በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 43

ተስፋ አትቁረጡ!

ተስፋ አትቁረጡ!

“ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”—ገላ. 6:9

መዝሙር 68 የመንግሥቱን ዘር መዝራት

ማስተዋወቂያ *

1. የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ደስታና ክብር የሚሰማን ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ደስታና ክብር ይሰማናል! በአምላክ ስም የመጠራት መብት አግኝተናል፤ እንዲሁም በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በመካፈል የእሱ ምሥክሮች እንደሆንን እናሳያለን። “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ” አማኞች እንዲሆኑ መርዳት መቻላችን ትልቅ ደስታ ያስገኝልናል። (ሥራ 13:48) ደቀ መዛሙርቱ ስኬታማ የስብከት ዘመቻ አድርገው ሲመለሱ ‘በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት ያደረገውን’ የኢየሱስን ስሜት እንጋራለን።—ሉቃስ 10:1, 17, 21

2. አገልግሎታችንን በቁም ነገር እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

2 አገልግሎታችንን በቁም ነገር እንመለከታለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ” በማለት አሳስቦታል። አክሎም “ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ” ብሎታል። (1 ጢሞ. 4:16) በመሆኑም የስብከቱ ሥራችን ሕይወት አድን ሥራ ነው። የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ስለሆንን ለራሳችን ምንጊዜም ትኩረት መስጠት አለብን። ሁሌም ቢሆን አኗኗራችን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣና ከምንሰብከው ምሥራች ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባል። (ፊልጵ. 1:27) በተጨማሪም ለሌሎች ከመስበካችን በፊት በሚገባ በመዘጋጀት እንዲሁም የይሖዋን በረከት ለማግኘት በመጸለይ ‘ለምናስተምረው ትምህርት ትኩረት እንደምንሰጥ’ እናሳያለን።

3. ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ምን ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ? ምሳሌ ስጥ።

3 ይሁንና አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ብናደርግ እንኳ በክልላችን ያሉ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት እምብዛም ፍላጎት ላያሳዩ ወይም ጥሩ ምላሽ ላይሰጡ ይችላሉ። ከ1929 እስከ 1947 ድረስ ብቻውን በአይስላንድ ይሰብክ የነበረውን የወንድም ጌኦርግ ሊንዳልን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወንድም ጌኦርግ በሺዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎችን ቢያበረክትም በዚያ አካባቢ አንድም ሰው እውነትን አልተቀበለም። “አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በቀጥታ ቢቃወሙም አብዛኞቹ ግን ግድየለሾች ነበሩ” በማለት ጽፏል። ጊልያድ ገብተው የሠለጠኑ ሚስዮናውያን ተመድበው የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት ጥረት ቢያደርጉም አይስላንድ ውስጥ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው የተጠመቁ ሰዎች የተገኙት ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ነው። *

4. ሰዎች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሳይሰጡ ሲቀሩ ምን ሊሰማን ይችላል?

4 ሰዎች ለምንሰብከው መልእክት ጥሩ ምላሽ ሳይሰጡ ሲቀሩ እንደምናዝን የታወቀ ነው። ጳውሎስ አይሁዳውያን በቡድን ደረጃ፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ እንደሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው “ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ” እንደተሰማው ተናግሯል፤ እኛም እንዲህ ሊሰማን ይችላል። (ሮም 9:1-3) ምናልባት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይኖርህ ይሆናል። ጥናትህን ለመርዳት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ብታደርግም እንዲሁም ስለ እሱ ብትጸልይም ጥናትህ እድገት ላያደርግ ይችላል። በዚህም ምክንያት ጥናታችሁን ለማቋረጥ ትገደድ ይሆናል። አሊያም ደግሞ እስካሁን ድረስ ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን የረዳኸው አንድም ሰው ላይኖር ይችላል። ታዲያ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማህ ወይም ይሖዋ አገልግሎትህን እንዳልባረከልህ ልታስብ ይገባል? በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን፦ (1) በአገልግሎታችን ስኬታማ ሆነናል ሊባል የሚችለው መቼ ነው? (2) ከስብከቱ ሥራችን ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው?

በአገልግሎታችን ስኬታማ ሆነናል ሊባል የሚችለው መቼ ነው?

5. ለይሖዋ ስንል የምናደርጋቸው ነገሮች አንዳንድ ጊዜ የጠበቅነውን ውጤት ላያስገኙ የሚችሉት ለምንድን ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፈቃድ ስለሚያደርግ ሰው ሲናገር “የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል” ይላል። (መዝ. 1:3) ይህ ሲባል ግን ለይሖዋ ስንል የምናደርጋቸው ነገሮች በሙሉ የፈለግነውን ውጤት ያስገኛሉ ማለት አይደለም። በእኛም ሆነ በሌሎች አለፍጽምና የተነሳ ሕይወታችን “በመከራ የተሞላ ነው።” (ኢዮብ 14:1) በተጨማሪም ተቃዋሚዎች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አገልግሎታችንን በተለመደው መንገድ እንዳናከናውን እንቅፋት ሊፈጥሩብን ይችላሉ። (1 ቆሮ. 16:9፤ 1 ተሰ. 2:18) ታዲያ ይሖዋ በስብከቱ ሥራ ውጤታማ መሆን አለመሆናችንን የሚለካው እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዱንን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከት።

ለሰዎች የምንሰብከው በአካል፣ በደብዳቤም ሆነ በስልክ ይሖዋ ጥረታችንን ከፍ አድርጎ ይመለከታል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. ይሖዋ ለእሱ ስንል የምናከናውነውን ሥራ ስኬት የሚመዝነው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ የሚመለከተው የምናደርገውን ጥረትና የምናሳየውን ጽናት ነው። ይሖዋ የሥራችንን ስኬታማነት የሚመዝነው ሌሎች በሚሰጡት ምላሽ ሳይሆን በምናሳየው ትጋትና ፍቅር ላይ ተመሥርቶ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።” (ዕብ. 6:10) የምናከናውነው ሥራ ጥሩ ውጤት ባያስገኝ እንኳ ይሖዋ ያደረግነውን ጥረትና ያሳየነውን ፍቅር አይረሳም። እንግዲያው ያሰብነውን ውጤት አገኘንም አላገኘን ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተናገረው ሐሳብ ለእኛም እንደሚሠራ እናስታውስ፤ ጳውሎስ “ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ [አይደለም]” ብሏቸዋል።—1 ቆሮ. 15:58

7. ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ከተናገረው ነገር ምን እንማራለን?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ በበርካታ ከተሞች አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ የረዳ የተዋጣለት ሚስዮናዊ ነው። ያም ሆኖ የክርስቶስ አገልጋይ ለመሆን ብቁ የሆነበትን ምክንያት አስመልክቶ ለሌሎች ማስረጃ ሲያቀርብ አማኞች እንዲሆኑ በረዳቸው ሰዎች ብዛት ላይ አላተኮረም። ከዚህ ይልቅ ከእሱ እንደሚበልጡ ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች ያቀረቡትን ሐሳብ ሲያስተባብል “ከሁሉም ይበልጥ ሠርቻለሁ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 11:23) እኛም ልክ እንደ ጳውሎስ ይሖዋ የሚያተኩረው በምናደርገው ጥረትና በምናሳየው ጽናት ላይ እንደሆነ እናስታውስ።

8. አገልግሎታችንን በተመለከተ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

8 አገልግሎታችን ይሖዋን ያስደስታል። ኢየሱስ 70 የሚያህሉ ደቀ መዛሙርቱን የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰብኩ ልኳቸው ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ከስብከት ዘመቻቸው የተመለሱት “ደስ እያላቸው” ነበር። የተደሰቱት ለምንድን ነው? “አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” በማለት ተናግረዋል። ኢየሱስ ግን አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት እንዲህ አላቸው፦ “መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ከዚህ ይልቅ ስማችሁ በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” (ሉቃስ 10:17-20) ኢየሱስ በአገልግሎታቸው እንዲህ ያሉ አስደሳች ተሞክሮዎችን የሚያገኙት ሁልጊዜ እንዳልሆነ ያውቃል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ መጀመሪያ ላይ የደቀ መዛሙርቱን መልእክት ከሰሙት ሰዎች መካከል ምን ያህሎቹ አማኞች እንደሆኑ አናውቅም። ደቀ መዛሙርቱ መደሰት ያለባቸው ባገኙት ውጤት ብቻ እንዳልሆነ መገንዘብ ነበረባቸው፤ ከሁሉ በላይ ሊያስደስታቸው የሚገባው ይሖዋ ባደረጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደተደሰተ ማወቃቸው ነው።

9. ገላትያ 6:7-9 ላይ እንደተገለጸው በአገልግሎታችን መጽናታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

9 በአገልግሎታችን የምንጸና ከሆነ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። የመንግሥቱን እውነት በሙሉ ልብ ስንዘራና ለማሳደግ ጥረት ስናደርግ የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ በነፃነት እንዲሠራ በመፍቀድ ‘ለመንፈስ ብለን እንዘራለን።’ ‘ተስፋ ካልቆረጥን’ ወይም “ካልታከትን” ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንደምናጭድ አረጋግጦልናል፤ አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር ራሱን ለይሖዋ እንዲወስን መርዳት አለመርዳታችን በዚህ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።—ገላትያ 6:7-9ን አንብብ።

ከስብከቱ ሥራችን ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው?

10. ሰዎች ለአገልግሎታችን የሚሰጡት ምላሽ በምን ላይ የተመካ ነው?

10 ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ በዋነኝነት የተመካው በልባቸው ሁኔታ ላይ ነው። ኢየሱስ ይህን እውነታ ለማስረዳት በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ ዘር የዘራን ሰው ምሳሌ ተጠቅሟል፤ ፍሬ ያስገኘው በአንደኛው አፈር ላይ የተዘራው ዘር ብቻ ነው። (ሉቃስ 8:5-8) ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሳቸው የተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ‘ለአምላክ ቃል’ የተለያየ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን የልብ ሁኔታ እንደሚያመለክት ተናግሯል። (ሉቃስ 8:11-15) ልክ እንደ ዘሪው ሁሉ እኛም የስብከቱ ሥራችን የሚያፈራውን ፍሬ መቆጣጠር አንችልም፤ ምክንያቱም ይህ የተመካው በአድማጮቻችን የልብ ሁኔታ ላይ ነው። የእኛ ኃላፊነት ጥሩውን ዘር ማለትም የመንግሥቱን መልእክት መዝራታችንን መቀጠል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው “እያንዳንዱ ሰው” እንደ ውጤቱ መጠን ሳይሆን “እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል።”—1 ቆሮ. 3:8

ኖኅ ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ቢሰብክም፣ አብረውት ወደ መርከቡ የገቡት የቤተሰቡ አባላት ብቻ ነበሩ። ያም ቢሆን ኖኅ አምላክን በመታዘዝ የተሰጠውን ሥራ አከናውኗል! (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ኖኅ ውጤታማ “የጽድቅ ሰባኪ” የነበረው ለምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

11 በጥንት ጊዜ የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች ከአምላክ የተቀበሉትን መልእክት ሲሰብኩ ጥሩ ምላሽ የማይሰጡ ሰዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር፤ ምናልባትም ለአሥርተ ዓመታት ያህል በዚህ ሥራ ቀጥሏል። (2 ጴጥ. 2:5) ይህን ሥራ ሲያከናውን ሰዎች ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ አድርጎ መሆን አለበት፤ ይሖዋ ግን ይህን የሚጠቁም ምንም ሐሳብ አልነገረውም። ከዚህ ይልቅ መርከቡን እንዲሠራ ትእዛዝ ሲሰጠው እንዲህ ብሎታል፦ “አንተም ወደ መርከቡ መግባት አለብህ፤ አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ወደ መርከቡ መግባት ይኖርባችኋል።” (ዘፍ. 6:18) ደግሞም ኖኅ፣ አምላክ እንዲገነባ የነገረውን መርከብ መጠንና የመያዝ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ለስብከቱ ምላሽ የሚሰጡት ሰዎች ቁጥር ውስን እንደሚሆን ገምቶ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 6:15) በኋላ እንደታየው በወቅቱ ከነበሩት ዓመፀኞች መካከል ለኖኅ ስብከት ምላሽ የሰጠ አንድም ሰው አልነበረም። (ዘፍ. 7:7) ታዲያ ኖኅ ያከናወነው ሥራ በይሖዋ ፊት ከንቱ ነበር? በፍጹም! በይሖዋ ዓይን ኖኅ ውጤታማ ሰባኪ ነበር፤ ምክንያቱም የታዘዘውን ሁሉ በታማኝነት ፈጽሟል።—ዘፍ. 6:22

12. ነቢዩ ኤርምያስ የሰዎችን ግድየለሽነትና ተቃውሞ ተቋቁሞ ደስተኛ መሆን የቻለው እንዴት ነው?

12 ነቢዩ ኤርምያስም የሰዎችን ግድየለሽነትና ተቃውሞ ተቋቁሞ ለአሥርተ ዓመታት ሰብኳል። በተቃዋሚዎቹ “ስድብና ፌዝ” በጣም ከማዘኑ የተነሳ ሥራውን ለማቆም እስከማሰብ ደርሶ ነበር። (ኤር. 20:8, 9) ሆኖም ኤርምያስ ተስፋ አልቆረጠም! የተሰማውን አሉታዊ ስሜት ለማሸነፍና በአገልግሎቱ ደስታ ለማግኘት የረዳው ምንድን ነው? በሁለት ወሳኝ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጉ ነው። አንደኛ፣ ኤርምያስ የሚናገረው መልእክት “የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን” የሚሰጥ ነበር። (ኤር. 29:11) ሁለተኛ፣ ኤርምያስ የይሖዋን ስም የመሸከም መብት አግኝቶ ነበር። (ኤር. 15:16) እኛም በጨለማ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ የተስፋ መልእክት የምንናገር ከመሆኑም ሌላ ምሥክሮቹ በመሆን የይሖዋን ስም የመሸከም መብት አግኝተናል። በእነዚህ ሁለት ወሳኝ ነገሮች ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ የሰዎች ምላሽ ምንም ይሁን ምን ደስተኛ መሆን እንችላለን።

13. ማርቆስ 4:26-29 ላይ ከሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 አንድ ሰው መንፈሳዊ እድገት የሚያደርገው ቀስ በቀስ ነው። ኢየሱስ ሌሊት ላይ ስለሚተኛው ዘሪ የሰጠው ምሳሌ ይህን እውነት ያስገነዝበናል። (ማርቆስ 4:26-29ን አንብብ።) ዘሪው የሥራውን ውጤት ያየው በጊዜ ሂደት ነው፤ ደግሞም ከዘሩ እድገት ጋር በተያያዘ አብዛኛው ነገር ከእሱ ቁጥጥር ውጭ ነው። እናንተም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስትካፈሉ የሥራችሁን ውጤት ወዲያውኑ ላታዩ ትችላላችሁ፤ ምክንያቱም እድገቱ ቀስ በቀስና ደረጃ በደረጃ የሚከናወን ነው። አንድ ገበሬ ሰብሉ እሱ በፈለገው ፍጥነት እንዲያድግ ማድረግ እንደማይችል ሁሉ እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን እኛ በፈለግነው ፍጥነት መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ መገፋፋት አንችልም። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችሁ እናንተ በፈለጋችሁት ፍጥነት እድገት ባያደርግ ልታዝኑ ወይም ተስፋ ልትቆርጡ አይገባም። ልክ እንደ ግብርና ሁሉ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራም ትዕግሥት ይጠይቃል።—ያዕ. 5:7, 8

14. የአገልግሎታችን ውጤት የሚታየው ቀስ በቀስ እንደሆነ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

14 በአንዳንድ ክልሎች የአገልግሎታችን ውጤት ለበርካታ ዓመታት ላይታይ ይችላል። በ1959 በካናዳ ኩዊቤክ ግዛት በሚገኝ አንድ ከተማ እንዲያገለግሉ የተመደቡትን ግላዲስ አለን እና ሩቢ አለን የተባሉ እህትማማቾች ተሞክሮ እንመልከት። * የክልላቸው ሰዎች ማኅበረሰቡና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባደረጉባቸው ጫና ምክንያት የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፈቃደኞች አልነበሩም። ግላዲስ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ አካባቢ ለሁለት ዓመት ያህል በየቀኑ ለስምንት ሰዓታት ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ብናገለግልም ሊያነጋግረን ፈቃደኛ የሆነ አንድም ሰው አላገኘንም! ሰዎቹ ወደ በሩ መጥተው ይመለከቱንና የበሩን መጋረጃ ከጋረዱ በኋላ ተመልሰው ይሄዳሉ። ቢሆንም ተስፋ አልቆረጥንም።” በጊዜ ሂደት የሰዎቹ አመለካከት መለወጥ ጀመረ፤ ክልሉም ይበልጥ ፍሬያማ ሆነ። በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ ሦስት ጉባኤዎች ተቋቁመዋል።—ኢሳ. 60:22

15. አንደኛ ቆሮንቶስ 3:6, 7 ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በተመለከተ ምን ያስተምረናል?

15 ደቀ መዛሙርት ማድረግ የጋራ ሥራ ነው። ከዚህ በፊት እንደተገለጸው አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን የመላው ጉባኤ እርዳታ ያስፈልጋል። (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አስፋፊ ፍላጎት ላሳየ ሰው ትራክት ወይም መጽሔት ይሰጠዋል። ከዚያ ግን አስፋፊው ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ፕሮግራሙ እንደማይፈቅድለት ስለተሰማው ሌላ ወንድም ይህን ሰው እንዲያነጋግረው ያመቻቻል። ይህ ወንድም ግለሰቡን ጥናት ያስጀምረዋል። ከዚያም የተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጥናቱ ላይ እንዲገኙ ይጋብዛል፤ የተጋበዙት ወንድሞችና እህቶች ጥናቱን በተለያዩ መንገዶች ያበረታቱታል። ሁሉም የእውነትን ዘር ውኃ በማጠጣቱ ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ እንዳለው ዘሪውም ሆነ አጫጁ በመንፈሳዊው የመከር ሥራ አብረው ይደሰታሉ።—ዮሐ. 4:35-38

16. ባጋጠማችሁ የጤና እክል ወይም የአቅም ገደብ ምክንያት በአገልግሎት የምትፈልጉትን ያህል ተሳትፎ ባታደርጉም ደስተኛ መሆን የምትችሉት ለምንድን ነው?

16 ይሁንና ባጋጠማችሁ የጤና እክል ወይም የአቅም ገደብ ምክንያት ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ የምትፈልጉትን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ ባትችሉስ? ያም ቢሆን በመከሩ ሥራ በምታበረክቱት አስተዋጽኦ ደስተኛ መሆን ትችላላችሁ። ንጉሥ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ቤተሰባቸውንና ንብረታቸውን ወረራ ካደረጉባቸው አማሌቃውያን ባስጣሉ ጊዜ የተከናወነውን ነገር እንመልከት። ከሰዎቹ መካከል 200 የሚሆኑት በጣም ከመድከማቸው የተነሳ ወደ ውጊያው ከመሄድ ይልቅ ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ። ወደ ውጊያ የሄዱት ሰዎች ድል አድርገው ሲመለሱ ዳዊት ጓዝ ለመጠበቅ የቀሩትን ሰዎች ጨምሮ ሁሉም ከምርኮው ላይ እኩል እንዲካፈሉ አዘዘ። (1 ሳሙ. 30:21-25) በዓለም ዙሪያ ከሚከናወነው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በዚህ ሥራ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል የሚያደርጉ ሁሉ አንድ አዲስ ሰው እውነትን ተምሮ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምር እኩል መደሰት ይችላሉ።

17. ይሖዋን ለማመስገን የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

17 ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበውን አገልግሎት በአድናቆት ስለሚቀበል አመስጋኞች ነን። የምናደርገው ጥረት የሚያስገኘውን ውጤት መቆጣጠር እንደማንችል ያውቃል። በመሆኑም የሚያተኩረው በምናሳየው ትጋትና ፍቅር ላይ ነው፤ ለዚህም ወሮታችንን ይከፍለናል። በተጨማሪም ይሖዋ በመከሩ ሥራ በምናበረክተው አስተዋጽኦ ደስተኛ እንድንሆን ያስተምረናል። (ዮሐ. 14:12) ተስፋ እስካልቆረጥን ድረስ የይሖዋን ሞገስ እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን!

መዝሙር 67 “ቃሉን ስበክ”

^ አን.5 ሰዎች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሲሰጡ እንደሰታለን፤ ጥሩ ምላሽ ሳይሰጡ ሲቀሩ ደግሞ እናዝናለን። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠኑት ሰው እድገት የማያደርግ ቢሆንስ? አሊያም እስካሁን አንድም ሰው ለጥምቀት እንዲበቃ መርዳት ካልቻላችሁስ? ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አልተሳካላችሁም ማለት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን በአገልግሎታችን ስኬታማ ሆነናል ሊባል የሚችለውና ደስተኛ መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

^ አን.14 በመስከረም 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ “አንዳች የምለውጠው ነገር አይኖርም!” በሚል ርዕስ የወጣውን የእህት ግላዲስ አለንን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።