በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሐዋርያው ጳውሎስ “በሕጉ በኩል ለሕጉ ሞቻለሁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?—ገላ. 2:19

ሐዋርያው ጳውሎስ “ለአምላክ ሕያው መሆን እችል ዘንድ በሕጉ በኩል ለሕጉ ሞቻለሁ” ሲል ጽፏል።—ገላ. 2:19

ጳውሎስ የጻፈው ሐሳብ፣ የሮም ግዛት በሆነችው በገላትያ ውስጥ ለሚገኙ ጉባኤዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከሚገኘው ዋነኛ ሐሳብ ጋር የተያያዘ ነው። በገላትያ የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሐሰተኛ አስተማሪዎች ተጽዕኖ እያደረጉባቸው ነበር። እንዲህ ያሉት የሐሰት አስተማሪዎች፣ አንድ ሰው መዳን ማግኘት ከፈለገ የሙሴን ሕግ በተለይም የግርዘትን ሕግ መጠበቅ እንዳለበት ያስተምሩ ነበር። ይሁንና ግርዘት አምላክ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀው ነገር መሆኑ እንደቀረ ጳውሎስ ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥብ በማቅረብ እነዚህን የሐሰት ትምህርቶች ውድቅ አድርጓል፤ እንዲሁም ወንድሞች በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጎለብቱ ረድቷቸዋል።—ገላ. 2:4፤ 5:2

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ሲሞት ከሕልውና ውጭ እንደሚሆን ማለትም በዙሪያው ያለው ነገር ምንም ተጽዕኖ እንደማያደርግበት በግልጽ ያስተምራል። (መክ. 9:5) ጳውሎስ “ለሕጉ ሞቻለሁ” ሲል የሙሴ ሕግ በእሱ ላይ ምንም ተጽዕኖ እንደማያሳድር እየገለጸ ነበር። ጳውሎስ በቤዛው ላይ ባለው እምነት የተነሳ “ለአምላክ ሕያው መሆን” እንደቻለ እርግጠኛ ነበር።

የጳውሎስ ሁኔታ የተቀየረው “በሕጉ በኩል” ነው። ይህ የሆነው እንዴት ነው? ጳውሎስ ጥቂት ቁጥሮች ቀደም ብሎ “አንድ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሆነ” ተናግሮ ነበር። (ገላ. 2:16) ሕጉ ጠቃሚ አገልግሎት እንዳከናወነ ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ “ሕጉ የተጨመረው፣ ቃል የተገባለት ዘር እስኪመጣ ድረስ ሕግ ተላላፊነትን ይፋ ለማድረግ ነው” በማለት ለገላትያ ክርስቲያኖች ጽፏል። (ገላ. 3:19) በእርግጥም ሕጉ ፍጹማን ያልሆኑ ኃጢአተኛ ሰዎች ሕጉን ፍጹም በሆነ ሁኔታ መጠበቅ እንደማይችሉና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ፍጹም መሥዋዕት ሊቀርብላቸው እንደሚገባ በግልጽ አሳይቷል። ስለዚህ ሕጉ ሰዎችን ወደ ‘ዘሩ’ ማለትም ወደ ክርስቶስ መርቷቸዋል። አንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በአምላክ ፊት መጽደቅ ይችላል። (ገላ. 3:24) ጳውሎስ መጽደቅ የቻለው በሕጉ በኩል ኢየሱስን በመቀበሉና በእሱ በማመኑ ነው። በዚህ መንገድ ጳውሎስ ‘ለሕጉ ሞቶ ለአምላክ ሕያው መሆን’ ችሏል። ከዚያ በኋላ በእሱ ላይ ኃይል ያለው አምላክ እንጂ ሕጉ አይደለም።

ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይም ተመሳሳይ ሐሳብ ጠቅሷል። “ወንድሞቼ፣ እናንተም [በክርስቶስ] አካል አማካኝነት ለሕጉ ሞታችኋል፤ . . . አስሮ ይዞን ለነበረው ሕግ ስለሞትን ከሕጉ ነፃ ወጥተናል።” (ሮም 7:4, 6) ይህ ጥቅስም ሆነ ገላትያ 2:19 እንደሚያሳየው ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው በሕጉ መሠረት ኃጢአተኛ ሆኖ ስለ መሞት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ነፃ ስለመውጣት ነው። ከዚህ በኋላ ሕጉ በእሱም ሆነ እንደ እሱ ባሉ ክርስቲያኖች ላይ ምንም ተጽዕኖ አያሳድርም። እነዚህ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ቤዛ በማመናቸው ነፃ ወጥተዋል።