በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 15

ከኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት ተማሩ

ከኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት ተማሩ

“በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት።”—ማቴ. 17:5

መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”

ማስተዋወቂያ *

1-2. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የመጨረሻዎቹን ቃላት የተናገረው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው?

ዕለቱ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ነው። ኢየሱስ በሐሰት ከተከሰሰ በኋላ ባልሠራው ወንጀል ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ተፈረደበት። ከዚያም ጠላቶቹ ተዘባበቱበት፤ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ አሠቃዩት፤ እንዲሁም በመከራ እንጨት ላይ ሰቀሉት። እጆቹና እግሮቹ በሚስማር ተቸንክረዋል። አንዲት ቃል መናገር፣ ሌላው ቀርቶ መተንፈስ እንኳ ከፍተኛ ሥቃይ ያስከትልበታል። ይሁንና ሊናገር የሚገባው በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ስላለ ከመናገር ወደኋላ አላለም።

2 ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ ሳለ የተናገራቸውን ቃላትና ከእነዚህ ቃላት የምናገኘውን ትምህርት እስቲ እንመልከት። በሌላ አባባል ኢየሱስን ‘እንስማው።’—ማቴ. 17:5

“አባት ሆይ፣ . . . ይቅር በላቸው”

3. ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ . . . ይቅር በላቸው” ሲል ስለ እነማን እየተናገረ ሊሆን ይችላል?

3 ኢየሱስ ምን ብሏል? ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ሲሰቀል “አባት ሆይ፣ . . . ይቅር በላቸው” በማለት ጸልዮአል። ኢየሱስ ይቅር እንዲባሉ የጸለየው ስለ እነማን ነው? ሙሉውን ሐሳብ ስናነበው መልሱን እናገኛለን፤ ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ብሏል። (ሉቃስ 23:33, 34) ኢየሱስ እየተናገረ ያለው እጆቹንና እግሮቹን በሚስማር ስለቸነከሩት ሮማውያን ወታደሮች ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በእርግጥ ማን እንደሆነ አላወቁም ነበር። ወይም ደግሞ ኢየሱስ፣ እንዲሰቀል ከጠየቀው ሕዝብ መካከል ያሉ አንዳንድ ሰዎችን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል፤ እነዚህ ሰዎች ከጊዜ በኋላ በእሱ አምነዋል። (ሥራ 2:36-38) ኢየሱስ ግፍ ቢደርስበትም በሁኔታው አልተማረረም፤ ቂምም አልያዘም። (1 ጴጥ. 2:23) ከዚህ ይልቅ ገዳዮቹን ይቅር እንዲላቸው ይሖዋን ጠይቋል።

4. ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑ ምን ያስተምረናል?

4 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። (ቆላ. 3:13) ቤተሰቦቻችንን ጨምሮ አንዳንዶች እምነታችንን እና ሕይወታችንን የምንመራበትን መንገድ መረዳት ስለሚከብዳቸው ሊቃወሙን ይችላሉ። ስለ እኛ ውሸት ይናገሩ፣ በሰዎች ፊት ያዋርዱን፣ ጽሑፎቻችንን ይቀዳድዱ አልፎ ተርፎም አካላዊ ጥቃት እንደሚሰነዝሩብን ይዝቱ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ቂም ከመያዝ ይልቅ ይሖዋ የሚቃወሙንን ሰዎች ዓይናቸውን እንዲከፍትላቸውና እውነትን ለመቀበል እንዲረዳቸው መጸለይ እንችላለን። (ማቴ. 5:44, 45) እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ይቅር ማለት ቀላል ላይሆን ይችላል፤ በተለይ ደግሞ ከባድ በደል ተፈጽሞብን ከሆነ እንዲህ ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ይሁንና ቂምና ምሬት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ከፈቀድን የምንጎዳው እኛው ነን። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይቅር ባይ መሆን ሲባል የተፈጸመብንን በደል ችላ ብለን እናልፈዋለን ወይም ደግሞ ሌሎች መጠቀሚያ ሲያደርጉን ዝም ብለን እንመለከታለን ማለት እንዳልሆነ አውቃለሁ። ከዚህ ይልቅ በበደለን ሰው ላይ ቂም አንይዝም ማለት ነው።” (መዝ. 37:8) ይቅር ለማለት ስንወስን በደረሰብን በደል ምክንያት በምሬት ላለመዋጥ መርጠናል ማለት ነው።—ኤፌ. 4:31, 32

“ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”

5. ኢየሱስ አጠገቡ ለተሰቀለው ወንጀለኛ ምን ቃል ገብቶለታል? ይህን ቃል የገባለትስ ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ምን ብሏል? ከኢየሱስ ግራ እና ቀኝ የተሰቀሉ ሁለት ወንጀለኞች ነበሩ። መጀመሪያ ላይ ሁለቱም ይነቅፉት ነበር። (ማቴ. 27:44) በኋላ ግን አንደኛው አመለካከቱን ለወጠ። ወንጀለኛው፣ ኢየሱስ “ምንም የሠራው ጥፋት” እንደሌለ ተገነዘበ። (ሉቃስ 23:40, 41) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳና አንድ ቀን ንጉሥ ሆኖ እንደሚገዛ ያለውን እምነት ገለጸ። በሞት አፋፍ ላይ ላለው አዳኝ “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” አለው። (ሉቃስ 23:42) ይህ ሰው ያሳየው እምነት እንዴት አስደናቂ ነው! ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።” (ሉቃስ 23:43) * ኢየሱስ “እልሃለሁ፣” “እኔ፣” እና “ትሆናለህ” የሚሉትን ቃላት መጠቀሙ ለወንጀለኛው በግለሰብ ደረጃ ቃል እንደገባለት ያሳያል። ኢየሱስ አባቱ መሐሪ መሆኑን ስላወቀ በሞት አፋፍ ላይ ላለው ለዚህ ወንጀለኛ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነግሮታል።—መዝ. 103:8

6. ኢየሱስ ለወንጀለኛው ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን?

6 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነው። (ዕብ. 1:3) ቀደም ሲል ለፈጸምነው ኃጢአት ከልብ ንስሐ ከገባንና በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ እንደምናገኝ እምነት ካለን ይሖዋ ይቅር ሊለንና ምሕረት ሊያሳየን ፈቃደኛ ነው። (1 ዮሐ. 1:7) አንዳንዶች ቀደም ሲል ለፈጸሙት ኃጢአት ይሖዋ ጨርሶ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ይሰማቸው ይሆናል። አንተም አልፎ አልፎ እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ እስቲ ይህን ለማሰብ ሞክር፦ ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ አብሮት ለተሰቀለው ወንጀለኛ ምሕረት አሳይቶታል። እምነቱን በተግባር ለማሳየት አጋጣሚ ያላገኘው ይህ ወንጀለኛ ምሕረት ከተደረገለት፣ ይሖዋ ትእዛዛቱን ለመከተል ከፍተኛ ጥረት ለሚያደርጉ ታማኝ አገልጋዮቹማ ምሕረት እንደሚያደርግላቸው ምንም ጥያቄ የለውም!—መዝ. 51:1፤ 1 ዮሐ. 2:1, 2

“ልጅሽ ይኸውልሽ! . . . እናትህ ይህችውልህ!”

7. በዮሐንስ 19:26, 27 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ኢየሱስ ማርያምንና ዮሐንስን ምን አላቸው? ይህን ያለው ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ምን ብሏል? (ዮሐንስ 19:26, 27ን አንብብ።) ኢየሱስ የእናቱ ጉዳይ በጣም አሳስቦት ነበር፤ በወቅቱ ማርያም መበለት ሳትሆን አትቀርም። ሌሎቹ ልጆቿ የሚያስፈልጋትን ቁሳዊ ነገር ሊያሟሉላት ይችሉ ይሆናል። ሆኖም መንፈሳዊ ፍላጎቷንስ ማን ያሟላላታል? በዚህ ወቅት የኢየሱስ ወንድሞች ደቀ መዛሙርቱ እንደሆኑ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። ዮሐንስ ግን የኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያና የቅርብ ወዳጅ ነበር። ኢየሱስ አብረውት ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎችን መንፈሳዊ ቤተሰቡ እንደሆኑ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ማቴ. 12:46-50) በመሆኑም ኢየሱስ ለማርያም ባለው ፍቅርና አሳቢነት ተነሳስቶ ለዮሐንስ በአደራ ሰጣት፤ የሚያስፈልጋትን መንፈሳዊ ነገር በሙሉ ዮሐንስ እንደሚያሟላላት ተማምኖ ነበር። እናቱን “ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። ዮሐንስን ደግሞ “እናትህ ይህችውልህ!” አለው። ከዚያ ቀን ጀምሮ ዮሐንስ ማርያምን ወደ ቤቱ ወስዶ እንደ እናቱ አድርጎ ተንከባክቧታል። ኢየሱስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ለተንከባከበችውና ሲሞትም ከጎኑ ላልተለየችው ውድ እናቱ ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል!

8. ኢየሱስ ለማርያም እና ለዮሐንስ ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን?

8 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? ከክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለን ዝምድና ከቅርብ ቤተሰባችን ጋር ካለን ዝምድና የጠነከረ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ቤተሰቦቻችን ይቃወሙን ይባስ ብሎም ያገሉን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ይሖዋን እና ድርጅቱን የሙጥኝ እስካልን ድረስ ያጣነውን ነገር ሁሉ “100 እጥፍ” እናገኛለን። አፍቃሪ የሆኑ ብዙ ልጆች፣ እናቶች ወይም አባቶች እናገኛለን። (ማር. 10:29, 30) ለይሖዋና እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር እንዲሁም በእምነት የተሳሰሩ አባላት ያሉት መንፈሳዊ ቤተሰብ ክፍል በመሆንህ ምን ይሰማሃል?—ቆላ. 3:14፤ 1 ጴጥ. 2:17

“አምላኬ ለምን ተውከኝ?”

9. በማቴዎስ 27:46 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ምን ያስገነዝቡናል?

9 ኢየሱስ ምን ብሏል? ኢየሱስ ልክ ከመሞቱ በፊት “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” በማለት ጮዃል። (ማቴ. 27:46) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እንዲህ ያለው ለምን እንደሆነ አይገልጽልንም። ሆኖም እነዚህ ቃላት ምን እንደሚያስገነዝቡን እንመልከት። አንደኛ ነገር፣ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት መናገሩ በመዝሙር 22:1 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። * ከዚህም ሌላ እነዚህ ቃላት ይሖዋ በልጁ ዙሪያ ‘የአጥር ከለላ’ እንዳላደረገ ያሳዩናል። (ኢዮብ 1:10) ኢየሱስ ጠላቶቹ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲፈትኑት አባቱ መፍቀዱን ያውቅ ነበር፤ ማንም ሰው የዚህን ያህል ተፈትኖ አያውቅም። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ለሞት የሚያበቃ ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልፈጸመ ያረጋግጣሉ።

10. ኢየሱስ ለአባቱ ከተናገራቸው ቃላት ምን እንማራለን?

10 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ከእምነት ፈተናዎች ከለላ እንዲያደርግልን መጠበቅ እንደሌለብን እንማራለን። ኢየሱስ እስከ መጨረሻ ድረስ እንደተፈተነ ሁሉ እኛም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታችንን ለማስመሥከር ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። (ማቴ. 16:24, 25) ይሁን እንጂ አምላክ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ቆሮ. 10:13) ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ ሌላስ ምን እንማራለን? እንደ ኢየሱስ ግፍ ሊደርስብን ይችላል። (1 ጴጥ. 2:19, 20) ተቃዋሚዎቻችን ስደት የሚያደርሱብን የዓለም ክፍል ባለመሆናችን እና ስለ እውነት በመመሥከራችን ነው እንጂ የሠራነው ጥፋት ስላለ አይደለም። (ዮሐ. 17:14፤ 1 ጴጥ. 4:15, 16) ኢየሱስ፣ መከራ እንዲደርስበት ይሖዋ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ያውቅ ነበር። በአንጻሩ ግን መከራ የደረሰባቸው አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች፣ ይሖዋ መከራ እንዲደርስባቸው የፈቀደው ለምን እንደሆነ ግልጽ አልሆነላቸውም። (ዕን. 1:3) መሐሪና ታጋሽ የሆነው አምላካችን እነዚህ አገልጋዮቹ እንዲህ የተሰማቸው እምነት በማጣታቸው እንዳልሆነ ያውቃል፤ እነዚህ የይሖዋ ሕዝቦች እሱ ብቻ ሊሰጣቸው የሚችለው ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል።—2 ቆሮ. 1:3, 4

“ተጠማሁ”

11. ኢየሱስ በዮሐንስ 19:28 ላይ የሚገኙትን ቃላት የተናገረው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ምን ብሏል? (ዮሐንስ 19:28ን አንብብ።) ኢየሱስ “ተጠማሁ” ያለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ያለው “የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም” ይኸውም በመዝሙር 22:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ነው፤ ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፤ ምላሴ ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ።” በተጨማሪም ኢየሱስ ብዙ መከራ ደርሶበታል፤ አሁንም በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እየተሠቃየ ነው፤ ስለዚህ በጣም ተጠምቶ መሆን አለበት። ጥሙን ለማርካት እርዳታ ያስፈልገው ነበር።

12. ኢየሱስ “ተጠማሁ” ማለቱ ምን ያስተምረናል?

12 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስ፣ ስሜቱን መናገር የድክመት ምልክት እንደሆነ አልተሰማውም፤ እኛም እንደዚህ ሊሰማን አይገባም። አንዳንዶቻችን የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ ይከብደን ይሆናል። ሆኖም የሌሎች እገዛ የሚያስፈልገን ከሆነ እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለብንም። ለምሳሌ ዕድሜያችን ከገፋ ወይም የአቅም ገደብ ካለብን፣ ገበያ አሊያም ሐኪም ቤት ለመሄድ የወዳጆቻችንን እርዳታ መጠየቅ ሊያስፈልገን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ስሜታችን ከተደቆሰ ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከተሰማን ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ክርስቲያን ስሜታችንን አውጥተን ልንነግረው እንችላለን። በተጨማሪም የሚያበረታታ “መልካም ቃል” እንዲያካፍለን ልንጠይቀው እንችላለን። (ምሳሌ 12:25) ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይወዱናል፤ እንዲሁም ‘በመከራ ቀን’ ሊረዱን ይፈልጋሉ። (ምሳሌ 17:17) ይሁንና በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ማንበብ አይችሉም። እኛ ራሳችን እስካልነገርናቸው ድረስ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ላያውቁ ይችላሉ።

“ተፈጸመ”

13. ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ ምን እንዲፈጸም አድርጓል?

13 ኢየሱስ ምን ብሏል? ኒሳን 14 ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ላይ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “ተፈጸመ” አለ። (ዮሐ. 19:30) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ይሖዋ የሚጠብቅበትን ነገር ሁሉ አከናውኗል። ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ብዙ ነገሮችን ፈጽሟል። አንደኛ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ፣ አንድ ፍጹም ሰው ሰይጣን ምንም ዓይነት መከራ ቢያደርስበት ንጹሕ አቋሙን ሙሉ በሙሉ መጠበቅ እንደሚችል አሳይቷል። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። የእሱ መሥዋዕታዊ ሞት ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በአምላክ ፊት እንደ ጻድቅ እንዲቆጠሩ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ አስገኝቶላቸዋል። ሦስተኛ፣ ኢየሱስ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል፤ እንዲሁም የአባቱ ስም ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን አድርጓል።

14. እያንዳንዱን ቀን እንዴት ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል? አብራራ።

14 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? በየቀኑ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አስተማሪ የነበረው ወንድም ማክስዌል ፍሬንድ የተናገረውን እንመልከት፤ ወንድም ፍሬንድ በአንድ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ስለ ታማኝነት ንግግር ሲያቀርብ እንዲህ ብሏል፦ “ዛሬ ልትናገሩ ወይም ልታደርጉ የምትችሉትን ነገር ለነገ አታሳድሩት። ነገ በሕይወት መኖራችሁን እንዴት እርግጠኛ ልትሆኑ ትችላላችሁ? እያንዳንዱን ቀን፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቁ መሆናችሁን ለማሳየት የሚያስችል የመጨረሻ አጋጣሚ አድርጋችሁ ተመልከቱት።” እኛም እያንዳንዱን ቀን፣ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ እንደሚያስችል የመጨረሻ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው ይገባል! እንዲህ ካደረግን ከሞት ጋር ብንፋጠጥ እንኳ “ይሖዋ ሆይ፣ ንጹሕ አቋሜን ለመጠበቅ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲሁም ስምህን ለማስቀደስና ሉዓላዊነትህን ለመደገፍ የቻልኩትን ሁሉ አድርጌያለሁ!” ማለት እንችላለን።

“መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ”

15. ሉቃስ 23:46 እንደሚያሳየው ኢየሱስ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

15 ኢየሱስ ምን ብሏል? (ሉቃስ 23:46ን አንብብ።) ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት በልበ ሙሉነት ተናግሯል። ኢየሱስ የወደፊት ሕይወቱ የተመካው በይሖዋ ላይ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር፤ አባቱ እንደሚያስታውሰውም እርግጠኛ ነበር።

16. የጆሹዋ ተሞክሮ ምን ያስተምረናል?

16 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? ሕይወታችሁን በይሖዋ እጅ አደራ ለመስጠት ፈቃደኞች ሁኑ። እንዲህ ለማድረግ ‘በሙሉ ልባችሁ በይሖዋ መታመን’ ያስፈልጋችኋል። (ምሳሌ 3:5) የ15 ዓመት ወጣት የሆነውን ጆሹዋ የተባለ ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጆሹዋ በማይድን በሽታ ተይዞ ነበር። ይህ ወጣት የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ሕክምና ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። ከመሞቱ በፊት እናቱን እንዲህ ብሏት ነበር፦ “እማዬ አሁን በይሖዋ እጅ ነኝ። . . . ይሖዋ በትንሣኤ እንደሚያስነሳኝ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ። እሱ በልቤ ውስጥ ያለውን ያውቃል፤ ከልቤ እወደዋለሁ።” * እያንዳንዳችን እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘ሕይወቴን አደጋ ላይ የሚጥል የእምነት ፈተና ቢያጋጥመኝ ይሖዋ እንደሚያስታውሰኝ በመተማመን ሕይወቴን በእጁ አደራ እሰጣለሁ?’

17-18. ምን ትምህርቶች አግኝተናል? (“ ከኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት የምናገኘው ትምህርት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

17 ከኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት በጣም ግሩም ትምህርቶች አግኝተናል! ሌሎችን ይቅር ማለት አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም ይሖዋ ይቅር እንደሚለን መተማመን እንዳለብን ተምረናል። እኛን ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ አፍቃሪ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ግሩም መንፈሳዊ ቤተሰብ በማግኘታችን ታድለናል። ይሁንና እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ እንዲረዱን ልንጠይቃቸው ይገባል። ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመወጣት እንደሚረዳን እናውቃለን። በተጨማሪም እያንዳንዱን ቀን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የምንችልበት የመጨረሻ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው እንደሚገባ ተምረናል፤ እንዲሁም ሕይወታችንን በይሖዋ እጅ አደራ እንሰጣለን።

18 በእርግጥም ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ ሳለ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት ብዙ ትምህርት ይዘውልናል! ያገኘናቸውን ትምህርቶች በሥራ ላይ ስናውል ይሖዋ እንዳዘዘን ‘ልጁን እንሰማዋለን።’—ማቴ. 17:5

መዝሙር 126 ነቅተህ ኑር፣ ጸንተህ ቁም፣ በርታ

^ አን.5 ማቴዎስ 17:5 እንደሚገልጸው ይሖዋ ልጁን እንድንሰማው ይፈልጋል። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ ሳለ ከተናገራቸው ቃላት የምናገኛቸውን የተለያዩ ትምህርቶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።

^ አን.5 ኢየሱስ፣ ወንጀለኛው ወደ ሰማይ ሄዶ በመንግሥቱ አብሮት እንደሚሆን አልተናገረም፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ተነስቶ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ይኖራል።

^ አን.9 ኢየሱስ በመዝሙር 22:1 ላይ ያለውን ሐሳብ የተናገረው ለምን ሊሆን እንደሚችል ማብራሪያ ለማግኘት በዚህ እትም ላይ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

^ አን.16 በጥር 22, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የሚገኘውን “የጆሹዋ እምነት—ከልጆች መብት ጋር በተያያዘ የተገኘ ድል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።