በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 23

ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ፈጽሞ ብቻህን አይደለህም

ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ፈጽሞ ብቻህን አይደለህም

“ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው።”—መዝ. 145:18

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

ማስተዋወቂያ *

1. የይሖዋ አገልጋዮች አልፎ አልፎ ብቸኝነት የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

አብዛኞቻችን አልፎ አልፎ ብቸኝነት ይሰማናል። ለአንዳንዶች እንዲህ ያለው ስሜት ብዙም ሳይቆይ ያልፋል። ሌሎች ግን የብቸኝነት ስሜቱ ረጅም ጊዜ ይቆይባቸዋል። በሰዎች መሃል ብንሆንም እንኳ ብቸኝነት ሊሰማን ይችላል። አንዳንዶች አዲስ ጉባኤን መልመድ ከባድ ይሆንባቸዋል። ሌሎች ደግሞ በጣም በሚቀራረብ ቤተሰብ ውስጥ ስላደጉ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው መኖር ሲጀምሩ ብቸኝነት ይሰማቸዋል። አንዳንዶች በሞት ያጡት የቤተሰባቸው አባል በጣም ስለሚናፍቃቸው የብቸኝነት ስሜት ያጠቃቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ በተለይ በቅርቡ ወደ እውነት የመጡ ደግሞ የማያምኑ የቤተሰባቸው አባላት ወይም የቀድሞ ጓደኞቻቸው ሲያገሏቸው ወይም ስደት ሲያደርሱባቸው ብቸኝነት ይሰማቸዋል።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ይሖዋ ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ያውቃል፤ እንዲሁም ስሜታችንን ይረዳል። ብቸኝነት ሲሰማን ይህን ያስተውላል፤ እንዲሁም ይህን ስሜት እንድናሸንፍ ሊረዳን ይፈልጋል። ታዲያ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? እኛስ የብቸኝነት ስሜትን ለመቋቋም ምን ማድረግ እንችላለን? እንዲሁም ብቸኝነት የሚሰማቸውን በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ አንድ በአንድ እንመልከት።

ይሖዋ ስሜታችንን ይረዳልናል

ይሖዋ፣ ለኤልያስ መልአክ በመላክ ብቻውን እንዳልሆነ አረጋግጦለታል (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)

3. ይሖዋ ለኤልያስ አሳቢነት ያሳየው እንዴት ነው?

3 ይሖዋ የሁሉም አገልጋዮቹ ደህንነት ያሳስበዋል። ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ቅርብ ነው፤ እንዲሁም ስሜታችን ሲደቆስ ያስተውላል። (መዝ. 145:18, 19) ይሖዋ ለነቢዩ ኤልያስ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠውና እንዴት እንደረዳው እንመልከት። ታማኙ ኤልያስ የኖረው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ላይ ነው። በዚህ ወቅት የይሖዋ አገልጋዮች ከባድ ስደት ይደርስባቸው ነበር፤ ኃያል የሆኑት የአምላክ ጠላቶች በተለይ ኤልያስን የጥቃት ዒላማቸው አድርገውት ነበር። (1 ነገ. 19:1, 2) ኤልያስን ያስጨነቀው ሌላው ነገር ደግሞ ከይሖዋ ታማኝ ነቢያት መካከል የቀረው እሱ ብቻ እንደሆነ ማሰቡ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 19:10) አምላክ ኤልያስን ለመርዳት ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ። ይሖዋ መልአኩን በመላክ ኤልያስ ብቻውን እንዳልሆነና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው በርካታ እስራኤላውያን እንዳሉ አረጋገጠለት።—1 ነገ. 19:5, 18

4. ማርቆስ 10:29, 30 ይሖዋ ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ላጡ አገልጋዮቹ እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ አንዳንዶቻችን እሱን ለማገልገል ስንመርጥ ብዙ ነገር መሥዋዕት እንዳደረግን ያውቃል። መሥዋዕት ካደረግናቸው ነገሮች መካከል ከማያምኑ ዘመዶቻችን ወይም ከቀድሞ ጓደኞቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ይገኝበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህ ጉዳይ አሳስቦት ሊሆን ይችላል፤ በአንድ ወቅት ኢየሱስን “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” በማለት ጠይቆት ነበር። (ማቴ. 19:27) በመሆኑም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንደሚያገኙ በመግለጽ አበረታታቸው። (ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።) የመንፈሳዊ ቤተሰባችን ራስ የሆነው ይሖዋ ደግሞ እሱን ማገልገል የሚፈልጉትን እንደሚደግፋቸው ቃል ገብቷል። (መዝ. 9:10) የይሖዋን እርዳታ ለማግኘትና የብቸኝነት ስሜትን ለመቋቋም ማድረግ ያለብህን አንዳንድ ነገሮች እስቲ እንመልከት።

ብቸኝነት ሲሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

5. ይሖዋ እያደረገልህ ባለው ድጋፍ ላይ ማተኮርህ ምን ጥቅም አለው?

5 ይሖዋ እያደረገልህ ባለው ድጋፍ ላይ አተኩር። (መዝ. 55:22) እንዲህ ማድረግህ ስለ ሁኔታህ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳሃል። ኬሮል * የተባለችውን ያላገባች እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ከቤተሰቧ አባላት መካከል አንዳቸውም እውነት ውስጥ አይደሉም። ኬሮል እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ባጋጠሙኝ መከራዎች ሁሉ እንዴት እንደረዳኝ መለስ ብዬ ሳሰላስል ብቻዬን እንዳልሆንኩ ይሰማኛል። እንዲሁም ይሖዋ ወደፊትም ከጎኔ እንደሚሆን እንድተማመን ያደርገኛል።”

6. አንደኛ ጴጥሮስ 5:9, 10 ከብቸኝነት ስሜት ጋር የሚታገሉ ክርስቲያኖችን የሚያበረታታው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ብቸኝነት የሚሰማቸውን የእምነት አጋሮችህን እየረዳቸው ያለው እንዴት እንደሆነ አስብ። (1 ጴጥሮስ 5:9, 10ን አንብብ።) ሂሮሺ ለበርካታ ዓመታት እውነት ውስጥ ቢኖርም ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዳቸውም ወደ እውነት አልመጡም፤ እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤ ውስጥ ሁሉም ሰው የየራሱ ችግር እንዳለው በቀላሉ ማየት ይቻላል። ሆኖም ሁሉም ይሖዋን ለማገልገል አቅሙ የፈቀደውን እያደረገ ነው፤ እውነት ውስጥ ቤተሰብ የሌለን ይህን ስናይ እንጽናናለን።”

7. ጸሎት የሚረዳህ እንዴት ነው?

7 ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይኑርህ። ይህም የሚሰማህን ስሜት ለይሖዋ በግልጽ መንገርን ይጨምራል። (1 ጴጥ. 5:7) ማሲዬል የተባለችን ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ማሲዬል ከቤተሰቧ መካከል እውነትን የተቀበለችው እሷ ብቻ በመሆኗ ብቸኝነት ይሰማት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የብቸኝነት ስሜቴን ለመቋቋም የረዳኝ ዋነኛው ነገር ወደ ይሖዋ አጥብቄ መጸለዬ ነው። ይሖዋ ለእኔ አባት ሆኖልኛል፤ በየቀኑ በተደጋጋሚ ወደ እሱ በመጸለይ የሚሰማኝን ስሜት እነግረዋለሁ።”

በድምፅ የተቀረጸውን መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማዳመጥ ብቸኝነት የሚሰማቸውን ወንድሞች ሊረዳቸው ይችላል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት) *

8. የአምላክን ቃል ማንበብና ባነበብከው ላይ ማሰላሰል የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

8 የአምላክን ቃል አዘውትረህ አንብብ፤ እንዲሁም ይሖዋ ለአንተ ያለውን ፍቅር ጎላ አድርገው በሚገልጹ ዘገባዎች ላይ አሰላስል። ቤተሰቧ ተስፋ አስቆራጭ ንግግር የሚናገሯት ቢያንካ እንዲህ ብላለች፦ “ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ስላጋጠማቸው የይሖዋ አገልጋዮች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችንና ሌሎች የሕይወት ታሪኮችን ማንበቤና ማሰላሰሌ በጣም ጠቅሞኛል።” አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደ መዝሙር 27:10 እና ኢሳይያስ 41:10 ያሉ የሚያጽናኑ ጥቅሶችን በቃላቸው ይይዛሉ። ሌሎች ደግሞ ለስብሰባ ሲዘጋጁ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ በድምፅ የተቀረጸውን ንባብ ያዳምጣሉ፤ እንዲህ ማድረጋቸው የብቸኝነት ስሜትን ለመቋቋም እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

9. በስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

9 በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ለመገኘት ጥረት አድርግ። የሚቀርበው ትምህርት ያበረታታሃል፤ እንዲሁም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ይበልጥ የመተዋወቅ አጋጣሚ ታገኛለህ። (ዕብ. 10:24, 25) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ማሲዬል እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ዓይናፋር ብሆንም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ሐሳብ ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ። ይህ ደግሞ የጉባኤው ክፍል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።”

10. ከታማኝ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ከታማኝ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት መሥርት። በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑልህ የሚችሉ ወዳጆች ፈልግ፤ እነዚህ ወንድሞች ከአንተ የተለየ ዕድሜና አስተዳደግ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ” እንደሚገኝ ይናገራል። (ኢዮብ 12:12) በዕድሜ ተለቅ ያሉ ክርስቲያኖችም ከታማኝ ወጣቶች ብዙ የሚማሩት ነገር አለ። ዳዊት ከዮናታን ዕድሜው በጣም ያንስ ነበር፤ ይህ መሆኑ ግን የቅርብ ወዳጅነት ከመመሥረት አላገዳቸውም። (1 ሳሙ. 18:1) ዳዊትና ዮናታን እርስ በርስ መረዳዳታቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። (1 ሳሙ. 23:16-18) በቤተሰቧ ውስጥ ብቸኛ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው አይሪና እንዲህ ብላለች፦ “የእምነት ባልንጀሮቻችን መንፈሳዊ ወላጆቻችን፣ ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ሊሆኑልን ይችላሉ። ይሖዋ የሚያስፈልገንን እርዳታ ለመስጠት በእነሱ ሊጠቀም ይችላል።”

11. ጠንካራ ወዳጅነት ለመመሥረት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

11 በተለይ ዓይናፋር ከሆንክ አዲስ ጓደኛ ማፍራት ሊከብድህ ይችላል። ዓይናፋር የሆነችውን ራትና የተባለች እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ራትና እውነትን ስትማር ተቃውሞ አጋጥሟት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የመንፈሳዊ ቤተሰቤ እርዳታና ድጋፍ እንደሚያስፈልገኝ አምኜ መቀበል ነበረብኝ።” ስሜትህን አውጥተህ ለሌላ ሰው ማካፈል ከባድ ሊሆንብህ ይችላል፤ ግን የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የሚቻለው የልብን አውጥቶ በመነጋገር ነው። ወዳጆችህ ሊያበረታቱህና ሊደግፉህ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ልትነግራቸው ይገባል።

12. ጥሩ ወዳጆች ለማፍራት ምን ሊረዳህ ይችላል?

12 ወዳጅነት መመሥረት ከሚቻልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ከእምነት አጋሮችህ ጋር በአገልግሎት መካፈል ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኬሮል እንዲህ ብላለች፦ “ከእህቶች ጋር በአገልግሎትና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል በርካታ ጥሩ ጓደኞች አግኝቻለሁ። ባለፉት ዓመታት ይሖዋ በእነዚህ ወዳጆቼ አማካኝነት ደግፎኛል።” በእርግጥም ከታማኝ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የምታደርገው ጥረት የሚክስ ነው። ይሖዋ እንዲህ ባሉ ወዳጆች ተጠቅሞ እንደ ብቸኝነት ያሉ አሉታዊ ስሜቶችን እንድትቋቋም ይረዳሃል።—ምሳሌ 17:17

ሌሎች የቤተሰባችን ክፍል እንደሆኑ እንዲሰማቸው እርዷቸው

13. በጉባኤው ውስጥ ያሉ በሙሉ ምን ኃላፊነት አለባቸው?

13 በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ጉባኤው ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት ቦታ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፤ እንዲህ ካደረጉ ማንም የባይተዋርነት ስሜት አይሰማውም። (ዮሐ. 13:35) የምንናገረውና የምናደርገው ነገር በሌሎች ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል! አንዲት እህት ምን እንዳለች ልብ በል፦ “እውነትን ስማር ጉባኤው ቤተሰቤ ሆነ። ወንድሞችና እህቶች ባይረዱኝ ኖሮ የይሖዋ ምሥክር መሆን አልችልም ነበር።” ታዲያ እውነት ውስጥ ቤተሰብ የሌላቸው ክርስቲያኖች የጉባኤው ክፍል እንደሆኑ እንዲሰማቸው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

14. ከአዲሶች ጋር ጓደኝነት መመሥረት የምትችለው እንዴት ነው?

14 ቅድሚያውን ወስዳችሁ ከአዲሶች ጋር ጓደኝነት መሥርቱ። ልንወስደው የምንችለው የመጀመሪያ እርምጃ አዲሶች ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ ሞቅ ያለ አቀባበል ማድረግ ነው። (ሮም 15:7) ሆኖም ሞቅ ያለ ሰላምታ መስጠታችን ብቻ በቂ አይደለም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከእነሱ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት እንፈልጋለን። ስለዚህ ለአዲሶች ደግነትና ልባዊ አሳቢነት አሳዩአቸው። በግል ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ ሳትገቡ ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳት ጥረት አድርጉ። አንዳንዶች ስሜታቸውን አውጥተው መናገር ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል፤ ስለዚህ እንዲያዋሯችሁ አትጫኗቸው። ከዚህ ይልቅ የማያሸማቅቃቸው ጥያቄ በመጠየቅ የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ አበረታቷቸው፤ መልስ ሲሰጧችሁ ደግሞ በጥሞና አዳምጡ። ለምሳሌ እውነትን የሰሙት እንዴት እንደሆነ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ።

15. የጎለመሱ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎችን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

15 በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ፣ የጎለመሱ ክርስቲያኖች በተለይም ሽማግሌዎች ትኩረት ሲሰጧቸው በመንፈሳዊ እያደጉ ይሄዳሉ። የሜሊሳን ምሳሌ እንመልከት፤ ሜሊሳን እውነት ውስጥ ያሳደገቻት እናቷ ነች። ሜሊሳ እንዲህ ብላለች፦ “እውነት ውስጥ ባሳለፍኳቸው ዓመታት መንፈሳዊ አባት የሆኑልኝን ወንድሞች ከልቤ አደንቃቸዋለሁ። የማነጋግረው ሰው ስፈልግ ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጠኝ አጥቼ አላውቅም።” ሞሪሲዮ የተባለ ወጣት ወንድም የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚው እውነትን በተወበት ጊዜ በጣም አዝኖና ብቸኝነት ተሰምቶት ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “ሽማግሌዎች በግለሰብ ደረጃ ለእኔ ትኩረት መስጠታቸው በጣም ረድቶኛል። ሁልጊዜ ያነጋግሩኝ ነበር። አብረውኝ አገልግሎት ይወጡ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ያገኟቸውን ዕንቁዎች ያካፍሉኝ አልፎ ተርፎም አብረውኝ ኳስ ይጫወቱ ነበር።” ሜሊሳም ሆነች ሞሪሲዮ በአሁኑ ጊዜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው።

አብረኸው ጊዜ በማሳለፍ ወይም ደግነት በማሳየት ልታበረታታው የምትችለው ሰው በጉባኤህ ውስጥ አለ? (ከአንቀጽ 16-19⁠ን ተመልከት) *

16-17. ሌሎችን በየትኞቹ ተግባራዊ መንገዶች መርዳት እንችላለን?

16 ተግባራዊ በሆነ መንገድ እርዷቸው። (ገላ. 6:10) ከቤተሰቡ በጣም ርቆ በሌላ አገር በሚስዮናዊነት የሚያገለግለው ሊዮ እንዲህ ብሏል፦ “በአብዛኛው ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ የተደረገልን የደግነት ድርጊት ትንሽ ቢመስልም እንኳ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። በአንድ ወቅት የመኪና አደጋ ባጋጠመኝ ጊዜ የተፈጠረውን ነገር አልረሳውም። ከአደጋው በኋላ ቤት ስደርስ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነበርኩ። ከዚያ ግን አንድ ባልና ሚስት ቤታቸው ጋበዙኝ፤ ያቀረቡት ቀለል ያለ ምግብ ነበር። ምን እንደበላን አላስታውስም፤ ግን በደግነት እንዳዳመጡኝ ትዝ ይለኛል። በስተ መጨረሻ በጣም ተረጋጋሁ!”

17 ሁላችንም እንደ ወረዳና ክልል ስብሰባ ባሉ ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶች ላይ መገኘት ያስደስተናል፤ ለዚህ አንዱ ምክንያት ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍና ስለ ስብሰባው መጨዋወት መቻላችን ነው። ይሁንና ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኬሮል “በተለይ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ ብቸኝነት ይሰማኛል” ብላለች። ለምን? እንዲህ ብላለች፦ “በዙሪያዬ በመቶዎች አልፎ ተርፎም በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ቢኖሩም አብዛኛውን ጊዜ ሁሉም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ናቸው። እነሱን ሳይ ይበልጥ ብቸኝነት ይሰማኛል።” ሌሎች ደግሞ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ካጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ ስብሰባ ላይ ሲገኙ የብቸኝነት ስሜት በጣም ያስቸግራቸዋል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማቸው ወንድሞችና እህቶች ታውቃላችሁ? በቀጣዩ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከቤተሰባችሁ ጋር አብረው እንዲቀመጡ ለምን አትጋብዟቸውም?

18. ሌሎችን ስንጋብዝ 2 ቆሮንቶስ 6:11-13⁠ን በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

18 አብራችኋቸው ጊዜ አሳልፉ። ግብዣ ስታዘጋጁ የተለያዩ ወንድሞችና እህቶችን ለማካተት ጥረት አድርጉ፤ በተለይ ብቻቸውን እንደሆኑ የሚሰማቸውን አትርሷቸው። እንዲህ ላሉ ወንድሞች ‘ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት’ እንፈልጋለን። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሜሊሳ “ወንድሞችና እህቶች ቤታቸው ሲጋብዙን ወይም አብረናቸው ወጣ ብለን እንድንዝናና ሲጠይቁን በጣም ደስ ይለን ነበር” ብላለች። በጉባኤያችሁ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች መካከል ማንን መጋበዝ ትችላላችሁ?

19. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጊዜ ማሳለፋችን ይበልጥ ጠቃሚ የሚሆነው መቼ ሊሆን ይችላል?

19 ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን ጊዜ ማሳለፋችን ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል። አንዳንዶች በበዓላት ወቅት ከማያምኑ ቤተሰቦቻቸው ጋር መሆን ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ በአንዳንድ ቀናት ለምሳሌ በየዓመቱ፣ የቤተሰባቸው አባል የሞተበት ቀን ሲደርስ ይበልጥ ብቸኝነት ይሰማቸዋል። እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ስንጥር ‘ከልብ እንደምንጨነቅላቸው’ እናሳያለን።—ፊልጵ. 2:20

20. በማቴዎስ 12:48-50 ላይ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ብቸኝነት ሲሰማን የሚረዳን እንዴት ነው?

20 አንድ ክርስቲያን አልፎ አልፎ ብቸኝነት እንዲሰማው ሊያደርጉ የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ይሁንና ይሖዋ ስሜታችንን ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም። የሚያስፈልገንን እርዳታ ሁሉ ይሰጠናል፤ አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚያደርገው በእምነት አጋሮቻችን አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 12:48-50ን አንብብ።) እኛ ደግሞ መንፈሳዊ ቤተሰባችንን ለመደገፍ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ይሖዋ ላደረገልን ፍቅራዊ ዝግጅት ያለንን አድናቆት እናሳያለን። አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት ቢሰማንም እንኳ መቼም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን ነው!

መዝሙር 46 ይሖዋ እናመሰግንሃለን

^ አን.5 የብቸኝነት ስሜት አልፎ አልፎ ያታግልሃል? ከሆነ ይሖዋ ስሜትህን በሚገባ እንደሚረዳልህና የሚያስፈልግህን እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ እርግጠኛ ሁን። የብቸኝነት ስሜትን ለመቋቋም ምን ማድረግ እንደምትችል በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። በተጨማሪም ብቸኝነት የሚሰማቸውን የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንዴት ማበረታታት እንደምንችል እናያለን።

^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ ባለቤቱን በሞት ያጣ አንድ ወንድም በድምፅ የተቀረጸውን መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች ጽሑፎችን ሲያዳምጥ።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድምና ሴት ልጁ በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉ አንድ አረጋዊ ወንድምን በመጠየቅ ደግነት ሲያሳዩአቸው።