በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 33

ባገኛችኋቸው መብቶች ተደሰቱ

ባገኛችኋቸው መብቶች ተደሰቱ

“በምኞት ከመቅበዝበዝ ይልቅ ዓይን በሚያየው መደሰት ይሻላል።”—መክ. 6:9

መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች

ማስተዋወቂያ *

1. ብዙዎች በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ያሉት እንዴት ነው?

 ይህ ሥርዓት ወደ መጨረሻው በተቃረበ መጠን የምናከናውነው ብዙ ሥራ አለን። (ማቴ. 24:14፤ ሉቃስ 10:2፤ 1 ጴጥ. 5:2) ሁላችንም አቅማችን በፈቀደ መጠን በይሖዋ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንፈልጋለን። ብዙዎች አገልግሎታቸውን እያሰፉ ነው። አንዳንዶች በአቅኚነት ማገልገል ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ በቤቴል ማገልገል ወይም በቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች ግንባታ መካፈል ይፈልጋሉ። በተጨማሪም በርካታ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት እየተጣጣሩ ነው። (1 ጢሞ. 3:1, 8) ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚያሳዩትን የፈቃደኝነት መንፈስ ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!—መዝ. 110:3፤ ኢሳ. 6:8

2. አንዳንዶቹ መንፈሳዊ ግቦቻችን ላይ ባንደርስ ምን ሊሰማን ይችላል?

2 ይሁንና አንዳንድ መንፈሳዊ ግቦቻችን ላይ ሳንደርስ ረጅም ጊዜ ካለፈ ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በዕድሜያችን ወይም በሌሎች ሁኔታዎች የተነሳ አንዳንድ መብቶችን ማግኘት ባለመቻላችን እናዝን ይሆናል። (ምሳሌ 13:12) ሜሊሳ * እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟታል። ሜሊሳ በቤቴል ማገልገል ወይም በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መካፈል ትፈልጋለች። ሆኖም እንዲህ ብላለች፦ “አሁን ዕድሜዬ ስላለፈ እነዚህን መብቶች ማግኘት አልችልም። በዚህም ምክንያት አልፎ አልፎ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይሰማኛል።”

3. አንዳንድ ክርስቲያኖች ተጨማሪ መብቶች ለማግኘት የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ምን ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል?

3 ወጣትና ጤናማ የሆኑ አንዳንዶች ተጨማሪ መብቶችን ለማግኘት የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት በመንፈሳዊ መጎልመስና አንዳንድ ባሕርያትን ማዳበር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ምናልባትም እነዚህ ወጣቶች ፈጣን አእምሮ ይኖራቸው ይሆናል፤ ውሳኔ ለማድረግም አይቸገሩ ይሆናል፤ እንዲሁም ለማገልገል ጉጉት ይኖራቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ትዕግሥት በማሳየት፣ ሥራቸውን በጥንቃቄ በማከናወንና አክብሮት በማሳየት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። አስፈላጊዎቹን ባሕርያት በማዳበር ላይ ትኩረት ካደረግህ ባልጠበቅኸው ጊዜ፣ የምትፈልገውን የአገልግሎት መብት ልታገኝ ትችላለህ። የኒክን ተሞክሮ እንመልከት። ኒክ በ20 ዓመቱ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ስላልተሾመ በጣም አዝኖ ነበር። ኒክ እንዲህ ብሏል፦ “የሆነ ችግር ቢኖርብኝ ነው ብዬ አሰብኩ።” ሆኖም ኒክ ተስፋ አልቆረጠም። የተከፈቱለትን ሌሎች የአገልግሎት መብቶች ጥሩ አድርጎ ተጠቀመባቸው። በአሁኑ ወቅት የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ ያገለግላል።

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

4 አንድ መንፈሳዊ ግብ ላይ እስካሁን መድረስ አለመቻልህ ተስፋ አስቆርጦሃል? ከሆነ ስሜትህን ለይሖዋ ንገረው። (መዝ. 37:5-7) በተጨማሪም ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት ማሻሻያ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ እንዲጠቁሙህ የጎለመሱ ወንድሞችን ጠይቅ፤ ከዚያም ምክራቸውን በተግባር ለማዋል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። እንዲህ ካደረግህ የፈለግኸውን መብት ልታገኝ ወይም ግብህ ላይ ልትደርስ ትችል ይሆናል። ይሁንና ቀደም ሲል እንደተጠቀሰችው እንደ ሜሊሳ አንተም የምትፈልገው መብት በአሁኑ ጊዜ ጨርሶ ልትደርስበት የማትችለው ቢሆንስ? ደስታህን ሳታጣ መኖር የምትችለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይህ ርዕስ የሚከተሉትን ነጥቦች ያብራራል። (1) ደስታ የሚያስገኘው ምንድን ነው? (2) ደስታህን መጨመር የምትችለው እንዴት ነው? (3) ደስታህን ለመጨመር ምን ዓይነት ግቦች ማውጣት ትችላለህ?

ደስታ የሚያስገኘው ምንድን ነው?

5. ደስተኛ ለመሆን በምን ላይ ማተኮር ይኖርብናል? (መክብብ 6:9)

5 መክብብ 6:9 ደስታ ለማግኘት የሚረዳን ምን እንደሆነ ይናገራል። (ጥቅሱን አንብብ።) ‘ዓይኑ በሚያየው የሚደሰት’ ሰው አሁን ያለውን ነገር ያደንቃል። በምኞት የሚቅበዘበዝ ሰው ግን ሊያገኘው የማይችለውን ነገር ሲመኝ ይኖራል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ደስታ ለማግኘት፣ ባለን ነገር እና ልንደርስበት በምንችለው ግብ ላይ ማተኮር ይኖርብናል።

6. የትኛውን ምሳሌ እንመለከታለን? ይህ ምሳሌስ ምን ያስተምረናል?

6 ይሁንና አሁን ባለን ነገር መርካት በእርግጥ ይቻላል? ብዙዎች የማይቻል ይመስላቸዋል፤ ምክንያቱም ሁላችንም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አዲስ ነገር መሞከር እንፈልጋለን። ሆኖም ባለን ነገር መርካት በእርግጥ የሚቻል ነገር ነው። ዓይናችን በሚያየው ነገር ከልባችን መደሰት እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መልሱን ለማግኘት በማቴዎስ 25:14-30 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ ስለ ታላንቱ የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት። ይህ ምሳሌ አሁን ባሉን በረከቶች መደሰት፣ አልፎ ተርፎም ደስታችንን መጨመር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል።

ደስታህን መጨመር የምትችለው እንዴት ነው?

7. ኢየሱስ ስለ ታላንቱ የሰጠውን ምሳሌ በአጭሩ ግለጽ።

7 በምሳሌው ላይ አንድ ሰው ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ተነሳ። ከመሄዱ በፊት ባሪያዎቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው የሚነግዱበት ታላንት ሰጣቸው። * ሰውየው የባሪያዎቹን ችሎታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለአንዱ ባሪያ አምስት ታላንት፣ ለሌላኛው ባሪያ ሁለት ታላንት፣ ለሦስተኛው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጣቸው። ሁለቱ ባሪያዎች ለጌታቸው ትርፍ ለማስገኘት በትጋት ሠሩ። ሦስተኛው ባሪያ ግን ለጌታው ትርፍ ለማምጣት ምንም ያደረገው ነገር የለም፤ በዚህም ምክንያት ከሥራው ተባረረ።

8. በምሳሌው ላይ የተጠቀሰውን የመጀመሪያውን ባሪያ ሊያስደስተው የሚችል ምን ነገር ነበረ?

8 የመጀመሪያው ባሪያ፣ ጌታው አምስት ታላንት ስለሰጠው ከፍተኛ ክብር ተሰምቶት መሆን አለበት። አምስት ታላንት በጣም ብዙ ገንዘብ ነው። ባሪያው ይህን ያህል ገንዘብ የተሰጠው መሆኑ ጌታው ምን ያህል እንደሚተማመንበት ያሳያል። ይሁንና ስለ ሁለተኛው ባሪያስ ምን ማለት ይቻላል? የመጀመሪያውን ባሪያ ያህል ብዙ ታላንት ስላልተሰጠው ሊያዝን ይችል ነበር። ሆኖም ይህ ባሪያ ምን አደረገ?

በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ከተጠቀሰው ከሁለተኛው ባሪያ ምን ትምህርት እናገኛለን? (1) ጌታው ሁለት ታላንት ሰጠው። (2) ለጌታው ትርፍ ለማስገኘት በትጋት ሠርቷል። (3) የጌታውን ታላንት በእጥፍ አሳድጓል (ከአንቀጽ 9-11⁠ን ተመልከት)

9. ኢየሱስ ስለ ሁለተኛው ባሪያ ምን አላለም? (ማቴዎስ 25:22, 23)

9 ማቴዎስ 25:22, 23ን አንብብ። ኢየሱስ ሁለተኛው ባሪያ፣ ሁለት ታላንት ብቻ ስለተሰጠው እንዳዘነ ወይም በጌታው እንደተበሳጨ አልገለጸም። ኢየሱስ ባሪያው እንዲህ ብሎ እንዳጉረመረመም አልተናገረም፦ ‘ለእኔ የሚሰጠኝ ይሄ ብቻ ነው? እኔ አምስት ታላንት ከተሰጠው ባሪያ በምን አንሼ ነው? የእሱን ያህል ችሎታ አለኝ! ጌታዬ ምን ያህል ዋጋ እንዳለኝ ካልገባው እነዚህን ሁለት ታላንቶች ቀብሬ የራሴን ጉዳይ ባከናውን ይሻለኛል።’

10. ሁለተኛው ባሪያ በተሰጠው ታላንት ምን አደረገ?

10 እንደ መጀመሪያው ባሪያ ሁሉ፣ ሁለተኛው ባሪያም የተሰጠውን ኃላፊነት በቁም ነገር ተመልክቶታል፤ እንዲሁም ጌታውን ለማገልገል አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። በመሆኑም የጌታውን ታላንት በእጥፍ ማሳደግ ችሏል። ይህ ባሪያ በትጋት በመሥራቱ በሚገባ ተክሷል። ጌታው የተደሰተበት ከመሆኑም ሌላ ይህን ባሪያ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንደሆነ አድርጎ ቆጥሮታል!

11. ደስታችን እንዲጨምር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

11 እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ አገልግሎት በተሰጠን በማንኛውም ሥራ ላይ ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ በማሳረፍ ደስታችንን መጨመር እንችላለን። በስብከቱ ሥራ ‘በእጅጉ ተጠመድ’፤ እንዲሁም በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳትፎ አድርግ። (ሥራ 18:5፤ ዕብ. 10:24, 25) በስብሰባዎች ላይ የሚያንጹ ሐሳቦች መስጠት እንድትችል በሚገባ ተዘጋጅ። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ የተሰጠህን ማንኛውንም የተማሪ ክፍል በቁም ነገር ተመልከተው። በጉባኤ ውስጥ አንድ ሥራ ከተሰጠህ ሥራህን በጊዜው አከናውን፤ እንዲሁም እምነት የሚጣልብህ ሁን። በጉባኤ ውስጥ የተሰጠህን የትኛውንም ሥራ ሳትንቅ ጊዜ ሰጥተህ አከናውን። በተመደብክበት ሥራ ችሎታህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 22:29) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና በተሰጡህ ኃላፊነቶች ላይ ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ እንዲያርፍ ካደረግህ እድገትህ ይፋጠናል፤ ደስታህም ይጨምራል። (ገላ. 6:4) በተጨማሪም አንተ ለማግኘት የምትመኘውን መብት ሌሎች ሰዎች ቢያገኙ ከእነሱ ጋር አብረህ መደሰት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።—ሮም 12:15፤ ገላ. 5:26

12. ሁለት ክርስቲያኖች ደስታቸውን ለመጨመር ምን አድርገዋል?

12 በቤቴል ለማገልገል ወይም በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል ትጓጓ የነበረችውን የሜሊሳን ምሳሌ በድጋሚ እንመልከት። ሜሊሳ እነዚህን መብቶች ማግኘት ባትችልም እንዲህ ብላለች፦ “በአቅኚነት አገልግሎቴ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግና በሁሉም ዓይነት የአገልግሎት ዘርፎች ለመካፈል ጥረት አደርጋለሁ። ይህም ታላቅ ደስታ አስገኝቶልኛል።” የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ባለመሾሙ ምክንያት አዝኖ የነበረው ኒክስ ምን አደረገ? እንዲህ ብሏል፦ “ማድረግ በምችለው ነገር ላይ ለምሳሌ በአገልግሎት በመካፈልና በስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያለው ሐሳብ በመስጠት ላይ ትኩረት አደረግኩ። በተጨማሪም ለቤቴል አገልግሎት አመለከትኩ፤ የሚገርመው ልክ በቀጣዩ ዓመት ተጠራሁ።”

13. አሁን ባለህ ኃላፊነት ላይ ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ እንዲያርፍ ማድረግህ ምን ያስገኝልሃል? (መክብብ 2:24)

13 አሁን ባለህ ኃላፊነት ላይ ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ እንዲያርፍ ካደረግህ ወደፊት ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ታገኛለህ ማለት ነው? ሊሆን ይችላል፤ የኒክ ሁኔታ ይህን ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ መብቶችን ባታገኝም እንኳ እንደ ሜሊሳ ደስታህ እንዲጨምር ማድረግ ትችላለህ፤ እንዲሁም ከፍተኛ እርካታ ታገኛለህ። (መክብብ 2:24ን አንብብ።) በተጨማሪም የምታደርገው ጥረት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያስደስተው ማወቅህ በእጅጉ ያስደስትሃል።

ደስታችንን ለመጨመር የሚረዱ ግቦች

14. ከመንፈሳዊ ግቦች ጋር በተያያዘ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

14 አሁን ባሉን መብቶች ላይ ትኩረት እናደርጋለን ሲባል ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት ለማስፋት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለግ እናቆማለን ማለት ነው? በፍጹም! በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እንዲሁም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይበልጥ ለመርዳት የሚያስችሉንን መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት እንችላለን፤ እንዲህ ማድረግም ይኖርብናል። ልካችንን በማወቅ በራሳችን ላይ ሳይሆን ሌሎችን በማገልገል ላይ ትኩረት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ከመሆኑም ሌላ ግቦቻችን ላይ ለመድረስ ይረዳናል።—ምሳሌ 11:2፤ ሥራ 20:35

15. ደስታህን ለመጨመር የሚረዱህ አንዳንድ ግቦች የትኞቹ ናቸው?

15 የትኞቹን ግቦች ማውጣት ትችላለህ? ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች ለማስተዋል እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። (ምሳሌ 16:3፤ ያዕ. 1:5)  በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ እንደተገለጸው ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚ ለመሆን፣ በቤቴል ለማገልገል ወይም በቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች ግንባታ ለመካፈል ግብ ማውጣት ትችል ይሆን? አሊያም ደግሞ ምሥራቹን ለማስፋፋት አልፎ ተርፎም በሌላ አገር ለማገልገል አዲስ ቋንቋ መማር ትችል ይሆናል። ስለ እነዚህ ግቦች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 መመልከት ወይም ከጉባኤህ ሽማግሌዎች ጋር መነጋገር ትችላለህ። * እንደ እነዚህ ያሉ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ እድገትህ በግልጽ ይታያል፤ ደስታህም ይጨምራል።

16. በአሁኑ ወቅት አንድ ግብ ላይ መድረስ ባትችል ምን ማድረግ ትችላለህ?

16 ይሁንና ቀደም ሲል የተጠቀሱት ግቦች ላይ በአሁኑ ወቅት መድረስ ባትችልስ? ልትደርስበት የምትችለው ሌላ ግብ ለማውጣት ሞክር። እስቲ አንዳንድ አማራጮችን እንመልከት።

ልትደርስበት የምትችለው ግብ የትኛው ነው? (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት) *

17. በ1 ጢሞቴዎስ 4:13, 15 መሠረት አንድ ወንድም የማስተማር ችሎታውን ማሻሻል የሚችለው እንዴት ነው?

17 አንደኛ ጢሞቴዎስ 4:13, 15ን አንብብ። የተጠመቅህ ወንድም ከሆንክ የመናገር እና የማስተማር ችሎታህን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ትችል ይሆናል። ይህን ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? ምክንያቱም በማንበብ፣ በመናገርና በማስተማር ላይ ‘ትኩረትህን ሙሉ በሙሉ ማሳረፍህ’ አድማጮችህን ይጠቅማቸዋል። ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ በሚለው ብሮሹር ላይ ያሉትን የንግግር ባሕርያት በሙሉ ለማጥናትና በእያንዳንዱ የንግግር ባሕርይ ላይ ለመሥራት ግብ ማውጣት ትችላለህ። አንዱን የንግግር ባሕርይ መርጠህ ካጠናህ በኋላ ቤት ውስጥ በትጋት ተለማመደው፤ ከዚያም ንግግር ስታቀርብ በዚያ የንግግር ባሕርይ ላይ ለመሥራት ጥረት አድርግ። ረዳት ምክር ሰጪውን ወይም “በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ” ሌሎች ሽማግሌዎችን ምክር ጠይቅ። * (1 ጢሞ. 5:17) የንግግር ባሕርዩን በማዳበር ላይ ብቻ ሳይሆን አድማጮችህ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ በመርዳት ወይም አንድን እርምጃ እንዲወስዱ በማበረታታት ላይ ትኩረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ የአንተም ሆነ የአድማጮችህ ደስታ ይጨምራል።

ልትደርስበት የምትችለው ግብ የትኛው ነው? (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት) *

18. በአገልግሎት ረገድ ያወጣናቸው ግቦች ላይ ለመድረስ ምን ይረዳናል?

18 ሁላችንም የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሮም 10:14) በዚህ በጣም አስፈላጊ ሥራ ረገድ ክህሎትህን ማዳበር ትፈልጋለህ? ማስተማር የተባለውን ብሮሹር አጥና፤ እንዲሁም ያገኘኸውን ትምህርት በሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ ግቦች አውጣ። ከዚህም ሌላ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ እንዲሁም በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ በሚታዩት የውይይት ናሙና ቪዲዮዎች ላይ ተጨማሪ ሐሳቦችን ማግኘት ትችላለህ። ውጤታማ የሆነውን ዘዴ ለማግኘት የተለያዩ አማራጮችን ሞክር። እነዚህን ሐሳቦች በሥራ ላይ ማዋልህ የተዋጣልህ አስተማሪ ለመሆን ይረዳሃል፤ ይህ ደግሞ ታላቅ ደስታ ያስገኝልሃል።—2 ጢሞ. 4:5

ልትደርስበት የምትችለው ግብ የትኛው ነው? (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት) *

19. ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

19 ልታወጣ ከምትችላቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ግቦች መካከል አንዱ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር ነው። (ገላ. 5:22, 23፤ ቆላ. 3:12፤ 2 ጴጥ. 1:5-8) እዚህ ግብ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ጠንካራ እምነት ለማዳበር ግብ አወጣህ እንበል። እምነትህን ለማጠናከር የሚረዱ ሐሳቦችን የሚሰጡ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ ርዕሶችን ማንበብ ትችላለህ። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የተለያየ ፈተና ሲያጋጥማቸው አስደናቂ እምነት ያሳዩት እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ በ​JW ብሮድካስቲንግ ላይ የወጡ ቪዲዮዎችን መመልከትህም ይጠቅምሃል። ከዚያም እምነታቸውን መኮረጅ የምትችልባቸውን መንገዶች አስብ።

20. ደስታችንን መጨመር እና የምንፈልገውን መብት አለማግኘት የሚያስከትለውን ሐዘን መቀነስ የምንችለው እንዴት ነው?

20 ሁላችንም በይሖዋ አገልግሎት አሁን ከምናከናውነው ይበልጥ ማከናወን ብንችል ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል እንችላለን። እስከዚያው ድረስ ግን በተከፈቱልን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም ደስታችንን መጨመር እንዲሁም የምንፈልገውን መብት አለማግኘት የሚያስከትለውን ሐዘን መቀነስ እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘ለደስተኛው አምላካችን’ ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ እናመጣለን። (1 ጢሞ. 1:11) እንግዲያው አሁን ባሉን መብቶች እንደሰት!

መዝሙር 82 “ብርሃናችሁ ይብራ”

^ አን.5 ይሖዋን በጣም እንወደዋለን፤ እንዲሁም በእሱ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። በመሆኑም አገልግሎታችንን ለማስፋት እንፈልግ ወይም በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ መብቶችን ለማግኘት እንጣጣር ይሆናል። ይሁንና የምንችለውን ያህል ብንጥርም እንኳ አንዳንድ ግቦች ላይ መድረስ ባንችልስ? በይሖዋ አገልግሎት መጠመድና ደስታችንን ሳናጣ መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ ታላንቱ በሰጠው ምሳሌ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እናገኛለን።

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.7 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ አንድ ታላንት አንድ ሠራተኛ 20 ዓመት ሙሉ ሠርቶ ከሚያገኘው ደሞዝ ጋር ተቀራራቢ ዋጋ አለው።

^ አን.15 የተጠመቁ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ እና ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች እንዲያሟሉ ይበረታታሉ። ስለ እነዚህ ብቃቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 እና 6 ተመልከት።

^ አን.17 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ረዳት ምክር ሰጪ፣ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ክፍሎችንና የሕዝብ ንግግሮችን ለሚያቀርቡ እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለሚመሩ ወይም በእነዚህ ወቅቶች ለሚያነቡ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በግል ምክር የመስጠት ኃላፊነት የተሰጠው ሽማግሌ ነው።

^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የማስተማር ችሎታውን ለማሻሻል ያወጣው ግብ ላይ ለመድረስ በጽሑፎቻችን ተጠቅሞ ምርምር ሲያደርግ።

^ አን.66 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ግብ ካወጣች በኋላ ለአንዲት አስተናጋጅ የአድራሻ ካርድ ስትሰጥ።

^ አን.68 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማሳየት ስለፈለገች ለእምነት ባልንጀራዋ ባልጠበቀችው ጊዜ ስጦታ ስትሰጣት።