በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 36

የወጣቶችን ጉልበት አድንቁ

የወጣቶችን ጉልበት አድንቁ

“የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው።”—ምሳሌ 20:29

መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ

ማስተዋወቂያ *

1. ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ምን ግብ ማውጣት እንችላለን?

ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ‘በአንድ ወቅት አደርገው የነበረውን ያህል በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት አልችልም’ የሚል ስጋት ያድርብን ይሆናል። የቀድሞውን ያህል ጉልበት እንደማይኖረን ባይካድም ያካበትነውን ጥበብና ተሞክሮ ተጠቅመን ወጣቶች ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ እንዲያገለግሉ እንዲሁም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን እንዲሸከሙ ልናሠለጥናቸው እንችላለን። ለረጅም ዓመታት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በዕድሜ መግፋት የተነሳ አቅሜ እንደተገደበ በተሰማኝ ጊዜ ሥራውን ተረክበው ማከናወን የሚችሉ ብቃት ያላቸው ወጣት ወንድሞች በመኖራቸው ተደስቼ ነበር።”

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 ወጣቶች በዕድሜ ከገፉ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረባቸው እንዴት እንደሚጠቅማቸው ባለፈው ርዕስ ላይ ተመልክተን ነበር። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች እንደ ትሕትና፣ ልክን ማወቅ፣ አመስጋኝነትና ልግስና ያሉ ባሕርያትን ማዳበራቸው ከወጣቶች ጋር ለመሥራት እንዴት እንደሚረዳቸው እንመለከታለን። በዚህ መልኩ ተባብረው መሥራታቸው ለመላው ጉባኤ ጥቅም ያስገኛል።

ትሑት ሁኑ

3. በፊልጵስዩስ 2:3, 4 መሠረት ትሕትና ምንድን ነው? አንድ ክርስቲያን ትሕትናን ማዳበሩ የሚረዳውስ እንዴት ነው?

3 አረጋውያን ወጣቶችን መርዳት ከፈለጉ ትሑት መሆን አለባቸው። ትሑት የሆነ ሰው ሌሎች ከእሱ እንደሚበልጡ አድርጎ ያስባል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4ን አንብብ።) ትሑት የሆኑ አረጋውያን አንድን ነገር ማከናወን የሚቻልባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊና ውጤታማ የሆኑ በርካታ መንገዶች እንዳሉ ይገነዘባሉ። በመሆኑም ሁሉም ሰው ነገሮችን እነሱ ድሮ ያከናውኑ በነበረበት መንገድ መሥራት እንዳለበት አይሰማቸውም። (መክ. 7:10) ለወጣቱ ትውልድ ሊያካፍሉ የሚችሉት ብዙ ጠቃሚ ተሞክሮ ቢኖራቸውም “የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ” በመሆኑ አዳዲስ አሠራሮችን መልመድ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይገነዘባሉ።—1 ቆሮ. 7:31

አረጋውያን ተሞክሯቸውን ለሌሎች በማካፈል ልግስና ያሳያሉ (ከአንቀጽ 4-5⁠ን ተመልከት) *

4. የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በጥንት ዘመን የኖሩት ሌዋውያን የነበራቸው ዓይነት አመለካከት የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

4 ትሑት የሆኑ አረጋውያን ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ቀድሞ ያከናውኑት የነበረውን ያህል ማከናወን እንደማይችሉ ይገነዘባሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾቻችንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ወንድሞች 70 ዓመት ሲሆናቸው ሌላ ምድብ ላይ እንዲያገለግሉ ይጋበዛሉ። እርግጥ ይህን ለውጥ ማስተናገድ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። በወረዳ ሥራ ወንድሞቻቸውን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ይህን ምድባቸውን የሚወዱት ከመሆኑም ሌላ በዚሁ አገልግሎት የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ያም ሆኖ ሥራውን ከእነሱ በዕድሜ የሚያንሱ ወንድሞች ቢያከናውኑት የተሻለ እንደሆነ ይገነዘባሉ። እነዚህ ወንድሞች በጥንቷ እስራኤል የኖሩት ሌዋውያን የነበራቸው ዓይነት አመለካከት ያንጸባርቃሉ፤ ሌዋውያኑ 50 ዓመት ሲሆናቸው በማደሪያ ድንኳኑ የሚያከናውኑትን አገልግሎት ማቆም ነበረባቸው። በዕድሜ የገፉት ሌዋውያን የአገልግሎት ምድባቸው መለወጡ ደስታቸውን አላሳጣቸውም። ማከናወን የሚችሉትን ነገር በቅንዓት የሚያከናውኑ ከመሆኑም ሌላ ወጣቶቹን ሌዋውያን ይረዷቸው ነበር። (ዘኁ. 8:25, 26) በዛሬው ጊዜም የወረዳ የበላይ ተመልካች የነበሩ ወንድሞች እንደ ቀድሞው በርካታ ጉባኤዎችን ባያገለግሉም እንኳ ለተመደቡበት ጉባኤ ውድ ሀብት ናቸው።

5. ከዳን እና ከኬቲ ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

5 ለ23 ዓመታት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለውን ወንድም ዳንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዳን 70 ዓመት ሲሆነው እሱና ባለቤቱ ኬቲ ልዩ አቅኚዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ተመደቡ። በአዲሱ ምድባቸው ላይ ስለሚያከናውኑት አገልግሎት ምን ይሰማቸዋል? ዳን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ሥራ እንዳለው ይናገራል። በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ኃላፊነቶች ይወጣል፤ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት እንዲያሟሉ ይረዳል፤ እንዲሁም በትላልቅ ከተሞችና በማረሚያ ቤቶች በሚከናወነው አገልግሎት እንዴት መካፈል እንደሚችሉ አስፋፊዎችን ያሠለጥናል። እናንት ውድ አረጋውያን፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ሆናችሁም አልሆናችሁ ሌሎችን መርዳት የምትችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ከአዲሱ ሁኔታችሁ ጋር ተላመዱ፤ አዳዲስ ግቦችን አውጡ፤ እንዲሁም ማድረግ በማትችሉት ነገር ላይ ሳይሆን ማድረግ በምትችሉት ነገር ላይ አተኩሩ።

ልካችሁን የምታውቁ ሁኑ

6. ልክን ማወቅ የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

6 ልኩን የሚያውቅ ሰው የአቅም ገደብ እንዳለበት ይገነዘባል። (ምሳሌ 11:2) ልኩን የሚያውቅ መሆኑ ከሚችለው በላይ ለማከናወን እንዳይሞክር ይረዳዋል። ይህም ደስታውን እንዳያጣና በትጋት መሥራቱን እንዲቀጥል ያስችለዋል። ልኩን የሚያውቅ ሰው ዳገት ላይ መኪና ከሚነዳ ሾፌር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሾፌሩ ዳገቱን ለመውጣት ማርሽ ቀይሮ ከባድ ማርሽ ማስገባት ያስፈልገዋል። ይህን ማድረጉ ፍጥነቱን እንደሚቀንስበት የታወቀ ነው፤ ሆኖም ወደፊት መሄዱን እንዲቀጥል ያስችለዋል። በተመሳሳይም ልኩን የሚያውቅ ሰው ይሖዋን ማገልገሉን እና ሌሎችን መርዳቱን መቀጠል እንዲችል ለውጥ ማድረግና ፍጥነቱን መቀነስ ያለበት መቼ እንደሆነ ያውቃል።—ፊልጵ. 4:5

7. ቤርዜሊ ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

7 የቤርዜሊን ምሳሌ እንመልከት፤ ንጉሥ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ እንዲኖር ቤርዜሊን ሲጋብዘው ቤርዜሊ 80 ዓመቱ ነበር። ቤርዜሊ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለነበረ የንጉሡን ግብዣ አልተቀበለም። ቤርዜሊ ዕድሜው አቅሙን እንደሚገድብበት ስለተገነዘበ ወጣቱ ኪምሃም በእሱ ምትክ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲሄድ ሐሳብ አቀረበ። (2 ሳሙ. 19:35-37) በዛሬው ጊዜ ያሉ አረጋውያንም እንደ ቤርዜሊ፣ ወጣቶች በእነሱ ምትክ ሥራውን እንዲያከናውኑ አጋጣሚውን መስጠት ይፈልጋሉ።

ንጉሥ ዳዊት ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ልጁ እንደሆነ አምላክ ሲነግረው ውሳኔውን ተቀብሏል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8. ንጉሥ ዳዊት ከቤተ መቅደሱ ግንባታ ጋር በተያያዘ ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

8 ንጉሥ ዳዊትም ልክን በማወቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በጣም ጓጉቶ ነበር። ይሁንና ይሖዋ ቤተ መቅደሱን የመሥራት መብት የሰጠው ለወጣቱ ሰለሞን እንደሆነ ለዳዊት ሲነግረው ዳዊት የይሖዋን ውሳኔ በመቀበል ሥራውን በሙሉ ልቡ ደግፏል። (1 ዜና 17:4፤ 22:5) ዳዊት፣ ሰለሞን ‘ገና ወጣት እና ተሞክሮ የሌለው’ በመሆኑ ይህን ሥራ በተሻለ መንገድ ማከናወን የሚችለው እሱ ራሱ እንደሆነ አልተሰማውም። (1 ዜና 29:1) ዳዊት የግንባታው ሥራ ስኬታማ መሆኑ የተመካው በይሖዋ በረከት እንጂ ሥራውን በሚያከናውኑት ሰዎች ዕድሜ ወይም ተሞክሮ ላይ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። እንደ ዳዊት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አረጋውያንም የነበራቸው ኃላፊነት ቢለወጥም በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈላቸውን ይቀጥላሉ። ደግሞም እነሱ በአንድ ወቅት ያከናውኑ የነበረውን ሥራ አሁን የሚሠሩትን ወጣቶች ይሖዋ እንደሚባርካቸው ያውቃሉ።

9. አንድ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ልኩን የሚያውቅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

9 በዘመናችንም ልክን በማወቅ ረገድ ምሳሌ የሚሆኑን ክርስቲያኖች አሉ። የሺጌኦን ሁኔታ እንመልከት፤ ሺጌኦ በ1976 የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ እንዲያገለግል ሲሾም 30 ዓመቱ ነበር። በ2004 የቅርንጫፍ ኮሚቴው አስተባባሪ ሆነ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን አቅሙ እየደከመ እንደሆነና እንደ ቀድሞው ሥራውን በቅልጥፍና ማከናወን እንደከበደው ተገነዘበ። ስለ ጉዳዩ ከጸለየ በኋላ ከእሱ በዕድሜ የሚያንስ ወንድም ኃላፊነቱን መረከቡ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አሰበ። ሺጌኦ በአሁኑ ወቅት የቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪ ባይሆንም ከሌሎቹ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ጋር ተባብሮ መሥራቱን ቀጥሏል። ከቤርዜሊ፣ ከንጉሥ ዳዊትና ከሺጌኦ ምሳሌ መመልከት እንደምንችለው ትሑት የሆነና ልኩን የሚያውቅ ሰው በወጣቶች ተሞክሮ ማነስ ላይ ሳይሆን በጥንካሬያቸው ላይ ያተኩራል። እንደ ተፎካካሪዎቹ ሳይሆን አብረውት እንደሚሠሩ ወንድሞቹ አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ምሳሌ 20:29

አመስጋኝ ሁኑ

10. አረጋውያን በጉባኤያቸው ውስጥ ላሉ ወጣቶች ምን አመለካከት አላቸው?

10 አረጋውያን ወጣቶችን ከይሖዋ እንዳገኟቸው ስጦታዎች አድርገው ይመለከቷቸዋል፤ ለእነዚህ ስጦታዎችም አመስጋኝ ናቸው። አረጋውያን አቅማቸው እየደከመ ሲሄድ ሥራውን ለማከናወንና ጉባኤውን ለማገልገል ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች በመኖራቸው ደስተኞች ናቸው።

11. በሩት 4:13-16 ላይ የሰፈረው ዘገባ አረጋውያን የወጣቶችን እርዳታ በአመስጋኝነት መቀበላቸው በረከት እንደሚያስገኝ የሚያሳየው እንዴት ነው?

11 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው አረጋዊቷ ናኦሚ የወጣቶችን እርዳታ በአመስጋኝነት በመቀበል ረገድ ግሩም ምሳሌ ትታልናለች። መጀመሪያ ላይ ናኦሚ፣ መበለት የሆነችውን ምራቷን ሩትን ወደ ሕዝቧ እንድትመለስ አበረታታት ነበር። ሆኖም ናኦሚ፣ ሩት አብራት ወደ ቤተልሔም ለመሄድ እንደቆረጠች ስታውቅ የዚህችን ታማኝ ሴት እርዳታ በደስታ ተቀብላለች። (ሩት 1:7, 8, 18) ይህም ለሁለቱም ሴቶች ታላቅ በረከት አምጥቶላቸዋል! (ሩት 4:13-16ን አንብብ።) አረጋውያን ትሑት መሆናቸው የናኦሚን ምሳሌ ለመከተል ያነሳሳቸዋል።

12. ሐዋርያው ጳውሎስ አመስጋኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ ወንድሞቹ ላደረጉለት እርዳታ አመስጋኝ ነበር። ለምሳሌ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ለላኩለት ቁሳዊ እርዳታ አመስግኗቸዋል። (ፊልጵ. 4:16) ጢሞቴዎስ ላደረገለት እርዳታም ምስጋናውን ገልጿል። (ፊልጵ. 2:19-22) በተጨማሪም ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም በተወሰደበት ወቅት አንዳንድ ክርስቲያኖች እሱን ለማበረታታት በመምጣታቸው አምላክን አመስግኗል። (ሥራ 28:15) ጳውሎስ ምሥራቹን ለመስበክና ጉባኤዎችን ለማጠናከር በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘ ብርቱ ሰው ነበር። ያም ቢሆን ወንድሞቹና እህቶቹ ያደረጉለትን እርዳታ በትሕትና ተቀብሏል።

13. አረጋውያን በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወጣቶች አመስጋኝ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 እናንት አረጋውያን፣ በጉባኤያችሁ ላሉ ወጣቶች አመስጋኝ መሆናችሁን ማሳየት የምትችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ወደምትፈልጉበት ቦታ ሊያደርሷችሁ፣ አስቤዛ ሊገዛዙላችሁ አሊያም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሊያከናውኑላችሁ እንደሚፈልጉ ከነገሯችሁ እርዳታቸውን በአመስጋኝነት ተቀበሉ። እንዲህ ያለውን እርዳታ የይሖዋ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ወንድሞቻችሁ የሚሰጧችሁን እርዳታ መቀበላችሁ ከእነሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድትመሠርቱ ሊረዳችሁ ይችላል። እነዚህን ወጣቶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው፤ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል የሚያደርጉት ጥረት ምን ያህል እንደሚያስደስታችሁም ግለጹላቸው። አብራችኋቸው ጊዜ አሳልፉ፤ እንዲሁም በሕይወታችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ተሞክሮ ንገሯቸው። ይህን ስታደርጉ ይሖዋ ወጣቶችን ወደ ጉባኤው ስለሳባቸው “አመስጋኝ መሆናችሁን” ታሳያላችሁ።—ቆላ. 3:15፤ ዮሐ. 6:44፤ 1 ተሰ. 5:18

ለጋስ ሁኑ

14. ንጉሥ ዳዊት ልግስና ያሳየው እንዴት ነው?

14 የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ ስንመረምር አረጋውያን ሊያሳዩት የሚገባ ሌላ ግሩም ባሕርይ እናገኛለን፤ ይህም ልግስና ነው። ዳዊት የቤተ መቅደሱን ግንባታ ለመደገፍ ከራሱ ሀብት ከፍተኛ መዋጮ አድርጓል። (1 ዜና 22:11-16፤ 29:3, 4) ለቤተ መቅደሱ ሥራ በዋነኝነት የሚመሰገነው ልጁ ሰለሞን መሆኑ፣ ዳዊት በልግስና ከመስጠት ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። ዕድሜያችን በመግፋቱ የተነሳ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለመካፈል ጉልበት ባይኖረንም አቅማችን በፈቀደ መጠን መዋጮ በማድረግ እነዚህን ፕሮጀክቶች መደገፋችንን መቀጠል እንችላለን። በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት ያካበትናቸውን ተሞክሮዎች ለወጣቶች ልንነግራቸው እንችላለን።

15. ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ምን ግሩም ስጦታ ሰጥቶታል?

15 ልግስና በማሳየት ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስን በሚስዮናዊነት አብሮት እንዲያገለግል የጋበዘው ከመሆኑም ሌላ የስብከትና የማስተማሪያ ዘዴዎቹን በማስተማር ልግስና አሳይቶታል። (ሥራ 16:1-3) ጳውሎስ የሰጠው ሥልጠና ጢሞቴዎስ ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪና አስተማሪ እንዲሆን ረድቶታል። (1 ቆሮ. 4:17) ጢሞቴዎስም በበኩሉ የጳውሎስን ዘዴዎች ለሌሎች አስተምሯል።

16. ወንድም ሺጌኦ ሌሎችን ያሠለጠነው ለምንድን ነው?

16 በዛሬው ጊዜ ያሉ አረጋውያን እነሱ በጉባኤ ውስጥ የሚያከናውኑትን ሥራ እንዲሠሩ ወጣቶችን ቢያሠለጥኑ ተፈላጊነታቸው እንደሚቀንስ አይሰማቸውም። ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የወንድም ሺጌኦን ምሳሌ እንመልከት፤ ሺጌኦ በዕድሜ ከእሱ የሚያንሱ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትን ለዓመታት ሲያሠለጥናቸው ቆይቷል። ይህን ያደረገው በተመደበበት አገር ውስጥ ያለው የመንግሥቱ ሥራ እንዲቀጥል የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲል ነው። በመሆኑም ሺጌኦ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪ ሆኖ ማገልገሉን ባቆመበት ወቅት እሱን የሚተካ በሚገባ የሠለጠነ ወንድም ሊኖር ችሏል። ሺጌኦ ከ45 ለሚበልጡ ዓመታት በቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ በማገልገል ያካበተውን ተሞክሮ በዕድሜ ከእሱ ለሚያንሱ ወንድሞች ማካፈሉን ቀጥሏል። በእርግጥም እንደነዚህ ያሉት ወንድሞች ለአምላክ ሕዝቦች በረከት ናቸው!

17. በሉቃስ 6:38 መሠረት አረጋውያን ምን ማድረግ ይችላሉ?

17 እናንት አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች፣ ይሖዋን በእምነትና በታማኝነት ማገልገል ከሁሉ የተሻለ የሕይወት ጎዳና መሆኑን የምታረጋግጡ ሕያው ማስረጃ ናችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መማርና ተግባራዊ ማድረግ የሚክስ መሆኑን በምሳሌያችሁ አሳይታችኋል። ቀደም ሲል ነገሮች እንዴት ይከናወኑ እንደነበረ ታውቃላችሁ፤ ሆኖም አዳዲስ ሁኔታዎችን ለማስተናገድ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ትገነዘባላችሁ። በቅርቡ የተጠመቃችሁ አረጋውያንም ለሌሎች ልታካፍሉ የምትችሉት ብዙ ነገር አላችሁ፤ በዚህ ዕድሜያችሁ ስለ ይሖዋ ማወቃችሁ ምን ያህል እንዳስደሰታችሁ መናገር ትችላላችሁ። ወጣቶች ተሞክሯችሁንና ያገኛችሁትን ትምህርት መስማት ያስደስታቸዋል። ካካበታችሁት ተሞክሮ ‘ለሰዎች ከሰጣችሁ’ ይሖዋም አብዝቶ ይባርካችኋል።ሉቃስ 6:38ን አንብብ።

18. አረጋውያንና ወጣቶች ተባብረው መሥራታቸው ለሁለቱም ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?

18 እናንት ውድ አረጋውያን፣ ከወጣቶች ጋር መቀራረባችሁ እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል። (ሮም 1:12) እናንተ የሌላችሁ ነገር እነሱ አላቸው፤ እነሱ የሌላቸው ነገር ደግሞ እናንተ አላችሁ። አረጋውያን በረጅም ዕድሜ ያካበቱት ጥበብና ተሞክሮ አላቸው። ወጣቶች ደግሞ ጉልበትና ብርታት አላቸው። ወጣቶችና አረጋውያን ተባብረው ሲሠሩ ለአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ውዳሴ ያመጣሉ፤ ለመላው ጉባኤም በረከት ይሆናሉ።

መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ

^ አን.5 የይሖዋን ድርጅት ለመደገፍ ጥረት የሚያደርጉ በርካታ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች በጉባኤዎቻችን ውስጥ በመኖራቸው ተባርከናል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አረጋውያን ባሕላቸው ወይም አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን፣ ወጣቶች በይሖዋ አገልግሎት ጉልበታቸውን በሚገባ እንዲጠቀሙበት ሊረዷቸው ይችላሉ።

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች 70 ዓመት ሲሆነው እሱና ባለቤቱ ሌላ ምድብ ተሰጣቸው። ባለፉት ዓመታት ያካበቱት ተሞክሮ አሁን በተመደቡበት ጉባኤ ሌሎችን ለማሠልጠን አስችሏቸዋል።