በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 50

የጥሩውን እረኛ ድምፅ ስሙ

የጥሩውን እረኛ ድምፅ ስሙ

“ድምፄንም ይሰማሉ።”—ዮሐ. 10:16

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

ማስተዋወቂያ *

1. ኢየሱስ ተከታዮቹን ከበጎች ጋር ያመሳሰላቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

 ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የቀረበ ግንኙነት በአንድ እረኛና በበጎቹ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐ. 10:14) ይህ ንጽጽር ተገቢ ነው። ምክንያቱም በጎች እረኛቸውን ያውቁታል፤ ድምፁንም ሰምተው ይከተሉታል። አንድ ቱሪስት ይህን በዓይኑ ተመልክቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ሜዳ ላይ ተሰማርተው የነበሩ በጎችን ቪዲዮ መቅረጽ ስለፈለግን ወደ እኛ እንዲቀርቡ ለማድረግ ሞከርን። በጎቹ ግን ድምፃችንን ስላላወቁት ወደ እኛ አልመጡም። ብዙም ሳይቆይ አንድ ትንሽ ልጅ መጣ፤ ልጁ እረኛቸው ነበር። ልጁ ልክ እንደጠራቸው በጎቹ ተከተሉት።”

2-3. (ሀ) የኢየሱስ ተከታዮች ድምፁን እንደሚሰሙ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

2 ይህ ቱሪስት ያጋጠመው ነገር፣ ኢየሱስ በጎቹን ማለትም ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። ኢየሱስ “ድምፄንም ይሰማሉ” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 10:16) ሆኖም ኢየሱስ ያለው በሰማይ ነው። ታዲያ ድምፁን መስማት የምንችለው እንዴት ነው? የጌታችንን ድምፅ እንደምንሰማ ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ትምህርቶቹን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ነው።—ማቴ. 7:24, 25

3 በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ ካስተማራቸው ነገሮች አንዳንዶቹን እንመረምራለን። ኢየሱስ አንዳንድ ነገሮችን ማድረጋችንን እንድንተው፣ አንዳንድ ነገሮችን ደግሞ እንድናደርግ እንዳስተማረን እናያለን። እስቲ በመጀመሪያ፣ ጥሩ እረኛ የሆነው ኢየሱስ ማድረጋችንን እንድንተው ያስተማረንን ሁለት ነገሮች እንመልከት።

‘መጨነቃችሁን ተዉ’

4. በሉቃስ 12:29 መሠረት ‘እንድንጨነቅ’ ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው?

4 ሉቃስ 12:29ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ። ኢየሱስ ተከታዮቹን ስለ ቁሳዊ ነገሮች ‘መጨነቃቸውን እንዲተዉ’ አሳስቧቸዋል። ኢየሱስ የሚሰጠው ምክር ምንጊዜም ቢሆን ጥበብ የሚንጸባረቅበትና ትክክለኛ እንደሆነ እናውቃለን። በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ልናደርገውም እንፈልጋለን። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ይህን ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ለምን?

5. አንዳንዶች ስለ ቁሳዊ ነገሮች የሚጨነቁት ለምን ሊሆን ይችላል?

 5 አንዳንዶች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይኸውም ስለ ምግብ፣ ስለ ልብስና ስለ መጠለያ ይጨነቁ ይሆናል። የሚኖሩት ድሃ አገር ውስጥ ሊሆን ይችላል። ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት የሚያስችል ገቢ ማግኘት ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ወይም ደግሞ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ሰው ስለሞተ የቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ለማግኘት ተቸግረው ይሆናል። ከዚህም ሌላ ብዙዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሥራቸውን ወይም ገቢያቸውን አጥተዋል። (መክ. 9:11) እኛም እንደነዚህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውን ሊሆን ይችላል። ታዲያ ኢየሱስ መጨነቃችንን እንድንተው የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ስለ ቁሳዊ ነገሮች በማሰብ በጭንቀት ማዕበል ከመዋጥ ይልቅ በይሖዋ ላይ ይበልጥ ተማመኑ (ከአንቀጽ 6-8⁠ን ተመልከት) *

6. ሐዋርያው ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ምን አጋጠመው?

6 በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት በገሊላ ባሕር ላይ በጀልባ እየተጓዙ ሳለ ኃይለኛ ማዕበል ተነሳ። በዚህ ወቅት ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ ሲመጣ ተመለከቱ። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለ። ኢየሱስ ጴጥሮስን “ና!” ሲለው ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ። ቀጥሎስ ምን ሆነ? ጴጥሮስ “አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ። መስጠም ሲጀምርም ‘ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!’” ብሎ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ በመያዝ አዳነው። ጴጥሮስ ትኩረቱን በኢየሱስ ላይ ባደረገበት ወቅት በማዕበል በሚናወጠው ባሕር ላይ መራመድ ችሎ ነበር። አውሎ ነፋሱን ማየት ሲጀምር ግን ፍርሃትና ጥርጣሬ ስላደረበት መስጠም ጀመረ።—ማቴ. 14:24-31

7. ከጴጥሮስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ከጴጥሮስ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ጴጥሮስ ከጀልባው ወርዶ በባሕሩ ላይ መጓዝ ሲጀምር ማዕበሉን ፈርቶ መስጠም እንደሚጀምር አልጠበቀም ነበር። በውኃው ላይ እየተራመደ ጌታው ጋ ለመድረስ ፈልጎ ነበር። ሆኖም ትኩረቱን በጌታው ላይ ከማድረግ ይልቅ ማዕበሉን ማየት ጀመረ። እኛ በውኃ ላይ መሄድ እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ይሁንና እምነታችንን የሚፈትኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። በይሖዋ እና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ትኩረት ካላደረግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ልንሰጥም እንችላለን። በሕይወታችን ውስጥ እንደ ማዕበል ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በይሖዋና እኛን ለመርዳት ባለው ችሎታ ልንተማመን ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

8. ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች በማሰብ ከሚገባው በላይ እንዳንጨነቅ ምን ሊረዳን ይችላል?

8 ስላሉብን ችግሮች በማሰብ ከመጨነቅ ይልቅ በይሖዋ መተማመን ይኖርብናል። አፍቃሪ የሆነው አባታችን ይሖዋ መንፈሳዊ ነገሮችን ካስቀደምን የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንደሚያሟላልን ቃል መግባቱን ልናስታውስ ይገባል። (ማቴ. 6:32, 33) ይሖዋ ይህን ቃሉን ሳይጠብቅ የቀረበት ጊዜ የለም። (ዘዳ. 8:4, 15, 16፤ መዝ. 37:25) ይሖዋ ለወፎችና ለአበቦች የሚያስፈልጋቸውን ያሟላላቸዋል፤ ታዲያ እኛስ የምንበላው ወይም የምንለብሰው እናጣለን ብለን መጨነቅ ይኖርብናል? (ማቴ. 6:26-30፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ወላጆች ልጆቻቸውን ስለሚወዷቸው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር እንደሚያሟሉላቸው የታወቀ ነው፤ በተመሳሳይም የሰማዩ አባታችን ሕዝቦቹን ስለሚወዳቸው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ያሟላላቸዋል። በእርግጥም ይሖዋ እንደሚንከባከበን እርግጠኞች መሆን እንችላለን!

9. አንድ ባልና ሚስት ካጋጠማቸው ነገር ምን ትምህርት አግኝተሃል?

9 ይሖዋ ቁሳዊ ፍላጎታችንን እንዴት እንደሚያሟላልን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት በስደተኞች መጠለያ የሚኖሩ እህቶችን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ለማምጣት አሰቡ፤ እነዚህን እህቶች ለማምጣት በአሮጌ መኪናቸው ከአንድ ሰዓት በላይ መጓዝ አስፈልጓቸዋል። ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ስብሰባው ሲያልቅ እነዚህን እህቶች ቤታችን ጋበዝናቸው። በኋላ ላይ ግን ለእነሱ የምናቀርበው ምንም ምግብ እንደሌለን ትዝ አለን።” ታዲያ እነዚህ ባልና ሚስት ምን ያደርጉ ይሆን? ወንድም አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ቤት ስንደርስ በራችን ላይ በሁለት ትላልቅ ዘንቢሎች አስቤዛ ተቀምጦ አገኘን። አስቤዛውን እዚያ ያስቀመጠው ማን እንደሆነ አላወቅንም። በእርግጥም ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሰጥቶናል።” ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ የእነዚህ ባልና ሚስት መኪና ተበላሸ። መኪናው ለአገልግሎታቸው የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም መኪናውን ለማሠራት የሚሆን ገንዘብ አልነበራቸውም። መኪናቸውን ለማሳየት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጋራዥ ወሰዱት። መኪናው እዚያ እያለ አንድ ሰው መጣና “ይህ መኪና የማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ወንድማችን መኪናው የእሱ እንደሆነ፣ ሆኖም ጥገና እንደሚያስፈልገው ገለጸለት። ሰውየውም “ችግር የለውም። ባለቤቴ ይህን መኪና፣ ልክ በዚህ ቀለም ትፈልገዋለች። ስንት ትሸጥልኛለህ?” አለው። ወንድማችን ይህን መኪና ሲሸጥ ሌላ መኪና ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ አገኘ። ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የዚያን ዕለት ምን ያህል እንደተደሰትን ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። ይህ የሆነው በአጋጣሚ እንዳልሆነ እናውቅ ነበር። የይሖዋን እጅ በሚገባ ተመልክተናል።”

10. መዝሙር 37:5 ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች እንዳንጨነቅ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

10 ጥሩውን እረኛ የምንሰማና ስለ ቁሳዊ ፍላጎታችን ከመጠን በላይ መጨነቃችንን የምንተው ከሆነ ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝሙር 37:5ን አንብብ፤ 1 ጴጥ. 5:7)  በአንቀጽ 5 ላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች መለስ ብለን እናስብ። እስካሁን ድረስ ይሖዋ በቤተሰባችን ራስ ወይም በቀጣሪያችን አማካኝነት የሚያስፈልገንን ሲያሟላልን ቆይቶ ይሆናል። ሆኖም የቤተሰቡ ራስ ቤተሰቡን ማስተዳደር ባይችል ወይም ከሥራ ብንቀነስ ይሖዋ በሆነ መንገድ የሚያስፈልገንን ማሟላቱን ይቀጥላል። ይሖዋ ይህን እንደሚያደርግ አንጠራጠርም። እስቲ ጥሩው እረኛ እንድንተው ከነገረን ነገሮች መካከል ሌላውን ደግሞ እንመልከት።

“መፍረዳችሁን ተዉ”

በሌሎች መልካም ጎን ላይ ማተኮር መፍረዳችንን እንድንተው ይረዳናል (አንቀጽ 11, 14-16⁠ን ተመልከት) *

11. በማቴዎስ 7:1, 2 ላይ ኢየሱስ ምን ማድረጋችንን እንድንተው መክሮናል? ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ፈታኝ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?

11 ማቴዎስ 7:1, 2ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ። ኢየሱስ ሰዎች ፍጹማን ባለመሆናቸው በሌሎች ላይ መፍረድ እንደሚቀናቸው ያውቅ ነበር። “መፍረዳችሁን ተዉ” እንዳለ ልብ በሉ። በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ ላለመፍረድ ጥረት እናደርግ ይሆናል። ይሁንና ይህ አንዳንድ ጊዜ ላይሳካልን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን የመተቸት አዝማሚያ እንዳለን ብናስተውል ምን ማድረግ ይኖርብናል? የኢየሱስን ምክር በመስማት በሌሎች ላይ መፍረዳችንን ለመተው ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።

12-13. ይሖዋ ንጉሥ ዳዊትን በያዘበት መንገድ ላይ ማሰላሰላችን በሌሎች ላይ መፍረዳችንን እንድንተው የሚረዳን እንዴት ነው?

12 ይሖዋ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ይጠቅመናል። ይሖዋ ትኩረት የሚያደርገው በሰዎች መልካም ጎን ላይ ነው። ይሖዋ ከንጉሥ ዳዊት ጋር በተያያዘ ያደረገው ነገር ይህን ያሳያል። ዳዊት ከባድ ስህተቶችን ሠርቷል፤ ለምሳሌ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ፈጽሟል፤ ይባስ ብሎም ባሏን አስገድሎታል። (2 ሳሙ. 11:2-4, 14, 15, 24) ዳዊት እንዲህ ያለ ድርጊት በመፈጸሙ የጎዳው ራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሚስቶቹንና መላውን ቤተሰቡን ጭምር ነው። (2 ሳሙ. 12:10, 11) በሌላ ጊዜ ደግሞ ዳዊት ይሖዋ ሳያዘው የእስራኤልን ሠራዊት በማስቆጠር በአምላኩ ሳይታመን ቀርቷል። ዳዊት ይህን ያደረገው በሠራዊቱ ብዛት ኩራት ስለተሰማውና በሠራዊቱ ስለተማመነ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህን ማድረጉ ምን አስከተለ? ሰባ ሺህ የሚያህሉ እስራኤላውያን በመቅሰፍት ሞቱ!—2 ሳሙ. 24:1-4, 10-15

13 በዚያ ወቅት በእስራኤል ብትኖሩ ኖሮ ለዳዊት ምን አመለካከት ይኖራችሁ ነበር? የይሖዋን ምሕረት ማግኘት አይገባውም ብላችሁ ትፈርዱበት ነበር? ይሖዋ እንዲህ አልተሰማውም። ይሖዋ ትኩረት ያደረገው ዳዊት በመላ ሕይወቱ ታማኝ በመሆኑና ከልቡ ንስሐ በመግባቱ ላይ ነው። በመሆኑም ዳዊት እነዚህን ከባድ ኃጢአቶች ቢፈጽምም ይሖዋ ይቅር ብሎታል። ይሖዋ ዳዊት ከልቡ እንደሚወደውና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ እንደሚፈልግ ያውቅ ነበር። እኛም ይሖዋ በመልካም ጎናችን ላይ የሚያተኩር በመሆኑ አመስጋኞች ነን!—1 ነገ. 9:4፤ 1 ዜና 29:10, 17

14. ክርስቲያኖች በሌሎች ላይ መፍረዳቸውን እንዲተዉ የሚረዳቸው ምንድን ነው?

14 ይሖዋ ከእኛ ፍጽምና አይጠብቅም፤ እኛም ከሌሎች ፍጽምና ከመጠበቅ ይልቅ በመልካም ጎናቸው ላይ ልናተኩር ይገባል። ብዙውን ጊዜ የሌሎችን ጉድለት ማየትና መተቸት ቀላል ነው። መንፈሳዊ አመለካከት ያለው ሰው ግን የሌሎችን ጉድለት ቢያስተውልም ጉድለታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ከእነሱ ጋር ተስማምቶ ለመሥራት ይጥራል። ተቆርጦ ያልተሞረደ አልማዝ እምብዛም አይማርክ ይሆናል፤ አስተዋይ የሆነ ሰው ግን አልማዙ ሲቆረጥና ሲሞረድ የሚኖረውን መልክ አሻግሮ ያስባል። እኛም የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በሰዎች ድክመት ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ ማተኮር ይኖርብናል።

15. ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚመሩ ከግምት ማስገባታችን እንዳንፈርድባቸው የሚረዳን እንዴት ነው?

15 በሌሎች መልካም ጎን ላይ ማተኮር በእነሱ ላይ ላለመፍረድ እንደሚረዳን ተመልክተናል። በዚህ ረገድ የሚረዳን ሌላስ ምን አለ? ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚመሩ ለማሰብ ሞክሩ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ አንድ ቀን ቤተ መቅደስ ውስጥ እያለ አንዲት ድሃ መበለት አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች በመዋጮ ሣጥኑ ውስጥ ስትከት አየ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ይቺን ብቻ ነው እንዴ የምትሰጠው?” ብሎ አላሰበም። ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው መበለቷ ባዋጣችው ገንዘብ መጠን ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን ለማድረግ ያነሳሳትን የልብ ዝንባሌ እና ያለችበትን ሁኔታ ከግምት አስገብቷል፤ እንዲሁም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ በማድረጓ አመስግኗታል።—ሉቃስ 21:1-4

16. ቬሮኒካ ካጋጠማት ሁኔታ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

16 ቬሮኒካ የተባለች እህት ያጋጠማት ነገር፣ ሌሎች ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ማስገባት ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል። ቬሮኒካ ያለችበት ጉባኤ ውስጥ ልጇን ብቻዋን የምታሳድግ አንዲት እናት አለች። ቬሮኒካ እንዲህ ብላለች፦ “ይህች እናትና ልጇ በጉባኤ እንቅስቃሴዎችና በአገልግሎት አዘውትረው እንደማይካፈሉ ይሰማኝ ነበር። በዚህም የተነሳ ለእነሱ ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም። ሆኖም አንድ ቀን ከእናትየው ጋር አገልግሎት ወጣን። ይህች እናት፣ ልጇ ኦቲዝም የተባለ የአእምሮ ሕመም እንዳለበትና በዚህም የተነሳ ተፈታታኝ ሁኔታ እንደሚያጋጥማት ነገረችኝ። በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገች ነበር። በልጇ ጤንነት ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ሌላ ጉባኤ ለመካፈል ትገደዳለች። እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ፈጽሞ አልተገነዘብኩም ነበር። አሁን፣ ይህች እህት በይሖዋ አገልግሎት ለመካፈል የምታደርገውን ጥረት በጣም አደንቃለሁ፤ እንዲሁም አከብራታለሁ።”

17. በያዕቆብ 2:8 ላይ ምን መመሪያ ተሰጥቶናል? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

17 በአንድ የእምነት ባልንጀራችን ላይ እንደፈረድን ከተገነዘብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ወንድሞቻችንን ልንወዳቸው እንደሚገባ ማስታወስ አለብን። (ያዕቆብ 2:8ን አንብብ።) ከዚህም ሌላ ይሖዋ በሌሎች ላይ መፍረዳችንን እንድንተው እንዲረዳን በጸሎት እንለምነው። በውስጣችን የፈረድንበትን ወንድም ለመቅረብ ጥረት በማድረግ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ እንችላለን። ይህን ማድረጋችን ግለሰቡን ይበልጥ ለማወቅ ያስችለናል። ምናልባትም አብሮን እንዲያገለግል ልንጠይቀው ወይም ቤታችን ልንጋብዘው እንችል ይሆናል። ወንድማችንን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ በጎ ባሕርያቱ ላይ በማተኮር የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይህን ስናደርግ ጥሩው እረኛ “መፍረዳችሁን ተዉ” በማለት የሰጠንን ትእዛዝ እንደምንሰማ እናሳያለን።

18. የጥሩውን እረኛ ድምፅ እንደምንሰማ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

18 በጎች የእረኛቸውን ድምፅ እንደሚሰሙ ሁሉ የኢየሱስ ተከታዮችም የእሱን ድምፅ ይሰማሉ። ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች መጨነቃችንን እንዲሁም በሌሎች ላይ መፍረዳችንን ለመተው ጥረት የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ እና ኢየሱስ ጥረታችንን ይባርኩልናል። ‘የትንሹ መንጋ’ አባላትም ሆንን ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የጥሩውን እረኛ ድምፅ መስማታችንንና መታዘዛችንን እንቀጥል። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 10:11, 14, 16) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያደርጉ ያሳሰባቸውን ሁለት ነገሮች እንመረምራለን።

መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት

^ አን.5 ኢየሱስ በጎቹ ድምፁን እንደሚሰሙ ሲናገር፣ ደቀ መዛሙርቱ ትምህርቶቹን እንደሚያዳምጡና በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ እንደሚያደርጓቸው መግለጹ ነበር። በዚህ ርዕስ ላይ ከኢየሱስ ትምህርቶች ሁለቱን እንመለከታለን፤ ኢየሱስ ስለ ቁሳዊ ነገሮች መጨነቃችንን እና በሌሎች ላይ መፍረዳችንን እንድንተው አስተምሮናል። ይህን ምክር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

^ አን.51 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ከሥራ ተባሯል፤ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለመግዛት ገንዘብ የለውም፤ እንዲሁም ቤት ማግኘት አለበት። በጭንቀት ከመዋጡ የተነሳ መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ ለማለት ሊፈተን ይችላል።

^ አን.53 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ጉባኤ የደረሰው አርፍዶ ነው። ሆኖም መልካም ባሕርያት አሉት፤ ለምሳሌ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይመሠክራል፤ አንዲትን አረጋዊት ያግዛል፤ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሹን ይንከባከባል።