በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 27

ይሖዋን በጽናቱ ምሰሉት

ይሖዋን በጽናቱ ምሰሉት

“ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ።”—ሉቃስ 21:19

መዝሙር 114 “በትዕግሥት ጠብቁ”

ማስተዋወቂያ *

1-2. በኢሳይያስ 65:16, 17 ላይ ይሖዋ የተናገረው ሐሳብ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

“ተስፋ አትቁረጡ!” የ2017 የክልል ስብሰባ እንዲህ የሚል ስሜት ቀስቃሽ ርዕስ ነበረው። ስብሰባው የሚያጋጥሙንን መከራዎች እንዴት በጽናት መቋቋም እንደምንችል አስተምሮናል። ስብሰባውን ካደረግን አራት ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ የተለያዩ ችግሮችን በጽናት እየተቋቋምን ነው።

2 አንተስ በቅርቡ የደረሰብህ መከራ አለ? የቤተሰብህን አባል ወይም የምትወደውን ጓደኛህን በሞት አጥተሃል? ከማይድን በሽታ ጋር እየታገልክ ነው? እርጅና ሕይወትህን አስቸጋሪ አድርጎብሃል? የተፈጥሮ አደጋ፣ ወንጀል ወይም ስደት ደርሶብሃል? በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወይም በሌሎች በሽታዎች ምክንያት ችግር ደርሶብሃል? ይህ ሁሉ መከራ ያለፈ ታሪክ የሚሆንበትንና ጨርሶ የማይታወስበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን!ኢሳይያስ 65:16, 17ን አንብብ።

3. ከአሁኑ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

3 በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት በጣም ከባድ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ከባድ ሊሆን እንደሚችል እንጠብቃለን። (ማቴ. 24:21) በመሆኑም ለመጽናት የሚያስችል አቋም እንዲኖረን ከአሁኑ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:19) ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፈተና ያጋጠማቸው ሰዎች እንዴት እንደጸኑ ማሰባችን እኛም በጽናት እንድንቀጥል ይረዳናል።

4. ይሖዋ ከሁሉ የላቀ የጽናት ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

4 ጽናት በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ማን ነው? ይሖዋ አምላክ ነው። ይህ ሐሳብ ያስገርምህ ይሆናል። ግን እስቲ አስበው። ይህ ዓለም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር በመሆኑ በብዙ ችግሮች የተሞላ ነው። ይሖዋ እነዚህን ችግሮች በቅጽበት ለማጥፋት ኃይሉ አለው፤ ግን ይህን ለማድረግ ጊዜው እስኪደርስ በትዕግሥት እየጠበቀ ነው። (ሮም 9:22) አምላካችን፣ የቀጠረው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ይጸናል። ይሖዋ ከዘጠኝ ነገሮች ጋር በተያያዘ ጽናት እያሳየ ያለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ የትኞቹን ነገሮች በጽናት እያሳለፈ ነው?

5. የአምላክ ስም ነቀፋ የተሰነዘረበት እንዴት ነው? አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?

5 በስሙ ላይ የደረሰው ነቀፋ። ይሖዋ ስሙን ይወደዋል፤ እንዲሁም ሁላችንም ስሙን እንድናከብረው ይፈልጋል። (ኢሳ. 42:8) ይሁንና ላለፉት 6,000 ዓመታት ገደማ የይሖዋ መልካም ስም ነቀፋ ሲደርስበት ቆይቷል። (መዝ. 74:10, 18, 23) የአምላክ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ነቀፋ የተሰነዘረበት በኤደን ገነት ውስጥ ነው፤ ዲያብሎስ (“ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው) አዳምና ሔዋን ደስተኛ ሆነው ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ነገር አምላክ እንደከለከላቸው በመግለጽ የይሖዋን ስም አጎደፈ። (ዘፍ. 3:1-5) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ‘የሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ነፍጓቸዋል’ የሚል የሐሰት ክስ ሲሰነዘርበት ቆይቷል። ኢየሱስ በአባቱ ስም ላይ እየተሰነዘረ ያለው ነቀፋ አሳስቦት ነበር። በዚህም ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል።—ማቴ. 6:9

6. ይሖዋ በሉዓላዊነቱ ላይ የተነሳው ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ ረጅም ጊዜ እንዲያልፍ የፈቀደው ለምንድን ነው?

6 በሉዓላዊነቱ ላይ የተነሳው ተቃውሞ። ሰማይንና ምድርን የመግዛት መብት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ ደግሞም የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ ነው። (ራእይ 4:11) ይሁን እንጂ ዲያብሎስ መላእክትንና ሰዎችን በማሳት አምላክ የመግዛት መብት እንደሌለው እንዲያስቡ ለማድረግ ሞክሯል። የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ በአንድ ጀንበር የሚፈታ አይደለም። ጥበበኛ የሆነው አምላካችን፣ የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር እንዲሞክሩ ረዘም ያለ ጊዜ ሰጥቷቸዋል፤ ይህም ሰዎች ያለፈጣሪ እርዳታ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንደማይችሉ በግልጽ እንዲታይ አድርጓል። (ኤር. 10:23) አምላክ ትዕግሥት ማሳየቱ በሉዓላዊነቱ ላይ የተነሳው ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ እንዲያገኝ ያደርጋል። በምድር ላይ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ማስፈን የሚችለው የእሱ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ሲረጋገጥ የአምላክ ሉዓላዊነት ትክክለኛ እንደሆነ በግልጽ ይታያል።

7. በይሖዋ ላይ ያመፁት እነማን ናቸው? ምን እርምጃስ ይወስድባቸዋል?

7 ከልጆቹ መካከል አንዳንዶቹ ማመፃቸው። ይሖዋ መላእክትንና ሰዎችን ሲፈጥር ምንም እንከን አልነበረባቸውም፤ ሁሉም ልጆቹ ፍጹም ነበሩ። በኋላ ግን ከመላእክት አንዱ ይኸውም ሰይጣን (“ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም አለው) በይሖዋ ላይ ዓመፀ፤ እንዲሁም ፍጹም የሆኑት አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ አደረጋቸው። ሌሎች መላእክትና ሰዎችም በዓመፁ ተባበሩ። (ይሁዳ 6) ከጊዜ በኋላ ደግሞ የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ከሆኑት ከእስራኤላውያን መካከል እንኳ አንዳንዶቹ አምላክን ትተው ጣዖታትን አምልከዋል። (ኢሳ. 63:8, 10) ይሖዋ እንደተከዳ ቢሰማው የሚያስገርም አይደለም። ያም ቢሆን ይሖዋ ጸንቷል፤ እንዲሁም ሁሉንም ዓመፀኞች የሚያጠፋበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ መጽናቱን ይቀጥላል። ልክ እንደ እሱ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ክፋት በጽናት እየተቋቋሙ ያሉት ታማኝ አገልጋዮቹ ያን ጊዜ እፎይ ይላሉ።

8-9. ሰይጣን ስለ ይሖዋ የትኞቹን ውሸቶች ያስፋፋል? እኛስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንችላለን?

8 ዲያብሎስ የሚያስፋፋቸው ውሸቶች። ሰይጣን ኢዮብም ሆነ ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች አምላክን የሚያገለግሉት ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ እንደሆነ በመናገር ክስ ሰንዝሯል። (ኢዮብ 1:8-11፤ 2:3-5) ዲያብሎስ ዛሬም ቢሆን እንዲህ ያለ ክስ እየሰነዘረ ነው። (ራእይ 12:10) እኛም ፈተና ሲያጋጥመን በመጽናትና ለይሖዋ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ለእሱ ታማኝ በመሆን የሰይጣን ክስ ውሸት መሆኑን ማጋለጥ እንችላለን። ይሖዋ ኢዮብን እንደባረከው ሁሉ እኛም ከጸናን ይባርከናል።—ያዕ. 5:11

9 ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት መሪዎች በመጠቀም ‘ይሖዋ ጨካኝ ነው’ እንዲሁም ‘በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው እሱ ነው’ የሚል ትምህርት ያስፋፋል። እንዲያውም አንዳንዶች፣ ሕፃናት ሲሞቱ ‘አምላክ ተጨማሪ መላእክት ስለሚያስፈልጉት ወደ ሰማይ ወስዷቸዋል’ ብለው ያስተምራሉ። ይህ በአምላክ ላይ የተሰነዘረ ስድብ ነው። እኛ ግን ይሖዋ አፍቃሪ አባት እንደሆነ እናውቃለን። በመሆኑም በከባድ በሽታ ብንያዝ ወይም የምንወደውን ሰው በሞት ብናጣ በፍጹም አምላክን አንወቅስም። እንዲያውም አንድ ቀን አምላክ ነገሮችን እንደሚያስተካክል እምነት አለን። ይሖዋ አፍቃሪ አምላክ መሆኑን ሰሚ ጆሮ ላለው ሁሉ እንናገራለን። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ እሱን ለሚነቅፈው አካል ግሩም ምላሽ እንዲሰጥ ያስችለዋል።—ምሳሌ 27:11

10. መዝሙር 22:23, 24 ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

10 በሚወዳቸው አገልጋዮቹ ላይ የሚደርሰው ሥቃይ። ይሖዋ ሩኅሩኅ አምላክ ነው። በስደት፣ በሕመም ወይም በአለፍጽምናችን የተነሳ ስንሠቃይ በሚመለከትበት ጊዜ በጣም ያዝናል። (መዝሙር 22:23, 24ን አንብብ።) ይሖዋ ሥቃያችን ይሰማዋል፤ ከሥቃያችን ሊገላግለን ይፈልጋል፤ ደግሞም ይገላግለናል። (ከዘፀአት 3:7, 8 እና ከኢሳይያስ 63:9 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ‘እንባን ሁሉ ከዓይናችን የሚያብስበት እንዲሁም ሞት፣ ሐዘን፣ ጩኸትና ሥቃይ የማይኖርበት’ ጊዜ ይመጣል።—ራእይ 21:4

11. ይሖዋ በሞት ካንቀላፉ ታማኝ አገልጋዮቹ ጋር በተያያዘ ምን ይናፍቀዋል?

11 በሞት ካንቀላፉ ወዳጆቹ መለየቱ። ይሖዋ በሞት ያንቀላፉ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን በተመለከተ ምን ይሰማዋል? እንደገና ሊያያቸው ይናፍቃል! (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ወዳጁን አብርሃምን ምን ያህል እንደሚናፍቀው ማሰብ ትችላለህ? (ያዕ. 2:23) “ፊት ለፊት” ያነጋግረው የነበረውን ሙሴንስ? (ዘፀ. 33:11) ይሖዋ ዳዊትና ሌሎቹ ዘማሪዎች ማራኪ የሆኑ የውዳሴ መዝሙሮችን ሲዘምሩ ለመስማት ምንኛ ይጓጓ ይሆን! (መዝ. 104:33) እነዚህ የአምላክ ወዳጆች በሞት ቢያንቀላፉም ይሖዋ አልረሳቸውም። (ኢሳ. 49:15) ስለ እነሱ እያንዳንዱን ነገር ያስታውሳል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእሱ አመለካከት አንጻር ሁሉም ሕያዋን ናቸው” የሚለው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 20:38 ግርጌ) አንድ ቀን ከሞት ያስነሳቸዋል፤ በዚያ ጊዜ፣ ለእሱ የሚያቀርቡትን ልባዊ ጸሎት ይሰማል፤ አምልኳቸውንም ይቀበላል። የምትወደውን ሰው ሞት ነጥቆህ ከሆነ ይህ ሐሳብ እንደሚያጽናናህ ተስፋ እናደርጋለን።

12. በእነዚህ ክፉ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋን በጣም የሚያሳዝነው ነገር ምንድን ነው?

12 ክፉዎች በሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጭቆና። በኤደን ዓመፅ በተነሳበት ወቅት ይሖዋ ሁሉ ነገር የሚስተካከልበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱ አውቆ ነበር። ይሖዋ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የተስፋፋውን ክፋት፣ የፍትሕ መጓደልና ዓመፅ ይጠላል። ይሖዋ ከጥንት ጀምሮ በተለይ ደካማና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች፣ ለምሳሌ ወላጅ ለሌላቸው ልጆችና ለመበለቶች በጣም ያስባል። (ዘካ. 7:9, 10) ይሖዋ በተለይ ደግሞ ታማኝ አገልጋዮቹ ጭቆና ሲደርስባቸውና ሲታሰሩ ሲያይ እጅግ ያዝናል። መከራ ቢደርስባችሁም በጽናት ረገድ ይሖዋን የምትመስሉ አገልጋዮቹ ሁሉ፣ እሱ እንደሚወዳችሁ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ!

13. የሰው ዘር ምን ዓይነት የሥነ ምግባር ዝቅጠት ላይ ደርሷል? አምላክስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ያደርጋል?

13 የሰው ልጆች የሥነ ምግባር ዝቅጠት። ሰይጣን በአምላክ መልክ የተፈጠሩት የሰው ልጆች ራሳቸውን ሲያዋርዱ ማየት ያስደስተዋል። በኖኅ ዘመን “ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛ” ሲመለከት “ሰዎችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም አዘነ።” (ዘፍ. 6:5, 6, 11) ከዚያ ወዲህ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል? በፍጹም! ዲያብሎስ ተቃራኒም ሆነ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ብልግና ጨምሮ ሁሉም ዓይነት የፆታ ብልግና በዓለም ላይ እንደተስፋፋ ሲያይ በጣም እንደሚደሰት ጥያቄ የለውም። (ኤፌ. 4:18, 19) በተለይ የይሖዋ አምላኪ የሆኑ ሰዎች ከባድ ኃጢአት እንዲፈጽሙ በማድረግ ረገድ ሲሳካለት ሰይጣን በጣም ይደሰታል። ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎችን በሙሉ ጠራርጎ በማስወገድ ማንኛውንም ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግና አጥብቆ እንደሚጸየፍ ያሳያል።

14. የሰው ልጆች በተፈጥሮ ላይ ምን እያደረሱ ነው?

14 የሰው ልጆች የፍጥረት ሥራዎቹን ማበላሸታቸው። “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ” ነው፤ ይህም እንዳይበቃ ደግሞ የሰው ልጆች ይሖዋ በአደራ የሰጣቸውን ምድርንና እንስሳትን እያጠፉ ነው። (መክ. 8:9፤ ዘፍ. 1:28) አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የሰው ልጆች በሚያደርጉት ነገር ምክንያት በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ዝርያዎች * ከምድር ገጽ ሊጠፉ ይችላሉ። ባለሙያዎች ምድር አደጋ ላይ እንደሆነች መናገራቸው አያስገርምም። ደስ የሚለው፣ ይሖዋ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን ለማጥፋትና’ መላዋን ምድር ገነት ለማድረግ ቃል ገብቷል።—ራእይ 11:18፤ ኢሳ. 35:1

ይሖዋ ካሳየው ጽናት ምን እንማራለን?

15-16. ከይሖዋ ጋር አብረን እንድንጸና ሊያነሳሳን የሚገባው ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

15 በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በጽናት ያሳለፋቸውን አስጨናቂ ችግሮች ለማሰብ ሞክር። (“ ይሖዋ በጽናት እያሳለፋቸው ያሉት ነገሮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት በማንኛውም ጊዜ ሊያጠፋው ይችላል። ይሁንና ይሖዋ መታገሡ ብዙ በረከት አስገኝቶልናል! ነጥቡን ለማብራራት አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ባልና ሚስት የሚወልዱት ልጅ ከባድ የጤና እክል እንደሚኖርበት ተነገራቸው እንበል፤ ልጁ ሕመሙ እንደሚያሠቃየውና ገና በለጋ ዕድሜው እንደሚሞት ሐኪሞች ገለጹላቸው። ወላጆቹ ከባድ መሥዋዕት የሚያስከፍላቸው ቢሆንም ልጁን ለመውለድ ወሰኑ። ለልጃቸው ያላቸው ፍቅር የትኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ በጽናት ተቋቁመው በተቻለ መጠን ልጁ ጥሩ ሕይወት እንዲመራ ለመርዳት ያነሳሳቸዋል።

16 በተመሳሳይም ሁሉም የአዳምና የሔዋን ዘሮች ሲወለዱ ጀምሮ ፍጹማን አይደሉም። ያም ቢሆን ይሖዋ ይወዳቸዋል፤ እንዲሁም ያስብላቸዋል። (1 ዮሐ. 4:19) ደግሞም በምሳሌው ላይ ከተጠቀሱት ወላጆች በተለየ መልኩ ይሖዋ በልጆቹ ላይ የሚደርሰውን መከራ የማስቆም ኃይል አለው። በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ቀን ቀጥሯል። (ማቴ. 24:36) ይሖዋ እንደሚወደን ማወቃችን እሱ የቀጠረው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እኛም አብረነው እንድንጸና ሊያነሳሳን አይገባም?

17. በዕብራውያን 12:2, 3 ላይ የሚገኘው ስለ ኢየሱስ የሚናገረው ሐሳብ በጽናት እንድንቀጥል የሚያበረታታን እንዴት ነው?

17 ይሖዋ በጽናት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስም የአባቱን የጽናት ምሳሌ ተከትሏል። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ለእኛ ሲል የተቃውሞ ንግግርን እና ውርደትን በጽናት ተቋቁሟል፤ እንዲሁም በመከራ እንጨት ላይ እስከመሞት ድረስ ጸንቷል። (ዕብራውያን 12:2, 3ን አንብብ።) ኢየሱስ እንዲጸና ብርታት የሆነው የይሖዋ የጽናት ምሳሌ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። የይሖዋ ምሳሌ እኛንም ሊያበረታን ይችላል።

18. ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:9 የይሖዋ ትዕግሥት የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያሳየው እንዴት ነው?

18 ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:9ን አንብብ። ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ መቼ እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ ትዕግሥት ማሳየቱ እሱን የሚያመልክና የሚያወድስ በሚሊዮኖች የሚቆጠር እጅግ ብዙ ሕዝብ እንዲሰበሰብ አድርጓል። ይሖዋ ለረጅም ጊዜ መጽናቱ እነዚህ ሰዎች እንዲወለዱ፣ ስለ እሱ እንዲማሩና እንዲወዱት እንዲሁም ራሳቸውን ለእሱ እንዲወስኑ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ናቸው። ይሖዋ እስከ መጨረሻው የጸኑትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚባርክበት ጊዜ፣ ለመጽናት ያደረገው ውሳኔ ትክክል እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል!

19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? ምን ሽልማትስ እናገኛለን?

19 በደስታ መጽናት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ከይሖዋ እንማራለን። ሰይጣን ብዙ መከራና ሐዘን ቢያደርስም ይሖዋ አሁንም ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው። (1 ጢሞ. 1:11) እኛም ይሖዋ ስሙን የሚያስቀድስበት፣ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበት፣ ክፋትን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበት እንዲሁም አሁን ላሉብን ችግሮች መፍትሔ የሚያመጣበት ጊዜ እስኪደርስ በምንጠባበቅበት ወቅት ደስተኛ መሆን እንችላለን። እንግዲያው እስከ መጨረሻው ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲሁም የሰማዩ አባታችንም እየጸና መሆኑን በማወቃችን እንጽናና። እንዲህ ካደረግን የሚከተለው ጥቅስ ከእኛ ጋር በተያያዘ ሲፈጸም እናያለን፦ “ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ፣ ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ቃል የገባውን የሕይወት አክሊል ይቀበላል።”—ያዕ. 1:12

መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ

^ አን.5 ሁላችንም የተለያዩ ዓይነት ችግሮች ያጋጥሙናል። ብዙዎቹ ችግሮች በአሁኑ ጊዜ መፍትሔ የላቸውም፤ ስለዚህ መጽናት ይኖርብናል። ሆኖም መጽናት የሚያስፈልገን እኛ ብቻ አይደለንም። ይሖዋም ብዙ ነገሮችን በጽናት እያሳለፈ ነው። ይሖዋ መጽናት እንዲያስፈልገው ካደረጉት ነገሮች መካከል ዘጠኙን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። ይሖዋ መጽናቱ ምን መልካም ውጤት እንዳስገኘ እንዲሁም ከእሱ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝም እንመለከታለን።

^ አን.14 “ዝርያ” የሚለው ቃል፣ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጸው “ወገን” ከሚለው ቃል የተለየ ነው፤ “ወገን” የተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታትን ያቀፈ ሰፋ ያለ ቡድንን ያመለክታል።