በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

“ከሌሎች ብዙ ተምሬያለሁ!”

“ከሌሎች ብዙ ተምሬያለሁ!”

ድቅድቅ ያለ ጨለማ ነበር፤ እኔ ያለሁበት የፈረንሳይ ክፍለ ጦር በአልጄሪያ ተራሮች ላይ ሰፍሯል፤ አልጄሪያ ውስጥ ጦርነቱ ተፋፍሟል። መትረየስ ይዤ ምሽጌ ውስጥ ብቻዬን ዘብ ቆሜያለሁ። በድንገት ከኋላዬ ኮቴ ሰማሁ። በዚህ ጊዜ ክው አልኩ። በወቅቱ ገና 20 ዓመቴ ገደማ ነበር፤ መግደልም ሆነ መገደል አልፈለግኩም። “ወይኔ! አምላኬ!” አልኩ።

ያ አስፈሪ አጋጣሚ ሕይወቴን ለወጠው፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶ ስለ ፈጣሪ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። በዚያ ምሽት ቀጥሎ የተከናወነውን ነገር ከመተረኬ በፊት ግን ስለ ልጅነት ሕይወቴ እና አምላክን ለመፈለግ ስላነሳሳኝ ነገር ልንገራችሁ።

በልጅነቴ ከአባቴ ያገኘሁት ትምህርት

በ1937 በሰሜናዊ ፈረንሳይ በምትገኝ ጌናን የተባለች ማዕድን የሚወጣባት ከተማ ተወለድኩ። የድንጋይ ከሰል በማውጣት ሥራ የተሰማራው አባቴ ታታሪ ሠራተኛ የመሆንን አስፈላጊነት አስተምሮኛል። ከአባቴ የወረስኩት ሌላው ነገር ለፍትሕ መቆርቆርን ነው። አባቴ ይህ ባሕርይው በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ለሚሠሩት የማዕድን አውጪዎች እንዲሟገት አነሳስቶታል። የሚሠሩበት ሁኔታ እንዲሻሻል ለማድረግ ሲል በሠራተኛ ማኅበራት ውስጥ ገብቶ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በአድማዎች ይካፈል ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው የነበሩ ቀሳውስት ግብዝነት ያበሳጨው ነበር። ብዙዎቹ የተደላደለ ሕይወት ይመሩ የነበረ ቢሆንም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ከሆኑት የማዕድን አውጪዎች ምግብና ገንዘብ ይጠይቁ ነበር። አባቴ በቀሳውስቱ ምግባር በጣም ስለሚናደድ ስለ ሃይማኖት አስተምሮኝ አያውቅም። እንዲያውም ስለ አምላክ ጨርሶ ተነጋግረን አናውቅም።

እያደግኩ ስሄድ እኔም ለፍትሕ መጓደል ጥላቻ አዳበርኩ። ለምሳሌ አንዳንዶች ፈረንሳይ ውስጥ በሚኖሩት የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት መድልዎ በጣም ያበሳጨኝ ነበር። ከስደተኞቹ ልጆች ጋር እግር ኳስ እጫወት ነበር፤ ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍም ያስደስተኝ ነበር። ለነገሩ የእኔም እናት ብትሆን ፖላንዳዊት እንጂ ፈረንሳዊት አልነበረችም። የዘር መድልዎ የሚጠፋበትና ሁሉም ሰው በሰላም አብሮ የሚኖርበት ጊዜ እንዲመጣ እመኝ ነበር።

ስለ ሕይወት ዓላማ ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ

በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እያለሁ

በ1957 ለውትድርና አገልግሎት ተመለመልኩ። በአልጄሪያ ተራሮች ላይ ቅድም የጠቀስኩት ሁኔታ ውስጥ የገባሁት ከዚህ በኋላ ነው። “ወይኔ! አምላኬ!” ካልኩ በኋላ ዞር ስል ለካ የመጣው የጠላት ወታደር ሳይሆን የዱር አህያ ነው! ይህን ሳይ እፎይ አልኩ! ሆኖም ይህ አጋጣሚና ጦርነቱ በጥቅሉ ስለ ሕይወት ትርጉም በጥልቀት እንዳስብ አደረገኝ። ‘የተፈጠርነው ለምንድን ነው? አምላክ ያስብልናል? ዘላቂ ሰላም ይመጣ ይሆን?’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ።

ከጊዜ በኋላ ወላጆቼን ልጠይቅ ሄጄ ሳለ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘሁ። እሱም በካቶሊኮች የተዘጋጀ የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ የሰጠኝ ሲሆን ወደ አልጄሪያ ከተመለስኩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሱን ማንበብ ጀመርኩ። በተለይ ትኩረቴን የሳበው ራእይ 21:3, 4 ነበር፤ ጥቅሱ “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ . . . እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” ይላል። * ጥቅሱ በጣም አስገረመኝ። ‘ይህ ሐሳብ በእርግጥ ይፈጸም ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። በወቅቱ ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል።

በ1959 የውትድርና አገልግሎቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ፍራንሷ ከተባለ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘሁ፤ እሱም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን አስተማረኝ። ለምሳሌ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየኝ። (መዝ. 83:18) በተጨማሪም ይሖዋ በምድር ላይ ፍትሕ እንደሚያሰፍን፣ ምድርን ገነት እንደሚያደርጋት እንዲሁም በራእይ 21:3, 4 ላይ የሚገኘውን ቃል እውን እንደሚያደርገው አብራራልኝ።

የተማርኩት ትምህርት በጣም አሳማኝና ልብ የሚነካ ነበር። በሌላ በኩል ግን ቀሳውስቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ ትምህርት በማስተማራቸው በጣም ስለተበሳጨሁ ላወግዛቸው ፈለግኩ። የአባቴ አመለካከት ያሳደረብኝ ተጽዕኖ ገና ስላለቀቀኝ ነው መሰለኝ ጉዳዩን ጊዜ ልሰጠው አልፈለግኩም። ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ ፈለግኩ!

ሆኖም ፍራንሷ እና ያፈራኋቸው ሌሎቹ የይሖዋ ምሥክር ጓደኞቼ እንድረጋጋ ረዱኝ። የክርስቲያኖች ሥራ መፍረድ ሳይሆን የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ለሰዎች ተስፋ መስጠት መሆኑን አብራሩልኝ። ኢየሱስ ራሱ ያከናወነውና ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው ሥራ ይህ ነው። (ማቴ. 24:14፤ ሉቃስ 4:43) ከዚህም ሌላ ሰዎች በሚያምኑበት ነገር ባልስማማም እንኳ እነሱን በደግነትና በዘዴ ማነጋገር እንዳለብኝ ተማርኩ። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር [ሊሆን ይገባዋል]” ይላል።—2 ጢሞ. 2:24

አስፈላጊውን ማስተካከያ ካደረግኩ በኋላ በ1959 በተካሄደ የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። በዚያም አንጄል ከምትባል ደስ የምትል ወጣት እህት ጋር ተዋወቅኩ። እሷ ወደምትሄድበት ጉባኤ አልፎ አልፎ መሄድ ጀመርኩ። ከዚያም በ1960 ተጋባን። አንጄል ምርጥ ሴት፣ ግሩም ሚስት እና ከይሖዋ ያገኘኋት ውድ ስጦታ ነች።—ምሳሌ 19:14

በሠርጋችን ዕለት

ጥበብና ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ

ባለፉት ዓመታት ጥበበኛ ከሆኑና ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን አግኝቻለሁ። ካገኘኋቸው ትምህርቶች ዋነኛው ይህ ነው፦ በየትኛውም ከባድ የአገልግሎት ምድብ ስኬታማ ለመሆን ትሑት መሆን እንዲሁም በምሳሌ 15:22 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለብን፤ ጥቅሱ ‘የታቀደው ነገር በብዙ አማካሪዎች እንደሚሳካ’ ይናገራል።

ፈረንሳይ ውስጥ በወረዳ ሥራ ስንካፈል፣ 1965

ከ1964 ወዲህ ባሉት ዓመታት ያጋጠሙኝ ነገሮች በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ምክር ምን ያህል እውነተኛ እንደሆነ እንዳስተውል ረድተውኛል። በ1964 የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ፤ ወንድሞችን ለማበረታታትና በመንፈሳዊ ለማነጽ ጉባኤዎችን እጎበኝ ነበር። ሆኖም በወቅቱ ገና 27 ዓመቴ ነበር፤ ተሞክሮም አልነበረኝም። ስለዚህ አንዳንድ ስህተቶችን ሠርቻለሁ። ያም ቢሆን ከስህተቶቼ ለመማር ጥረት አደርግ ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ጥሩ ችሎታ ካላቸውና ጥበበኛ ከሆኑ “አማካሪዎች” ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን አግኝቻለሁ።

ለምሳሌ ጉባኤዎችን መጎብኘት በጀመርኩበት ጊዜ አካባቢ ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ። በፓሪስ የሚገኝን አንድ ጉባኤ ከጎበኘሁ በኋላ በመንፈሳዊ የጎለመሰ አንድ ወንድም በግል ሊያነጋግረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። እኔም “እሺ” አልኩት።

“ሉዊ፣ ሐኪሞች የሚረዱት ማንን ነው? ጤነኞችን ነው ወይስ ሕመምተኞችን?” በማለት ጠየቀኝ።

እኔም “ሕመምተኞችን” ብዬ መለስኩ።

ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ልክ ነህ። አንተ ግን በአብዛኛው ጊዜ የምታሳልፈው ከጉባኤ ሽማግሌውና በመንፈሳዊ ጠንካራ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንደሆነ አስተውያለሁ። በጉባኤያችን ውስጥ መንፈሳቸው የተሰበረ፣ በእውነት ውስጥ አዲስ የሆኑ ወይም ዓይናፋር የሆኑ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አሉ። አብረሃቸው ጊዜ ብታሳልፍ ወይም ቤታቸው ሄደህ አብረሃቸው ምግብ ብትበላ በጣም ይበረታታሉ።”

ይህ አሳቢ ወንድም የሰጠኝ ምክር በጣም ተገቢና ጠቃሚ ነበር። ለይሖዋ በጎች ያለው ፍቅር ልቤን ነካው። ስለዚህ ኩራቴን ዋጥ አድርጌ የሰጠኝን ምክር ወዲያውኑ በሥራ ላይ ማዋል ጀመርኩ። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ወንድሞችን ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።

በ1969 እና በ1973 በኮሎምብ፣ ፓሪስ በተካሄዱት ሁለት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የምግብ አገልግሎት ክፍል የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመድቤ ነበር። በ1973 በተካሄደው ስብሰባ ላይ ለአምስት ቀናት ያህል 60,000 ገደማ ለሚሆኑ ሰዎች ምግብ ማቅረብ ነበረብን! ኃላፊነቱ ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። ይሁንና በዚህ ጊዜም ቢሆን የረዳኝ ነገር ምሳሌ 15:22⁠ን ተግባራዊ ማድረጌ ይኸውም ጥበበኞችን ማማከሬ ነው። ከምግብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ልምድ ያላቸውን በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞች አማከርኩ። ከእነሱ መካከል ሥጋ አቅራቢዎች፣ አትክልት አምራቾች፣ ምግብ አብሳዮችና የዕቃ ግዢ ባለሙያዎች ይገኙበታል። እንደ ተራራ ሆኖ የታየኝን ኃላፊነት ከእነዚህ ወንድሞች ጋር በመተባበር ተወጣነው።

በ1973 እኔና ባለቤቴ በፈረንሳይ በሚገኘው ቤቴል እንድናገለግል ተጋበዝን። እዚያ የተሰጠኝ የመጀመሪያ ሥራም በጣም ከባድ ነበር። አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በካሜሩን ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ጽሑፍ ማድረስ ነበረብኝ፤ በካሜሩን ከ1970 እስከ 1993 ሥራችን ታግዶ ነበር። ይህ ኃላፊነትም ቢሆን ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። በወቅቱ በፈረንሳይ የሚካሄደውን ሥራ በበላይነት ይመራ የነበረው ወንድም መፍራቴን ስላስተዋለ ሳይሆን አይቀርም “በካሜሩን ያሉ ወንድሞቻችን መንፈሳዊ ምግብ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። እንመግባቸው!” በማለት አበረታታኝ። እንዳለውም መገብናቸው።

ከካሜሩን ከመጡ ወንድሞች ጋር ናይጄርያ ውስጥ የተደረገ ስብሰባ፣ 1973

በካሜሩን የሚኖሩ የጉባኤ ሽማግሌዎችን አግኝቼ ለማነጋገር የካሜሩን አጎራባች ወደሆኑ አገሮች በተደጋጋሚ እሄድ ነበር። ደፋርና ጠንቃቃ የሆኑት እነዚህ ወንድሞች ወደ ካሜሩን በቋሚነት መንፈሳዊ ምግብ እንዲደርስ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ ረድተውኛል። ይሖዋም ጥረታችንን ባርኮልናል። እንዲያውም ለ20 ዓመት ገደማ ያህል በዚያ አገር የሚኖሩ ወንድሞች አንድም መጠበቂያ ግንብም ሆነ ወርሃዊው የመንግሥት አገልግሎታችን አላመለጣቸውም።

እኔና አንጄል ከካሜሩን ከመጡ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ጋር ናይጄርያ ውስጥ፣ 1977

ከውዷ ባለቤቴ ብዙ ተምሬያለሁ

ከአንጄል ጋር መጠናናት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ በጣም መንፈሳዊ ሴት እንደሆነች አስተውዬ ነበር። በትዳር ሕይወታችን ደግሞ ይህን ይበልጥ መመልከት ችያለሁ። እንዲያውም በሠርጋችን ምሽት ላይ የሚገርም ነገር ጠይቃኝ ነበር፤ “ይሖዋ በትዳር ሕይወታችን እሱን በተሟላ ሁኔታ እንድናገለግለው እንዲረዳን እንጸልይ” አለችኝ። ይሖዋ ይህን ጸሎታችንን መልሶልናል።

አንጄል በይሖዋ ላይ ይበልጥ እንድተማመንም ረድታኛለች። ለምሳሌ በ1973 በቤቴል እንድናገለግል በተጋበዝንበት ወቅት ግብዣውን ለመቀበል አመንትቼ ነበር፤ ምክንያቱም የወረዳ ሥራውን በጣም እወደው ነበር። ሆኖም አንጄል ሕይወታችንን ለይሖዋ የወሰንን እንደመሆናችን መጠን ድርጅቱ የሚጠይቀንን ማንኛውንም ነገር ለማከናወን ፈቃደኞች መሆን እንዳለብን አስታወሰችኝ። (ዕብ. 13:17) ያነሳችው ነጥብ በጣም አሳማኝ ነበር! ስለዚህ ወደ ቤቴል ሄድን። በትዳር ባሳለፍናቸው ረጅም ዓመታት ባለቤቴ ልባም፣ አስተዋይና መንፈሳዊ መሆኗ ትዳራችንን አጠናክሮልናል፤ እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ረድቶናል።

ከአንጄል ጋር በፈረንሳይ ቤቴል ግቢ ውስጥ

አሁን ዕድሜያችን እየገፋ ቢሆንም ውዷ ባለቤቴ አንጄል አሁንም በእጅጉ ትደግፈኛለች። ለምሳሌ እኔና አንጄል በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ለመካፈል ስንል የእንግሊዝኛ ችሎታችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ጀመርን፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የሚካሄዱት በእንግሊዝኛ ነው። ለዚህም ስንል በ70ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ሳለን ወደ እንግሊዝኛ ጉባኤ ተዛወርን። የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል እንደመሆኔ መጠን ብዙ ኃላፊነቶች ስላሉብኝ አዲስ ቋንቋ መማር ተፈታታኝ ነበር። ሆኖም እኔና አንጄል እርስ በርስ እንረዳዳ ነበር። አሁን ዕድሜያችን 80ዎቹ ውስጥ ሲሆን አሁንም ለጉባኤ ስብሰባዎች የምንዘጋጀው በእንግሊዝኛም በፈረንሳይኛም ነው። በተጨማሪም አቅማችን በፈቀደ መጠን አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በአገልግሎት ለመካፈል ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋም እንግሊዝኛ ለመማር ያደረግነውን ጥረት ባርኮልናል።

በ2017 ትልቅ በረከት አገኘን። እኔና አንጄል በፓተርሰን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ በሚካሄደው ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አገኘን።

በእርግጥም ይሖዋ ታላቅ አስተማሪ ነው። (ኢሳ. 30:20) በመሆኑም ወጣት አረጋዊ ሳይል ሕዝቦቹ በሙሉ ከሁሉ የተሻለውን ትምህርት ማግኘታቸው አያስገርምም! (ዘዳ. 4:5-8) ይሖዋን እንዲሁም ተሞክሮ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶች የሚያዳምጡ ወጣቶች ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እንደሚያደርጉና ስኬታማ አዋቂዎች እንደሚሆኑ አስተውያለሁ። ምሳሌ 9:9 እንደሚለው “ጥበበኛን ሰው አስተምረው፤ ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል። ጻድቅን ሰው አስተምረው፤ ተጨማሪ እውቀት ያገኛል።”

ከ60 ዓመት ገደማ በፊት በአልጄሪያ ተራሮች ላይ በዚያ አስፈሪ ምሽት ያጋጠመኝን ነገር አልፎ አልፎ አስታውሰዋለሁ። እንዴት ያለ አርኪ ሕይወት እንደሚጠብቀኝ በወቅቱ አላወቅኩም ነበር። ከሌሎች ብዙ ተምሬያለሁ! ይሖዋ ለእኔና ለአንጄል አርኪና አስደሳች የሆነ ሕይወት ሰጥቶናል። በመሆኑም ከሰማዩ አባታችን እንዲሁም እሱን ከሚወዱ ጥበበኛ የሆኑና ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች መማራችንን መቼም ላለማቆም ወስነናል።

^ አን.11 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ።