በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 22

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ ተጠምቀው ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እርዷቸው

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ ተጠምቀው ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እርዷቸው

“እያንዳንዳችሁ . . . ተጠመቁ።”—ሥራ 2:38

መዝሙር 72 የመንግሥቱን እውነት ማሳወቅ

ማስተዋወቂያ *

1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተሰበሰቡት እጅግ ብዙ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ተነገራቸው?

ከበርካታ አገሮች የመጡና የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ እጅግ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ተሰብስበዋል። በዚያ ቀን አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጸመ። አንዳንድ አይሁዳውያን በድንገት በጎብኚዎቹ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ! ከዚህ አስደናቂ ክንውን ይበልጥ ትኩረት የሚስበው ግን እነዚህ አይሁዳውያንና ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገሩት መልእክት ነው። ይህ መልእክት፣ ሕዝቡ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መዳን ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጽ ነው። ሕዝቡ በመልእክቱ ልባቸው በጥልቅ ተነካ። በመሆኑም “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” በማለት ጠየቁ። ጴጥሮስም “እያንዳንዳችሁ . . . ተጠመቁ” የሚል መልስ ሰጣቸው።—ሥራ 2:37, 38

አንድ ወንድም ከባለቤቱ ጋር ሆኖ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ አንድን ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠና (አንቀጽ 2⁠ን ተመልከት)

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (ሽፋኑን ተመልከት።)

2 ቀጥሎ የተከናወነው ነገር በጣም አስገራሚ ነው። በዚያ ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጠምቀው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ታላቅ ተልእኮ ይኸውም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የጀመረው በዚህ መንገድ ነው። ይህ ሥራ እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመንም ቀጥሏል። እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሰዎችን ወደ ጥምቀት ደረጃ ማድረስ አንችልም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እዚህ ግብ ላይ እስኪደርስ ወራት፣ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ጊዜ ሊፈጅበት ይችላል። ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ ብዙ ሥራ ይጠይቃል፤ በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናው ሰው ካለ ይህ እንደሚገባህ ጥያቄ የለውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ የተጠመቀ ደቀ መዝሙር እንዲሆን መርዳት የምትችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ የሚማረውን ነገር በሥራ ላይ እንዲያውል እርዳው

3. ማቴዎስ 28:19, 20 እንደሚያሳየው አንድ ጥናት እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ምን ማድረግ አለበት?

3 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጠመቅ እንዲችል የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል አለበት። (ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።) ጥናቱ የተማረውን ነገር በሥራ ላይ የሚያውል ከሆነ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እንደጠቀሰው “አስተዋይ ሰው” ይሆናል፤ ይህ ሰው ቤቱን በዓለት ላይ ለመገንባት ሲል በጥልቀት ቆፍሯል። (ማቴ. 7:24, 25፤ ሉቃስ 6:47, 48) ታዲያ ጥናቱ የተማረውን ነገር በሥራ ላይ እንዲያውል ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው? ሦስት መንገዶችን እስቲ እንመልከት።

4. አንድ ጥናት በቀጣይነት እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው? (“ ጥናትህ ግቦች እንዲያወጣና ግቦቹ ላይ እንዲደርስ እርዳው” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

4 ጥናትህ ግቦች እንዲያወጣ እርዳው። እንዲህ ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ረጅም መንገድ የምትጓዝ ከሆነ በየመሃሉ ቆም እያልክ አካባቢውን ለማየት ታስብ ይሆናል። ይህን ማድረግህ መድረሻህ በጣም ሩቅ ሆኖ እንዳይሰማህ ያደርጋል። በተመሳሳይም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የአጭር ጊዜ ግቦችን የሚያወጣና እነዚህ ግቦች ላይ የሚደርስ ከሆነ ጥምቀትም ሊደረስበት የሚችል ግብ እንደሆነ መገንዘቡ አይቀርም። ጥናትህ እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ላይ ያለውን “ግብ” የሚለውን ገጽታ ተጠቀም። እያንዳንዱን ምዕራፍ አጥንታችሁ ስትጨርሱ በትምህርቱ ላይ የተጠቀሰው ግብ ካጠናችሁት ርዕሰ ጉዳይ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ተወያዩበት። ጥናትህ ሌላ ግብ እንዲያወጣ የምትፈልግ ከሆነ “ሌላ” በሚለው ቦታ ላይ ማስፈር ይቻላል። “ግብ” የሚለውን ሣጥን አዘውትራችሁ በመጠቀም ጥናትህ ስላወጣቸው የአጭር ጊዜም ሆነ የረጅም ጊዜ ግቦች መወያየት ትችላላችሁ።

5. በማርቆስ 10:17-22 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ አንድን ሀብታም ሰው ምን እንዲያደርግ ነግሮታል? ለምንስ?

5 ጥናትህ በሕይወቱ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ እርዳው። (ማርቆስ 10:17-22ን አንብብ።) ኢየሱስ ሀብታም ሰው ንብረቱን ሁሉ መሸጥ ከባድ እንደሚሆንበት ያውቅ ነበር። (ማር. 10:23) ያም ቢሆን ኢየሱስ ለሀብታሙ ሰው ይህን ከባድ ለውጥ እንዲያደርግ ነግሮታል። ለምን? ይህን ሰው ስለወደደው ነው። አንዳንድ ጊዜ ጥናታችን አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ እንዳልሆነ ስለሚሰማን የተማረውን ነገር በሥራ ላይ እንዲያውል ከማበረታታት ወደኋላ እንል ይሆናል። እርግጥ ሰዎች የቀድሞ ልማዶቻቸውን ትተው አዲሱን ስብዕና እስኪለብሱ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። (ቆላ. 3:9, 10) ሆኖም ስለ ጉዳዩ ቶሎ ማንሳታችን ጥናታችን ቶሎ ብሎ ለውጥ ማድረግ እንዲጀምር ሊረዳው ይችላል። ጥናትህ ለውጥ እንዲያደርግ ማበረታታትህ እንደምታስብለት ያሳያል።—መዝ. 141:5፤ ምሳሌ 27:17

6. የአመለካከት ጥያቄዎችን መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው?

6 የአመለካከት ጥያቄዎች ጥናቱ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ያለውን ሐሳብ ወይም ግንዛቤ ለማወቅ ያስችላሉ። ጥናትህ ትምህርቱን እንደተረዳውና እንዳመነበት ለማወቅ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ተጠቀም። እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን አዘውትረህ የምትጠቀም ከሆነ ለመቀበል ሊከብዱት የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተህ ማወያየት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ብዙ የአመለካከት ጥያቄዎችን ይዟል። ለምሳሌ ምዕራፍ 04 ላይ “ይሖዋ በስሙ ስትጠቀም ምን የሚሰማው ይመስልሃል?” የሚል ጥያቄ አለ። ምዕራፍ 09 ላይ ደግሞ “ስለ የትኞቹ ጉዳዮች መጸለይ ትፈልጋለህ?” የሚል ጥያቄ አለ። መጀመሪያ ላይ ጥናትህ የአመለካከት ጥያቄዎችን መመለስ ሊከብደው ይችላል። ሆኖም በጥቅሶቹና በሥዕሎቹ ላይ እንዲያመዛዝን በመርዳት ልታሠለጥነው ትችላለህ።

7. ተሞክሮዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

7 ጥናትህ ምን ማድረግ እንዳለበት ከተገነዘበ በኋላ ያንን እርምጃ እንዲወስድ ለማበረታታት ተሞክሮዎችን ተጠቀም። ለምሳሌ ጥናትህ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከከበደው ምዕራፍ 14 ላይ “ምርምር አድርግ” በሚለው ክፍል ሥር ያለውን ይሖዋ ስለ እኔ ያስባል የሚለውን ቪዲዮ ልታሳየው ትችላለህ። ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ላይ በብዙዎቹ ምዕራፎች ውስጥ “ጠለቅ ያለ ጥናት” ወይም “ምርምር አድርግ” በሚሉት ክፍሎች ሥር እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎችን ማግኘት ትችላለህ። * ሆኖም “እሱ ከቻለ አንተም አያቅትህም” በማለት ጥናትህን ከሌላ ሰው ጋር እንዳታወዳድረው ተጠንቀቅ። ጥናትህ እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ ራሱ ቢደርስ ይሻላል። በቪዲዮው ውስጥ ያለው ግለሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ተግባራዊ እንዲያደርግ የረዱትን ቁልፍ ነጥቦች አውጥተህ ለጥናትህ አብራራለት። ግለሰቡን የረዳውን ጥቅስ ወይም የወሰደውን አንድ እርምጃ ልታጎላለት ትችል ይሆናል። የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ደግሞ ይሖዋ ያንን ግለሰብ የረዳው እንዴት እንደሆነ ጎላ አድርገህ ግለጽ።

8. ጥናታችን ይሖዋን እንዲወድ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው?

8 ጥናትህ ይሖዋን እንዲወደው እርዳው። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የይሖዋን ባሕርያት ጎላ አድርገህ ለመግለጽ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፈልግ። ጥናትህ፣ ይሖዋ የሚወዱትን ሰዎች የሚደግፍ ደስተኛ አምላክ እንደሆነ እንዲገነዘብ እርዳው። (1 ጢሞ. 1:11፤ ዕብ. 11:6) የተማረውን ነገር በሥራ ላይ ማዋሉ እንደሚጠቅመው ግለጽለት፤ እንዲሁም ይሖዋ እንዲህ ያለ ጠቃሚ መመሪያ መስጠቱ ለእሱ ያለውን ፍቅር እንደሚያሳይ አብራራለት። (ኢሳ. 48:17, 18) ጥናትህ ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ ሲሄድ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ይበልጥ ይነሳሳል።—1 ዮሐ. 5:3

ጥናትህን ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር አስተዋውቀው

9. በማርቆስ 10:29, 30 መሠረት አንድ ሰው ተጠምቆ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገውን መሥዋዕት እንዲከፍል ምን ሊረዳው ይችላል?

9 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ አንዳንድ መሥዋዕቶችን መክፈል ያስፈልገዋል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሀብታም ሰው ሁሉ አንዳንድ ጥናቶች ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ሥራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ከሆነ ሥራቸውን መቀየር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ብዙዎች ይሖዋን የማይወዱ ጓደኞቻቸውን መተው ያስፈልጋቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮችን የማይወዱ ቤተሰቦቻቸው አግልለዋቸው ይሆናል። ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶችን መክፈል ከባድ ሊሆንባቸው እንደሚችል ገልጿል። ሆኖም እሱን የሚከተሉ ሰዎች መካሳቸው እንደማይቀር ቃል ገብቷል። አፍቃሪ የሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ በማግኘት ይባረካሉ። (ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ይህን ግሩም ስጦታ እንዲያገኝ ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

10. ከማኑዌል ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 ለጥናትህ ጓደኛ ሁንለት። ለጥናትህ እንደምታስብለት ልታሳየው ይገባል። ለምን? በሜክሲኮ የሚኖረው ማኑዌል ምን እንዳለ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስን እያጠና ስለነበረበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አስጠኚዬ ሁልጊዜ ጥናት ከመጀመራችን በፊት እንዴት እንደሰነበትኩ ይጠይቀኝ ነበር። ዘና እንድል እንዲሁም ነፃነት ተሰምቶኝ ስለ ማንኛውም ነገር እንዳነጋግረው አድርጎኛል። ከልቡ እንደሚያስብልኝ ይሰማኝ ነበር።”

11. ጥናቶቻችን ከእኛ ጋር ጊዜ ማሳለፋቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ጊዜ ያሳልፍ እንደነበረ ሁሉ ከጥናቶችህ ጋር ጊዜ አሳልፍ። (ዮሐ. 3:22) ጥናትህ እድገት እያደረገ ከሆነ ቤትህ ልትጋብዘውና ሻይ ቡና ልትሉ፣ አብራችሁ ልትመገቡ ወይም ወርሃዊ ብሮድካስቶቻችንን ልትመለከቱ ትችላላችሁ። ጥናትህ በተለይ በበዓላት ወቅት ብቸኝነት ሊሰማው ስለሚችል በዚህ ወቅት ብትጋብዘው ይበልጥ ሊደሰት ይችላል። በኡጋንዳ የሚኖረው ካዚብዌ እንዲህ ብሏል፦ “ከአስጠኚዬ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ስለ ይሖዋ የተማርኩት ነገር በጥናቴ ወቅት ከተማርኩት አይተናነስም።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሕዝቦቹን ምን ያህል እንደሚንከባከብ እንዲሁም የይሖዋ ሕዝቦች ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ተመለከትኩ። እኔም በሕይወቴ እንዲህ ዓይነት ደስታ ማግኘት እፈልግ ነበር።”

ጥናት ስትመራ የተለያዩ አስፋፊዎችን መጋበዝህ ጥናትህ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ይበልጥ ቀላል እንዲሆንለት ያደርጋል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) *

12. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ የተለያዩ አስፋፊዎችን መጋበዛችን ምን ጥቅም አለው?

12 በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ላይ የተለያዩ አስፋፊዎችን ጋብዝ። ጥናታችንን ብቻችንን ማስጠናት ወይም ሁልጊዜ ተመሳሳይ አስፋፊ መጋበዝ ሊቀናን ይችላል። ይህን ማድረግ አመቺ ሊሆን ቢችልም አልፎ አልፎ በጥናቱ ላይ የተለያዩ አስፋፊዎችን መጋበዛችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ይጠቅመዋል። በሞልዶቫ የሚኖረው ዲሚትሪ እንዲህ ብሏል፦ “በጥናቴ ላይ የተጋበዘው እያንዳንዱ አስፋፊ ትምህርቱን የሚያስረዳበት መንገድ የተለያየ ነው። ይህም ትምህርቱን ከተለያየ አቅጣጫ እንዳየው ረድቶኛል። በተጨማሪም ብዙዎቹን ወንድሞችና እህቶች በጥናቴ ላይ ተጋብዘው ስለተዋወቅኳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ ስገኝ ያን ያህል እንግድነት አልተሰማኝም።”

13. ጥናታችን በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ልንረዳው የሚገባው ለምንድን ነው?

13 ጥናትህ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ እርዳው። ይህን ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ አገልጋዮቹ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ አዟል፤ ስብሰባ የአምልኳችን ክፍል ነው። (ዕብ. 10:24, 25) ከዚህም ሌላ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊ ቤተሰባችን ናቸው። ከእነሱ ጋር አብረን ስንሰበሰብ አብረን ሆነን ጣፋጭ ምግብ እየተመገብን ያለን ያህል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ስትረዳው ወደ ጥምቀት ከሚያመሩ ወሳኝ እርምጃዎች መካከል አንዱን እንዲወስድ እየረዳኸው ነው። ሆኖም ጥናትህ ይህን እርምጃ መውሰድ ሊከብደው ይችላል። ታዲያ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ጥናትህ በስብሰባዎች ላይ እንዳይገኝ እንቅፋት የሆነበትን ማንኛውንም ነገር እንዲወጣ ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?

14. ጥናታችን በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ልናበረታታው የምንችለው እንዴት ነው?

14 ጥናትህ በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ለማበረታታት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተጠቀም። መጽሐፉ ከመውጣቱ በፊት የመጽሐፉን ውጤታማነት እንዲሞክሩ የተመረጡ ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች ምዕራፍ 10⁠ን ተጠቅመው ሲያስጠኑ ጥናቶቻቸው በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ በመርዳት ረገድ በጣም ተሳክቶላቸዋል። እርግጥ ጥናትህ በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ለመጋበዝ ምዕራፍ 10 ላይ እስኪደርስ ድረስ መጠበቅ አያስፈልግህም። በተቻለ ፍጥነት በስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋብዘው፤ እንዲሁም አዘውትረህ መጋበዝህን ቀጥል። እያንዳንዱ ጥናት በስብሰባ ላይ እንዳይገኝ እንቅፋት የሚሆንበት ነገር የተለያየ ነው። ስለዚህ ጥናትህ የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር፤ እንዲሁም ተገቢውን እርዳታ አበርክትለት። ጥናትህ ቶሎ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ባይጀምር ተስፋ አትቁረጥ። ታጋሽ ሁን፤ እንዲሁም እሱን መጋበዝህን አታቋርጥ።

ጥናትህ ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ እርዳው

15. ጥናታችንን ምን ሊያስፈራው ይችላል?

15 መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና በነበረበት ወቅት የይሖዋ ምሥክር መሆን አስፈርቶህ ነበር? ምናልባት ፈጽሞ ከቤት ወደ ቤት መስበክ እንደማትችል ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ቤተሰቦችህና ጓደኞችህ እንዳይቃወሙህ ፈርተህ ይሆናል። እንደዚህ ተሰምቶህ ከነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ስሜት ይገባሃል። ኢየሱስ ሰዎች እንዲህ ያለ ፍርሃት ሊያድርባቸው እንደሚችል ገልጿል። ሆኖም ተከታዮቹ በፍርሃት ተሸንፈው ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንዳይሉ አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 10:16, 17, 27, 28) ኢየሱስ ተከታዮቹ ፍርሃታቸውን እንዲያሸንፉ የረዳቸው እንዴት ነው? አንተስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?

16. ጥናታችን ስለ እምነቱ ለሌሎች እንዲናገር ልናሠለጥነው የምንችለው እንዴት ነው?

16 ጥናትህ ስለ እምነቱ ለሌሎች እንዲናገር ደረጃ በደረጃ አሠልጥነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት በላካቸው ወቅት ፍርሃት አድሮባቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ የት እንደሚሰብኩና የሚሰብኩት መልእክት ምን እንደሆነ በመንገር ረድቷቸዋል። (ማቴ. 10:5-7) አንተስ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ጥናትህ የት መስበክ እንደሚችል እንዲያስተውል እርዳው። ለምሳሌ ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስታጠኑ ‘ይህን መረጃ ብትነግረው ሊጠቀም የሚችል ሰው ታውቃለህ?’ ብለው ልትጠይቀው ትችላለህ። ከዚያም ይህን እውነት በቀላሉ ማስረዳት የሚችለው እንዴት እንደሆነ በማሳየት እንዲዘጋጅ እርዳው። ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ለዘላለም በደስታ ኑር! በሚለው መጽሐፍ ላይ ያሉትን “አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ” እና “አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ?” የሚሉትን ገጽታዎች በመጠቀም ልምምድ ማድረግ ትችላላችሁ። በልምምዱ ወቅት ጥናትህ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ ሌሎችን ቅር በማያሰኝ መንገድ ግልጽ መልስ እንዲሰጥ አሠልጥነው።

17. ማቴዎስ 10:19, 20, 29-31⁠ን ተጠቅመን ጥናታችን በይሖዋ እንዲተማመን ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው?

17 ጥናትህ በይሖዋ እንዲተማመን እርዳው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይሖዋ ስለሚወዳቸው እንደሚረዳቸው ዋስትና ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:19, 20, 29-31ን አንብብ።) አንተም ለጥናትህ ይሖዋ እንደሚረዳው አረጋግጥለት። ግቦቹን በተመለከተ ወደ ይሖዋ አብረኸው በመጸለይ በይሖዋ ላይ እንዲታመን ልትረዳው ትችላለህ። በፖላንድ የሚኖረው ፍራንቺሼክ እንዲህ ብሏል፦ “አስጠኚዬ በጸሎቱ ላይ ስለ ግቦቼ አዘውትሮ ይጠቅስ ነበር። ይሖዋ የአስጠኚዬን ጸሎት እንደመለሰለት ስመለከት እኔም ወዲያውኑ መጸለይ ጀመርኩ። በጉባኤ ስብሰባዎችና በትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከአዲሱ ሥራዬ እረፍት መውሰድ ባስፈለገኝ ወቅት የይሖዋን እርዳታ አይቻለሁ።”

18. ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመሩ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን ሥራ በተመለከተ ምን ይሰማዋል?

18 ይሖዋ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በጥልቅ ያስብላቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመሩ ክርስቲያኖችም ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ለመርዳት የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት ያደንቃል፤ እንዲሁም ይህን በማድረጋቸው ይወዳቸዋል። (ኢሳ. 52:7) በአሁኑ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሌለህ ሌሎች አስፋፊዎች ጥናት ሲመሩ በመገኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት ትችላለህ።

መዝሙር 60 ስብከታችን ሰው ያድናል

^ አን.5 ይህ ርዕስ፣ ኢየሱስ ሰዎች ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም እኛ የእሱን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደምንችል ያብራራል። በተጨማሪም ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው አዲስ መጽሐፍ ያሉትን አንዳንድ ገጽታዎች እንመለከታለን። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ለመርዳት ታስቦ ነው።

^ አን.7 ተጨማሪ ተሞክሮዎችን (1) የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ” ከሚለው ዋና ርዕስ በታች “ተግባራዊ ጠቀሜታ” ከዚያም “‘መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል’ (የመጠበቂያ ግንብ ዓምድ)” በሚለው ሥር ወይም (2) JW Library® ላይ ሚዲያ በሚለው ክፍል ውስጥ “ቃለ መጠይቅ እና ተሞክሮ” በሚለው ሥር ማግኘት ትችላለህ።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ከባለቤቱ ጋር ሆኖ አንድን ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠና። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የተለያዩ ወንድሞችን ጥናቱ ላይ ይጋብዛል።