በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 34

የይሖዋን ጥሩነት “ቅመሱ”—እንዴት?

የይሖዋን ጥሩነት “ቅመሱ”—እንዴት?

“ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው።”—መዝ. 34:8

መዝሙር 117 ጥሩነት

ማስተዋወቂያ *

1-2. በመዝሙር 34:8 መሠረት ስለ ይሖዋ ጥሩነት መማር የምንችለው እንዴት ነው?

አንድ ሰው ከዚህ ቀደም ቀምሰኸው የማታውቀውን ምግብ አቀረበልህ እንበል። ምግቡን በማየት፣ በማሽተት፣ እንዴት እንደተሠራ በመጠየቅ ወይም ምግቡን የቀመሱ ሰዎች ምን እንደተሰማቸው በመጠየቅ ስለ ምግቡ የተወሰነ መረጃ ማግኘት ትችላለህ። ሆኖም ምግቡ የምትወደው ዓይነት መሆኑን ማረጋገጥ የምትችለው ራስህ ከቀመስከው ብቻ ነው።

2 እኛም መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ጽሑፎቻችንን በማንበብ እንዲሁም ሌሎች ከይሖዋ ስላገኙት በረከት ሲናገሩ በመስማት ስለ ይሖዋ ጥሩነት የተወሰነ ነገር ማወቅ እንችላለን። ሆኖም ስለ ይሖዋ ጥሩነት ከሁሉ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት የምንችለው ጥሩነቱን ራሳችን ‘ስንቀምስ’ ነው። (መዝሙር 34:8ን አንብብ።) እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ እንመልከት። በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል አስበሃል እንበል። እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ ግን ኑሮህን ቀላል ማድረግ ይጠበቅብሃል። ምናልባትም የአምላክን መንግሥት ካስቀደምክ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር በሙሉ እንደሚያሟላልህ ኢየሱስ የገባውን ቃል ብዙ ጊዜ አንብበኸው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ቃል በአንተ ሕይወት ሲፈጸም አላየህም። (ማቴ. 6:33) ያም ቢሆን ኢየሱስ በገባው ቃል ላይ እምነት በማሳደር ወጪህንና የሥራ ሰዓትህን ቀነስክ፤ እንዲሁም በአገልግሎትህ ላይ ትኩረት አደረግክ። እንዲህ ስታደርግ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚያሟላልህ በራስህ ሕይወት ማየት ትችላለህ። በዚህ መንገድ የይሖዋን ጥሩነት ‘ትቀምሳለህ።’

3. በመዝሙር 16:1, 2 መሠረት ይሖዋ ጥሩነት የሚያሳየው ለእነማን ነው?

3 “ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው”፤ ለማያውቁትም ሰዎች ጭምር ማለት ነው። (መዝ. 145:9፤ ማቴ. 5:45) በተለይ ግን ይሖዋ የሚወዱትንና በሙሉ ነፍሳቸው የሚያገለግሉትን ሰዎች አብዝቶ ይባርካቸዋል። (መዝሙር 16:1, 2ን አንብብ።) ይሖዋ ካደረገልን ጥሩ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

4. ይሖዋ ሰዎች ወደ እሱ መቅረብ ሲጀምሩ ጥሩነቱን የሚያሳያቸው እንዴት ነው?

4 ከይሖዋ የምናገኘውን ትምህርት በሥራ ላይ ባዋልን ቁጥር፣ እንዲህ ማድረጋችን የሚያስገኘውን መልካም ውጤት በሕይወታችን ማየት እንችላለን። ስለ ይሖዋ እየተማርንና እሱን እየወደድነው በመጣን መጠን፣ ይሖዋ ከእሱ የሚያርቁንን አስተሳሰቦችና ልማዶች እንድናስወግድ ረድቶናል። (ቆላ. 1:21) ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ስንጠመቅ ደግሞ ንጹሕ ሕሊና እና ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት የመመሥረት መብት ስለሰጠን ጥሩነቱን ይበልጥ ማየት ችለናል።—1 ጴጥ. 3:21

5. በአገልግሎታችን የይሖዋን ጥሩነት የምንመለከተው እንዴት ነው?

5 በአገልግሎት ስንካፈል የይሖዋን ጥሩነት የምንመለከትበት ተጨማሪ አጋጣሚ እናገኛለን። በተፈጥሮህ ዓይናፋር ነህ? በርካታ የይሖዋ ሕዝቦች ዓይናፋር ናቸው። የይሖዋ ምሥክር ከመሆንህ በፊት፣ ጨርሶ የማታውቀውን ሰው በር አንኳኩተህ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ያልሆነ መልእክት መናገር እንደምትችል ፈጽሞ አስበህ አታውቅ ይሆናል። አሁን ግን አዘውትረህ ይህን ታደርጋለህ። እንዲያውም በይሖዋ እርዳታ የስብከቱን ሥራ በጣም ወደኸዋል! የይሖዋን እርዳታ በተለያዩ መንገዶች ማየት ችለሃል። ተቃዋሚ ሲያጋጥምህ እንድትረጋጋ ረድቶሃል። በተጨማሪም ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ልባቸውን የሚነካ ጥቅስ አስታውሰህ እንድታነብላቸው ረድቶሃል። ከዚህም ሌላ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ግዴለሽ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሙህ በሥራው ለመቀጠል የሚያስፈልግህን ብርታት ሰጥቶሃል።—ኤር. 20:7-9

6. ይሖዋ የሚሰጠን ሥልጠና ጥሩነቱን የሚያሳየው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ለአገልግሎት የሚያስፈልገንን ሥልጠና በመስጠትም ጥሩነቱን አሳይቶናል። (ዮሐ. 6:45) በሳምንቱ መሃል ስብሰባችን ላይ የታሰበባቸው የውይይት ናሙናዎች እንሰማለን፤ በአገልግሎት ላይ እንድንጠቀምባቸውም እንበረታታለን። አዲስ ነገር መሞከር መጀመሪያ ላይ ሊያስፈራን ይችላል፤ ስንሞክረው ግን አዲሱ ዘዴ በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎችን እንደሚማርክ ልንገነዘብ እንችላለን። ከዚህም ሌላ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንድንካፈል በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንበረታታለን፤ ከእነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች መካከል አንዳንዶቹን ከዚህ በፊት ሞክረናቸው አናውቅ ይሆናል። ይህም ቢሆን ያልለመድነውን ነገር መሞከር ይጠይቅብናል፤ እንዲህ ስናደርግ ግን ይሖዋ እንዲባርከን አጋጣሚ እንሰጠዋለን። ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ለይሖዋ ምርጣችንን ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ ዘዴዎችን ስንሞክር የምናገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች እስቲ እንመልከት። ከዚያም አገልግሎታችንን ማስፋት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እናያለን።

ይሖዋ የሚታመኑበትን ይባርካቸዋል

7. አገልግሎታችንን ለማስፋት ጥረት ስናደርግ ምን በረከት እናገኛለን?

7 ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን። ከባለቤቱ ጋር በኮሎምቢያ የሚያገለግለውን ሳሙኤል * የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሳሙኤል እና ባለቤቱ በጉባኤያቸው ውስጥ የዘወትር አቅኚዎች ነበሩ፤ ሆኖም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ጉባኤ በመዛወር አገልግሎታቸውን ለማስፋት ፈለጉ። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ አንዳንድ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ ነበረባቸው። ሳሙኤል እንዲህ ብሏል፦ “ማቴዎስ 6:33⁠ን ተግባራዊ ያደረግን ከመሆኑም ሌላ የማያስፈልጉንን ነገሮች መግዛት አቆምን። ከሁሉ ይበልጥ የከበደን ግን የምንኖርበትን አፓርታማ ትተን መሄድ ነበር። አፓርታማው ልክ በምንፈልገው መንገድ የተሠራ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ የቤቱ ዕዳ ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ ነበር።” ባልና ሚስቱ በአዲሱ ምድባቸው ማገልገል ሲጀምሩ ከቀድሞ ገቢያቸው አንድ ስድስተኛ የሚሆነው ለኑሮ እንደሚበቃቸው አስተዋሉ። ሳሙኤል እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሲመራንና ጸሎታችንን ሲመልስልን ተመልክተናል። ከዚህ በፊት አይተን በማናውቀው መንገድ ሞገሱንና ፍቅሩን አይተናል።” አንተስ አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? እንዲህ ካደረግህ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደምትቀርብና የእሱ እንክብካቤ እንደማይለይህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—መዝ. 18:25

8. ኢቫን እና ቪክቶሪያ ከተናገሩት ሐሳብ ምን እንማራለን?

8 በአገልግሎታችን ደስታ እናገኛለን። በኪርጊስታን በአቅኚነት የሚያገለግሉት ኢቫን እና ቪክቶሪያ የተባሉ ባልና ሚስት ምን እንዳሉ እንመልከት። የግንባታ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ለየትኛውም የአገልግሎት ምድብ ራሳቸውን ለማቅረብ ሲሉ ኑሯቸውን ቀላል አድርገው ነበር። ኢቫን እንዲህ ብሏል፦ “በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ ከልባችን እንሠራ ነበር። ስንሠራ ውለን ምሽት ላይ ቢደክመንም ጉልበታችንን ያዋልነው በመንግሥቱ ሥራ ላይ እንደሆነ ስለምናውቅ ሰላምና እርካታ እናገኛለን። በተጨማሪም ብዙ አዲስ ጓደኞች በማፍራታችን እና በርካታ አስደሳች ትዝታዎችን በማግኘታችን በጣም ተደስተናል።”—ማር. 10:29, 30

9. በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አንዲት እህት አገልግሎታቸውን ለማስፋት ምን አድርገዋል? ምን ውጤትስ አግኝተዋል?

9 በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ በይሖዋ አገልግሎት ደስታ ማግኘት እንችላለን። በምዕራብ አፍሪካ የሚኖሩትን ሚሬ የተባሉ መበለት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እህት ሚሬ ከሕክምና ሙያቸው ጡረታ ከወጡ በኋላ አቅኚነት ጀመሩ። እህት ሚሬ ከባድ አርትራይትስ ስላለባቸው ረጅም መንገድ መጓዝ አይችሉም፤ በመሆኑም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ከአንድ ሰዓት በላይ መሳተፍ አይችሉም። ሆኖም በአደባባይ ምሥክርነት ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ ይችላሉ። እህት ሚሬ በርካታ ተመላልሶ መጠየቆችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሏቸው፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን የሚያነጋግሯቸው በስልክ ነው። እህት ሚሬ እንዲህ ያለ ጥረት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? እንዲህ ብለዋል፦ “ልቤ ለይሖዋና ለክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ ፍቅር ተሞልቷል። በተጨማሪም ይሖዋ በእሱ አገልግሎት አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ እንዳደርግ እንዲረዳኝ አዘውትሬ በጸሎት እለምነዋለሁ።”—ማቴ. 22:36, 37

10. አንደኛ ጴጥሮስ 5:10 እንደሚያሳየው አገልግሎታቸውን ለማስፋት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ከይሖዋ ምን ያገኛሉ?

10 ከይሖዋ ተጨማሪ ሥልጠና እናገኛለን። በሞሪሸስ የሚኖር ኬኒ የተባለ አቅኚ ይህ እውነት መሆኑን ተመልክቷል። ኬኒ እውነትን ሲሰማ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋረጠ፤ ከዚያም ተጠምቆ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባ። እንዲህ ብሏል፦ “‘እነሆኝ! እኔን ላከኝ!’ በማለት እንደተናገረው እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ዓይነት አመለካከት ለመያዝ ጥረት አደርጋለሁ።” (ኢሳ. 6:8) ኬኒ በበርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ተካፍሏል፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋው በመተርጎሙ ሥራ እገዛ አበርክቷል። ኬኒ “ሥራዬን ለማከናወን የሚያስፈልጉኝን ክህሎቶች ለማዳበር ሥልጠና አግኝቻለሁ” ብሏል። ሆኖም ያገኘው ከሥራው ጋር የተያያዘ ሥልጠና ብቻ አይደለም። ኬኒ እንዲህ ብሏል፦ “በየትኞቹ ነገሮች ረገድ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገኝ እንዲሁም የተሻለ የይሖዋ አገልጋይ ለመሆን የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።” (1 ጴጥሮስ 5:10ን አንብብ።) አንተም ከይሖዋ ተጨማሪ ሥልጠና እንድታገኝ በሕይወትህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችል ይሆን?

አንድ ባልና ሚስት፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ሲሰብኩ፤ አንዲት ወጣት እህት በስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ስትካፈል፤ በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት በስልክ ምሥክርነት ሲሰጡ። ሁሉም በአገልግሎታቸው በጣም ደስተኞች ናቸው (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ እህቶች በአገልግሎት ለመካፈል ምን ጥረት አድርገዋል? ምን ውጤትስ አገኙ? (ሽፋኑን ተመልከት።)

11 ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖችም ጭምር አዲስ ዓይነት የአገልግሎት መስክ ሲሞክሩ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በደቡብ ኮሪያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ያሉ ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፦ “በጤናቸው ምክንያት በመስክ አገልግሎት መካፈል እንደማይችሉ ይሰማቸው የነበሩ አንዳንዶች አሁን በቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ አማካኝነት ይሰብካሉ። በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሦስት እህቶች ይህን አዲስ ቴክኖሎጂ የተማሩ ሲሆን በየዕለቱ ማለት ይቻላል በዚህ የአገልግሎት ዘዴ ተጠቅመው ማገልገል ችለዋል።” (መዝ. 92:14, 15) አንተስ አገልግሎትህን ማስፋትና የይሖዋን ጥሩነት ይበልጥ ማጣጣም ትፈልጋለህ? እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ልትወስዳቸው የምትችላቸውን አንዳንድ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።

አገልግሎትህን ለማስፋት ምን ይረዳሃል?

12. ይሖዋ በእሱ ለሚታመኑ ሰዎች ምን ቃል ገብቷል?

12 በይሖዋ መታመንን ተማር። ይሖዋ በእሱ ከታመንን እና ምርጣችንን ከሰጠነው የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልን ቃል ገብቷል። (ሚል. 3:10) በኮሎምቢያ የምትኖር ፋቢዮላ የተባለች አንዲት እህት ይሖዋ በዚህ ረገድ የገባውን ቃል ሲፈጽም ተመልክታለች። ከተጠመቀች ብዙም ሳትቆይ የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ፈልጋ ነበር። ሆኖም ከባለቤቷ ጋር ሆና ሦስት ልጆቿን ለማሳደግ የእሷም ገቢ ያስፈልጋቸው ነበር። ጡረታ መውጣት የምትችልበት ዕድሜ ላይ ስትደርስ ግን ይሖዋ እንዲረዳት አጥብቃ ለመነችው። እንዲህ ብላለች፦ “አብዛኛውን ጊዜ የጡረታ መብት ለማስከበር ረጅም ጊዜ ይወስዳል፤ እኔ ግን ማመልከቻ ባስገባሁ በአንድ ወር ውስጥ ተፈቀደልኝ። ተአምር እንደተፈጸመ ነበር የተሰማኝ!” ፋቢዮላ ከሁለት ወራት በኋላ በአቅኚነት ማገልገል ጀመረች። አሁን በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ትገኛለች። ከ20 ዓመት በላይ በአቅኚነት ስታገለግል ቆይታለች። በዚህ ጊዜ ውስጥ ስምንት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው እንዲጠመቁ ረድታለች። እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ቢደክመኝም ይሖዋ በአቅኚነት እንድቀጥል በየዕለቱ እየረዳኝ ነው።”

አብርሃምና ሣራ፣ ያዕቆብ እንዲሁም የዮርዳኖስን ወንዝ የተሻገሩት ካህናት በይሖዋ እንደሚተማመኑ ያሳዩት እንዴት ነው? (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13-14. በይሖዋ ታምነን አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚረዱ ተሞክሮዎችን የት ማግኘት እንችላለን?

13 በይሖዋ ከታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ተሞክሮ ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት የተካፈሉ በርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዟል። አብዛኞቹን ሰዎች ይሖዋ ልዩ በሆነ መንገድ የባረካቸው በእሱ እንደሚታመኑ የሚያሳይ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነው። ለምሳሌ አብርሃምን ይሖዋ የባረከው “ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም” ይኖርበት የነበረውን ስፍራ ለቆ ከወጣ በኋላ ነው። (ዕብ. 11:8) ያዕቆብም ልዩ በረከት ያገኘው ከመልአኩ ጋር ከታገለ በኋላ ነው። (ዘፍ. 32:24-30) የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገባ በተቃረበበት ጊዜ ደግሞ ሕዝቡ የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር የቻሉት ካህናቱ በኃይል ወደሚፈሰው ወንዝ እግራቸውን ካስገቡ በኋላ ነበር።—ኢያሱ 3:14-16

14 በይሖዋ ታምነው አገልግሎታቸውን ለማስፋት ጥረት ካደረጉ በዘመናችን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ብዙ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ። ፓይተን የተባለ ወንድም እና ባለቤቱ ዳያና፣ አገልግሎታቸውን ስላሰፉ ወንድሞችና እህቶች የሚናገሩ ተሞክሮዎችን ለምሳሌ “ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል” * በሚለው ዓምድ ሥር የተጠቀሱ ታሪኮችን ማንበብ ያስደስታቸዋል። ፓይተን እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎችን ስናነብ ጣፋጭ ምግብ እየተመገበ ያለን ሰው እንደምንመለከት ሆኖ ይሰማን ነበር። መመልከታችንን ስንቀጥል እኛም ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰን ለማየት’ ጓጓን።” ከጊዜ በኋላ ፓይተን እና ዳያና የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛወሩ። አንተስ “ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡ ተሞክሮዎችን አንብበሃቸዋል? በ​jw.org ላይ የወጡትን ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች መስበክ—አውስትራሊያ እና ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች መስበክ—አየርላንድ የሚሉትን ቪዲዮዎችስ ተመልክተሃል? እነዚህ ተሞክሮዎች አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልባቸውን መንገዶች እንድታስብ ይረዱሃል።

15. ጥሩ ወዳጆች የሚረዱን እንዴት ነው?

15 ግብህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህ ጓደኞች ምረጥ። አንድን ምግብ በጣም ከሚወዱ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፋችን እኛም ያንን ምግብ እንድንሞክረው ያነሳሳናል። በተመሳሳይም በሕይወታቸው ውስጥ ይሖዋን ከሚያስቀድሙ ሰዎች ጋር የምንወዳጅ ከሆነ እኛም አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚያስችሉንን መንገዶች ለመፈለግ መነሳሳታችን አይቀርም። ኬንት እና ቬሮኒካ የተባሉ ባልና ሚስት ይህ እውነት መሆኑን በሕይወታቸው ተመልክተዋል። ኬንት እንዲህ ብሏል፦ “ጓደኞቻችን እና ቤተሰቦቻችን አዳዲስ የአገልግሎት መስኮችን እንድንሞክር ያበረታቱን ነበር። የአምላክን መንግሥት ከሚያስቀድሙ ሰዎች ጋር መቀራረባችን እኛም አዲስ ነገር እንድንሞክር አደፋፍሮናል።” ኬንት እና ቬሮኒካ በአሁኑ ወቅት ሰርቢያ ውስጥ ልዩ አቅኚዎች ሆነው እያገለገሉ ነው።

16. ኢየሱስ በሉቃስ 12:16-21 ላይ የተናገረው ምሳሌ እንደሚያሳየው መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

16 ለይሖዋ ስትል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ሁን። ይሖዋን ለማስደሰት፣ የምንወደውን ነገር ሁሉ መሥዋዕት ማድረግ አለብን ማለት አይደለም። (መክ. 5:19, 20) ሆኖም የምንወደውን ነገር መሥዋዕት ማድረግ ስለማንፈልግ ብቻ በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ነገር ከማድረግ ወደኋላ ካልን ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ሰው የሠራውን ዓይነት ስህተት ልንፈጽም እንችላለን፤ ይህ ሰው የተመቻቸ ሕይወት ለመምራት ጥረት ሲያደርግ አምላክን ችላ ብሏል። (ሉቃስ 12:16-21ን አንብብ።) ክርስቲያን የተባለ በፈረንሳይ የሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋና ለቤተሰቤ ጊዜዬንና ጉልበቴን በበቂ መጠን እየሰጠሁ አልነበረም።” ከጊዜ በኋላ ግን እሱና ባለቤቱ አቅኚ ለመሆን ወሰኑ። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ግን ሥራቸውን መልቀቅ ነበረባቸው። ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር በጽዳት ሥራ መካፈል ጀመሩ፤ እንዲሁም በትንሽ ገንዘብ ረክቶ መኖርን ተማሩ። ታዲያ ይህን መሥዋዕት በመክፈላቸው ተክሰዋል? ክርስቲያን እንዲህ ብሏል፦ “አሁን አገልግሎታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኗል። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እና ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግላቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ ሲማሩ በማየት እንደሰታለን።”

17. በአገልግሎታችን አዲስ ነገር ከመሞከር ወደኋላ እንድንል የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

17 አዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎችን ለመሞከር ፈቃደኛ ሁን። (ሥራ 17:16, 17፤ 20:20, 21) በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሸርሊ የተባለች አቅኚ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በአገልግሎቷ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነበረባት። መጀመሪያ ላይ የስልክ ምሥክርነት ለመስጠት አመንትታ ነበር። በወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ወቅት ሥልጠና ካገኘች በኋላ ግን አዘውትራ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል ጀመረች። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ያስፈራ ነበር፤ አሁን ግን በጣም ወድጄዋለሁ። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ከምናገኘው በላይ ብዙ ሰዎችን እያገኘን ነው!”

18. አገልግሎታችንን ለማስፋት ጥረት ስናደርግ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ምን ይረዳናል?

18 ዕቅድ አውጣ እንዲሁም በዕቅድህ ተመራ። ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ እንዲረዳን እንጸልያለን፤ እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታችንን ተጠቅመን ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ዕቅድ እናወጣለን። (ምሳሌ 3:21) አውሮፓ ውስጥ በሮማኒ ቋንቋ ቡድን የምታገለግል ሶንያ የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ዕቅዶቼን በወረቀት ላይ ጽፌ ወረቀቱን ፊት ለፊት አስቀምጠዋለሁ። ጠረጴዛዬ ላይ የመስቀለኛ መንገድ ሥዕል አለ። ውሳኔ የሚፈልግ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ ያንን መስቀለኛ መንገድ እመለከትና ውሳኔዬ ወደ የትኛው አቅጣጫ እንደሚወስደኝ ቆም ብዬ አስባለሁ።” ሶንያ ስለሚያጋጥሟት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት ታደርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “የሚያጋጥመኝ እያንዳንዱ ሁኔታ እንቅፋት ሊሆንብኝ ወይም ደግሞ እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ሊሆንልኝ ይችላል፤ ይህ የተመካው በአመለካከቴ ላይ ነው።”

19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

19 ይሖዋ በብዙ መንገዶች ይባርከናል። ለእሱ ክብር ለማምጣት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ለይሖዋ በረከቶች አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። (ዕብ. 13:15) ይህም አገልግሎታችንን ማስፋት የምንችልባቸውን አዳዲስ መንገዶች መፈለግን ሊጨምር ይችላል፤ እንዲህ ስናደርግ ደግሞ ተጨማሪ በረከቶች እናገኛለን። እንግዲያው ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰን ማየት’ የምንችልባቸውን መንገዶች በየቀኑ እንፈልግ። እንደዚያ ካደረግን እኛም እንደ ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” ማለት እንችላለን።—ዮሐ. 4:34

መዝሙር 80 “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”

^ አን.5 ይሖዋ የጥሩ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ነው። ለሁሉም ሰው፣ ለክፉ ሰዎች እንኳ ሳይቀር ጥሩ ነገሮችን ይሰጣል። በተለይ ግን ለታማኝ አገልጋዮቹ ጥሩ ነገሮችን ማድረግ ያስደስተዋል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ጥሩነቱን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም አገልግሎታቸውን የሚያሰፉ ክርስቲያኖች የይሖዋን ጥሩነት ልዩ በሆነ መንገድ የሚያጣጥሙት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

^ አን.7 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.14 ቀደም ሲል መጠበቂያ ግንብ ላይ ይወጣ የነበረው ይህ ዓምድ አሁን jw.org ላይ ይገኛል። ስለ እኛ > ተሞክሮዎች > መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ በሚለው ሥር ተመልከት።