በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 20

ለአገልግሎታችሁ አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ

ለአገልግሎታችሁ አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ

“ዘርህን ዝራ፤ . . . እጅህ ሥራ አይፍታ።”—መክ. 11:6

መዝሙር 70 የሚገባቸውን ሰዎች ፈልጉ

ማስተዋወቂያ *

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሩሳሌምና በሌሎች ቦታዎች በቅንዓት ሰብከዋል (አንቀጽ 1⁠ን ተመልከት)

1. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ምሳሌ ትቶላቸዋል? እነሱስ ምሳሌውን የተከተሉት እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ አዎንታዊ አመለካከት ነበረው፤ ተከታዮቹም ለአገልግሎት አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። (ዮሐ. 4:35, 36) ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ጋር በነበሩበት ወቅት የስብከቱን ሥራ በቅንዓት አከናውነዋል። (ሉቃስ 10:1, 5-11, 17) ኢየሱስ ከተያዘና ከተገደለ በኋላ ግን ደቀ መዛሙርቱ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የአገልግሎት ቅንዓታቸው ቀዝቅዞ ነበር። (ዮሐ. 16:32) ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አበረታታቸው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በከፍተኛ ቅንዓት ከመስበካቸው የተነሳ ጠላቶቻቸው “ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል” ብለዋቸው ነበር።—ሥራ 5:28

2. ይሖዋ የስብከቱን ሥራ የባረከው እንዴት ነው?

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን ሥራ የሚመራው ኢየሱስ ነበር፤ ይሖዋም እድገት እንዲያደርጉ በመርዳት ባርኳቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ በዓል በተከበረበት ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጠምቀዋል። (ሥራ 2:41) የደቀ መዛሙርቱም ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ማደጉን ቀጠለ። (ሥራ 6:7) ያም ቢሆን ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ በመጨረሻዎቹ ቀናት ይበልጥ ፍሬያማ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል።—ዮሐ. 14:12፤ ሥራ 1:8

3-4. አንዳንዶች የስብከቱ ሥራ ተፈታታኝ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ሁላችንም ለአገልግሎታችን አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናደርጋለን። በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ለአገልግሎት አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ቀላል ነው። ለምን? ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ አንዳንዶቹ የሚያስጠናቸው የይሖዋ ምሥክር እስከሚገኝ ድረስ ተመዝግበው መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል! በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ግን የስብከቱ ሥራ ይበልጥ ተፈታታኝ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ቤታቸው አይገኙም፤ ቤታቸው የሚገኙ ሰዎችም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ እምብዛም ፍላጎት አይኖራቸው ይሆናል።

4 እናንተም የምትኖሩት የስብከቱን ሥራ ማከናወን ተፈታታኝ በሆነበት አካባቢ ከሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሐሳቦች እንደሚረዷችሁ ተስፋ እናደርጋለን። አንዳንዶች በአገልግሎት ላይ ተጨማሪ ሰዎችን ለማግኘት ምን እርምጃ እንደወሰዱ እንመለከታለን። በተጨማሪም ሰዎች መልእክታችንን ተቀበሉም አልተቀበሉ አዎንታዊ አመለካከት ይዘን መቀጠል ያለብን ለምን እንደሆነ እንመረምራለን።

ሰዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም ምንጊዜም አዎንታዊ ሁኑ

5. በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

5 በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎት ሲካፈሉ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነባቸው መጥቷል። አንዳንድ አስፋፊዎች የሚኖሩት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው አፓርታማዎች ወይም በአጥር የተከለሉ መኖሪያ ሰፈሮች በሚበዙበት አካባቢ ነው። እነዚህ ሰፈሮች ወይም አፓርታማዎች ዘበኛ የሚኖራቸው ሲሆን በዚያ ከሚኖር ሰው ፈቃድ ያላገኘ ማንኛውም ግለሰብ ወደ ውስጥ መግባት አይችልም። ሌሎች አስፋፊዎች ደግሞ የሰዎችን ቤት እንዳያንኳኩ የሚከለክላቸው ባይኖርም ሰዎቹን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። አንዳንድ አስፋፊዎች የሚያገለግሉት ብዙ ሰው በማይኖርባቸው ገጠራማ ወይም ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ነው። እነዚህ አስፋፊዎች አንድ ቤት እንኳ ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ በቦታው ሲደርሱ ደግሞ ቤት ውስጥ ሰው ላያገኙ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ካጋጠሙን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ታዲያ እንዲህ ያሉ እንቅፋቶችን መወጣትና አገልግሎታችንን ፍሬያማ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

6. ሰባኪዎችን ከዓሣ አጥማጆች ጋር የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?

6 ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ ዓሣ ከማጥመድ ጋር አመሳስሎታል። (ማር. 1:17) አንዳንድ ዓሣ አጥማጆች አንድም ዓሣ ሳያጠምዱ ቀናት ሊቆጠሩ ይችላሉ። ሆኖም ተስፋ አይቆርጡም፤ ከዚህ ይልቅ ማስተካከያ ያደርጋሉ። ዓሣ የሚያጠምዱበትን ሰዓት፣ ቦታ ወይም ዘዴ ይቀይራሉ። እኛም በአገልግሎታችን ላይ ተመሳሳይ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንችላለን። እስቲ አንዳንድ ምክሮችን እንመልከት።

በምታገለግሉበት አካባቢ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነባችሁ በሌላ ጊዜ፣ በሌላ ቦታ ወይም በሌላ ዘዴ እነሱን ለማግኘት ሞክሩ (ከአንቀጽ 7-10⁠ን ተመልከት) *

7. የምንሰብክበትን ሰዓት ስንለውጥ ምን ውጤት ልናገኝ እንችላለን?

7 በሌላ ጊዜ ሰዎችን ለማግኘት ሞክሩ። ሰዎች በአብዛኛው ቤታቸው በሚገኙበት ሰዓት ላይ ከሰበክን ብዙ ሰዎችን ልናገኝ እንችላለን። መቼም ሁሉም ሰው የሆነ ሰዓት ላይ ቤቱ መመለሱ አይቀርም! በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከሰዓት በኋላ ወይም ምሽት ላይ ሲያገለግሉ ብዙ ሰዎችን ቤታቸው ያገኛሉ። በተጨማሪም ሰዎቹ በዚህ ሰዓት ሰፊ ጊዜ ስለሚኖራቸው ለመወያየት ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ዴቪድ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችሉ ይሆናል። ዴቪድ ለተወሰኑ ሰዓታት ከቤት ወደ ቤት ካገለገለ በኋላ ሰው ወዳላገኘባቸው ቤቶች ተመልሶ ድጋሚ እንደሚሞክር ተናግሯል። “የሚገርመው ነገር ቤቶቹን በድጋሚ ስናንኳኳ ብዙዎቹን ሰዎች ቤታቸው እናገኛቸዋለን” ብሏል። *

በምታገለግሉበት አካባቢ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነባችሁ በሌላ ጊዜ እነሱን ለማግኘት ሞክሩ (ከአንቀጽ 7-8ን ተመልከት)

8. በመክብብ 11:6 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት ነው?

8 ሰዎቹን ለማግኘት ጥረት ማድረጋችንን ማቆም የለብንም። ይህ ርዕስ የተመሠረተበት ጥቅስ የሚያሳስበን ይህን ነው። (መክብብ 11:6ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዴቪድ ተስፋ አልቆረጠም። ወደ አንድ ቤት ደጋግሞ ከሄደ በኋላ በስተ መጨረሻ ቤት ውስጥ ሰው አገኘ። የቤቱ ባለቤት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ፈቃደኛ ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “እዚህ ቤት ውስጥ ለስምንት ዓመት ኖሬያለሁ፤ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ መጥተው አግኝቻቸው አላውቅም።” ዴቪድ “ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ ሰዎችን ቤታቸው ስናገኛቸው በአብዛኛው መልእክታችንን እንደሚቀበሉ አስተውያለሁ” ብሏል።

በምታገለግሉበት አካባቢ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነባችሁ በሌላ ቦታ እነሱን ለማግኘት ሞክሩ (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

9. አንዳንድ አስፋፊዎች በቀላሉ የማይገኙ ሰዎችን አግኝተው ለማነጋገር ምን አድርገዋል?

9 በሌላ ቦታ ሰዎችን ለማግኘት ሞክሩ። አንዳንድ አስፋፊዎች፣ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በቀላሉ የማይገኙ ሰዎችን ለማነጋገር ሲሉ የሚሰብኩበትን ቦታ ቀይረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከቤት ወደ ቤት መስበክ በማይፈቀድባቸው ትላልቅ አፓርታማዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ለማግኘት መንገድ ላይ ማገልገል ወይም የጽሑፍ ጋሪዎችን መጠቀም ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። እነዚህ ዘዴዎች በሌላ መንገድ የማይገኙ ሰዎችን በአካል አግኝቶ ለማነጋገር ያስችላሉ። ከዚህም ሌላ በርካታ አስፋፊዎች፣ በመናፈሻ ቦታዎችና በንግድ አካባቢዎች የሚያገኟቸው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ወይም ጽሑፍ ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኛ እንደሚሆኑ አስተውለዋል። ፍሎራን የተባለ በቦሊቪያ የሚኖር የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “ከቀኑ 7:00 እስከ 9:00 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ ቦታዎች እንሄዳለን፤ በዚህ ሰዓት ነጋዴዎቹ ሥራ አይበዛባቸውም። ብዙውን ጊዜ ከሰዎቹ ጋር ጥሩ ውይይት ማድረግ አልፎ ተርፎም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንችላለን።”

በምታገለግሉበት አካባቢ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነባችሁ በሌላ ዘዴ እነሱን ለማግኘት ሞክሩ (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

10. ሰዎችን ለማግኘት የትኞቹን ዘዴዎች መጠቀም እንችላለን?

10 በሌላ ዘዴ ሰዎችን ለማግኘት ሞክሩ። አንድን ሰው ለማግኘት በተደጋጋሚ ሞክራችኋል እንበል። በተለያዩ ጊዜያት ቤቱ ብትሄዱም ልታገኙት አልቻላችሁም። እንዲህ ያለውን ሰው ማግኘት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖሩ ይሆን? ካታሪና እንዲህ ብላለች፦ “በተደጋጋሚ ብሄድም ቤታቸው ላላገኘኋቸው ሰዎች ደብዳቤ እጽፍላቸዋለሁ፤ በአካል ባገኛቸው ኖሮ የምነግራቸውን ነገር ደብዳቤው ላይ አሰፍረዋለሁ።” ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አገልግሎታችሁን ስታከናውኑ በክልላችሁ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙሉ ለማግኘት የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቀሙ።

ሰዎች ግድየለሽ ቢሆኑም ምንጊዜም አዎንታዊ ሁኑ

11. አንዳንድ ሰዎች ለመልእክታችን ግድየለሽ የሆኑት ለምንድን ነው?

11 አንዳንድ ሰዎች ለመልእክታችን ግድየለሽ ናቸው። ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ እንደሚያስፈልጋቸው አይሰማቸውም። በዓለም ላይ መከራ እጅግ እንደበዛ ስለሚያዩ በአምላክ አያምኑም። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ እንመራለን የሚሉ የሃይማኖት መሪዎችን ግብዝነት ስለሚመለከቱ መጽሐፍ ቅዱስን አይቀበሉም። ሌሎች ደግሞ የሚያስቡት ስለ ሥራቸው፣ ስለ ቤተሰባቸው ወይም ስላሉባቸው ችግሮች ብቻ ነው፤ ስለዚህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ ለሕይወታቸው ጥቅም እንዳለው አይሰማቸውም። ታዲያ የምንሰብክላቸው ሰዎች መልእክታችን ጠቃሚ እንዳልሆነ ቢሰማቸውም እንኳ ደስታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

12. በፊልጵስዩስ 2:4 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን በአገልግሎት ላይ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

12 ልባዊ አሳቢነት አሳዩ። መጀመሪያ ላይ ለመልእክታችን ግድየለሽ የነበሩ ብዙ ሰዎች፣ የመሠከረላቸው አስፋፊ ከልብ እንደሚያስብላቸው ሲያስተውሉ ምሥራቹን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሆነዋል። (ፊልጵስዩስ 2:4ን አንብብ።) ለምሳሌ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው መልእክታችንን መስማት እንደማይፈልግ ቢናገር መጽሐፍ ቅዱሳችንን እና ጽሑፎቻችንን ወደ ቦርሳችን ከትተን ‘እንዲህ የተሰማህ ለምን እንደሆነ ብትነግረኝ ደስ ይለኛል’ እንለዋለን።” ሰዎች ከልብ የሚያስብላቸውን ሰው መለየት አይከብዳቸውም። የተናገርነውን ነገር ላያስታውሱ ይችላሉ፤ አሳቢነት እንዳሳየናቸው ግን ማስታወሳቸው አይቀርም። የቤቱ ባለቤት ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ ፊታችን ላይ የሚነበበው ስሜትና ምግባራችን ከልብ እንደምናስብለት ሊያሳየው ይችላል።

13. የምናነጋግረውን ሰው ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መግቢያችንን መቀየር የምንችለው እንዴት ነው?

13 የቤቱ ባለቤት የሚያስፈልጉትን እና ትኩረቱን የሚስቡትን ነገሮች ከግምት አስገብተን መግቢያችንን በመቀየር ልባዊ አሳቢነት ማሳየት እንችላለን። ለምሳሌ ሰውየው ልጆች እንዳሉት የሚጠቁም ነገር አለ? ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን ስለ ማሳደግ ወይም የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ የሚሰጠውን ጠቃሚ ምክር ብናካፍለው ትኩረቱ ሊሳብ ይችላል። በበሩ ላይ ብዙ መቆለፊያዎች አሉ? ከሆነ በዓለም ላይ ወንጀል ስለ መስፋፋቱና ይህ ስላስከተለው ስጋት ልናነሳለት እንችል ይሆናል፤ ከዚያም ወንጀል ሙሉ በሙሉ የሚጠፋበት ጊዜ እንደሚመጣ ልንነግረው እንችላለን። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ የምታነጋግሯቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እነሱን እንደሚጠቅማቸው እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥረት አድርጉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካታሪና “እውነትን ማወቄ ሕይወቴን ምን ያህል እንዳሻሻለልኝ ለማስታወስ እሞክራለሁ” በማለት ተናግራለች። ካታሪና ይህን ማድረጓ በልበ ሙሉነት እንድትሰብክ ረድቷታል፤ የምታነጋግራቸው ሰዎችም ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም።

14. በምሳሌ 27:17 መሠረት የአገልግሎት ጓደኛሞች እርስ በርስ መረዳዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 የሌሎችን እርዳታ ተቀበሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ የስብከትና የማስተማር ዘዴዎቹን ለጢሞቴዎስ አካፍሎት ነበር፤ እንዲሁም ጢሞቴዎስ እነዚህን ዘዴዎች ለሌሎችም እንዲያሳይ አበረታቶታል። (1 ቆሮ. 4:17) እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖች እርዳታ ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 27:17ን አንብብ።) ሾን የተባለን ወንድም እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሾን ለተወሰነ ጊዜ በአቅኚነት ባገለገለበት ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች፣ የራሳቸው ሃይማኖት እንዳላቸው የሚናገሩ ነበሩ። ታዲያ ደስታውን ጠብቆ መኖር የቻለው እንዴት ነው? ሾን “በተቻለ መጠን ከሌላ ሰው ጋር ለማገልገል እሞክር ነበር” ብሏል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ከአንዱ ቤት ወደ ቀጣዩ ቤት ስንሄድ በጉዞ ላይ የምናሳልፈውን ጊዜ የማስተማር ክህሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱ ሐሳቦችን ለመለዋወጥ እንጠቀምበት ነበር። ለምሳሌ የቤቱን ባለቤት ስላነጋገርንበት መንገድ እንወያያለን። ከዚያም ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ማስተካከያ ማድረግ እንደምንችል እንነጋገራለን።”

15. ስለ አገልግሎታችን መጸለይ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ እንዲረዳችሁ ጸልዩ። በአገልግሎት በተካፈላችሁ ቁጥር የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጸልዩ። ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ባይረዳን ኖሮ ማናችንም ምንም ነገር ማከናወን አንችልም ነበር። (መዝ. 127:1፤ ሉቃስ 11:13) ወደ ይሖዋ ስትጸልዩ የምትፈልጉትን ነገር ለይታችሁ ጥቀሱ። ለምሳሌ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያለውና ለመስማት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ለማግኘት እንዲረዳችሁ ልትጸልዩ ትችላላችሁ። ከዚያም ለምታገኟቸው ሰዎች ሁሉ በመስበክ ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰዱ።

16. በአገልግሎታችን ውጤታማ ለመሆን የግል ጥናት ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

16 ለግል ጥናት ጊዜ መድቡ። የአምላክ ቃል “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]” ይላል። (ሮም 12:2) ስለ አምላክ ያወቅነው ነገር እውነት እንደሆነ እርግጠኞች በሆንን መጠን በአገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ስንነጋገር ይበልጥ በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካታሪና እንዲህ ብላለች፦ “ከተወሰነ ጊዜ በፊት ስለ አንዳንድ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እምነቴን ማጠናከር እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ፈጣሪ መኖሩን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲሁም አምላክ በአሁኑ ወቅት የሚጠቀምበት ድርጅት እንዳለው በሚያሳዩ ማስረጃዎች ላይ በጥልቀት ምርምር አደረግኩ።” ካታሪና የግል ጥናት ማድረጓ እምነቷን እንዳጠናከረላትና በአገልግሎት የምታገኘውን ደስታ እንደጨመረላት ተናግራለች።

ምንጊዜም ለአገልግሎታችን አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?

17. ኢየሱስ ለአገልግሎቱ አዎንታዊ አመለካከት የነበረው ለምንድን ነው?

17 ኢየሱስ አንዳንዶች ለመልእክቱ ግድየለሽ ቢሆኑም እንኳ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ መስበኩን ቀጥሏል። ለምን? ሰዎች እውነትን መስማት ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቦ ነበር፤ እንዲሁም በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት የመቀበል አጋጣሚ እንዲያገኙ ፈልጓል። ከዚህም ሌላ መጀመሪያ ላይ ለመልእክቱ ግድየለሽ የነበሩ ሰዎች ከጊዜ በኋላ መልእክቱን እንደሚቀበሉ ተገንዝቦ ነበር። በራሱ ቤተሰብ ውስጥ ያጋጠመውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ለሦስት ዓመት ተኩል በዘለቀው አገልግሎቱ ወቅት ከወንድሞቹ መካከል አንዳቸውም ደቀ መዝሙሩ አልሆኑም ነበር። (ዮሐ. 7:5) ከሞት ከተነሳ በኋላ ግን ክርስቲያኖች ሆነዋል።—ሥራ 1:14

18. መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

18 የምናስተምረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማን መቼ እንደሚቀበል አናውቅም። አንዳንዶች መልእክታችንን ለመቀበል ረጅም ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። መልእክታችንን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ መልካም ምግባራችንን እና አዎንታዊ አመለካከታችንን ሲመለከቱ ከጊዜ በኋላ ‘አምላክን ማክበር’ ሊጀምሩ ይችላሉ።—1 ጴጥ. 2:12

19. በ1 ቆሮንቶስ 3:6, 7 መሠረት ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

19 የምንተክለውና የምናጠጣው እኛ ብንሆንም የሚያሳድገው አምላክ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7ን አንብብ።) በኢትዮጵያ የሚያገለግለው ጌታሁን እንዲህ ብሏል፦ “የምኖረው ምሥራቹ እምብዛም ባልተሰበከበት አካባቢ ነበር፤ ከ20 ዓመት በላይ በአካባቢው ያለሁት የይሖዋ ምሥክር እኔ ብቻ ነበርኩ። አሁን ግን በዚያ አካባቢ 14 አስፋፊዎች አሉ። ባለቤቴን እና ሦስቱን ልጆቼን ጨምሮ 13ቱ የተጠመቁ አስፋፊዎች ናቸው። በስብሰባዎቻችን ላይ በአማካይ 32 ሰዎች ይገኛሉ።” ጌታሁን፣ ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ድርጅቱ እስኪስብ ድረስ በትዕግሥት በመጠበቁና መስበኩን በመቀጠሉ ደስተኛ ነው።—ዮሐ. 6:44

20. ከሕይወት አድን ሠራተኞች ጋር የምንመሳሰለው በምን መንገድ ነው?

20 ይሖዋ የሁሉንም ሰው ሕይወት ውድ አድርጎ ይመለከተዋል። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በመሰብሰቡ ሥራ ከልጁ ጋር አብረን የመሥራት መብት ሰጥቶናል። (ሐጌ 2:7) የስብከቱ ሥራችን፣ ሕይወት አድን ሠራተኞች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አደጋ አጋጥሟቸው ከማዕድን ማውጫ ውስጥ መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን ለማዳን ከተሰማሩ ሕይወት አድን ሠራተኞች ጋር እንመሳሰላለን። ከአደጋው በሕይወት የተረፉት ጥቂት ማዕድን አውጪዎች ብቻ ቢሆኑም እንኳ ሁሉም ሕይወት አድን ሠራተኞች ያከናወኑት ሥራ ትልቅ ዋጋ አለው። ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ከዚህ በኋላ ከሰይጣን ሥርዓት መትረፍ የሚችሉ ምን ያህል ሰዎች እንዳሉ አናውቅም። ሆኖም ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ማናችንንም ሊጠቀም ይችላል። በቦሊቪያ የሚኖረው አንድሪያስ “አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ተምሮ እንዲጠመቅ መርዳት የቡድን ሥራ እንደሆነ ይሰማኛል” በማለት ተናግሯል። እኛም ለአገልግሎታችን እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ይባርከናል፤ ከአገልግሎታችንም እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን።

መዝሙር 66 ምሥራቹን አውጁ

^ አን.5 በአገልግሎት ስንካፈል ብዙ ሰዎች በቤታቸው ባይገኙ ወይም ለመልእክታችን ግዴለሾች ቢሆኑ እንኳ ለአገልግሎታችን አዎንታዊ አመለካከት ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ርዕስ አዎንታዊ አመለካከት ይዘን እንድንቀጥል የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዟል።

^ አን.7 አስፋፊዎች በዚህ ርዕስ ውስጥ በተጠቀሱት የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሲካፈሉ ለአካባቢው የሚሠሩ የመረጃ ጥበቃ ሕጎችን ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ (ከላይ ወደ ታች)፦ አንድ ባልና ሚስት ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ክልል ሲያገለግሉ። የመጀመሪያው ቤት ባለቤት ሥራ ቦታ ነው፤ የሁለተኛው ቤት ባለቤት ሆስፒታል ሄዳለች፤ የሦስተኛው ቤት ባለቤት ገበያ ወጥታለች። ባልና ሚስቱ የመጀመሪያውን ቤት ባለቤት አመሻሹ ላይ ሲመጡ አገኙት። የሁለተኛውን ቤት ባለቤት ሆስፒታሉ አቅራቢያ በአደባባይ ምሥክርነት ሲካፈሉ አግኝተው አነጋገሯት። የሦስተኛውን ቤት ባለቤት ደግሞ በስልክ ምሥክርነት ሲካፈሉ አገኟት።