በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 48

“ቅዱሳን ሁኑ”

“ቅዱሳን ሁኑ”

“በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።”—1 ጴጥ. 1:15

መዝሙር 34 በንጹሕ አቋም መመላለስ

ማስተዋወቂያ *

1. ሐዋርያው ጴጥሮስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ምን ምክር ሰጥቷቸዋል? ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ የማይቻል የሚመስለውስ ለምንድን ነው?

 ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሰጠውን ምክር መመርመራችን ይጠቅመናል። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ‘እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ’ ተብሎ ተጽፏልና።” (1 ጴጥ. 1:15, 16) ይህ ጥቅስ በቅድስና ረገድ ወደር የሌለው ምሳሌ የሆነውን ይሖዋን መምሰል እንደምንችል ያስገነዝበናል። በምግባራችን ቅዱሳን መሆን እንችላለን፤ ደግሞም ቅዱሳን መሆን ይኖርብናል። ፍጹማን ስላልሆንን ይህን ማድረግ እንደማንችል ይሰማን ይሆናል። ጴጥሮስ ራሱም ቢሆን አንዳንድ ስህተቶች ሠርቷል፤ ሆኖም የእሱ ምሳሌ ‘ቅዱሳን መሆን’ እንደምንችል ያሳያል።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

2 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ ቅድስና ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ቅድስና ምን ያስተምረናል? በምግባራችን ቅዱሳን መሆን የምንችለው እንዴት ነው? እንዲሁም ቅዱሳን መሆናችን ከይሖዋ ጋር ካለን ዝምድና ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

ቅድስና ምንድን ነው?

3. ብዙ ሰዎች “ቅዱስ” ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ምን ዓይነት ሰው ነው? ሆኖም ስለ ቅድስና ትክክለኛ መረጃ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

3 ብዙዎች፣ “ቅዱስ” ስለሚባሉ ሰዎች ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ሃይማኖታዊ ልብስ የለበሰ፣ ፊቱ የማይፈታ እና ደስታ የራቀው ሰው ነው። ሆኖም እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል አይደለም። የአምላክ ቃል፣ ቅዱስ የሆነውን ይሖዋን “ደስተኛው አምላክ” በማለት ይጠራዋል። (1 ጢሞ. 1:11) አገልጋዮቹም “ደስተኛ” እንደሆኑ ይገልጻል። (መዝ. 144:15) ኢየሱስ የተለየ ሃይማኖታዊ ልብስ የሚለብሱና ጽድቃቸውን ለሌሎች ለማሳየት የሚጥሩ ሰዎችን አውግዟል። (ማቴ. 6:1፤ ማር. 12:38) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅድስና ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። ቅዱስና አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ልንፈጽመው የማንችል ትእዛዝ እንደማይሰጠን እርግጠኞች ነን። ስለዚህ ይሖዋ “እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ካለን ይህን ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥያቄ የለውም። እርግጥ ነው፣ በምግባራችን ቅዱሳን መሆን እንድንችል በመጀመሪያ ቅድስና ራሱ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አለብን።

4. “ቅዱስ” እና “ቅድስና” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

4 ቅድስና ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቅዱስ” እና “ቅድስና” የሚሉት ቃላት በሥነ ምግባር ወይም በአምልኮ ንጹሕ መሆንን ያመለክታሉ። ለይሖዋ አገልግሎት የተለዩ መሆንንም ሊያመለክቱ ይችላሉ። በሌላ አባባል፣ በሥነ ምግባር ንጹሕ ከሆንን፣ ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ካመለክነው እንዲሁም ከእሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ የቀረበ ዝምድና ከመሠረትን ቅዱስ ልንባል እንችላለን። ፍጹማን ካለመሆናችን አንጻር፣ ቅዱስ ከሆነው አምላካችን ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት መመሥረት መቻላችን በራሱ፣ ለማሰብ እንኳ የሚከብድ ልዩ መብት ነው።

“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”

5. ከታማኝ መላእክት ስለ ይሖዋ ምን እንማራለን?

5 ይሖዋ በሁሉም መንገድ ንጹሕ እና ቅዱስ ነው። ሱራፌል የተባሉት በይሖዋ ዙፋን አቅራቢያ የሚያገለግሉ መላእክት ይሖዋን ከገለጹበት መንገድ ይህን እንማራለን። ሱራፌል “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው” በማለት አውጀዋል። (ኢሳ. 6:3) እርግጥ ነው፣ ቅዱስ ከሆነው አምላካቸው ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ መላእክት ራሳቸው ቅዱሳን መሆን አለባቸው፤ ደግሞም ቅዱሳን ናቸው። ወደ ምድር መልእክት ለማድረስ የመጡ መላእክት የቆሙበት መሬት ቅዱስ እንደሆነ የተገለጸው ለዚህ ነው። ሙሴ የሚነደውን ቁጥቋጦ በተመለከተበት ወቅት የሆነውም ይኸው ነው።—ዘፀ. 3:2-5፤ ኢያሱ 5:15

“ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚለው ሐሳብ በጠፍጣፋ ወርቅ ላይ ተቀርጾ በሊቀ ካህናቱ ጥምጥም ላይ ይደረግ ነበር (ከአንቀጽ 6-7⁠ን ተመልከት)

6-7. (ሀ) በዘፀአት 15:1, 11 ላይ ሙሴ የይሖዋን ቅድስና ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ሁሉም እስራኤላውያን አምላክ ቅዱስ መሆኑን ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነበር? (ሽፋኑን ተመልከት።)

6 ሙሴ እስራኤላውያንን እየመራ ቀይ ባሕርን ካሻገራቸው በኋላ፣ አምላካቸው ይሖዋ ቅዱስ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጾላቸዋል። (ዘፀአት 15:1, 11ን አንብብ።) የግብፅን አማልክት የሚያመልኩ ሰዎች ምግባራቸው ከቅድስና ፈጽሞ የራቀ ነበር። የከነዓንን አማልክት የሚያመልኩ ሰዎችም እንደዚያው ነበሩ። አምልኳቸው ሕፃናትን መሥዋዕት ማድረግን እና አስጸያፊ በሆነ የፆታ ብልግና መካፈልን ይጨምር ነበር። (ዘሌ. 18:3, 4, 21-24፤ ዘዳ. 18:9, 10) በአንጻሩ ግን ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ራሳቸውን በሚያዋርዱ ድርጊቶች እንዲካፈሉ ፈጽሞ አይጠይቃቸውም። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ቅዱስ ነው። ሊቀ ካህናቱ በሚያደርገው ጥምጥም ላይ በሚቀመጠው ጠፍጣፋ ወርቅ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ ይህን በግልጽ ያሳያል። በወርቁ ላይ “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ነበር።—ዘፀ. 28:36-38

7 በወርቁ ላይ የተቀረጸውን ጽሑፍ የሚያይ ማንኛውም ሰው፣ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ቅዱስ እንደሆነ መረዳት ይችላል። ሆኖም ወደ ሊቀ ካህናቱ መቅረብ ባለመቻሉ የተነሳ በወርቁ ላይ የተቀረጸውን ጽሑፍ ማየት የማይችል እስራኤላዊስ? ይህን ወሳኝ መረጃ ማግኘት አይችልም ማለት ነው? አይደለም! ሕጉ በወንዶች፣ በሴቶችና በልጆች ፊት ስለሚነበብ ሁሉም እስራኤላውያን ይህን መልእክት መስማት ይችሉ ነበር። (ዘዳ. 31:9-12) እናንተም እዚያ ብትሆኑ ኖሮ የሚከተለው ሐሳብ ሲነበብ ትሰሙ ነበር፦ “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝና፤ እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም . . . ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።” “እኔ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ለእኔ ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።”—ዘሌ. 11:44, 45፤ 20:7, 26

8. ከዘሌዋውያን 19:2 እና ከ1 ጴጥሮስ 1:14-16 ምን ትምህርት እናገኛለን?

8 ለሁሉም እስራኤላውያን ከሚነበበው ሐሳብ መካከል በዘሌዋውያን 19:2 ላይ በሚገኝ አንድ ዓረፍተ ነገር ላይ ትኩረት እናድርግ። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ ብሎታል፦ “ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።’” ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን “ቅዱሳን ሁኑ” ብሎ ሲመክራቸው ይህን ጥቅስ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። (1 ጴጥሮስ 1:14-16ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ እኛ በሙሴ ሕግ ሥር አይደለንም። ያም ቢሆን ጴጥሮስ የሰጠው ምክር ከዘሌዋውያን 19:2 የሚገኘው የሚከተለው ትምህርት ዛሬም እውነት እንደሆነ ያስታውሰናል፦ ይሖዋ ቅዱስ ነው፤ እሱን የሚወዱ ሰዎችም ቅዱስ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር፣ ቅዱስ መሆን ይጠበቅብናል።—1 ጴጥ. 1:4፤ 2 ጴጥ. 3:13

“በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ”

9. ዘሌዋውያን ምዕራፍ 19⁠ን መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

9 ቅዱስ የሆነውን አምላካችንን ማስደሰት ስለምንፈልግ እኛም እንዴት ቅዱስ መሆን እንደምንችል ለመማር እንጓጓለን። ይሖዋ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። በዚህ ረገድ ከዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ግሩም ትምህርቶች እናገኛለን። የዕብራይስጥ ምሁር የነበሩት ማርከስ ካሊሽ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ከዘሌዋውያን መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ከመላው ኦሪት የዚህን ምዕራፍ ያህል ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ የሚዳስስ፣ የተለያዩ የሕይወት ዘርፎችን የሚነካ እንዲሁም በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ምዕራፍ የለም ማለት ይቻላል።” ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ምክር የሚሰጡንን በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሐሳቦች እንመርምር። ይህን ስናደርግ፣ በምዕራፉ መግቢያ ላይ የሚገኙትን “ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል” የሚሉትን ቃላት በአእምሯችን እንያዝ።

በዘሌዋውያን 19:3 ላይ የሚገኘው ወላጆችን ስለማክበር የሚናገረው ትእዛዝ ክርስቲያኖች ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል? (ከአንቀጽ 10-12⁠ን ተመልከት) *

10-11. ዘሌዋውያን 19:3 ምን ማድረግ እንዳለብን ይናገራል? ይህን ትእዛዝ መከተል ያለብንስ ለምንድን ነው?

10 ይሖዋ እስራኤላውያን ቅዱስ መሆን እንዳለባቸው ከተናገረ በኋላ የሚከተለውን መመሪያ ሰጣቸው፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ . . . እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።”—ዘሌ. 19:2, 3

11 አምላክ ወላጆቻችንን እንድናከብር የሰጠንን መመሪያ መታዘዝ እንዳለብን ግልጽ ነው። አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ጥሩ ነገር ማድረግ ይኖርብኛል?” በማለት እንደጠየቀው የሚገልጸውን ዘገባ እናስታውሳለን። ኢየሱስ ከሰጠው መልስ መካከል “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው መመሪያ ይገኝበታል። (ማቴ. 19:16-19) እንዲያውም ኢየሱስ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይህን መመሪያ ላለመታዘዝ በማሴራቸው አውግዟቸዋል። እንዲህ በማድረጋቸው “የአምላክን ቃል ሽራችኋል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 15:3-6) ‘የአምላክ ቃል’ ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል አምስተኛውን እንዲሁም በዘሌዋውያን 19:3 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን መመሪያ ያካትታል። (ዘፀ. 20:12) አሁንም ቢሆን፣ በዘሌዋውያን 19:3 ላይ የሚገኘው “ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር” የሚለው መመሪያ “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል” የሚለውን ትእዛዝ ተከትሎ እንደሚመጣ ልብ እንበል።

12. በዘሌዋውያን 19:3 መሠረት ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

12 ይሖዋ ወላጆቻችንን እንድናከብር የሰጠንን መመሪያ ስናስብ ‘እኔስ በዚህ ረገድ እንዴት ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። እስካሁን ድረስ ይህን መመሪያ በበቂ መጠን እንዳልታዘዛችሁ ከተሰማችሁ ከዚህ በኋላ ማስተካከያ ለማድረግ ልትወስኑ ትችላላችሁ። ያለፈውን መቀየር አትችሉም፤ ሆኖም ከዚህ በኋላ ወላጆቻችሁን ለማክበር አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ትችላላችሁ። ምናልባት ከእነሱ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ትችሉ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ለእነሱ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ ወይም ስሜታዊ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ተጨማሪ ነገር ማድረግ ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ በዘሌዋውያን 19:3 ላይ ያለውን ትእዛዝ ታከብራላችሁ።

13. (ሀ) በዘሌዋውያን 19:3 ላይ ሌላ ምን ምክር እናገኛለን? (ለ) በሉቃስ 4:16-18 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ዘሌዋውያን 19:3 ቅዱስ ከመሆን ጋር በተያያዘ ሌላም ትምህርት ይሰጠናል። ጥቅሱ ሰንበትን ስለመጠበቅ ይናገራል። ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ስላልሆኑ ሳምንታዊውን ሰንበት ማክበር አይጠበቅባቸውም። ሆኖም እስራኤላውያን ሰንበትን የጠበቁት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይህን ማድረጋቸው ምን ጥቅም እንዳስገኘላቸው ማጥናታችን በእጅጉ ይጠቅመናል። እስራኤላውያን በሰንበት ቀን ከዕለት ተዕለት ሥራቸው አርፈው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር። * ኢየሱስ በሰንበት ቀን የአምላክን ቃል ለማንበብ ባደገበት ከተማ ወደሚገኝ ምኩራብ የሄደው ለዚህ ነው። (ዘፀ. 31:12-15፤ ሉቃስ 4:16-18ን አንብብ።) አምላክ በዘሌዋውያን 19:3 ላይ ‘ሰንበቶቼን ጠብቁ’ በማለት የሰጠው መመሪያ ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ጊዜ ገዝተን ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት እንድንሰጥ ሊያነሳሳን ይገባል። በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባችሁ ይሰማችኋል? ዘወትር ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ የምትመድቡ ከሆነ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኖራችኋል፤ ይህ ደግሞ ቅዱስ ለመሆን ወሳኝ ነው።

ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጠናክሩ

14. በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የትኛው መሠረታዊ እውነት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል?

14 በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ፣ ቅዱስ ሆነን ለመኖር የሚረዳን አንድ መሠረታዊ እውነታ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ቁጥር 4 መጨረሻው ላይ “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ” ይላል። ይህ ዓረፍተ ነገር ወይም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አገላለጽ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ 16 ጊዜ ይገኛል። ይህም ከአሥርቱ ትእዛዛት የመጀመሪያውን፣ ማለትም “እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ” የሚለውን ትእዛዝ ያስታውሰናል። (ዘፀ. 20:2, 3) ቅዱስ መሆን የሚፈልግ ክርስቲያን ሁሉ፣ ማንም ወይም ምንም ነገር ከአምላኩ ጋር ካለው ዝምድና እንዳይበልጥበት መጠንቀቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራ እንደመሆናችን መጠን ቅዱስ ስሙን የሚያስነቅፍ ወይም የሚያሰድብ ማንኛውንም ነገር ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።—ዘሌ. 19:12፤ ኢሳ. 57:15

15. በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙት ስለ መሥዋዕቶች የሚናገሩት ጥቅሶች ምን እንድናደርግ ሊያነሳሱን ይገባል?

15 እስራኤላውያን ይሖዋን እንደ አምላካቸው አድርገው እንደሚቀበሉት የሚያሳዩት የሰጣቸውን በርካታ ሕጎች በማክበር ነበር። ዘሌዋውያን 18:4 እንዲህ ይላል፦ “ድንጋጌዎቼን ተግባር ላይ አውሉ፤ ደንቦቼንም በመጠበቅ በእነሱ ሂዱ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።” በምዕራፍ 19 ውስጥ ለእስራኤላውያን የተሰጡት አንዳንድ ‘ደንቦች’ ይገኛሉ። ለምሳሌ ከቁጥር 5-8 እንዲሁም ቁጥር 21, 22 ስለ እንስሳት መሥዋዕቶች ይናገራሉ። እነዚህ መሥዋዕቶች ‘የይሖዋን ቅዱስ ነገር በማያረክስ’ መንገድ መቅረብ ነበረባቸው። እነዚህን ጥቅሶች ማንበባችን ይሖዋን ለማስደሰትና ዕብራውያን 13:15 እንደሚናገረው ለእሱ ተቀባይነት ያለው የውዳሴ መሥዋዕት ለማቅረብ ሊያነሳሳን ይገባል።

16. አምላክን በሚያገለግሉ እና በማያገለግሉ ሰዎች መካከል ስላለው ልዩነት የሚያስታውሰን የትኛው መሠረታዊ ሥርዓት ነው?

16 ቅዱስ መሆን ከፈለግን ከሌሎች የተለየን ለመሆን ፈቃደኞች መሆን አለብን። እርግጥ ከሌሎች የተለየን መሆን ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። አብረውን የሚማሩ ልጆች፣ የሥራ ባልደረቦቻችን፣ የማያምኑ ዘመዶቻችን ወይም ሌሎች ሰዎች ከአምልኳችን ጋር የሚጋጭ ነገር እንድናደርግ አንዳንድ ጊዜ ይጫኑን ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመን ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅብናል። ታዲያ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን ምንድን ነው? በዘሌዋውያን 19:19 ላይ የሚገኝ አንድ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓት እንመልከት፤ ጥቅሱ “ከሁለት የተለያዩ የክር ዓይነቶች የተሠራ ልብስ አትልበስ” ይላል። ይህ ሕግ፣ እስራኤላውያን በዙሪያቸው ካሉ ብሔራት የተለዩ እንዲሆኑ አድርጓል። እርግጥ ክርስቲያኖች ከተለያየ ዓይነት ክር የተሠራ ልብስ ቢለብሱ ስህተት የለውም፤ ለምሳሌ ከጥጥ እና ከሱፍ የተሸመነ ልብስ ልንለብስ እንችላለን። ይሁንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ እምነት ወይም ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር መመሳሰል አንፈልግም፤ እነዚህ ሰዎች አብረውን የሚማሩ ልጆች፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም ዘመዶቻችን ቢሆኑም እንኳ ከእነሱ የተለየን ለመሆን ፈቃደኞች ነን። እርግጥ ነው፣ ዘመዶቻችንን እንወዳቸዋለን፤ ለሌሎች ሰዎችም ፍቅር እናሳያለን። ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ወሳኝ በሆኑ የሕይወታችን ዘርፎች ረገድ ከሌሎች የተለየን ለመሆን ፈቃደኞች ነን። እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ቅዱስ መሆን ሲባል ለአምላክ የተለዩ መሆንንም ይጨምራል።—2 ቆሮ. 6:14-16፤ 1 ጴጥ. 4:3, 4

የአምላክ ሕዝቦች ከዘሌዋውያን 19:23-25 ምን ትምህርት ሊያገኙ ይገባ ነበር? አንተስ ከዚህ ጥቅስ ምን ትምህርት አግኝተሃል? (ከአንቀጽ 17-18⁠ን ተመልከት) *

17-18. ከዘሌዋውያን 19:23-25 ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

17 “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ” የሚለው አገላለጽ እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር ላላቸው ዝምድና ቅድሚያ እንዲሰጡ ሊያነሳሳቸው ይገባ ነበር። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ዘሌዋውያን 19:23-25 አንዱን መንገድ ይናገራል። (ጥቅሱን አንብብ።) እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ይህ ጥቅስ ለእነሱ ምን ትርጉም እንደሚኖረው እስቲ አስቡ። አንድ ሰው ለምግብ የሚሆን ዛፍ ቢተክል ለሦስት ዓመት ከእሱ መብላት የለበትም። በአራተኛው ዓመት ፍሬውን ለይሖዋ መቅደስ ይሰጣል። ባለቤቱ ከፍሬው መብላት የሚችለው በአምስተኛው ዓመት ነው። ይህ ሕግ፣ እስራኤላውያን ለራሳቸው ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት እንደሌለባቸው አስገንዝቧቸው መሆን አለበት። ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጣቸው መተማመንና የእሱን አምልኮ መደገፍ ይጠበቅባቸው ነበር። ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም አምላክ የእሱ አምልኮ ማዕከል ለነበረው ለመቅደሱ በልግስና መዋጮ እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል።

18 በዘሌዋውያን 19:23-25 ላይ የሚገኘው ሕግ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን . . . ብላችሁ አትጨነቁ።” አክሎም “በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” ብሏል። አምላክ ወፎችን እንደሚንከባከባቸው ሁሉ እኛንም ይንከባከበናል። (ማቴ. 6:25, 26, 32) ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚሰጠን እንተማመናለን። በተጨማሪም ለተቸገሩ ሰዎች በስውር “ምጽዋት” እንሰጣለን። የጉባኤውን ወጪዎች ለመሸፈንም በልግስና መዋጮ እናደርጋለን። ይሖዋ የምናሳየውን ልግስና ይመለከታል፤ መልሶም ይከፍለናል። (ማቴ. 6:2-4) በልግስና ስንሰጥ በዘሌዋውያን 19:23-25 ላይ የሚገኘው ትምህርት እንደገባን እናሳያለን።

19. ዘሌዋውያን ምዕራፍ 19⁠ን በመመርመርህ ምን ጥቅም አግኝተሃል?

19 እስካሁን የተመለከትነው ቅዱስ የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል የሚረዱ በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙ ጥቂት ሐሳቦችን ብቻ ነው። ‘በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን በመሆን’ እሱን ለመምሰል ጥረት እናደርጋለን። (1 ጴጥ. 1:15) ይሖዋን የማያመልኩ ብዙ ሰዎች መልካም ምግባራችንን በዓይናቸው ማየት ችለዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ በዚህ ምክንያት ይሖዋን ለማክበር ተነሳስተዋል። (1 ጴጥ. 2:12) ከዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ሌሎች በርካታ ትምህርቶችንም ማግኘት እንችላለን። በቀጣዩ ርዕስ ላይ፣ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ተጨማሪ ጥቅሶችን እንመረምራለን። ይህም ጴጥሮስ በመከረን መሠረት ‘ቅዱሳን መሆን’ የምንችልባቸውን ሌሎች የሕይወታችንን ዘርፎች ለማስተዋል ይረዳናል።

መዝሙር 80 “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”

^ አን.5 ይሖዋን በጣም እንወደዋለን፤ ልናስደስተውም እንፈልጋለን። ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ አገልጋዮቹም ቅዱሳን እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። ሆኖም ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በእርግጥ ቅዱሳን መሆን ይችላሉ? አዎ፣ ይችላሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለእምነት ባልንጀሮቹ የሰጠውን ምክር እንዲሁም ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ መመርመራችን በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስገነዝበናል።

^ አን.13 ስለ ሰንበትና ከሰንበት ስለምናገኘው ጥቅም ማብራሪያ ለማግኘት በታኅሣሥ 2019 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ለሥራም ሆነ ለእረፍት ‘ጊዜ አለው’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሰው ከወላጆቹ ጋር ጊዜ ያሳልፋል፤ ከባለቤቱና ከልጁ ጋር ሆኖ ይጠይቃቸዋል፤ እንዲሁም በየጊዜው ያዋራቸዋል።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ እስራኤላዊ ገበሬ፣ በተከለው ዛፍ ላይ ያሉትን ፍሬዎች ሲመለከት።