቴ ግን 21 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ አቅኚ መሆን እንደማይፈቀድልኝ ነገረኝ። እኔ ደግሞ እስከዚያ የመቆየት ሐሳብ አልነበረኝም። ስለዚህ 16 ዓመት ሲሆነኝ አውስትራሊያ ወዳለችው ታላቅ እህቴ
ሄጄ ከእሷ ጋር እንድኖር ጠየቅኩት፤ እሱም ፈቀደልኝ። በመጨረሻ 18 ዓመት ሲሞላኝ አቅኚ ሆንኩ።አውስትራሊያ ሳለሁ ከሃርቪ ጋር ተዋወቅኩ። ሁለታችንም በሚስዮናዊነት ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት ነበረን። በ1951 ተጋባን። ለሁለት ዓመት በአቅኚነት ካገለገልን በኋላ በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጠየቅን። ወረዳችን የምዕራባዊ አውስትራሊያን ሰፊ ክልል የሚሸፍን ነበር፤ ስለዚህ ብዙ ጊዜ በመኪናችን በረሃማና ገለልተኛ የሆኑ አካባቢዎችን አቋርጠን መጓዝ ያስፈልገን ነበር።
ሕልማችን እውን ሆነ
በ1954 በጊልያድ ትምህርት ቤት 25ኛ ክፍል ላይ እንድንማር ተጋበዝን። ሚስዮናዊ የመሆን ሕልማችን እውን የሚሆንበት ጊዜ ደረሰ! መርከብ ተሳፍረን ኒው ዮርክ ሄድን፤ ከዚያም ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መማር ጀመርን። የጊልያድ ትምህርት ቤት መርሃ ግብር የስፓንኛ ቋንቋ ትምህርትንም ይጨምር ነበር፤ ሃርቪ ስፓንኛ መማር ከብዶት ነበር፤ በተለይ አንድ የስፓንኛ ፊደል የሚጠራበትን መንገድ ሊለምደው አልቻለም።
በኋላ ላይ አስተማሪዎቹ ጃፓን መመደብ የሚፈልግ ሰው ካለ የጃፓንኛ ቋንቋ ለመማር እንዲመዘገብ ማስታወቂያ ተናገሩ። እኛ ግን የይሖዋ ድርጅት ወደመደበን ወደ የትኛውም ቦታ እንሄዳለን ብለን ወስነን ስለነበር አልተመዘገብንም። ከዚያም ከጊልያድ አስተማሪዎቻችን አንዱ የሆነው አልበርት ሽሮደር እንዳልተመዘገብን አወቀ። እሱም “እስቲ እንደገና አስቡበት” አለን። አሁንም ማመንታታችንን ሲያይ ወንድም ሽሮደር እንዲህ አለን፦ “እኔና ሌሎቹ አስተማሪዎች አስመዝግበናችኋል። እስቲ ጃፓንኛውን ደግሞ ሞክሩት።” ሃርቪ ይህን ቋንቋ መማር ቀለለው።
በ1955 ወደ ጃፓን ሄድን፤ በወቅቱ በመላ አገሪቱ የነበሩት አስፋፊዎች 500 ብቻ ነበሩ። ሃርቪ 26 ዓመቱ እኔ ደግሞ 24 ዓመቴ ነበር። የወደብ ከተማ በሆነችው በኮቤ እንድናገለግል ተመደብን፤ በዚያም አራት ዓመት አገልግለናል። በኋላም እንደገና በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ስንጋበዝ በጣም ተደሰትን፤ የምናገለግለው በናጎያ ከተማ አቅራቢያ ነበር። ከአገልግሎት ምድባችን ጋር በተያያዘ ሁሉንም ነገር ወደነው ነበር፤ ወንድሞችን፣ ምግቡን፣ መልክዓ ምድሩን በጣም ወደድነው። ብዙም ሳይቆይ ግን ይሖዋ የሚጠይቀንን ሁሉ እሺ ብለን እንደምንቀበል የምናሳይበት ሌላ አጋጣሚ ተፈጠረ።
አዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ይዞ የመጣ አዲስ የአገልግሎት ምድብ
በወረዳ ሥራ ሦስት ዓመት ካገለገልን በኋላ የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ወደ ታይዋን ሄደን ከአሚስ ወንድሞች ጋር እንድናገለግል ጠየቀን። በዚያ ክህደት ተነስቶ ነበር፤ ስለዚህ የታይዋን ቅርንጫፍ ቢሮ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ጃፓንኛ * በጃፓን ያለውን አገልግሎታችንን ስለወደድነው ውሳኔ ማድረግ ከብዶን ነበር። ሃርቪ ግን የሚሰጠውን ማንኛውም ኃላፊነት እሺ ብሎ መቀበልን ስለተማረ ለመሄድ ተስማማን።
አጥርቶ የሚናገር ወንድም ይፈልግ ነበር።ኅዳር 1962 ታይዋን ደረስን። በወቅቱ በታይዋን ከነበሩት 2,271 አስፋፊዎች መካከል አብዛኞቹ የአሚስ ተወላጆች ነበሩ። መጀመሪያ ግን ቻይንኛ መማር ነበረብን። የነበረን አንድ ቻይንኛ መማሪያ መጽሐፍ ብቻ ነው፤ አስተማሪያችን ደግሞ እንግሊዝኛ አትችልም፤ ያም ቢሆን እንደምንም ብለን ቋንቋውን ተማርን።
ታይዋን ከሄድን ብዙም ሳይቆይ ሃርቪ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ እንዲሆን ተሾመ። ቅርንጫፍ ቢሮው ትንሽ ስለነበር ሃርቪ የቢሮ ሥራውንም እየሠራ በወር ውስጥ ለሦስት ሳምንት ያህል ከአሚስ ወንድሞች ጋር ያገለግል ነበር። አልፎ አልፎ ደግሞ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኖ በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ንግግር ይሰጥ ነበር። የአሚስ ወንድሞች ጃፓንኛም ስለሚችሉ ሃርቪ ንግግሮቹን በጃፓንኛ ቢሰጥ መረዳት አይከብዳቸውም ነበር። መንግሥት ግን ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች በቻይንኛ ብቻ እንዲካሄዱ ሕግ አውጥቶ ነበር። ስለዚህ ሃርቪ በተሰባበረ ቻይንኛ ንግግሮቹን ማቅረብ ነበረበት፤ አንድ ወንድም ደግሞ ያን ወደ አሚስ ያስተረጉምለታል።
ታይዋን በወቅቱ በወታደራዊ ሕግ ሥር ስለነበረች ወንድሞች የወረዳ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ፈቃድ ማግኘት ነበረባቸው። ፈቃድ ማግኘት ቀላል አልነበረም፤ ብዙውን ጊዜ ፖሊሶቹ ፈቃድ የማግኘቱን ሂደት ያጓትቱት ነበር። ፖሊሶቹ የወረዳ ስብሰባው የሚካሄድበት ሳምንት ደርሶም ፈቃድ ካልሰጡ ሃርቪ እስኪሰጡት ድረስ እዚያው ፖሊስ ጣቢያ ቁጭ ብሎ ይጠብቃቸዋል። ፖሊሶቹ አንድን የውጭ አገር ዜጋ ጣቢያው ውስጥ ቁጭ አድርጎ ማጉላላት ስለሚከብዳቸው ቶሎ ፈቃድ ይሰጡን ነበር፤ ይህ ዘዴ ብዙ ጊዜ ሠርቶልናል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ተራራ የወጣሁበት ዕለት
ከወንድሞች ጋር በምናሳልፋቸው ሳምንታት ብዙውን ጊዜ አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ በእግር መጓዝ ነበረብን፤ ይህ ደግሞ ተራራ መውጣትና ወንዞችን በእግር ማቋረጥ ይጠይቅ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ተራራ የወጣሁበትን ዕለት አልረሳውም። ቶሎ ቁርሳችንን ከበላን በኋላ ከሌሊቱ 11:30 ላይ አውቶቡስ ተሳፍረን ርቆ ወደሚገኝ መንደር ተጓዝን፤ ከዚያም አንድ ሰፊ ወንዝ ተሻገርንና ተራራውን መውጣት ጀመርን። ተራራው ቀጥ ያለ አቀበት ከመሆኑ የተነሳ ፊት ፊቴ የሚሄደው ወንድም እግር አፍንጫዬ ሥር ነበር ማለት ይቻላል።
ያን ዕለት ጠዋት፣ ሃርቪ በአካባቢው ካሉ አንዳንድ ወንድሞች ጋር አገልግሎት ወጣ፤ እኔ ደግሞ ጃፓንኛ የሚናገሩ ሰዎች በሚኖሩበት አንድ መንደር ውስጥ ብቻዬን አገለገልኩ። ቀትር ላይ ሰባት ሰዓት ገደማ ሲሆን ለሰዓታት ምግብ ስላልበላሁ ጠኔ ሊጥለኝ ደረሰ። መጨረሻ ላይ ከሃርቪ ጋር ስንገናኝ ወንድሞች በአካባቢው አልነበሩም። ሃርቪ የተወሰኑ መጽሔቶችን በሦስት ጥሬ እንቁላሎች ለውጦ ነበር። ከዚያም እንቁላሉን በሁለቱም ጫፍ በስቼ እንዴት መምጠጥ እንደምችል አሳየኝ። ምንም እንኳ ለመብላት የሚጋብዝ ባይሆንም ዝም ብዬ አንዱን ሞከርኩ። ሦስተኛው እንቁላል ግን ለማን ሊሆን ነው? ሃርቪ ሦስተኛውንም እንቁላል ለእኔ ሰጠኝ፤ ምክንያቱም ጠኔ ከጣለኝ እኔን ተሸክሞ ከተራራ ላይ ለመውረድ የሚያስችል አቅም እንዳለው አልተሰማውም።
ባልተለመደ ሁኔታ ገላዬን ታጠብኩ
በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ አንድ ያልጠበቅኩት ነገር አጋጠመኝ። ያረፍንበት ወንድም ቤቱ የሚገኘው ከስብሰባ አዳራሹ አጠገብ ነበር። ሰውነትን መታጠብ በአሚስ ተወላጆች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ስለሆነ የወረዳ የበላይ
ተመልካቹ ሚስት እንድንታጠብ ውኃ አዘጋጀችልን። ሃርቪ ሥራ በዝቶበት ስለነበር መጀመሪያ እኔ እንድታጠብ ጠየቀኝ። ገላችንን እንድንታጠብ ሦስት ዕቃዎችን አዘጋጅታልን ነበር፤ ቀዝቃዛ ውኃ የያዘ ባልዲ፣ ሙቅ ውኃ የያዘ ባልዲና ባዶ ሳፋ ተቀምጦልን ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሚስት ገላዬን እንድታጠብ ዕቃዎቹን ያስቀመጠችው ከስብሰባ አዳራሹ ፊት ለፊት እንደሆነ ሳውቅ ደነገጥኩ፤ ምክንያቱም የወረዳ ስብሰባውን ለማዘጋጀት ወዲያ ወዲህ የሚሉ ወንድሞች በግልጽ ሊያዩኝ ይችላሉ። ስለዚህ መከለያ የሚሆን ነገር እንድትሰጠኝ ጠየቅኳት። ያመጣችልኝ ግን እይታ የማይጋርድ ስስ ላስቲክ ነበር። ከዚያም ከቤቱ ጀርባ ሄጄ ከለል ብዬ ብታጠብስ ብዬ አሰብኩ፤ እዚያ ግን ውጭ ያሉ ዳክዬዎች አንገታቸውን በአጥሩ በኩል አሾልከው ወደዚያ የተጠጋውን ሰው ሁሉ ጠቅ ያደርጉ ነበር። ‘እንግዲህ መታጠቡ ይቅርብኝ ብል ቅር ሊላቸው ይችላል’ ብዬ አሰብኩ። ‘ወንድሞች በሥራ ስለተጠመዱ ልብም አይሉኝም፤ እዚሁ ብታጠብ ይሻላል!’ ብዬ ወሰንኩ። ስለዚህ እዚያው ታጠብኩ።በአሚስ ቋንቋ ጽሑፎች ማዘጋጀት
ሃርቪ፣ የአሚስ ወንድሞች በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንደከበዳቸው ተገነዘበ፤ ይህ የሆነው ብዙዎቹ ማንበብና መጻፍ ስለማይችሉ እንዲሁም በቋንቋቸው የተዘጋጀ ጽሑፍ ስላልነበረ ነው። በዚያው ጊዜ አካባቢ የአሚስ ቋንቋ በላቲን ፊደላት መጻፍ ጀምሮ ነበር፤ ስለዚህ ወንድሞች በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ እንዲችሉ ማስተማር ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተሰማን። ይህ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነገር ነበር፤ ውሎ አድሮ ግን ወንድሞች እውነትን በገዛ ቋንቋቸው ማጥናት ቻሉ። በ1966 ገደማ ጽሑፎቻችን በአሚስ ቋንቋ መዘጋጀት ጀመሩ፤ በ1968 ደግሞ የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም በአሚስ ቋንቋ ወጣ።
ሆኖም መንግሥት ከቻይንኛ ውጭ በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች እንዳይሰራጩ እገዳ ጥሎ ነበር። ስለዚህ ችግር ውስጥ ላለመግባት ሲባል ወደ አሚስ ቋንቋ የተተረጎመውን መጠበቂያ ግንብ በተለያዩ መንገዶች ማውጣት ጀመርን። ለምሳሌ ለተወሰነ ጊዜ ያህል መጠበቂያ ግንብ የቻይንኛና የአሚስ ቋንቋን አጣምሮ እንዲይዝ ተደርጎ ነበር። ሰዎች ጽሑፉን ሲያዩ ሕዝቡን ቻይንኛ ለማስተማር ጥረት እያደረግን እንዳለ ስለሚያስቡ ጥያቄ የሚፈጠርበት ሰው አይኖርም። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ድርጅት እነዚህ ቅን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ለመርዳት ብዙ ጽሑፎችን በአሚስ ቋንቋ አዘጋጅቷል።—ሥራ 10:34, 35
የማጥራት ጊዜ
በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ዓመታት የአምላክን መሥፈርቶች የማይከተሉ ብዙ የአሚስ ወንድሞች ነበሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሙሉ በሙሉ ስላልተረዱ
ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት የሚመሩ ነበሩ፤ አንዳንዶች ደግሞ ይሰክሩ ወይም ትንባሆና ቢትል ነት ይጠቀሙ ነበር። ሃርቪ ብዙ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ወንድሞች ይሖዋ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥረት አድርጓል። መግቢያው ላይ የጠቀስኩት ሁኔታ ያጋጠመን እንዲህ ባለው ጉብኝት ወቅት ነው።ትሑት ወንድሞች ማስተካከያዎቹን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኑ፤ የሚያሳዝነው ግን ብዙዎች እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም፤ በመሆኑም በታይዋን የነበረው የአስፋፊዎች ቁጥር በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ2,450 ወደ 900 ወረደ። ይህ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር! ያም ቢሆን ይሖዋ ንጹሕ ያልሆነን ድርጅት እንደማይባርክ ተገንዝበን ነበር። (2 ቆሮ. 7:1) በጊዜ ሂደት መጥፎ ልማዶችን ማጥራት ተቻለ፤ ደስ የሚለው፣ ይሖዋ ሥራውን ስለባረከው በአሁኑ ወቅት ታይዋን ውስጥ የአስፋፊዎች ቁጥር ከ11,000 በላይ ሆኗል።
ከ1980ዎቹ ዓመታት ወዲህ በአሚስ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉት ወንድሞች መንፈሳዊነት ተጠናክሯል፤ ይህም ሃርቪ፣ ቻይንኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ባሉበት ክልል ላይ የበለጠ ጊዜ እንዲያሳልፍ አጋጣሚ ሰጥቶታል። ብዙ የማያምኑ ባሎች እውነትን እንዲሰሙ መርዳት ችሏል፤ ይህም ደስታ አስገኝቶለታል። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ ሲሰማ ሃርቪ ምን ያህል እንደተደሰተ ትዝ ይለኛል። እኔም ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ የመርዳት መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። እንዲያውም በአንድ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናኋት እህት ልጆች ጋር ታይዋን ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አብሬ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።
ውዱን ባለቤቴን አጣሁ
የሚያሳዝነው በአሁኑ ወቅት ባለቤቴ በሕይወት የለም። ለ59 ዓመታት በትዳር አብረን ከኖርን በኋላ የምወደው ባለቤቴ ሃርቪ በካንሰር ሕመም የተነሳ ጥር 1, 2010 ሕይወቱ አለፈ። ሃርቪ ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፏል። ሃርቪ አሁንም በጣም ይናፍቀኛል። ያም ቢሆን በሁለት ለየት ያሉ አገሮች ውስጥ ሥራው በተጀመረበት ጊዜ አካባቢ አብሬው የማገልገል መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሁለት ከባድ የእስያ ቋንቋዎችን መናገር ችለናል፤ ሃርቪ ደግሞ እነዚህን ቋንቋዎች መናገር ብቻ ሳይሆን መጻፍም ይችል ነበር።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ የበላይ አካሉ ዕድሜዬ እየገፋ ስለሆነ ወደ አውስትራሊያ ብመለስ የተሻለ እንደሚሆን ወሰነ። መጀመሪያ ላይ ‘ታይዋንን ትቼ መሄድ አልፈልግም’ ብዬ አስቤ ነበር። ሆኖም የይሖዋ ድርጅት አንድ ነገር ሲጠይቀኝ ምንጊዜም እሺ ብዬ መቀበል እንዳለብኝ ከሃርቪ ተምሬያለሁ። ስለዚህ በውሳኔው ተስማማሁ፤ በኋላ ላይ ይህ ውሳኔ ያለውን ጥቅም ማስተዋል ችያለሁ።
በአሁኑ ወቅት ከሰኞ እስከ ዓርብ በአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አገለግላለሁ፤ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ በአካባቢው ካለ ጉባኤ ጋር አገለግላለሁ። ጃፓንኛና ቻይንኛ መማሬ በእነዚህ ቋንቋዎች ቤቴልን ለማስጎብኘት አስችሎኛል። ከምንም በላይ በጉጉት የምጠባበቀው፣ የትንሣኤ ተስፋ እውን የሚሆንበትን ጊዜ ነው፤ በዚያ ጊዜ ይሖዋ፣ እሱ የሚለውን ነገር ምንጊዜም እሺ የሚለውን ሃርቪን እንደሚያስታውሰውና እንደሚያስነሳው አውቃለሁ።—ዮሐ. 5:28, 29
^ አን.14 በአሁኑ ወቅት የታይዋን የሥራ ቋንቋ ቻይንኛ ቢሆንም በዚያ ጊዜ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የሥራ ቋንቋ ሆኖ የቆየው ጃፓንኛ ነው። በመሆኑም በወቅቱ በታይዋን ያሉ የተለያዩ ጎሣዎች ጃፓንኛም ይናገሩ ነበር።